Logo

አዳማ ዩኒቨርሲቲ እና የሰሞኑ ውዝግብ

June 7, 2011

ቢሆንም ሰልፉንም እንዳያደርጉ በመከልከላቸው ምክንያት ውጥረቱ እየተባባሰ ይሄድና ወደ ረብሻ ይለወጣል፡፡ የተቆጡት ተማሪዎች ለሰላማዊ ሰልፍ ያዘጋጁትን የተለያየ መፈክር በመያዝ በጉልበት ሰላማዊ ሰልፉን ለማድረግ ተሰባስበው ከግቢው የጥበቃ ኃይል አቅም በላይ በመሆን የግቢውን ዋና በር በመስበር ከግቢው ወጥተው ጉዟቸውን ወደ መሐል ከተማ በማድረግ ላይ እንዳሉ ብዙም ሳይርቁ ጨርቃ ጨርቅ አካባቢ ሲደርሱ ፖሊስ ደርሶ በማስቆም ወደ ግቢያቸው እንዲመለሱ ቢጠይቃቸውም ተማሪዎቹ ፍቃደኛ ስላልሆኑ ፖሊስ ከፊት የተሰለፉት ተማሪዎች ላይ የሃይል እርምጃ በመውሰድ የተሰበሰቡትን ተማሪዎች ለመበተን ቢችልም ወደግቢ በመሸሽ ላይ የነበሩት ተማሪዎች ከፊትለፊታቸው ለመንገድ መስሪያ የተዘጋጀ የኮብል ድንጋይ ተከምሮ በማግኘታቸው ድንጋዩን በማንሳት ተመልሰው ፖሊሶች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ፖሊሶቹን

ለአጭር ግዜ ወደኃላ ያስመልሳሉ፡፡ እጃቸው ላይ ያለው ድንጋይ በማለቁ ተመልሰው ድንጋይ ለማምጣት በሚሐዱበት ጊዜ በሌላ አቅጣጫ የመጣ የፖሊስ ሀይል ቀድሞ የድንጋይ ክምሩን በመክበብ ተማሪዎቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል እና ወደ ግቢያቸው እንዲገቡ ማድረግ ችሏል፡፡ በዚህ ወቅት በአካባቢው ከነበሩ ሰዎች ለመረዳት እንደተቻለው ፖሊሶች መሳሪያ እንዳይተኩሱ ጥብቅ ትዕዛዝ በአካባቢው ከነበሩ አዛዦች ሲተላለፍ እንደነበር እና እንደውም ተማሪዎቹ በድንጋይ ፖሊስ ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ አዛዡ መሳሪያ የያዙ ፖሊሶች ከተማሪዎቹ እይታ በተቻላቸው መጠን እና ፍጥነት እንዲሰወሩ ሲያዙ እንደነበር ተነግሯል፡፡

ወደ ግቢ የተመለሰው ተማሪ በግቢ ውስጥ በፖሊስ ተከቦ ከቆየ በኋላ በሚያስገርም ፍጥነት የሲቭል ሰርቪስ ሚንስትሩ አቶ ጁነዲን ሳዶ በግቢው ተገኝተው ለውይይት ተማሪዎቹ በአንድ ቦታ እንዲሰበሰቡ እና ውይይት እንዲደረግ በሚሞከርበት ጊዜ ረብሻ በድጋሚ በመነሳቱ ከተማሪዎች በተሰነዘረ ጥቃት አንድ የሚንስትሩ ጠባቂ ሲፈነከት የመኪናቸው መስተዋትም ተሰብሯል፡፡
አቶ ጁነዲን ተማሪዎቹን ለብቻ በሆቴል ለማነጋገር ሁኔታዎችን ካመቻቹ በኃላ በናዝሬት ሪፍት ቫሊ ሆቴል ውስጥ አንድ ሳምንት የፈጀ ውይይት ከተማሪዎች ከመምህራን እና ከአስተዳደር ሰራተኞች ጋር በተናጥል ከተወያዩ በኃላ በመጨረሻው ቀን አጠቃላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን የኢህአዴግ አባል ከሆኑ ተማሪዎች ጋር ደግሞ ለብቻ ሌላ ውይይት ተደርጓል ፡፡

በውይይቱ ተማሪዎች መምህራን እና ሰራተኞች በግቢው ውስጥ አለ የሚሉትን ችግር አዛው የስራ ኀላፊዎች በተገኙበት እንዲናገሩ እድል ሲሰጣቸው እጅግ በጣም ብዙ የሚባሉ ጉዳዮችን ያነሱ ሲሆን በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ በመድረኩ ላይ ያሉ የስራ ኃላፊዎች መልስ እንዲሰጡ ሲደረግ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ከቀረቡት ውስጥ እጅግ አስገራሚ እና አሳዛኝ ጉዳዮችም ነበሩባቸው፡፡ የተወሰኑትን ለመዘርዘር አሞክራለሁ፡፡

በወቅቱ ከተነሱ ነጥቦች ውስጥ አብዛኛው ማለት በሚቻል መጠን ሙስና ዋናው ርእስ ነበር፡፡ አስገራሚ ከሆኑት የሙስና አይነቶች ውስጥ በግቢው ውስጥ ከተገነቡት ህንፃዎች መሀል ሁለቱ የመጥፋታቸው ጉዳይ ነበር፡፡ በግቢው ውስጥ ሰፊ የሆነ የማስፋፊያ ስራ እየተካሔደ ሲሆን ከሚሰሩት ፐሮጀክቶች ውስጥ የአስር ህንፃዎች ስራ አንዱ ነበር፡፡ በዲዛይን ስራው ላይ በሳይት ፕላኑ ላይም ይሁን በበጀት ደረጃ 10 ህንፃዎች እንደሚሰሩበት የታቀደው ይህ ፐሮጀክት ተጠናቆ ስራውን በኮንትራት የወሰደው ድርጅት ለዩኒቨርሲቲው ይህንኑ ማስረከቡን በሰነድ ተፈራርሞ ስራውን ያጠናቅቃል፡፡ ከወራት በኃላ የተሰሩት ህንፃዎች ሲታዩ ስምንት ብቻ ሆነው ይገኛሉ፡፡ ይህ ጉዳይ በስብሰባው ላይ ከሰራተኞች ተነስቶ ውይይት የተደረገበት ሲሆን ጉዳዩን አቶ ጁነዲን አሳዛኝ እና አሳፋሪ ሲሉ የገለጹት ሲሆን ሌላ ነገር ሊጠፋ ይችላል ህንጻ ግን እንዴት ይጠፋል ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ አስገራሚው ነገር ይህ ጉዳይ ይፋ የሆነው ከ1ወር በፊት ሲሆን እስካሁን ድረስ አንድም ሰው ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር መዋሉ የተሰማ ነገር የለም፡፡ የዩኒቨርስቲው የወቅቱ ፐሬዝዳንት የነበሩት ጀርመናዊ ይህንን ጉዳይ ካወቁ በኃላ እንደ አቶ ጁነዲን አባባል ለመንግስት ብጣሽ ወረቀት በመላክ ምንም አይነት ርክክብ ሳያደርጉ አገሪቱን ለቀው ወደ ጀርመን ሄደዋል፡፡

በሌላ በኩል በዚሁ መልክ በግቢው ውስጥ ከሚሰሩ የመንገድ ስራወች ውስጥ አንዱን ኮንትራት አሸንፎ ስራውን የሚሰራው እዛው በአስተዳደር ውስጥ የሚሰራ አንድ ግለሰብ ሲሆን የመንገዱ ጨረታ ሲወጣ እና በጀት ሲያዝለት በአስፓልት ደረጃ እንዲሰራ ሲሆን ስራው ግን በኮብል ድንጋይ ተሰርቶ ማለቁ በስብሰባው ላይ ተነስቷል፡፡ ይህንንም ይሁን የህንፃውን መጥፋት ጉዳዩ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች እዛው ስብሰባ ላይ ተጠይቀው አምነዋል፡፡ ግን በስብሰባው ላይም ይሁን ከስብሰባው በኃላ እስካሁን ድረስ እነዚህ ግለሰቦችን ተጠያቂ ለማድረግ የተወሰደ እርምጃም ሆነ ቃል አልታየም አልተሰማም፡፡ በሃገሪቱ ውስጥ የኮንስትራክሽን ስራ እየተሰራ እንደሆነ በተለያየ አጋጣሚ በኢአዴግ ሲነገር የምንሰማ ሲሆን ኮንስትራክሽን ኢህአዴግ ከሚኮራባቸው ውጤቹ ዋናው እንደሆነ በድፍረት ይናገራል፡፡ ውስጡ ሲታይ ግን ይህን ይመስላል፡፡ ይህ ብቻ ሳሆን በአዳማ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተሰሩትን እና እየተሰሩ ያሉትን ህንፃዎች ጥራት ያየ በእውነት ያፍራል፡፡ ማንኛውም ግለሰብ በግቢው አጥር ስር ሲያልፍ ከህንጻዎቹ ግድግዳ ላይ የሚታየውን የሻወር ቤት እና የሽንት ቤት ፍሳሽ እርጠበት ማየት ይችላል፡፡  ከአዲስ አበባ በ100 ከ.ሜ. ርቀት ላይ በምተገኘው አዳማ ይህ ከተፈፀመ አፋር እና ጋንቤላ ባሌ እና ሐረር ምን ሊሰራ እንደሚችል መገመት ያስፈራል፡፡

በጣም አሳዛኝ አሳፋሪ እና አስደንጋጭ የሆነው ደግሞ በሬጅስትራር አካባቢ ይሰራል ተብሎ በተማሪዎች የቀረበው አቤቱታ ነው፡፡ ይኸውም በሬጅስትራር ውስጥ ያለ አንድ ግለሰብ በተለይ ለሴት ተማሪዎች በአስተማሪያቸው የተሰጣቸውን ውጤት በመቀየር ተማሪዎቹ የሚፈልጉትን ውጤት እንዲያገኙ በማድረግ ከተማሪዎች የተለያዩ በተለይም ፆታዊ ጥቅሞችን እንደሚቀበል የቀረበው ጉዳይ ነው፡፡ የሚገርመው የሬጅስትራር ኃላፊው ስለጉዳዩ ተጠይቀው ጉዳዩን በደንብ እንደሚያውቁት እና መሰል አቤቱታ በተደጋጋሚ እንደሚደርሳቸው አምነው በቃል ማስጠንቀቂያ እንደሰጡት እና ካስፈለገም በስብሰባው ላይ ማን እንደሆነ ግለሰቡን ለማሳየት እንደሚችሉ ገልፀው ለምን እስካሁን እርምጃ እንዳልወሰዱበት ሲጠየቁ በስራ መደራረብ ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ሽፋንን በከፍተኛ ጥራት እና ፍጥነት እያስፋፋ እንደሆነ የሚናገረው ኢህአዴግ መንግስት በአንድ በኃገሪቱ ውስጥ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በትምህርት ጥራቱ እና በአፈጻጻም ብቃቱ በቅርብ ከተሸለመ ዩኒቨርሲቲ እንዲህ አይነት ነገር ሲሰማ ጉዳዩን ያዘበት ሁኔታ ሲታይ እውነትም ይህች አገር ምን ውስጥ ነው ያለችው ያሰኛል፡፡ 

በወቅቱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ላይም የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስቶባቸዋል፡፡ ፐሬዝዳንቱ ደ/ር ቶላ በሪሶ ሲሆኑ በዚሁ ዩኒቨርሲቲ ከሁለት አመታት በፊት ፕሬዝዳንት ሆነው ሲሰሩ በወቅቱ በግቢው ተማሪዎች እና ሰራተኞች በቀረበባቸው ተቃውሞ ከፕሬዘዳንትነታቸው ተነስተው የነበረ ሲሆን በዚህ አመት ከ4 እና 5 ወራት በፊት የአዳማ ከተማ ከንቲባ ሆነው ተሾመው የነበረ ቢሆንም በዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ በግምገማ ምክንያት ከከንቲባነታቸው ተነስተው በአሁኑ ወቅት የአዳማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ሆነው ተሾመዋል፡፡ ታዲያ ይህ ጉዳይ በዩኒቨርሲቲው መምህራን እና ሰራተኞች በስብሰባው ላይ ከፈተኛ ተቃውሞ የቀረበበት ቢ
ንም በአቶ ጁነዲን በኩል ግን ብዙም ትኩረት ሳይሰጠው ቀርቷል፡፡  ይህ አንድ የኢህአዴግ ባለስልጣን በምንም አይነት ሙስና እና አቅም ማነስ ቢወነጀልም ለድርጅቱ ታማኝ እስከሆነ ድረስ ከቦታ ቦታ ይለዋወጣል እንጂ ምንም አደጋ አይደርስበትም ለሚለው የአንዳንድ ታዛቢዎች አባባል ጥሩ ማሳያ ነው፡፡

በአጠቃላይ የዩኒቨርሲቲው የሰሞኑ ሁኔታ በጥቂቱ ይህንን የሚመስል ሲሆን አሳፋሪ በሆነ መልኩ በስብሰባው የመጨረሻ ቀን ምሽት ለተማሪዎች በሆቴሉ ውስጥ ሰፊ የመጠጥ ግብዣ ተደርጎ ተማሪዎች ሰክረው እርስ በርስ ሲደባደቡ እና ከተማውን ሲያውኩ ማደራቸውን ማስተዋል ተችሏል፡፡ ተማሪን በመንግስት ደረጃ በሆቴል ቤት ያለ ልክ አልኮል መጠጥ መጋበዝ ምን ታስቦ እንደሆነ ልብ የሚል ይገባዋል፡፡

እኔ ይህንን ፅሁፍ ስጽፍ እንደው ዝም ብዬ የረብሻውን ዜና ለማሰማት ሳይሆን ይህ ልማታዊ ነኝ እያለ ነጋ ጠባ የሚያደነቁረን መንግስት አፍንጫዬ ስር የሚያደርገውን ነገር ሳይ አንጀቴ ቢቃጠል ነው፡፡ በሌላም በኩል አቲቪን በማየት እና የኢህአዴግ ካድሬዎችን ጩኸት በመስማት ብቻ ይህን መንግስት ለኢትዮጵያ የመጣ የእግዜር በረከት አድርገው የሚወስዱት ወገኖቼ ቢታዘቡበት ብዬም ነው፡፡ ኢህአዴግ ምንም አይነት ነገር የማስፈፀም አቅም እንደሌለው በብዙ ነገሮች ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

ከረብሻው ጋር ተያይዞ የሚነሱትን የዘረኝነት ወሬዎች እንኳን መፃፍ መስማትም ያሳምማል፡፡ በጣም ብዙ ነገሮችን አልፃፍኩም ግን ለኢትዮጵያ እና ለእኛ አዘንኩ፡፡ መች ይሆን አንቺም ሐገር አኛም ዜጋ የምንሆንሽ?

Share

One comment on “አዳማ ዩኒቨርሲቲ እና የሰሞኑ ውዝግብ

  1. ALL UNIVERSITY OF ETHIOPIA ARE CENTER OF CORRUPTION NOT CENTER OF RESEARCH ACADEMIC.

Comments are closed