Logo

የጥቁርና ነጭ ፖለቲካችን መክሰምና የሶስተኛ አማራጭ መሰረት መጣል

February 6, 2011

ኢዴፓን በመመስረቱ ሂደት ተሳትፎ የነበራቸው “የ3ኛ አማራጭ ጠንሳሾች” በተቃዋሚው ጎራ ውስጥ ጎላ ጎላ ብለው የሚስተዋሉ ችግሮችን በዝርዝር አቅርበው ከተወያዩ በኋላ “ለእነዚህ ችግሮች መፍትሄው ምንድን ነው? ምንስ መደረግ አለበት?” የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት የመፍትሔ ሃሳቦችንም አስቀምጠዋል፡፡ መደረግ የሚገባውን አቅጣጫም ለማመላከት ጥረት አድርገዋል፡፡ ከመፍትሄ ሃሳቦቹ መካከልም የሚከተሉት ተጠቃሽ ናቸው። እነሱም፡-

•    የፍረጃ ፖለቲካን በተመለከተ፣ በሀገሪቱ ለዘመናት ስር ሰዶ በመቆየት የተቃውሞ ፖለቲካውን እንቅስቃሴ እግር ከወርች ጠፍሮ በመያዝ አላላውስ ያለው “ወይ ተቃዋሚ ነህ አለበለዚያ የገዢው ፓርቲ ወገን ነህ” የሚል ሁለት ጽንፍ ላይ የተንጠለጠለ የጥቁርና ነጭ የፍረጃ ፖለቲካን በማስወገድ፣ አንድን ጉዳይ በውስጡ በያዘው ምንነቱ ላይ ተመስርቶ ምክንያታዊ (Rational) የሆነ ተቃውሞ ወይም ድጋፍ የማቅረብ አሰራርን የመከተል መርህ የመጀመሪያውና ቀዳሚው የመፍትሄ ሃሳብ ነበር፡፡

•    ከገዢው ፓርቲ ጋር ያለን የርዕዮተ-ዓለም፣ የአሰራር፣ የመርህ፣… ልዩነቶችን በአግባቡ ፈትሾና አንጥሮ በማውጣት ግልጽ የሆነና የጠራ አቋም መያዝ፤ እንዲሁም ከሌሎች ተቃዋሚዎች ጋር በአንድነት፣ በውህደትና በህብረት ስለሚሰራበት ሁኔታ ግልጽ የሆነ መርህና የአሰራር ስርዓት እንዲኖር ማድረግ ከመፍትሄዎቹ ውስጥ አንዱ እንዲሆን ማድረግ፣

•    የብዙዎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ችግር የሚከተሉትን የትግል ስልት ግልጽ በሆነ መልኩ ለማስቀመጥ አለመቻላቸው በመሆኑ፣ በዚህ ረገድ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ከትግል ስልት አኳያ ሰላማዊ ትግል አማራጭ የሌለው ብቸኛው አማራጭ መሆኑን በመቀበል ይህን ስልት በመርህ ደረጃ መቀበል ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ በተግባር ማረጋገጥ በመፍትሄ ሃሳብነት እንዲቀመጥ ተደርጓል። ሰላማዊ ትግል ማድረግ ብቻ ሳይሆን ህብረ-ብሔራዊ አደረጃጀትን መከተልም ለሰላማዊ ትግሉ መሰረት በመሆኑ እንደ ዓላማ ይዞ መስራት ተገቢ መሆኑም ታምኖበታል። 

•    የጠራ የርዕዮተ-ዓለም አቅጣጫን በማስቀመጥ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን የያዘ የፖለቲካ ፕሮግራም መቅረጽ፣ በዚህም ውስጥ በሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፕሮግራም ውስጥ ያልተካተቱ አዳዲስ ሀገራዊና ህዝባዊ አጀንዳዎችን ይዞ በመውጣት ህዝቡን በሰላማዊ ትግሉ ዙሪያ እንዲሰለፍ ማድረግም ሌላው የመፍትሄ ሃሳብ ነበር፡፡

•    የገዢውን ፓርቲ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ብቻ ሳይሆን፤ በተቃዋሚው ጎራ የተሰለፉ የፖለቲካ ኃይሎችን አሰላለፍ እንዲሁም ጠንካራና ደካማ ጎናቸውን ጭምር በዝርዝር በማውጣት መታገል፣ ይህንንም ትግል ለማድረግ ሶስት የትግል አቅጣጫዎችን መከተል እንደሚገባ ተሰመረበት፡፡ እነዚህም ሶስት የትግል አቅጣጫዎች፤ አንደኛ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ ማህበራዊ ደህንነትም ሆነ ፖለቲካዊ መረጋጋትና መልካም አስተዳደር ማረጋገጥ ያልቻለውን ገዢውን ፓርቲ በሰላማዊ መንገድ መታገል፡፡ ሁለተኛ፤ በተቃዋሚው ጎራ የተኮለኮሉ የፖለቲካ ኃይሎች ትግሉን በአግባቡ መርተው የህዝብ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙ ባለማድረጋቸው እነሱንም ቢሆን አብሮ በመስራት ማጠናከር ወይም መንፈሳዊ ቅናት እንዲያድርባቸው በማድረግ እንዲጠናከሩ ማድረግ፣ ይህንን መቀበል ያልቻሉትንና ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አቋም የሚያራምዱትን ከገዢው ፓርቲ ጎን ለጎን መታገል፡፡ ሶስተኛ፤ በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉና ለዘመናት የተንሰራፉ ለሰላማዊ ትግሉ እንቅፋት የሆኑ አሉታዊ አስተሳሰቦችንና አሰራሮችን መታገል የሚሉ ናቸው፡፡

•    ብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢህአዴግንም ሆነ መሪዎቹን እንደ ጠላትና እንደ ወራሪ ኃይል የመመልከት የተሳሳተ አቅጣጫ በማረም ለገዢው ፓርቲና ለመንግስት ተቋማት ተገቢውን እውቅና በመስጠት፣ ከጥላቻ በራቀ መንፈስ የርዕዮተ-ዓለም ትግል ማካሄድ የሚል መርህ መከተል ተገቢ መሆኑ ታምኖበታል፡፡ ይህም ማለት ከፖለቲካ ስልጣን ባላንጣነት ውጪ ከገዢው ፓርቲም ሆነ ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ምንም ዓይነት የጠላትነት መንፈስ አለማሳየት ብቻ ሳይሆን፣ የጋራ ሀገራዊ አጀንዳዎችን በተመለከተ በጠረጴዛ ዙሪያ በመምከር ብሔራዊ እርቅና አገራዊ መግባባት መፍጠር የሚል የመፍትሄ አቅጣጫ እንዲቀመጥ ማድረግ፣

•    የሚመሰረተው ፓርቲ አባላት በእውቀት ላይ የተመሰረተ ሰላማዊ የርዕዮተ ዓለም ትግል ለማድረግ እንዲችሉ ቁርጠኛ የፖለቲካ አመራር መስጠት፣ ቁጥሩ እጅግ ያልተንዛዛ አባላትን በማሰባሰብ የፓርቲውን ርዕዮተ-ዓለም፣ ዓላማዎች፣ አሰራሮችና መርሆዎች ጠንቅቀው እንዲገነዘቡ ማድረግ፣

የሚሉትንና የመሳሰሉትን የመፍትሄ አቅጣጫዎችና አሰራሮች በማስቀመጥ የነጭና ጥቁር ጽንፈና ፖለቲካችንን በማክሰም የሶስተኛ አማራጭን መሰረት የሚጥሉ የመፍትሄ ሃሳቦች እንዲቀመጡ ተደረገ፡፡

ከዚህ በኋላ ቀሪው ስራ ይህንን የሶስተኛ አማራጭነት ጥንስስ፤ ቅርጽና ይዘት እንዲኖረው በማድረግ ህጋዊ ሰውነት እንዲያገኝ የማድረጉን እንቅስቃሴ ማከናወን ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን፣ ሶስተኛው አማራጭ አዲስ አስተሳሰብና የአሰራር መርህ እንደመሆኑ መጠን ይህንን አስተሳሰብ፣ አሰራርና መርሆዎች ይዘን ወደ መድረክ ስንወጣ ከገዢው ፓርቲ፣ ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ከህብረተሰቡ ምን ዓይነት ተግዳሮት (Challenge) ይጠብቀናል? እነዚህን ችግሮችስ እንዴት መወጣት እንችላለን? የሚሉትን ጥያቄዎች በማንሳት የሶስተኛ አማራጭን መሰረት የጣሉት የኢዴፓ መስራቾች ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡ (ክፍል 6 ይቀጥላል)

Share

2 comments on “የጥቁርና ነጭ ፖለቲካችን መክሰምና የሶስተኛ አማራጭ መሰረት መጣል

  1. Dear Mergu
    EDP is a very modern party from the begining. You Have to proud of that. Every opposition even the woyane is copying your idea. EDPs aim is impelementd in one way another. Those who cant generate their own idea will copy and talk about it .That is Good is inn´t it? EDP is working day and night for the people not for few individuals. Bravo!!!!!!!!!!!!!!

  2. Dear Mergu

    It’s good idea! Other opposition group must learn from EDEP what is the mening of struggel!

Comments are closed