Logo

ድርድሩ የተሳካ እንዲሆን ሀሉም ወገን የበኩሉን ይወጣ! (ከ6ቱ ፓርቲዎች በጋራ የተሰጠ መግለጫ )

February 7, 2017

Press release by Ethiopian opposition parties

የዛሬ 22 ዓመት የመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርዓት ህገ-መንግስታዊ ዕውቅና ማግኘቱ የሚታወቅ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ዴሞክራሲያዊ ስርዓትና የመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ አስታሰሰብ በሃገራችን እንዲገነባ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥረት ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ሆኖምበሃገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ከመጠናከርና ከመጎልበት ይልቅ ዓምባገነናዊነት እየነገሰ፣ መድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርዓት ከመስፋፋትናለፓርቲዎች ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ይልቅ ወደ ኋላ እየተጎተተና እየተዳከመ ይገኛል፡፡ ይባስ ብሎም ገዥው ፓርቲ ከዴሞክራሲ መገለጫዎች ዋነኛው የሆነውን የምርጫ ስርዓት የስልጣን እድሜ ማራዘሚያ በማድረግ ከላይ እስከታች የሚገኙትን የምክር ቤት መቀመጫዎች ፍጹም ኢ- ዱሞክራሲያዊ በሆነ ሁኔታ ጠቅልሎ ወስዷል፡፡ በዚህም ሳያፍር̈አውራ ፓርቲ ነኝ̈ በማለት የምርጫ ስርዓቱን ሲያቃልለው ይታያል ፡፡ ይሄም ከልክ ያለፈ የገዥው ፓርቲ ትዕቢት፣ የስልጣን ስግብግብነትና አምባገነናዊ ባህሪ አሁን ሃገራችን የምትገኝበት አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንድትገኝ አድርጓታል፡፡

ባለፈው አንድ አመት በሀገራችን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ተቀስቅሶ የነበረው ህዝባዊ አመጽ ያስተላለፈው መልዕክት ስርዓቱ ከልክ ያለፈ አምባገነናዊ ስርዓት እንደሆነ ነው፡፡ በዚህ የህዝብ ተቃውሞም ውድ የሆነው የሰው ህይወት ጠፍቷል፣ ብዙዎች ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፣ የሀገርና የህዝብ ሃብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፣ ህዝቡ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ተንቀሳቅሶ መስራት ከማይችልበት ደረጃ ላይ ከመደረሱ በተጨማሪ ሀገራችን ከፍተኛ የህልውና ስጋት ውስጥ እንድትወድቅ አድርጓታል፡፡

ይሄም በሃገሪቷና ህዝቧ ላይ ያንዣበበውን አደጋ በትኩረት ስንከታተል የነበርን ፓርቲዎች ችግሩ ተባብሶ የሃገራችን ህልውና አደጋ ውስጥ እንዳይወድቅ ያለንን ስጋት በተደጋጋሚ ስናሰማ ቆይተናል፡፡ይሄም የህልውና ስጋት እንዳይባባስ ለሚመለከተው ሁል መልዕክት አስተላልፈናል አደጋውንም ጠቁመናል፡፡ በተለይ መንግስት ተቃውሞውን በሃይል ለማፈን የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አጥብቀን ኮንነናል፡፡ ለዚህ ዓይነቱ መጠነ ሰፊ የህዝብ ተቃውሞ መነሻው ህዝቡ ተደራጅቶ ድምጹን የሚያሰማበት መንገድ በመታጣቱና የፓለቲካ ምህዳሩ ከመጥበቡ የተነሳ መሆኑን ባገኘነው መድረክ ሁሉ አስገንዝበናል፡፡ ይሄ መጠነ ሰፊ የፖለቲካ ቀውስ ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ሊፈታ የሚችለውምገዥው ፓርቲና መንግስት ለድርድርና ለውይይት በሩን ከፍት ሲያደርግ ብቻ መሆኑን በተደጋጋሚ ተናግረናል፡፡

ገዥው ፓርቲ ከረፈደም ቢሆን በአሁኑ ሰዓት ለድርድር ዝግጁ መሆኑን አስታውቆ ጥሪ አስተላልፎልናል ፡፡ ይሄየገዥው ፓርቲና የመንግስት ዝግጁነት የድርድሩ ሂደትና ውጤት ወደ ፊት የሚታይ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በጎ ጅምር ነው ብለን እናምናለን፡፡
ጥር 10 ቀን 2009 ዓ.ም ገዥው ፓርቲ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ባደረገው ጥሪ መሰረት የድርድር ቅድመ ውይይት ተካሂዷል፡፡በውይይቱም ላይ ፓርቲዎች ተገናኝተን በአራት ነጥቦች ላይ አማራጭ ሃሳባችንን እንድናቀርብ ከስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ በዚህም መሰረት በቅድመ ድርድር ውይይቱ ላይ ከተሳተፍነው ፓርቲዎች መካከል መኢአድ፣ ኢዴፓ፣ ሰማያዊ፣ መኢዴፓ፣ ኢራፓና ኢብአፓ ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች በጋራ ተወያይተንና ተስማምተን ድርድሩ የሚካሄድበትን የስነ-ስርዓት አማራጭ ሃሳብ ለመንግስት በጋራ አስገብተናል፡፡

እኛ ሰነዱን በጋራ ያቀረብን 6ቱ ተደራዳሪ ፓርቲዎችድርድሮችና ውይይቶች የአገርና የህዝብን ጥቅም በሚያስቀድም ቅንነትና ቁርጠኝነት ከተካሄዱ ምትክ በሌለው ሁኔታ ውጤታማ ይሆናሉ የሚል እምነት አለን፡፡

ከወቅቱም ድርድር እኛ 6ቱ ተደራዳሪ ፓርቲዎች የምንጠብቀው አንድን የፖለቲካ ሃይል አሸናፊ፣ሌላውን ተሸናፊ የሚያደርግ ድርድር ሳይሆን አገራችን ከገባችበት የህልውና ስጋትና የፖለቲካ ቀውስ ተላቃ ህዝብ በምርጫ ካርድ ያልፈለገውን ከስልጣን የሚያወርድበትና የፈለገውን ወደ ስልጣን የሚያወጣበት ውጤት ማግኘት ነው፡፡ይህ ሁኔታም እንዲፈጠር የድርሻችንን በሀቀኝነትና በቁርጠኝነት ለመወጣት ያለንን ዝግጁነት እንገልጻለን፡፡ይሄ ድርድርም ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ

1ኛ- መንግስት ድርድሮችን እንደከዚህ ቀደሙ ለሚዲያ ፍጆታነት፣ ለግዜ መግዣና ለማስመሰል ከማድረግ ተቆጥቦ ከድርድሩ የሚገኘው ውጤት ሀገርና ህዝብን እንደሚጠቅም አምኖ እንዲንቀሳቀስ

2ኛ- ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተበታተነና ባልተቀናጀ ሁኔታ የምናደርገው ድርድር እንደማይጠቅም ተረድተን በጋራ ተመካክረን ድርድሩን ለማድረግ እንድንችል ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

3ኛ- መንግስት ድርድሩ ውጤታማ እንዲሆን ቁርጠኝነት ካለው ድርድሩ ላይተሳታፊ ለሆኑ የተቃዋሚ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮችና የፓርቲ አባላት ላይ ያልተገባ ወከባና እንግልት እናዳይኖር ደህንነታቸውን የመጠበቅ ሃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ፣

4ኛ- ህዝቡ ይሄ ድርድር የተሳካ ውጤት እንዲያስመዘግብናተደራዳሪ ፓርቲዎች ድርድሩን በግልጽነትና በሃቀኝነት መንፈስ እንዲያካሂዱ በጎ የሆነ ተጽዕኖውን በማሳረፍ የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ፣

5ኛ- በሃገር ውስጥናበውጭ የሚታተሙ የግል የህትመት ውጤቶች፣ በሃገር ውስጥና በውጭ ተደራሽነት ያላቸው የመገናኛ ብዙሃን፣ የፖለቲካ አክቲቪስቶች፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ፣ የሃይማኖት ተቋማትና የሀገራ ሽማግሌዎች የድርድሩ ሂደትና ውጤት የተሳካ እንዲሆን የድርሻችሁን እንድትወጡ፣

6ኛ- በውጭ ሃገር የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ድርድሩ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣና ገዥው ፓርቲና መንግስት በግልጽና በሃቀኝነት በመደራደር ሃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ገንቢና በጎ የሆነ ፖለቲካዊ ተጽዕኖአችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

ጥር 29 2009 ዓ.ም
አዲስ አበባ

ምንጭ ፌስቡክ
Share

One comment on “ድርድሩ የተሳካ እንዲሆን ሀሉም ወገን የበኩሉን ይወጣ! (ከ6ቱ ፓርቲዎች በጋራ የተሰጠ መግለጫ )

  1. “በውጭ ሃገር የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ድርድሩ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣና ገዥው ፓርቲና መንግስት በግልጽና በሃቀኝነት በመደራደር ሃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ገንቢና በጎ የሆነ ፖለቲካዊ ተጽዕኖአችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን”

    ጥሪው ተገቢ ነው። ይሁን እንጂ በውጭ ያሉ አንዳንድ ሰዎች ድርድሩ እንዳይሳካ ቢያንስ በቀን ሁለቴ እየጸለዩ እንደሆነ ከሚያወጧቸው ጽሁፎች መታዘብ ይቻላል። ለምሳሌ – “እመኑኝ፤ ነጻ ሜዲያ ነኝ ” የሚለው ኢትዮሜዲያ፤ የስድስቱን ተቃዋሚዎች መግለጫ ሳያወጣ ነገር ግን የተቃዋሚዎቹን ድርድር የሚንኳስሡትን ጽሁፍ ግን እየመረጠ ሲለጣጥፍ አያለሁ።
    በርግጥ ጥቂት በብእር ስም የሚጽፉ ግለሰቦች አብዛኛውን በውጭ የሚኖር ህዝብ ባይወክሉም፤ እነሱ የማየመሩት እና ሀገርቤት የሚደረግ እንቅስቃሴ ካለ እንዲሰተጓጎል የማይቧጥጡት ገደል የለም።
    ስለዚህ አገርቤት ያሉ ተቃዋሚዎች በውጭ ሀገር የሚነዙ መጥፎ ፕሮፓጋንዳም የመመከት አቅማቸውንም በማጎልበት ብዙሃኑ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለመድረስ ጥረት ማድረግ ያለባቸው ይመስለኛል።

Comments are closed