Logo

ህግ መንግስቱ “ከበባን” አሸንፎ እንዲዘልቅ የማድረግ አስፈላጊነት

January 10, 2012

ሰቴንግል በዚህ ጹሁፉ በአሜሪካ ህገ መንግስት ዙሪያ ከህገ መንግስቱ የመጀመሪያ ዓመታት ጀምሮ በአሜሪካዊያን መካከል እጅግ የተራራቁ ሀሳቦች ሲጋጩና ሲፋጩ የኖሩ መሆናቸዉን ይተነትንና ሁለት እጅግ አስፈላጊ ነጥቦችን ያነሳል ፡፡የመጀመሪያዉ አነኝህ ህገ መንግስቱ በሚዘጋጅበት ሂደት በህግ መንግስቱ አባቶች መካከል ከነበሩ ልዩነቶችና ፍጭቶች የበለጠ ሰፍተዉና ተራሪቀዉ የማያዉቁ መሆናቸዉ ነዉ፡፡ሁለተኛዉ ህገ መንግስቱ በመቶዎች በሚቆጠረዉ ዓመታት ዕድሜዉ በእነኝህ በተራራቁ ሀሳቦች መካከል የሚደረጉበትን ከበባ አሸንፎ ታላቅ ሰነድነቱን እያረጋገጠ እስከዚህ ደረስ መዝለቁ ነዉ፡፡

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ከጸደቀ ዘንድሮ አስራ ሰባተኛዉ ዓመቱ ነዉ፡፡ ባለፉት ዓመታት በኢፌደሪ ህገ መንገስት ዙሪያ ከመነሻዉ ጀምሮ የተለያዩና ተራራቁ ሀሳቦች ሲፋጩና ሲጋጩ ቆይተዋል፡፡ እነኝህ ምንም ያህል እርስ በርስ የሚቃረኑ ቢሆኑም ሁሉም ከኢትዩጵያ ታሪክና ፖለቲካ መሰረታዊ እዉነታዎች የሚመነጩ ናቸዉ፡፡የኢፌዴሪ ህገ መንግስትን ከአሜሪካ ህገ መንግስት ፤የኢትዩጵያን ዴሞክራሲን ከአሜሪካ ዴሞክራሲ እድገት ደረጃ ጋር ማነጻጸር ያስቸግራል፡፡ ነገር ግን በማነኛዉም ደረጃ የሚገኝ ዴሞክራሲ የጋራ በሆኑ እሴቶችና መንፈሶች መነሻነት ምን መሆን ሲገባዉ ምን እየሆነ እንደሆነ ማየትና ማሳየት ይቻላል፡፡
ለዘህ መነሻ በኢትዩጵያ ህገ መንግስት ዙሪያ አንዳንድ ሀሳቦችን እናነሳለን፡፡እነኝህን ልዩነቶች የግሌን እምነት በሚያንፀባርቁ መልኮች መቅረባቸዉ የተደበቀ አይደለም፡፡

በዚህ አጭር ጹሁፍ ሶስት ሀሳቦችን እናነሳለን፡፡የመጀመሪያዉ ለመሆኑ በኢፌዴሪ ህገ መንገስት ዙሪያ ከመነሻዉ ጀምሮ ሲፋጩና ሲጋጩ የቆዩት የልዩነት ሀሳቦች ምንድናቸዉ የሚለዉ ነዉ፡፡ ሁለተኛዉ ከህገ መንግሰቱ ተግባራዊነት አኳያ አገራችን የህገ መንግስቱን ዘላቂነት በሚያረጋግጥ ህገ መንግስታዊነት ሂደት ላይ ነች ወይ የሚለዉ ነዉ፡፡ ሶስተኛዉ መንግስት በሚያወጣቸዉ ህጎችና ሌሎች እርምጃዎች እንዲሁም አስደማሚ በሆኑ ፖለቲካዊ ህፀፆችን ላይ ከህገ መንግስቱ አንጻር ጥያቄ እያነሳንባቸዉ በግልጽ ልንወያይ የሚያስፈልግ መሆኑን እናነሳለን፡፡ ህገ መንግስቱ አሜሪካዊ ጸሀፊ በሚያስረዳን መልክ የሚደረግ “ከባብ” እያሸነፈ እንዲዘልቅ ካልተደረገ በምን ሁኔታ የአዲስቱ ኢትዩጵያ ምሶሶ ሆኖ ይቀጥላል የሚለዉ የዚህ ጹሁፍ ዋነኛዉ ጥያቄ ነዉ፡፡

1.በኢፌዴሪ ህገ መንግስት ዙሪያ ከወዲህና ወደያ የሆኑ ሀሳቦች

እንደኢህአዴግ አስተሳሰብ የኢትዩጵያ ፖለቲካ መሠረታዊ ቅራኔ የብሄር ጭቆና ነዉ፡፡ ከዚህ መነሻ በመነሳት ኢህአዴግ የህገ መንግስቱ መሰረታዊ ዓላማ ከኢትዩጵያ የብሄር ጭቆናን ማስወገድ እንዲሆንና የዚህም ማረጋገጫ የዜጎች መብቶች ሣይሆን የብሄሮች መብቶች ቅድሚያ የሚሰጣቸዉ እንዲሆኑ አደርጓል፡፡ኢህአዴግ የብሄሮች ሁለንተናዊ መብቶች ባልተረጋገጡበት ሁኔታ አገሪቱም እንደአገር የምትቀጥል አትሆንም ሲል ቆይቷል፡፡ ህገ መንግስቱም የብሄር/ብሄረሰቦችነ መብት ማረጋገጫ መሳሪያ እንዲሆን የዜጎች ሰነድ ሳይሆን የብሄር/ብሄረሰቦች ሰነድ አንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህንን በ1994 የማስታወቂያ ሚ/ር ያሳተመዉ አንድ
ሰነድ ህገ መንግስቱ “ዜጎች በተናጠል የወሰኑበት ሳይሆን ብሄር/ብሄረሰቦች እንደብሄር ብሄረሰቦች በተወካዩቻቸዉ አማካኝነት የጋራ ዓላማዎቻቸዉና እምነቶቻቸዉ ማስፈጸሚያ ይሆናል ብለዉ ያፀደቁት የቃል ኪዳን ሰነድ ነዉ፡፡” ብሉ ያስረዳል፡፡

በመሠረቱ ዜጉች በህገ መንግቱም ሆነ በሌላ ነገር ላይ እንደዜጋ በጋራ እንጂ በተናጥል የሚወስኑበት አግባብ ሊኖር አይችልም፡፡የብሄር ብሄረሰቦች ተወካዮች የየብሄረሰቦቻቸዉን ተወላጆች የሚወክሉ በመሆናቸዉ ተወላጆቹ እንደሰዉ ሚቆጠሩ ስለሆኑ ያዉ ዜጎች እንጂ ሌላ አይደሉም፡፡ችግሩ ኢህአዴግ ብሄር /ብሄረሰቦች ሲል የብሄረሰብ የጋራ ፍላጎትን ከብሄረሰብ አባላት የተናጠል ፍላጎት ድምርነት ነጥሎ የሚመለከት መሆኑ ነዉ፡፡አንዳንዴ የአህአዴግ የብሄር/ብሄረሰብ አስተሳሰብ ብሄር ብሄረሰቦች ሰዎች ካልሆነ ሌላ ማናቸዉ የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡

በወቅታዊዉ የኢትዩጵያ ፖለቲካ የብሄር መብት መከበር አለበት ወይስ መከበር የለበትም የሚለዉ የልዩነት መነሻ ሆኖ አያዉቅም፡፡የብሀር/ብሀረሰቦችን መብት ማስከበር የኢትዩጵያ ፖለቲካዊ ትግል አንደኛዉ ዓላማ ሆኖ ቆይቷል፡፡ አካራካሪዉ ጉዳይ የብሄር ብሄረሰቦች መብት እንዴትና እስከየት ይከበር የሚለዉ ነዉ፡፡በአንዳንድ ሰዎች አስተሳሰብ ህገ መንግስቱ የግለሰብ መብትን መነሻ አድርጎ የቡድን መብትን የሚያስከብር ቢሆን የቡድን መብትንና የግለሰብ መብትን ሣይነጣጠል ለማስከበር የተሻለ ይሆን ነበር፡፡በህገ መንግስቱ ለቡድን መብቶች ቅድሚያ የተሰጠበት ሁኔታ ለግለሰብ መብቶች መታፈን ምክንያት ሆኗል፡፡አቶ
ልደቱ አያሌዉ “መድሎት” በተባለዉ መጽሐፋቸዉ ህገ መንግስቱ የዜግነት መብት ከእያንዳንዱ ኢትዩጵያዊ ዜግነት ጋር ተያይዞ መታየቱ ቀርቶ ከቡድን መብት ጋር ተያይዞ ብቻ እንዲታይ በማድረግ የኢትዩጵያዊ ዜጎቸን የአገር ባለቤትነትን መብት ነጥቋል ይላሉ፡፡ ይህ የአህአዴግን አስተሳሰብን የሚቃረን ነዉ፡፡ከላይ በተጠቀሰዉ የማስታወቂያ ሚ/ር ህትመት ኢህአዴግ የህዝቦች መብት መከበር የዜጎች መብትን ለማስከበር ብቸኘዉ አማራጭ ነዉ የሚል ቢሆንም ህገ መንግስቱ የግለሰብ መብትንም ያከብራል ብሎ ይከራከራል፡፡በህገ መንግስቱ በአንቀጽ 25 ስለግለሰብ መብቶች የተደነገጉትን በመተንተን “ህገ መንግስታችን በጋራ
ብቶች ሽፋን የግለሰብ መብት መርገጥ የተከለከለ መሆኑን በግልጽ ያስቀምጣል”ይላል፡፡

ሌላ እጅግ ሲያከራክር የቆየዉ ጉዳይ የመገንጠል መበት ጉዳይ ነዉ፡፡የብሄሮች/ብሄረሰቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጉዳይ የማያከራክር ቢሆንም ይህ መብት እሰከመገንጠል ድረስ ህገ መንግስታዊ መብት መሆኑ የከፍተኛ ብሄራዊ ፖለቲካዊ ልዩነት ምንጭ ሆኖ ቆይቷል፡፡ኢህአዴግ ለብሄሮች የመገንጠል መብትን ማረጋገጥ በኢትዩጵያ ያልተገደበ መብት ያላቸዉ መሆኑን ተረድተዉ ይኖራሉ ይላል፡፡በ1997 ዓ.ም ኢህአዴግ “ዴሞክራሲና ዴሞክራሲያዊ አንድነት በኢትዩጵያ” በሚል ረዕስ ባሳተመዉ አንድ ሰነድ ላይ በኢትዩጵያ ለብሄር/ብሄረሰቦች የመገንጠል መብትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስገድዱ ሶስት ሁኔታዎችን ይተነትናል
፡የመጀመሪያዉ ብሄር/ ብሄረሰቦች መብት ተረጋግጦላችኋል ስለተባሉ ብቻ የአንድነት አማራጭን ይከተላሉ ማለት የማይቻል ስለሆነ የሚል ነዉ፡፡ የመገንጠል መብት መኖሩ መብቶቻቸዉ ሁሉ የተረጋገጠላቸዉ ስለመሆኑ ዋስትና ነዉ የሚል ክርከር ነዉ፡፡ሁለተኛዉ ብሄራዊ ጭቆና እንደገና እንዳይመጣ መከላከያ ነዉ የሚል ነዉ፡፡ ሶስተኛዉ ኢትዩጵያዊነትን የማይፈለግ ብሄር ካለ በሰላም እንዲሰናብት ማደረግ ስለሚያስፈልግ የሚል ነዉ፡፡

በእዉነት ይህ እጅግ አስገራሚ ክርክር ነዉ፡፡ በመጀመሪያ ብሄር /ብሄረሰቦች መብቶቻቸዉ መከበሩ በህገ መንግስት ከተረጋገጠ በዚህ ተማምነዉ ብቻ ህዝባዊ አንድነት አማራጭን የማይከተሉበት ምክንያት ምንድነዉ?ምናልባት የተረጋገጠዉ መብት በስራ ላይ አይዉልም የሚል ስጋት አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ይህ ከሆነ መፍትሔዉ በህገ መንግስት የተረጋገጡ መብቶች ተግባራዊ የሚሆኑበትን አማራጭ ማስፋት እንጂ እንዴት የመገንጠል መብት መኖር በራሱ መተማመኛ ወይም ማሳመኛ ይሆናል? የሁለተኛዉ መከራከሪያ በሌላ አገላለጽ ብሄር ብሄረሰቦችን መብቶች የማያከብሩ ሓይሎቸን ማስፈራሪያ ነዉ ማለት ነዉ፡፡በመሰረቱ ማነኛዉም
መብት መከበር ያለበት በተወሰኑ ሓይሎች ፍላጎትና ፍቃድ መነሻነት ወይም ማንንም ለማስፈራራት መሆን የለበትም፡፡ ሁሉም መብቶች መከበር ያለባቸዉ ከመሆኑ በተጨማሪ የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶችን ማስከበርና ማክበር የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መሰረታዊ ዓላማ ስለሆነ እንጂ፡፡በዴሞክራሲያዊ ስርዓት መዳበር ሂደት የሚፈጠር ህገ መንግስታዊነት ዕድገት የአንዳንድ ሃይሎች ፖለቲካዊ ፍላጎት ከሌሎች ወገኖች መብት በታች የሚሆንበትን ሁኔታ የሚፈጠር መሆኑ ካላከራከረ መፍትሄዉ የዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለሁሉም መብቶች መረጋገጥ በቂ ዋስትና ወደሚሰጥበት ደረጃ ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆን እንጂ እንዴት ተብሎ ነዉ የመገንጠል መብት የአንዳንድ ሐይሎች ፖለቲካዊ ፍላጎት መግቻ ተደርጉ መወሰድ የሚገባዉ? መገንጠልን የሚያስከትሉ ሁኔታዎች ሊከሰቱ አይችሉም የሚል ክርክር የለኝም፡፡ የሚሻለዉ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንዳይከሰት የመብቶች ሰርዓታዊነትን ማረጋገጥ ወይስ በማንኛዉም ምክንያት አልተመቸኝም የሚል ሁሉ ለቆ እንዲወጣ በር ከፍቶ ማመቻቸት? የአገር አንድነት አሰፈላጊነትን የማይጠረጥር ኃይል የህዝቦች ሰብአዊና ዴመክራሲያዊ መብቶቻቸዉ በተሟላ ሁኔታ የሚረጋገጥበትን ዴሞክራሲያዊ ሰርዓት ፈጥሮ በአንድነት እንዲኖሩ ማድረግ የሚቻል ነዉ በሚል ቁርጠኝነት አንድነትን መገንባት ይጠበቅበታል እንጂ ያኮረፈን በሰላም ማሰናበት አማራጭን ለምን ያቀነቅናል?

በዓለም ላይ ብዙ ብሄር/ብሄረሰቦች ያላት አገር ኢትዩጵያ ብቻ አይደለችም፡፡ በአንድነት መኖርም የኢትዩጵያዊያን ምርጫ ብቻ አይደለም፡፡ዴሞክራሲያዊ ሰርዓትም ለዓለም የኢትዩጵያ ስጦታ አይደለም፡፡ዴሞክራሲን በገነቡ አገሮች ህዝቦች በአንድነት የሚኖሩት የዴሞክራሲያዊ ሰርዓቱ በፈጠራላቸዉ የመብት መረጋገጥ ዋስትናነት አንጂ መገንጠል መብት ስለተረጋገጠላቸዉ አይደለም፡፡የመገንጠል መብት እስካልተረጋገጠ የብሄር መብት መረጋገጥ መተማመኛም አይሆንም የአገር አንድነትም አይረጋገጥም የሚለዉ የአህአዴግ ክርከር በምንም መንገድ አሳማኝ አይደለም፡፡ይህ አጀንዳ ለኢህአዴግ ኢትዩጰያ እኔ እንደምፈልገዉ
ልተዋቀረችና ካልኖረች እኔ ብቻ ካልገዛኋት እንዲትፈርስ አደርጋለሁ ብሎ የሚያስፈራራበት አጀንዳ ነዉ፡፡ኢህአዴግ የብሄር መብት በኢትዩጵያ የሚኖረዉና የሚከበረዉ እሱ ብቻ በስልጣን ላይ እስከቆየ ድረስ ብቻ እንደሆነ የሚቀስቀሰዉም ለዚሁ ነዉ፡፡በዚህ መነሻነትም በህገ መንግስቱ የመገንጠል መብት መኖር ብዙ ፖለቲካዊ ሃይሎች የሚቃወሙት ሆኖ ቆይቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዩጵያ የመንግስት አወቃቀር ፌዴራላዊ እንዲሆን የማደረጉ ጉዳይ የሚያከራክር አይደለም፡፡አከራከሪዉ ጉዳይ የፈዴራል አወቃቀሩ መሪህ በዋነኛነት የብሄረሰብ አሰፋፈርና የቋንቋ ስርጭት መሆኑ ነዉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የአትዩጵያ ፌደራሊዝም በጎሳ ላይ የተመሰረተ (Ethnic Federalism) ተብሎ ይታወቃል፡፡ኢህአዴግ ይህን የብሄረሰቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን ለማረጋገጥ እንደቅድመ ሁኔታ ሲያስረዳን ቆይቷል፡፡ይሁን እንጂ አወቃቀሩ ከእነዚህ በተጨማሪ የህዝብ አሰፋፈርን ፍቃደኝነትን መልካዓ ምድርን የልማት አመቺነትንና ሌሎችን በሚያሰባጥር መልኩ አለመሆኑ የልዩነት ምንጭ ነዉ፡፡የመ
ት ይዞታ ጉዳይም እንዲሁ የልዩነት ምንጭ ሆኖ ይገኛል፡፡ ህገ መንግስቱ መሬት የመንግስትና የብሄር ብሄረሰቦች እንደሆነ በመደንገግ ዜጉች የመሬት ባለቤት እንዳይሆኑ አድርጓል፡፡ጥያቄየዉ ይህ የዜግነት መበት የሚያሳጣ መሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ለዕኮኖሚ እድገት አንጻርም ጎታች ይሆናል የሚል ነዉ፡፡

በህገ መንግሰቱ ዙሪያ የልዩነት ምንጭ ሆነዉ የሚገኙት እነኝህ ነጥቦች ብቻ አይደሉም፡፡እነኝህ ዋና ዋናዎቹ አከራካሪ ጉዳዮች ናቸዉ፡፡

2. የህገ መንግስታዊነት ጥያቄ

ካለፉት ቀርብ ዓመታት ጀምሮ ህገ መንግስቱን በህብረተሰቡ ዉስጥ ለማስረጽ በሚል በከፍተኛ ደረጃ ህገ መንግስቱን የማስተማር ስራዎች እየተከናዉኑ ነዉ፡፡ በዚህ ሂደት ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸዉን ጥያቄዎቸን የሚያጭሩ ነገሮች እየተስተዋሉ ነዉ፡፡ የመጀመሪያዉ ህገ መንግስቱ ምንም እንከን የሌለበት እንደሆነ ለማቅረብ የሚደረገዉ መከራ ነዉ፡፡ የየትኛዉም ዴሞክራሲያዊ አገር ህገ-መንገስትም ቢሆን እንከን የለዉም የሚባል አይሆንም፡፡ህገ-መንግስት ሰዎች የሚጽፉትና የሚሰሩት ሰነድ ነዉ፡፡ ህገ-መንግስት በህገ-መንግስትነቱ እንኳን የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት የአሜሪካ ህገ-መንግስትም ቢሆን ብዙ እንከኖች አሉበት፡፡ ህገ-መንግስት ፖለቲካዊ ሰነድ ነዉ፡፡ በየጊዜዉ ፖለቲካዊ ዉይይትና ክርከር ይደርግበታል፡፡ ይሻሻላል ይለወጣልም፡፡ይህን እያልኩ ያለሁት ህገ መንግስታችን ቀለል ተብሎ መታየት አለበት ከሚል መነሻ አይደለም፡፡ ህገ መንግስቱን የሚከበር ከማድረግ በላይ የሚፈራ እንዲሆን ከተደረገ በህገ መንግስቱ ላይ ጥያቄ ማንሳትና ህገ መንግስታዊ ጥያቄዎች ዙሪያ መወያየት አስፈሪ ይሆናል፡፡በዚያ ልክ ህገ መንግስቱ የመብት ምንጭ መሆኑ እየቀረ ይመጣል፡፡ለህገ መንግስቱም የማይበጀዉ ነገር ይህ ነዉ፡፡

ሁለተኛዉ በህገ መንግስቱ ዙሪያ አህአዴግ ከሚለዉ በተቃራኒ ያሉ ሀሳቦች ሁሉ በስህተት ላይ የተመሰረቱ እንደሆነ ተደርጉ እየቀረበ ነዉ፡፡ከላይ በአጭሩም ቢሆን የቀረቡ በህገ መንግስቱ ዙሪያ ያሉ ከአህአዴግ በተለየ የሚቀርቡ ሀሳቦች ጠንካራና በቂ መነሻ ያላቸዉ ለአገር ከማሰብና ከመቆርቆር የሚመነጩ መሆናቸዉን በቀላሉ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ኢህአዴግ ህገ መንግስቱን ሰዎች ከአህአዴግ አስተሳሰብ አንጻር ብቻ እንዲረዱ ጫና እየፈጠረ ነዉ፡፡ይህ ከህገ መንግስቱ አንጻር የተለየ አስተሳሰብ ያላቸዉ ሄይሎችን መብት ማጥበብ ነዉ፡፡ በሌላ በኩል ህገ መንግስቱን መጻረር ነዉ፡፡

ሶስተኛዉ ህገ መንግስቱን ማክበር መቀበልና ማመን የሚባሉ ነገሮች ጉዳይ ነዉ፡፡ህገ መንግስት የአንድ አገር ህጎች ሁሉ የበላይ የሆነ ህግ ነዉ፡፡ ይህ የህገ መንግስት በላይነት መሪህ አንደኛዉ የህገ በላይነት ማረጋገጫ ነዉ፡፡ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ ዘጠኝ ስለህገ መንግስቱ በላይነት ይደነግጋል፡፡ በዚሀ ድንጋጌ መሰረት መንግስት ፖለቲካዊ ፓርቲዎች ማህበራት ባለስልጣኖች ዜጎች ሁሉም ህገ መንግስቱን የማክበር ግዴታ አለባቸዉ፡፡ ይህ ሊያከራክር የሚገባ ጉዳይ አይደለም፡፡ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በየትኛዉም ዴሞክራሲያዊ አገር ወንጀል የሚሆነዉ ህገ መንግስትን አለማክበር እንጂ ህገ መንግስቱን አለመቀበልና በህገ መንግሰቱ አለማመን ሆኖ አያዉቅም፡፡ የትኛዉም ዴሞክራሲያዊ አገር ህገ መንግስት ሁሉም ዜጎች የሚያምኑበትና የሚቀበሉት ሆኖ አያዉቅም፡፡ነገር ግን ህገ መንግስትን ብቻ ሳይሆን ህግን በጠቅላላ ማክበር የዜጎች ሁሉ ግዴታ ነዉ፡፡ ህገ መንግስት የበለጠ መከበር አለበት፡፡ የህግ በላይነት መሪህም ይህንን ይጠይቃል፡፡ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ህገ መንግስቱ ከተመሰረተበት አሰተሳሰብ አንጻር እንዲሁም ከህገ መንግስቱ ድንጋጌዎች አንጻር ያሉ ልዩነቶችን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለማራመድ ራሱ ህገ መንግሰቱ ያገናጸፈዉም መብትም በአግባቡ መከበር አለበት፡፡

ባለፉት አስራ ሰባት ዓመታት ህገ-መንግስቱን መቀበልና አለመቀበል የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሓይሎችና የኢህአዴግ ዋነኛዉ የልዩነት አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ለመሆኑ የዚህ ምክንያት ምንድነዉ? ይህ እጅግ አስፈላጊ ጥያቄ ነዉ፡፡ ወደዚህ ጥያቄ ምላሽ ከመሄዳችን በፊት አንዳንድ ተቃዋሚዎች ህገ መንግስቱን የማይቀበሉ መሆናቸዉና በህገ መንግስቱም የማያምኑበት መሆናቸዉ ለኢህአዴግ ህገ መንግስቱን የማስከበር መንግስታዊ ስልጣኑን የመጠቀም መብቱን የማይቀንስበት መሆኑን አስምሮ ማለፍ ተገቢ ነዉ፡፡ይህ ከፍተኛ ችግር ተደርጎ መታየት ያለበት በአገራችን ከተጀመረዉ ዴሞክራሲያዊ ሰርዓት ግንባታ አኳያ ከሚያስፈልገዉ የጋራ
መግባባት አንጻር ነዉ፡፡እንግሊዛዊዉ የፖለቲካ ሳይንቲስት ሬግናልድ ባሴት(Reginald Basset) The Essentials of Parliamentary Democracy በሚለዉ መጽሐፉ ማነኛዉም ህገ-መንግስት የበላይ ህግ ሆኖ የሚገዛበትንና ፖለቲካዊ ሁኔታንና በሱ በላይነት ሥር የሚንቀሳቀሱ ፖለቲካዊ ኋይሎችን ባህርይንና ፍላጎትን የሚያቀራረብ እስካልሆነ ድረስ ተቀባይነቱ ደካማ እንደሚሆንና ቀጣይነቱም አጠያያቂ እንደሚሆን ያስረዳል፡፡ ይህ ስለ ህገ መንግስት የሚመራመሩ ሊቃዉንት ሁሉ የሚስማሙበት ነዉ፡፡ የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት በኢትዩጵያ ፖለቲካዊ ኃይሎች መካከል የጋራ ተቀባይነት ያጣበት አንዱ ምክንያት ለኢትዩጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት አማራጭነት ዙርያ በፖለቲካዊ ሓይሎች መካከል የአገራዊ መግባባት ማረጋገጫ እንዲሆን ሳይሆን የኢህአዴግን የተናጠል ድርጅታዊ እምነትንና ፋላጎትን የአገር ዕጣ ፋንታ ብቸኛ መወሰኛ ለማድረግ በሚያስችል መልክ ስለተሰናዳ ነዉ፡፡ ይህ ከባድና ቀጣይነት ያለዉ ችገር እንደሚሆን ኢህአዴግ አሰቀድሞ አልገመተም ይሆናል፡፡ ወይም ከዚህ አንጻር ያሉ መሰረታዊ እዉነታዎችን አምኖ መቀበል አልፈለገም ይሆናል፡፡የሆነ ሆኖ በአሁኗ ኢትዩጵያ ፖለቲካ ወስጥ ዋነኛዉ ችግር ይህ ነዉ፡፡ ይህ ህገ መንግስቱን ማሻሻል የፖለቲካ አጀንዳ መሆኑም የግድ ሆኗል፡፡

ኢህአዴግ ያንን ስህተት ለማረም የሚያስችሉ ሁለት ነገሮችን ስለማደረግ በጥንቃቄ ማሰብ መጀመር አለበት፡፡የመጀመሪያዉ በህገ- መንግስቱ የተደነገገዉ ስርዓታዊ መልክ በአገራችን እንዲያድግ የሚያስችል ፖለቲካዊ ማሳለጥ እያደረገ ህገ መንገስቱን መሰረት ባደረገ መልኩ በተገቢ ፖለቲካዊ ሓይሎች ህብረትና ትብብር ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ሰርዓት ለመመስረት እንድንችል መተባበር ነዉ፡፡ በፖለቲካ ሓይሎች ስምምነት ላይ ያልተመሰረተ ህገ መንግስትም ሆነ ስርዓት ዘለቄታ እንደማይኖረዉ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ሁለተኛዉ ኢህአዴግ ራሱ ህገ መንግስቱን ማክበር ያለበት መሆኑ ነዉ፡፡ አሁን እንደሚታየዉ ከሆነ ኢህአዴግ ራሱ በህገ መንግስቱ ላይ እየቀለደ ነዉ፡፡ ኢህአዴግ በህገ- መንግስቱ ከተቀረጸዉ ስርዓታዊ ማቀፍ ዉጪ አገሪቱን ጠቅልሉና ጨምቆ በመግዛት የህገ -መንግስቱን ቀጣይነትንና በኢትዮጵያ ስርዓታዊና ህገ- መንግስታዊነት አድገትን እያመከነ ነዉ፡፡ነጻና ሚዛናዊ ምርጫን ለማየት እየታደለን አይደለንም፡፡ በህዝብ ሀቀኛ ፍላጎት የተመረጠ መንግስትንና በህዝብ ሀቀኛ ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ ስርዓት ባለቤት ለመሆን አልቻልንም፡፡ በህግ የበላይነት ላይ ተመስርቶ በግልጽነትና ተጠያቂነት መሪህ የሚመራ መንግስታዊ አሰራር የለንም፡፡ በመንግስት አሰራር ዴሞከራሲ የሚጠይቀዉ የስልጣን ከፍፍል የለም፡፡ ነገር ግን እነኝህ ሁሉ የሌሉት በህገ መንግሰቱ ስላልተደነገጉ አይደለም፡፡

ዛሬ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ወሰጥ የዴሞከራሲያዊ መብቶች መረጋገጥ የመጨረሻ ማረጋገጫ ለሆነዉ ለዜግነት ሰብአዊና ፖለቲካዊ መብቶች ቦታ የለም፡፡ ለአንድ የብሄረሰብ አባል በህገ መንግስቱ የተደነገገዉ የግለሰብ መብቶችና ነጻነቶች የሚረጋገጡለት ዜጋ በመሆኑ ሳይሆን የኢህአዴግ አባል ወይም ደጋፊ ሲሆን ብቻ እንደሆነ በህግ የተደነገገ የመሰለበት ሁኔታ ሰፍኗል፡፡ አንድ ዜጋ የኢህአዴግ አባል ካልሆነ ወይም ኢህአዴግን ካልደገፈ በተሰማራበት የስራ መስክ በዜግነቱ ሊያገኝ የሚገባዉን ጥቅምና ክብር የማሳጣት ተግባር ይፈጽመበታል፡፡ የመንግስት ሠራተኛ በዜግነቱና በሰራተኝነቱ የሚገባዉን መብት ሊያገኝ የሚችለዉ የኢህአዴግ አባል ሲሆን ነዉ፡፡ ሌላዉ ቀርቶ በሙያዉ ከፍተኛ ችሎታ ያለዉ ትጉህ ሰራተኛ ቢሆን እንኳን ይህ ተገቢዉን እዉቅና የሚያገኘዉ የኢህአዴግ አባል ሲሆን ብቻ ነዉ፡፡ በህገ መንግስቱ ለአንድ ሰዉ የፈለገዉን ዓይነት የፖለቲካ አስተሳሰብ መቀበልና መከተል መብት ሆኖ የተደነገገ ቢሆንም አስተሳሰቡ ከኢህአዴግ አስተሳሰብ ጋር ተጻራሪ ከሆነ የተለያዩ ጥቃቶች ይፈፀምበታል፡፡ የአህአዴግ አባል ካልሆነ ሌላዉ ቀርቶ የስራ ዋስትና የለም፡፡ በደርግ ጊዜ ሰዎች ስርዓቱን አስካልተቃወሙ ድረስ የመስራትና የመኖር ዋስትና የሚያሳጣቸዉ አደጋ እንደድንገት እንደማይገጥማቸዉ መተማመን ይችሉ ነበር፡፡ ዛሬ የኢህአግ ደጋፊ እስካልሆኑ ድረስ የዜግነት መብትነንና ነጻነትን የሚያሳጣ አደጋ በየተኛዉም አቅጣጫ በጣም ቅርብ ነዉ፡፡አንስተኛ ብድር ለማግኘት በአንስተኛና ጥቃቅን ተደራጅቶ ተጠቃሚ ለመሆን የመንግስት ሰራተኛ ሆኖ ለመቀጠር የሚያስችለዉ ዜግነት ወይም የብሄር ብሄረሰብ አባልነት ሳይሆን የኢህአዴግ አባልነት ነዉ፡፡ይህ ሆኖ የሚገኘዉ ዛሬም በኢትዮጵያ በሰዎች መካከል እኩልነት ባለመረጋገጡና በህገ መንግስቱ ለዜጎች የተረጋገጡ መብቶች የማይከበሩ በመሆናቸዉ ነዉ፡፡

በእዉነት ዛሬ የኢፌድሪ ህገ መንግስት የመብትና ነጻነት ህጋዊነት ማረጋገጫ እየሆነ ነዉ? ትልቁ ችግር ህገ መንግስቱ የማይከበር መሆኑ ነዉ፡፡ ህገ መንግስቱ መብቶችን በበቂ ሁኔታ የደነገገ ቢሆንም ከእነኝህ መብቶች ተግባራዊነት ይልቅ መብቶች ሁሉ የተረጋገጡ ናቸዉ የሚለዉን ፖለቲካ ይበልጥ እያገለገለ ነዉ፡፡ ትልቁ እንቅፋት ህገ መንግስቱ የደነገጋቸዉ መብቶችን መነሻ ያደረገ የነጻነት አስተሳሰብ ራሳቸዉን የህገ መንግስቱ ባለቤትና ጠባቂ ባደረጉ ሰዎች አስተሳሰብ ውስጥ አለመኖሩ ነዉ፡፡አሜሪካዊ ዳኛዉ ለርኒድ ሀንድ(Learned Hand) “ከሁሉም በላይ ነፃነት በሰዎች ልብ ወስጥ የሚገኝ መሆን አለበት፡፡ በሰዎች ልብ ዉስጥ የማይገኝ ነፃነትን ህገ መንግስት ከየትም አያመጣም፡፡ ህገ መንግስት ስላለ ብቻ ነጻነት አለ ማለት አይቻልም “ ያለዉ ከአሁኗ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር እጅግ አስፈላጊ አባባል ነዉ፡፡

3. ህገ መንግስቱ “ከበባን” አልፎ እንዲዘልቅ የማድረግ አስፈላጊነት

የታይም መጽሄት ፀሐፊ ከበባ ያለዉ በአሜሪካ ህገ መንግስት ዙሪያ የሚደረገዉን የጋለ ክርከርና አልፎ አልፎ የመንግስት እርምጃ የሚያስከትለዉን ህገ መንግስታዊ ጥያቄንና ዉዝግብን በተለይም በህግ አዉጪዉና በህግ አሰፈጻሚዉ መካከል የሚደረገዉን መቆራቀስ ነዉ፡፡ ይህ በተደላደለ ዴሞክራሲ (functioning democracy)የዕለት ተዕለት ፖለቲካ ነዉ፡፡ በሰላማዊና በሰለጠና መንገድ እሰከተከናወነ ድረስ በየተኘዉም ዕድገት ደረጃ ላይ ለሚገኝ ዴሞክራሲ የሚያስፈራ መሆን የለበትም፡፡በሁሉም አስፈላጊ ጉዳዮች ላይ መከራከር መወያትና መደራደር በዚህም ሂደት መስጠትንና መቀበልን ተቋማዊ በማድረግ ልዩንትን እያጠበቡ መጓዝ የዴሞራሲያዊ ፖለቲካ ባህርይ ነዉ፡፡

ከዚህ መነሻ በመነሳት እርስ በርስ በሚቃረኑ ሀሳቦች መካከል በሚደረጉ ጤናማ ግጭቶችና ፍጭቶች እንዲሁም የህገ መንግስት ጥቄን ስለሚያስነሱ ህጎችና የመንግስት እርምጃዎች በግልጽ በሚደረጉ ክርክሮችና ወይይቶች ሂደት ከበባ አሸንፎ ነጥሮ እየወጣ በእያንደንዱ ደረጃም ጊዜዉ በሚጠይቀዉ መጠን እየተሻሻለና እየተለጠጠ መጓዝን ታሳቢ ያላደረገ ህገ መንግስት እንዴት አድርጉ የአገር ፖለቲካ ምሶሶ ሆኖ ሊቀጥል ይችላል?

ተመሳሳይ አስተሳሰብና አቋም ያላቸዉ ሰዎች በየጊዜዉ እየተሰበሰቡ ስለህገ መንግስቱ እንከን የለሽነት ቃላትን በማዝነብ እንዲሁም ከህገ መንግሰቱ አንጻር ተቃራኒ አቋም ያላቸዉን ወገኖች በማዉገዝ የሚያጠናቀቁት ስብሰባዎች ህገ መንግሰቱንም ሆነ ህገ መንግስታዊነትን የሚረዱ ስለአለመሆናቸዉ እርግጠኛ መሆን ይቻላል፡፡ከላይ በተገለጸዉ ፖለቲካዊ ሂደት በህገ መንግስቱ ዙሪያ ላሉ ሀሳቦች ሁሉ በቂ እድል አየተሰጠ የሚንሸራሸሩ ቢሆኑ አንዳቸዉ በሌላቸዉ ላይ የሚያገኙት ተገቢ በላይነት እየተረጋገጠ ተቋማዊም እየሆነ ያድጋል፡፡ይህ ከህገ መንግስቱ ተግባራዊ ሂደትና ከህገ መግስታዊ አድገት ጉዞ ጋር በቁርኝት እያሳለጠ በቀጠለ ቁጥር ህገ መንግስቱ እየዳበረ ተቀባይነቱና ተከባሪነቱ እየሠፋ ከትዉልድ ወደትዉልድ የሚሸጋገር ይሆናል፡፡የህገ መንግስቱን ዕድሜ አጭር ሊያደርገዉ የሚችለዉ ለእንዲህ ዓይነት ሂደት ክፍት አለመሆኑ እንጂ አንዳንድ ወገኖች የማይቀበሉና የማያምኑበት መሆናቸዉ ሊሆን አይችልም፡፡ የአገራችን መሪዎች ይህን ዓይነቱን ሂደት ፈርተዉ ስለአቋማቸዉ ትክክለኛት በፈጠሩት ጠባብ ዓለም ታጥረዉ ሌሎች ወገኖች ከእነሱ ጋር ስላልተሰማሙበት ምክንያት ደካማነት ብቻ እንድናስብ ማስገደድን የመጨረሻ ምርጫቸዉ አድርገዉ እስከቀጠሉ ድረስ የሚያረጋግጡልን እዉነታ የጠሉትን መታገልና የታገሉትን ማሸነፍን እንጂ ዘመናዊ አገርንና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን የመገንባት ችሎታ እንደሌላቸዉ ብቻ ነዉ፡፡

Share

2 comments on “ህግ መንግስቱ “ከበባን” አሸንፎ እንዲዘልቅ የማድረግ አስፈላጊነት

  1. በዓለም ላይ ብዙ ብሄር/ብሄረሰቦች ያላት አገር ኢትዩጵያ ብቻ አይደለችም፡፡ በአንድነት መኖርም የኢትዩጵያዊያን ምርጫ ብቻ አይደለም፡፡ዴሞክራሲያዊ ሰርዓትም ለዓለም የኢትዩጵያ ስጦታ አይደለም፡፡ዴሞክራሲን በገነቡ አገሮች ህዝቦች በአንድነት የሚኖሩት የዴሞክራሲያዊ ሰርዓቱ በፈጠራላቸዉ የመብት መረጋገጥ ዋስትናነት አንጂ መገንጠል መብት ስለተረጋገጠላቸዉ አይደለም፡፡የመገንጠል መብት እስካልተረጋገጠ የብሄር መብት መረጋገጥ መተማመኛም አይሆንም የአገር አንድነትም አይረጋገጥም የሚለዉ የአህአዴግ ክርከር በምንም መንገድ አሳማኝ አይደለም፡፡ይህ አጀንዳ ለኢህአዴግ ኢትዩጰያ እኔ እንደምፈልገዉ
    ልተዋቀረችና ካልኖረች እኔ ብቻ ካልገዛኋት እንዲትፈርስ አደርጋለሁ ብሎ የሚያስፈራራበት አጀንዳ ነዉ፡፡ኢህአዴግ የብሄር መብት በኢትዩጵያ የሚኖረዉና የሚከበረዉ እሱ ብቻ በስልጣን ላይ እስከቆየ ድረስ ብቻ እንደሆነ የሚቀስቀሰዉም ለዚሁ ነዉ፡፡በዚህ መነሻነትም በህገ መንግስቱ የመገንጠል መብት መኖር ብዙ ፖለቲካዊ ሃይሎች የሚቃወሙት ሆኖ ቆይቷል፡

Comments are closed