Logo

በመኢአድ ውስጥ ያለው ችግር ተባብሷል፤ ኃይሉ ሻውል “ቤቱን ሳላፀዳ ስልጣን አለቅም” አሉ

February 12, 2011

በዚህም የአባራሪና የተባራሪ ትእይንት ምክንያት የፓርቲውን ዋና ጽሕፈት እነ ዶ/ር ታዲዎስና እነ አቶ ማሙሸት አማረ ሲቆጣጠሩ፤ እነ ኢ/ር ኃይሉ ሻውል ላፍቶ አካባቢ በሚገኘው የኢ/ር ኃይሉ የመዝናኛ ስፍራ የፓርቲውን ስራ እያከናወኑ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል። እነ ኢ/ር ኃይሉ ሻውል የተቀሙትን የፓርቲ ጽ/ቤት ለማስመለስ በከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ ሲሆኑ፣ ሰሞኑን በወሰዱት እርምጃ እነ ዶ/ር ታዲዎስን በፍርድ ቤት ከሰዋል።

የእነ ኢ/ር ኃይሉ የክስ ጭብጥ “በዶ/ር ታዲዎስ የሚመራው ቡድን ለጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ አይገዛም። በአመራሩ ላይ ያልተገባ ቅስቀሳ ያደርጋል። ሁከት ፈጥረዋል። የንብረት ክፍሉ ቁልፍ ይዞ ተሰውሯል። ከእያንዳንዱ የጠቅላላ ጉባዔ አባል የውሎ አበል ላይ ሃምሳ ሃምሳ ብር ቀንሰው ከፍለዋል፣…” የሚል ሲሆን፤ ይህንኑም ክስ በፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ለአራዳ ምድብ ችሎት ማቅረባቸው ታውቋል።

እነ ዶ/ር ታዲዎስ በበኩላቸው “19 ዓመት ሙሉ ፍትህ የለም ብለን ወያኔን ስንታገል እንዳልቆየን ኢ/ር ኃይሉ እኛን በወያኔ ፍርድ ቤት መክሰሳቸው ተገቢ አደለም። ፖሊስ ይዘው በመምጣት የመኢአድ ወጣቶች በሀገራቸው ጉዳይ እንዳይመክሩ በማድረግ አሸባሪ ናቸው ያሉትና ሁከት የቀሰቀሱት እነሱ ናቸው። የፓርቲውን ህገ ደንብ በመጣስ በአምቻ ጋብቻ የሾሙት እሳቸው ናቸው” የሚል ምላሽ መስጠታቸውን የዘጋቢያችን ሪፖርት ያመለክታል።

በዚህ ሁኔታ እልህ ውስጥ የገቡት ኢ/ር ኃይሉ የፓርቲውን ስልጣን የሚለቁት ቤቱ ከፀዳ በኋላ መሆኑን ነጋድራስ ለተባለ በአገር ቤት ለሚታተም ጋዜጣ ገልጸዋል። አያይዘውም “አሁን እልህ ይዞኛል። ቤቱን ሳላፀዳ ስልጣን አለቅም” ያሉት ኢ/ር ኃይሉ፣ እልሃቸውን ለመወጣት ጉዞ ወደ ፍርድ ቤት ማድረጋቸውን ከስፍራው የደረሰን ዜና አመልክቷል።

በጉዳዩ ላይ አስተያየት የተጠየቁ አንድ የመኢአድ አባል “መሪዎቻችን ገና ሀገራዊ ስልጣን ሳይዙ ምንጣፍ እያነጠፍን፣ አበባ እየበተንን ስናስተናግዳቸው ኖረናል። በተቃዋሚው ጎራ ለ19 ዓመታት ነግሰው የቆዩት ኢ/ር ኃይሉን ከአሁን በኋላ እንደ ግብጹ ሆስኒ ሙባረክ የሚሰማቸው የለም። ጀምበራቸው ጠልቃለች። ተጨማሪ ውርደት ሳይከተላቸው ስልጣናቸውን አስረክበው ፓርቲውን ቢለቁ ይሻላል” ብለዋል።

በአጠቃላይ፣ በአገር ቤት በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱት ፓርቲዎች በውስጥ ጉዳያቸው ተጠምደው እርስ በርስ ሲካሰሱና ሲሻኮቱ፤ በቅርቡ በሚካሄደው በርካታ መቀመጫዎች ባሉት የማሟያ ምርጫ ለመሳተፍ አለመቻላቸውን የሪፖርተራችን ዘገባ አስታውቋል።

Share