Logo

እውን የኢፊዲሪ ህገ መንግስት ችግር ፈቺ ነው?

September 28, 2016

ethiopian constitutionይድረስ ለእነ አቶ ገብሩ አሥራት

ሰሎሜ ኢዮብ
መስከረም 2009
ሻሸመኔ

በፈረንጅ ሀገር መንገደኞች በባቡር ሲጓዙ የምሳ ሰዓት ደርሶ ኖሮ ተሳፋሪዎች በየምናምኑ የያዙትን ምግብ እያወጡ መመገብ ይጀምራሉ፡፡ አንዱ ተሳፋሪ የሚመገበው አሣ ነበር፡፡ የአሣውን ጭንቅላት በጥንቃቄ እየሰበረ እርጥበት በማይስብ ወረቀት እየጠቀለለ ከኪሱ በመክተት ሌላውን እየቆረጣጠመ ሲበላ ከፊለፊቱ የተቀመጠ ሌላው ተሳፋሪ በመገረም ይመለከተዋል፡፡ ተገራሚው መንገደኛ ለጫወታ መክፈቻ ይሆነው ዘንድ በመስኮት ስለሚአየው የዓየር ሁኔታ ከጠቃቀሰ በኋላ ስለምን ሌላውን እየበላ የአሣውን ጭንቅላት ከኪሱ መክተት እንዳስፈለገው ይጠይቀዋል፡፡ የጭንቅላት ችግር ላለባቸው ፍቱን መድኃኒት ስለሆነ እሸጠዋለሁ ይለዋል፡፡ እንግዲያውስ ለእኔ ሽጥልኝ ይለውና በሁለት ዶለር ይገዛዋል፡፡ ገዢው ጥቂት እንደቆረጣጠመ ለእኔ ጭንቅላቱን በሁልት ዶለር የሸጥክልኝ አንተ ሙሉውን አሣ በምን ያክል ብተገዛው ነው ብሎ ሻጩን ይጠይቀዋል፡፡ በሁለት ዶለር ብሎ ሲመልስለት ገዢው በስጨት ብሎ እንዴት እንደዚህ ታደርጋለህ በሚል ሙግት ገጠመው፡፡ ሻጩም የኔ ወንድም ሲሆን ልታመሰግነኝ ይገባል እንጂ ልትጣላኝ አያስፈልግህም፡፡ ይሄው ጭንቅላትህ በተጨባጭ መሥራት ስለጀመረ አልተጎዳህም ብሎ መለሰለት፡፡

ይሄን ተረት ከጓደኞቼ ጋር ሆኜ ከአንድ ጋዜጣ ቃለመጠይቅ አምድ ያነበብኩት ከባድሜ ጦርነት መልስ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር በሃሳብ ልዩነት ከሁለት መከፈሉን ስንሰማ እነዚህ ሰዎች ቢዘገዩም ማሰብ ጀመሩ የተባባልነውን ግምት ለማብላላት ስንወያይ ነበር፡፡ በእኔ በኩል ግምታችን ስህተት መሆኑን ከተረዳሁት ውሎ ቢአድርም አሟጥጬ እርም ያልኩት እነአቶ ገብሩ አሥራት፤ ጄኔራአበበ ተክለሃማኖት፡ ጄኔራል ፃድቃን ገብረተንሳይ ሌሎችም የቀድሞና የአሁን ወያኔዎች ለዓመታት ያስቆጠረውን ችግራችንንም ሆነ አሁን አገራችን ያለችበትን ቀውስ ለመታደግ የኢፌደሪ ህገ መንግስት አልፋና ኦሜጋ እንደሆነ ሲሰብኩ ስሰማና የፃፉትን ሳነብ ነው፡፡ ይህ የሆነው በቀድሞ አስተሳሰባቸው ቢሆን ኖሮ ከቁብ አልቆትረውም ነበር፡፡ ሁኔታው ፈቅዶላቸው ዓይናቸውን ከገለጡ በኋላም እዛው መሆናቸው ገርሞኛል፡፡ በዚህ ሂሳብ እንደተፈጠሩ ካሉት ወያኔዎች በጎ ነገር መጠበቅ በራሱ ከነሱ አንሶ መገኘት ነው፡፡ ለማንኛውም በሥራ ልምድም ሆነ ተምረው የባህሪ ለውጥ መቀዳጀት ስለተሳናቸው የሚአውቁ መስሏቸው ስለህግ ልዕልናና ትርጓሜ ተሳስተው እንዳያሳስቱ እነሱ ዕጹብ ድንቅ ስለሚሉት የኢፌዲሪ ህገ መንግስት እኔ ያለኝን ግንዛቤ ለእነሱና ለሚአነቡኝ ወገኖቼ ማካፈል ፈለግሁ፡፡ (በነገራችን ላይ ጄኔራል ጻድቀን ከፐሮፌሰር መሳይ ከበደ ጋር እያደረጉት ያሉት የሀሳብ ልውውጥ በራሱ (በፍሬ ጉዳዩ ላይ በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ) መበረታታት ያለበት የሰለጠነ ሰው ባህሪ ነው በሚል እምነት በግሌ አደንቃለሁ፡፡)

ብዙዎቻችን እንደምናስታውሰው ህወሀት በግንቦት 1983 ምኒልክ ቤተ መንግሥት ገብቶ የበተረ-መንግሥትነት ሥልጣን ከጨበጠ በኋላ የሚፈልጋቸውን ዓላማዎቹን በህግ ሽፋን ለማስፈጸም የኢትዮጵያ ህጎች ሁሉ የበላይ ህግ የሆነ ሰነድ ማዘጋጀት የግድ አለው፡፡ በወቅቱ የተመቹትን የፖለቲካ እድርተኞቹንና የተዘናጉለትን ኃይሎች አሰባስቦና እንደነ አቶ ክፍሌ ወዳጆ ያሉ ወዶገባ ምሁራን ቀጥሮ የኢትዮጵያን ዕጣ ፋንታ ከህወሃት ህልውና ጋር ያቆራኘ የህገ መንግሥት ረቂቅ አዘጋጀ፡፡ ወደኋላ ላይ የምመለስበት የዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶች ድንጋጌም ታከለበትና የተባለው ረቂቅ በርካታ የህግ ግድፈቶችና የተዛቡ እሳቤዎች እንደያዘ በህወሃት የፖለቲካ እድርተኞቹና የሀገሪቱን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦች፤ ሕዝቦች ይወክላለሉ በተባሉ እንግዶቹ ህዳር 29 ቀን 1987 አዲስ አበባ የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ተብሎ እንዲጸድቅ አስደረገ፡፡ ይህ ህገ መንግስት በከፊል ጠቃሚ ድንጋጌዎች ቢይዝም ከመረቀቁ እስከ መጽደቁ ያለው ሂደት ኢዲሞክራሲያዊ ከመሆኑም በላይ በዋናና መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ህልውና፤ የግለሰብ የዜግነት መብቶች፤ የፌደራል መንግስቱ መዋቅሮችና በተለይም የህግ ተርጓሚው ተቋም ላይ አፋኝና አፍራሽ የሆኑ ድንጋጌዎች ይዧል፡፡ ለማሳያ ያክል አንድ አራቱን አንቀፆች እንያቸው ፡፡

በኢፌዲሪ ህገ መንሥት አንቀጽ 8(1) መሠረት የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ብሔሮች፤ ብሔረሰቦች፤ ሕዝቦች ናቸው ይላል፡፡ በህግ ትርጓሜ ይህ የቡድን መብት ነው፡፡ የዚህ ቡድን ትርጉም በአንቀጽ 39(5) ላይ በጥብቅ ተደንግጓል፡፡ በቡድኑ የታቀፉት አባል አካሎች ደግሞ ሦስት ናቸው (ብሔሮች፤ ብሔረሰቦች፤ ህዝቦች)፡፡ የእነዚህ ሦስት አካሎች የተናጠል ትርጉማቸው፤ አንዱ ከሌላው ልዩነታቸውና አንድነታቸው በህግ ተደንግጎ አልተገለጸም፡፡ ስለሆነም በአንቀጽ 8(1) ለብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች የተሰጠው የሉዓላዊ አገር ባለቤትነት መብት ለኢትዮጵያዊ ዜጎች ሁሉ ተፈጻሚ ስለመሆን አለመሆኑ፤ ምንአልባት ከሆነም ህጉን በመተርጎምና በማስፈጸም ሂደት ሊነሱ የሚችሉ ጥያቄችን የሚመልስ ማብራሪያ በህገ መንግሥቱ አልተካተተም፡፡ ህግ ተርጓሚው አካል ህጉን ለመተርጎም የነዚህን ጥያቀዎች መልሶች ጠንቅቆ ማወቅና መረዳት ይጠበቅበታል፡፡ ህግ በኦፊሴል የተደነገገ አንቀጽ ተጠቅሶ እንጂ በግምትና በማድበስበስ አይተረጎምም፡፡ ፍትህ በህግ የበላይነት እንጂ በባለሥልጣን መመሪያና በዘፈቀደ አሠራር አይተገበርም፡፡ ከዚህ እውነታ አንጻር የኢፌዲሪ ህገ መንግስት በነዚህ የህግ ህጸፆች የተተበተበ ስለሆነ ችግር ፈቺ ሳይሆን እራሱ ችግር ፈጣሪ መሆኑን ቀጥሎ በጥልቀት እናየዋለን፡፡

አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከነዚህ በአንቀጽ 8(1) የተመለከቱት አካሎች (ብሔሮች፤ ብሔረሰቦች፤ ሕዝቦች) መሀከል ከአንደኛው ተወላጅ ወይም አባል ካልሆነ ወይም ማንነቱን በተወለደበት ዘር (ብሔር ብሔረሰብ) ብሎ ከሌላው እራሱን መለየት ካልፈለገ ወይም ወላጆቹ ከቡድኑ አካሎች ውስጥ የሁለቱ አካሎች ቅይጦች (ለምሳሌ አባት ኦሮሞ እናት አማራ) ወይም ወላጆቹ እራሳቸው ከሁለት በላይ ከሆኑ ብሔሮች ወይም ብሔረሰቦች የተወለዱ ቢሆኑ ልጃቸው በማንኛቸው ብሔር ወይም ብሔረሰብ ማንነቱ እንደሚለይ ወይም ግለሰቡ በትውልድ የውጭ አገር (በአንቀጽ 6(2) የውጭ አገር ዜጎች የኢትዮጵያ ዜግነት ማግኘት ይችላሉ ስለሚል ጋና፤ ጃማይካ፤ ጣሊያን፤ ወዘተ) ቢሆንና በዜግነት ኢትዮጵያዊ ቢሆን የሉዓላዊ አገር ባለቤትነት መብቱን የሚአስከብርበት የህግ አግባብ በኢፌዲሪ ህገ መንግስት ውስጥ የተደነገገ ህግ የለም፡፡ በአንቀጽ 6(3) ዜግነትን በሚመለከት ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል ይበል እንጂ የግለሰብ ዜጋ የሉዓላዊ አገር ባለቤትነትን መብት ስለማካተቱ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ የተባለውም ዝርዝር ስለመውጣቱ እስካሁን ይፋ አልተደረገም፡፡ የሉዓላዊ አገር ባለቤትነት መብት ለብሔሮች፤ ብሔረሰቦች፤ ሕዝቦች የተሰጠውን ድንጋጌ በቡድን መብትነት ማእቀፍ ለቡድኑ አባላት ሁሉ እንደሚሠራ እንቀበለው ቢባል እንኳን የዜግነት መብት እንደመሆኑ ዞሮ ዞሮ መሬት ወርዶ ተፈጻሚ የሚሆነው የቡድኑ አባል በሆነ ግለሰብ ዜጋ ላይ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ህገ መንግስቱ በአንቀጽ 8(1) የያዛቸው ድንጋጌዎች ስለግለሰብ ዜጋ የሉዓላዊ አገር ባለቤትነት መብት ያሉት ነገር ባለመኖሩ ለህግ ትርጓሜ የማይበቁ በድርብርብ የቃላት ጫወታ ተጠቅለው የተዳፈኑ የመንደርዳሪያ ሀሳቦች ስብስብ ሆነው ቀርተዋል፡፡ ይህ ትልቅ የህግ ሕፀጽ ነው፡፡ ለሰው ልጅ ሁለንተናዊ ደህንነትና ሰብአዊ ክብር የህጎች ሁሉ ዋና መሠረት የሆነውን የግለሰብ መብት መጣስ ነው፡፡ ሰዎች ለሰዎች በሰዎች የተፈጠረ አካል ወይም ቡድን ምንጊዜም በየትም ቦታ መነሻ እርሾው (አስኳሉ) ግለሰብ ነው፡፡ ስለሆነም የግለሰቡ መብት ሲከበር በግለሰቦች የተገነቡት አካሎች ወይም ቡድኖች ወይም ድርጅቶች መብቶች ሁሉ ያለጥርጥር ይከበራሉ፡፡ የዚህ ተገላቢጦሽ ግን ማለትም የቡድኑ መብት ስለተከበረ የእያንዳዱ ብሔር ወይም ብሔረሰብ ተወላጅ መብት ወይም የቡድኑ አባል መሆን ያለመሆኑ በውል ያልታወቀና ስለመሆኑም መረጃ ማቅረብ የማይችል ግለሰብ መብት እንደሚከበር መቁጠር በህግ አግባብ ተቀባይነት የለውም፡፡ ሕግ በይሆናል አይተረጎምም፡፡ ከዚህም በላይ አንድ ግለሰብ የአንድ ብሔር ወይም ብሔረሰብ ተወላጅ ወይም አባል ቢሆንም እንኳን የግለሰብ መብቶች ከቡድን መብቶች በላይ እጅግ የረቀቁና የተወሳሰቡ ስለሆነ በተናጠል እንጂ በጅምላ የህግ ትርጓሜ በፍጹም ሊዳኙ አይገባቸውም፡፡ አይቻላቸውምም፡፡ የኢፌዲሪ ህገ መንግስት ይህን መሰረታዊ የህግ መርሆ ጥሷል፡፡

በህገ መንግስቱ አንቀጥ 8(1) ሌላው ግንዛቤ ሊያዝበት የሚገባው ጉዳይ በስነቋንቋ አስተምህሮት ቃሉና ዕቃው (ሀሳቡ) ዝምድና የላቸውም፡፡ የሚአዛምዳቸው ተጠቃሚው ህብረተሰብ ነው፡፡ ቋንቋ ማደግም መክሰምም ሚችል የሰው ልጅ መግባቢያ መሳሪያና ተፈጥሮአዊ የማንነት መለያም ቅርስ ነው፡፡ ያረጁ ቃላት በአዳዲስ ቃላት የመተካት ወይም የትርጉም ለወጥ ማድርግ እንደሚችሉ እንደዚሁም አንዱ ቋንቋ ከሌላው ቃላት መዋስና ማመሳሰል እንደሚችል ማወቅና መቀበል ተገቢ ነው፡፡ ከዚሁ አኳያ በኢፌዲሬ ህገ መንግስት ውስጥ የተደነገገውን ስልጣንና መብት በትክክል ለመተርጎም እንዲቻል ስለተሰጣቸው ትርጉም የተባለ ነገር ስለሌለ ማን ብሔር ነው ማንስ ብሔረሰብ ነው የሚለውን ለመለየት ቢአሰቸግርም ዛሬ ከ60ዎቹና ከዚያ በላይ ያለው ትውልድ ስሞቹን (ብሔር/ብሔረሰብ) 1ኛ በንጉሱ ጊዜ በተማሪዎች ንቅናቄ፤ 2ኛ በደርግ ዘመን ስለ ኮሚኒስት ርዕዮት ሲአቀነቅንና የብሔረሰቦች ኢነስቲቱሽን (ተቋም) ይጠቀምባቸው ስለነበር፤ 3ኛ ዛሬ በተለይ አዲሱን ትውልድ ጨምሮ በህወሃት እለት በእለት ስለምንሰማቸው ስሜት እየሰጡንና እየለመድናቸው መጥተዋል፡፡ የህዝባችንን በቋንቋ፤ በባህል፤ በስነልቦና፤ በመሳሰሉት የሚለያይ እንደመሆኑ የኦሮሞ፤ የአማራ፤ የትግሬ ወዘተ ብሔሮች ወይም ብሔረሰቦች ብለን ለይተን ለመግለጽ ጠቅመውናል፡፡ አሁን አሁን ሁሉም ወገን (ኤሊቱም ተራውም ሕዝብ) እያፈራረቀ እየተጠቀመባቸው ነው፡፡ የሁለቱን ልዩነት ወደፊት በሂደት እንደምናጠራው በማሰብ ለጊዜው እንዳሉ በማፈራረቅ እየተጠቀምንባቸው መቀጠል ነው ሁላችንንም ሊአስማማን የሚችለው፡፡ ሕዝቦች የሚለው ቃል ግን በአንቀጹ ውስጥ ያለምንም አገልግሎት የተሸነቀረ ነው፡፡ ምንአልባት ከሁለትና ከዚያ በላይ ከሆኑ ብሔር ብሄረሰቦች የተወለዱ ወይም በትውልድ የሌላ አገር ሆነው በዜግነት ኢትዮጵያዊ ለሆኑ ወገኖች እንደ ማጽናኛ መጠለያቸው እንዲቆጥሩት ታስቦላቸው ይሆናል፡፡ ልብ በሉ! ቢቸግረን ነው እንጂ በየትም አገር በምናልባትና በማስተዛዘኛነት ሕግ አይደነገግም፤ አይተረጎምም፡፡ ወደቃሉ አጠቃቀም ስንመለስ አቶ ልደቱ ዓያሌው መድሎት በተባለው መጽሀፉ እንደአብራራው በመጀመሪያ ደረጃ በቋንቋ ቁጥር (ብዜት) ህግ መሠረት ሕዝብ (people) በራሱ ብዙ ነው፡፡ ሕዝቦች (peoples) የብዙ ብዙ ነው፡፡ ስለሆነም ስለአንድ ሉዓላዊ አገር ባለቤቶች የምንናገር ከሆነ ሕዝብ እንላለን፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደማለት፡፡ በዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ዘንድ በተለይ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ሕዝቦች (peoples) የሚለውን መጠቅም የሚቻላቸው ከሁለትና ከዚያ በላይ ሉዓላዊ የሆኑ አገሮችን ባለቤቶችን ለመግለጽ ሲፈልጉ ነው፡፡ የእንግሊዝ፡ የጀርመንና የፈረንሳይ ሕዝቦች እንደማለት፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ የሆነው የአማርኛ ሰዋስውም (grammar) ይሄንኑ ነው የሚአስተምረው፡፡ የኢፌዲሪ ህገ መንግስት የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሚለው ምንአልባት በአንቀጽ 39(1) መሠረት ወደፊት መገነጣጠሉን ታሳቢ በማረግ የዘጠኙ ክልሎች መስተዳድር መንግስታትን በየፊናቸው እንደ ሉዓላዊ አገሮች በመውሰድ፤ በውስጣቸው ነዋሪ የሆኑትን ዜጎችንም እንደ ዘጠኝ ሉዓላዊ አገሮች ባለቤቶች ቆጥሯቸው ይሆናል፡፡ በዚህ ዓይነት የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት የሀሳብ ድርቀትና የህግ አወጣጥ መፋለስ ብቻ ሳይሆን የቋንቋም ችግር አለበት፡፡

በ21ኛው ክፍለ ዘመን ይሄን ያክል የወረደና ጉልህ የህግ መፋለስና የሥራ ቋንቋ መወለካከፍ የበዛበት ህገ መንግሥት ይዞ መገኘትና በዜጎች ላይ መጫን ዛሬ ላይ ሰብአዊ መብቶችን ይጥሳል፡፡ የዲሞክራሲን ደብዛ ያጠፋል፡፡ ዜጎች በስርአቱ ላይ እምነት ያጣሉ፡፡ የህብረተሰቡን ሕይወት እያመሰቃቀለ ለብጥብጥና ለቀውስ ይዳርጋል፡፡ ለነገውም የታሪክ ተወቃሽ ያደርጋል፡፡ ክልላዊ ብሔርተኝነት የህወሀት የፖለቲካ መሠረትና የስልጣኑ ምንጭ በመሆኑ ይሄንኑ በህብረተሰቡ ውስጥ ለማስረጽ በሚደረገው ትንቅንቅ ዛሬ በህወሀት ኢትዮጵያ አንድ ሰው የቀበሌ መታወቂያ ለማግኘት የግድ ብሔሩን ወይም ብሔረሰቡን መናገር አለበት፡፡ ባለ ጉዳዩ ኢትዮጵያዊ ነኝ ወይም ቅይጥ ነኝ ወይም አላውቀውም ካለ የሚጠብቀው ከግልምጫ ጋር ሁለት ነገር ነው፡፡ ወይ መታወቂያው ይከለከለዋል ወይም የቀበሌው ባለሥልጣን በራሱ ምርጫ የፈለገውን ብሔር ብሔረሰብ (ብዙውን ጊዜ አማራ) ብሎ በመታወቂያው ላይ ይጽፍበታል፡፡ ባለጉዳዩ ብሔሩን ወይም ብሔረሰቡን ለመናገር ፍቃደኛ ከሆነ ደግሞ መናገር የሚጠበቅበት የአባቱን ወገን ነው፡፡ ምንአልባት በኢትዮጵያ ባህል ልጅ ባባቱ የስም መስመር ስለሚጠራ ይሆናል፡፡ የዘር ሀረግን በባህል እይታ ብቻ መወሰን የስነተፈጥሮ መሃይምነት ነው፡፡ አንድ ግለሰብ የዘር ሀረጉን በእናቱ ወይም ባባቱ ደም ብቻ እንዲወስን ማድረግ የግለሰቡን መብት መጋፋት ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮንም መጻረር ነው፡፡ ይሁዲዎች ዘር የሚቆጥሩት በናት ነው፡፡ የነርሱ ተልእኮ የተለየ ነው፡፡ ግለሰቡ በትክክል የአይሁድ ደም ያለው መሆኑን እርግጠኛ ለመሆን ነው፡፡ የህወሃት ዓላማ ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ክልላዊ ብሔርተኝነትን አሳድጎ አገራዊ ብሔርተኝነት ለማቀጨጭ ብቻ ሳሆን አንዱን ኢትዮጵያዊ ከሌላው ኢትዮጵያዊ የሚመሳሰለበትን አጣጥሎ የሚለይበትን ለማጉላት ያለመ ነው፡፡ የሆነስ ሆነና እነአቶ ስዩም መስፍን ስለጀርመንና ሩዋንዳ የዘር ማጥፋት አሰቃቂ እልቂት ብዙ ሲአወሩ በግለሰብ መታወቂያ ላይ ብሔር ወይም ብሔረሰብ መጻፍ በሩዋንዳ ስላስከተለው መዘዝ ለምን መተንፈስ አልፈለጉም? እውነትን በመጋፈጥ እንጂ በማለባበስ ማለፍ የጥፋት መንገዱን አያስቀይረውም፡፡

ቀድሞ ነገር አንድን ግለሰብ የተወለድክበትን ብሔር ብሔረሰብ ስም በመታወቂያህ ላይ አጽፍ ማለትን ምን አመጣው? ለምንስ አስፈለገ? ያልተወለዱትን ተወልደነዋል፤ ያልወከላቸውን እንወክለዋለን እያሉ በድርቅና የብሔር ብሔረሰብ ስም እንደሹመት የሚቀባበሉ የራሳቸው ሰዎች እነ አቶ በረከት ስምዖን፤ አዲሱ ለገሰ፤ ደ/ር ወርቅነህ ገበየሁ፤ የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ንፁሃኑንና እራሱን ሆኖ የሚኖረውን ዜጋ ምን አርግ ይሉታል? እኔ እንደገባኝ መንደርተኝነት ከሰውነት በታች ያወርዳል፡፡ ከአለማወቅ የሚመነጭ እብሪት ሲደነድን እጅግ ደፋር ያደርጋል እንጂ የዚህ የብሔረሰብ ወይም ብሔር ማንነት በየግለሰቡ መታወቂያ ላይ ካልተገለጸ ተብሎ ዜጎችን የማጉላላት ጦስ እንደዛር ቀድሞ የሚነግሠው ባዛዡ ላይ ነው፡፡ የሰደድ እሳት ቀድሞ የሚለበልበው ቆስቋሹን ነው፡፡ ከህወሃት የዘር ብልት መሀንዲሶቹና የጥላቻ ፖለቲካ አቀንቃኝ ሊቆቹ መሀከል ከሟቹ ባለራዕይ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ቀጥሎ በቁም ካሉት ሁለቱ ስዩም መስፍንና አባይ ፀሐዬ ከሰሞኑ ስለሩዋንዳው የኢንተርሃምዌ (Interahamwe) እና ስለናዚ ጀርመኒ ሆሎኮስት (holocaust) የዘር ማጥፋት ግድያ አስፈሪነት በእነሱ እይታ እየተረኩ በቴሌቪዢን መስኮት ሲአስፈራሩን ሰነበቱ፡፡ ለመሆኑ ዘረኝነትንና የጥላቻ ፖለቲካን በህገ መንገስት ደረጃ መደላድል አሠርቶለት በሀገራችን ያነገሰውና አሁንም ቤንዚን እያርከፈከፈ በማቀጣጠል ላይ ያለው ማን ሆነና ነው እነሱ ሌላውን መካሪና አስፈራሪ የሆኑት? የሚአወሩትን የዘር ማጥፋቱን እልቂት የፈጸሙት እኮ እስከአፍጫቸው የታጠቁትና የብዙሃን መገናኛ በቁጥጥራቸው ስር የነበረው በጀርመን በናዚ ጦር፤ በሩዋንዳ ደግሞ በኢንተርሃምዌ (የሁቱዎች ፓርላሜንታሪ ድርጅት) የሚታዘዙ ሚሊሺያዎች ነበሩ፡፡ ታዲያ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ በማንኛውም መስፈርት ቢሊካ ለናዚና ለኢንተርሃመዌ የሚቀርብ ብቻ ሳይሆን በአስተሳሰብም ሆነ በቁሳዊ ሎጂስቲክ በትክክል የሚመስላቸውና የሚስተካከላቸው ድርጅት ከህወሃት በስተቀር ማን አለ? በዘር ማጥፋት ግድያው ለገዳዮቹ ሰለባዎቹን ለይቶ ያመቻቸው እንደ ጀርመንና ቤልጂየም ቅኝ ገዚዎች ሥርአት በዜጎች መታወቂያ ላይ የዘር ስም በግዳጅ እያጻፈ ያለው ድርጅት ከህወሃት በስተቀር ሌላ ማን ነው? በየቦታው እስር ቤቶች በእሳት ሲጋዩ እስረኞችን በጥይት መቁላት ከሆሎኮስት ቢብስ እንጂ በምን ያንሳል? በቅርቡ ሦስት ዲፕሎማቶች የዓይን ምስክርነታቸውን እንደተናገሩት ከመተማ-ዮሐንስ የትግራይ ተወላጆች ጓዛቸውን በስርአት ጠቅልለው ወደ ሱዳን እንዲሄዱና ከቀናት ቆይታ በኋላ እንዲመለሱ በማድረጉ ተግባር አቀነባባሪዎቹና ፊልም ቀራጮቹ የመንግስት ደህንነቶች መሆናቸው የሐውዜን ታሪክ ከመድገም በምን ይለያል? ይህ ድራማ የተፈለገበት ዓላማውስ ምንድን ነው? እራስን አለማወቅ ወይም እየታዩ መደበቅ ትልቅ የጤንነት ችግር ነው፡፡

የዘር ማጥፋት ወንጀል ጉዳይ ሲነሳ መረሳት የሌለበት በአውሮፓ የሂትለር ናዚ ጀርመን መንግሥት እ.ኤ.አ. ከ1933-1945 ባለው ጊዜ 6 ሚሊዎን በሚሆኑ ይሁዶች ላይ የፈጸመው አሰቃቂ ጭፍጨፋ በግንባር ቀደምትነት ሲጠቀስ በአፍሪቃ አህጉር ደግሞ በሩዋንዳ አገር ትልቁ የዘር ማጥፋት ዘግናኝ ግድያ አፈጻጸሙ እንደሚከተለው ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በሚያዚያ ወር 1994 በሩዋንዳ በመቶ ቀናት ውስጥ ብቻ 800,000 ቱትሲ ብሄረሰቦችና የተወሰኑ ለዘብተኛ ሁቱ ብሄረሰቦች ፆታ እድሜ ሳይለይ በዘግናኝ ሁኔታ ተጨፈጨፉ፡፡ ቱትሲዎች በቆዳ ቀለምና በተክለ ሰውነት (በአንጻራዊነት) ኢትዮጵውያንን ስለሚመስሉና በአፈ ታሪክ ከኢትዮጵያ የፈለሱ ናቸው ስለሚባል በዐባይ ወንዝ በኩል ወደአገራችሁ ተመለሱ እያሉ የተወሰኑትን ከነነፍሳቸው፤ የተወሰኑት ደጎሞ አስከሬናቸው ቪክቶሪያ ሐይቅ ውስጥ ተጥሎ ሲንሳፈፍ ሰንብቷል፡፡ ጥላቻ እስከዚህ የሰውን ልጅ ከሰውነት በታች ያወርደዋል፡፡ የዘር ማጥፋቱ ሰለባዎች ገዳዮቻቸው በኢንተርሃምዌ ድርጅት የሚደገፉ በወቅቱ የሩዋንዳ መንግሥት ታጣቂዎች ነበሩ፡፡ ለዚህ አሰቃቂ ግድያ የመንግስት ትራንስፖርትና የብዙሃን መገናኛዎች ቤተ እምነቶች ሳይቀሩ በተዘዋዋሪና በቀጥታ እጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ ሩዋንዳውያን የዘር ጥላቻው መርዝ በቅኝ ገዚዎቻቸው የተዘራባቸው ሲሆን ሲአመረቅዝ ቆይቶ የፈነዳው በትውልድ ከሁቱ ብሔር ወይም ብሔረሰብ የሆነው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት (Juvenal Habyarimana) የተሳፈረበት አውሮፕላን በላወንቸር ተመቶ በመሞቱ የቱትሲዎች እጅ አለበት በሚል ጥርጣሬ ቂም በቀል ነበር፡፡ እነዚህ ነፍሰበላ ገዳዮች ዘግናኝ የጅምላ ግድያውን ሲፈጽሙ ማን ቱትሲ ብሔር ወይም ብሔረሰብ እንደሆነ ማንኛው ሁቱ እንደሆነ ለመለየት ያስቻላቸው ቀደም ሲል በጀርመን በኋላም በበልጂየም ሩዋንዳውያን ቅኝ ተገዢ በነበሩበት ጌዜ በመታወቂያቸው ላይ የብሔራቸው ወይም ብሔረሰባቸው ስም ዛሬ በህወሃት እኛ አገር በቀበሌ መታወቂያ ላይ እንዲጻፍ እንደሚደረገው በግድ ይጻፍ ስለነበረና እ.አ.አ በ1962 ነጻ ከወጡ በኋላም ያው አሠራር ስለቀጠለ ነው፡፡ ጀርመኖች ለቱትሲዎች (አናሳዎቹ) ብሔሮች ኮኬሺያን ትመስላላችሁ እያሉ ከቤት አሽከርነት ጀምሮ በተላላኪነት፤ በወታደርነት፤ በዝቅተኛ የቢሮ ሥራ በመሳሰሉት በመቅጠር ሲአደሉላቸው በኋላ የተረከቧቸው ቅኝ ገዢ ቤልጂየሞች በበኩላቸው ለሁቱዎች (ብዙሃኖቹ) አላግባብ ተበድላችኋል በማለት ያዳሉላቸው ነበር፡፡ የሁለቱም ቅኝ ገዢዎች ዓላማ ግልጽ ነው፡፡ ጥቁሮቹን በብሔረሰብ ዘራቸው ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲመቿቸው ማድረግ ነበር፡፡ የእኛውም ህወሃት እንዳቅሙ (በብዙ ምከነያት ከቅኝ ገዢነት የሚመነጭ የበላይነት ስሜት ሊአድርበት ባይችልም ምንአልባት ከአናሳነትና ከብቃት ማነስ በመነጨ በበታችነት ስሜት፡ በፍራትና በጥላቻ በመመረዝ ካልሆነ በስተቀር) ከዚህ የተለየ ዓላማ ይኖረዋል ማለት እርጥብ ሞኝነት ይሆናል፡፡ ህገ መንግሥቱ ሀገራዊ ብሄራዊነትን እያኮሰመነ ክልላዊ ብሄርተኝነትን እንዲነግስ ማድረጉ፤ አንዱን ብሔረሰብ ከሌላው ማደናቆሩ አልበቃ ብሎት በቀበሌ ደረጃ ወርዶ ማን የትኛው ብሔር ብሔረሰብ እንደሆነ የሚለይበት አሠራር የዘረጋው ለዚሁ ለመከፋፈሉ እንዲጠቅም ነው ከማለት ባለፈ አይበለውና በሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ብሔሮች ወይም ብሔረሰቦች መሀከል ከእስካሁኑ በባሰ የመረረ ግጭት ቢቀሰቀስ የህወሃት የቀበሌ መታወቂያ ማን ከየትኛው ወገን እንደሆነ በመለየት ሥራውን ሠራ ማለት ነው፡፡ ይህን አይነቱን ግጭት ለመፍጠር ደግሞ በህገ መንግስቱ በተለይ በአንቀጽ 8(1)፤ 39(1)፤ 47(1-2)፤ 62(2፤ 3 እና 9) ላይ ጊዜ የሚጠብቁ ፈንጆች ተቀብረዋል፡፡

ከላይ አንዱን (አንቀጽ 8(1)) እንዳየነው ሌሎቹንም በዚህ አጭር ጽሁፍ ለማሳየት ባይመችም የኢፌዲሪ ህገ መንግሥት በተለይ አንቀጽ 8፤ 39፤ 40፤ 46; 47፤ 50; 62፤ 74፤ 89፤ 104 የየራሳቸው ትልቅ ችግር እንዳለባቸው ማጤኑ ተገቢ ነው፡፡ በጥቅል አገላለጽ የዜጎችን የአገር ብሔራዊ ስሜት ያዳክማሉ፡፡ የአገር ብሔራዊ ጥቅምና የማህበረሰቡ ብሔራዊ ደህንነት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅእኖ አላቸው፡፡ ለምሳሌ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 39(1) መሠረት ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፤ በሔረሰብ፤ ሕዝብ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን እስከመንገጠል ያለው መብቱ በማንኛውም መልኩ የተጠበቀ ነው ይላል፡፡ ልብ በሉ! ይህ መብት በተግባር ይተርጎም ቢባል ዋናው ችግር የአንድ ወይም ሁለት ሦስት ክልል መሄድ አለመሄድ አይደለም፡፡ ተፈጥሮና ኑሮ ለዘመናት ያስተሳሰሩት ሕዝብ በህወሃት ሰራሽ ችግር እኛና እነሱ እንዲባባል ተደርጎ የጎሪጥ በመተያየትና በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከማደግ ማነስ ተመርጦ እንደ ሰሜን ኮሪያ እናትና ልጅ ሲለያዩ፤ ህበረተሰቡ ሕይወቱ ሲመሰቃቀል፤ ተስፋው ሲደበዝዝ፤ በአገሩ የህግ ከለላ ሲአጣ ማየቱ ነው የሰው ልጅ መሸከም ከሚችለው በላይ ችግሩን የሚአገዝፈው፡፡ በዚህና መሰል ህገ መንግስቱ በከፈታቸው ቀዳዳዎች እየተጠቀሙ የዘመኑ ሰዎች ባሳደሩባቸው ኢሰብአዊ በደልና የባይተዋርነት ስሜት ብዙ ኢትዮጵያውያን ውድ አገራቸውን እንደኮንትራት ቤት እንዲቆጥሯት አድርጓቸዋል፡፡ እንኳንስ እራሳቸው አባት እናቶቻቸውና አያቶቻቸው ተወልደው በኖሩበት ቀዬ መጤ ተብለው ግድያ፤ ዘረፋና መፈናቀል ደርሶባቸዋል፡፡ በአገራቸው ከሁለተኛ ዜጋ ባነሰ መብት እንዲተዳደሩ ተገደዋል፡፡ ዜጎች በአገራቸው በመረጡበት የመኖርም ሆነ ተዘዋውረው የመሥራት መብታቸው የህግ ከለላ አጥቷል፡፡ ይሄ ኢሰባዊነትና የፖለቲካ ስካር በሂደት ሊለዝብ ይችል ይሆናል፡፡ እየለዘበም ነው፡፡ ነገር ግን ከሁሉም በላይ የሚአሳዝነውና የሚአስቆጨው አዲሱ ትውልድ የማንነት ቀውስ (identity crisis) ውስጥ እንዲገባ እየተደረገ ነው፡፡ የአገራዊ ማንነት ቀውስ ሰለባ የሚሆኑት ሕፃናት የሦስቱም ወገን ማለትም መገንጠልን የሚአቀነቅኑትም፤ የሚቃወሙትም፤ የልዩነቱን አቀጣጣይ ዳኞችም (የወያኔዎችም) ልጆች ናቸው፡፡ ምክነያቱም ሕፃናት ከወላጆቻቸው እየሰሙ የሚአድጉት በወደፊት ማንነታቸው ላይ ወሳኝ የሆነ ተፅእኖ አለውና፡፡ ለሚገባው ሰው ይሄ የልጆቻችን የማንነት ቀውስ እጅግ ከባድ አገራዊ ኪሳራ ነው፡፡ በግልም የህሌና ፀፀትና እንደየእምነታችን ፈጣሪ የማይፈቅደው ክፉ ሥራ ነው፡፡ ወላጅ ለልጁ የማያወርሰው ብሔራዊ ውርደት ነው፡፡ በትውልዱ ላይ ከሚአደርሰው የስነልቦና ስብራት ባሻገር ብሔራዊ ስሜት ያለው ዜጋ በሌለበት የአገር ፍቅር፤ ለአገር ታማኝነት፤ ለአገር ተቆርቋሪነት፤ ዘላቂ ሰላም፤ የአገር ልማትና እድገት ብሎ ነገር ከካድሬ ጫጫታ ያለፈ ትርጉም አይኖረውም፡፡ መዋሸት፤ መስረቅ፤ ማጭበርበር፤ ጥላቻ፤ ጎጠኝነት፤ እራስ ወዳድነት፤ በራስ አለመተማመን፤ ወዘተ አስነዋሪ ባህሪያት ሁሉ ዛሬ በዘመኑ ሰዎች እንደ ብልጠትና ልዩ ችሎታ የተቆጠሩት ይሉኝታ ብሎ ነገር፤ የአገር ፍቅር ብሎ ነር አሽቀንጥረው ስለጣሉት ነው፡፡ ልጆቻችንን ይችን አገራቸውን የሩቁን ብንዘነጋው ከቅርቡ ቅድመአያት፤ አያት፤ ወላጆቻቸው እስከ የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለው ያወረሷቸው እንደመሆኗ ባለፈው ታሪካቸው እየኮሩ፤ የዛሬውንም ከነሙሉ ክብርና ጠቄሜታዋ ኖረውባት ነገም እነርሱ በተራቸው ያለጥርጥር ለልጆቻቸው የሚአወርሷት መተኪያ የማይገኝላት ብርቅዬ አገራቸው ስለመሆኗ የኢፌድሪ ህገ መንግስት ዋስትና አሳጥቷቸዋል፡፡ ይሄ ትልቅ የአገርና የወገን ክህደት ነው፡፡ የስዩም መስፍንን የሰሞኑን የፌደራላዊ ሥርአት የጨበጣ ስብከት ያፋለሰውን ሀሳብ ለማስተካከል በጻፉት መጣጥፍ ገለታው ዘለቀ የተባሉ ምሁር እንዳሉት ህገ መንግሥቱ ወይም መንግስታዊ ስርአቱ ሲዋቀር አንደኛው ወገን ክልላዊ ማንነት በማራግብ ሌላው ደግሞ ብሔራዊ ማንነትን በማራገብ እንዲጠመድ አድርጎታል፡፡ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 39(1) መሠረት ለክልተኛው በፈለገው ጊዜ ፌደራሉን አፍርሶት እንዲሄድ በር ከፍቶ ስለተዋቀረ አንዱ የክልል መንግስት ባሻው ጊዜ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተሸርፎ ሊሄድ ይችላል፡፡ አንድ ሰው መሄድ ትችላለህ ስለተባለ አለመሄድን ይመርጣል የሚሉት ፈሊጥ የደናቁርቶች ሎጂክ ነው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያ ዛሬ እንደ ኮንትራት ቤት (ቦታ) ብትታይ ምን ይደንቃል? ስለዚህም የኢፌዲሪ ህገ ምንግስት አገር እስከ ማፍረስ የሚሄድ ችግር ፈጣሪ እንጂ ችግር ፈቺ አይደለም፡፡

ዜጎች በዚህና በመሰል አገራዊ ችግሮች ሲጠመዱ ግርግር ለሌባ ያመቻል እንዲሉ የኢፌዲሪ ህገ መንግስት ከጸደቀበት እስከ የኦሮሞ ሕዝብ ተቃውሞ ገኖ እስከወጣበት ህዳር 2008 እና ቀጥሎም የአማራው ተቃውሞ እስተቀጣጠለበት ጊዜ ድረስ ታስቦበት ለተደነገገበት ዓላማ ማለትም የህወሃትን ህልውና ያለተቀናቃኝ ለማራዘም፤ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነቱን በህግ ሽፋን እንደያዘ ለመቀጠል እንዲችል በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ በደንብ ሲጠቀምበት እንደቆየ የማይታበል እውነት ነው፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ የህገ መንግስቱ ተልእኮ መነሻና መድረሻ በብሔር ብሐረሰቦች መብት ማስከበር ሽፋን የአናሳውን ቡድን የህወሃትን ሥርአት ማራዘም ነው፡፡ በፌዴራል የመንግስት አወቃቀር እራስን በራስ ማስተዳደር ሽፋን ማእከላዊነትን ማጠናከር ነው፡፡ በስማቸው የሚነገደው የብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች ተወካይ እንግዶች የተረፋቸው በየዓመቱ ህዳር 29ን እየጠበቁ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ እንዳሉት እራቁታቸውን ጭምር እያዘለሏቸው ህገ መንግስቱ የጸደቀበትን ቀን በፌሽታ ማክበር ነው፡፡ ለነገሩ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም በክደት ቁልቁለት መጽሀፋቸው እንደተነተኑት ብዙዎቻችንን የሚአስፈራን አንቀጽ 39ም ቢሆን ግብታዊነት የተጫጫናቸውን ክልላዊ ብሔርተኞች በማማለል (በእንቁልልጮ) ከጎኑ አሰልፎና አገራዊ ብሔራዊነት የሚሰማቸውን ቅስም በመስበር በዚህ መሀከል ህወሃት አስታራቂ ዳኛ መስሎ የአናሳ ቡድን የበላይነቱን ለማደላደል ተጠቀመበት እንጂ ለመሆኑ እስካሁን ማን በዚህ አንቀጽ መሠረት ተገንጥሎ አገር ሆነ? የኤርትራም ከሆነ በጦር ሜዳ ያለቀ ጉዳይ ነው፡፡ አቶ መለስ ለኤርትራ መገንጠል እውቅና ለመስጠት የተሸቀዳደመው አንድም በውለታ ከፋይነት ሌላውም ሻቢያን ለማሞኘት ነበር፡፡

የሆነስ ሆነና ለመሆኑ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 39(1) በተፈቀደው መሰረት መገነጣጠሉ ቢተገበር ወይም ወያኔዎች ብቻ በግላቸው የ1968ቱ የፖለቲካ ፕሮገራማቸውን ከጣሉበት አንስተው እንደገና ቢገፉበት በብዙ ምክንያቶች ማን ነው ከሁሉም ቀድሞ የመረረ ፀፀት ሰለባ የሚሆነው? ቀድሞ ነገር የትኑም ያክል በኢንተርሃምዌ ቢአስፈራሩት፤ የቱንም ያክል በኃይል ተሰንጎ ቢያዝ ኢትዮጵያዊነቱን እንዲነጥቁት የትግራይ ሕዝብ የሚፈቅድላቸው አይመስለኝም፡፡ አሁን ያሉበት ደረጃ እስኪደርሱ በአንድ በኩል ከስርአቱ ተጠቃሚው፤ በሌላ ወገን እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ በፍራት ቆፈን መያዙ እንዳለ ሆኖ የትግሬ ሐዝብ በአደባባይ ሲሆን ጀግኖች ልጆቻችን ደርግን አሸንፈው (በሹክሹክታ የአፄ ዮሐንስን ዘውድ አስመልሰው) አገራችንን እየመሩ ነው በሚል ተደስቶም ተኩራርቶም ነውራቸውን (የወያኔዎቹን) ሁሉ እንዳላየ አይቶ ታግሶአቸው ይሆናል፡፡ ከዳሞትና እና ከአክሱም ስርወ መንግሥታት (በትንሹ ከ1000 ዓ.ዓ.) ጀምሮ የኢትዮጵያዊነት የእራስ ቅል ከሆኑት ብሔር ብሔረሰቦች መሀከል ከፍተኛውን ሚና ሲጫወት የኖረው የትግራይ ብሔር ብሔረሰብ ይሄን የመሰለ የአባቶቹን አኩሪ ታሪክና ውለታ ዘንግቶ፤ የራሱንና የልጆቹን ክብር አዋርዶ ኢትዮጵያዊነቱን ለድርድር የሚአቀርበው አይመስለኝም፡፡ ይሄን እውነታ ደግሞ ከማንኛችንም በላይ ወያኔዎቹ ያውቃሉ፡፡ የተበላሹት ትግሬዎች (ወያኔዎች) አሻፈረን ብለው ካረጉትና ጨዋው የትግራይ ህዝብ ካልተቃወማቸው ከዛሬው አብሮነታችን ጉርብትናችን ሳይሻለን አይቀርም የሚለው ሕዝብ እንዳይበዛ እሰጋለሁ፡፡ በዘረፋና በስርቆት በግል እና በእነ ኤፈርት ስም በወያኔዎችና በደጋፊዎቻቸው የተጋበሰ የአገር ሀብት ምንጩ ከደረቀና የገበያው መንገድ ከታጠረ ሁሉም ነገር የእንቧይ ካብ፤ የስርቆት ሀብቱም የጧት ጤዛ እንደሚሆን የዘመኑ ገዢዎቻችን የሚአጡት አይመስለኝም፡፡ ከሻቢያም ሳይማሩ አይቀርም፡፡ የቧሁን ወገን ለማስፈራራት እንጂ ያሉበት የቅምጥል ኑሮ ሳያሳሳቸው ቀርቶ አይደለም፡፡ በግንቦት1997 ብሔራዊ ምርጫ ህወሃት ከነአሽከር ድርጅቶቹ ሙልጭ ሲወጣ የተወሰኑ የ2ኛ ደረጃ አሽከር (አጋር) ድርጅቶቹን ኢህአዲግ (የህወሃት የአደባባይ ስም) ስልጣን ካጣ እንገነጠላለን እያሉ እንዲዝቱ ማድረጉ ትዝ ይለኛል፡፡ ዛሬም ጠቀመውም አልጠቀመው ህወሃት አጣብቂኝ ውስጥ በገባ ቁጥር ይችን ካርድ መምዘዙ አይቀሬ ነው፡፡ ሆኖም ዛሬ እንደ ትናንቱ ምን ያክሉ ሕዝብ በዚህ ሊሸበርላቸው እንደሚችል የሚያውቁት ወያኔዎች ብቻ ናቸው፡፡ ይልቁንስ የእኔ ስጋት ባለራዕዩ መሪያቸው ይል እንደነበረው መንገዱን ጨርቅ ያርግላችሁ ወይም በሊማሊሞ አቋርጡ ተብለው ማጠፊያው እንዳያጥራቸው ነው፡፡ ከሆነላቸውና ካዋጣቸው የመገንጠል ምህድስና ባለሟሎቹ እስካሁን ከጠቀስኳቸው በተጨማሪ እነ አቶ ስብሀት ነጋ፤ አርከበ ዕቁባይ፤ ጌታቸው አሰፋ፤ ሌሎችም አሉላቸው፡፡ የአገር ውስጥና የውጪውን ግር ግር ለመቀነስ ደግሞ ቀድሞውኑ ተስሎ የተዘጋጀው መበለቻ ካራው የኢፌዲሪ ህገ መንግስት ያለው በጃቸው ነው፡፡

ህወሃት ሆን ብሎ የሀገሪቱን ዕጣ ፋንታ ከህወሃት ህልውና ጋር በህግ አቆራኝቶታል እየተባለ በህግ ምሁራን ዘንድና በውጭ ታዛቢዎችም ወያኔ ክፉኛ የሚወቀስበት አንዱና ዋናው ይሄው እኛ በበላይነት የማንገዛት ኢትዮጵያ ዘጠኝ ቦታ ትበጣጠስ የሚለው ፍልስፍናው ነው፡፡ የህወሃት ሰዎች በዲሞክራሲ አግባብ በቁመታቸው ልክ ስልጣን መጋራትን እንደሞት ስለቆጠሩት ነው፡፡ ለዚህም ነው ኢህአዲግ ከሌለ ኢትዮጵያ ትበታተናለች እያሉ አፋቸውን ሞልተው የሚአስፈራሩን፡፡ እንደዚህ የዜጎችን ብሐራዊ ስሜት ገሎ የእነርሱን የአናሳ ቡድን ፍላጎታቸውንና ጥቅማቸውን እንዲአስጠብቅላቸው አርገው ቀድመው ያመቻቹት ህገ መንግስት ስለሆነ ነው ለምሳሌ ከአፋር፤ ከወሎና ከጎንደር በማን አለብኝነት ነጥቀው ወደትግራይ ያካለሏቸውን ለም መሬቶችና የጥንት ነዋሪ ሕዝቡን ፍላጎትና የማንነት ጥያቄ እየደፈጠጡ ግድ የለም ጣጣ አታብዙ፤ በህግ አግባብና በህገ መንግሥቱ ብቻ መፈታት አለበት እያሉ የሚመጻደቁት፡፡ ወልቃይቶችን ለትግራይ ክልላዊ ምንግሥት አመልክቱ እያሉ የሚአሾፉባቸው ለዚህ አንዱ ዓይነተኛ ማሳያ ነው፡፡ ለመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃማሪያም የወለቃይት ጉዳይ በህገ መንግስቱ መልስ የተሰጠበት ስለሆነ አንመለስበት ብሎ በአደባባይ ተናግሯል፡፡ ታዲያ የትግራይ ክልል ም/ቤት ከህገ መንግስቱ በላይ ሆኖ ነው ወይስ ጠቅላይ ሚኒስተሩ ፍትህ ከአጓደለ የትግራይ ክልል ም/ቤት ይግባኝ የመስማት ስልጣን አለው? ወይስ ጠቅላይ ሚኒስተሩ ቀድሞዉኑ የተናገረው ስለማያውቀው ነገር ነው? ከሆነስ ሁሉም መረጃ በእጁ ያለው ዶ/ር ደብረጽዮን ለምን አላረመውም? ጎበዝ ግራ የተጋባ ነገር እኮ ነው የገጠመን፡፡ አለቃና ምንዝሩ የጠፋበት ዘመነ ግሪንቢጥ!!!

ወልቃይት ጠገዴን በመሬቱ ለምነትና ብሎም መገነጣጠሉ ከመጣ ሁመራንና መተማን ጠቅሎ ወደወዳጅ አጎራባች አገሮች ለማጮለቂያ መስኮትነት ስለፈለገው ከወዲሁ ለመዘጋጀት በሚመስል ሁኔታ ዘመኑንና ኃይሉን ተማምኖ የነጠቃቸው የትግራይ ክልል እራሱ ሆኖ ሳለ ምን ሊአገኙ ነው ወልቃይቶች ለነጣቂው ጉልበተኛ መቀሌ ድረስ ሄደው አቤቱታ የሚአቀርቡት? የሚገርመው የትግራይ ክልል ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችል ቅድሚያ ታሳቢ ተደርጎ ሳይሆን አይቀርም ለፌዴሬሽን ም/ቤት ይግባኝ ማለት እንደሚችሉም ወልቃይቶች ከወዲሁ እየተነገራቸው ነው፡፡ ካስፈለገም ማንነታችሁ በሕዝበ ውሳኔ እልባት ያገኛል እየተባሉም ነው፡፡ ለወልቃይቶች ትግሬ ወይም አማራነታቸውን የህወሃት ካድሬዎች የሚሰበስቡት ሕዝብ እንደ ላቦራቶሪ ስነዘራቸውን መርምሮ ማንነታቸውንና ከማን ጋር መካለል እንዳለባቸው ሊወስንላቸው ነው፡፡ ከቀን በኋላ በወልቃይቶች መሬት ላይ ያሰፈራቸው በብዙ አሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች የወልቃይቶችን ማንነትና ወዴት መካለል እንደለባቸው ለመወሰን ድምጽ ይስጡ አይስጡ ለዲሲፕሊን ሲባል ይመስላል ህወሃት እስካሁን ያለው ነገር የለም፡፡ ሙያ በልብ ነው ነው ነገሩ፡፡

ልብ በሉ! በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 62(1) መሠረት የፌዴሬሽን ም/ቤት ህገ መንገሥቱን የመተርጎም ስልጣን አለው፡፡ ይህ ማለት ክፍተኛ ፍ/ቤትን ተክቶ የአገሪቱን ከፍተኛ የፍትህ ስልጣን ይዟል ማለት ነው፡፡ በተጨማሪ በአንቀጽ 62(3) በተሰጠው ስልጣን መሠረት በአንቀጽ 39(1) ላይ ተደነገገው የመገንጠል ጥያቄ ሲነሳ የፌዴሬሽን ም/ቤቱ የመወሰን ስልጣን አለው፡፡ ስለዚህ የፌዴሬሽን ም/ቤት ማንነትንም የመወሰን ትልቅ ስልጣን አለው ማለት ነው፡፡ በአንቀጽ 62(9) መሠረት ደግሞ ማንኛውም ክልል ህገ መንግስቱን በመጣስና ህገ ምንግስታዊ ስረአቱን አደጋ ላይ ይጥላል ብሎ ካመነበት የፌዴሬሽን ም/ቤት የፌዴራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ የማዘዝ ስልጣን ተሰቶታል፡፡ በዚህም በህገ መንግስቱ አንቀጽ 72(1) ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሚኒስተሮች ም/ቤት የተሰጠውን ስልጣን እና በአንቀጽ 74(1) የጠ/ሚኒስትሩን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥነትን ስልጣን ይቀናቀናል፡፡ ለማንኛውም ወልቃይቶች ከፍ ሲልም አማሮችም ሆኑ አፋሮች በትግራይ ክልል ተነጠቅን ስለሚሉት መሬት የፌዴሬሺን ም/ቤት አርፋችሁ ተቀመጡ ቢላቸውና አሻፈረን ቢሉ አንቀጽ 62(9) በሚፈቅደው መሰረት የፌዴራል መንግስቱን አዞ ልክ የማስገባት ስልጣን እንዳለው ከወዲሁ ይወቁት፡፡ ስለዚህ የፌዴሬሽን ም/ቤት ከህገ መንግስት መተርጎም ጀምሮ የብሄር ብሄረሰቦችን ማንነትና የአገር ብሄራዊ ደህንነት እስከማስጠበቅ የዘለቀ ተደራራቢና ከባድ ኃላፊነት ተሸክሟል፡፡ የፌዴሬሽን ም/ቤት ተቋም የተዋቀረው ደግሞ በህወሃት የመንግስት የፖለቲካ ሹመኞች ነው፡፡ የአገራችን ተጨባጭ እውነታ እንደሚአሳየው አንድ ሰው ፍጹም የሆነ ለህወሃት መንግሥት ፖለቲካ ታማኝነት ሳይኖረው ለዚህ ከፍተኛ የሹመት እርከን መብቃት የማይታሰብ ነው፡፡ ስለዚህ የፌዴራል መንግስቱን የማዘዝ ስልጣኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ህገ ምንግስትን ያክል ነገር የመተርጎምና የዜጎችን ማንነት እስከመወሰን የሚአስችል ከፍተኛው የፍትህ ሥራ በህወሃት ካድሬዎች አውጫጭኝ እየተተወነ ነው ማለት ነው፡፡ በነገራችን ላይ በአገራችን የፍትህ አካሉ ነፃና ገለልተኛ ነው የሚባለው ተራ ቧልት ስለመሆኑ ከዚህ በላይ ማስረጃ የሚአስፈልግ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ትልቅ ግንዛቤ ሊያዝበት የሚገባው ሌላው ቁም ነገር ለፌዴሬሽን ም/ቤት በተሰጠው ስልጣን ምክነያት በዓለማችን የአብዛኞቹ አገሮች ካላቸው ሦስቱ የመንግስት መዋቅሮች (ህግ አውጪ፤ ህግ አስፈጻሚ፤ ህግ ተርጓሚ) መሀከል በተለይ 3ኛው ማለትም የህግ ተርጓሚው አካል ሥልጣን ከላይ እንዳየነው በዋንኛነት ለፌዲሬሽን ም/ቤት ስለተሰጠ በዛሬዬቱ ኢትዮጵያ ህገ መንግሰት መሠረት ህግ ተርጓሚው ተቋም በፌደራል መንግስቱ መዋቅር ውስጥ እንዳለ የሚቆጠር አይደለም፡፡ በዚህም የኢፌዲሪ ህገ መንግስት የፌዴራል መንግስቱን መዋቅር አፍርሶታል፡፡

እነዚህንና መሰል የውጭ ትችቶችን ለማለዘብና በተለይም የለጋሽ አገሮችን አንጀት ለመብላት ይመስላል የዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ በህገ መንግስቱ ውስጥ እንዲካተት ተድርጓል፡፡ በፖለቲካ ብስለትና በዲሞክራሲያዊ አሠራር እድገት፤ በህግ የበላይነት መከበር፤ ሕዝባዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት አደረጃጀት፤ በኢኮኖሚ መበልጸግና በሪሶረስ ብቃት ከኢትዮጵያ እጅግ በጣም የሚበልጡ በርካታ አገሮች ይሄን ‹‹የሰው ልጅ ሊቀዳጀው የሚገባ ወርቃማው ህግ – A GOLDEN RULE MAN TO ACHIEVE›› እያለ የዓለም አቀፉ ህብረተሰብ የሚአሞካሸውን የዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ ህወሃት አውቆ በብልጣብልጥነት ይሁን ሳያውቅ በድፍረት በኢፌዲሬ ህገ መንግስቱ ውስጥ ማካተቱ ለምዕራቡ ዓለም ታዛቢዎች በጣም የሚገርም ሆኖባቸዋል፡፡ ድንጋጌውን ለመተግበር የሚጠይቀውን ብቃት፡ ዝግጁነትና ፍቃደኝነት ለማያውቀው ወገን በደፈናው ጮቤ የሚአስረግጥ ነው፡፡ የህውሃትን ባህሪና የመንግስቱን አቅም፤ የዲሞክራሲያዊ ተቋማትና ነፃ የሆነ የፍትህ ሰርአትና ሲቪል ማህበራት አለመኖር ለምናውቀው ለእኛ ለባለጉዳዮቹ ግን ከጌጥነት ያለፈ ትርጉም የለውም፡፡ በህወሃት ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ ተግባራዊነት ጉዳይ ላም አለኝ በሰማይ ነው፡፡ ለማንኛውም የኢፌዲሪ ህግ መንግስት እንደዚህ ከተኳኳለ በኋላ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦች፤ ሕዝቦች እንደዐይናቸው ብሌን እንዲጠብቁት ጥብቅ አደራ ተጥሎባቸዋል፡፡ ህወሃት በራሱ ግን ባዘቦቱ ቀን ከቁብ አይቆጥረውም፡፡ ሲሻውም ብዙ ጊዜ በፖለቲካ ደንገጡርነት ይጠቀምበታል፡፡ ታማኞቹም ሁሉ በየመንገዱ የየራሳቸውን ህግ እንዲአወጡ ፈቅዷል፡፡ በጭንቅ ጊዜ ግን ለዚሁ ህገ መንግሥት የሚሰጠው ክብርና ሞገስ ለየት ይላል፡፡ ከበድ ያለ የህወሀትን ጥፋት ለመሸፋፈን በተለይ ፍትህ ተነፍጎት ለተማረረው ተራው ሕዝብ ካለይ ከሰማየ ሰማያት በኪነጥበቡ የወረደ መለኮታዊ ፈውስ በሚመስል ሁኔታ እዚህም እዚያም ሲጠቀስለትና ሲሞካሽለት እንሰማለን፡፡ እነ ጄኔራል አበበም እያደረጉ ያሉት ይሄንኑ ነው፡፡ በነዚህና በሌሎችም በዚህ መጣጥፍ ያልተዳሰሱ የህግ ህፀፆች፤ የህግ አተረጓጎምና የሙያያው አጠቃቀም መሳከር፤ ከህግ የበላይነት አለመከበርና ከነባራዊ የሀገሪቱ ቀውስ አንጻር የኢፌዲሪ ህገ መንግስት በራሱ ችግር ፈጣሪ እንጂ በምንም መስፈርት ችግር ፈቺ የመሆን አቅም የለውም፡፡

ስለዚህም በአንቀጽ 9(3) ላይ በዚህ ህገ መንግስት ከተደነገገው ውጭ በማንኛቸውም አኳኋን የመንግሥት ስልጣን መያዝ የተከለከለ ነው የሚለውን ገደብ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማክበር አይገደድም፡፡ ግፍና ጭቆናው ከሚሸከመው በላይ ስለሆነበት አለመገደዱንም በኦሮሞና በአማራ ክልል፤ በደቡብ የኮንሶን ህበረተሰብ ጨምሮ በተግባር እያሳየ ነው፡፡ ይሄን ሁሉ የህወሃት ሲመች በተሳከረ የህግ ሽፋን ሆድ ሲአውቅ ዶሮ ማታ ድብብቆሽ፤ ሳይመች በጡንቻ አገዛዝ ስንረገጥ ለ25 ዓመት የከረምንበትን የግፍ አገዛዝ መጨረሻ የምናይበት ቀን በጣም የተቃረበ ይመስላል፡፡ ስለዚህም በአንድ በኩል የለውጡን መምጫ ጊዜ ለማሳጠር በሌላም በኩል በሂደቱ የሚከተለውን ጥፋት ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ባይቻልም ለመቀነስ ምንጊዜም በመረጃና በእውቀት ላይ የተመሠረተ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ የህወሃትን ሥርአት ለመለወጥ ተግቶ መሥራት አንድ ነገር ሆኖ ሳለ ከዛ በኋላ ስላለው አገራዊ ጉዳያችን ከወዲሁ መላ መምታት የግድ ይላል፡፡

ታላቅ ክብር በሕዝባዊ እንቢተኝነት እንቅስቃሴ ተሳትፏቸው ለተሰዉ፤ ያካል ጉዳት ለደረሰባቸውና በየእስር ቤቱ ስለእኛ ለሚሰቃዩ ጀግኖቻችን!!!

ፈጣሪያችን ፅናትና ብርታቱን ለቤተሰቦቻቸው ይስጥልን!!

Share

2 comments on “እውን የኢፊዲሪ ህገ መንግስት ችግር ፈቺ ነው?

 1. ከሩዋንዳ ጋር በተያያዘ ለግንዛቤ ያህል
  … there is no longer any ethnic discrimination as such in the country, like there
  was before the genocide of the Tutsis. This observation is the result of measures
  taken by the Rwandan government to eradicate ethnic segregation following the
  genocide. These measures consist of abolishing any mention of ethnicity in
  government-issued papers (identity card, passport, work papers …) that were used
  as identification tools for ethnic segregation.

  source: https://www.justice.gov/sites/default/files/eoir/legacy/2014/10/14/RWA102814.FE.pdf

 2. It is a woderful article. It is a good begining. It is a misnomer to say the least. There is no such thing as Ethiopian constitution at the moment. It is TPLF’ political programme. It was enacted to serve TPLF’ sinister plan.

Comments are closed