Logo

“ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌቱን እያካሄደች ድርድሩን ትቀጥላለች” የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች

The Grand Ethiopian Renaissance Dam (GERD)
June 21, 2020

በህዳሴው ግድብ ዙርያ ለሚነሱት ውዝግቦች ዋነኛ መፍትሄ የተጀመረውን የሶስትዮሽ ድርድር ማስቀጠል መሆኑን እንደምታምንና ኢትዮጵያ ውይይቶችን ሳታቋርጥ የግድቡን ግንባታም ሆነ የውሃ ሙሌት እንደምትቀጥል በሶስትዮሹ ድርድር የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን ተደራዳሪዎች ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ተናግረዋል።
የህዳሴ ግድብ የብሔራዊ ኤክስፐርቶች ፓናል ሰብሳቢና በሕዳሴው ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር ኮሚቴ አባል ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው እንደሚገልጹት፤ ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌቱን እንዳታደርግ የሚያግዳት ስምምነትም ሆነ ህግ የለም። በመሆኑም በቀጣዩ ሐምሌ ወር ውሃውን እየሞላች በቀሪ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማካሄዷን ትቀጥላለች። በዚህ መሰረት በመጀመሪያ ዓመት 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ይሞላል፤ በሁለተኛው ዓመት ደግሞ በአጠቃላይ 18 ነጥብ 4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ይደርሳል። እንዲህ እንዲህ እያለች ኢትዮጵያ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃውን እንደምትሞላ ግልጽ አድርጋለች።

እንደ ኢንጂነር ጌዲዮን ገለጻ፤ አሁን ላይ የሚደረጉ ውይይቶች በድርቅ ወቅት የውሃ አጠቃቀም ምን ይሁን በሚለው ጉዳይ ላይ ነው። በዚህ ረገድ ስለውሃ ሙሌቱ ስምምነት ሳይደረስ ኢትዮጵያ ውሃ መሙላት አትችልም የሚል ይዘት ያላቸው መረጃዎችን ግብጽም ሆነ አሜሪካ ማውጣታቸው የውይይቱን ይዘት የማይወክሉ እና የተሳሳቱ መሆናቸው መታወቅ አለበት። ኢትዮጵያ ውሃ ሙሌቱ መብቷ መሆኑን ብታውቅም መፍትሄዎችን በውይይት እና በድርድር ማምጣት ይቻላል የሚል እምነት በመያዟ እስከመጨረሻው ድረስ ውይይቶችን ለማካሄድ ወስናለች።
ሱዳኖችም በተመሳሳይ ጉዳዩን በውይይት መፍታት እንደሚቻል እንደሚያምኑ የገለጹት ኢንጂነር ጌዲዮን፤ ግብጽ ግን ኢትዮጵያ ከግድቡ ውሃ ሙሌት ጋር በተያያዘ ጽኑ አቋም በመያዟ ግብጽ ከድርድሩ ልትወጣ እንደምትችል የሚጠቁሙ አንዳንድ መረጃዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። እንደ እርሳቸው፤ ይሁንና ግብጽ ውይይቱን ወደጎን ብላ ከውይይቱ ብትወጣ የእራሷ ውሳኔ ነው የሚሆነው፤ ይህን ካደረገችም ስህተት እንደሰራች ነው የሚቆጠረው። ምክንያቱም በኢትዮጵያ በኩል የውሃ ሙሌቱን የሚያግድ
ዓለም አቀፍ ህግም ሆነ የመርህ ስምምነት ስለሌለ ሥራው እየተከወነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ አብሮ እየተነጋገሩ መቀጠሉን ኢትዮጵያ ትገፋበታለች። እናም ኢትዮጵያ ድርድሩ ላይ ቆይታ የግድቡንም ግንባታ ሳታቋርጥ ውሃውን የመሙላት ተግባሯ አይቀሬ ነው ሲሉ ኢንጅነር ጌዲዮን አመልክተዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ሀብት መምህርና የህዳሴው ግድብ የቴክኒክ ቡድን አባል ዶክተር በለጠ ብርሃኑ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ አቋም ምንጊዜም ቋሚ መሆኑን ይገልጻሉ። እንደእርሳቸው፤ ውሃ ሙሌቱን የሚያግድ ህግ ባለመኖሩ ውይይቱን እያካሄደች ግንባታውንም ታከናውናለች። ግብጽ ግን አላስፈላጊ ትርክቶችን እያመጣች ውሳኔ ለማግኘት ከምትሞክር ይልቅ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውይይት ማድረግ የሚበጃት ቢሆንም የግብጽ ተደራዳሪዎች የውሃ ሙሌቱን ለማስተጓጎል እየሄዱበት ያለው መንገድ የሚያዋጣ አይደለም። ኢትዮጵያ ግን ማንንም ሳይጎዳ ውሃውን የመሙላት ሙሉ መብት እንዳላት ብታውቅም ጉዳዩን በትብብር መከወን ይገባል ከሚል ሰላማዊ አቋም በመነሳት
የውይይት እድሉን ሰጥታቸዋለች።
እንደ ዶክተር በለጠ ከሆነ፤ ግብጾች ጉዳዩን ከሙያዊ ሥራ ይልቅ ወደፖለቲካ ይዘት እየወሰዱት ነው፤ ከሰሞኑ በተደረገው የቪዲዮ ውይይት ላይ የየሀገራቱ መሪዎች መነጋገር እንዳለባቸው የሚል አቋም አንጸባርቀዋል። ኢትዮጵያ ውሃ መሙላቷ ግብጾችም ሆነ ሱዳኖች ላይ ጉዳት እንደማያደርስ ቢያውቁትም ጥቅማቸውን ከፍ ለማድረግ ሲባል ግን የማይጨበጥ ችግር ያነሳሉ። በመሰረቱ የውሃ ሙሌቱ የግንባታው አካል እንጂ የድርድሩ አካል ባለመሆኑ የትኛውንም ዓለም አቀፍህግና የተፋሰስ ሀገራትን መብት አይጋፋም። ጎረቤት ሀገራትን ያማከለ የትብብር ሥራ ለማከናወን ውይይት ተመረጠ እንጂ ኢትዮጵያ ውሃ መሙላትም ሆነ ከግድቡ መጠቀም የሚከለክላት ምንም ህግ የለም። ይህንን ግብጾችም ሆኑ አሜሪካኖች ቢያውቁትም ጉዳዩን ያላገናዘበ የተሳሳተ መረጃ እያወጡ ነው። የአሜሪካ መንግሥት ችግሩን መፍታት ሲያቅተው መግለጫ ያወጣ ሲሆን ኢትዮጵያ ግን ውይይቱን እያካሄደች ግድቡን ከጫፍ እንደምታደርስ ጽኑ አቋም አላት። በኢትዮጵያ በኩልም ውይይቱ ሳይቋረጥ የውሃ ሙሌቱን የምትገፋበት ይሆናል ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውሃ መሀንዲስና የህዳሴው ግድብ ተደራዳሪ ቡድን አባል ዶክተር ይልማ ስለሺ በበኩላቸው እንደሚገልጹት፤ በውሃ ሙሌቱ ላይ ግብጾች ይጎዳናል የሚሉት ውሸታቸውን ነው እንጂ በአብዛኛው ተስማምተዋል። ይሁንና የግብጽ ተደራዳሪዎች የኢትዮጵያን የወደፊት የውሃ ጥቅም ለመግታት ነው ፍላጎታቸው። የውሃ ሙሌቱ ላይ በአብዛኛው ቀደም ብሎ ስምምነት ተደርጓል፤ ይህን ግን ግብጾች እንደመያዣ ለመጠቀም የቀየሱት ስልት ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ አካሄዳቸው ስህተት መሆኑን በግልጽ ተናግራለች።
እንደ ዶክተር ይልማ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ ውሃ ውን ስተሞላም ሆነ ስትጠቀም ሌሎች ላይ ጉዳት አለማድረሱን መከታተል እንጂ ስለሥራው የሀገራቱን ፍቃድ የመጠየቅ ግዴታ የለባትም ። ስለዚህ በአባይ ወንዝ ከሚያልፈው ውሃ ውስጥ አስር በመቶውን ማለትም 4ነጥብ 9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃን በመጀመሪያ የመያዝ መብት አላት፤ ለዚህ ደግሞ ፍቃድ አያስፈልግም። ኢትዮጵያ ውሃ ሙሌቱንም ሆነ ቀሪ የግንባታ ሥራዎችን መቀጠል ነው ያላት አማራጭ የሚሉት ዶክተር ይልማ፤ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ህጎችን ጠብቃ ውሃ መሙላቷን ትቀጥልበታለች ሲሉ አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2012

Share