Logo

ኢህአዴግ: ማደስ ወይስ መታደስ?

October 31, 2016

ከ 6 ሳምንት በፊት የቀድሞው የኦሮምያ ፕሬዝዳንት አቶ አባዱላ ገመዳ ፤ የቀድሞው ስኳር ኮርፖሬሽን ሀላፊ አቶ አባይ ፀሀዬ፤ አቶ በረከት ስምዖን ከዶክተር ካሱ ጋር ተሰልፈው “ፋታ ስጡን እንጂ” እንታደሳለን የሚለውን ቃለ ምልልስ ሰጥተዋል። አቶ አባዱላ ስለ ሙስና፤ አቶ አባይ ደግሞ 77 ቢሊየን ብር በጀት ተሰጥቷቸው ከመሩት የስካር ኮርፖሬሽን ለምን አንድ ኪሎ ስኳር እንዳላቀመሱን ሳይነግሩን ፤ ስለ ወጣቶች ስራ ማጣት በመቆርቆር ጊዜ ስጡን ስሊ ይሁን ብለን ነበር።

እንታደሳለን ከተባለ ይሄው ሁለት ወር አለፈ። ተሀድሶ ይጀመራል ብለን ስንጠብቅ የዩኒቨርስቲ መምህራን ማንቃት፤ ማስተማር ተጀመረ። ይሄንን ያየ ኢህአዴግ የወሰነው እራስን መርምሮ ለመቀየር ነበር ወይንስ ህዝብን ለመቀየር የሚለውን ጥያቄ አስነሳ። ይህም ሙከራ ውጤታማ አልሆነም። ምክንቱም፥ብዙዎች ኢህአዴግ መታደስ አይፈልግም፤ ብንናገርም በተዘጋጀልን ወጥመድ አስገብቶ ለማጥቃት ነው እንጂ የለውጥ ፍላጎት የለውም ብለው ያመኑ ምሁራን ዝምታን መረጡ። በእርግጥም በድፍረት ሀሳባቸውን የገለጹትን እንደ የአንቦ ዩኒቨርስቲ መምህር አቶ ስዩም ተሾመ ወደ እስር መወርወራቸው በቅርብ ተሰማ።

ዛሬ ደግሞ ህገመንግስቱን የሚገድብ የጊዚያዊ ጊዜ አዋጅ መታወጁንና፤ ህገመንግስቱ አጎናጸፋቸው የተባሉትም መብቶች መታገዳቸው ታወጀ። አዋጁ ከዚህ በፊት ተከብረው የነበሩና አሁን የነጠቃቸው መብቶች ባይኖሩም ህገ መንቱ የሰጠኝ መብት ይከበርልኝ ለሚል ህዝብ ይህቺኑም መብት መገደብና ወደወታደራዊ አስተዳደር መጓዝ ተጀመረ።በአዲሱ አዋጅ “የሲቢል አስተዳደሩን ልፍስፍስ ነው፤ የጀርባ አጥንት የለውም” በማለት በአደባባይ ይተቹ የነበሩትን በኢታማጆር ሹሙ ከአቶ ሀይለማሪይም ወሳኝነቱን የተቀበሉበት የብልጠት መንገድ ይመስለኛል። ይህ ዝርዝር ጽሁፍ የሚጠይቅ ስለሆነ ለግዜው አልፈውናመለወጥ ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን ለማመላከት እሞክራለሁ።

የነ አባ ዱላና ካሳ ተክለብርሀን ውይይቶች እንዴት እንለወጥ?፤ ምን እንለውጥ? ብለው ጠይቀው ቢሆን ኖሮ ብዙ ምክር በተገኘ፤ ብዘም ድጋፍ በጎረፈ ነበር። አላማው ግን እራስን መለወጥ ሳይሆን ህዝብን መለወጥ ነበር። የሚያሳዝነው ደግሞ ለመለወጫ የተጠቀሙበት ያው በቀን ለ24 ሰአታት እና ለ25 ዓመታት ተብሎ፤ ተዘፍኖ እዚህ ያደርሰንን በመድገም የህዝብ እምነት እናስለውጣለን ተብሎ መታስቡ ነው። ይህ የብልጣ ብልጥ መንገድ በጣም ውድ የሆነውንጊዜ ከማባከንና የህዝቡንም ብሶት ከማዳፈንና ባልታሰበና ባልተጠበቀ ጊዜ እንዲፈነዳ ከማድረግ ውጪ ኢህአዴግን አልጠቅምም። በእርግጥ ኢህአዴግ መለወጥ የሚፈልግ ከሆነ መለወጥ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አንድ ሁለት ብዮ ሏመላክት።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር ተሀድሶ ማለት ከጋራ ላይ የሚወርድን ናዳ እንደማምለጥ ነው ብለው ነበር በማለት አቶ በረከት ጽፈዋል። ከናዳው ለማምለጥ ፍጥነት ወሳኝ ነው። ከናዳ የሚሸሸው ናዳው ከጅምሩ ቢደፈጥጠው ወይንም ሮጦ ሮጦ ከከለላው ለመድረስ 1ሜትር ሲቀረው ናዳው ቢደፈጥጠው ልዩነት የለውም። የሞተው በፍጥነት ባለመሮጡ ነው። ኢህአዴግ ከተደፈጠጠ በግብጽ ወይንም በሻቢያ ተንኮል ሳይሆን የተሰጠውን እድልተጠቅሞ መሮጥ ባለ መቻሉ ነው።

የኢሀዴግ ዋነኛ ችግሩ እራሱን እንደ የገዢ መደብ ማሰብ መጀመሩ ነው። የገዢ መደብ ደግሞ ይናገራል እንጂ አያዳምጥም፤ ይገስጻል እንጂ አይገሰጽም፤ ይጠይቃል እንጂ አይጠየቅም፤ ይለውጣል እንጂ አይለወጥም። የገዢ መደብ ከገባሩ ግብር እንጂ ሀሳብ አይቀበልም። ገባሩ መገበር ፤ ደጅ መጥናት፤ የእጅ መንሻ ማቅረብ፤ ማሞገስ እና መታዘዝ ነው። ከዚህ በላይ ካሰበ በራሱ ሳይሆን በርኩስ መናፍስት ወይንም በታሪካዊ ጠለቶቻችን ተጽእኖ ስር ነው ያለው ተብሎ ይመከራል፣ ይቀጣል፣ ይታረማል እንጂ ያስባል ወይንምከፍቶታል አይባልም።

ተሀድሶ ለማድረግ ብዙ መድከምን አያሻም። ህዝብንና፤ ምሁራንን ሰብስቦ ድክመታችን ምንድነው? ምን ብንቀይር የተሻለ ስራ መስራት እንችላለን? የህዝብንስ ጥያቄ በምን መንገድ መመለስ እንችላለን ብሎ መጠየቅ ብቻ በቂ ነበር።

ዘመናዊ ትምህርት ባልተማረ ህብረተሰብ ውስጥ የተወለዱት የ1960ዎቹ የግራ ክንፍ ተማሪ ችግር የስነልቦና ቀውስ ነበረባቸው። ገና 8ኛ ክፍልን አልፎ ዊንጌት የገባ ተማሪ ሁሉ “ሊህቃን” ነኝ፤ ሁሉን አውቃለሁ ብሎ የሚያስብ ትውልድ ነበር። ሰፊው ህዝብ ደግሞ ምንም የማያውቅ፤ መሀይም ፤ መንቃት ፤መደራጀት፤ ሞግዚት የሚያስፈልገው ተከታይ ነው ብሎ የሚያምኑ ነበረ። ስለዚህ ህዝብን የመስማት፤ የማድመጥ ነገር በመዝገበ ቃላታቸው ውስጥ አልነበረም። ይህ ባይሆንማ ኖሮ “የነጻ አውጪ” የሚል ትልቅ ስያሜ ለራሳቸው ባልሰጡ ነበር። ገና ያኔ በደንብ ጠንቅቀው ማንበብና መጻፍ በማይችሉበት ዘመንቀርቶ ዛሬም ከአርባ አመት ቦሃላ በአንባቢነትና በሊህቃን ተርታ የሚያሰልፍ እውቀት ያለው አንድ በመሀከላቸው የለም።

ይህ ለህዝብ ያለ ትልቅ ንቀት የ10ኛ እና የ1ኛ አመት የዩኒቨርድቲ ተማሪ እራስን ነጻ አውጪ የሚል ስያሜ ባልሰጠ። እኔ አውቃልሀለሁ የሚል አባዜ ባይኖር ሰለጠነው አለም የሌበር ፓርቲ፤ዲሞክራቲክ ፓርቲ፤ ሶሻሊስት ፓርቲ ወይንም ሪፖብሊካን በተባለ ነበር። ህዝብ አያውቅም፤ ሞግዚት ያሻዋል የሚለው እምነት ለገዢነት ፍላጎት፤ ለስልጣን ጥማት፤ የገዢነቱ ተራ ይገባኛል ለሚል ፍላጎት መሸፋፋኛ “የነጻ አውጪነት” ካባ ሆነ።

ለዚህ ነው ኢህአዴግ መለወጥ መታደስ የማይችለው። ገዢነት ስሜትና የግራ አክራሪነት እብሪት ተጨምሮ እስከሁን ለውጥ አልተጀመረም። ምክንያቱም ለውጥ ማለት ገዢነትን ትቶ አገልጋይ መሆን መሆን ማለት ነው። ስለዚህ መታደስ ማለት ኢህአዴግ ካልገባው አንድ፤ሁለት ብለን እንጠቁመው።

1. እውነት እንነጋገር ካልን ስልጣንን ሁሉም የሚፈልጋት ጥቅም ስለምታመጣ ነው።ስልጣንንስ የአፍሪካ መሪዎች ብዙ የግብር ከፋይን ሀብት አፍስሰው “ጃስ” ሲሉት የሚናከስ ሰራዊት የሚያደራጁት ስልጣን የጥቅም ቁልፍ ስለሆነ ነው። በሙስናን መዋጋት ማለት ጥቅምን መተው ማለት ነው፡፡ ጥቅሙን ኣሳልፎ መስጠት ግን ቀላል አይደለም። ይህንን ለማድረግ የተዘጋጀ ፓለቲከኛ ካለ እዚህ አለሁ ይበል፡፡ የአንድ ቀበሌ በጀት በአመት በሚያስከፍሉ ትምህርት ቤቶች 5 ልጅ እያስተማሩ ሙስናን ለመዋጋት ቆርጠናል ማለት እንዴት ይሆናል። መታደስ ማለት ከግል ት/ቤት ልጅን አውጥቶ በደሞዝ መኖርና በመንግስት ት/ቤት ልጆችን ማስተማር ማለት ነው። ይህንን ማነው ሊቀበል የተዘጋጀ። መለወጥ ማለት እንደ ህዝቡ በደሞዝ ጦም በያይነቱ፣ ሽሮ በልቶ ውድኪ ሳይሆን ጉሽ ጠላ ጠጥቶ ተመስገን ማለት ነው። ማንኛው የኢህአዴግ ባለስልጣን ነው በገጸ በሪከት ከባለሀብት የሚጎርፈውን ውስኪና ሻምፓኝ ይቅር ብሎ አገርኛውን በደሞዝ ጥትት አድርጎ ተመስገን ለማለት የተዝጋጀው ባለስልጣን። መታደስ ማለት በታይላንድ ባለ ሀብት አስከፍሎ ሆስፒታል ሄዶ መተኛት ሳይሆን እንደ ህዝቡ በወጌሻም፤ በጥቁር አንበሳም ሆስፒታል በገቢ ልክ መታከም ማለት ነው። መታደስ ማለት የመንግስት መሬት በራስ፤ በሚስት፤በዘመድ አዝማድ መዝረፍ አይደለም። መታደስ ማለት ወገንን ጠቅሞ ወገን የሌለውን እድል መዝጋትን መተው ማለት ነው። በመንደር፤ በጎሳ፤ በቋንቋ፤ በዝምድና አድልዎ በማድረግ የራስን ሰው በህዝብ ንብረት ማብቃት ማበልጸግ ማለት አይደለም። ይህንን እርግፍ አለማድጎ ትቶ፤ ሁሉንም አትዮጵያዊ በእኩልነት ማለት ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ የተዘጋጀው የኢህአዴግ መሪ ማንኛው ነው? ሁሉም ሌላውን ገፍቶ እራስን የጥቅም ባህር ውስጥ ለመዋኘት ተብሎነው ይህ ሁሉ ማማጥ የቀጠለው። አሀንም በጥቅም የተሳሰሩትን ሙሰኞች ሳይሆን ተባባሪ ያልሆኑትን ነው ሙሰኞቹ መንጥረው የሚያባርሩዋቸው።

2.  መታደስ ማለት በረጂም ጠረጴዛ ተቀምጦ፤ የእልፍኝ አስከልካይ ሳይታጠሩ፤ የሉም፤ ስብሰባ ላይ ናቸው፤ ሳያስብሉ ቢሮን ለህዝብ ክፍት አድርጎ፡፡ በገዢነት እብሪት ሳይሆን በአገልጋይነት መንፈስ ከወንበር ላይ ብድግ ብሎ ባለጉዳይን በፈገግታ ተቀብሎ ማስተናገድ፡፡ ጉዳዩን በጽሞና አዳምጦ፤ ጥቅምን፡ ጎሳን፡ የፓለቲካ ወገንተኛነትን መመዘኛ ሳያደርጉ ውሳኔ መስጠትን፡ ፍትህን ማደላደል ማለት ነው፡፡

3. መታደስ ማለት ጠረጴዛን እየደበደቡ ጣትን እያወራጩ፡ አይንን እያጉረጠረጡ ህዝብን ማስፈራሩ፤ ማሸማቀቅ፤ አርፈህ ብትገዛ ይሻልሀል፤ ነጻ አውጥቼሀለሁ፤ ኮብልስቶን አንጥፌልህ፤ እንዴት ብትንቀኝ ነ የተዳከምኩ፤ ጉልበቴ የደከመ፤ ክንዴ የዛለ፤ ጅራፌ የተበጠሰ መስሎህ ነው ብሎ ማሰብን ማቆምና፡ማስፈራራት ሳይሆን ህዝብን የስልጣን ምንጭ፤ ቀጣሪና አሰናባች መሆኑን መቀበልና ማክበር ማለት ነው፡፡ ሕዝብን ካልመረጥከኝ በግሌ የማዘውና “ጃስ” ስለው የሚናከስ፤ የሚዘነጥል፤ ፍዳህን የሚያስቆጥርህ ሰራዊት አለኝ ብሎ አለማሰብና ካልወደድከኝ ገለል እልልሀለሁ ብሎ ማሰብ ማለት ነው።

4. መታደስ ማለት አስቀድሞ ጥያቀየ በታደላቸው፤ ተሸማቀውና ተሸቆጥቁጠው በሚያድሩ ጋዜጠኞች ተጠይቆ ለአንድ ሰአት አዋቂ መስሎ ለመታየት መሞከር ሳይሆን እራሱን አስተምሮ፤ አንብቦ፤ ተዘጋጅቶ ደጋፊና ተቃዋሚ ሳያሉ ሁሉም ይጠይቀኝ ብሎ ጋዜጠኞችን መጋፈጥ፡ ያልተዘጋጁበትንም ጥያቄ መቀበል፤ የሚያውቁትን መመለስ፤ የማያውቁትን አላውቅም ማለት። ሀሳብን በሀሳብ በማሸነፍ እንጂ ከተፈቀደልህ ውጪ ከጠይቅክ ከቃለመጠይቁ ቦሃላ አገኝሀለሁ ጃስ ስለው የሚያስር፤ ጃስ ስለው የሚከስስ አቃቤ ህግ፤ ጃስ ስለው የሚፈርድ፤ ወደ ቂሊንጦ፡ ዝዋይ፡ ሸዋ ሮቢት የሚሸኝ ታዛዥ አለኝ ብሎ ማስፈራራት መተው ማለት ነው።

5. መታደስ ማለት ይህንን ይህንን ያላሟላ ህዝብ ህጋዊ አይደለም፤ ቅጥረኛ ነው፤ ጸረ ሰላም፤ ጠባብ ነው፤ ትምክህተኛ ነው፡ ብሎ ህዝብን አለማሸማቅ፡፡ በገዢነት ማማ ላይ ተቀምጦ እኔ ሳልፈቅድልህ ለምን ጠየቅክኝ፤ ቅሬታህን ለምን ገለጽክ፡፡ እንዴት ተደፈርኩ፤ እቺ ጥሬ ካደረች አትቆረጠምም፤ አታውቅም እንዴ ፤ የማዘው፤ የምቀልበው፤ ለምን ብሎ የማይጠይቀኝ ሰራዊት አለኝ፡ እሱን ልኬ ደም እንባ አስለቅስሀለሁ፡ ልጅህን ነጥቄ መቅ አስለብስሀለሁ፡ ሀገርህ ላይ ፈንጂ ቀብሬ በታትንሃለሁ፡ ማለት ሳይሆን የመረጥከኝ ላገለግልህ ነበር፡ ግልጋሎቴ በቂ ካልሆነ፤ ለውጥ ከፈለክ ገለል እልልሀለሁ፤ በፈቃዴ ለቅልሀለሁ፤ የሚመስልህን መርጠህ መተዳደር ትችላለህ ብሎ መቀበል ማለት ነው፡፡

6. መታደስ ማለት ከሚወዱትም ከማይወዱትም፤ ከሚደግፍም ከሚቃወምም፤ ከሚመርቀንም ከሚረግምም ጋር እከል ነኝ፤ በዚህ ሀገር በመወለዱ ብቻ የዚህ ሀገር ጉዳይ ያገባዋል፤ መጠየቅ፤ መቃወም፤ መጻፍ፤ መሰለፍ፤ መወያየት መብቱ ነው፤ እጁን አጣምሮ፤ ደረቱ ላይ መፈክር ተነቅሶ፤ ኮፍይ አሰርቶ መሔድ መብቱ መሆኑን መቀበል፤ በዱላ በጥይት ሳይሆን በውይይት ለመፍታት፤ በክብ ጠረጴዛ በገዢነት ስሜት ሳይሆን በእኩልነት ለማሳመን ማለት ነው፡፡

7. መታደስ ማለት እራስን ከሁሉ በላይ አዋቂ፤ ተቆርቋሪ፤ ሀሳቢ አድርጎ በማስብ፤ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል በሚል መርህ፤ እኔ ከስልጣን ከወረድኩ ሀገር ትጠፋለች ፤ ጸሀይ ትጠልቃለች፤ ዘር ይጠፋል ብሎ አለማሰብና፤ ለ4 ሺህ ዘመን አብሮ የኖረ ህዝብን ከኔ ክላሽንኮብ በስተቀር ተቻችሎ አይኖርም፤ እኔና እኔ ብቻ ነኝ ለዚህ ህዝብ ያለሁት። ከኔ የተሻለ ኢትዮጵያዊ ሊኖር አይችልም፤ ብሎ ማሰብን መተው። ህዝብና ሀገር ከኔ በፊትም ነበረ ከኔም ቦኃላ ይኖራል፤ ህዝብም በደጉም በክፉውም አብሮ ኖርዋል፤ ወደፊትም ይኖራል፡፡ ከኔ የተሻለ ትውልድ ይወለዳል የሚለውን መቀበልና እራስን እንደ ስዮመ እግዚአብሄር ሳያዩ ህዝብን እንደ አላዋቂ ሳይቆጥሩ የህዝብን ውሳነየ መቀበል ነው፡፡

8. ከሁሉም በላይ ደግሞ መታደስ ማለት እራስን እንደ ገዢ አለማሰብና ለህዝብ እንደ ተገዢ አለየማት ነው፡፡ ይህንን ማነው ሊቀበል የተዘጋጀ።

Addisu W/Mariam
Addisuwmariam@gmail.com

 

Share

One comment on “ኢህአዴግ: ማደስ ወይስ መታደስ?

Comments are closed