Logo

የጄኔራል ሰዓረ መኮንን ጉዳይ

General Seare Mekonnen
June 27, 2020

በሙሉሸዋ አንዳርጋቸው

ጄኔራል ሰዓረ “ፕሮፌሽናል ወታደር አገር እንጂ ብሄር የለውም” በሚል ተገቢና ወቅቱን ያገናዘበ መሪ ቃል፣ የሕወሃትን የበላይነት ለመጠበቅ ተብሎ ለ27 ዓመት የተገነባውን የትህነግን አጋዚ ጦር በዘዴ፣ ካለምንም ኮሽታ፣ በልበ ሙሉነት ከፍተኛ ታማኝ  የሕወኃት ጄኔራል መኮንኖችን ከጦሩ ከፍተኛ አመራር ውስጥ በመላ ዞር በማድረግ የኢትዮጵያንና  ህዝቧን ታደገ ። ሕወኃት ጄኔራል ሳሞራን መፈንቅለ መንግስት አድርግ ብሎ እንደቀረበው፣ በጄኔራል ሳዕረ ዘመን ሕወኃት መፈንቅለ መንግስት አድርጉ ብሎ እንኳን እንዳይጠይቅ በሩ ጥርቅም ተደርጎ በሳዕረ እስከ ወዲያኛው ተዘጋበት።
ሕወሃቶች ጨርቃቸውን ጥለው ሊያብዱ ደረሱ። የዛሬን አያድርገውና በጊዜው የሕወኃት ዋና ዋና ተከፋይ  ፕሮፓጋንዲስቶች ጄኔራል ሳዕረ ላይ የልተቋረጠ  የተቀነባበረ የጥላቻ ዘመቻ በማህበራዊ ሚዲያ ከፈቱበት። ዳንኤል ብርሃኔ ሳዕረን “ከሃዲ” ብሎ ነጋ ጠባ መክሰሱ ሳይበቃው፣ የሳዕረ አባት አቶ መኮንን የወሎ አማራ መሆናቸውን፣ ትግራይ የኢትዮጵያ ወታደር ሆነው ሄደተው የሳዕረን እናት ከትግራይ አግብተው ሳዕረን እንደወለዱ፣ እውነተኛ ስሙም አሸናፊ መኮንን፣ የበረሃ ስሙ ደግሞ ሳዕረ መኮንን መሆኑን አብራራልን። ድሮም “ከወለዬ ከአማራ ከከሃዲነት” ውጪ ምን ይጠበቃል ብሎ በጎሳ ፓለቲካ  የተበላሸውን አይምሮውን ከፍቶ አሳየን።
ለነገሩ ሳዕረ “ከዳም” ከተባለ፣ “የከዳው” ሕወኃትን እንጂ ኢትዮጵያን አገሩን አይደለም። ሕወኃትን መክዳት ደግሞ በኢትዮጵያ ህዝብ ዓይን ያሸልማል።  ይሄ ድርጊት ደግሞ እንደ ሳዕረ አይነት አባቱ የኢትዮጵያ ወታደር ሆኖ ካገለገለ ልጅ የሚጠበቅ ነበር።
ሳዕረ የኢትዮጵያ ኩራት ሆኖ፣ ስለ ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያ ብሎ ፕሮፌሽናል ወታደር አገር እንጂ ብሄር የለውም በማለት ኢትዮጵያን በዛ ክፉ ቀን የታደገ፣ ወርቃማ የታሪክ አሻራውን አሳርፎ ያሸለበ የኢትዮጵያ ጀግና ነው። እንደ ማናቸውም የኢትዮጵያ ጀግኖች የሳዕረ ስም ከመቃብር በላይ ሆኖ ይኖራል።
ስለ ሳዕረ ይሄን ያህል ካልኩኝ፣ ለዛሬው ጽሁፌ ምክንያት ወደሆነኝ የሳዕረ ሚስት የኮሎኔል ጽጌ ከኦ ኤም ኤን ጋር ወደ አደረገችው ቃለመጠይቅ ልመልሳችሁ።
በመጀመርያ ደረጃ ሳዕረ የሞተው ለኢትዮጵያ ብሎ ስለሆነ፣ ኮሎኔል ጽጌ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ( ኦሮሞው፣ ጉራጌው፣…) ለምን ፍትህ ለሳዕረ ብለው ሲጮሁ አይታይም ብላ ጠይቃለች። እኔ ኦሮሞ ነኝ፣ እኔ ሲዳማ ነኝ፣ …. የሚል በጎሳ መነጽር ሁሉን ነገር የሚያይ ዘመኑን የማይመጥን ሰው የሳዕረ ለኢትዮጵያ ብሎ መሞት እንደማያሳስበው ለኮሎኔል ጽጌ በልበ ሙሉነት መናገር ይቻላል።
ይሄን ጥያቄውን የኢትዮጵያ ጉዳይ ብቻ የሚያገባቸው፣ እራሳቸውን ከጎሳ በላይ ማየት የሚችሉ ብሄረ ኢትዮጵያኖች ናቸው የኮሎኔል  ጽጌ ተማጽኖ ከልብ ወስደው ከጎኗ የሚቆሙት። ስለዚህ ወደፊት ኮሎኔል ጵጌ ጥሪ ስታቀርብ ለኢትዮጵያ ህዝብ ቢሆን ተገቢ ይመስለኛል።
ትህነግም ሳዕረን” ከሃዲ” ብለው ነጋ ጠባ ሲሰድቡት እንዳልነበረ፣  ጄኔራል ሳዕረ ሲሞት እንደለመደባቸው የፓለቲካ  ትርፍ በሳዕረ ሞት ለማግኘት ብለው ተጣድፈው መቀሌ ወስደው ቀብረውታል። እንድ እንደ እቴጌ ጣይቱ ብልህ ኢትዮጵያዊ ቢኖር ኖሮ፣ ንጉስ ጦናን እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ንጉስ ከኢትዮጵያ ከነገስታት ጋር አብሮ አዲስ አበባ ይቀበራል እንጂ፣ ወላይታ አይቀበርም ብለው ከነገስታት ጎን አዲስ አበባ እንዳስቀበሩት፣ ሳዕረም ለኢትዮጵያ ብሎ ስለሞተ በአዲስ አበባ በኢትዮጵያኖች ሁሉ ዋና ከተማ መቀበር ነበረበት። የግል ምርጫዋን እያከበርኩኝ፣  ኮሎኔል ጽጌ በዚህ ነገር ብታስብበት ጥሩ ይመስለኛል። የኢትዮጵያ ጀግኖችና ባለውለታዎች መቀበርያ አዲስ አበባ ስላሴ ቤተክርስትያን ነው።
ኮሎኔል ጽጌ ጄኔራል ሳዕረንና ገዛኢን ለሁለት ደቂቃ ያክል በረንዳ ትቼያቸው ወደ ሳሎን ስገባ የተኩስ ድምጽ ሰምቼ ስወጣ፣ ሳዕረም ገዛኢም በጥይት ወንበራቸው ላይ እንደተቀመጡ ተመተው ደረስኩኝ። ጠባቂው ወታደር  አስር አለቃ መሳፍንትም መሬት ላይ አጠገባቸው ስለተኛ የሞተ መስሎኝ ነበር። ሳዕረ አለመሞቱን አውቀን አምቡላንስ ለመጥራትና ሌሎቹን የጥበቃ አባላት ለመጥራት ስንሯሯጥ፣ አስር አለቃ መሳፍንት ተነስቶ እየሮጠ ወደ ሳሎን ሲገባ አይቼው፣ ጥበቃውን ጠርቼ መሳፍንት ሳሎን ሮጦ ገባ ብዬ ነግሬው፣ መሳፍንት ከሳሎን፣ ጥበቃው ከበረንዳ መታኮስ ጀመሩ አለች። ከዚያም መሳፍንት እግሩን ተመቶ ተያዘ። እግሩን መመታቱን ግን በአይኔ አላየሁም። ያቆሰለው ጠባቂ እንደነገረኝ ነው አለች።
ሶስት ተገቢ ጥያቄዎችን ከኮሎኔል ጽጌ ቃለመጠይቅ ተንተርሼ ላንሳ፤
1. ከእኔ በስተቀር መሳፍንትን ያቆሰለውን ጠባቂ ጨምሮ፣ መሳፍንት እሮጦ ወደ ሳሎን እኪገባ ድረስ ማንም ድርጊቱን ያየ ስለሌለ፣ ለምንድነው የእኔ ቃል እንደ ብቸኛ በእይኑ በብሌኑ ወንጀሉን እንዳየ ዋና ምስክር ተድርጌ ያልተወሰድኩት ብላ ጠይቃለች። አቃቤ ህግ ኮሎኔል ጽጌን እንደ ዋና ምስክር ለምን እንዳልወሰደ የህግ አንቀጽ ጠቅሶ ህጋዊ ማብራሪያ በጉዳዩ በአስቸኳይ ሊሰጥ ይገባል።
2. ኮሎኔል ጽጌ የሳዕረ የፍርድ ሂደት እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከፌስ ቡክና ከሚዲያ ነው የምሰማው አለች። ትልቅ ጥፋት ነው። ትክክል አይደለም። ሊታረም ይገባል። በሰለጠኑት አገሮች ከሚዲያ በፊት ለvictim’s ቤተሰቦች ጉዳዩ የት እንደደረሰ ከስር ከስሩ የሚገልጽላቸው ቋሚ የፓሊስ liaison officer አለ። እኛ አገር ይሄ የህግ አሰራር ከሌለ፣ ፓሊስ ቢያሰብበት በጣም ጥሩ ነው።
በተለይ ደግሞ  ወንጀሉ እንደዚህ ትልቅ ከአገር ህልውና ጋር ሲያያዝ ቤተሰብን ጥርቅም አድርጎ መዝጋት ትክክል አይደለም። አቃቤ ህግንና ፓሊስን የፍትህ ክትትሉ የት እንደደረሰ ግለጹልኝ ብዬ ብጠይቅ፣ ከሰው አልቆጥር ብለው አልሰማ አሉኝ ትላለች። በፍትህ ሂደቱ ተስፋ በቆረጠ አንደበት፣ ከእንግዲህ የእግዚአብሔርን ፍርድን ብቻ ነው የምጠብቀው አለች።
3. ኮሎኔል ጽጌ ጄኔራል አሳምነው የበላዮች ሳይሳተፉበት ሳዕረ ሞተ የሚለውን አልቀበልም ትላለች። ጣቷን ወደ ላይ ትጠቁማለች።
በምዕራቡ አለም በፍርድ ቤት የተያዘን ወንጀል በሚዲያ መዘገብ ወንጀል ነው። The right to fair trial ጋር ይጣረሳል ተብሎ ስለሚፈራ። የኢትዮጵያ ህግ በጉዳዩ ምን እንደሚል አላውቅም። የኢትዮጵያ ህግን የማይጋጭ ከሆነና፣ በፍርድ ቤት ንቀት (በcontempt of court)  የማያስከስስ ከሆነ፣ የኢትዮጵያ አጀንዳ የሚያራምዱ ሚዲያዎች ኮሎኔል ጽጌን ጥሪ ተቀብለው የአቅማቸውን ያህል  እንዲረዷት ጥሪዬን አቀርባለሁ።
ፍትህ ለጄኔራል ሳዕረ!
Share