Logo

አቶ ልደቱን በማሰር ሃሳብን ማሸነፍ አይቻልም!

July 29, 2020

ከኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የተሰጠ መግለጫ

ኢዴፓ ላለፉት 20 ዓመታት በአገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ እና ስር የሰደደው የጥላቻ፣ የበቀል እና የሴራ አሮጌ የፖለቲካ ባህል በሃሳብ፣ በውይይትና በድርድር ላይ በተመሰረተ የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል እንዲተካ የራሱን ወሳኝ ሚና ሲጫወት ቆይቷል፡፡ በዚህ በፅናት ከሚያራምደው የምክንያታዊ ፖለቲካ አስተሳሰቡ የተነሳ በገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ እና በአገር ውስጥ እና በውጭ በሚገኙ ፅንፈኛ የፖለቲካ ሃይሎች የአሉባልታ እና የጥላቻ ፖለቲካ ሰለባ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ሆኖም ፓርቲያችን ለነዚህ አሉባልታዎች እና የጥላቻ ፖለቲካ አራማጆች እጅ ሳይሰጥ፣ ከምክንያታዊ የፖለቲካ አስተሳሰቡ ፈቀቅ ሳይል የያዘውን ዋነኛ ሰላማዊ የትግል መስመር ሳይለቅ እዚህ ደርሷል፡፡ ፓርቲያችን ትናንትም ሆነ ዛሬ በሃይል እና በአመፅ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሊገነባ አይችልም ከሚለው ከመርህ የመነጨ አስተሳሰቡም ለአፍታም ወደ ኋላ አፈግፍጎ አያውቅም፡፡ የመጣውን መከራ እና ስቃይ በፅናት ይቀበላል እንጂ አሁንም ቢሆን የኃይል እና የአመፅ ድርጊቶችን ያወግዛል፡፡ ይሄ በሰላማዊ ትግል ላይ ያለን አቋም እና መርህም ሲሞቀን የምናወልቀው ሲበርደን የምንለብሰው ጃኬት አይደለም፡፡
ፓርቲያችን ኢዴፓ ከለውጡ በፊት ባሉት ሶስት ዓመታትም ሆነ ከለውጡ በኋላ ባሉት ሁለት ዓመታት የተለያዩ የህልውና ፈተናዎች እየተጋረጡበት እነሱን እያለፈ ህልውናውን ጠብቆ እዚህ ደርሷል፡፡ ነገር ግን ኢዴፓን የማዳከም እና የማጥፋት ዘመቻ አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ የአሁንን የኢዴፓ ፈተና ለየት የሚያደርገው ጥቃቱ የመንግስት ጠበቃ በሆኑ ተቃዋሚ ተብዬዎች፣ የድል አጥቢያ አክቲቪስቶች እና በመንግስት ጥምረት በስውር ሳይሆን በአደባባይ የሚፈፀም ደባ መሆኑ ነው፡፡ በተለይ በመንግስት በኩል ኢዴፓ ከሌሎች ሁለት ፓርቲዎች ጋር በአብሮነት መንቀሳቀስ በጀመረበት አጭር ግዜ ውስጥ የፈጠረው ጥምረት ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን ሲያይ ስልታዊ በሆነ መንገድ ፓርቲውን ለማዳከም ጥረት አድርጓል፡፡
ኢዴፓ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት የለውጡን ጉዞ እየገመገመ ለአገራችን ዘላቂ ሰላም እና ዴሞክራሲ ግንባታ የሚጠቅሙ ጠንካራ ሃሳቦችንና አማራጮችን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ በተለይም በነሃሴ 2012 ዓ.ም ይደረጋል ተብሎ መርሃ ግብር ተይዞለት የነበረው አገር አቀፍ ምርጫ መካሄድን አስከትሎ የያዘው አቋም እና ያቀረበው አማራጭ ዋነኛው ነው፡፡ ኢዴፓ ይሄ ምርጫ ዘላቂ ወደ ሆነ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚያሸጋግር ምርጫ ሳይሆን ካለፉት 5 ምርጫዎች የተሻለ እንደማይሆንና ምን አልባትም አገራችንን ወደ ባሰ ብጥብጥ እና ቀውስ የሚወስድ በታሪክ ለመጨረሻ ጊዜ የምናደርገው ምርጫ ነው የሚሆነው በሚል ምርጫው ቢያንስ ለሁለት ዓመት እንዲራዘም እና ሁሉን አሳታፊ የሆነ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም የሚል አቋም ሲያራምድ ቆይቷል፡፡ በዚህ ጊዜ በመንግስትና በአንዳንድ ተቃዋሚዎች ሳይቀር ምርጫውን በምንም ተአምር ከመስከረም 30 በኋላ ለአንድም ቀንም ቢሆን ለማራዘም የሚያስችል ሁኔታ የለም በማለት ሲቃወሙ ከርመዋል፡፡
ነገር ግን የኮሮና ቫይረስ መከሰትን ተከትሎ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ሆነ መንግስት በፊት የነበራቸውን አቋም በመቀየር ምርጫውን ማካሄድ እንደማይቻል ከገለፁ በኋላ ግልፅ የሆነ ህገ-መንግስታዊ ቀውስ በመፈጠሩ ከዚህ ህገ-ህገመንግስታዊ ቀውስ እንዴት እንውጣ? አገራችንን እስከ ቀጣዩ ምርጫ እንዴት እናስቀጥል? የሚለው ጥያቄ ሌላ መልስ የሚፈልግ የፖለቲካ አጀንዳ ሆኖ ብቅ አለ፡፡ በአንድ በኩል የመንግስትን የስልጣን እድሜ ከመስከረም 30 በኋላ ሊያስቀጥል የሚችል ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌ ባለመኖሩ፣ በሌላ በኩል በአገሪቱ ያለው የፖለቲካ ውጥረት ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ በመሆኑ ፓርቲያችን ከዚህ በፊት ሲያራምድ የቆየውን የሽግግር መንግስት ጥያቄ የበለጠ እንዲገፋበት አስገደደው፡፡ በዚህም መሰረት ፓርቲያችን የሽግግር መንግስቱን ስኬታማ ለማድረግ የሚያስችል ሰነድ ጭምር በማዘጋጀት በተጠናከረ ሁኔታ ሃሳቡን ከህገ-መንግስትም ሆነ ከሃገራችን ተጨባጭ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር በማዛመድ ለህዝቡ ይፋ አደረገ፡፡ ነገር ግን መንግስት በህገ-መንግስት ትርጉም ስም በህገ-ወጥ መንገድ ስልጣኑን ለማራዘም ሙከራ በመጀመሩ ፓርቲያችን ይሄንን ድርጊት በመቃወም መንግስት ከድርጊቱ እንዲቆጠብ ባገኘው መድረክ ሁሉ ሞግቷል፡፡ በዚህ ረገድ የፓርቲያችን ከፍተኛ አመራር አቶ ልደቱ አያሌው ፓርቲያቸው የሰጣቸውን ሃላፊነት በመቀበል አማራጫችንን በሰፊው በማብራራት እና የመንግስትን ህገ-ወጥ ድርጊት በማጋለጥ ረገድ የማይተካ ሚናቸውን ተወጥተዋል፡፡
ይሄንን አማራጭ ሃሳብ ፓርቲያችን በማቅረቡ እና የመንግስትን ህገ-ወጥ አካሄድ በማጋለጡ ብቻ እንደ ሁከት ናፋቂ እና ሃገር አፍራሽ በመቁጠር ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጀምሮ በተለያዩ አካላት በፓርቲያችን አመራሮቹ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ የሚያስጠነቅቅ መግለጫዎች በግልፅ ሲሰጥ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡ በአንዳንድ የለውጡ ደጋፊ ነን ባይ ጋዜጠኞች፣ አድርባይ አክቲቪስቶችና አንቱ የተባሉ ሽማግሌዎች ሳይቀር የኛ ሃሳብ ተቀባይነት ከሌለው አገር ይፈርሳል ባላልንበት ሁኔታ የሚነዙብን ፕሮፖጋንዳ እና አሉባልታ እጅግ አሳዛኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ይሄ ድርጊታቸው የነሱን የሞራል ደረጃ ከማጋለጥ ባለፈ በኛ የትግል ሞራል ላይ የሚፈጥረው አንዳችም ተፅዕኖ አይኖረውም፡፡ በተለይም ሃሳቡን በሃሳብ ማሸነፍ እየተቻለ የስርዓቱ የደህንነት ሰዎች አቶ ልደቱን ኢላማ በማድረግ ሲወጣ እና ሲገባ በመኪና በመከታተል እና በማዋከብ ለማሸማቀቅ መሞከር ሲጀምሩ ለውጡ ምን ያህል አደገኛ ባህሪ ባላቸው ሰዎች እየተመራ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሃቅ ነበር፡፡
ከሰሞኑም በህግ ማስከበር ስም በፓርቲያችን ከፍተኛ አመራር አቶ ልደቱ አያሌው ላይ የተወሰደው እርምጃ የሚያሳየው መንግስት ወደ ፍፁማዊ አንባገነንነት መቀየሩን የሚጠቁም ብቻ ሳይሆን አገራችን ከለውጡ በፊት ወደ ነበረችበት ሁኔታ የተመለሰች መሆኑን የሚያሳይ ጭምር ነው፡፡ ፓርቲያችን ከሰላማዊ የትግል አማራጭ ውጭ የሃይል አማራጭን እንደሚጠየፍ በግልፅ እየታወቀ፣ የሰላማዊ ትግል አርበኛ የሆነውን የፓርቲያችንን መስራች እና የብሔራዊ ምክር ቤት አባል አቶ ልደቱን ከሁከት እና ብጥብጥ ጋር እጅህ አለበት በሚል ማሰር ፍፁም ተቀባይነት የሌለው ውንጀላ ነው፡፡ በተለይም የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች ሁከትና ብጥብጡ በተከሰተበት ወቅት አቶ ልደቱን ለደህንነትህ ያሰጋሃል በማለት አጅበው ወደ አዲስ አበባ አስገብተው ሲያበቁ መልሶ ከሁከት እና ብጥብጥ ጋር አስታኮ ማሰር የበለጠ ጉዳዩን አሳፋሪ ያደርገዋል፡፡
አቶ ልደቱ ሃምሌ 20 ቢሾፍቱ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት ባላቸው የህክምና ቀጠሮ መሰረት የዛሬ ዓመት የልብ ቀዶ ጥገና ወዳደረጉበት አሜሪካ ለመሄድ በዝግጅት ላይ እያሉ መንግስት የአርቲስት ሃጫሉን ሞት ተከትሎ ተፈጠረ ባለው ሁከትና ብጥብጥ ጠርጥሬሃለው ብሎ እንዳሰራቸው፣ ከወንጀሉ ጋር ፍፁም ግንኙነት የሌላቸው መሆኑን፣ ፖሊስም በቂ ማስረጃ ማቅረብ አለመቻሉን፣ አቶ ልደቱ የአስም እና የልብ ህመም ያለባቸው መሆኑን፣ ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት አላቸው ከተባለም ሁከት እና ብጥብጡ በመላው አገሪቱ የተፈፀመ በመሆኑ፣ የአገር አቀፍ ፓርቲ አመራር በመሆናቸው እና ቋሚ የመኖሪያ አድራሻቸውም አሁንም በአዲስ አበባ ላይ በመሆኑ እሳቸውን ወደ ቢሾፍቱ ወስዶ ማሰሩ ተገቢ አለመሆኑን በመግለፅ በዋስትና እንዲለቀቁና ጉዳያቸውም በአዲስ አበባ እንዲታይ የጠየቁት ጥያቄ ውድቅ ተደርጎባቸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበዓለ ሲመታቸው ላይ ባደረጉት ንግግር ማንም ሰው የተጣራ ማስረጃ ሳይገኝበት አይታሰርም በሚል ቃል የገቡ ቢሆንም ፖሊስ ማስረጃ ለማሰባሰብ በሚል በአቶ ልደቱ ላይ 14 ቀን ጊዜ ከጠሮ ጠይቆባቸው ወደ ጣቢያ ተመልሰዋል፡፡
አቶ ልደቱ በጠባብ እስር ቤት ውስጥ ከ35 እስረኞች ጋር በመታሰሩ ለኮሮና ወረርሽኝ ተጋላጭ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ በጣቢያው ላይ የፊት መሸፈኛ ጭምብል የሚያደርጉት አቶ ልደቱን ጨምሮ ሌላ አንድ እስረኛ ሲሆኑ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያስችሉ የማስክም ሆነ የእጅ ንፅህና መጠበቂያ አልኮል እና ሳኒታይዘር ባለመኖሩ ፓርቲያችን የአቶ ልደቱ ህይወት ላይ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ስጋት አድሮበታል፡፡ የበለጠ ስጋታችንን የሚያባብሰው ደግሞ ለኮሮና ቫይረስ የበለጠ ተጋላጭ የሚያደርጋቸው የአስም ህመም እና የልብ ህመም ያለባቸው መሆኑ ነው፡፡

በመሆኑም፤-
1ኛ- አቶ ልደቱ አያሌውም ሆነ ፓርቲያቸው ኢዴፓ ከሃሳብ እና የመፍትሄ አማራጭ ከማቅረብ ውጪ ህይወት የሚያጠፋ፣ ንብረት የሚያቃጥል እና ድንጋይ የሚወረውር አባል እና ደጋፊ የሌላቸው መሆኑ እየታወቀ በህግ ማስከበር ስም በሁከት፣ በብጥብጥ፣ ገንዘብ በመርዳትና በማስተባበር መክሰስ ማንንም የማያሳምን ጭፍን እርምጃ በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲፈቱ፤
2ኛ- ብልፅግና ፓርቲ የለውጡ መባቻ ላይ ለህዝቡና ለፖለቲካ ሃይሎች ቃል ገብቶ የነበረውን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅን መብት በማክበር በህግ ማስከበር ስም ከሁከትና ብጥብጡ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን የሃሳብ ሰዎችንና የሚቃወሙትን የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ኢላማ አድርጎ ማሰሩን በአስቸኳይ እንዲያቆም፣
3ኛ- የግል መገናኛ ብዙሃን እና የመንግስት መገናኛ ብዙሃን 27 ዓመት የተለመደውን በጭፍን የመደገፍ እና በጭፍን የመቃወም ባህሪ ተላቀው ሙያዊ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ እናቀርባለን፤
4ኛ- የአገራችን ወቅታዊ ቀውስ እና ከቀውሱም የምንወጣው መዋቅራዊ የሆኑ መፍትሄዎችን በድፍረት ስንወስድ መሆኑ ታውቆ የሚመለከታቸው አካላት ማለትም ህዝቡ፣ የእምነት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ ምክንያታዊ አክቲቪስቶች እና የዲፕሎማቲክ ተቋማት መንግስት አገሪቱን ወደለየለት ቀውስ ውስጥ የሚከተውን ጭፍን እርምጃ ትቶ ሁሉን አቀፍ የውይይት መድረክ እንዲያመቻች እና ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲመቻች በመንግስት ላይ በጎ ተፅዕኖ በመፍጠር አገራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

የኢዴፓ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
ሃምሌ 21 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ

 

የዜና ምንጭ ኢዴፓ

Share