የትግራይ ህዝብ የለውጡ ኣጋር እንጂ ተጠቂ ሊሆን ኣይገባም
መርስዔ ኪዳን
ሜኔሶታ፤ ሃገረ ኣሜሪካ
ሰሞኑን በሃገራችን ውስጥ እየተካሄደ ባለው ህዝባዊ አመፅ ምክኒያት ብዙ የሰው ህይወት፣ የኣካል ጉዳትና የንብረት ውድመት እየደረሰ ነው። ይህ ሁኔታ እንዲፈጠር ያበቁ ብዙ ምክኒያቶች ቢኖሩትም ኣንዱና ዋነኛው ምክኒያት በሃገሪቱ ውስጥ ፍትሃዊ የሆነ የፖለቲካ ስርዓት ኣለመኖሩ ነው። ኢትዮጵያ ብዙ ብሄሮች ብቻ ሳይሆን ብዙ ፖለቲካዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አመለካከት ያለው ህዝብ የሚኖርባት አገር ነች። ሆኖም ያለው የፖለቲካ ስርአትና በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ይህንን ልዩነት ማክበርና ማስተናገድ ባለመቻሉ ብቻ ሳይሆን ፍላጎትም ባለማሳየቱ ለዚህ ችግር ተዳርገናል። ኢህኣዴግ የሚመራው መንግስት ሠሞኑን የተፈጠረውን ችግር በተመለክተ ያወጣው መግለጫ የችግሩን መጠን በውሉ ያላጤነና ጭራሽም ዋነኛውን የችግሮቹ ሁሉ መንስኤ ያልተመለከተ ነው።1 ለሙስናውም፣ ለመልካም አስተዳደር እጦቱም፡ ለብሄር ነክ ጥያቄዎችም፤ ለሌሎች ችግሮችም ምክኒያት የሆኑት ዋነኞቹ መሰረታዊ ችግሮች ህዝብ ያሻውን የሚመርጥበት ዴሞክራሲያዊ ስርኣት አለመኖር፣ ህዝብ ሲበደል ብሶቱን የሚገልፅበት ነፃ መድረክ አለመኖር፣ የተለየዩ የፖለቲካ አመለካከቶች የተወከሉበት መንግስት አለመኖር፣ የኣገሪቱ ህግ አውጪና ህግ ኣስፈፃሚ ኣካላት መቶ በመቶ በኢህኣዴግ ቁጥጥር ስር መሆን፣ የፍትህ ኣካላት በነፃነት ለመስራት አለመቻል ናቸው።