Logo

በዳያስፖራ ከትግራይ ተወላጆች የተሰጠ መግለጫ

October 7, 2016

ህውሓት/ኢህአዴግ ቢሾፍቱ ላይ ባደረሰው አሰቃቂ እልቂት በጣም አዝነናል
የሽግግር መንግስት በአፋጣኝ ይቋቋም!
የትግራይ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ህውሓት ባዘጋጀው ወጥመድ መግባት የለባቸውም

ባሳለፈነው እሁድ (22.01.2009) ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተሰባሰቡ ዜጎች በተገኙበት በቢሾፍቱ ከተማ በደማቅ ሁኔታ በመከበር ላይ በነበረው የኢሬቻ በዓል ላይ፣ ዜጎች በአፋኙ “መንግስት” ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ባዶ እጃቸውን አጣምረው በሰላማዊ መንገድ በማሰማታቸው ምክንያት፣ ሰብአዊነት በጎደለውና ጭካኔ በተሞላበት የህውሓት/ኢህአዴግ አሰቃቂ እርምጃ የብዙኃን ህይወት ተቀጥፏል። የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ም/ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ በቪኦኤ ቀርበው እንደገለፁት፣ የህውሓት/ኢህአዴግ ታጣቂዎች በፈፀሙት በዚህ አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ምክንያት 678 ዜጎች መሞታቸው ተረጋግጧል። ከ400 በላይ ሰዎች በሞትና በህይወት መካከል ይገኙ የነበረ ሲሆን ትክክለኛ የሟቾች ቁጥር ከዚህ በላይም ሊያሻቅብ እንደሚችል ይገመታል።

እኛ ስማችን ከታች የተዘረዘረው የትግራይ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን፣ ጭካኔ በተሞላበት በዚህ አረመኔያዊ ድርጊት በከፍተኛ ሁኔታ ማዘናችንን ለመግለፅ እንወዳለን። የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን ለመግለፅ ቃላት ያጥሩናል። ህውሓት/ኢህአዴግ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነቱን ለማስጠበቅ ሲል በዜጎች ላይ ያለውን አያያዝ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ በመሄድ፣ ዛሬ ህዝብን የሚያስተዳድር መንግስት ሳይሆን ህዝብን የሚያሸብር ወንበዴ መሆኑን በተግባር ያስመሰከረበት ዘግናኝ እልቂት ለማየት በቅተናል። በተለይ ደግሞ ይህን የሚያደርገው ህውሓት፣ የተለያዩ የብሔር ትንኮሳዎችን እያራገበና ከመቼውም በላይ በትግራይ ህዝብ ስም እየነገደና ጥላቻን እየበተነ ባለበት በዚህ ወቅት በመሆኑ ሀዘናችንን የከበደ አድርጎታል።

ቀደም ሲል ባወጣነው የጋራ መግለጫ እንደጠቀስነው፣ ህውሓት/ኢህአዴግ ከስልጣኑ ወርዶ የሽግግር መንግስት ባገሪቱ ካልተመሰረተ፣ ስልጣን ላይ በሚቆይበት እያንዳንዱ ተጨማሪ ቀን በዜጎች ላይ የባሰ እልቂትን እያስከተለና የአገሪቱን ህልውና ይበልጥ አደጋ ላይ እየጣለ መዝለቁ አይቀሬ ነው። ህውሓት/ኢህአዴግ ከህዝብ ራሱን ነጥሎ በትምክህትና በጉልበት ረግጦ ለመግዛት የሚሞክረው አካሄድ መቼም ቢሆን ሊሳካለት እንደማይችል ተረድቶ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም ቢሰራ ለሁሉም የሚበጅ ነውና በድጋሚ ለመምከርና ለመዘከር እንወዳለን።

ህውሓት/ኢህአዴግና የኢትዮጵያ ህዝብ የገቡበት ቅራኔ ከዚህ ብኋላ በሌላ በማንኛውም መንገድ ሊታረቅ የሚችል ቅራኔ ባለመሆኑ መፍትሔው የሽግግር መንግስት በመመስረት ህዝብ በነፃና ገለልተኛ ምርጫ ይሆነኛል የሚለውን ስርዓት እንዲመርጥ መንገድ ማመቻቸት ብቻና ብቻ ነው የሚለው እምነታችን አሁንም ፅኑ ነው።

ይህ እንዳለ ሆነ፣ ካለፈው ባህሪው ተነስተን ህውሓት/ኢህአዴግ በጎ ፈቃደኝነት ይኖረዋል ብለን ለማመን ስለምንቸገር፣ ይህን የማሳከት ሃላፊነቱና የዜግነት ግዴታው የተጣለው በመላው አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ላይ መሆኑን በፅኑ እናምናለን። በመሆኑም በመላ አገሪቱ ለነፃነቱ በጋራ እየተነሳ እንዳለው ህዝባችን፣ በተለያዩ የተቃውሚ ጎራ፣ የሲቪክ ተቋማት፣ የእምነት ተቋማት፣ እና የሙያ ማህበራት ስር የምንገኝ ኢትዮጵያውያን (በተለይም በመሪነት ደረጃ የተቀመጥን ዜጎች) ጊዜያዊ ልዩነታችንን ወደጎን ብለንና የጋራ መድረክ በማዘጋጀት ሁሉንም ያቀፈና ያሳተፈ የሽግግር መንግስት የመፍጠር ሂደት ከወዲሁ እንድንጀምር በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን ለማስተላለፍ እንወዳለን።

ከዚህ በተጓዳኝ ግልፅ ለማድረግ የምንፈልገው አንድ ነገር አለ። ይኸውም ህውሓት በትግራይ ህዝብ ስም የሚነግደውና በትግራይ ህዝብ ስም ጥላቻ የሚነዛው አልበቃ ብሎት፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ የትግራይ ተወላጆችን በማታለል ከቤት ንበረታቸው እያፈነቀለ ወደ ትግራይ ለማጓጓዝ እንቅስቃሴ መጀመሩን ከታማኝ ምንጮች ለመረዳት ችለናል። ይህንን ሴራውን ለማሳካት በትግራይ ተወላጆች ላይ ሃላፊነት የጎደለው እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ሁሉ ጥቆማዎች ደርሰውናል። ይህን የአቋም መግለጫ በምናዘጋጅበት ሰዓት አንዳንድ የትግራይ ተወላጆች ከኦሮሚያ ክልል መውጣት መጀመራቸውን አረጋግጠናል።

የትግራይ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን በህውሓት ፕሮፓጋንዳና ሽንገላ ተታለው ለዓመታት ጎጆ ቀልሰው ከኖሩበትና ጥረው ግረው ካፈሩት ቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው፣ ከኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው በመነጠል አፋኙና ነፍሰ በላው የህውሓት ቡድን ባዘጋጀላቸው ወጥመድ እንዳይገቡ ለማስጠንቀቅ እንወዳለን። ዛሬ ለትግራይ ህዝብ ከህውሓት በላይ ሌላ ጠላት እንደሌለው እያንዳንዱ የትግራይ ተወላጅ ሊያውቀው ይገባል። በህውሓት ስር ያሉ ወሮበላዎች ለትግራይ ህዝብ ቀርቶ አብረው ለታገሉ ጓዶቻቸውና ለቤተሰቦቻቸውም ምህረት የማያውቁ አረመኔዎች መሆናቸውን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊገነዘብ ይገባል።

በሁሉም የአገሪቱ ክፍል የምትኖሩ የትግራይ ተወላጅ ወገኖቻችን ህውሓት ባዘጋጀላችሁ ወጥመድ ሳትገቡና የህውሓትን ህልም አሳክታችሁ ራሳችሁን መቋጫ ለሌለው ሰቆቃ ሳትዳርጉ በፊት፣ በያላችሁበት ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገናችሁ ጋር በጋራ በመቆም ለነፃነታችሁ እንድትታገሉ በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን። ሁሉም ነፃ ካልወጣ ማንም ነፃ ሊወጣ እንደማይችል ተገንዝበን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ጎን በጋራ በመቆም ለነፃነት የሚደረገውን ትግል በያለንበት እንድንቀላቀል በድጋሚ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
በአገሪቱ በሁሉም አቅጣጫ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን፣ ለዘመናት በመካከላችሁ አብረዋችሁ የኖሩ የትግራይ ተወላጅ ወገኖቻችሁ ከማንኛውም ኃይል ሊደርስባቸው ከሚችል ጥቃት የመጠበቅ አደራ ተጥሎባችኋል። አብዛኛው የትግራይ ተወላጅ ዜጋ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወገኑ በአፈናና በጭቆና ስር የሚኖር ወንድማችሁ በመሆኑ፣ በተለይ ህውሓት ህልሙን ለማሳካት ሊፈፅምባቸው ከሚችል ደባ ለመጠበቅና ለነፃነት ትግሉ ከጎናችሁ ለማሰለፍ የዜግነት ግዴታችሁን እንደትወጡ እንማፀናለን።

በማጠቃለል በቢሾፍቱ በደረሰ አሰቃቂ እልቂት ልባችን የደማ መሆኑን በድጋሚ እየገለፅን፣ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸውና በአጠቃላይ ሀዘን ላይ ለተቀመጠው ኢትዮጵያዊ ወገናቸው እግዚአብሔር መፅናናቱን እንዲሰጥልን፣ የሙታንን ነፍስ በሰላም እንዲያሳርፍልን እንመኛለን። እግዚአብሔር በምህረቱ ይጎብኘን፤ አገራችንንም ይባርክልን። አሜን!
የስም ዝርዝር

1. ህይወት ተሰማ
2. ሓረገወይኒ:ገ/ኢየሱስ
3. ሕሉፍ በርሀ
4. ሜሮን አብርሃ
5. ሲራክ ኣማረ
6. ስልጣን ኣለነ
7. በላቸው ለማ
8. በየነ ገብራይ
9. ብሩክ እንግዳ
10. ተስፋዬ መሓሪ
11. ተስፋይ ኣፅብሃ
12. ታደሰ በርሀ
13. ታደሰ ገብረእዝጊ
14. ነጋሲ በየነ
15. ናትናኤል ኣስመላሽ
16. አሰር አሉላ
17. አባይ ኪሮስ
18. ዶክተር ኣረጋዊ በርሀ
19. ኣብራሃ በላይ
20. ኣብርሃም ኀይለ
21. ኤልያስ በየነ
22. ኪዳነ ኃይሌ
23. ኪዳነማርያም ፀጋይ
24. ካሕሳይ በርሀ
25. ዘልኣለም ንርአ
26. ዮሃንስ በርሀ
27. ዮሴፍ ብርሃነ
28. ዮናስ ሓጎስ
29. ዮናስ መብራህቱ
30. ደስታ ኣየነው
31. ገብረኪዳን ዳዊት
32. ዶክተር ግደይ ኣሰፋ
33. ጥላሁን አረፈ
34. የማነ ምትኩ
35. ሸዋዬ ሽፈራው
36. ደረጀ ገ/ሂወት

ማሳሰቢያ!

ከኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው መረጃ በማቀበልና አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን በማስተባበር እየተባበሩን ያሉ የትግራይ ተወላጆች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን፣ በርካቶች ስማቸው እዚህ እንዲካተት የፈቀዱ ቢሆንም ሊደርስባቸው ከሚችል አደጋ ለመጠንቀቅ ስንል በሚስጥር ለመጠበቅ ተገደናል።

አስተባባሪዎቹ

Share