Logo

የግዮን ቆይታ ከአንዳርጋቸው ጽጌ ጋር

June 8, 2018

ግዮን፡አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንኳን ደስ ያለህ፤ እንኳን ለቤትህ አበቃህ?

አንዳርጋቸው ጽጌ ፡አመሰግናለሁ እንኳን አብሮ ደስ ያለን::

ግዮን፡– መቼና እንዴት ነበር መፈታትህን የሰማኸው?

አንዳርጋቸው ጽጌ ፡ከመፈታቴ በፊት ስድስት ሣምንት ቀደም ብሎ ቴሌቭዥን ክፍሌ ውስጥ አስገቡልኝ:: ከዛ በፊት በነበሩኝ ጊዜያት ቴሌቭዥን፣ ሬድዮም ሆነ ሌሎች የመገናኛ ብዙኃንን እንድከታተል አልፈቀዱልኝም፤ እድሉም አልተሰጠኝም ነበር። ከጠቀስኩልህ ወዲያ ግን ቴሌቭዥን ስላስገቡልኝ የወቅቱን ሁኔታ፣ የአዲሱን ጠ/ሚኒስትር መመረጥና ወደ ሥልጣን መምጣት ማወቅ የቻልኩት በዚህ አጋጣሚ ነው። ቅዳሜ ቀን ቤተሰቦቼ ሊጠይቁኝ የሚመጡት ሠባት ሠዐት ስለሆነ ከእነሱ ጋር በማደርገው ቆይታ የሠዐቱ ዜና ስለሚያመልጠኝ እስኪ የስድስት ሠዐቱ ዜና ምን ይላል? ብዬ ቴሌቭዥኑን ከፈትኩት፡ በጊዜው ዜና የለም፤ የሆነ ገፅ ዳሰሳ ነው፣ ግምገማ የሚል ፕሮግራም አለ፤ እዛ ላይ ጋዜጠኞች ከበው “ዛሬ ፌስ ቡክ (ማህበራዊ ድረ ገፅ) አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ እንዲፈቱ በሚል ጥያቄ ነው የተሞላው፤ በዚህ መሠረት አቃቤ ህግ ዛሬ በጉዳዩ ላይ መልስ ሰጥቷል፤ ለአቶ አንዳርጋቸውም ይቅርታ እንደተደረገላቸው አስታውቋል” ብለው ሲናገሩ ሰማሁ። “እንዲህ ነው እንዴ?” ብዬ ነው ያዳመጥኩት።

ግዮን፡– ይቅርታ እንደተደረገልህና እንደምትፈታ ስታውቅ ምን ተሰማህ?

አንዳርጋቸው ጽጌ ፡ብዙም የተለየ ስሜት አልነበረኝም፤ ዝም ብዬ ዜና እንደማድመጥ ያህል ነው የሰማሁት። እስኪ ቤተሰቦቼ ሊጠይቁኝ ሲመጡ እነሱን በደንብ እጠይቃለሁ ብዬ ተውኩት። በኋላ እነሱም የነገሩኝ ሸገር ሬድዮኖች ጉዳዩን ሰምተው ደውለውላቸው ነበር። ስለ ጉዳዩ ያውቃሉ እና አባቴ ብዙ ጊዜ ቁጭ ብሎ ነበር የሚያነጋግረኝ፤ የዛ እለት ግን ከውስጥ ብቅ ስል ከተቀመጠበት ብድግ ነው ያለው። “ዛሬ እንዴት ነው ይሄን ሁሉ ኢነርጂ ያገኘኸው አልኩት?” ያው ዜናውን እኔም እንደሰማሁት ነገርኳቸው።

ግዮን፡– ተፈትተህ እዚህ አሁን ያለንበት የአባትህ  መኖሪያ ቤት ስትደርስ የነበረው ከፍተኛ የህዝብ  አቀባበል እንዴት አየኸው?

አንዳርጋቸው፡በህዝቡ አቀባበል በጣም ነው የተገረምኩት። እኔ ከማረሚያ ቤቱ ቀጥታ ወደ ቤት ይዘውኝ ሲመጡ አባቴ ስላልተነገረው ግቢ ውስጥ ሲንጎራደድ፤ እኔ በር ተከፍቶ ስገባ እንዳይደነግጥ የሚል ሃሳብ ገብቶኝ ነበር። እየመጣሁ በነበረበት ጊዜ እዚህ ስደርስ ግን ሌላ ነው፤ መጀመሪያ ከላይ ጀምሮ ብዙ ህዝብ ስለነበር “ምንድነው ሰፈሩ ወደ መርካቶነት ተቀየረ እንዴ?” የሚል ነገርም መጥቶብኛል። ኦሎምፒያ ከላይ ከሸዋ ዳቦ ቤት መገንጠያ አንስቶ ያለው መንገድ ሁሉ በህዝቡ ቢጨናነቅም ነገሩ አልገባኝም። ወደ ቤታችን መዞሪያ ላይ ልደርስ ስል ባሉ ምልክቶች ነው ህዝቡ እኔን ለመቀበል እንደወጣ የተረዳሁት። በጣም ይደንቃል ፈፅም ይሆናል ብዬ የማልጠብቀው ነገር ነው የሆነው። በጣም የሚያስደሰትና የሚያኮራ አቀባበል ነው የኢትዮጵያ ህዝብ ያደረገልኝ፤ የህዝቡ ፍቅርና አክብሮት ልብ የሚነካ ነው። እንዳህ አይነት ተዐምረኛ አቀባበል ይደረጋል ብዬ መቼም ቢሆን አስቤ አላውቅም።

ግዮን፡– ቅዳሜ ዕለት እንደምትፈታ ተነግሮ ብዙ ህዝብ ቅዳሜና እሁድ ቢጠብቅህም ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ እስከ ማክሰኞ እንድትቆይ ተደረገ በዛ መሃል መጥቶ ያነገጋገረህ አካል ነበር?

አንዳርጋቸው ጽጌ ፡ሰኞ ዕለት ጠዋት የእስር ቤቱ አስተዳደር ሲያነጋግረኝ “ችግር ገጥሞናል ወረቀቱ እኛ እጅ አልደረሰም፤ የአንተ ብቻ ሳይሆን ይቅርታ ተደርጎላቸዋል የተባሉት 500 እስረኞች ወረቀት እኛ ዘንድ አልመጣም። እና እሱን እየጠበቅን ነው፤ እነሱ ከላኩልን በእኛ በኩል ለመልቀቅ ዝግጁ ነን” ብሎኝ ሄደ። ከሠዐት በኋላ አንድ ወረቀት ይዞ መጥቶ “አሁን ሁሉ ነገር ስለደረሰን እዚህ ላይ ፈርም” አሉኝ፤ ግልባጩን ለእነሱ አስቀርቶ ነው መሠለኝ ነጠላ ወረቀቱን ሰጠኝ። ከዚያ ያው እንዳያችሁት ዛሬ ማክሰኞ በአምቡላንስ መኪና ተጭኜ ነው እዚህ ድረስ ያመጡኝ።

ግዮን፡– በተፈታህበት ዕለት ምሽት ቤተሰቦችህን አግኝተሃል፤ ባለቤትህን፣ ልጆችህን ማለት ነው እንደው በአጋጣሚው ምን ተሰማህ?

አንዳርጋቸው፡በቪዲዮ ነው ያየኋቸው በጣም ትንንሽ ልጆች ሆነው ነበር የተለየኋቸው፤ እኔ ስታሰር ሠባት ዓመታቸው ነበር። አሁን አስራ አንድ ዓመት ሞልቷቸዋል፤ ትልልቆች ሆነዋል በመፈታቴ በጣም ተደስተዋል። እኔም ሳያቸው የተሠማኝ ስሜት ልዩ ነው። ግንኙነታችን በጣም ቅርበት ያለው ስለነበር እርግጠኛ ነኝ በእስር ላይ በሆንኩበት ወቅት እኔን ሲያጡ በጣም እንደተጎዱ ይገባኛል። አሁንም ደግሞ ለወንድሜ እያነሱለት ሥለሆነ ”በጣም እንደፈሩ ድጋሚ እንዳያስሩኝ እንደሠጉ” እገነዘባለሁ:: ስለዚህ አሁን ቅድሚያ ለእነሱ ሰጥቼ ሞራላቸውን ትንሽ ማስተካከል ያለብኝ ይመስለኛል። ገና ልጆች ስለሆኑ በሥነልቦና እየተጎዱ ነው፤ ግን በመፈታቴ ልዩ ደስታ ተሰምቷቸዋል። እኔም በጣም ነው ደስ ያለኝ።

ግዮን፡– ወደ ኋላ እንመለስ ከየት ተነስተህ ወዴት  ስትሄድና እንዴት ባለ አጋጣሚ ነበር የተያዝከው?

አንዳርጋቸው፡ከዱባይ ወደ ኤርትራ ለመሄድ የመን ላይ ነው የተያዝኩት። እኔ በየመን አየር መንገድ የመሄድ ፍላጎት አልነበረኝም። ምክንያቱም ችግር እንደሚመጣ አውቄያለሁ። ቡክ አድርጌ የነበረው በኤርትራ አየር መንድ ነበር፤ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም። ግን የእኔን ብቻ አጣሞታል፤ ከእንግሊዝ አገር በላኩለት ሳይሆን ከአንድ ወር ወደ ፊት አድርጎ ነው የበረራ ጊዜዬን የመዘገበው፤ የሌሎችን ግን በሥነ ስርዓቱ ነው የመዘገቡት። ”ከዚህ ውጪ ቦታ የለንም፤ ፈርስት ክላስ ግን አለ” ሲሉኝ ስንት ነው የምጨምረው? አልኳቸው ”400 ዶላር ከጨመርክ መሄድ ትችላለህ” አሉኝ። ያኔ አራት ሺህ ዶላር በኪሴ ይዣለሁ ለስራ የሚሆን፤ ግን 400 ዶላር የድርጀት ገንዘብ በጭማሪ አላወጣም በሙስና ህዝብ በሚሰቃይበት አገር የድርጅት ገንዘብማ አላባክንም፤ ተጨማሪ ወጪ ይቅርብኝ፤ ርካሹ ይሻለኛል ብዬ ነው በየመን አየር መንገድ የተጓዝኩት።

ግዮን፡–  የመን ላይ የኢትዮጵያ የደህነንት ሰዎች እንደት ነበር የያዙህ?

አንዳርጋቸው፡የየመኑን በረራ ቡክ ካደረግኩ በኋላ ነው የበለጠ አደጋ ሊገጥመኝ እንደሚችል እየተሰማኝ የመጣው፤ ከዛ በፊት አንድ ጊዜ በየመን አየር መንገድ ተጉዣለሁ። ግን በዛ ወቅት የነበረው የሀገሪቱ ሁኔታና የሁለተኛው ጉዞዬ ሁኔታ የተቀያየረ ለመሆኑ የተወሰነ ጥርጣሬ ስለነበረኝ በጉዞዬ ላይ የተወሰነ ስጋት ተሰምቶኛል። እዛ አገር ላይም ቢሆን በአየር በረራው ላይ ብዙ ኢትዮጵያዉያን ነው ያሉት። በመሃሉ የኢህአዴግ ሰላዮቹና የመረጃ ሰዎች ይኖራሉ፤ የመን በጣም ሙሰኛ ሰዎች ያሉባት አገር ናት። ለእነሱ ስንት ብር ከፈሏቸው? ለሚለው እግዜር ይወቀው። ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ በጉቦነት ሳይሰጥ አይቀርም፤ ከዚህ ውጪ በነፃ ምንም ነገር የመኖች እንደማያደርጉ ግልፅ ነው። በዚህ አይነት መንገድ አውሮፕላን ማረፊያው ላይ ነው ደህንነቶች የጠበቁኝ፤ በረራው የመን ላይ ትራንዚት አለው፤ ሰንአ ወርጄ ነው እንደገና ወደኤርትራ የምበረው። ገና ከአውሮፕላን እንደወረድኩ አንድ የየመን ሰው ልክ ማፊያ እንደሚያደርገው ተንደርድሮ መጥቶ እንደ ዘመድ ነው ተጠምጥሞ የሳመኝ፤ ለተላኩት ሰዎች እንደመለያ ጥቆማ እያደረገ ነው ያኔ ሁሉ ነገር ገብቶኛል፤ ሰውዬው የየመን የደህንነት ሰው ነው። ትንሽ ቆይቶ የራሳቸው ሰዎች መጡ፤ እዛው ኤርፖርት ውስጥ በጣም ሚያስፈራ ቦታ አለ። የመኖች ኤርፖርታቸው ግቢ ውስጥ እንደዛ አይነት ቆሻሻና የገማ ቦታ ይኖራቸዋል ብሎ ለማሰብየሚከብድ ቦታ ነው። ወደ ትራንዚት ለመሄድ አውቶብስ ውስጥ ስገባ ሌላውን አስቀርቶ ብቻዬን እኔን ገንጥሎ ወደ እዛ መጥፎ ቤት ወሰደኝ። እዛ ቁጭ ባልኩበት የእዚህ አገር የደህንነት ሰዋች አውሮላን ይዘው መጡ። በእቃ ማሸጊያ ትልቅ ፕላስተር አይኔንም፣ አፌንም አሸጉ፣ እጄን ወደኋላ በካቴና አስረው፣ ፊቴን በጆንያ ሸፍነው አስረው ነው ያመጡኝ።

ግዮን፡– ስለዚህ ለአንተ መያዝ ተባባሪው የየመን የደህንነት ሰዎች ናቸው ማለት ነው?

አንዳርጋቸው፡በትክክል፤ አሳልፈው የሰጡኝ እነሱ ናቸው። በጊዜው እኔ የመንን አልረገምኳትም ነበር። ግን ከዛ በኋላ ብዙም ሳትቆይ የኢትዮትያን ህዝብ ረግሟታል መሰለኝ እንዲህ አይነት አስከፊ ችግር ውስጥ ገብታለች።

ግዮን፡– ያኔ የየመን ደህንነቶች ለኢህአደግ ደህንነቶች አሳልፈው ሲሰጡህ፤ ከነበሩት ሰዎች መሃል የምታውቀው ሰው ነበር?

አንዳርጋቸው፡አንዱን የማውቀው ይመስለኛል፤ ሌሎቹን ግን አይቻቸውም አላውቅም። ይሄን በተመለከተ በጣም ሰፊና ዝርዝር ጉዳይ ወደፊት ለህዝቡ አወጣለሁኝ ብያለሁ። ምክንያቱም በጣም ጠቃሚ የሆኑ ጉዳዮች ናቸው፤ እኔ ሁሌ የምታገልባቸውና መሆን አለባቸው የምላቸው ጉዳዮች ብዙ ናቸው። ለአገር የሚበጅ፤ ለሁሉም ህዝብ የሚበጅ በሚሆንበት መልኩ የሚወጣበት አጋጣሚ ይኖራል። ሌላ ነገር ታስቦ ሳይሆን መገለፅ ያለበት ተዛማጅ ብዙ ጉዳይ ስላለው ነው።

ግዮን፡– የደህንነት አባላቱ ብዛት ስንት ነበር?

አንዳርጋቸው፡አራት ናቸው። እጄን ጠምዝዝው በብዙ መከራ ነው መኪና ውስጥ የገባሁት፤ በግብግቡ ጊዜ እጄን ሰብረውታል። ያው ቀደም ሲል እንደነገርኩህ ሙሉ ፊቴን ሸፍነው ነው ወደ አዲስ አበባ ያመጡኝ።

ግዮን፡– በጊዜው ግን ከየመን በቀጥታ ወደ መቀሌ ወስደውሃል ሲባል ነበር እኮ?

አንዳርጋቸው፡እኔም መጀመሪያ ላይ መቀሌ የወሰዱኝ ነበር የመሰለኝ። ምክንያቱም አሳሪዎቼ በሙሉ ትግሪኛ ነበር የሚናገሩት፤ ከተያዝኩም በኋላ ያለሁበት ቦታ እየመጡ የሚያዩኝ፣ የሚያነጋግሩኝ፣ የሚጠብቁኝ በጠቅላላ ከትግረኛ ውጨ ሌላ ቋንቋ ሲናገሩ ስላልሰማሁ መቀሌ ነው ያመጡኝ ብዬ ደምድሜ ነበር። ፈፅሞ አዲስ አበባ ውስጥ ያስሩኛል ብዬ አልጠበቅኩም ነበር። በኋላ ግን የእንግሊዝ አምባሳደር ከታሰርኩ ከአንድ ወር በኋላ መጥቶ ሲያነጋግረኝ “አዲስ አበባ ውስጥ ነው እንዴ ያለሁት?” ብዬ በጠየቅኩት መሰረት እሱ ነው አዲስ አበባ ውስጥ እንዳለሁ ያረጋገጠልኝ።

ግዮን፡– የታሰርክበት ቤት ምን አይነት ነበር?

አንዳርጋቸው፡አንድ ቪላ ቤት ውስጥ ነው፤ አንዱ ክፍል ውስጥ ነው እኔን ያሰሩኝ። መስኮቱ ተነቃቅሎ ግድግዳ ላይ ትንሽ ቀዳዳ የተሰራለት ቤት ውስጥ ስለሆነ ያስገቡኝ የት እንዳለሁ በፍፁም ማወቅ አልቻልኩም። የማገኛቸው ሰዎች በሙሉ የህወሃት የደህንነት ሰዎች ናቸው፤ ምንም አይነት ያለህበትን ቦታ ፍንጭ የሚያሳይ ነገር አታገኝም።

ግዮን፡– በእስር ላይ በነበርክበት ጊዜ የደረሰብህ ችግር ነበር፤ ድብደባ፣ ግርፋት የመሳሰሉ ነገሮች ተፈፅሞብሃል?

አንዳርጋቸው፡ድብደባ የሚያሰፈልገው ነገር አልነበረም፤ እጄን ግጥም አድርገው ወደኋላ አስረው ብዙ ቀናት መተኛት በማልችልበት ሁኔታ ነው ያስቀመጡኝ። በጣም የሚገርም አይነት ህመም ነው የሚሰማህ፤ስቃዩ ከባድ ነው። ከዛ ውጪ መጀመሪያ ላይ እንዳልኩህ እጄን ሰብረውታል። ሌላ የተለየ ሰውነቴ ላይ የተደረገ ግርፋትና ድብደባ የለም።

ግዮን፡– ከእንግሊዝ አምባሳደር ውጪ ከሌሎች የኢምባሲው ዲፕሎማቶች ጋርስ የመገናኘቱ እድል ገጥሞሃል?

አንዳርጋቸው፡ከአምባሳደሩ በስተቀር ሌላ ሰው መጥቶ ሊያነጋግር አይችልም ብለው ስለነበር ቆንስሎች እንኳን እንዲያዩኝ አልፈቀዱም። አምባሳደሩ ላይ ብቻ እንዲህ አይነት ስራ ለማብዛት ለምን እንደፈለጉ አልገባኝም። አንድ አመት ከአንድ ወር እዛው መጀመሪያ ያሰሩኝ ቦታ ነው የቆየሁት።

ግዮን፡– ያን ያህል ጊዜ የቆየህበትን ቦታ ለማወቅ ጥረት አላደረግክም?

አንዳርጋቸው፡አምባሳደሩ ሲመጡ እሳቸውን ለማነጋገር ሲወስዱኝ ፊቴ በብርድ ልብስ ተሸፍኖ ነው። ይህ እንቅስቀሴ ገና ከክፍሏ ስወጣ ነው የሚጀምረው፤ ምንም ነገር እንዳታይ ነው የሚደረገው። ግን በእኔ ግምት የተለያዩ ነገሮችን ደምሬ ቀንሼ በሃሳቤ የደረስኩበት ገነት ሆቴል አካባቢ ካሉ ቪላ ቤቶች ውስጥ በአንዱ እንደታሰርኩ ነው የሚገባኝ። እንዲህ አይነት በርካታ ሰው ማሰሪያ ቪላዎች እንዳላቸው ነው የገባኝ፤ ከአውሮፕላን ከወረድን በኋላ የተለያዩ ቦታዎች ሄደን ሲጠይቁ እየመለሷቸው መጨረሻ ላይ ያሰሩኝ ቦታ ተገኘና እዛ አስገቡኝ።

ግዮን፡–  ያመጡህ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው ?

አንዳርጋቸው፡የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው፤ ያው እኔን ከየመን ደህንነቶች እንደ ተቀበሉኝ ፊቴን ስለሸፈኑት አላየሁም፤ ግን አማርኛ የምታወራ የሆስተስ ድምፅ ሰምቻለሁ። ቻርተር በረራ እንጂ ትልቅ የመንገደኞች አውሮፕላን አይደለም ይዘው የመጡት። አፌ፣ አይኔ፣ አፍንጫዬ በፕላስተር ፊቴ በጆንያ የተሸፈነ በመሆኑ በግልፅ ለማየት ባልችልም አውሮፕላኑ ውስጥ ከእነሱ በስተቀር ማንም ሰው አልነበረም። ወደአውሮፕላኑ ሲያስገቡኝ የወጣሁት ሶስትና አራት ደረጃ ብቻ ስለነበር የያዟት ፕሌን ትንሽ መሆኗን ተረድቻለሁ።

ግዮን፡ከምን ያህል ጊዜ በኋላ ነበር ወደ ቃሊቲ የወሰዱህ?

አንዳርጋቸው፡አንድ አመት ከአንድ ወር በላይ በዚያ ቪላ ቤት ውስጥ ነው የታሰርኩት። ሐምሌ 3 ቀን 2007 ም ነው ወደ ቃሊቲ የተዛወርኩት።

ግዮን፡በአንድ አመት ቆይታህ ከቤተሰበችህ ጋር ተገናኝተሃል?

አንዳርጋቸው፡ማንንም አላገኘሁም፤ እንዲጠይቁኝም የተፈቀደላቸው የት እንዳለሁም የሚያውቁ አይመስለኝም። አምባሳደሩ ብቻ ናቸው የጠየቁኝ።

ግዮን፡ከመንግስት ባለስልጣናት በታሰርክበት ጊዜ መጥተው ያነጋገሩህ ነበሩ?

አንዳርጋቸው፡የደህንነት ሰዎች ናቸው በተለያየ ጊዜ ያናገሩኝ። ያው በደንብ ባላውቀውም ጌታቸው አሰፋ የሚባለው የደህንነት ሃላፊውን ጨምሮ የተለያዩ የተቋሙ ውሳኝ ሰዎች አነጋግረውኛል። ከዚህ በፊት በ1997 .ም በታሰርኩበት ጊዜ ዝዋይ መጥተው አነጋግረውኝ ነበር። ያኔ እነ መለስ ዜናዊ ልከውት ነው መጥቶ ያነገገረኝ፤ የሚገርም ጥያቄ ነበር በወቅቱ የጠየቀኝ። ”ኢህአዴግ እንደዚህ የሆነው ምን ሆኖ ነው የሚል ጥያቄ ጠይቀው ተብዬ ነው የመጣሁት” ነበር ያለኝ። ኢንተለጀንትና በተወሰነ ደረጃ ነገሮች የሚገባው ሰው ነው፤ ውይይቱም ቢሆን ረጅም ሰአት የፈጀና ብዙ ቀን የፈጀ ውይይት ነው ያደረግነው። ችግር ያለው ነገር አልነበረም::

ግዮን፡ያኔ ከፍተኛው የደህንነት አመራሮች ያቀርቡልህ የነበረው ጥያቄና የምትወያዩበት ጉዳይ ምን ነበር?

አንዳርጋቸው፡በአጠቃላይ እኛ /ግንቦት ሰባት/ የምናደርገውን እንቅሰቃሴ ነው ለማወቅ የሚፈልገው። አብዛኛው ነገር ግልፅ ነው፤ እንደ አጋጣሚ በጣም መጥፎ የሆነው ነገር ኦርጋናይዝ አደርጋለሁ ብዬ በፍላሽና በኤክስተርናል ድራይቮች ላይ የያዝኳቸውን ብዙ ዶክመንቶችን በያዙኝ ወቅት ስላገኙ ብዙ የተጫኑኝ ነገር አልነበረም። ከዚህ ውጪ አንዳንድ ነገሮች በእጄ የሌሉ አሉ፤ እኔ ኤርትራ በመመለስ ሙሉ ለሙሉ ከንቅናቄው ውጪ ሆኜ ስለ ነበር እዛ ላይ ብዙ ጥልቅ የሆኑ መረጃዎች አልነበሩኝም። ብዙው ነገር በአደባባይ የሚውቁት ነው፤ የኤርትራ ጉዳይ አለ ስለ እሱ ከዛ በፊት ራሳቸው ሲያወሩት የነበረ ጉዳይ ነው። የ500 ሺህ ዶላሩ ጉዳይም አለ፤ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ግብፅ ስብሰባ እንደሄደና እንደተነጋገረ ጠይቀውኝ እኔም ተገቢውን ምላሽ ሰጥቻቸዋለሁ።

ግዮን፡ከግብፅ ገንዘብ ተቀብላችኋል ወይ ነው ጥያቄው?

አንዳርጋቸው፡አዎ አላመኑም መሰለኝ፤ ይሄን ያህል ገንዘብ እንዴት ይሰጧቸዋል? ብለው አላመኑም ይመስለኛል። እንዴት እንዲህ ታደርጋለች? የሚል ስሜት ነው ያላቸው። ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለንን ግንኙነት፣ ከሱዳንና ከደቡብ ሱዳን ጋር ያለንን ግንኙነት በተመለከተ ጠይቀውኛል። ከዚህ በተረፈ የአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ነው በጣም ሰፊ የሆነ ውይይት ያደረግነው። ያለውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ በተመለከተ በቃል ከማስረዳት ባሻገር በፅሁፍ መቶ ሰማኒያ አምስት ገፅ እንዴትና ምን ማድረግ እንዳለባቸው ገልጬላቸዋለሁ። ከ1997 .ም ምርጫ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ሰአት ድረስ ያሉትን ነገሮች በዝርዝር የሚያሳዩ ፅሁፍ ሰጥቻቸዋለሁ። ኮምፒዩተር ሰጥተውኝ ጊዜ ወስጄ በችግሮቹና በልዩነታችን ላይ ብሎም በመፍትሔዎቻችን ላይ ጭምር ዝርዝር ማብራሪይያ ፅፌ ሰጥቻቸዋለሁ።

ግዮን፡/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር በነበሩበት ወቅት “አንዳርጋቸው መፅሃፍ እየፃፈ ነው፤ ላፕቶፕ አስገብተንለታል” ብለው ነበር፤ ይሄ ነገር እውነት ነው?

አንዳርጋቸው፡አዎ መጀመሪያ እኔ የምፅፈውን ነገር ከፖለቲካ አኳያ ስለፈለጉት ኮምፒዩተር የሰጡኝ ይመስለኛል። ግን በእሱ አልቆመም ኮምፒዩተር ከሰጡኝ በኋላ ሌላ የምፅፈው ነገር እንዳለ ለጌታቸው ገልጬለት ተጨማሪ የምፈልገው ነገር ካለ እንደሚተባበሩኝ በገለጸልኝ መሰረት ለጽሁፌ የሚረዳኝ ሪፈረንስ መፅሃፍም እንዳስገባ ፈቅዶልኛል። አሁን እንግዲህ ወደ 850 ገፅ ደርሷል የፃፍኩት ልክ እንደ ዘውዴ ረታ “አፄ ሃይለ ስላሴ” የተሰኘውን ትልቅ መፅሃፍ ያህላል መጠኑ። በመፅሃፍ ደረጃ ኮምፒዩተሬ ላይ ተቀምጧል፤ “እኛም እንናገር፣ ትውልድ አይደናገር” የሚል ስምንት መቶ ሃምሳ ገፅ ያለው መፅሃፍ ነው። በተለይ ድሮ በኢህአፓ ጊዜ የቤተሰባችንን፣ የከተማዋን፣ የአዲስ አበባን አጀማመርና አመሰራረትና ህይወቷን በጠቅላላ ማለትም እኔ ከእዚህ ከተማ እስከወጣሁበት 1970 .ም ድረስ የነበረውና የህዝቡን ህይወት የሚዳስስ ነው። ስለዚህ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ያለው እውነቱን ነው። ግን የመጀመሪያው ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነው፤ ያንን ካገነኘሁት አገኘሀት ካላገኘሁት የሚሆነውን እስኪ እናያለን። ዛሬ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ችግርና ድክመት አንድም ሳይቀር በዝርዝር የያዘ ዶክመንት ነው። እኔ በተገኘው አጋጣሚ እነሱን ዙሪያቸውን የከበቧቸው አድርባዮች የማይነግሯቸው ችግሮች የሚያመላክቷቸውን እውነታዎች ነግሬያቸዋለሁ። የሚቀጥለው ዓይነት ነገር ውስጥ መግባት ከፈለጉ፤ የፍርድ ቤቱን ውሰኔ የሚያስፈፅሙም ከሆነ አንድ ትልቅ ነገር ነው በሚል ምንም አይነት ቁጠባ በሌለው መንገድ መልኩ ነው ፅፌ የሰጠኋቸው።

ግዮን፡አንተ ችግሮቻችሁ እነዚህ ናቸው ብለህ ፅፈህ ስትሰጣቸው እነሱ የተከራከሩትና ያነሱት ነገር አለ?

አንዳርጋቸው; በውይይታችን ጊዜ ነበር በጽሁፉ ላይ ግን ውይይት አልተደረገም። ለመንግስት ባለስልጣናት የሰጧቸው አይመስልም፤ እኔም በግልፅ የፃፍኩት ለሌሉች ድርጅቶች ሳይሆን ለህወሃት ብዬ ነው። ሌሎች ድርጅቶችን በተወሰነ ደረጃ ሊያስቀይም የሚችል ነገር አለው። ምክንያቱም እኔ በዋነኝነት ሁሉን ነገር የምትሰሩት እናንተ ናችሁ ለልማቱም ለጥፋቱም ተጠያቂ፤ እናንተ ናችሁ። አሁን ያለውም ችግር ይሄ ነው፤ ብዬ ህወሃቶችን በግልፅ የፃፍኩላቸው፤ የነገርኳቸው። በዝርዝር ውስጥ ችግሮችን ከመጠቆምና ከማመልከት ባሻገር መደረግ ያለባቸውንም መፍትሔዎችን ገልጫለሁ። በዛ መልኩ እነሱ የፈለጉት ነገር መጀመሪያ ስለነበረ ነው ኮምፒዩተር እንዲገባና እንድፅፍ የተፈቀደው።

ግዮን፡አሁን እነዛ ፅሁፎች በአንተ እጅ አሉ?

አንዳርጋቸው፡የሉም እነሱ ጋር ስለሚገኝ እጠይቃለሁ፤ ፅሁፎችን የማግኘት እድል ይኖረኛል ብዬ ነው የማስበው።

ግዮን፡ወደ ከተማ ወጥተህ በአዲስ አበባ የጎተራ ማሳለጫ መንገድን እንድትጎበኝ ተደርገሃል የሚባለውስ?

አንዳርጋቸው፡ብዙ ጊዜ በከተማ ልማት ላይ እንከራከር ስለነበር ከሰራነው መሃል አንዳንዱን ነገር እናሳይህ ብለው የተወሰኑ ቦታዎችን አሳይተውኛል። ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ የሚሄደውን የፍጥነት መንገድ፣ ኮንዶምኒየሞች፣ ማሳለጫውን አሳይተውኛል።

ግዮን፡የዛኔ በሚደያዎች ላይ የወጣው ፎቶ ትክክል ነበር ማለት ነው?

አንዳርጋቸው፡በዛ መንገድ ይጠቀሙበታል ብዬ አልጠበቅኩም። ምክንያቱም በተወሰነ ደረጃ ያለውን ነገር አላውቅምና እነሱ ምንም የሆነው ነገር የለም ለማለት የተጠቀሙበት ይመስለኛል። ግንባታና በአጠቃላይ በከተማ ልማት ዙሪያ የሰራችሁት ዝም ብሎ ተራ የሆነ ነገር ነው የሚል ከፍተኛ ክርክር ስለዳረኩባቸው እኔን ለማሳመን የተጠቀሙበት ዘዴ ነው።

ግዮን፡አንዳርጋቸውን “ከድርጅቱ ሰዎች መሃል አሳልፎ የሰጠው ሰው አለ“ የሚል ነገር አለ፤ አንተ ታምንበታለህ?

አንዳርጋቸው፡የለም ፈፅሞ ሊኖር አይችልም። ምክንያቱም ይሄ ነገር በጣም በቀላሉ ሊሆን የሚችል ነገር ነው፤ ስለዚህ እንዲህ አይነት መረጃ ላይ ያልተመሰረተ ዝም ብሎ የሚወራ ነገር ነው፤ ተገቢም አይደለም። ነገሩን ከስሩ ካየነው ከዱባይ ስነሳ ከኤርፖርት ጀምሮ ብዙ ሰው ነው የነበረው። ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ሰዎችም የሚሳፈሩበት አውሮላላን ነው። እኔ በይፋ የምታወቅ ሰው በመሆኔ የእነሱ ሰው “አንዳርጋቸው እዚህ አውሮፕላን ላይ አለ“ ብሎ ለመናገር በጣም ቀላል ነበር።

ግዮን፡ሲይዙህ ቤተሰቦችህ፣ ልጆችህን ፣በተለይም ደግሞ ኤርትራ በረሃ ድረስ ያወረደህን ትግልህን ስታስበው.. በቃ ሃሳቤን ከግብ ሳላደርስ ሊገሉኝ ነው የሚል ፍርሃት አላሳደረብህም?

አንዳርጋቸው፡እንደውም እኔ የመን ላይ ከመያዜ በፊት ኤርትራ ውስጥ ሆኜ የሚገለኝን ሰው የላኩ በመሆናቸው ለምንም ነገር እንደማይመለሱ አውቅ ነበር። በየመን በኩል ለመሄድ ጉዞ ስጀምር ትንሽ ስለተጠራጠርኩ እዛ ያለው የኤርትራ አምባሳደርን እስከምሄድ ደረስ እንዲያገኘኝ ላኩልኝ ብዬ ለየማነ ነግሬው ነበርና አምባሳደሩ እንደሰማሁት እዛ ሰነአ ኤርፖርት ነበር። በዚህ የተነሳም እንዲህ አይነት ነገር ሊኖር እንደሚችል መረጃው ስላላቸው ወሬው ይወጣል በሚል ስጋት ይሆናል እርምጃ ሳይወስዱብኝ የተረፍኩት ብዬ አስባለሁ።

ግዮን፡መረጃዎች እንዳይዙብህ ለማሸሽ አልሞከርክም?

አንዳርጋቸው፡አልቻልኩም በጊዜው ብቻዬን ነው የነበርኩት፤ እንደያዝኳቸው ነው በቁጥጥር ውስጥ ያዋሉኝ።

ግዮን፡ቃሊቲ ከገባህ በኋላም ለብቻህ የታሰርክበት ክፍል ቀደም ሲል እነ ታምራት ላይኔና ስዬ አብርሃ የታሰሩበት ነው። እንደውም ክፍሉ በተለየ ሁኔታ እየተሰራና እየታደሰ ስለነበር ከአንተ ቀድመው የታሰሩት እስክንድር፣ አንዱአለምና አበበ ቀስቶ ሁኔታውን በንቃት ሲከታተሉት ነበር።

አንዳርጋቸው፡መጀመሪያ ቃሊቲ እንደሄድኩኝ አንድ ሰው ብቻ ያለበት ጠበብ ያለች ክፍል ነው ያስገቡኝ። በኋላ ቤቱን በተባለው መንገድ አስተካከሉና ሌሎች ሁለት ሰዎችን ጨምረው እዛ ክፍል ውስጥ አስገቡኝ። እነዚያ አብረውኝ እንዲታሰሩ የተደረጉት በተራ ነፍስ ግድያ ተከሰው የታሰሩና ምንም አይነት የህይወት ተሞክሮ የሌላቸው ምንም አይነት ትምህርትና እውቀት የሌላቸው ኑሮን በጣም አስቸጋሪ ማድረግ የሚችሉ ሰዎች ናቸው። ሌላው እስረኛ የሚያገኘው የቴሌቭዥንና ሬድዮ የመከታተል መብት እኔ ጋር አልተፈቀደልኝም። ማንኛውም ሰው ቤተሰቦቹ እንደፈለገ ይጠይቁታል እኔ ከአባቴና ባለቤቱ ሌላ ሰው እንዲጠይቀኝ አልተደረገም። ፍርድ ቤት ውሳኔ የሰጠበት ግልባጭ የሚባል ቅፅና ቁጥር ሁሉ እስረኛ አለው፤ እኔ ግን የእስረኛ ቁጥር የለኝም። ጭራሹኑ አንደኛው የወህኒ ቤቱ ሰው “በአደራ ነው የተቀመጥከው እንጂ እኛ ብዙም የሚያገባን ነገር የለም” ነው ያለኝ። በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ነው የቆየሁት። ኤምባሲው በመደበኛነት መፅሃፎችን ያመጡልኛል፤ አንዳንድ አማርኛ መፅሃፎችን ማን እንደላከልኝ ባላውቅም አገኛለሁ። ምናልባት እህቴ ትሆናለች፤ የዶክተር ምህረትን ሁለቱን መፅሃፎች እዛ ነው ያነበብኩት። ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉ መፅሃፎችን እስር ላይ እያለሁ አንብቤያለሁ።

ግዮን፡ምግብና ህክምናን በተመለከተስ ያለው ነገር እንዴት ነው?

አንዳርጋቸው፡ምግብ ያው ወላጆቼ በሳምንት አንዴ የሚያመጡት ነገር ነው። አልፎ አልፎ ጉድለት በሚኖርበት ሰአት ላይ እኔ ብዙም ለምግብ የምጨነቅበት ሁኔታ ስለሌለ እዛ ያለውንም ምግብ እጠቀማለሁ። እዚያ ያለው ምግብ የኢትዮጵያ ህዝብ ዘጠና በመቶ የሚሆነው እንጀራ በወጥ በመሆኑ ያንን የእስረኞች ምግብ እጠቀማለሁ፤ መሆንም ያለበት ይሄ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ምሳና እራቱን በአግባቡ የማይበላ ከሆነ አንደኛውን መቀነስ አለብኝ የምል ፖለቲከኛ ነኝ እኔ። ስለዚህ በምግብ ረገድ አማርሬ አላውቅም። ሌላውን ነገር አማርሬ አላውቅም። ህክምና ከጥርስ ጋር በተያያዘ ለሰባት ጊዜያት ያህል ጉንጩን አሳብጦት ከፍተኛ ህመም ገጥሞኛል። ግን ከማደንዘዣዝና አንቲ ባዮቲክ በስተቀር ሌላ ቦታ የተሻለ ህክምና እንዳገኝ ማድረግ የማይታሰብ ነገር ነው። አራቱን አመት ከእኔ ጋር የታሰሩት ሰዎች ጥቁር አንበሳ፣ ኢቭን የግል ሆስፒታሎች ጭምር ወስደው ያሳከሙበትና ያስመረመሩበት ሁኔታ አይቻለሁ። እኔን ግቢው ውስጥ መጥታ የምትመለከተኝ አንድ የጤና ኦፊሰር ነው የመደቡት። ለማንኛውም ነገር እሷ ነች የምትመጣው።

ግዮን፡በቅርቡ ቴሌቭዥን የታሰርክበት ክፍል ገብቶልህ ነበር፤ ለመሆኑ አዲሱን ጠ/ ማኒስትር እንዴት አየሃቸው?

አንዳርጋቸው፡የዶክተር አብይን ንግግራቸውን ነው የሰማሁት ፊታቸውን ነው ያየሁት። ከዛ በፊት አላውቃቸውም ግን አጀማመራቸው በጣም ጥሩ ነው፤ እንደ ነጂ ሳይሆን እንደመሪ ነው የሚናገሩት። አንድን ሰው መጀመሪያ በንግግሩ፤ ከዛ በድርጊቱ ነው የምትለካው። እስካሁን ድረስ ግን አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ባደረጓቸው ንግግሮች፤ ከንግግሮቻቸው ጋር በፊት ገፅታቸው ላይ የምታየው ስሜት ዝም በለው ለለባጣ የሚናገሩ ሰው እንዳልሆኑ በስሜታቸው የሚናገሩ ሰው እንደሆኑ ትመለከታለህ። ከዚህ በመነሳት የተሻለ ነገር ሊሰሩ ይችሉ ይሆናል የሚል ተሰፋ አሳድሮብኛል።

ግዮን፡– “አንዳርጋቸውን በማሰራችን 11 ቢሊየን ዶላር አጥተናል፤ አንዳርጋቸው እንዲፈታ እምነቴ በመሆኑ ወስኛለሁ“ብለው ለትግራይ አርቲስቶችና ባለሃብቶች ባደረጉት ግብዣ ላይ የተናገሩት ዶ/ር አብይ ከመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር አንተን ለማሰፈታት ከፍተኛ አለመግባባት ውስጥ እንደነበሩ ተናግረዋል። በዚህ ላይ ምን ትላለህ?

አንዳርጋቸው፡እኔ ይሄ ነገር መኖሩ አይገርመኝም፤ ግን የተባለው ነገር እውነት ከሆነ የህወሃት ሰዎች ተሳስተዋል። የህወሃት ሰዎች ከእኔ በላይ ወዳጅ የላቸውም፤ ምክንያቱም በዙሪያቸው የተሰበሰበው አድርባይ የማይነግራቸውን እየነገርኩ በጊዜ ገና በ1983 እና 84 ላይ የተናገርኩት ኢትዮጵያ ቴሌቭዥን አለ። በዛን ጊዜ ችግር ሊመጣ እንደሚችልና ምን መስተካከል እንዳለባቸው ነው የነገርኳቸው። ይሄ ደግሞ ከማንኛውም አገሪቷ ውስጥ ካለው ህዝብ የበለጠ በቅርበት አብሬው በመኖር ብዙ የችግርና የመከራ ጊዜን ከልጆቼ አፍ ቀንሶ መግቦ ላኖረኝ ለትግራይ ህዝብ ካለኝ ፍቅር፣ ያ ህዝብ ከዋለልኝ በመነሳት ነው። በህዝቡ ላይ ምንም አይነት ችግር ሊደርስ የሚችልበት ሁኔታ እንዲመጣ ስለማልፈልግ መሪዎች በሚያጠፉበት ሰአት ላይ በጊዜ ነው መስተካከል የሚኖርባቸውን ነገሮች ለመናገር የሞከርኩት። እነዛ አመራሮች እንዲህ አይነት ተቃውሞ ማቅረብ አልነበረባቸውም። በዙሪያቸው አድርባይ የሆኑ፣ በጣም አጎብዳጅ የሆኑ፣ እውነቱን የማይነግሯቸውና በጊዜ መስተካከል ያለባቸውን ችግሮች የማይጠቅሟቸውን ሰዎች እንደ ወዳጅ አድርገው ማየት የለባቸውም ነው ያልኩት። እኔ እዚህ አገር በ1983 .ም ስመጣ ኢህዴንን ወይም ሌላውን ድርጅት አይደለም የማውቀው። ያኔ የማውቀው ህወሃቶችን ነው፤ እንግሊዝ አገር ሆኜ ህወሃትን መደገፍ ፋሽን ባልነበረበት ሰአት እኔ ነበርኩ የምደግፈው። ከእነሱ ጋር ያለኝ ግንኙነት በመርህ ላይ የተመሰረተ በከፍተኛ ወዳጅነት ላይ የተመሰረተ እንጂ በጠላትነት ላይ የተመሰረተ አልነበረም። ግን ስህተት ሲሰሩ በአድርባይነት የማለፍ ባህሪይ የለኝም። እኔ በምናገርበት ሰአት ላይ ራሳቸውን መመርመር ነው እንጂ የሚገባቸው በጠላትነት ፈርጀው ማየት አልነበረባቸውም። እነሱን ሊጠቅሙ የሚችሉ ያላቀረብኳቸው ሃሳቦች የሉም፤ እኔ ክርክሬ በሙሉ ድርጅቱን ይጠቅማል። ድርጅቱን በህዝቡ ተወዳጅ ያደርጋል በሚል መልኩ ነው አቅርብ የነበረው። ያልኳቸው ነገሮች ሁሉ በተግባር ውለው ቢሆን ኖሮ እንደ ጣኦትነት የሚመለኩበት ሁኔታ መፍጠር እንችል ነበር።

ግዮን፡ከእስር እንደተፈታህ ዶ/ር ብርሃኑ፣ ጃዋር መሃመድ፣ ኦኤምኤን እና ኢሳት ክሳቸው ተቋርጧል የሚል ነገር ተናግሯል። ይሄ የፖለቲካ ምህዳሩን ያሰፋዋል?

አንዳርጋቸው፡ተስፋ የሚሰጥ ነገር ነው፤ መደረግም ያለበት ነገር ነው። በአጠቃላይ እኔ የተቃውሞ ሱስ የለብኝም፤ እውነት ለመናገር ሁሉን ነገር ጨርሼ ወደ ስነ ፅሁፍ እገባለሁ ባልኩበት ሰአት በ1997 ምርጫ ወቅት የሰሩት ስራ ነው መልሶ ፖለቲካ ውስጥ የጨመረኝ። እዚህ አገር ውስጥ ያየሁት ከፍተኛ የሆነ የመብት ገፈፋና ኢ ሰብአዊ ድርጊት ነው መልሶ ፖለቲካ ውስጥ የጨመረኝ እንጂ እኔ በስፋት ወጣቱ ሊያነባቸው የሚችል፣ ማንነትን ሃገሩን የኢትዮጵያ ህዝብ ያደረገውን ትግል የሚገልፅ አራት አምስት መፅሃፎችን ፅፌ መጨረሻዬ ሰአት ላይ እሆን ነበር። በዚህ አይነት ወደፊት የሚሰራ ከሆነ አስተማማኝ የሆነ የፖለቲካ ምህዳር እስከተፈጠረ ድረስ፤ ደጋግመን እኛ ያስቀመጥነው ነገር አለ። እንደ ግንቦት ሰባት እኛ ስልጣን የመያዝ ጉዳይ አይደለም ጥያቄያችን፤ ሁሉንም ህዝብ በነፃነት በእኩልነት የሚያገለግሉ፣ ነፃ ተቋማት መኖር አለባቸው ነው የምንለው፤ ነፃ ተቋማት ጥያቄ የፖለቲካ ምህዳሩን እናሰፋለን ስለተባለ ብቻ የሚቃለል አይደለም። በተጨባጭ እነዚህ ተቋማት መታየት አለባቸው። ነፃ ተቋማት ስንል መከላከያውን ፣ነፃ ተቋማት ስንል ደህንነቱን፣ ነፃ ተቋማት ስንል የፍርድ ስርአቱን፣ ነፃ ተቋማት ስንል ፖሊስን፣ ነፃ ተቋማት ስንል ሚዲያውን፣ የምርጫቦርዱን ነው። እነዚህን በነፃ ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅትና አጠቃላይ የአገሪቱ ህዝብ ነፃና ገለልተኛ ናቸው ብሎ በእርካታ በሚቀበልበት ሰአት፤ እውነትም ይህች አገር በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ገብታለች። በዚህ አጋጣሚ ባለፉት ዓመታት ለታየው የህዝብ ንቅናቄና ለተሳተፉትና እኔን ለማስፈታት በተደረገው እንቅስቃሴ ላይ ለተሳተፉት ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ትልቅ አክብሮት እንዳለኝ በዚህ አጋጣሚ እገልፃለሁ። አመሰግናለሁ ይሄን መሰሉ ድጋፍ የበለጠ በመንገዳችን እንድንገፋ ያደርገናል፤ ህዝቡም ለመብቱ መታገሉን ችግሮች እስካልተፈቱ ድረስ ወደ ፊት መቀጠል ይኖርበታል።

source deregenegash.wordpress.com

Share