Logo

በመኢአድ ውስጥ ውዝግብ ያስነሱት ያዕቆብ ልኬ ከምክትል ፕሬዝዳንትነት ሊታገዱ ነው ተባለ

July 31, 2011

በአቶ ያዕቆብ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆኖ መሾም ምክንያት መኢአድ በሶስት አንጃ ተከፍሎ አመራሩና አባላቱ እየተሻኮቱ በመሆኑ ከኢህአዴግ ጋር የሚደረገው ትግል አረም ተጭኖበታል። አባላቱም በአመራሩ ተስፋ በመቁረጣቸው ወደ ሌሎች ፓርቲዎች እየፈለሱ ነው ሲል ሪፖርተራችን አብራርቷል።

ይኸው የመኢአድ የውስጥ ሽኩቻ ሰሞኑን እየተጋጋመ መምጣቱን የሪፖርተራችን ዘገባ አመልክቶ፣ የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ያዕቆብ ልኬ በፓርቲው በቆዩበት ጊዜ የፓርቲውን አባላት በማስፈራራትና ስልጣኑ የኔ ብቻ ነው በማለታቸው ምክንያት ከፓርቲው ሊታገዱ መሆኑን ውስጥ አዋቂ ምንጮችን ዋቢ አድርጎ ሪፖርተራችን ዘግቧል።

ውስጥ አዋቂ ምንጮ ለኢትዮ-ፋክት ዘጋቢ እንደሰጡት ገለጻ፣ አብዛኛውን ጊዜ በቢሯቸው የማይገኙት አቶ ያዕቆብ በፈለጉት ጊዜና ሰዓት በስራ ገበታቸው ላይ ከመገኘታቸው በተጨማሪ ስልጣናቸውን ተገን በማድረግ የፓርቲውን አባላት በማስፈራራትና በማንገላታት ተቃውሞ ስለገጠማቸው አዲስ በተመረጡት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንዲጻፍላቸው መደረጉ ታውቋል። በቅርብ ቀናት በሚደረግ የላዕላይ ምክር ቤት ስብሰባ አቶ ያዕቆብ እንደሚታገዱና በጠቅላላ ጉባዔው ከፓርቲው እስከ መሰናበት የሚደርስ እርምጃ እንደሚወሰድም የዜና ምንጮቹ አብራርተዋል።

አቶ ያዕቆብ ከፓርቲያቸው እውቅና ውጭ ከኢህአዴግ የደህንነት ሰዎች ጋር የኢ-ሜይል ግንኙነት እንደሚያደርጉ የዜና ምንጮቹ ጠቅሰው፣ ይህንንም መረጃ አትሞ ለመያዝ ጥረት እየተደረገ መሆኑንና እስከ አሁን አስር የሚደርሱ መልእክቶችን ከደህንነት ጋር በኢ-ሜይል መጻጻፋቸውን ገልጸዋል። ይህንን መረጃ በእጅ ለማስገባት የአቶ ያዕቆብን ቢሮ ቁልፍ አስቀርጸው ክትትል እያደረጉ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል ሲል የሪፖርተራችን ዘገባ አመልክቷል።

ሳምንታዊው አዲስ አድማስ ጋዜጣ በቅዳሜ ሐምሌ 23 ቀን 2003 እትሙ የመኢአድን ዋና ፀሐፊ አቶ ተስፋዬ ታሪኩን በጉዳዩ ላይ ያነጋገረ ሲሆን፣ እሳቸውም “ማንም ሰው ከፓርቲው ሕገ ደንብ ውጪ ከሆነ የራሳችንን ውሳኔ እንወስዳለን። ይሄ ግን በአቶ ያዕቆብ ላይ ተግባራዊ አልሆነም፡፡ አቶ ያዕቆብ ለድርጅት ስራ በቂ ጊዜ የሌላቸው ናቸው” የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ዘግቧል።

ለተነሱት ክሶች አስተያየት የሰጡት አቶ ያዕቆብ በበኩላቸው “እኔን ማገድ የሚችል ጠቅላላ ጉባዔ ብቻ ነው። ግለሰብ ስራ አስፈጻሚ ማገድ አይችልም። አልታገድኩም። ተራ ወሬ ነው። የቢሮ ቁልፍ መቀረጹም የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም” በማለት ለአዲስ አድማስ ምላሽ ሰጥተዋል ሲል ሪፖርተራችን ዘግቧል።

አቶ ያዕቆብ አባላትን ያንገላታሉ የተባለውን አላስፈላጊ ባህሪ በተመለከተ “እኔ ከአርባ ዓመት በላይ የስራ ልምድ ያለኝ ነኝ። አባላትን አላስፈላጊ ነገር አልተናገርኩም። ተራ ባለጌ ካልሆነ በስተቀር ማንንም ለመናገር ቀርቶ አስቤ አላውቅም” በማለት ገልጸው፣ “አንዳንድ አግባብ የሌላቸው ሰዎች የቢሮ ቁልፍ አስቀርጸው ጠብቀውኛል። ይሄም ንቀታቸውን ያሳያል። እኔ ከፈለግኩ አስገንጥዬ መግባት እችላለሁ” በማለት መናገራቸውንም አብራርቷል።

አቶ ያዕቆብ “ከኢህአዴግ ጋር ግንኙነት አላቸው” የተባለውን በተመለከተ፣ “ብፈልግ የኢህአዴግ ሚኒስትር ሆኜ መስራት እችላለሁ። ገንዘብ ሳይከፈለኝ ገንዘቤን እያፈሰስኩ በዚህ ፓርቲ ውስጥ የምቀመጠው ምን ፍለጋ ነው?” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል ሲል ሪፖርተራችን የላከልን ዘገባ አመልክቷል።

Share

2 comments on “በመኢአድ ውስጥ ውዝግብ ያስነሱት ያዕቆብ ልኬ ከምክትል ፕሬዝዳንትነት ሊታገዱ ነው ተባለ

  1. As the Saying says,

    Yematreba Fiyel 9 Tiwoldalech,
    Lijochuam Yalqalu Esuam Timotalch!

Comments are closed