Logo

የኢትዮጵያ ፓርላማ የመጪውን ዓመት በጀት እና የኦነግን፣ ኦብነግንና የግንቦት 7ን አሸባሪነት አፀደቀ

June 15, 2011

በመገባደድ ላይ ያለው የ2003 ዓ.ም የሀገሪቱ በጀት 77 ቢሊዮን እንደነበር የኢትዮ ፋክት ዘጋቢ አስታውሶ፣ የመጪው የ2004 ዓ.ም በጀት ደግሞ 117 ቢሊዮን መሆኑንና ይህም ካለፈው ዓመት በጀት ጋር ሲነጻጸር የ40 ቢሊዮን አብላጫ እንዳለው ገልጿል። የቀረበው ረቂቅ በጀት በቁጥር (በአሃዝ) ደረጃ ካለፈው ዓመት ሃምሳ በመቶ በላይ እንደጨመረ ቢስተዋልም፣ በሀገሪቱ አሁን ያለው የዋጋ ግሽበት በዚሁ መጠን በማሻቀቡ የሀገሪቱ በጀት “አድጓል ወይም ጨምሯል” ለማለት እንደማይቻል ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ይህ በዚህ እንዳለ፣ የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው በአምስት የፖለቲካ ቡድኖች ላይ “ሽብርተኛ ናቸው” የሚል ውሳኔ ማሳለፉን   የኢትዮ ፋክት ዘጋቢ የላከልን ተጨማሪ ዘገባ አመልክቷል። ከእነዚህ አምስት ድርጅቶች ውስጥ ሶስቱ በኢትዮጵያውያን የተቋቋሙ አገር በቀል ድርጅቶች ሲሆኑ፣ ሁለቱ ደግሞ የውጭ አገር ድርጅቶች መሆናቸው ታውቋል።

ሶስቱ ሀገር በቀል ድርጅቶች ኦነግ፣ ኦብነግ እና በእነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የሚመራው ግንቦት 7 ሲሆኑ፣ ሁለቱ የውጭ አገር “አሸባሪ” ድርጅቶች ደግሞ አልቃዒዳ እና በመንግስት አልባዋ ሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው አል-ሸባብ ናቸው ተብሏል።

ከተሰናበተ አንድ ዓመት የሆነው የቀድሞው የኢትዮጵያ ፓርላማ በ2001 ዓ.ም ካወጣቸው አጨቃጫቂ ሕጎች አንዱ የፀረ-ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 ሲሆን፣ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 25 መሰረት ድርጅቶቹ “ሽብርተኛ” ተብለው መሰየማቸውን የሪፖርተራችን ዘገባ ጨምሮ ገልጿል።

የፀረ-ሽብር አዋጁ በኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ዘንድ ጧት ማታ የሚወገዝና “አፋኝ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ደግሞ አዋጁ እንደ አውስትራሊያ ካሉ በዴሞክራሲ የታወቁ ሀገራት የተቀዳ መሆኑን በመግለጽ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አስፈላጊ መሳሪያ ነው ተብሎ ይሞካሻል ሲል የሪፖርተራችን ዘገባ አብራርቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከላይ የተጠቀሱትን ድርጅቶች “ሽብርተኛ” ብሎ መሰየም ለምን እንዳስፈለገው እየተነገረ ያለው ምክንያት “አንደኛ የህግ የበላይነትን ለማስፈን፣ ሁለተኛ ህግንና ስርዓትን የማስከበር ስልጣን ያላቸው አካላት በተሰየሙት ድርጅቶችና አባላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ እንዲችሉ” ነው ተብሏል።

የሶስቱ አገር በቀል ድርጅቶች የሽብርተኛነት ተግባር በፓርላማው የመንግስት ዋና ተጠሪ በወ/ሮ አስቴር ማሞ አማካይነት በዝርዝር ቀርቧል። በዚሁ ወቅት፣ በተለይ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በኩል ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ “ተፈጽመዋል” የተባሉ 106 የሽብር ተግባራት ተዘርዝረዋል። ይሁን እንጂ፣ ኦነግ በወተር እና በበደኖ በአንድ ብሔር ተወላጆች ላይ አድርሶት የነበረው ጭፍጨፋ በዚህ ዝርዝር ውስጥ አለመካተቱን ዘጋቢያችን ገልፆ፣ ምናልባትም ያ ጭፍጨፋ በወቅቱ በነበረው የሽግግር መንግስት የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተጣርቶ ኦነግም ጥፋቱን አምኖ በወቅቱ የድርጅቱ ምክትል ሊቀ መንበር በነበሩት በአቶ ሌንጮ ለታ አማካይነት ይቅርታ በመጠየቁ ጥፋቱ እስከ መጨረሻው ተፍቆ ሊሆን ይችላል የሚል ግምቱን ገልጿል።

Share

3 comments on “የኢትዮጵያ ፓርላማ የመጪውን ዓመት በጀት እና የኦነግን፣ ኦብነግንና የግንቦት 7ን አሸባሪነት አፀደቀ

  1. I don’t understand why a usless organisation such as Ginbot 7 should be given focus unless the government wants the public to give it attention. Birhanu’s Ginbot 7 is limited to internt activity, nothing more than that.

  2. Honestly speaking OLF and Ginbot 7 are like non existent in ethiopia. So probably you are right that diverting attention from peaceful struggle can be one reason. I hear about the two organizations only when governmet media and Dr Birhanu’s propaganda machine, ESAT mention them. By the way i am surprised to hear Eritrean government hugely contribute for ESAT.

  3. ዶሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጠልፈው ጣሏት ነው የሚባለው?
    የኢንተርኔት ፓርቲ የሆነው የነብርሀኑ/አንዳርጋቸው ፓርቲም ወግ ደርሶት ቴረሪስት ተባለ:: ጋሽ ብሬ
    Wow that’s great achievement የሚሉ ይመስለኛል

Comments are closed