Logo

ከሳምንቱ የጋዜጦች ዘገባ

January 14, 2011

ቅዳሜ ታህሳስ 30 ቀን 2003 ዓ.ም የወጣው ሳምታዊው አዲስ አድማስ ጋዜጣ በፊት ለፊት ገጹ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነጋዴዎችን አስጠነቀቁ” በሚል ርእስ ሰፊ ዘገባ አቅርቧል። ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባለፈው ሀሙስ እለት በአዲስ አበባ ነዋሪ ከሆኑ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ጋር ባደረጉት ስብሰባ፣ ከውጪ ሀገር በሚገቡ ሸቀጦች ላይ መንግስት የዋጋ ተመን ያወጣ መሆኑንና ነጋዴዎች ለተፈጻሚነቱ የማይተባበሩ ከሆነ በዘርፉ የውጪ ሀገር ባለሀብቶች እንዲሳተፉ የሚያደርግ እርምጃ እንደሚወሰድ ማስጠንቀቁን ጋዜጣው አስታውቋል።

የዋጋ ቁጥጥር የሚደረግባቸው መሰረታዊ የአገር ውስጥ ሸቀጦች የትኞቹ እንደሆኑ አዲስ አድማስ ጋዜጣ በዝርዝር አቅርቧል። ጋዜጣው በመቀጠልም፣ መንግስት በተመነው ዋጋ መሸጥ ኪሳራ ላይ እንደሚጥላቸው አንዳንድ ነጋዴዎች መናገራቸውንም ጨምሮ ገልጿል። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ስብሰባ ተቀምጠው የነበሩት የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በዘይት ዋጋ ላይ አስተያየታቸውን ከመግለጻቸው በስተቀር በሌሎቹ ሸቀጦች ላይ ዝምታን መምረጣቸው መስተዋሉንም ጋዜጣው ዘግቧል።

ለዚህም አባባል ማረጋገጫ ይሆን ዘንድ፣ አንድ ነጋዴ “ነጋዴው አሁን ዝም ሲል የተስማማ እንዳይመስላችሁ። ስለሚፈራ ዝም ይላል። ከዚህ ሲወጣ ያጉረመርማል። ግንኙነታችን እንዲህ መሆን አልነበረበትም። እኛ ከፍተኛ ታክስ ከፋይ እንደመሆናችን ግንኙነታችን የጌታና የሎሌ መሆን አይገባውም” በማለት የብዙሃኑን ነጋዴ ፍላጎት የሚያንጸባርቅ ሃሳብ መሰንዘራቸውን አዲስ አድማስ አስነብቧል። አንድ ሌላ ነጋዴ ደግሞ “የጠራችሁን ይህ ጉዳይ ይመለከታችኋል ብላችሁ ከሆነ፣ የተመናችሁትን ዋጋ ልትነግሩን ሳይሆን ልንወያይበት ይገባ ነበር” ማለታቸውንም ጋዜጣው ጨምሮ ገልጿል።

በሳምንት ሁለት ጊዜ ረቡዕ እና እሑድ የሚታተመው ኢትዮ ቻናል ጋዜጣ በበኩሉ፣ “ነጋዴዎች ለመናገር ስጋት አለብን” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ፣ “ለምን ትሰጋላችሁ?” ማለታቸውን መሪ ርእስ አድርጎ ሰፋ ያለ ዘገባ አቅርቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ባደረጉት በዚሁ ስብሰባ ላይ የጥናት ሰነዳቸውን ያቀረቡት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መላኩ ፈንታ የተባሉ የመንግስት ሹም፣ “የኢትዮጵያን የገበያ ዋጋ የሚወስኑት ከሶስት መቶ ነጋዴዎች አይበልጡም” ማለታቸውን የኢትዮ ቻናል ዘገባ አመልክቷል።

ሪፖርተር ጋዜጣ እሑድ ጥር 1 ቀን 2003 ዓ.ም በወጣው እትሙ “የሰሞኑ የገበያ ውዥንብር” በሚል ርእስ በመንግስት የሸቀጦች ዋጋ ተመንና በገበያው ሁኔታ ዙሪያ በአምስት ሪፖርተሮቹ የተጠናቀረ በጣም ሰፊ ዘገባ አስነብቧል። በዚሁ ዘገባ ውስጥ የተለያዩ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችና ነጋዴዎች አስተያየት ተካቶ ቀርቧል።

“አንዋር ሙሰማ የተባለ በሃያዎቹ ዕድሜ ክልል ላይ የሚገኝ በሸቀጣ ሸቀጥ ችርቻሮ ንግድ ላይ የተሠማራ ወጣት ነጋዴ ሰሞኑን ከመንግሥት በተሰጠው መመሪያ መሠረት የሚሸጣቸውን ዕቃዎች የዋጋ ዝርዝር ለእይታ አመቺ በሆነ ሥፍራ ለጥፏል፡፡ ከአንዋር መደብር በቅርብ ርቀት የሚገኙ ሁለት ሱቆች ታሽገዋል፡፡ የመታሸጋቸው ምክንያት ነው ተብሎ በማሸጊያው ወረቀት ላይ የሚታየው፣ ‘የዋጋ ተመን በተነገረው መሠረት ባለመለጠፋቸው’ የሚል ነው” ይላል ጋዜጣው ሀተታውን ሲጀምር፡፡  በዚህ መሰረት በርካታ መደብሮች እጣ ፋንታቸው መታሸግ መሆኑን ያብራራል ጋዜጣው።

መርካቶ ውስጥ በተለምዶ ‘ቦምብ ተራ’ የሚባለው አካባቢ የሸቀጣ ሸቀጦች ዋነኛ መገበያያ ሥፍራ ነው፡፡ ሪፖርተር በአካባቢው ውዥንብር የተሞላበትን የግብይት ሥርዓት ሥፍራውን በቃኘበት ወቅት ማስተዋሉን ገልጿል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአገሪቷ ውስጥ ተጽእኖ ፈጣሪ ናቸው የተባሉ 584 ነጋዴዎችን በጽሕፈት ቤታቸው ጠርተው ማነጋራቸውን ሪፖርተር አስታውሶ፣ ለኅብረተሰቡ በጣም አስፈላጊ ናቸው ያሏቸውን 16 ምርቶች የሚሸጡባቸውን ዋጋ አሳውቀዋል ይላል።

የመንግሥትን ዕርምጃ ተከትሎ ይህ ነው የማይባል ውዥንብር በአገሪቱ የግብይት ሥርዓት ውስጥ ተፈጥሯል ያለው ሪፖርተር፣ ለወትሮ በገበያተኞች ይጨናነቅ የነበረው የመርካቶው “ቦምብ ተራ” አካባቢ፣ የገበያተኞችን እግር ሲናፍቅ ተስተውሏል በማለት ዘግቧል። እንዲህ ጭር ያለውም ቸርቻሪ ነጋዴዎች ላለፉት ሁለት ቀናት መጥተው ሸቀጦችን ባለመግዛታቸው ነው ተብሏል፡፡

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አስመጪ ነጋዴ “አሁን እየተወሰደ የሚገኘው ዕርምጃ ያልተገባ ነው” ማለታቸውን ሪፖርተር ጠቅሶ፣ “እየሸጥኩት ያለሁት በኪሳራ ሲሆን፣ ይህም መንግሥት አስሮኝ ስቃይ ከሚደርስብኝ ገንዘቤን ብከስር ይሻላል በሚል ፍርሐት ነው”  ማለታቸውን ጋዜጣው አስነብቧል።

በዚሁ በሰሞኑ የንግድ ሁኔታ የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት  ልዩ ስብሰባ መጥራቱን ሪፖርተር ገልጿል፡፡ የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ምክር ቤታቸው መንግስት በወሰደው እርምጃ ዙሪያ በመወያየት ውሳኔ ይወስናል ማለታቸውንም ሪፖርተር ዘግቧል፡፡
ረብሻ በአዲስ አባባ ዩኒቨርስቲ፤

በሳምንቱ ውስጥ የታተሙት ጋዜጦች በሌሎች ጉዳዮችም ዙሪያ የተለያዩ ዘገባዎችን አስነብበዋል። በዚሁ መሰረት፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአራት ኪሎ ሳይንስ ፋከልቲ ተማሪዎች የተቃውሞና የብጥብጥ እንቅስቃሴ ማሳየታቸውን አዲስ አድማስ ጋዜጣ አስነብቧል። የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ረብሻውን የቀሰቀሱት ዓርብ እለት የተከበረውን የገና በዓል በዩኒቨርስቲው ግቢ ውስጥ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እንዳያከብሩ በመከልከላቸው መሆኑንም ጋዜጣው ጨምሮ ገልጿል። በዚህም ምክንያት ፖሊስ ከ4 ኪሎ ዩኒቨርስቲ ግቢ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ላይ በርካታ ተማሪዎችን በሶስት መኪናዎች ጭኖ መውሰዱን ጋዜጣው አስታውቋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ተመሳሳይ የተማሪዎች የረብሻ እንቅስቃሴ እንደነበርና በአዳማ ዩኒቨርስቲ ደግሞ በሴቶች መኝታ ቤት ውስጥ በተነሳ ድንገተኛ እሳት አምስት የሴቶች የመኝታ ክፍሎች ከነሙሉ የተማሪዎቹ ንብረት መውደሙን አዲስ አድማስ ባወጣው ዜና አስታውቋል።

ሦስት ፓርቲዎች ራሳቸውን አገለሉ፤

ሰንደቅ ጋዜጣ ረቡእ እለት በወጣው እትሙ፣ “ዋነኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከማሟያ ምርጫ ራሳቸውን አገለሉ” በሚል ርእስ አንድ ዜና አስነብቧል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው የካቲት 20 ቀን 2003 ዓ.ም በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልሎች በተጓደሉ የምክር ቤት አባላት ምትክ በሚያካሂደው የማሟያ ምርጫ ላይ ጋዜጣው “ዋነኛ” ያላቸው ሶስት ፓርቲዎች እንደማይሳተፉ ዘግቧል።

እንደ ጋዜጣው ዘገባ ከሆነ፤ በዚህ የማሟያ ምርጫ ላይ “አንሳተፍም” ያሉት ፓርቲዎች መድረክ፣ መኢአድ እና ኢዴፓ ናቸው። እነዚህ ፓርቲዎች በማሟያ ምርጫው የማይሳተፉበትን ምክንያት በተመለከተ፤ ኢዴፓ በመጪው መጋቢት ወር ጠቅላላ ጉባዔ ስለሚያካሂድ፣ መኢአድና መድረክ ደግሞ በግንቦቱ ምርጫ የታዩ ጉድለቶችን በተመለከተ ያቀረቧቸው ጥያቄዎች ሳይመለሱ ወደ ሌላ ምርጫ እንደማይገቡ በማስታወቃቸው መሆኑን ጋዜጣው አብራርቷል።

Share

5 comments on “ከሳምንቱ የጋዜጦች ዘገባ

  1. ለዘገባዉ እናመሰግናለን
    የ አቶመለስ ዜናዊ አገዛዝ የገደል ጫፍ ላይ የደረሰ መሆኑን እያንዳንዱ ጋዜጣ በተለያየ መልኩ ከማሳየቱ በላይ
    የ መለሰ የሰልጣን ላይ የመቆየት ሙከራ ምንም ነገር ከማደረግ ወደኋላ እንደማይል ያሳያል
    የኛ GADAFI

  2. yegan sitl enant ybinladon lijoch mhonachihu new atawra serteh asay letqmach semay qrbu new yalut

  3. ሰውዬውና ጋሻጃግሬዎቹ ምን ይጐድልባቸውና የተጐዳ እኔንና እኔን መሰሉ ተቀጣሪ እውነት የሱን መጨረሻ ያሳየኝ ይሆን?

Comments are closed