Logo

“በአርባ ምንጭ ከተማ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ታላቅ የሃይማኖት አባት ታሰሩ”

August 27, 2008

ቤተክርስቲያናቱ በሚያስገቡት ገቢ ምክንያት ከጋሞ ጐፋ ዞን ሊቀጳጳስ አባ ቶማስና ከዚህ ቀደም የቤተክርስቲያኖቹን ከምዕመናን የሚገኝ ገንዘብ በመመዝበር ከሚታወቁት የተወሰኑ የሰበካ ጉባኤ አባላት ጋር የተጋጩት አባ ሚካኤል፤ ከዛሬ አንድ ወር በፊት ነው መሣሪያ በታጠቁ ኃይሎች ተይዘው አርባ ምንጭ ከተማ ውስጥ ወደሚገኘውና ሸቻ ደረቅ ጦቢያ ተብሎ ወደሚታወቀው የእስር ጣቢያ የተወሰዱት፡፡

የሚያስተዳድሩዋቸው ቤተክርስቲያናት ገቢ እንዳይዘረፍ በወሰዱት አቋምና ከምዕመናን ጋር በፈጠሩት የመንፈሳዊ አባትነት ሕብረት ምክንያት “የአካባቢውን ሰላም ለማወክ ሕዝቡን አነሳስተዋል” በሚል ተወንጅለው ለእስር የተዳረጉት አባ ሚካኤል፤ ለአምስት ጊዜያት ያህል በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ እና በጋሞ ጐፋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት የቀረቡ ቢሆንም፤ በጠበቃቸው አቶ ወንዱ ካይሮ በኩል ያቀረቡት በዋስ የመፈታት ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡

ምቹ ባልሆነውና ለእስረኞች የሚሆን ቀለብ በማይሰፈርበት የእስር ጣቢያ ወዳጅ ዘመድ እንዳይጐበኛቸው በተከለከሉበት ሁኔታ የታሰሩት የቤተክርስቲያኒቱ አለቃ፤ /ዛሬ/ ነሐሴ 20 ቀን 2ሺ ዓ..ም. እንደኢትዮጵያ አቆጣጠር ጠዋትና ከሰዓት በኋላ ጉዳያቸውን እያየ ባለው የጋሞ ጐፋ ዞን ከፍተና ፍ/ቤት የቀረቡ ቢሆንም /ለነገ/ ነሐሴ 21 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ የተያዘላቸው ከመሆኑ በቀር ከእስር ነፃ ሊሆኑ የሚችሉበት ምላሽ ሊያገኙ አለመቻላቸውን ጠበቃቸው አቶ ወንዱ ካይሮ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡

አባ ሚካኤል ከዞኑ ሊቀ ጳጳስ ጋር ለአንድ ዓመት ያህል የዘለቀ አለመግባባት የፈጠሩ መሆናቸው ሲታወቅ፣ በዚህም ምክንያት ወርሃዊ ደሞዛቸው ታግዶ፤ አይነሱብንም በሚለው ምዕመን መዋጮ ደሞዝ እየተቆረጠላቸው መቆየታቸውን የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች አስታውቀዋል፡፡

አባ ሚካኤልና ጥቅማችን በእሳቸው ጫና ምክንያት ተጓድሎብናል የሚሉት ወገኖች ቅራኔያቸውን እንዲፈቱ ጠ/ቤተክህነት ጣልቃ የገባችበት ሁኔታ ቢኖርም የአካባቢው ምዕመናን ከፍተኛ ድጋፍ ያላቸው አባ ሚካኤል ግን መታሰራቸው አልቀረም፡፡

ከእሳቸው ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከ50 የሚበልጡ የሀገር ሽማግሌዎች ከ50፣ የቤት እመቤቶች፣ የመንግስት ሠራተኞች እና ወጣት የቤተክርስቲያኒቱ ምዕመናን መታሠራቸውን የአባ ጠበቃ ለጋዜጠኞች ከሰጡት ቃል መገንዘብ ተችሏል፡፡

አባ ሚካኤል ከተያዙበት ቀን ጀምሮ የሲቀላ ደብረ ኃይል ቅ/ገብርኤል ቤተክርስቲያንን መንፈሳዊ አገልግሎት መስጠት አቁሟል፡፡ በእስር ላይ ከሚገኙት ሰዎች መካከልም፡-

አቶ ዘሩ ጥላሁን፣ አቶ ጌታቸው ጦና፣ አቶ ዘነበና ወ/ሮ ጦቢያሽ የተባሉት እንደሚገኙበትም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ስለጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ሻለቃ ታዬ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለሁም ብለዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ማምሻውን ከወደ አርባምንጭ የደረሰን ዜና በመቶዎች የሚቆጠሩ የከተማው ነዋሪ ምዕመናን የሀይማኖት አባታቸው አባ ሚካኤል ታደሰ እንዲፈቱ ለመጠየቅ ወደ ጋምጐፋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አካባቢ አምርተው የተቃውሞ ድምፅ ማሰማታቸውን እና ከፖሊስ ጋር መጋጨታቸውን አመልክቷል፡፡ አያይዞም አባ ሚካኤል በነገው ዕለት /ነሐሴ 21 ቀን 2000 ዓ.ም../ ከሚገኙበት የእስር ጣቢያ ወደ ደቡብ ሕዝቦች መንግስት ወህኒ ቤት ሊያመሩ እንደሚችሉም ጠቁሟል፡፡

Share

One comment on ““በአርባ ምንጭ ከተማ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ታላቅ የሃይማኖት አባት ታሰሩ”

Comments are closed