Logo

ከመኢአድ የተባረሩት እነ ማሙሸት አማረ አዲስ ፓርቲ ያቋቁሙ ይሆን?

September 1, 2011

የመዐሕድ የወጣት ክንፍ አባላት የነበሩት እነ አቶ ልደቱ አያሌው ልዩነታቸውን በፓርቲው ውስጥ በውይይት መፍታት ሳይችሉ ቀርተው በመባረራቸው ከሌሎች ወጣቶች ጋር ተሰባስበው በ1992 ዓ.ም ኢዴፓን ለመመስረት በቅተዋል፡፡

ከምርጫ 1997 በኋላ ደግሞ የመኢአድ ምክትል ፕሬዝዳንት በነበሩት በአቶ ሙላት ጣሰው እና በእነ ኢ/ር ኃይሉ ሻውል መካከል የተነሳው የሃሳብ ልዩነት እየተካረረ ሄዶ እነ ሙላት ጣሰው እንዲባረሩ በማድረግ የውስጥ ችግሩን ለጊዜው ለማርገብ ቢቻልም፣ ይህም እርምጃ እንደ ኢዴፓ ሁሉ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ውስጥ አዲስ ፓርቲ እንዲወለድ አድርጓል፡፡ በዚህም ምክንያት ብርሃን ለአንድነትና ለዴሞክራሲ (ብርሃን) ፓርቲ ለመመስረት በቅቷል፡፡

የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መዐሕድ) ወደ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በተሸጋገረበትም ወቅት ይህንን ሽግግር ያልደገፉ ወገኖች በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ አስተባባሪነት መዐሕድ እንዲቋቋም በማድረጋቸው እስከ አሁን ድረስ ይህንን ስም ይዘው እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የመኢአድ ጉዳይ በዚህም አያበቃም፡፡ ከታህሳስ ወር 2003 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባዔ በኋላ በድርጅቱ አመራሮች መካከል በተፈጠረው ውዝግብ ከፍተኛ አመራሩ ቡድን ለይተው እስከ መደባደብና አንዱ ሌላውን ሲያባርርና ሲያግድ ከርሞ በመጨረሻ በኢ/ር ኃይሉ የሚመራው ቡድን ነባርና መዐሕድን መስራች የነበሩ አባላቱን ጭምር በማባረር አሸናፊነቱን ያረጋገጠ ሲሆን፣ ተባራሪው የእነ ማሙሸት አማረ ቡድን የተለያዩ አማራጮችን እያነሳ እየጣለ በመምከር ላይ መሆኑን ሪፖርተራችን ያጠናቀረው ዘገባ አብራርቷል፡፡

ሪፖርተራችን ለአቶ ማሙሸት ቅርብ የሆኑ ምንጮችን ዋቢ አድርጎ በላከልን መረጃ መሰረት፣ የእነ ማሙሸት ቡድን እነ ኢ/ር ኃይሉ ሐምሌ 30 ቀን 2003 ዓ.ም ያደረጉትን የላእላይ ምክር ቤት ስብሰባ “ሕገ ወጥ ነው” በማለት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አቤቱታ ቢያቀርቡም አድማጭ ባለማግኘታቸው የቡድኑ አባላት ሌሎች መንገዶችን ለማየት መገደዳቸው ታውቋል፡፡

በዚህም መሰረት እነ ማሙሸት አማረ ከአዲስ አበባ እስከ ክልል ያሏቸውን ደጋፊዎች ይዘው፣ በመንቀሳቀስ ላይ ካሉት ፓርቲዎች አንዱ ጋር መጠቃለል የሚለው አንደኛ አማራጭ ሲሆን፤ በዚህም መሰረት በ2002 በተደረገው ምርጫ የጎላ ተሳትፎ ከነበረው ኢራፓ እና ከመኢዴፓ ጋር በመቀላቀል አንድ ጠንካራ ፓርቲ ለመፍጠር፣ ይህ የማይሳካ ከሆነ ደግሞ ወደ አንድነት ፓርቲ መቀላቀል የሚሉ አማራጮች ቀርበዋል ተብሏል፡፡

ሌላ አዲስ ፓርቲ የመመስረቱ አማራጭ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ ተደርጎ የተተወና የተዘጋ ባይሆንም እነ አቶ ማሙሸት አማረ በአሁኑ ወቅት ይህንን ለማድረግ ዝንባሌ እንደሌላቸው ምንጮች ለሪፖርተራችን ገልጸዋል፡፡

የእነ አቶ ማሙሸት ቡድን ከላይ ወደተገለጹት አማራጮች ያዘነበለው ለምርጫ ቦርድ ያቀረበው አቤቱታ ውድቅ በመደረጉና ከእነ ኢ/ር ኃይሉ ጋር ለመታረቅ ያደረገው የሽምግልና መንገድ ፍሬ በማጣቱ መሆኑንም ሪፖርተራችን ጨምሮ ገልጿል፡፡

Share

2 comments on “ከመኢአድ የተባረሩት እነ ማሙሸት አማረ አዲስ ፓርቲ ያቋቁሙ ይሆን?

  1. Let us see a party led by Mamushet, ex-DERG lieutenant! Ohhhh!… Mother Ethiopia in your name…

  2. Mnor melkam neger hulun yasayal.Mamushet k mead tebarere.Mead yeteshale selam yagengal.
    TILKU yewshet fabrika wodeke.Tayeng eko Mamushet party simesert.Mesadeb lela merat lela.
    Mamushetn yemikebel party kale berasu metfat yetemenge mehon albet.

Comments are closed