Logo

በምርጫ ያለመሳተፍ ትግል

ballotBox
May 26, 2009

በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ እና የፖለቲካ ፓርቲም ሳይሆን ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ግፊት በማድረግ ሚና የሚጫወት ድርጅት፤ ወይም ሥልጣን ላይ ባለና በተቃዋሚነት በሚገኝ የፖለቲካ ድርጅት አማካኝነት የሚፈጠር የፖለቲካ እንቅስቃሴና የሚያስከትለው ተፅዕኖ በጣም የተለያየ ነው። የሆኖ ሆኖ የፖለቲካ ተሳትፎ ስንል እነዚሕና ሌሎችም በፖለቲካው ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉትን ክፍሎችንና የሚያከናውኑትን እንቅስቃሴ የሚመለከት ነው። በቀላል የሂሳብ አገላለፅ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ስንል የፖለቲካው ንቁ ተሳታፊ የሆኑ ሰዎች በሚያደርጉት ክንዋኔ ሲባዛ ማለት ነው። ስለዚሕ የፖለቲካ ተዋናይ የሆኑ ክፍሎች እንቅስቃሴያቸው በጨመረ ቁጥር በሕብረተሰቡ ዘንድ ያለ የፖለቲካ ተሳትፎ እያደገ ይሄዳል። ነገር ግን ሕዝባዊ ተሳትፎ ያልዳበረበት የፖለቲካ ሂደት በአነስተኛ የፖለቲካው አሽከርካሪዎች ብቻ የሚዘወር መሆኑን ስለሚያሳይ የሥርዓቱን በጎነት አጠያያቂ ያደርገዋል።

በአገራችን በተለምዶ የሚራመድ አንድ የፖለቲካ አስተሳሰብ ቢኖር በምርጫ ያለመሳተፍ ብሂል ነው። በመሠረቱ የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ መደበኛ ሥራ ሕዝቡን ወደትግሉ እንዲመጣና በቆመላቸው ዓላማዎች ዙሪያ ድጋፉን እንዲሰጠው ማበረታታት ነው። ራሱን በአገሪቱ ውስጥ ከተሰለፉት የፖለቲካ ኃይሎች ሁሉ ለሕዝቡና ለአገሪቱ የተሻለ አጀንዳ እንዳለው በማሳየት ሥልጣን ይዞ እነዚሕን ዓላማዎቹን ለመፈፀም እንዲችል ሕዝቡ እንዲረዳው ይቀሰቅሳል። በምርጫ ወቅት ድምፅ ሰጪው ዜጋ ሁሉ ካርዱን እንዲያስገባለት ያለመታከት ያመለክታል። በዚሕ ሂደትም በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች የሕዝቡን የፖለቲካ ተሳትፎ እያሳደገ ይሄዳል። በኛ አገር ግን አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች ሲያራምዱት የቆዩትና አሁንም እየተቀጠለበት ያለ የትግል አቅጣጫ ከዚሕ የተለመደ መደበኛ የድርጅቶች ሚና ለየት ያለ ሆኖ እናገኘዋለን። ምክንያቱም በምርጫ ያለመሳተፍ ትግል በመሆኑ ነው።

እነዚሕ ተቃዋሚዎች የሚያቀርቡት ክርክር ገዥው ፓርቲ በጣም አፋኝና አምባገነን ስለሆነ በምርጫው ሂደት መካፈል ዋጋ የለውም የሚል ነው። ባለሥልጣኑ ፓርቲ ብቻ የሚያሸንፍበትን መንገዶች ለራሱ ባመቻቸበትና፤ ተቃዋሚዎች እንደልባቸው እንዳይንቀሳቀሱ ሁለገብ መሰናክሎችን ባስቀመጠበት ሁኔታ፤ ተወዳድረን አሸናፊ እንደማንሆን እየታወቀ ወደ ውድድር መግባት አያስፈልግም ይላሉ። እንዲያውም ትክክለኛና ፍትሃዊ ምርጫ በማይካሄድበት ሁኔታ በምርጫ መሳተፉና ያገኙትን ትንሽ መቀመጫ ይዞ ወደ ፓርላማ መግባት የገዥውን ፓርቲ ሕጋዊነት ለማፅደቅ የሚደረግ ተባባሪነት ስለሆነ ሊወገዝ ይገባዋል ብለው ያምናሉ። ሕዝቡም የሚወራውን የምርጫ ወሬ ችላ ብሎ ትቶ በምርጫ ቀን ወደጣቢያዎች እንዳይሄድ ይቀሰቅሳሉ። ከዚሕ ከረር ብለውም የተቋቋሙትን መንግሥታዊ ተቋሞች ብቻ ሳይሆን የገዥውን ጨምሮ በምርጫ የሚካፈሉትን ተቃዋሚ ፓርቲዎችም እውቅና ሊሰጣቸው አይገባም ብለው እስከማሰብ ይዘልቃሉ። በነዚሕ ኃይሎች አስተሳሰብ ጠንካራና ሃቀኛ የሆነ ተቃዋሚ የሚለካው ገዢው ፓርቲ የሚያዘጋጃቸውን የምርጫ ሂደቶች ርግፍ አድርጎ በመተውና በፓርላማውም ባለመግባት ነው። ብቻ የሥርዓቱን መጥፎ ገፅታዎች ለሕዝቡ በጠነከረ ቋንቋ እያጋለጡና ለውጭ መንግሥታት እያሳጡ በመቀመጥ በሂደት መንግሥትን ለማዳከም ይቻላል የሚል ግንዛቤ አለ።

ነገር ግን ይኽ አካሄድ እስካሁን ድረስ እንደተባለው ያስገኘው መፍትሔ አይታይም። እንዲያውም የሕዝቡን የፖለቲካ ተሳትፎ እያጠበበ በመሄድ ገዢውን ፓርቲ ያለጠንካራ ተቃዋሚ ብቻውን እሮጦ እንዲያሸንፍ እድል ሲሰጠውና ሲያደነድነው ነው የቆየው። አንድ የፖለቲካ ድርጅት ሕዝብን በተገኘው ሕጋዊ ቀዳዳ በማሰባሰብ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ማሳተፍና ትግሉን እያጎለበተ መሄድ ይገባዋል። ነገር ግን የገዢውን ድርጅት ጥፋት ብቻ ማጋለጥን ለትግሉ ብቸኛ መኖ አርጎ የራስን የማደራጀትና ለምርጫ የማዘጋጀትን ሥራ ሳይሰሩ መቀመጥ በራስ ላይ ድክመትን መጋበዝ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ፓርቲ ሃላፊነትን ያለመወጣትም ጭምር ነው። የፖለቲካ ድርጅት አይነተኛ ዓላማ በምርጫ አሸንፎ ሕጋዊ ሥልጣንን መረከብና የያዛቸውን መርሐ-ግብሮች መፈፀም ሆኖ ሳለ በምርጫ ያለመሳተፍ ትግል እንዴትስ እንደ ትግል ሊቆጠር ይችላል? ምክንያቱም ራስን ከፖለቲካ ሂደቱ ማግለል ማለት ነው። ችግሩን የበለጠ የሚያሰፋው ደግሞ ሌሎች ድርጅቶችም እነሱን መስለው ከትግሉ ሸሽተው እንዲቆሙና ሕዝቡም ለሚፈልገው ለውጥ ማድረግ ካለበት የምርጫ ተሳትፎ እንዲርቅ የሚያደርጉት ወከባ ነው። ‘በሰው ምድር ልጇን ትድር’ እንደሚባለው የራሳቸውን የፖለቲካ ፕሮግራም አዘጋጅተው ትግላቸውን በሰላማዊ የምርጫ ስርዓት ለማጎልበት ቆርጠው በተነሱ ድርጅቶች ላይ ፈራጅ በመሆን አጉል ተፅዕኖ ለመፍጠር መጣጣር የድርጅቶችን ነፃነት ያለማክበር ይሆናል። ባጠቃላይ በምርጫ አልሳተፍም ብሎ መቀመጥ ከላይ እንደጠቆምኩት ዲኖሚኔተሩን በዜሮ ማባዛት ስለሆነ ውጤቱ ዜሮ የፖለቲካ ተሳትፎ ማለት ነው። ስለዚህ በቂ የሆነ የፖለቲካ ተሳትፎ የሌለበት ሥርዓት አምባገነንነትን ያንፀባርቃል ካልን እነዚሕ ፀረ-ምርጫ ድርጅቶች አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ለዚሕ አይነት ሥርዓት መቀጠልና መጠናከር እገዛ ማድረጋቸው ግልፅ ነው።

በሌላ በኩል ግን አንድ ፓርቲ ምርጫን የሚያስብ ከሆነ ከተወዳዳሪዎቹ ሁሉ በልጦ ለመገኘት ዘርፈ-ብዙ ጥረቶችን ማድረግ ስለሚኖርበት ለአፍታ እንኳን የማያስቀምጥ የትግል እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገባ ይገደዳል። ይኽ ደግሞ የእውነተኛ የፖለቲካ ፓርቲ ባሕርይና ተግባር ነው። ፓርቲው በሕብረተሰቡ ውስጥ ሰርጾ እንዲገባ ጠንካራ ድርጅታዊ እንቅስቃሴ ማዋቀርና ማካሄድ ረፍት የማይሰጥ ሥራው ይሆናል። በፖለቲካው፡ በኤኮኖሚው፡ በማሕበራዊ መስኮች፡ በአገር ደሕንነት፡ በውጭ ግንኙነት ወዘተ ያለውን አስተሳሰብ አንጥሮ ማውጣትና ለሕዝቡ በትክክል የቆመበትን ቦታ ማሳየትን ይጠይቃል። የሚያምንባቸው የፍልስፍናና የፖሊሲ ሃሳቦች ከገዢውም ሆነ ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚለዩበትንና የሚሻሉበትን ምክንያቶች ጠንቅቆ ማወቅንና በግልጽ ማስረዳትን ይፈልጋል። የሌሎች አገሮችን ልማዶች ማጥናትና የሚበጀውን ለይቶ ለመጠቀሚያ ማውጣት ይኖራል። የአገሪቱንና የሕብረተሰቡን የእለት ተለት ችግሮች መከታተልና አቋምንና ስትራቴጂን እያጣጣሙ በንቃት መሟገትን የግድ ይላል። በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በጎረቤት አገሮችና በሰፊው አለም ያለውን ወቅታዊ የወታደራዊና የፀጥታ ሚዛን መገንዘብ፤ እንዲሁም የሚካሄደውን እለታዊ የፖለቲካና የኤኮኖሚ ሁኔታና የወደፊት አቅጣጫ ማጤንና ካገሪቱ ጥቅሞች አንፃር ማስላትን ይጋብዛል። ፓርቲው ለነዚሕና ለሌሎቹም ሥራዎች ሁሉ የሚሆኑትን የሰው ኃይል ከአባላቱ መምረጥ፤ ለሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ ገንዘብና ቁሳቁሶች መፈላለግ ወዘተ ረፍት ስለማይሰጡት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውጣ ውረዱ ፈርጀ-ብዙና ፈታኝ ናቸው። ባጠቃላይ ፓርቲው በገዥነት ላይ ባይሆንም ራሱን እንደ ነገው አገር አስተዳዳሪ ቆጥሮ ኃላፊነት በተሰማው መንገድ ሁለገብ ዝግጅትና ብቃትን ማዳበር አለበት። ለምርጫ መዘጋጀት ማለት እነዚሕንና ሌሎችንም የፓርቲ ሥራዎች ማካሄድ ማለት ነው። ሕዝቡ አምኖ ድምፁን ከሰጠውና ካሸነፈ በማግስቱ አስተዳደሩን መጀመር ስላለበት ዝግጅቱ አስቀድሞ የተሟላ መሆን ይገባዋል። ዝግጅቱ ለአሸናፊነቱ አስፈላጊ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን፤ በሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላ በአገርና በሕዝብ ላይ የሙከራ ጊዜ ብሎ ቀልድ እንደማይኖር ስለሚታወቅም ነው።

የአንድ የፖለቲካ ድርጅት ምርጫ በምርጫ ያለመሳተፍ ጥረት ከሆነ ግን ከዚሕ አቢይ ትርጉም ካለው የድርጅት ኃላፊነትና የትግል ውጣውረድ መሸሽ ነው የሚሆነው። ከፖለቲካ ትንቅንቁ ርቆ ብቻ የመንግሥትን ድርጊቶች በመተቸትና መምረጥና መመረጥ አያስፈልግም እያሉ በአድማና በኩርፊያ መቀመጥ ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ሥርዓትን ለመመሥረት የሚያመጣው ብዙም በጎ ነገሩ አይታይም። ፓርቲው የአደራጅነትና የመሪነት ድርሻውን ረስቶ ገዢው ፓርቲ የሚያደርጋቸውን ሥራዎች እየጠበቀ ምላሽ የሚሰጥ ተቀማጭ ይሆናል። ከዚሕም በተጨማሪ እንዲመጣ የሚፈለገው የሥርዓት ለውጥ እንዴት እንደሚመጣ ራዕይ ማጣትን ያመለክታል። በዚህ ሂደት ድርጅቱ እየቀጨጨና እየተዳከመ ከመሄድ በስተቀር በአገሪቱ ፖለቲካ ትርጉም ያለው ሥራ ወደሚሰራበት ደረጃ ከፍ ሊያደርጉት አይችሉም። ባለፉት 18 አመታት ራስንና ሌሎችን ከአገር ውስጡ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የማግለል ትግል እስካሁን ድረስ ምንም ያስገኘው ጥሩ ነገር እንደሌለ መረዳትና፤ በአንድ ልብ ‘በምርጫ ለውጥ የማምጣት ስትራቴጂ’ አምኖ አቅምን በማስተባበር ሰላማዊ ትግሉን ለማጠናከር መወሰን ጊዜ የማይሰጠው ነው።

በርግጥ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ሁሉ ነገር በተቃዋሚነት ለሚሰለፉ ክፍሎች የተመቻቸ ነው ማለት አይደለም። ሰዎች በመንግሥት ያለፍትሕ ይታሰራሉ፡ ይገደላሉ። የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕዝባዊ ድጋፍ እንዳያገኙና ጠንካራ ተቋሞች ሆነው እንዳይወጡ ብዙ ግፍ ይፈፀምባቸዋል። ነገር ግን ችግሮች ስላሉ በለውጥ ሂደቱ አንሳተፍም ማለት ለመፍትሔው አይረዳም። ችግሮቹ ስላሉም ነው ትግሉ የሚያስፈልገው። ምክንያት እየደረደሩ በምርጫው ከመሳተፍ መራቅ ግን የሚጎዳው ኢሕአዴግን አይደለም። በሥልጣን ላይ ያሉት የሚፈልጉት ሌሎች ኃይሎችን በተቻላቸው መጠን ማግለልና የሥልጣን ጊዜያቸውን ያለ ጠንካራ ተቀናቃኝ ማራዘም ስለሆነ ይኽ ቀላል ስሌት እስካሁን ለአንዳንድ ተቃዋሚዎች እንዴት ግልጽ እንዳልሆነ የሚያስገርም ነው። አሁንም ካለፈው ስህተት መማር ያስፈልጋል። እንቅፋቶቹ እንዲወገዱ እየታገሉ ወደምርጫው መጓዝ ሌላ ምትክ የሌለው መንገድ ነው። መንግሥት መለወጥ ካለበትና የተሻለ ሥርዓት እንዲመጣ የምንመኝ ከሆነ በፖለቲካ ሂደቱ ችግሮቹን ተቋቁመን መሳተፍ የግድ ይላል። የፖለቲካ ተሳትፎ እጥረት የሃሳብ ፍጭትን ይገድባል፤ የአስተሳሰብ እድገትን ያኮስሳል፤ የዲሞክራሲያዊ ተቋሞች ግንባታን ያዳክማል፤ የተሻለ ሥርዓት ምሥረታን ያዘገያል። በኛ ዘመን ካለፈው ታሪካችን ተምረን አዲስ ነገር ማሳየት አለብን። ይኽ ትውልድ እስካሁን በታሪካችን የምናውቀውን የሥልጣን አስተላለፍ ዘዴ ከጠመንጃ ኃይል ወደ ምርጫ ካርድ መቀየር አለበት። በኛ ዘመን አንድ ድርጅት በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ኃላፊነቱን ሲረከብ ማየት አለብን ብለን መነሳት ያስፈልገናል።

Click here to read pdf version
Share

14 comments on “በምርጫ ያለመሳተፍ ትግል

 1. መቼም አብዛኛው ሰው እንደሚያረገው ገና ጽሁፉን ሳላነብ ወደ ተቃውሞ መግባቴ አይደለም፡፡

  ይሁንና አቶ መለስና ፓርቲያቸው ሰላማዊ ትግል ታገሉ ነገር ግን ቀዩን መስመር ካለፋችሁ ከኔ ትጣላላችሁ ብለው በቀጥታ ባይሆንም በተዘዋዋሪ መንገድለማስረዳት ሞክረዋል፡፡ ከህዝብ ጋር እንኳን ፓርቲዎች እንዳይገናኙ በተለያየ ሰበብ የመሰብሰቢያ አዳራሽ መከልከልና ማስከልከል በጣም የተለመደ እና እየታየ ያለም ነው፡፡ ጠንቋይ ትቀልባለህ ወይ አትበሉኝና ይሄ ደግሞ እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ በሰፊው የሚታይ ነገር ነው፡፡

  እና እንዴት ተደርጎ ነው ታዲያ በምርጫ መሳተፍ የሚቻለው?

 2. ሰላምታዬ ይድረሳችሁ፣
  ኑሮአችን ሁሉ በአቶ መለስ በጎ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ባናደርገው ጥሩ ነው። አቶ መለስ እኮ ዘላለማዊ እድሜ የላቸውም፣ ነገ ወይም ከነገ ወዲያ … ተፈጥሯዊ ሞት ይሞታሉ። ያኔ ሁሉም ነገር ይለወጣል። ትልቁ ቁም ነገር በሀገራችን የምርጫ ስርዓት መዘርጋቱ ነው። አባቶቻችን ያወረሱን የምርጫ ስርአት ባለመኖሩ ዛሬ እኛ የአቶ መለስ ማላገጫ ሆነናል። እና እኛስ ለልጆቻችን የአመጽ መንገዱን እናውርሳቸው? ለኔ እስከሚገባኝ ድረስ፤ ዴሞክራሲ ፕሮሰስ ነው። ከፕሮሰሱ ተጠቃሚ እየሆኑ ለውጡን ማምጣት እንጂ አብዮት ማፈንዳት ለማንም የሚጠቅም መንገድ አይደለም። እነ ማርቲን ሉተር፣ እነ ማልኮልም ኤክስ፣ … ባይጮሁና ባይሞቱ ኖሮ ዛሬ አቶ ባራክ ሁሴን ፕሬዚዳንት አይሆኑም ነበር። አቶ መለስ ከማንኛው ኢትዮጵያዊ የተማሩትን ዴሞክራትነት እንዲያሳዩን ትፈልጋለህ? ከቴዎድሮስ? ከምኒሊክ? ከዮሐንስ? ከተፈሪ? ወይስ ከመንግስቱ? ይልቅ ረጋ ብለን እኛው እናስተምራቸው!!! ተግባባን?

 3. It is a timely article. However, my worry about election is that, last time the Ethiopian people voted largely for Kinijit. But, Kinijit declined to take the seats.

  So, if the people ask leaders whether they would decline taking up a Parliament or Regional seat after winning this time round, what would be the response? That is the most difficult bit to answer. I do not know how the people be reasonably convinced to come out enmass and vote the opposition.

 4. Well, for those of us who believe in peaceful struggle, we can not afford to boycot the coming election. WE need to start thinking hard about it. Welldone writer!

 5. It is better to speack to TPLF in the language it only understands i.e armed struggle. Peaceful struggle is a waste of time. Viva Ginbot 7.

 6. Why not co-ordinate peaceful and armed struggles rather than condemning the other which we do not support at a personal level?

  Peaceful struggle and armed struggle are not mutually exclusive. One can support and complement the other.

 7. ከጸሀፊው አገላለጽ እንደምረዳውና እኔም እነደምስማማበት ሰላማዊ ትግል ቀላል ነገር አይደለም፡፡ እልህ አስጨራሽና ውጤቱንም ለማየት ብዙ ጊዜ የሚፈጅና መስዋዕትነትም የሚጠይቅ ነው፡፡

  ሰላማዊ ትግል ማለት እየሞቱ ማታገል ማለት ነው፡፡ እንጂ እየሞቱልን ማታገል ማለት አይደለም፡፡ ለዚህም ነው ጋሼ ብርሀኑ ባልሳሳት የዛሬ ስምንት አመት ገደማ ይምሩን ተብለው ሲጠየቁ “ፖለቲካንና እሳትን ከሩቁ” ያሉት ታዲያ ምርጫው እየተቃረበ ሲመጣ በቴሌቭዥን መስኮት ይታይ የነበረው ክርክርና የህዝቡም ስሜት ሲታይ የኢህአዴግ ስልጣን መልቀቅ አይቀሬ መስሎ በመታየቱ እሳቸውን ጨምሮ ብዙ ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ወደ ፖለቲካው መጡ፡፡ በኋላ ግን ነገሮች እንደተጠበቀው ሳይሆን ቀርቶ እስሩም መጣ ከእስሩም በኋላ ወዲያውኑ ወደ ውጭ እገሬ አውጪኝ ተከተለ፡፡

  ከመቅጽበት መኮብለላቸው አይገርመኝም ምክንያቱም ሰላማዊ ትግል ያስፈራል፡፡ እኔም እፈራለሁ፡፡ የትጥቅ ትግል ግን አልፈራም ምክንያቱም እውጭ ሀገር ስለምኖር ማንም ና ታገል አይለኝም ዶላርህን አምጣ ነው የምባለው፡፡ አዎ አንዳንዴ ወጥቶ መጮህ ይኖራል ለዛም ቢሆን ወደ ማሪየት ሆቴል (Marriott Hotel) ጎራ ብዬ አንድ ሁለት በመጎንጨት ጉሮሮዬን ማራስ እችላለሁ፡፡
  እውነቴን ነው፡፡ በማንም ላይ አሽሙር መናገሬ አይደለም፡፡

 8. ፍቅሩ ባልከው ነገር እስማማለሁ፡፡ በየምክንያቱ የናቴ መቀነት አወላከፈኝ ከምንል የቻልነውን ያህል እየወደቅንም እየተነሳንም ተሳትፎና ትግላችንን መቀጠል አለብን፡፡

 9. I don’t think Ethiopian people have any desire for election game especially after the 2005 mess.

 10. ሰላም፣
  ዮኒ የኢትዮጵያ ህዝብ እኮ ወደ 80 ሚሊዮን ገደማ ነው። ስንቶቹን አነጋግረህ ነው “ለምርጫ ፍላጎት የለውም” የምትለን? የተማረ ሰው ሲሳሳት ልክ የለውም። እኔ ኢትዮጵያ ነው የምኖረው። ካንተ የተሻለ ግምት መናገር እችላለሁ። በኔ ግምት ተስፋ የሚያስቆርጥ ሁኔታ የለም። ደግሞም
  there is no shortcut for democracy.

  ኢትዮጵያ የተባሉት ጸሐፊ ደግሞ ሰላማዊና ትጥቅ ትግል አይለያዩም ይሉናል። አንድ ሰው በአንድ ጊዜ ክርስቲያንም እስላምም መሆን እንዴት ይቻለዋል። ሁለቱም መንገዶች መንግስተ ሰማያትን ያወርሳሉና የሁለቱም እምነቶች ተከታይ ልሁን ማለት ጤነኛነት ነው?

 11. በሀገራችን ከዚህ በፊትም በአንዳንድ ብሄረሰቦች ዴሞክራሲያዊ የሆነ የስልጣን ማስተላለፍ ነበር። ለምሳሌ በኦሮሞ ብሄረሰብ የገዳ ስርዓት። ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት በሰላማዊ መንገድ በምርጫ ተወዳድሮ ቢያሸንፍ ለህዝቡ ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል።አለበለዚያ ግን የብዙ ንፁሃን ህይወት መቀጨቱ አይቀርም። ስለዚህ እውነት ለሀገራችን ለወገናችን የሚናስብ ከሆነ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ መቅረብ ነው።

 12. እዉነትና ንጋት እያደር ይጠራል ሆኖባቸሁ እንጂ ኣቶ መለስ ምን ኣጠፉ የዲሞክራሲን መንገድ በፊሽካ ኣስጀመሩን መሮጥ ፈንታቸን ነዉ መንገዱን ይዘን እባካችሁ ኣትጨቅጭቁን
  ከዳር ቆማችሁ ልማታችን ላይ ኣታላግጡ

 13. the peopel as well as the government must participate very well for the fairenes of our national election

Comments are closed