Logo

(OMN) ከአቶ ጁነዲን ሳዶ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ

September 24, 2016

ከቀድሞው ከፍተኛ ባለስልጣን ከአቶ ጁነዲን ሳዶ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ

Share

2 comments on “(OMN) ከአቶ ጁነዲን ሳዶ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ

 1. አቶ ጁነዲን ጠባብ አይደለሁም ይላሉ። ነገር ግን በቃለ መጠይቁ እንደሰማሁት የሚጨነቁትና የሚያወሩት በሙሉ ስለ አንድ ብሄር ብቻ ነው። ስለዚህ እሳቸውም ልክ እንደ ህውዋት ሰዎች ጠባብንት እንዳላቸው ነው የምገነዘበው። አንድ ሁሉን ይወክላል በሚባል የፈዴራል መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን የነበረ ሰው ለአንድ በሄር ብቻ ሳይሆን ሰለሌላውም ለምሳሌ ስለ አማራው፣ ጉራጌው፣ ትግሬው ወይም ጋምቤላው ያማይጨነቅበት ምክንያት አይገባኝም፤ ጠባብነት ካልሆነ በስተቀር።

  ሌላው ደግሞ እሳቸው ለኦሮሞ ህዝብ መብት ተቆርቋሪ አድርገው ያቀረቡበት ሁኔታም በ ራሱ የተሳሳተና እንዲያው እኔ የኦሮሞ ህዝብ ጠላት አድርጌ ነው የምቆጥራቸው። አንድ ማሳያ ሊሆን የሚችለው የኦሮሞ ህዝብ አማርኛ መማር የለበትም የሚለውን የህወዋት ፖሊሲ ሲያስፈጽሙ መቆየታቸው ነው። በዛ ምክንያት ከደርግ ውድቀት በኋላ የተወለዱ ልጆች አማርኛ እንዳያውቁ እገዳ ስለተደረገባቸው እንደልባቸው ወዴ ሌሎች ክልሎች ሄደው ስራ ለመወዳደርም ይሁን ንግድ ለመነገድ ሲቸገሩ ይታያሉ። ያ ብቻ ሳይሆን የኦሮሞ ተወላጅ የሆነ ሰው የፌዴራሉ የስራ ቋንቋ የሆነውንና ሁሉንም የሚያግባባውን የአማርኛ ቋንቋ ባለማወቁ ብቻ ወደፊት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሆን የሚችልበትን መንገድ የአቶ ጁነዲን ኦህዴድ ጥርቅም አድርጎ ዘግቶት ቆይቷል።

 2. ከኢንተርኔት ያገኝሁት

  “የምንፈልገው ምንድን ነው? እንዴትስ እናገኘዋለን ?

  ከበደ ሉሌ

  በተለያየ ምክንያት በውጥረት ውስጥ ያለ ሰው የተረጋጋና ውጤታማ የሆነ ውሳኔ ላይ ለመድረስ በመጀመሪያ የውጥረቱን መንስኤና አሁን ያለበትን ሁኔታ በትክክል መረዳት ይገባዋል። ባልተረጋጋ ሁኔታና ውጥረቱ በፈጠረብን ስሜት ውስጥ ሆነን የምንወስዳቸው የትኛውም አይነት እርምጃውች ከስህተት ሊጸዱ አይችሉም። ይህም ስህተት ወደ ባሰ አለመረጋጋትና ውጥረት ከዚያም ወደ ሌላ ስህተት ከሚከተን በስተቀር የምንፈልገውን ውጤት ሊያስገኝልን አይችልም። የትኛውም ስህተት በሌላ ስህተት ሊታረም አይችልምና።

  አሁን አገራችንና በውስጧ የምንኖር ህዝቦቿ ያለንበት ሁኔታ በውጥረት የተሞላ ነው። ይህ ውጥረት ደግሞ መልኩን እየቀያየረ ለወራት ዘልቋል። እስከማስታውሰው ድረስ (ባለፉት 40 አመታት) ይህን መሰል ውጥረት ውስጥ ስንገባ ለመጀመሪያችን አይደለም። የውጥረቱ መጠን አካባቢያዊ፣ ወረዳ፣ ክልላዊና አገር አቀፋዊ ሆኖ በተለያየ መጠን ጉዳት አድርሶ አልፏል፤ ጉዳት እያደረሰም ነው።

  ካለፈው ህዳር 2008 ዓ/ም በኦሮሚያ ጀምሮ በአማራና በደቡብ እየተስፋፋ የመጣው ውጥረት የበርካታ ሰዎችን ህይወት፣ አካልና ንብረት አውድሟል፤ እያወደመም ነው። ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ሰዎች ታስረዋል እየታሰሩም ነው። በአንድ በኩል ህዝብ ለመንግስት “ጥያቄ አለኝ” ይላል፤ በሌላ በኩል መንግስት “ጥያቄው የሚቀርብበት መንገድ ህጋዊ ስላልሆነ ህግን ማስከበር አለብኝ” ይላል። ህዝቡ “መንግስት ጥያቄየን እስኪመልስ ድረስ በየትኛውም መንገድ” ቢሆን እገፋበታለሁ ሲል፤ በሌላ ወገን መግስት “በሃይልም” ጭምር ህግን አስከብራለሁ በሚል አንድምታ ውጥረቶችና እልሆች በሁለቱም ወገን እየቀጠለ የሰው ህይወት፣ አካልና ንብረት ላይ የሚደርሰው ጥፋት እንደቀጠለ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ በውጥረቱ ውስጥ የማይፈለጉ የጎንዮሽ ውጤቶች ብቅ ብቅ እያሉ ይታያሉ። የእኔም የዛሬ ትኩረት በዚህ ላይ ያጠነጥናል።

  ጥያቄ ያላቸው ወገኖች ጥያቄአቸውን ያቀረቡት ህጋዊ ተጠያቂነት ላለውና ላለፉት 25 ዓመታት አገሪቱን ሲያስተዳድር ለኖረ ፓርቲና እርሱ ለመሰረተው መንግስት ነው። ገለልተኛ ሆኖ አንድ ሰው “ህዝብ መንግስትን እየጠየቀ ያለው ጥያቄ ምንድን ነው?” ብሎ ቢጠይቅ፤ በእኔ እይታ ጥያቄው
  በሁለት የተከፈለ ነው። አንዱ ወገን ያለው ህገ-መንግስት አተገባበር ላይ ያተኮረ ሲሆን ሌላው ደግሞ ራሱን ህገ-መንግስቱ ላይ ያነጣጠረ ነው። ጠቅለል ብለው ሲታዩ በመጀመሪያው ወገን ያሉ ጥያቄዎች፤

  1. መንግስትና ገዢው ፓርቲ ህገ-መንግስቱን አላከበረምና በተግባርም ባስቸኳይም ያክብር፤ ህገመንግስታዊ መብቶችን (ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን በተመለከተ) የሚሸረሽሩና የሚገድቡ ህጎች ይቀየሩ።
  2. ህገ-መንግስቱ የፈቀደው ፌደራላዊ አስተዳደር (ራስን በራስ የማስተዳደር ጉዳይ) በተግባር እየተሸራረፈ ስለሆነ ይከበር።

  የሁለተኛው ወገን ጥያቄ ደግሞ፤

  1. በህገ-መንግስቱ ቋንቋን መሰረት ያደረገው ውስጣዊ አስተዳደራዊው አከላለል ትክክል አይደለምና ህገ-መንግስቱ ይሻሻል የሚል ነው። (የድንበርና የማንነት ጥያቄዎች እዚህ ስር የሚወድቁ ይመስለኛል።)
  2. በስራ ላይ ያለው መንግስት እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ የማይችል ስለሆነ የምርጫ ጊዜውን ሳይጠብቅ ስልጣን ይልቀቅ የሚሉ ናቸው።

  በእኔ እይታ አየሩን የሞሉት ጥያቄዎች ሲጨመቁ ይህን ይመስላሉ። እነዚህ ጥያቄዎች በ2008 የጀመሩ ሳይሆኑ ላለፉት 25 አመታት ሲነሱና የተለያዩ ወገኖችን ሲያከራክሩ የኖሩ ብሎም የገዢውን ፓርቲ ጨምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሮግራም ሆነው የምረጡን መቀስቀሻዎች ነበሩ፤ አሁንም ናቸው። አሁን ጥያቄውን ልዩ ያደረገው ጠያቂዎች እንደ ፖለቲካ ፓረቲዎች በቢሮ አድራሻ ተወስነው የመንግስትን ፈቃድ ጠይቀው ከገዥው ፓርቲ ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ ውይይቶችንና ክርክሮችን የሚያደርጉ ሳይሆኑ፤ ጠያቂዎች በራሳቸው መንገድ የሚጠይቋቸውና በራሳቸው መንገድ እንዲመለሱላቸው የሚፈልጉ ሆነው መገኘታቸው፤ መንግስትም ጥያቄዎችን ተቀብሎ የሚያስተናግድበት መንገድ ሃይል የተቀላቀለበት መሆን ለሰው ህይወትና ለንብረት ውድመት መስኤዎች መሆኑ ነው። መንግስትም ሆነ ገዥው ግንባር ለጥያቄዎቹ አዲስ አይደለም፤ ላለፉት 25 ዓመታት ሲጠየቅና ሲከራከር ኖሯል። አሁንም በጥያቄዎቹ ሳይሆን ጥያቄው በሚቀርብበት መንገድ ላይ ነው “ህጋዊ አይደለምና ህግ አስከብራለሁ።” በማለት ውጥረት ውስጥ የገባው። ጥያቄዎቹ በተቀመጡበት ቅደም ተከተል የመጀመሪያዎችን ሁለት ጥያቄዎችን መንግስትና ገዥው ፓርቲ “በራሴ መንገድ ጥያቄዎችን እየመለስኩ ነው፣ ውጤቱ በአንድ ሌሊት ላይታይ ይችላል፤ ሆኖም ቀስበቀስ ሁሉንም አሟላለሁና ፋታ (እድል) ይሰጠኝ” የሚል መልስ ይሰጣል። መልሱ ጠያቂዎችን አላረካም “25 ዓመታት እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ከበቂ በላይ ነው፤ ከዚህ በላይ መታገስ በቃ።” የሚል ጩኸት ከየአቅጣጫው ይሰማል።

  ጥያቄዎቹ መሰረታዊ ከመሆናቸው የተነሳ አሁንም በመንግስትና በገዥው ፓርቲ ህዝብን በሚያረካ መልኩ በተግባር ቢመለሱ ጠያቂዎችን፣ መላውን የኢትዮጵያ ህዝብና ራሱን ገዥውን ፓርቲና መንግስት ጭምር ከጥፋትና ከውድቀት ያድናሉ ብዬ በግሌ አምናለሁ። ህግን ለማስከበር ህግን ማክበር፣ ህገ-መንግስትን ለማስከበር፤ ህገ-መንግስቱን ማክበር ለመንግስት የመጀመሪያው ጉዳይ ነውና።

  ሁለተኛው ክፍል ጥያቄ በራሱ በህገ-መንግስት ላይ ያነጣጠረ ስለሆነ፣ ህገ-መንግስቱ በሚሻሻልበት መንገድ ላይ የሰከነ ውይይት ይጠይቃል። በመጀመሪያ በመሻሻሉ ላይ ስምምነት መደረስ አለበት፤ ቀጥሎ ደግሞ የትኞቹ አንቀጾች ይሻሻሉ? ምንስ ተብለው ይሻሻሉ? ለሚሉት ጥያቄዎች ሁሉንም የሚያግባባ መልስ ለማግኘት፣ የተለያዩ ወገኖችን ፍላጎትና የአገሪቱና የአለምን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ ውይይትና የሚያግባባ ስምምነት ላይ ለመድረስ፤ በሁሉም ወገን ዘንድ የሰከነ መንፈስ፣ ቁርጠኝነትና ለአገርና ለህዝብ ጥቅም የሚያስብ ልቦና ያስፈልጋል። ይህ በእንዲህ እያለ፤ ይህ በጠያቂና በተጠያቂ መካከል የተፈጠረው ውጥረት የማያስፈልግ የጎንዮሽ ውጤት እያስከተለ ነው።

  ከሞት፣ ከአካልና ከንብረት ውድመት፣ ከእስርና ከመንገላታት በተጨማሪ በመንግስትና በህዝብ መካከል ያለውን መተማመንና መቀባበል እየሸረሸረ ይገኛል። ከዚያም አልፎ በህዝብና በህዝብ መካከል ዘርንና ቋንቋን መሰረት ያደረገ መነጣጠል፤ ነጥሎ አንድን ህዝብ ለዚህ ሁሉ ችግር ፈጣሪና ተጠያቂ የማድረግ አዝማሚያ ተከስቷል። ለዚህ ነው በመነሻዬ ምንድን ነው የምንፈልገው? እንዴትስ ነው የምናገኘው? ስል የጠየቅሁት። አየሩን የሞሉት ጥያቄዎች ተጨምቀው ሲታዩ ከላይ የዘረዘርኳቸውን ከመሰሉ፤ ጥያቄዎቹም ሆኑ መልሶች የሚገኙት ከመላውን ከኢትዮጵያ ህዝብ እንጂ ከአንድ የተወሰነ ቡድን ወይም ጎሳ አይደለም እላለሁ።

  ከላይ የተነሱት ጥያቄዎችም ሆኑ መልሶች የጋራ ካላደረግናቸው፣ የአንድ ወገን ወይም የአንድ “ክልል” ወይም የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝብ ብቻ እንደሆነ ተደርጎ እንዲታይ ከተደረገ፤ የሚመጣውም መልስ ሁሉንም በእኩል አያስደስትም። በጥያቄና በመልሱ ሂደት የሚገለል ወገን ከኖረ በራሱ ጊዜ ደግሞ የራሱን ጥያቄ ይዞ የራሱን መልስ ፍለጋ መነሳቱ አይቀርምና። ይህም እድገትን ሳይሆን ውድቀትን፣ አንድነትን ሳይሆን መነጣጠልና እርስበርስ መጠፋፋትን ያስከትላል። ይህ ደግሞ “የመቶ ዓመት የቤትስራ ሰጥተናቸዋል። ” ላሉ ወገኖች ትንቢት እንዲሰምር መፍቀዳችን ነው። “

Comments are closed