Logo

በደቡብ ክልል ምክር ቤት የሚገኙ የዎላይታ ሕዝብ ተወካዮች እራሳቸውን ከምክር ቤት አባልነት አገለሉ።

Wolaita
June 15, 2020

በደቡብ ክልል ምክር ቤት የሚገኙ የዎላይታ ሕዝብ ተወካዮች እራሳቸውን ከምክር ቤት አባልነት አገለሉ። የብሔሩ ተወካይ አባላት ራሳቸውን ከምክር ቤት አባልነት ያገለሉት የዎላይታ ሕዝብ እራሱን በራሱ ለማስተዳደር ያስችለኛል በሚል ላቀረበው በክልል የመደራጀት ጥያቄ ምክር ቤቱ ተገቢውን ምላሽ አልሰጠም በሚል ነው ተብሏል ።

የወላይታ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አበበች እራሾ ዛሬ ለዶቼ ቨለ ( DW ) በስልክ አንዳሉት የወላይታ ብሔር በክልል የመደራጀት ጥያቄ በኢፌድሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 47 መሠረት በዞኑ ምክር ቤት ፀድቆ በ2011 ዓ.ም ለክልሉ ምክር ቤት በማቅረብ ሕዝበ ዉሳኔ እንዲደራጅለት ጠይቆ ነበር ፡፡

ዋና አፈ ጉባኤዋ በማያያዝም «የደቡብ ክልሉ ምክር ቤት ጥያቄው በቀረበ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከምርጫ ቦርድ ጋር በመነጋገር ሕዝበ ውሳኔ ማደራጀት ሲገባው ምንም ምላሽ አልሰጠም። በ2011 ዓ.ም ባካሄዳቸዉ ሁለት መደበኛ ጉባኤዎችም ጉዳዩ በአጀንዳነት እንዲቀርብ በጽሑፍም ሆነ የጉባኤው አባላት በሆኑ የብሔሩ ተወካዮች ተጠይቆ ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል ። ምክር ቤቱ ሕዝባችንና የወከላቸውን ድምፅ ለማዳመጥ ፍላጎት የለውም ። ይህም ብሔሩን የወከሉ አባላት በምክር ቤቱ ላይ ያላቸው እምነት እየተሟጠጠና እየተሸረሸረ እንዲመጣ አድርጎታል» ብለዋል ።

«በመሆኑም ሀሳባችን ካልተደመጠ በምክር ቤት አባልነት መቀጠል ለእኛም ሆነ ለሕዝባችን ጥቅም የለውም » ያሉት ዋና አፈ ጉባኤዋ በዚህ መነሻም በደቡብ ክልል ምክር ቤት የሚገኙ 38 የብሔሩ ተወካዮች ከዛሬ ጀምሮ እራሳቸውን ከምክር ቤት አባልነት ማግለላቸውን አስታውቀዋል ።

አባላቱ አራሳቸውን ከምክር ቤቱ ስለማግለላቸው በፊርማቸው ያረጋገጡበትን ደብዳቤ ለደቡብ ክልል ምክር ቤት ፤ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት ፤ ለክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት እና ለክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ማስገባታቸውንና ሰሞኑን በሚደረገዉ ክልላዊ ጉባኤ ላይም እንደማይገኙ ዋና አፈ ጉባኤዋ ተናግረዋል።

በደቡብ ክልል ቀደም ሲል የሲዳማ ዞን በክልል ለመደራጀት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን ተከትሎ 11 ዞኖች የክልልነት ጥያቄ በማቅረብ በየምክር ቤቶቻቸው ማጽደቃቸው ይታወሳል ።

ከየአቅጣጫው «በክልል እንደራጅ» የሚል ጥያቄና ግፊት የበረታበት የጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ መንግሥት ነባሩን የደቡብ ክልል አራት ቦታ በመክፈል መልሶ ለማደራጀት ያስችላል ያለውን የመነሻ ምክረ ሀሳብ በማዘጋጀት ከክልሉ ፖለቲከኞችና ከአገር ሽማግሌዎች ጋር ተከታታይ ውይይቶችን እያደረገ እንደሚገኝ ይታወቃል።

ይሁንእንጂ የሰላም አምባሳደር በተባለው ኮሚቴ የቀረበው ይህ ምክረ ሀሳብ በወላይታ እና በጉራጌ ዞን መስተዳድሮችና በብሔሮቹ የለውጥ አራማጅ ቡድኖች በኩል ተቃውሞ እየገጠመው ነው። የየዞኖቹ መስተዳድሮች ሕዝቡ ጥያቄ ያቀረበው እራሱን ችሎ በክልል ለመደራጀት መሆኑን በመጥቀስ ምላሹ በዚሁ መንገድ ሊፈጸም ይገባል ሲሉ ሰሞኑን በየፊናቸው ባወጡት መግለጫ ማስታወቃቸውን ከሀዋሳ ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ በላከልን ዜና ጠቅሷል።
Source DW Amharic

Share