Logo

ሁለት ፓርቲዎች የተቃውሞ ሰልፍ አስበዋል፤ መድረክ ጥሪውን ውድቅ አደረገ፣ መኢአድ አጤነዋለሁ አለ

August 4, 2011

የትብብር ጥሪ ከተላለፈላቸው ፓርቲዎች ውስጥ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) “የሁለቱን ፓርቲዎች ሃሳብ እናደንቃለን። ስለጥሪውም እናመሰግናለን። ይሁን እንጂ በሰልፉ መሀል ጣልቃ በመግባት ሌላ ዓላማ ሊያራምድ የሚፈልግ አካል ቢኖር በምን መልኩ መከላከልና መቋቋም እንደሚቻል ራሱን የቻለ ጥናት ስለሚያስፈልገው መድረክ የራሱን ጊዜ ወስዶ ማጥናትና መዘጋጀት ያስፈልገዋል” በማለት የሰላማዊ ሰልፉን ጥሪ ውድቅ ማድረጉን የመድረክ የወቅቱ ሊቀመንበር ዶ/ር ሞጋ ፉሪሣ ለሪፖርተር ጋዜጣ መግለጻቸውን ሪፖርተራችን ዘግቧል።

የመድረክ ሊቀመንበር አያይዘውም “ሁለቱ ፓርቲዎች የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ የተነሱባቸው አጀንዳዎች መድረክ በተለያዩ ስብሰባዎቹና መግለጫዎቹ ለኅብረተሰቡ ያስተላለፋቸው በመሆናቸው ብዙም አዲስ ነገር የለበትም” በማለት ሃሳቡን አጣጥለዋል ሲል ሪፖርታችን ጨምሮ ገልጿል።

ይህንን ምላሽ በተመለከተ የሰልፉ አዘጋጅ የሆነው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ድርጅት (ኢዴአድ) ፕሬዝዳንት አቶ አድማሱ ኃይሉ “እኛ ጥሪ ያደረግንላቸው ነገ ተነስተን ሕዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ እናድርግ ለማለት ሳይሆን፣ አምባገነኑ የኢህአዴግ መንግስት በሕዝቡ ላይ እያደረሳቸው ባሉ የተለያዩ በደሎች ላይ ተወያይተን ሰላማዊ ሰልፍ እናድርግ ነው ያልነው” ማለታቸውን ሪፖርተራችን የላከልን ዘገባ አመልክቷል።
እንደ አቶ አድማሱ ገለጻ፣ “ምንም ፓርቲ ተሳተፈም አልተሳተፈም ሕዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ አዲሱ ዓመት ከመግባቱ በፊት በመስቀል አደባባይ ይደረጋል” ብለዋል። የተቃውሞ ሠልፍ የሚያደርጉባቸው ዋና ዋና የአጀንዳ ነጥቦችን በተመለከተም “ሚሊዮኖች በችግር፣ በፍትሕ እጦትና በረሀብ (ድርቅ) ሰለባ ስለሆኑበት የኑሮ ውድነት፣ እየተጣለ ባለው ገደብ ያጣ የግብርና የታክስ አወሳሰንና ሊከተል በሚችለው የዋጋ ንረት፣ የኢሕአዴግ መንግሥት የነፃውን ፕሬስና የሕዝቡን ጥያቄ ለማፈንና ለማሸማቀቅ ያወጣውን የሽብርተኝነት ሕግና ተግባራዊነቱን በሚመለከት፣ ግልጽ ባልሆነና ባልታወቀ ሁኔታ ለውጭ አገር ዜጎች ለ99 ዓመታት በሊዝ እየተሰጠ ስላለው የአገሪቱ ለም መሬት ጉዳይ፣ በመዋቅር ማሻሻያ ስም ሠራተኞች ከሕግ አግባብ ውጭ ከሥራ የማሰናበትና ማፈናቀል ሁኔታን በተመለከተ፣ የትምህርት ጥራት ጉድለትና ሌሎችንም በተመለከተ” መሆኑን ሁለቱ ፓርቲዎች ባወጡት የጋራ የጥሪ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ይህንን የትብብር ጥሪ በሀገሪቱ ካሉ ፓርቲዎች አንጋፋ ስብስብ ነኝ ብሎ የሚታበየው መድረክ ያጣጣለው ሲሆን መኢአድ በበኩሉ ጥሪውን ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አቅርቦ እንደሚያጤነው አስታውቋል ሲል ሪፖርተራችን ያጠናቀረው ዜና አመልክቷል።

ሁለቱ ፓርቲዎች ያነሷቸው አጀንዳዎች የሕዝብ ስሜት የሚስቡ አንገብጋቢና ወቅታዊ አጀንዳዎች ቢሆኑም፤ ስብሰባው የተጠራበት ወቅት ክረምት በመሆኑ ለአፈጻጸም አስቸጋሪ እንደሚሆን ሪፖርተራችን ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች ያስረዳሉ። ሌሎች የፖለቲካ ታዛቢዎች በበኩላቸው ሁለቱ ፓርቲዎች በሀገሪቱ ፖለቲካ ታዋቂነትም ተሰሚነትም የሌላቸው ናቸው። በተለይም ኢዴአድ የተባለው ፓርቲ ከሊቀመንበሩ ውጪ አባላት ያለው መሆኑ አጠራጣሪ ነው። ስብሰባውን ለማካሄድ የሚያስችል ቅስቀሳ ለማካሄድ ደግሞ ጠንካራ አባላትና ፋይናነስ ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ ሁለቱ ፓርቲዎች የያዙትን ሃሳብ ከሃሳብነት በዘለለ ለማስፈጸም የሚያስችል አቅም እንደሌላቸው ያስረዳሉ ሲል ሪፖርተራችን ያጠናቀረው ዘገባ ያመለክታል።

Share

4 comments on “ሁለት ፓርቲዎች የተቃውሞ ሰልፍ አስበዋል፤ መድረክ ጥሪውን ውድቅ አደረገ፣ መኢአድ አጤነዋለሁ አለ

  1. @solac,
    መልካም መኝታ! ብቻ ጥሩ ህልም አይተህ ተነሳ፡፡ በዛው እንዳትቀር አደራ፡፡ መቼስ ህልም አይከለከል ብሏል ጓድ መለስ፡፡

  2. Ethio-fact you ought to be proud of yourselves. Reporting at its best! The other so called websites should take a leaf out of your book. BRAVO!

  3. Berhane,

    I totally concur with you. Balanced and fair reporting–journalism par excellence.

Comments are closed