Logo

የዘንድሮውን የዘመን መለወጫ በዓል ማን እንዴት አከበረው?

October 14, 2009

ከበደ ረጋሣ

በእኔ ግንዛቤ ገና፤ ፋሲካና ዘመን መለወጫ ብዙ ሰው የሚሳተፍባቸው በዓላት ናቸው፡፡ በተለይ በከተሞች የሃይማኖት ልዩነትም በማህበራዊ መስተጋብሩ ላይ እምብዛም ተፅእኖ የለውም፡፡ ስነስርአቱ በዋዜማው ምሽት ይጀምራል፡፡ ከፊሉ ከቤቱ ለበነጋው ዝግጅት ጉድ – ጉድ ይላል፡፡ ሌላውም በእድሜና በአቅሙ ከሚመስለውና ከሚፈቅደው ጋር ሁለት ሶስት እየሆነ ወደ እሚመጥነው የምሽት መዝናኛ ይሄዳል፡፡

ለዘንድሮ ዘመን መለወጫ ዋዜማ ጳጉሜ 5 ቀን ሐሙስ ምሽት በተወሰኑ አካባቢዎች ተዟዙሬ ነበር፡፡ ለወትሮው በየዓመቱ አደርግ እንደነበረው ከጓደኖቼ ጋር እየጠጣሁና እየጨፈርኩ ለመደሰት አልነበረም የዘንድሮው ዙረቴ፡፡ ዛሬ ለዛ ፍላጎቱም አቅሙም የለም፡፡ በእርግጥ ላቀድኩት የግንዛቤ አሰሳ የሚጠቅም ከመሰለኝ ከፍ ባሉትም በዝቅተኞቹም ቡና ቤቶች ጎራ እያልኩ አንድ ሁለት ማለቴ አልቀረም፡፡ በዚህ ሁኔታ ከምሽቱ 12 ሰዓት ተኩል ከመርካቶ የከተማ ውስጥ አውቶቢሶች መናኸሪያ ጀምሬ አራዳ ገዳም ሰፈር – በአራት ኪሎ በኩል አምባሳደር – ልደታ – በቄራ በኩል ወሎ ሰፈር – በቦሌ መንገድ ታጥፌ በመገናኛ – በ22 ማዞሪያ – በባምቢስ አድርጌ በ5 ሰዓት ካሳንቺስ መናኸሪያ ደረስኩ፡፡

በየደረስኩበት ሰፈር የፌዴራልና የፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ የመንግስት ታጠቂዎች ብዛት ልክ የለውም፡፡ አመሻሹ ላይ አልፎ – አልፎ በመኖሪያ ጊቢዎች ችቦ ይበራል፡፡ የርችት ድምፅ የሰማሁት እጅግ ውስን ነው፡፡ ሁለት ሶስት የሚሆኑ ልጆች እየተቧደኑ በየበሩ ሆያ – ሆዬ ይላሉ፡፡ ማንም ከቁብ የሚቆጥራቸው የለም፡፡ የልጆቹም አድራጎት የበአል ለዛ የለውም፡፡ ተራ ልመና ነው የሚመስለው፡፡ አትጩሁብን ውጡልን ይባላሉ፡፡ አንዳንድ ቦታ ተገፍትረው ይወጣሉ፡፡ ገንዘብ ሲሰጣቸው ያየሁት ጥቂት ቦታዎች ነበር፡፡ ቢሰጡም በሳንቲም ደረጃ ነው፡፡ በደቂቃዎች ልዩነት ሌላው ቡድን ሲመጣ አድርሰናል ይባላል፡፡

በየመሀከሉ የማደርገው አጠር ያለ የእረፍቱ ጊዜ ቆይታ እስካሁን ያስነበብኳችሁን ለማጤንና ቀጥሎ የምሄድባቸውን ስፍራዎች መርጦ ለመወሰን ብቻ አልነበረም የጠቀመኝ፡፡ ‹‹የትልልቅ ሰዎችንም›› የመልካም ምኞትና የምክር መልክት ሰምቼበታለሁ፡፡ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት የመቶ አለቃ ግርማ ወልደጊዎርጊስ፤ ፓትሪያርኩ ብፁእ አቡነ ፓውሎስን ጨምሮ በርካታ የሃይማኖት አባቶችና የክልል መንግስታት ፕሬዝዳንቶች ነበሩ መልክቱን አስተላለፊዎቹ፡፡ የሁሉም መልክትና ምክር አንድ ወጥ ነበር፡፡ ለህዝባቸው ሰላምና ጤና ተመኝተው በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ የልማት ሥራው እንዲተጋ ይመክራሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ አቶ መለስ ዜናዊ ቀደም ሲል የሀገር ውስጥ ጋዜጠኞችን ሰብስበው ያሉትን ነው እነዚህም የደገሙት፡፡

ሌላም የታዘብኩት ነገር አለ፡፡ አንዳዱ ቡና ቤት ቴሌቪዥኑ አለ ግን አልተከ ፈተም፡፡ አንዳዱ ዘንድ ተከፍቷል ግን ዞር ብሎ የሚያየው የለም፡፡ ተከፍቶ የነበረውን ድምጹ ይቀነስ ወይም ይዘጋልን የሚሉ ተቃውሞች ባለቤቶቹን ያሰለቸ ጉዳይ መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ አንዳንድ ቦታ ይዘጋ በመባሉ ቅር የተሰኙ፤ አፍ አውጥተው ለመናገር ግን ያልተዳፈሩ ሰዎች እንዳሉም ታዝቤያለሁ፡፡ ዕጅግ ጥቂት በሆኑ ቤቶች ደግሞ ለራሱ ላለበት ቤት ብቻ ሳይሆን ላካባቢው ጭምር እንዲሰማ ታስቦ ድምጽ ማጉያ የተገጠመለት ያህል ድምጹ ያስተጋባል፡፡ አላፊ አግዳሚው ይጉተመትምበታል፡፡ እኔ ግን ለምን እንደፈለኳቸው ሳላውቀው እንደዛ ያሉ ሁለት ቤቶች ገብቼ ነበር፡፡ አንደኛው ቤት ካስተናጋጆች ሌላ ተገልጋይ ሰው የለበትም፡፡ በትህትና አስተናገዱኝ፡፡ ሁለተኛው ቤት ለአስተናጋጆቹም ሆነ ለነበሩት ተገልጋዮች ጸጉረ ልውጥ እንደሆንኩባቸው ከገጽታቸው ተረድቻለሁ፡፡ ይሁነኝ ብዬ ትንሽ ቆየሁ፡፡ አብረውኝ የቆዩት እየተሰረቁ የጎሪጥ ሲያዩኝ፤ አዲስ መጪው ሲያፈጥብኝ የሄድኩበት ዓላማ ተረሳኝ፡፡ እንደገባኝ አፍ አውጥተው ውጣልን ማለት ነበር የቀራቸው፡፡ ባይተዋርነት ተሰማኝ፡፡ ጀርመን በርሊን ወይም ፈረንሳይ ፓሪስ የወግ አጥባቂዎች መገናኛ ክበብ የገባሁ እንጂ ኢተዮጵያ አዲስ አበባ ውስጥ ከወገኔ መሀከል ያለሁ አልመስል አለኝ፡፡ 

የምሽቱ ሰዓት እየገፋ ሲሄድ ከእስካሁኑ ሁሉ ይበልጥ የሚያሳስቡ ነገሮች መታዘብ ቻልኩ፡፡ በአንዳዱ ሥፍራ ከውጪ የተኮለኮሉት መኪኖች ዓይነት እነማን ከቤቱ ውስጥ ሊኖሩ እንደሚችሉ አመልካች ነበር፡ ባንኮኒው ላይ ከተደረደሩት ሰዎች ብዙዎቹ  ውድ መጠጦች (ጎረደን ጂን፤ ብላክ ሌቤል፤ ሺቫዝ) ዊስኪ ጠርሙስ ነው ለሁለት ለሶስት የሚያወርዱት፡፡ በጠረቤዛ ዙሪያ የተቀመጡትም የቆርቆሮ (የውጭ) ቢራ፤ ዋይን ይቀላቅላሉ እንጂ በሚበላውና በሚጠጣው አይተናነሱም፡፡  ከቡና ቤቱ ጎን ካለው ልኳንዳ ቤት ክትፎው፤ ቁርጡ፡ ጎረድ ጎረድ፤ ጥብስ የመሳሰለው የሥጋ ዓይነት ይጋዛል፡፡ ተስተናጋጆቹ ብር አወጣጣቸው፤ አለበበሳቸውና አድራጎታቸው ሁሉ የዛሬዋ ኢትዮጵያዊ አያስመስላቸውም፡፡ በዚሁ መንፈስ እየተበላና ዕየተጠጣ የተለያዩ ብሔረሰቦች የዘፈን ትሪኢት ይታያል፡፡ በዘፋኞቹ ላይ በተናጠል የተጀመረው አቃቂር ማውጣት ወደ ማንነት ጥያቄ ተሸጋገረ፡፡ ከወደ ባልኮኒው አንደኛው ‹‹ቀድሞ ነገር መስከረም አንድን ማነው አዲስ ዓመት ያደረገው? የነማን በዓል ነው ነገ የሚከበረው? እንስማማ ካልን ሁላችንም በጊሪጎሪያን አቆጣጠር መጠቀም አለብን›› እያለ በሽሙጥ መልክ ነገር ማላኮስ እንደጀመረ ግርግርና ጩኸት ከውጭ ተሰማ፡፡ ከሉካንዳ ቤት ታዞ ይመጣ የነበረው ምግብ በጦም አዳሪዎች (የእኔ ቢጤዎች) ከበራፍ ላይ ተነጥቆ በመወሰዱ ነበር መጯጯሁና ግርግሩ የተፈጠረው፡፡

ሁለቱ አባሪዎቹ ሲያመልጡ አንደኛው ጦም አዳሪ ተይዟል፡፡ የማሪያም ጠላት ሆነ፡፡ ሁሉም ነገር ተረሳና በጦም አዳሪው ላይ ፍርድ መስጠት ተጀመረ፡፡ ‹‹እንዳይለምደው አርባ ይገረፍ፡፡ ኮሶና በርበሬ መታጠን አለበት፡፡ ለፖሊስ ቢሰጥ ተሻርከው ስለሚለቁት እዚሁ ታስሮ ከዘበኛ ቤት ቆሞ እንዲያድር ማድረግ ነው፡፡ ›› ብዙ ተባለ፡፡ አከላካይም አልጠፋም፡፡ መስማማት ግን አልተቻለም፡፡ መጨረሻውን ለማየት ፈልጌ ነበር፡፡ የራሴ ደህንነት አሳሰበኛና ሂሳቤን ከፍዬ ወደቤቴ ሄድኩ፡፡

ጉዞውና መጠጡ ተረዳድተው ያስያዙኝ እንቅልፍ የሞት ታናሽ ወንድም ነው የሆነብኝ፡፡ ህልም አይሉት ቅዠት ስጓዝ በውኔ ያየሁት በእልሜ እየመጣብኝ ተኝቼም ሰላም ነሳኝ፡፡ ለትልልቅ በዐላት ሲደረግ እንደቆየው ዐርብ ከጥዋቱ 12 ሰዓት የኢትዮጵያውያንን የዘመን መለወጫ ለማብሰር 21 ጊዜ መድፍ ሲተኮስ ነበር የባነንኩት፡፡ ወዲያው እቴ – አበባሽ የሚሉና አበባ ቢጤ ስለው የሚያዞሩ ህጻናት በር እያንኳኩ አላስተኛ አሉኝ፡፡ ቀኑ ለክርስትና (ኦርቶዶክስ) አማኖች ፆም ስለነበር አቅሙ ያላቸውም አላረዱም፡፡ ሉካንዳ ቤቶችም በማይፆመውም ላይ አድማ የመቱ ይመስላል፡፡ የሙስሊሙም ምእመናን ቢሆን በረመዳን ፆም ስለተዳከመ ቤቱ መዋልን ሳይመርጥ አልቀረም፡፡ ከአንበሳ አውቶቢስ በስተቀር የሀይገር በስ (ቀንደ አውጣ ይሉታል) እና ታክሲ በቁጥር ነው መንገድ ላይ የሚታዩት፡፡ በዚህ ሁሉ ድምር ውጤት አውዳመቱ በእለተ ቀኑ ቀዝቅዞ ዋለ፡፡

ይልቁንም በበነጋው ቅዳሜ ጠዋት መስከረም 2 ቀን 2002 ዓ. ም. በአንጻራዊ ደምቆ እንደዋለ ታዝቤያለሁ፡፡ የሐሙስ ምሽቱን ዓይነት ጉዞ ቅዳሜ ከጥዋቱ ሶስት ሰዓት እስከ የተሰዓት ዘጠኝ ሰዓት ነበር ያደረኩት፡፡ እንደ ዐርቡ ባይጠናም ዛሬም የመጓጓዣ ችግር ነበር፡፡ አልፎ – አልፎ የሐበሻ ባህል ልብስ የለበሱ ሴትና ወንድ፤ ከፊሎቹ ከልጆቻቸው ጋር እየሆኑ ታክሲ ሲጠብቁ አይቻለሁ፡፡ እነዚህ ቤተሰቦችና የመንገዱ ጭር ማለት፤ እንደዚሁም እርድ መኖሩን አመልካች አሞሮች በሰማዩ ላይ በርከት ብለው ማንዣበባቸው መሰለኝ የትናንትናው የዐርብ ቀን በዓል ዛሬ ቅዳሜ እየተከበረ መሆኑን የሚያስታውሱት፡፡

በቅዳሜው ጉዞዬ የተወሰኑ የቦታ ለውጦች አድርጌያለሁ፡፡ ዶሮ ተራ፤ በግ ተራ፤ ልኳንዳ ቤት፤ ፍርፋሪ ከሆቴል ቤቶች ተገዝቶ ግንፍልፍል ተሰርቶ በእጅ ጉርሻ የሚሸጥበትና ከቆሻሻ መድፊያ ገንዳዎች ውስጥ የሚበላ የሚፈልጉ ሰዎች ባሉበት አካባቢ ረዘም ያለ ጊዜ አሳልፌያለሁ፡፡ ከቅንጥብጣቢ ሥጋ የግምት ግዢ ጀምሮ እንደየ አቅሙ ሥጋ በኪሎ፤ ዶሮ፤ በግ፤ ወደ ካራ-አሎ (በኮተቤ በር)፤ ጉለሌ፤ ጅማ በር፤ ለቅርጫ የቀንድ ከብት መግዛት እረፋዱ ድረስ ተጧጡፎ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ከዳር እስከ መሀል ከተማ በዋና ዋና አስባልት መንገዶች ግራና ቀኝ ያሉት በጎች ብዛት ከአዲስ አበበአ ህዝብ ቁጥር የሚልቅ ይመስላል፡፡ ከየመግቢያው በር ወደ ቄራ የሚነዱት፤ በመኪናም የተጫኑ የእርድ ቀንድ ከብቶችም ብዛት ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ይሄ የጀመረው ከበዓሉ መቃረቢያ ሁለት ሶስት ቀናት ጊዜ ውስጥ ሁሉ መሆኑን አትዘንጉ፡፡ ከመኪና ጋር እልህ ተጋብቶ መንገድ ላለመልቀቅ የሚተሻሸው ከተሜ ከ30 እስከ 50 የሚሆን ሰንጋ ከፊቱ ሲመጣበት መግቢያ ቀዳዳ ጠፍቶት ሲራወጥ ማየት በራሱ ልዩ ትሪኢት ነበር ያን ሰሞን፡፡ በዚህ ይዞታ የበግና የበሬ ዘር በቅርብ ቀናት ተሟጦ ያልቃል የሚለውን ስጋት ለመጋራት የእርባታውን ይዞታ ማጥናት ይጠይቃል፡፡   

ለወደፊቱ መተካት ተቻለም አልተቻለ ብቻ እርዱ ቀጥሏል፡፡ በቁጥር በጣም ውስን የሆነው ቤተሰብ ሁሉንም የሥጋ ዓይነት (ዶሮ፡ በግ፡ የቀንድ ከብት ቅርጫ) እንደሚገዛ ተረድቻለሁ፡፡ አንድ ኪሎ ሥጋ ወይም ቅንጥብጣቢ የሚገዛው ሰው ቁጥር እንደሚበዛ ግን መገመት የሚያስችል መረጃ አግኝቼያለሁ፡፡ ከራሳቸው አንደበት እንደሰማሁት የእኔ ቢጤውዎች ሦስት አራት ከሚሆኑ ልጆቻቸው ጋር እርጥብ ነገር የሸተተው ፍርፋሪ የሚያገኙትና መጽዋቹ ወገን የሚራራላቸው ካዘቦቱ ቀን ይልቅ በአውዳመት ቀን ነው፡፡ ዕኛ በየጎዳናው ላይ፤ በየመስኪዱና በየቤተ ከርስቲያናት የምናያቸው ብቻ አይደሉም የከተማ ውስጥ ረሀብተኞቹ፡፡ የእከሌ ወገን ሆኖ እንዴት ይለምናል እንዳይባል ይሉኝታ ይዞት ወይም በጤና ችግር መንቀሳቀስ ባለመቻላቸው በየስርቻው ወድቀው በረሀብ አልንጋ የሚቆራመዱት ሰዎች ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ ነበር ካነጋግርኳቸው የእኔ ቢጤዎችና አረጋውያን የተረዳሁት፡፡

በእለቱ ከደረስኩባቸው ሥፍራዎች መሀከል ሦስቱ ማለትም የካ ሚካኤል፤ እስጢፋኖስና ኡራኤል ቤተክርስቲያናት የአጥር ግንቦችን የአንድ ወገን ተገን አርገው ከላስቲክ፤ ከሸራ፤ ከዶንያ፤ ከካርቶን ወይም ከዲሪቶዎች ወይም ከሁሉም ቅልቅል የተሠሩ መጠለያዎች አሉ፡፡ ነዋሪዎቹ ‹‹የቤቶቹ›› ባለቤት ወይም ተከራዮች ናቸው፡፡ የእኔ ቢጤዎችና የጎዳና ላይ ተዳዳሪዎች ተብለው በሁለት ይመደባሉ፡፡ ልዩነታቸው በውል አይገባኝም፡፡ የጠየኳቸው ሰዎች እንደነገሩኝ ከጎዳና ላይ ተዳዳሪዎች የተወሰኑት አይለምኑም፡፡ ሠርቶ ወይም ነጥቆ አዳሪ ናቸው፡፡ እነዚህም ሰዎች እንደሌላው ህብረተሰብ በአውዳመት ቀን ይገባበዛሉ፡፡ ዑራኤል ቤ/ክርስቲያን ታከሲ የምጠብቅ አንዳዴም መንገድ የጠፋኝ አስመስዬ እየተሰረቅሁ አያቸው ነበር፡፡ ከአንደኛው ማእዘን ሁለት ወንድና ሦስት ሴቶች ከአንደኛዋ የድንኳን መጠለያ በራፍ በየምናምኑ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ከሁኔታው ልጆቻቸው የመሰሉኝ አራት ህጻናት ከፊለፊት ካለው መጠለያ አጠገብ ቁጢጥ – ቁጢጥ ብለው ይጫወታሉ፡፡ ከትልልቆቹ ሰዎች ሴቶቹ እየተቀባበሉ ባንድ ዕቃ ሲጠጡ፤ ወንዶቹ በየግል በሃይላንድ (በውሀ ላስቲክ) ጠላ የሚመስል መጠጥ ይዘዋል፡፡ ብርጭቆ መሆኑ ነው፡፡ ከመሀከላቸው የእንጀራ ፍትፍትና የዳቦ ቁርስራሽ የተሞላ ሜካ (የላስቲክ ከረጢት) አለ፡፡ መሶብ መሆኑ ነው፡፡ ተረጋግተው እያወጉ፤ እየተሳሳቁ ይመገባሉ፡፡ ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል ማለት ይሄ አይደል? ሁሉ ነገር ተሟልቶለት ደስታ የራቀውን ወይም ያላወቀበትን ቤቱ ይቁጠረው፡፡

ስለዓመት በዓሉ ለማጥናት ከያዝጉት የቀረኝ የገበያ ዋጋ ሁኔታ ነው፡፡ የችግሩን ግዝፈት ለመረዳት የሚጠቅም መሰለኝ፡፡ 100 ኪሎ ቦቆሎ ከ600-700 ብር፤ ስንዴ 700-800፤ ቀይ/ትቁር ጤፍ ከ800-900፤ ማኛ ጤፍ 1300 ብር፡ ቀይ ሽንኩርት 10 ብር እና ከዛ በላይ፤ ቅቤ በኪሎ ከ60-70 ብር፤ ኪሎ ሥጋ በአማካኝ 60 ብር (በአዲስ አበባ 6ቱ በሮች ላይ ለምሳሌ በኮተቤ በኩል ካራ-አሎ ኪሎው ሥጋ 40 ብር ሲሸጥ ወደ ማህል ከተማ ለምሳሌ ልደታ ባለው የአሹ ሥጋ ቤት ቫት ተጨምሮበት 80 ብር ይሸጣል)፤ ዶሮ 60 ብር፤ አነስተኛ በግ ከ400 በላይ ነው፡፡ ትልቁ/ሙክት ሺህ ቤት ነው፡፡ ቀላል በሬ ብር 3000፤ የደለበ ሰንጋ እስከ 15000 ብር መሸጡን ሰምቻለሁ፡፡ ከሱቅ የሚገዛውም ዕቃ ቢሆን የዋጋው ንረት ብቻ ሳይሆን የለውጡ ፍጥነት ያስደነግጣል፡፡ ጠዋት በ10 ብር የገዙትን ዕቃ ከተሰዓት 15 ብር ሲባሉ ምን ይሉታል?

ተፈጥሮ በሚበድለን የአየር መዛባት የሚመጣውን ችግር መጋፈጥ ግድ ነው፡፡ ከዚህ ለመላቀቅ መጣርም የአባት ነው፡፡ የዜግነት ግዴታም ነው፡፡ የሰለቸን ሰበብ የነዳጅ ዋጋ መጨመር ነው፡፡ አንድ በርሜል ነዳጅ ዋጋ 140 ዶለር በነበረበት ጊዜም ሆነ ዛሬ ወደ 40ዎቹ በወረደበት ወቅት የእኛ ሀገር ኑሮ ማሸቀቡን እንደጉድ ቀጥሏል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዓለም ገንዘብ ቀውስ እንደ ሁለተኛ ሰበብ መጠቀስ ጀምሯል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ (አቶ መለስ) የገንዘብ ቀውሱ በኛ ላይ ትርጉም ያለው ጫና እንደ ማይፈጥር የዛሬ ወር ገደማ ለፓርላማቸው እርግጠኛ ሆነው ሲናገሩ ሰምቻቸው ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪቃ አደጋ እንደሆነ አምነው ለፍልሚያው (የለጋሽ ሀገሮች መንግሥታትን ለመለመንና ለማስጠንቀቅ) ግንባር ቀደምትነት የአፍሪቃን ሕብረት ውክልና ወስደዋል፡፡ አውቀው በንቀት ይሁን ሳያውቁ በስህተት ለፓርላማ ሰዎቻቸው የተሳሳተ መረጃ ስለመስጠታቸው ግን እኔ እስከማውቀው ድረስ ይቅርታ አልጠየቁም፡፡

ለኑሮአችን መወደድ ሦስተኛው ሰበብ ሙስናው እንደሆነ ይነገራል፡፡ እንደ አቶ መለስ አባባል ሁሉም ሹሞቻቸው ሌቦች ናቸው፡፡ ልዩነቱ ቀድሞ የመያዝና ያለመያዝ ጉዳይ መሆኑን በአደባባይ ነግረውናል፡፡ በፖለቲካው እየታገዙ ከህግ በላይ በመሆን ስለሚመዘብሩትና ሀገሪቱን ወደባሰ ቀውስ እየገፏት ስላሉት የፓርቲያቸው የንግድ ድርጅቶች ግን ያሉት ነገር የለም፡፡ በተነሳባቸው ቁጥር የማስተባበያ እንጂ የማስተካከያ ሀሳብ መስጠት አይፈልጉም፡፡ ጳጉሜ 4 ቀን በጋዜጠኖች ሲጠየቁም የዘነጉት አስመስለው ሳያነሱ አልፈውታል፡፡

ቁም ነገሩ ይሄ ጥቂቶች የታደሉት ያስረሽ ምቺው ገንዘብ ምንጩ ከየት ነው? ይሄን መሰል ምስቅልቅል ህይወት ውስጥ የሰማይና የምድር ያህል የተራራቀ የህብረተሰብ ጥንቅር ይዘን እውን ብሄራዊ ስሜት ያለው የወገን ተቆርቋሪ  ዜጋ ስለመኖሩ መናገር እንደፍራለን? ለወደፊትስ ማፍራት ይቻለናል? ካልቻልን ብሔራዊ ስሜት በሌለበት ብሄራዊ እድገት ይታሰባል? እንነጋገርበት፡፡

Share