Logo

የትግራይ በጀት የሞራልና የህግ ጥያቄዎች

Ethiopian Budget
August 20, 2021

የብሔረ-ኢትዮጵያውያን መንደር

ህወሃት ከፌደራል መንግሥት ጋር ውይይት ለማድረግ ካስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች አንዱ የፌደራል መንግስቱ የሁለት አመት በጀት ማለትም ወደ 20 ቢሊዮን የሚጠጋ ብር ሊሰጠኝ ይገባል ማለቱ ነው።

ህወሃት ከመንግሥት ጋር ለውይይት ከመቀመጤ በፊት ሊደረግለኝ ይገባል ብሎ ያቀረበውን ጥያቄ ከህግና ከሞራል አንጻር ተንትኖ     ግንዛቤ መጨበጥና የመንግሥት ምላሽም ምን ቢሆን ይሻላል የሚለውን መጠቆም ተገቢ ይመስላል።

የመጀመርያው የዚህ የይገባኛል ጥያቄ መነሻ በህወሃት ከፍተኛ አመራሮችና ካድሬዎች አአምሮ ውስጥ ለረዥም ዓመት ሰርጾ እያስቸገራቸው ያለው የትግራይ ህዝብ ማለት ህወሃት ነው ከሚለው የግል እምነታቸውና ቅዠታቸው የሚመነጨው እሳቤ ነው። ህወሃት የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ወታደራዊ ጥቃት ፈጽሞ ሠራዊቱ ከመከላከል ወደ ማጥቃት ተሸጋግሮ ወደመቀሌ ሲገሰግስ የህወሃት አመራር መቀሌን ለቆ ሸሽቶ ቆላ ተንቤን በተደበቀበት በዘጠኝ ወር ጊዜ ውስጥ ለትግራይ ህዝብ ለተሰጠው የትምህርት የጤና የባንክ የስልክ የኤሌትሪክ ..አገልግሎት የወጣውን፣ ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርና ለፌደራል መንግስትና ለክልሉ ተቋማት ሰራተኞች የተከፈለውን ደሞዝ፣ በአጠቃላይ በፌዴራል መንግስትና በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በኩል ለትግራይ ህዝብ ግልጋሎቶች እንዳልተሰጡና ወጪ እንዳልተደረገ በመካድ ይህንን የተበላ ገንዘብ በበጀት ስም መንግስት በድጋሚ ይስጠኝ ማለቱ ነው። ስለሆነም በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ተለቆ ህወሃት ቆላ ተንቤን ውስጥ ተወሽቆ በነበረበት ጊዜ ውስጥ ክልሉ ላይ ወጪ የተደረገና ለክፍያ የዋለ ያለፈው አመት በጀት ለጥያቄ የሚቀርብበት ሕጋዊና የሞራል መሠረት አይኖረውም።

በቅርቡ ጌታቸው ረዳ አሱም ሆነ የትግራይ ክልል መንግሥት የፌደራል መንግሥቱን አናውቀውም በማለት የሰጡትን አስትያየት ወደጎን ትተን እውቅና ከነፈጉት የፌደራል መንግሥት ይለቀቅልን በማለት የሚጠይቁት የዚህ አመት በጀት ግን የህግም የሞራልም መሰረት ይኖረዋል።

ይህ ጥያቄ የሚስተናገደው ህወሓት በሚቀጥለው በጀት አመት ሙሉ በሙሉ የክልሉ ከፍተኛ የአመራር አካል በመሆን መቀሌ ውስጥ ይቆያል፣ ይህም ሃይል ለህዝብ አገልጋሎት መስጠት ይችላል፣ የፌዴራል መንግስትም በፌዴራሊዝሙ ፊስካል ህግጋት መሰረት ህወሃት ከክልሉ በታክስ የሰበሰበውን የህዝብ ገንዘብ ምን ላይ እንዳዋለው፤ ወደ ፌደራል መንግስትም ምን ያህል ፈሰስ ማድረግ ይጠበቅበት ይሆን የሚለውን የፌደራል መንግሥት በየትኛውም ክልል ውስጥ እንደሚያደርገው ሁሉ ወደ ትግራይ ክልልም ባለሙያዎች ልኮ ያልተገደበ ኦዲት ማድረግ ይችላል ከሚለው እሳቤ በመነሳት ነው።

ይህ ካልሆነ ግን ከሌሎች ክልሎች ተሰብስቦ ወደ ፌደራል መንግሥት ፈሰስ የተደርገውን የህዝብ ገንዘብ መንግሥት ለህወሃት የመስጠት መብት አለው ወይ የሚለውን የህግ ጥያዌ ያስነሳል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የሞራል ጥያቄና ግዴታም ይነሳል።

በእርግጥ የኢትዮጵያ ፈደራላዊ መንግስት የሃገሪቱን በጀት ሲያጸድቅ ለትግራይ “ክልል” የተመደበውን መጠን ይፋ አድርጓል።  ይህም ዜና እንደሚጠበቀው ሁሉ የኢትዮጵያውያንን ቀልብ የሳበ ጉዳይ ሆኗል።

ለመሆኑ ይህ የ“በጀት” ምደባ አግባብነት ያለው ነው ወይ? የፈደራል መንግስቱ እንዴት አድርጎ ነው ይህንን “በጀት” ለትግራይ ህዝብ የሚያደርሰው? እነዚና እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎች በአብዛኛው ማህበረሰብ አእምሮ ውስጥ የሚብላሉ ጉዳዮች ናቸው።

በመሰረቱ “በጀት” ተብሎ መጠራቱ እና እንደወትሮው የብሄራዊ ሃብት አስተዳደር አካል እና ቅጥያ ተደርጎ መቅረቡ ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ነው። በዚህ ወቅት ለትግራይ መመደብ ያለበት ወትሮም የሚመደበው ዓይነት “በጀት” ነው? ወይንስ የወቅቱን ሁኔታ ያገናዘበ የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታንና የተቋረጡና ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ መሰረታዊ አገልግሎቶችን መልሶ ለመዘርጋትና ይህንንም ተግባራዊ ለማደርግ የሚወጣውን የአስተዳደር ወጪ የሚሸፍን ገንዘብ ነው? አግባብ የሚሆነው ሁለተኛው ነው። በግልጽ እንደሚታየው  የትግራይ ህዝብ በአሁኑ ወቅት በጦርነት ቀጠና ውስጥ የሚገኝ ህዝብ ነው። የመደበኛ ሥራ፣ የንግድም ሆነ ሌሎች ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች የማይካሄዱበት እና ህዝቡ በአብዛኛው በዕለታዊ የዕርዳታ አቅርቦት ህይወቱን እየገፋ የሚገኝበት ጊዜ ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የ”በጀት” ምደባው ትርጉም ምንድን ነው?

በእርግጥ መንግስት ለሌሎች ክልሎች እንደሚያደርገው በተቀመጠው ቀመር መሰረት ለትግራይ ክልል “ይህን ያህል ገንዘብ ይደርሰዋል” ብሎ አንድ የተወሰነ የገንዘብ መጠን ላይ መድረስ ይኖርበታል?  የፈደራላዊው መንግስት የአስተዳደር መዋቅር የትግራይን ህዝብ በቀጥታ መድረስ በማይችልበት ሁኔታስ የበጀት ዕቅዱ ፋይዳስ ምንድን ነው?

መንግስት “የተናጠል ተኩስ አቁም” አውጆ መቀሌን ለቆ ከወጣ በኋላ የፌደራል መንግስቱን መዋጋቱን የቀጠለውና ከክልሉ ዘሎ በመውጣት ግጭቱን ወደ አማራና አፋር ክልሎች በማስገባት የንጹሃን ዜጎችን ህይወት እየቀጠፈና ንብረት እያወደመ ያለው አሸባሪ ተብሎ የተፈርጀው ትህነግ የትግራይ “ክልል” ከተባለው አካባቢ ወደ ሁለት ሶስተኛውን ያህል የመሬት ስፋት ብቻ ተቆጣጥሮ ይገኛል። ምድር ላይ ካለው ይህ ሃቅ ስንነሳ የህወሃት ስፍራው አና ድርሻው ምንድን ነው? “ክልሉን” በሙሉ በእጁ እንዳስገባና እንደሚያስተዳድር አድርጎ ለውይይት ከመቀመጤ በፊት ከነሳንቲሙ ቆጥሮ ሊለቀቅልኝ ይገባል ያለው በቢሊዮን የሚቆጠር የሁለት ዓመት “በጀት” ተቆጥሮ ሊሰጠው ነው? ይህንን “በጀት” መልቀቅ ይቅርና ከሌሎች ክልሎች ህዝብ በቀረጥ ስም የተሰበሰበን ገንዘብ ለህወሃት እንስጠው ብሎ ለውይይት ማቅረብ በራሱ የሞራል መሰረት የለውም።

ህወሃት በሰሜን እዝ ላይ ባደረሰው ድንገተኛ ጥቃት በተቀሰቀሰው ጦርነት፡ በመከላከያ ሰራዊቱ አባላት፣ በአማራና አፋር የጸጥታ ሃይሎች የተከፈለው መስዋዕትነት፣ ባልታጠቁ ሰላማዊ ዜጎች ላይ በተፈጸመው ጭፍጨፋ የፈሰሰው ደም ገና ባልደረቀበት ሁኔታ፡ የፈደራሉ መንግስት በቢሊዮን የሚቆጠር ብር ለትህነግ ያስረክባል ብሎ መገመትም፤ ማሰብም፤ ማመንም ለአዕምሮ ይከብዳል።  ይህ ብር ደግሞ  ለጤና፣ ለትምህርት፣ለውሃ ስልክ መንገድ እና ሌሎችም ተመሳሳይ የማህበራዊ አገልግልሎቶች ይውላል ወይስ የህወሃት ቅምጥል መሪዎች ፕላኔት ሆቴል ውስጥ ለሚዝናኑበት ወጪ መሸፈኛና ለታጣቂዎቻቸው ማሰልጠኛና ደሞዝ ክፍያ ይውላል የሚል ህጋዊ ጥያቄንም ያስነሳል። በመቀጠልም የፌዴራል ታክስ በማይሰበስብበትና የፌዴራል ግልጋሎት በማይሰጥበት ክልል ከሌሎች ክልሎች በቀረጥ ስም የሰበሰበውን ገንዘብ መንግሥት አሳልፎ የመስጠት ህጋዊ ስልጣንስ አለው ወይ የሚል ጥያቄም ያስከትላል። ሌላው ደግሞ በአሁኑ ወቅት ህወሃት የክልሌ አካል ነው የሚለው ሆኖም በቁጥጥሩ ስር ያልወደቁ ሰፊ ቦታዎች አሉ። እናም በማይቆጣጠራቸው እነዚህ ቦታዎች ላይ ለሚኖሩ ዜጎች ምንም ግልጋሎት መስጠት በማይችልበት ሁኔታ ውስጥ እያለ በነዚህ ዜጎች ስም እንዴት በጀት ይጠይቃል? የጠየቀው በጀት ቢለቀቅለትስ የእነዚህ ዜጎች ድርሻ እንዴት ወደ መቀሌ ይላካል የሚለው ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል።

እናም መቼም ይህ መንግስት ብዙ ያልተጠበቁ ነገሮችን አድርጓልና ህወሃት ድርድር ለመጀመር እንደ ቅድሚያ ሁኔታ ያቀረበውን ይህንንም ጥያቄ መንግሥት እንዴት እንደሚያስተናግደው አሁንም እርግጠኛ መሆን አይቻል ይሆናል። በመሆኑም በዚህ ጉዳዩ ላይ ኢትዮጵያውያን በአስቸኳይ ተወያይተውበት ሃሳባቸውን መንግስት እንዲያውቀው ማድረግ ይኖርባቸዋል።

በሌላ በኩል ትግራይ አንዷ የኢትዮጵያ አካል ናት። የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያዊ ነው። የፌደራል መንግስት ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሃላፊነት እንዳለበት ሁሉ ለትግራይ ህዝብም ሃላፊነት አለበት። ምናልባትም በአሁኑ ጊዜ በጦርነቱ ምክንያት ከዚያ አካባቢ ቀረጥ ስለማይሰበሰብ፡ የፌደራሉ መንግስት በጀት የመመደብ ግዴታ የለበትም ብሎ ማሰብ ይዳዳ ይሆናል።  ይህ ግን ከሞራል አንጻር  የሁላችንንም ሃላፊነት የዘነጋ አመለካከት ነው የሚሆነው። ከዚህም በላይ፡ ለትግራይ ህዝብ አለመጨነቅ፣ ችግሩን እንደ ችግራችን የመመልከት ሃላፊነት አለማሳየት፡ የትህነግን እና የውጭ ጠላቶቻችንን ተልዕኮ የሚያግዝ ርምጃ ነው የሚሆነው።

ሌላው የመንግስትንና ሀወሃትን አይን አፍጥጦ የሚያየው እና መንግሥትም ሆነ ህወሃት እንዳላዩ ቢሆኑም እንደጉም በኖ የማይጠፋው ፊት ለፊታቸው የተጋረጠው እውነታ ከሌላ ክልል በሃይልና በግፍ ተነጥቀው ወደ “ትግራይ ክልል” የተካለሉትን አካባቢዎች ጉዳይ በማናቸውም የፖሊሲ ውሳኔዎች ውስጥ ሊታይ የሚገባው መሆኑ ነው።  ይህ ነጥብ በ”በጀቱ” አመዳደብ ላይም እጅግ ትልቅ እንደምታ ያለው ሃቅ ነውና መልሶ መላልሶ ማንሳት ተገቢ ይሆናል። ለመሆኑ በመንግስት የተገለጸው የገንዘብ መጠን ለነዚህ ስፍራዎች የሚከፋፈለው፣ እንዲደርስ የሚደረገው እንዴት ነው? የተወሰነውን በጀት በሙሉ ለትህነግ አስረክቦ በአሁኑ ወቅት በህወሃት ቁጥጥር ሥር ያልሆኑትና ከህውሃት የዘመናት አፓርታይድ ጭቆና ራሳችንን ነጻ አውጥታናል ያሉ ዜጎች ድጋሚ በትህነግ እጅ እስኪወድቁ ድረስ “በጀቱ”ን ህወሃት በአደራ መልክ ይይዝላቸዋል ወይም ይነግድበታል?

ወጣም ወረደ፡ ማዕከላዊው መንግሥትም ሆነ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በትህነግ ተይዘው የነበሩ ሆኖም አሁን በህወሃት ቁጥጥር ስር ባልወደቁት አካባቢዎች የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ከፌደራል መንግሥት በስሙ የተመደበለት በጀት እንዴት ሊደርሰው ይገባል በሚለው አብይ ጉዳይ ላይ ውይይት ማድረግና ፍትሃዊ የሆነ ውሳኔ ላይ መድረስ ያስፈልጋል።

አንድ ነገር ለመጨመር ያሀል! መቼም ትህነግ ለገንዘብ ያለው ፍቅር ስለሚታወቅ የሚመደበው ገንዘብ ወደ ክልሉ አካውንት በባንክ አይተላለፍለትም ተብሎ ይታሰባልና ገንዘቡን ለሚታሰብለት አላማ እንዲውል ለማድረግ ሌላ አማራጭ ማየት ግዴታ ይሆናል።  ይህም በጦርነት ቀጠና ውስጥ ላሉት ወገኖች  በተወሰነው ገንዘብ ምግብ፤ መድኃኒት፤ አልባሳት፤ ሁኔታው ፈቅዶላቸው በእርሻ ላይ መሰማራት የሚችሉ ገበሬዎች ካሉም፡ ማዳበሪያ እና ሌሎች ለእርሻ ግብዓት የሚውሉ ቁሳቁሶች የሚደርሱበትን መንገድ በብርቱ ማሰብ እና ማመቻቸት ያስፈልጋል። በእርግጥ ይህን ዕርዳታ ለማድረስ በሚደረገው ጥረት እና በሚዘረጋው ስርዓት ትህነግ የክልሉ አስተዳዳሪ የመሆን እድል ካጋጠማት በተቻላት ሁሉ ዕርዳታው ለህዝቡ እንዳይደርስና ስልጣኗን ለሚጠብቁላት ወታደሮቿና ሚሊሻዎቿ ብቻ እንዲሆን መስራቷ አይቀርም።  አሁን በሁሉም አቅጣጫዎች ስለተከበበች እንደ ድሮው የዕርዳታ እህልና ሌሎች እህል ነክ ያልሆኑ መገለገያዎች ሽጦ መሳሪያ መግዛት ቀላል አይሆንላትም።  ስለዚህ፡ ቢያንስ ቢያንስ ህዝቡ እንዳይደርሰው በማድረግ የበለጠ ለማነሳሳት እና ጦርነቱን ለማባባስ ትጠቀምበት ይሆናል። በቅርቡ አንድ ቤተሰብ ወደጦር ሜዳ የሚዘምት ወጣት ካላቀረበ የእርዳታ እህል እንድማያገኝ ወስና ወጣት ህጻናትን ከወላጆቻቸው እየነጠቀች ስለመሆኑ እየተሰማ ነው።

እናም ከሞትና እስር በተረፉት ጥቂት የህወሃት አመራሮች የቀረበው የሁለት አመት በጀት ይለቀቅልን ጥያቄ ስህተትና ተቀባይነት የለውም እንላለን።

የኢትዮጵያ ፊስካል ፌዴራሊዝም ይሄንን ማድረግ አይፈቅድም። ይህ ሊሆን የሚችለው ህወሃት የኢትዮጵያ የፌዴራል ተቋማት ወደ ትግራይ የሚመለሱበትንና ግልጋሎት መስጠት የሚችሉበትን ሲፈቅድ ነው።

ይሁንና ሰብአዊ ድጋፍ ማድረግና በየትኛውም ቦታ ያሉ ኢትዮጵያውያንን መደገፍ ግን አግባብ ነው። ይህንን አታድርጉ የሚል የኢትዮጵያ ፊስካል ፌዴራሊዝም የለምና።

Share