Logo

Ethiopian Teachers have lost a great friend

April 7, 2008

ሚስተር እስቲቭ ሲኖት በድንገተኛ ሞት ተለዩን!!

የእንግሊዝ (UK) ብሔራዊ መምህራን ማህበር (NUT) ወደር የሌላቸውን መሪውን ድንገተኛ ሞት ነጠቀው!!!

የኢትዮጵያ መምህራን አንድ ታላቅ ወዳጅ አጡ!!!

ሰላም ወዳዱ የዓለም አቀፉ ህብረተሰብ አንድ በተግባር የተፈተነ ለሠራተኛ/ለሙያ ማህበርና ለሰብአዊ  መብቶች መከበር የቆመ እውቅ ተሟጋች አጋሩን አጣ!!!


የኢመማ ሥ/አሰፈጻሚ ኮሚቴ

መጋቢት 28 ቀን 2000 ዓ. ም.(06 -04-08)

አዲስ አበባ

የእንግሊዝ (UK) ብሔራዊ መምህራን ማህበር (NUT) ዋና ፀሐፊ ሚስተር እስቲቭ ሲኖት ትናንት መጋቢት 27 ቀን 2000 ዓ. ም. (05 -04-08) በድንገተኛ ሞት ከዚህ ዓለም መለየታቸውን ዋናው ጽ/ቤት ብራስልስ ከሆነው ከEI እና ለንደን ካለው ከማህበራቸው ዋናው ጽ/ቤት እንደዚሁም በስደት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወዳጆቻችን በማከታተል በስልክ ሲነገረን እጅግ አስደንጋጭና ዘግናኝ ስለሆነብን የሰማነውን አምኖ መቀበል ተስኖን ነበር፡፡ መርዶው ያሳደረብን መሪር ሀዘን አካላችንን አቀዝቅዞና ተንፋሻችንን አሳጥሮ ልባችን ወደውስጥ እንዲደማ አድርጎታል፡፡ መሸከም የማንችለው የልብ ስብራት አሳድሮብናል፡፡

የእንግሊዝ (UK) ብሔራዊ መምህራን ማህበር (NUT) አባላትን ወደር የሌላቸውን መሪውን ሞት ሲነጥቃቸው የኢመማ አባል መምህራንን አንድ ታላቅ ተቆርቋሪ ወዳጃቸውን አሳጥቷቸዋል፡፡ ሰላም ወዳዱ የዓለም አቀፉ ህብረተሰብ በተለይም የዓለም መምህራን ማህበር (EI) እና በዓለም ዙሪያ ያሉ አባል ድርጅቶቹ አንድ ለሙያ ማህበራትና ለሰብአዊ መብቶች መከበር ሲባል የሀገር እርቀት፤ የባህል ልዩነትና የችግሮች ውስብስብነት ሳይበግረው ማንኛውንም መስዋእትነት ከ1975-2008 ሲከፍል የኖረ አንድ በተግባር የተፈተነ እውቅ አጋር እንዳጡ ተሰምቶናል፡፡

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበርና የUK ብሔራዊ መምህራን ማህበር የዓለም መምህራን ማህበር አባል ድርጅቶች እንደመሆናቸው ለ59 ዓመት የዘለቀ ወዳጅነትና የሥራ ግንኙነት አላቸው፡፡ የሁለቱ አቻ ማህበራት ይበልጥ መቀራረብና የላቀ ትርጉም ያለው ሥራ በጋራ መሥራትና መረዳዳት የጀመሩት ሚስተር ሲኖት በNUT ውስጥ የረዳት ዋና ፀሐፊነቱን ሥልጣን ከያዙ በተለይም የኢትዮጵያ መንግሥት በኢመማ ላይ እያደረሰ ያለው ማዋከብና አፈና እስከ ግድያ ከዘለቀበት እ.ኤ.አ. ከ1997 ዓ. ም. ጀምሮ ነው፡፡ እስቲቭ ማህበሩንና መንግሥትን በማቀራረብ ችግሩን በውይይት ለመፍታት ይህ ቀረው የማይባል እልህ አስጨራሽ ጥረት እስከለተሞታቸው ድረስ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ከ1999 እስከ የካቲት 2008 ባለው 9 ዓመት ውስጥ ለዚሁ ጉዳይና የኢመማን ድርጅታዊ አቅም ለማጎልበት 3 ጊዜ የዓለም መምህራን ልዑክ አባል ሆነው፤ 2 ጊዜ ደግሞ ማህበራቸውን ወክለው በድምሩ 5 ጊዜ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡

እስቲቭ በነዚህ በኢትዮጵያ ባደረጓቸው ቆይታዎች ‹ትክክለኛ መረጃ ኃይል ነው፤ ማየት ማመን ነው› በሚለው መርሆአቸው መሠረት በአዲስ አበባ ብቻ ሳይወሰኑ በደቡብ እስከ አዋሳ፤ በሰሜን ምዕራብ እስከ ባህርዳር ከተሞች ተጉዘው መምህራንን አነጋግረዋል፡፡ የመምህራን ስብሰባዎችን ተሳትፈዋል፡፡ በአንዳንድ ት/ቤቶች ተዘዋውረው በመጎብኝት የመማር ማስተማሩን ሂደት ያለበትን ችግር በተለይም የተማሪዎችን መጎሳቆል፤ መታረዝና በአንድ ክፍል ከ80 እስከ 100 ተማሪዎች በተሰባበሩ ጣውላዎችና በተኮለኮሉ ድንጋዮች ላይ ተቀምጠው በማየታቸው አዝነዋል፡፡ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህፃናት የዚሁንም ያክል የመማር እድል እንዳላገኙ አጢነዋል፡፡ ለዕለት ጉርስ ሲሉ ያለ እድሜያቸው በጉልበት ሥራ የተሰማሩ ልጆች ሁኔታ መሸከም ከሚችሉት በላይ የሆነ የሀዘን ድባብ ጥሎባቸዋል፡፡

ስለሆነም በሀገራቸው በእንግሊዝ መንግሥትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ተሰሚነት በመጠቀም በአንድ በኩል ለኢትዮጵያ የትምህርት ሥራና ለመሠረታዊ ሰብአዊ ፍጆታ የሚውል እርዳታ እንዲጨመርና እርዳታው ለታቀደው ተግባር በትክክል መዋሉን ግን ለጋሽ ወገኖች የቅርብ ክትትል እንዲያደርጉ ተማጽነዋል፡፡ ያሰቡትን ያክል ባይሆንም ተሳክቶላቸዋል፡፡ በሌላም በኩል የኢመማን ችግር የመፍታት ተልኳቸውን ለማሳካት ይጠቅማሉ የሚሏቸውን አምባሳደሮችና በተለያየ ደረጃ ያሉ ዲፕሎማቶች፤ ሀገር በቀልና እንደ ILO እና UNESCO የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የመፍትሄው አካል እንዲሆኑ በማግባባት፤ እንደዚሁም ሀገሪቱ ልታከብር የተስማማችባቸውን ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳኖች (ለምሳሌ ILO ኮነቬነሽን ቁ. 87 እና ቁ. 98) በማክበር በኢመማ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት እንዲታቀቡ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊን ጨምሮ አግባብ ያላቸውን የመንግሥት ባለስልጣናት በሮች ያለመታከት ሲአንኳኩ ቆይተዋል፡፡

እስቲቭ የማህበሩ አመራር በሰጥቶ መቀበል መርህ መሠረት በውይይት ችግርን የመፍታት ክሎት እንዲኖረው የሀሳብ፤ የማቴሪያልና የቴክኒክ ድጋፍ ከማድረጋቸው ባሻገር የኢመማንና አባላቱን ችግር ለመፍታት ካላቸው ብርቱ ጉጉት የተነሳ በመንግሥት ድጋፍና ጊፊት የሚንቀሳቀሱትን የተለጣፊ ማህበራት መሪዎችን ጭምር የመንግስትን ስልጣን መከታ አርገው በሙያ ባልደረቦቻቸውና በወገኖቻቸው ላይ ግፍ ከመፈጸም እንዲታቀቡ ተደጋጋሚ ምክር ሰጥተዋል፡፡

ሚስተር እስቲቭ ሲኖት በዚህ አይነት የደከሙበትን ሥራ ሁሉ ሙሉ በሙሉ ግቡን መቶ እንዳያዩት ሞት ቢቀድማቸውም 1ኛ – የኢመማና የአባላቱ ችግር ምን እንደሆነ፤ ዘላቂ መፍትሄውም ምን መሆን እንዳለበት የዓለም አቀፉ ህብረተሰብ በቂ ግንዛቤ እንዲይዝና ከኢመማ ጎን እንዲቆም በማድረግ የተዋጣለት ሥራ ሠርተዋል፡፡ 2ኛ – የማህበሩ ረዳት ዋና ፀሐፊ የአቶ አሰፋ ማሩ ግድያ ጉዳይ እስካሁንም ለፍርድ ባይቀርብም ታስቦበት ወይም በማን አለብኝነት የተፈጸመ የፖለቲካ ግድያ እንጂ ህግ የተላለፈ ወንጀለኛ ወይም የተራ ግጭት ሞት እንዳልሆነ ዓለም እንዲያውቀውና ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ መለስ ገዳዩን ለፍርድ ለማቅረብ ቃል እስከመግባት በማድረጉ ሥራ እስቲቭ የጎላ ሚና ተጫውተዋል፡፡ 3ኛ – የማህበሩ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታዬ ለ15 ዓመት ተፈርዶባቸው ከ6 ዓመት እስራት በኋላ እንዲፈቱ ዋና ምክነያት ነው ብለን የምናምነውን የዓለም አቀፍ ጫና በማስተባበር የእስቲቭ አስተዋጽኦ ቀላል አልነበረም፡፡ 4ኛ – የአርበኞች ግንባር በሚባል ድርጅት ውስጥ ተሳትፎ ይኖራቸዋል በሚል ጥርጣሬ በጥቅምት 2005 ጀምሮ ከዓመት በላይ ታሥረው ከፍተኛው ፍ/ቤት በዋስ እንዲወጡ ከበየነላቸው በኋላ የቻሉት ገንዘብ አስይዘው ወይም የሰው ዋስ ጠርተው ሲፈቱ ከኢመማ አባላት መምህር ብርሀኑ አባዴቢሳ፤ መምህር ወልዴ ዳና እና ባለቤታቸው ወ/ሮ ውቢት ሌጋሞ በነፍስ ወከፍ ብር 5000 ሺህ የሚያስይዙት ስላልነበራቸውና ኢመማም ሊረዳቸው ስላልቻለ ከወር በላይ ሳይፈቱ መቆየታቸውን እስቲቭ ሲኖት እንደሰሙ ማህበራቸው (NUT) ከፍሎላቸው በዋስ እንዲፈቱ አርገዋል፡፡ 5ኛ – በአንድ በኩል ከአሠሪው መ/ቤት ጋር በተደረገ ስምምነት ከክልል ተዛውረው የመጡ ያመራር አባላትን ያለፍርድ ከሥራ በማገድ፤ በሌላ በኩል በአባላት መዋጮ ማህበሩ እንዳይጠቀም ተደርጎ በገንዘብ ችግር የማህበሩ ህልውና እንዲያከትም በመንግሥት ካድሬዎች የተዶለተበትን ሴራ ለመስበር እስቲቭ ሲኖትና ማህበራቸው ያደረጉት ድጋፍ ታሪክ ምንጊዜም በመልካም አርአያነቱ ሲዘከረው የሚኖር የሶሊዳሪቲ መግለጫ ነው፡፡ 6ኛ – የማህበሩ ዋና ፀሐፊ አቶ ገሞራው በሁኔዎች አስገዳጅነት ለንደን በስደት በቆዩበት ወቅት በግላቸው ከነቤተሰቦቻቸው እንዳይቸገሩና ሞራላቸው እንዲጠበቅ ብሎም የሀገር ቤቱን ትግል ለማገዝ ያደርጉት ለነበረው እንቅስቃሴ ሁለገብ ድጋፍ ሲቸሯቸው ቆይተው በታህሣስ 2004 ወደ ሀገራቸው ሲመልሱም ከAObው አንድሬ ዱሞ ጋር ሆነው እስቲቭ ወደ ኢትዮጵያ አብረው በመምጣታቸው የዲፕሎማቱ ህብረተሰብ ለሁኔታው ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጠውና መምህራንም መብት የማስከበር የትግል ስሜታቸው እንዲጠናከር ማድረግ ችለዋል፡፡ 7ኛ – ባጭሩ ለኢትዮጵያ መምህራን ብቻ ሳይሆን የእርሳቸውን ድጋፍ ለሚሹ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ላሉ ሁሉ ለምሳሌ ለኮሎምቢያ፤ ለፓለስታይን፤ ለኢራቅ፤ ወዘተ ሀገሮች መምህራን እስቲቭ ሲኖት መተኪያ የሌላቸው ለተቸገረ ፈጥኖ ደራሽ የፍቅር ተምሳሌት፤ የዓላማ ጽናት ስብእና ባለቤትና የብሩህ ተስፋ ምንጭ ነበሩ፡፡

እኝህ ለሰው ልጆች ሰላምና ፍትህ የቆሙ፤ አንባገነኖችን ፊት ለፊት የሚጋፈጡ፤ እጅግ ሩህሩህና ታላቅ ጀግና ሰው በUK ሊቨርፑል በ1951 ዓ. ም. ተወለዱ፡፡ በ1974 የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሶሻል ሳይንስ ከሚድልሴክስ ፖሊቴክኒክ የተመረቁ ሲሆን እንደዚሁም በ1975 ከኤጅ ሂል ኮሌጅ የPGCE ስለጠና ወስደዋል፡፡

ሚስተር ሲኖት የሚወዱትና የላቀ ማህበራዊ ከበሬታና አድናቆት በሀገራቸው ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ዘንድ የተቀዳጁበትን የሰብአዊነት ትምህርት የማስተማር ሥራ የጀመሩት በ1975 ዓ. ም. በሊቨርፑል ቶክስትስ ባለው ሾርፊልድስ ኮምፕሪሄንሲቭ ት/ቤት ነበር፡፡ በ1979 ወደ ብሮውተን ከፍተኛ ደረጃ ት/ቤት ተዛውረው የኢኮኖሚክስና የቢዝነስ ጥናቶች ዘርፍ ተጠሪ ሆነው ለNUT ረዳት ዋና ፀሐፊነት እስተመረጡበት እስከ 1994 ዓ. ም. ድረስ በተጠቃሚው ህብረተሰብ አድናቆት የተቸረው ፍሬአማ አገልግሎት አበርክተዋል፡፡

እስቲቭ በNUT ውስጥ በተለያ ጊዚያት የማህበሩ ብሄራዊ ሥራ አስፈጻሚ አባል፤ ፕሬዝዳንት፤ ረዳት ዋና ፀሐፊና ከ2004 ጀምሮ ደግሞ በአባላቱ ከፍተኛ ድምጽ ለዋና ፀሐፊነት ተመርጠው እስከ እለተሞታቸው አፐሪል 5 ቀን 2008 ድረስ ማህበሩ የተጣላባቸውን ተደራራቢና ከባድ የውስጥ ሀላፊነትና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት በፍጹም ቅንነት፤ በታማኝነትና በብቃት ሲወጡት ቆይተዋል፡፡ የNUT ድርጅታዊ ጥንካሬ፤ የአባላቱ የአንድነትና የትግል ሰሜት በእስቲቭ ያመራር ዘመን ከምንጊዜውም የላቀ ስለመሆኑ ዘንድሮ ከማርች 21-25 ቀን 2008 በማንችስተር ከተማ የተካሄደው የጠቅላላ ጉባኤው የውይይት ሂደትና በሙሉ ድምጽ ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች ህያው መረጃዎች ናቸው፡፡

ሚስተር እስቲቭ ሲኖት ባለትዳር፤ የሁለት ልጆች አባትና የሁለት ህፃናት አያት ነበሩ፡፡ ሰው አፍቃሪ፤ ለተቸገረ ሁሉ ፈጥኖ ደራሽና አርቆ አሳቢ ሰው ነበሩ፡፡ እንደ እስቲቭ ያሉ ሰዎች ቢበራከቱ ይች ዓለም የሰዎች ሁሉ ጥሩ መኖሪያ መሆን በቻለች ነበር፡፡ አለመታደል ሆኖ እስቲቭ ገና በ56 ዓመታቸው እሩጫቸውን ጨረሱ፡፡ ከእንግዲህ እኛ ወደሳቸው እንጂ እሳቸው ወደኛ ስለማይመጡ ልዑል እጊዚአብሔር ነፍሳቸውን በተቀደሰ ስፍራ እንዲያኖርልን እየጸለይን፤ ለቤተሰባቸው፤ ለዘመድ አዝማድ፤ ለNUT አባላትና ለትግል አጋሮቻቸው ሁሉ ብርታትንና መጽናናትን እንመኛለን፡፡ እስቲቭ የጀመሩትንና ብዙ የደከሙበትን የሰብአዊ መብቶች መከበር፤ የሰላም፤ የፍትህና የእደገት ዕቅድ ከዳር ለማድረስ ቃል እንገባለን፡፡

የአሟሟታቸውን ሁኔታና ቀጣዩን ዝርዝር ሂደት ለማወቅ የማህበሩን ዌብ ሳይት www.teachers.org.uk ይከታተሉ፡፡

ገሞራው ካሣ

ዋና ፀሐፊ

የመ.ሣ.ቁ. 1639

Tel: +251 11 552 4668 (ቢሮ)፣ 011 320 6055 (ቤት)፤ 0911 471789 (ሞባይል)

Email: gemorawka@yahoo.com

Click here for pdf version

Share

5 comments on “Ethiopian Teachers have lost a great friend

 1. With no doubt, it is a very sad day for Ethiopia, friends of Ethiopia and those who believe in Human and Trade Unions Rights.

  In Mr Steve’s death, i believe, Ethiopians in general and ETA(Ethiopians Teachers Association)in particular has lost a very humane, committed,passionate, respected, articulate, valuable and trustworthy friend. Put simply, Mr Steve’s love and passion to Ethiopia and Ethiopians would make him irreplacable.

  Mr Steve’s death is too much to accept particularly to those Ethiopians who live in the UK and who have witnessed the positive deeds of Mr Steve first hand. Who is going to forget Mr Steve’s inspiring speeches in Ethiopian public meetings, vigils, demos, etc?

  I think, it goes with out saying that the Ethiopian community in the UK has to prepare a fitting farewell to this hero of Ethiopia.

  May God bless his soul.

  Yeneneh Woldegebriel.

 2. When I heard Mr Steve’s untimely death, it seemed clear to me that even God is not with us, Ethiopians, at the moment.

  What a great loss! Words can not express my sorrow.

  May God rest Mr Steve’s soul in peace.

 3. In my age and experience, i have never seen a foreigner as devoted to the cause of Ethiopia as Steve is.

  What a loss to Ethiopia!

  May the Almighty God bless his soul.

 4. My deepest condolences on the loss of a person who was a great friend of Ethiopia.
  May his soul rest in peace.

 5. Ethiopians lost one great friend and the best&honest Human Right defender. My sincere condolences to his bereaved Family.

Comments are closed