Logo

አንድነት ፓርቲ “ፍኖተ ነፃነት” የሚል የፓርቲ ልሣን ማዘጋጀት ጀመረ

August 6, 2011

የጋዜጣው የመጀመሪያ እትም ማክሰኞ ሐምሌ 26 ቀን 2003 ዓ.ም በአስራ ስድስት ገፆች ተዘጋጅቶ ገበያ ላይ መዋሉን ሪፖርተራችን የላከልን ዘገባ አመልክቶ፤ ጋዜጣው በፖለቲካዊ፣ በማህበራዊ፣ በመዝናኛ፣ በኢኮኖሚያዊና እና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚያተኩር በመጀመሪያው የጋዜጣው እትም የማስተዋወቂያ ገጽ ላይ መገለጹን ጨምሮ ገልጿል።

ይኸው የአንድነት ፓርቲ ልሣን በቀድሞው የኢሠፓ ልሳን የሰርቶ አደር ጋዜጣ አዘጋጅ በነበረው በመቶ አለቃ አንዳርጌ መስፍን ዋና አዘጋጅነት የሚዘጋጅ መሆኑን ሪፖርተራችን ጠቁሞ፣ በጋዜጣው አምደኛነትም የስምንት ፖለቲከኞች የስም ዝርዝር ተገልጿል ብሏል። ይሁን እንጂ በዓምደኛነት (በጽሁፍ አቅራቢነት) የስም ዝርዝራቸው ከተጠቀሱት ግለሰቦች ውስጥ አንዳንዶቹ ከአንድነት ፓርቲ ውጭ ያሉ የመድረክ አመራር አባላት ጭምር በመሆናቸው፣ ጋዜጣው የመድረክም ልሣን ሆኖ የማገልገል ሚና እንዲጫወት የታሰበ መሆኑን የሚጠቁም ነው ሲል ሪፖርተራችን በላከልን ዘገባ አመልክቷል። 

የአንድነት ፓርቲ ልሣን የሚዘጋጀው የፓርቲውን ርዕዮተ-ዓለም ወደ ሕዝብ ለማድረስ እንጂ ለትርፍ የተቋቋመ አለመሆኑን የአንድነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዱዓለም አራጌ መግለጻቸውም ታውቋል።

የጋዜጣውን ስርጭት በተመለከተ የተጠየቁት አቶ አንዱዓለም፣ የመጀመሪያው እትም አዲስ አበባን ጨምሮ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች መሰራጨቱን ገልጸው፣ ከቀጣዩ እትም ጀምሮ በሁሉም ክልሎች የሚከፋፈልበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑን አብራርተዋል ሲል ሪፖርተራችን ጨምሮ ገልጿል።

የፓርቲ ልሣን (Party Organ) በቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት እና በመሳሰሉት ኮሚኒስት ፓርቲዎች ባሉባቸው ሀገሮች እንጂ በምዕራባውያን አገሮች በሚገኙ ዴሞክራቲክ ፓርቲዎች እንደማይዘጋጅ ሪፖርተራችን አስታውሶ፣ በኢትዮጵያ ያሉ ፓርቲዎች ግን (ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ) የፓርቲ ልሣን የማቋቋም አቅጣጫን ይከተላሉ። ይህም “የፓርቲ ልሣን” ከሚለው ቃል ጀምሮ ከኮሚኒስት ፓርቲዎች የተወረሰ የግራ ፖለቲካ ቅኝት ውጤት ነው በማለት አብራርቷል።

የጋዜጣው የፊት ለፊት ሽፋን

Share