Logo

“የጥቁር እና ነጭ” ፖለቲካችን ጀንበር ማዘቅዘቅና የሶስተኛ አማራጭ መጠንሰስ

January 1, 2011

በምክክር መድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች ዋነኛ ጠንካራ ጎን ተደርጎ የተወሰደው ከገዢው ፓርቲ በተጨማሪ ለሀገሪቱ አማራጭ የፖለቲካ ኃይል እንደሚያስፈልግ ግንዛቤ በመውሰድ ተደራጅተው የፖለቲካ ፓርቲ (ድርጅት) ማቋቋማቸው ነው። በሁለተኛ ደረጃ የታየው ጠንካራ ጎን ደግሞ በነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች ዙሪያ የተሰበሰቡት ዜጎች በርካታዎቹ የሀገር ፍቅር ስሜት ያላቸው መሆናቸው ነው።

እነዚህ “ሀገር ወዳድ” (Nationalist) ፖለቲከኞች ጠመንጃም፣ ወታደርም፣ ደህንነትም፣ እስር ቤትም፣… ያለውን ኃይል (ኢህአዴግን) ባዶ እጃቸውን ሆነው በሰላማዊ መንገድ ለመታገል መነሳታቸው፤ ከራሳቸው ህይወት ይልቅ የሀገራቸው ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል የሚል እምነት አድሮባቸው የፈጸሙት በመሆኑ ይህ አገር ወዳድነታቸው ጠንካራ ጎናቸው ተደርጎ የሚወሰድ ብቻ ሳይሆን አክብሮትም የሚሰጠው ነው የሚል እምነት አለኝ።

ከእነዚህ ሁለት ዋና ዋና ጠንካራ ጎኖች ውጪ የፖለቲከኞቹ ችግሮችና ድክመቶች ከራስ ፀጉር የበረከቱ፣ ቁጥር ስፍር የሌላቸው መሆኑ ግንዛቤ ተወስዶበታል። በወቅቱ የተነሱት ችግሮችም በሚከተለው መልኩ ተጠቃለው ሊቀርቡ ይችላሉ። እነሱም፦

•    የጠራ ዓላማ፣ ፕሮግራምና ደንብ ያለመኖር ችግር፦ የኢዴፓ መስራቾች የበርካታዎቹን ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ዓላማ፣ ፕሮግራምና ደንብ በዝርዝር በተመለከቱበት ወቅት በሰነዶቻቸው ውስጥ የጠራ ዓላማ (ርዕዮተ ዓለም) የሌላቸው መሆኑን አይተዋል። የጠራ ዓላማ የሌላቸው በመሆኑ ምክንያትም ኢህአዴግን ከማስወገድ በኋላ መድረሻ ግባቸው ምን እንደሆነ በአግባቡ አላስቀመጡም። ዓላማና ፕሮግራማቸውን ብቻ ሳይሆን የጠራ ርዕዮተ ዓለም አስቀምጠው ለመታገል በቂ ዝግጅት ባለማድረጋቸው ጉዞአቸው የውር የድንብር እንዲሆን አድርጎታል። አባሎቻቸውንም ርዕዮተ ዓለም ሳይሆን ለኢህአዴግ ያላቸው የመረረ ጥላቻ ያሰባሰባቸው መሆኑ ታይቷል።

•    ከገዢው ፓርቲ ጋር ያላቸውን ልዩነት በውል ያለመገንዘብ ችግር፦ ብዙዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን “ተቃዋሚ ፓርቲ ነን” ብለው ከመጥራታቸው በስተቀር በፖለቲካ ፕሮግራም ይዘት ይሁን በአደረጃጀት ከኢህአዴግ የተለዩ አልነበሩም። በዚህም ምክንያት ከኢህአዴግ ጋር ያላቸውን አንድነትም ሆነ ልዩነት በአግባቡ የሚያውቁ ስላልነበሩ የሚታገሉትን ኃይል ለምን እንደሚታገሉት በውል ተገንዝበዋል ለማለት አያስደፍርም።

•    የአሰራርና የመርሆዎች ችግር፦ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሌላው ችግር የፖለቲካ ፕሮግራማቸውንና ዓላማቸውን ይዘው ያሰቡት ግብ ለማድረስ ስራቸውን የሚያከናውኑበት አንድ ሁለት ብለው የሚቆጠሩ የአሰራር ስርዓትና የሚመሩባቸው መርሆዎች (Principles) ባለማስቀመጣቸው፤ ጉዞአቸው ሁሉ የተሰነካከለና ለኢህአዴግ ደባ ያጋለጣቸው ሆኗል። በዚህ ረገድ በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችለው ሰላማዊ ትግል እናደርጋለን ብለው ተቋቁመው ትጥቅ ትግል እናካሂዳለን ከሚሉት ጋር አብረው ለመስራት የጋራ ግንባር (ህብረት) መመስረታቸው የሚስተዋል መሆኑ ነው። ይህም አካሄዳቸው ኢህአዴግ “ሰላማዊና ሰላማዊ ያልሆነውን ታጣቅሳላችሁ” በሚል ሰበብ ክስ ለመመስረት ምቹ ሁኔታን ፈጥሮለታል።

•    የርዕዮተ ዓለም ብቃትና ጽናት ያላቸው አባላት ያለመኖር ችግር፦ በርካታዎቹ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት፤ አባል የሆኑበትን ፓርቲ ፕሮግራም፣ ደንብ፣ መርሆዎች፣ አሰራሮች፣… በአግባቡ የተገነዘቡ ባለመሆናቸው ለኢህአዴግ ያላቸውን ጥላቻ ከመግለጽ ውጪ የፓርቲያቸውን ርዕዮተ ዓለም ለማስረዳት እንኳ አይችሉም። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ጊዜ ላይ ያለው አመራር እና ታች ያለው አባል የሚናገሩት ቋንቋ እጅግ የተለያየ መሆኑ ይታያል። ከዚህ በተጨማሪ በርካታዎቹ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት የኢህአዴግን ውድቀት አምርሮ ከመመኘት ውጪ የፓርቲያቸውን ዲስፕሊን አክብረው አባል የሆኑበትን ፓርቲ በገንዘብና በቁሳቁስ ደግፈው ሲንቀሳቀሱ አይታዩም። አንዳንዶቹማ የዓላማ ጽናት አጥተው  ቶሎ ጥሎ ጥቅማ ጥቅም የሚያስገኝላቸውን ድርጅት ፍለጋ ዛሬ ከአንዱ ፓርቲ ጋር ነገ ከሌላው ፓርቲ ጋር ሲባዝኑ ይታያሉ።

•    የፍረጃ ፖለቲካን እንደ ስልት የመከተል ችግር፦ ሌላው የተቃዋሚ ፓርቲዎች ዋነኛ ችግር “ፍረጃን” እንደ ፖለቲካ ስልት የመከተላቸው ጉዳይ ነው። ብዙዎቹ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ከ1960ዎቹ ጀምሮ ፍረጃን እንደ ስልት ስለሚጠቀሙበት ዓላማቸውን፣ ፕሮግራማቸውንና ርዕዮተ ዓለማቸውን ለሕዝብ አቅርበው “በመሸጥ” ድጋፍ ከማግኘት ይልቅ፣ አንዱን ፓርቲ ወይም የአንዱን ፓርቲ መሪ ደካማ ጎኖች አጉልተው በማውጣት (የሌለን ነገር በመፍጠር ጭምር) እንዲሁም ከእኔ ጋር የሌለ ሁሉ ከገዢው ፓርቲ ጋር ነው ብሎ በመፈረጅ “እንዲጠላ” ማድረግን እንደ የርዕዮተ ዓለም ማራመጃ ስልት ይጠቀሙበታል።

•    የሚታገሉትን ገዢውን ፓርቲ ያለማወቅ ችግር፦ ብዙዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች “ኢህአዴግን እንታገላለን” በሚል መንፈስ ፕሮግራም ቀርጸው፣ ደንብ አዘጋጅተው ቢቋቋሙም፤ ያ የሚታገሉት ኃይል ዓላማ ምን እንደሆነ፣ የሚከተለው ርእዮተ ዓለም ምን እንደሆነ፣ ምን ጠንካራና ምን ደካማ ጎኖች እንዳሉት በወጉ ተረድተውና በቂ ትንታኔ አስቀምጠው ስለማይንቀሳቀሱ አመርቂ ውጤት ለማስመስገብ አልቻሉም።

•    ለገዢው ፓርቲ እውቅና ያለመስጠት ችግር፦ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሌላው ችግር ገዢውን ፓርቲ (ኢህአዴግን) እንደ ወራሪና የባእድ ኃይል (እንደ ቅኝ ገዢ) “ጠላት” አድርጎ የመቁጠርና እውቅና ያለመስጠት ጉዳይ ነው። እውቅና ያልተሰጠውና እንደ ባእድ የተቆጠረው ኢህአዴግም ተቃዋሚዎቹን ሁሉ “የቀድሞ ስርዓት ናፋቂዎችና የትምክህተኞች ጎራ” የሚል ስም ሰጥቶ ተመሳሳይ የጅምላ አቋም እንዲይዝ አድርጎታል።

•    የአመራር (Leadership) ችግር፦ የበርካታዎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች ከተራ ሀገር ወዳድነት ባሻገር ለወቅቱ (ለዘመኑ) የሚመጥን የፖለቲካ ስልት የማይከተሉ፣ በትንታኔና በእውቀት ላይ የተመሰረተ አመራር ከመስጠት ይልቅ የሕዝብ ጊዜአዊ ስሜት ተከትለው የመነዳት አቅጣጫን ስለሚከተሉ ተገቢ የሆነ የሰከነ የመሪነት ሚና (Leadership Role) መጫወት አልቻሉም።

ኢዴፓን ለመመስረት በዝግጅት ላይ ነበረው የወጣቶች ስብስብ ለአርባ ስንምት እሑዶች ባደረገው ምክክር ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎች መለስተኛ ሊባሉ የሚችሉ ነጥቦችን እያነሳ ሰፊ ውይይት በማድረግ የጥቁር እና የነጭ ፖለቲካችንን ጀንበር ማዘቅዘቅና የሶስተኛ አማራጭ ብስራት መሰረት የሆኑ መነሻዎችን የሚያረጋግጡ የመፍትሄ ሃሳቦችንም አስቀምጧል። (ክፍል 5 ይቀጥላል)

Share