Logo

የኢዴፓ 5ኛ ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባኤን በተመለከተ አጭር ዘገባ

March 25, 2011

በተጨማሪም የህገመንግስቱ አንቀጽ 39 በሃገሪቱ ውስጥ ያሉ ክልሎችን መገንጠል በፈለጉ ሰዓት ያለምንም ጥያቄ የመገንጠልን መብት የሚፈቅድ በመሆኑ አሁንም ለሐገሪቱ ህልውና አደጋ በመሆኑ ሊሻሻል እንደሚገባው ታምኖበታል፡፡ የሐብት ክፍፍል እና የመሬት ባለቤትነትን በተመለከተም መሬት የመንግስት ንብረት መሆኑ ቀርቶ እንደ አካባቢው ሁኔታ የግል፣ የቡድን እና የመንግስት ሊሆን በሚችልበት መንገድ መስተካከል እንዳለብት አቋም ተወስዶበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ስለ የፌደሬሽን ምክር ቤት ሚና እና የምርጫ ስርዓቱ ውይይት ተደርጎ አቋም ተወስዷል፡፡

ምርጫ 2002 እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የኃይል አሰላለፍን በተመለከተ ገዢው ፓርቲ ምርጫውን ለማሸነፍ የቻለው ከ1997 ምርጫ በኋላ ራሱን እነደ አዲስ በማደራጀት እና ህዝቡ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደር በመቻሉ ሲሆን በዋናነት ግን የተቃዋሚ ፓርቲዎች መዳከምም እንደረዳው ተገልጿል፡፡

ፓርቲው ለወደፊት ትግሉን አጠናክሮ በመቀጠል የመንግስት ስልጣንን በመያዝ ለሐገሪቱ ፈጣን እድገት አና ስልጣኔን ለማምጣት እንደሚሰራ እና በቀጣይም ከሁለት አመት በኃላ በሚደረገው የአዲስ አበባ ከተማ ምርጫ ላይ በመሳተፍ አመርቂ ውጤት ለማምጣት ጠንክሮ እንደሚሰራ አቋሙን ገልጿል፡፡

ከዚህ በመቀጠል አንዳንድ በፓርቲው የመተዳደሪያ ደንቦች ላይ ማሻሻል ለማድረግ ከማእከላዊ ኮሚቴው ሐሳብ ቀርቦ ውይይት የተደረገ ሲሆን ከተሳታፊዎች የቀረበ አንድ የማሻሻያ ሐሳብ ከፍተኛ ውይይትን ያስነሳ ሆኗል፡፡ ይኸውም የፓርቲው ለቀመንበር የስራ ዘመንን የሚመለከት ሲሆን ሐሳቡን ያቀረቡት ግለሰብ አንድ አባል ለፓርቲው ሊቀመንበርነት በተጋጋሚ ለሁለት የስራ ዘመናት ከተመረጠ በኋላ አንድ ምርጫ እንዳይሳተፍ እየተደረገ ላልተወሰረ ግዜ እንዲሳተፍ የሚፈቅደው ክፍል ተሻሽሎ ለሁለት ተከታታይ አራት አመታት(በየአራት አመቱ አንድ ምርጫ ሳይሳተፍ) ካገለገለ በኋላ  የመወዳደር እድል እንዳይሰጠው በሚያግድ ደንብ ይተካ ብለው ሃሳባቸውን አቅርበዋል፡፡ በዚህ ላይ ከፍተኛ ውይይት ከተደረገ በኋላ ጉዳዩ ጥልቅ በመሆኑ እና በወቅቱ ከነበረው የሰዓት ጥበት አንፃር ውሳኔ መስጠት አስቸጋሪ ስለሚሆን የፓርቲው የጥናት እና የምርምር ኮሚቴ በጉዳዩ ላይ ጥናት አድርጎ ለሚቀጥለው ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡ ከዚህ በመቀጠል ቀጥታ ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴ ምርጫ ነበር የተሄደው፡፡   

ምርጫው ሲጀመር እኔ በግል ምክንያት ከአዳራሹ የወጣሁ ቢሆንም በቦታው ከነበሩ የቅርብ ጓደኞቼ ለመረዳት እንደቻልኩት ምርጫው የተካሔደው ሁኔታው በሚፈቅደው መጠን እጅግ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ነበር፡፡
በአጠቃላይ በእለቱ የነበረው የስብሰባ ሂደት ፍጹም ሰላማዊ እና መደማመጥ የነበረበት ሲሆን ከፍተኛ የሰዓት ጥበት ታይቷል፡፡

በውይይቶቹ ወቅት እያንዳንዱ ከአባላት የሚነሳ ሐሳብ በቂ ትኩረት ተሰጥቶት የታየ ሲሆን የግለሰቦችን ሐሳብ በማክበር ረገድ አስደሳች ነበር፡፡ ፓርቲው የመተዳደሪያ ድንብ እና የፖሊሲ ለውጥ ለማድረግ የተጠቀመበት አሰራር መሻሻል ያለበት ነው፡፡ ምክንያቱም አነዚህ ጉዳዮች በባህሪያቸው ሰፋ ያለ ውይይት የሚጠይቁ በመሆኑ ለአንድ ቀን በሚደረግ እንደዚህ ያለ ውይይት ላይ ማቅረብ ውጤት አይኖረውም፡፡
በመጨረሻም ፓርቲው ከምርጫ በፊት ህዝቡን ሊደርስበት የሚችልበትን የተለያዩ መድረኮች በመፍጠር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እንዲሁም በገቢ ራሱን የሚደግፍበትን መንገድ ማመቻቸት ይኖርበታል እያልኩ ከላይ ያቀረብኩት የስብሰባውን ውሎ የሚገልፅ ጽሁፍ በወፍበረር የተዘጋጀ ሲሆን ብዙ በፅሁፍ ያልተዳሰሱ ነገሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ በመጠቆም ፅሁፌን እቋጫለሁ፡፡
አመሰግናለሁ
ቢንያም አስቻለው
ናዝሬት
ኢትዮጵያ

Share

2 comments on “የኢዴፓ 5ኛ ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባኤን በተመለከተ አጭር ዘገባ

  1. Biniyam,
    What a superb report. Please keep on reporting such events to us. You also seem to have a very good understanding of the political situation of EDP. People like you can contribute a lot in helping the effort to democratize Ethiopia.

Comments are closed