Logo

ከሳምንቱ የጋዜጦች ዘገባ በጥቂቱ

December 30, 2010

የሺጥላ አክሊሉ፤

ዓርብ ዕለት የታተመው ነጋድራስ ጋዜጣ “የደርጎች የይቅርታና የብሔራዊ እርቅ አጀንዳ” በሚል ርእስ የታዋቂ ግለሰቦችንና የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን አስተያየት አስነብቧል። በዚሁ ጋዜጣ ላይ የሺጥላ አክሊሉ የተባሉ ግለሰብ “ኮሎኔል ዳንኤልና ዶ/ር ሰናይ ልኬ ውስጥ ውስጡን የመቦርቦር ስራ ይሰሩ ነበር። አብዮታዊ ሰደድ የወዝ ሊግ ወታደራዊ ክንፍ ሆኖ ሰርቷል። እነ ጄኔራል ተፈሪ በንቲ ላይ እርምጃ የወሰዱት ወዝ ሊጎች ናቸው። እነሱ ደግሞ ባልጠበቁት ሁኔታ ተመቱ…” የሚሉት አቶ የሺጥላ “ግብታዊነት፣ የንቃተ ህሊና ማነስ፣ በፖለቲካ አለመብሰልና ህግ አለማወቅ በደርግ ላይ ጎልተው የሚታዩ ችግሮች” እንደነበሩ ዘርዝረው፤ ይቅርታው የዘገየ ቢሆንም ሃሳቡ የሚደገፍ ነው ብለዋል።

ዶ/ር ያዕቆብ፤

በሩዋንዳው የዘር ማጥፋት ወንጀል ዙሪያ በአቃቤ ሕግነት የሰሩት ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማሪያም ደግሞ፤ የኢትዮጵያ የወንወጀል ህግ ስለዘር ማጥፋት ያለው ሃሳብና ዓለም አቀፍ የዘር ማጥፋት ህግ እንደማይጣጣሙ አስረድተዋል። አያይዘውም፣ እሳቸው ቃሊቲ እስር ቤት በነበሩበት ወቅት ለሁለት ወር ያህል ከደርግ አባላት ጋር ማሳለፋቸውን አስረታውሰው፣ ያነጋገሯቸው የደርግ አባላት በሙሉ የተደረገውን ሁሉ ያደረጉት ለሀገር ቅን በማሰብና በመመኘት መሆኑን እንደገለጹላቸው አስረድተዋል። ዶ/ር ያዕቆብ በመጨረሻም፣ “የደርግ ባለስልጣናት አላጠፉም አይባልም” ካሉ በኋላ፤ በነሱ ቤተሰብ መበተኑን፣ ወላጆች ጧሪ ቀባሪ ማጣታቸውን፣ ሴቶች ያለ ባል ልጆች ያለ አባት መቅረታቸውን ዘርዝረው “ቀይ ሽብር ትምህርት የሰጠ ጉዳይ በመሆኑ ሊለቀቁ ይገባል” ማለታቸውን ነጋድራስ ጋዜጣ ዘግቧል።

ዶ/ር ኃይሉ አርአያ፤

“የሃይማኖት አባቶች ከሞት በኋላ ስለአለው የሰው ልጅ እጣ ፋንታ ብቻ ሳይሆን፤ በህይወትም እያለ ቁሳዊ ህይወቱ እንዲሟላ መጣር አለባቸው። እናም እርቀ ሰላም እንዲመጣ” የሃይማኖት አባቶች የያዙት መንገድ ተገቢ ነው፣ ያሉት ደግሞ ዶ/ር ኃይሉ አርአያ ናቸው። ዶ/ር ኃይሉ ብሔራዊ እርቅ ከደርግ ባለስልጣናት ጋር ብቻ መያያዝ እንደሌለበትና እንደ አንድ የችግር መፍቻ መንገድ መታየት እንዳለበት ተናግረዋል። “አሁንም ችግር አለ ብለው መሳሪያ እስከ ማንሳት የደረሱ የህብረተሰብ ክፍሎች ስለአሉ፣ ለምን ወደዚያ አቅጣጫ ሄዱ ብሎ መመርመር የሁሉም ወገን ኃላፊነት ነው” ብለዋል ዶ/ር ኃይሉ በነጋድራስ ጋዜጣ ላይ።

አቶ ልደቱ አያሌው፤

የኢዴፓ ፕሬዝዳንት አቶ ልደቱ አያሌው ደግሞ የደርግ አባላት መፈታት ከብሔራዊ እርቅ አንዱ አድርገው እንደሚያዩት ገልጸው፣ “ለእኔ ብሔራዊ እርቅ ዓላማውም፣ ግቡም፣ መሰረቱም፣ ሰፊና ጥልቅ ነው” ብለዋል። በርካታ ፓርቲዎች እርስ በርስ በተገዳደሉበት እና ሕዝብ እርስ በርስ ቂም በተያያዘበት አገር፤ የደርግ ሰዎች መፈታት ቁንጽል ነው ባይ ናቸው አቶ ልደቱ።

አቶ ስዬ አብርሃ፤

የቀድሞው የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር አባል የነበሩት አቶ ስዬ አብርሃ በበኩላቸው፤ የኢህአዴግ መንግስት ለደርግ ባለስልጣናት ይቅርታ ለመስጠት በምንም ዓይነት መመዘኛ የሞራል ብቃት የሌለው መሆኑን አመልክተው፣ በጉዳዩ ውስጥ የገቡ የሃይማኖት አባቶች ለህሊናቸው የተስማማ ስራ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል። 

2. ስለ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባዔ፣

የፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባዔ የማካሄድ ጉዳይም እንዲሁ በሳምቱ ውስጥ የታተሙ ጋዜጦችን የዘገባ ሽፋን ያገኘ ጉዳይ ነበር። ነጋድራስ ጋዜጣ “መድረክ ጠቅላላ ጉባዔውን በአንድ ሳምንት አራዘመ” በሚል ርእስ የመድረክን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

ፕ/ር በየነ ለነጋድራስ ጋዜጣ በስልክ እንደገለጡት የመድረክ ጠቅላላ ጉባዔ ለአንድ ሳምንት እንዲራዘም የተደረገው ለጉባዔው መቅረብ የነበረባቸው ሪፖርቶች ባለመጠናቀቃቸው ነው ተብሏል። በሚቀጥለው ሳምንት መጨረሻ ላይ የሚሰበሰበው የመድረክ ጉባዔ የሰብሳቢነቱን ስልጣን ከኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው ወደ ተከታዩ ተረኛ ድርጅት እንደሚያስተላልፍ በጋዜጣው ተጠቅሷል።

ቀደም ሲል በተያዘው እቅድ መሰረት መድረክ እስከ የካቲት ወር መጠናቀቂያ ድረስ ራሱን ወደ ግንባር ደረጃ ከፍ እንደሚያደርግ የተገለጠ መሆኑን ጋዜጣው አስታውሶ፤ እስከ አሁን ድረስ አረና ትግራይ እና ኦፍዴን የተባሉት ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባዔአቸውን አድርገው መድረኩ ወደ ግንባር ማደጉን እንደሚቀበሉ አረጋግጠዋል ብሏል።

ቅዳሜ እለት የወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ደግሞ “መኢአድ አዲስ ፕሬዝዳንት ለመምረጥ አስቧል፤ ኢ/ር ኃይሉ ስልጣን ይለቃሉ” በሚል ርእስ የጠቅላላ ጉባዔ ዜና አቅርቧል። ኢ/ር ኃይሉ ስልጣን አስረክባለሁ ማለታቸው በአዲስ አድማስና በሌሎች መገናኛ ብዙሃን ቢዘገብም፤ ጠቅላላ ጉባዔው ተካሂዶ፣ ኢ/ር ኃይሉ አሁንም የመኢአድ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸው ታውቋል።

Share

2 comments on “ከሳምንቱ የጋዜጦች ዘገባ በጥቂቱ

  1. Good. This is what we want, fresh content. It is boring to read nonsense articles by the Phds such as pro. Alemayehu.

Comments are closed