Logo

የአቶ በረከት ስምኦን መጽሐፍ

January 10, 2012

የሁለቱ ረዕሰ ብሄራን መጽሀፎች ብቻ ሳይሆኑ የእነሱም ፖለቲካዊ ማዕቀፍም የማይገናኙ የነበረ ቢሆኑም ይህ መሆኑ በራሱ ትልቅ ነገር ነዉ፡፡ በቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ ጊዜ በከፍተኛ የአገር ኀላፊነት ላይ የነበሩ በደርግ ጊዜ ወታደራዊና ፖለቲካዊ መሪ የነበሩ ብዙ ሰዎች መጽሀፎችን ጽፈዋል፡፡ደርግን በገለበጠዉ ሰልፍ ውስጥ ዋነኛ ተዋናያን ሆነዉ ቆይተዉ ከቀድሞ ትግል ጓደኞቻቸዉ ጋር በሀሳብም ይሁን በጥቅም ተጋጭተዉ የተለዩ ሰዎችና በተቃዋሚዉ መተራመስ ዉስጥም ግንባር ቀደም የነበሩ ሰዎችም መጽሀፎችን ጽፈዋል፡፡ ይህ አብዩት ነዉ፡፡ ይህ አብዩት የተለመደዉን የኢትዩጵያ ፖለቲካ ምስጥረኝነትና ከሃሳብ እጥረት የሚመነጩ ወስብስብ ችግሮችን ይፈታ ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡

የአቶ በረከት መጽሐፍ ከላይ ከዘረዘርኳቸዉ ለየት ብሎ እንዲታይ የሚያደርግ አንድ ምክንያት ያለ መሆኑ ይሰማኛል፡፡ መጽሐፎቻቸዉን እያስነበቡን ያሉ የታላላቅ ታሪካዊ ሂደትና ድርጊት ተካፋዮች ብዙዎቹ የጻፉት በተጻፉባቸዉ ሂደቶች ከገጠማቸዉ ፈተናና ከደረሰባቸዉ ዉድቀት በመነሳት ራሳቸዉን ለመከላከልና የባለጋራዎቻቸዉን ማንነት በማሳየት ላይ በማተኮር ሲሆን የጥቂቶቹ ምስክርነት ነዉ፡፡ ምናልባት አቶ ልደቱ ከጻፉት ሁለት መጻፎች መካከል “መድሎት” ከድርጊቶች ትረካ ይልቅ በጉዳዩች ላይ ያተኮረ በመሆኑ ለየት ይል ይሆናል፡፡ ብዙዎቹ ባለታሪክ የሆኑ ጸሀፊዎች በሥልጣን ቆይተዉ የነበሩና ለስልጣን በመፋለም ላይ ያሉ በማለት ለሁለት ከፍለን ልናያቸዉ እንችላለን፡፡ የአቶ በረከትን መጽሀፍ ልዩ የሚያደርገዉ ከሁለቱም ያልሆነ በስልጣን ላይ ካሉ ሰዎች ተርታ በቀጥታ የቀረበ መሆኑ ነዉ፡፡ በስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ከስልጣናቸዉ ላይ ወደዉ ሳይሆን ተገደዉ ከወረዱ በኋላ ስለወረዱበት በምረት ከሚጽፉ በስልጣናቸዉ ላይም ሆነዉ ወደስልጣን ስለመጡበት በሥልጣን ላይ ሆነዉም ስለወሰኑት ዉሳኔና ስላደረጉት ድርጊት ምክንያትና ዉጤት ከግላቸዉ እምነትና ምኞት አንጻር በእንዲህ መልክ ቢጽፉ ጥቅሙ ብዙ ነዉ፡፡ ከሌላዉ በተጨማሪ እኛ በስልጣናቸዉ ስር ያለን በደንብ አድርገን እንድንረዳቸዉ በማድረግ እነሱን የሚጠቅም የመሆኑን ያክል በመካከላችን ያለዉን የገዥነትና ተገዥነት መራራ ግንኙነታችንን በማለዘብ እኛንንም ይጠቅመን ይሆናል፡፡ በመሆኑም በአቶ በረከት የተጀመረዉ በሌሎችም ይቀጥል፡፡

1. ስለአቶ በረከት ስምኦንና ስለመጻፋቸዉ

የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባል በነበርኩበት ጊዜ ስለአቶ በረከት ብቻ ሳይሆን አቶ በረከትንም ለማወቅ ተጨማሪ ዕድል ነበረኝ፡፡ አቶ በረከት በመጻፋቸዉ ከተረኳቸዉ አንዳንድ ድርጊቶች ጋር በነበረኝ ተዛምዶ ምክንያት በተደጋጋሚ ያገኛኋቸዉ ከመሆኔ በተጨማሪ በሌሎች ስራዎች ምክንያትም ለመወያት ዕድል ነበረኝ፡፡አቶ በረከት ስምኦን ለረጅም ዓመታት በድርጅት አመራርና የፖለቲካ መሪነት ካዳበሩት ልምድ በተጨማሪ ባልተቋረጠ የማንበብ ህይወት ወስጥ የኖሩ መሆናቸዉን ለማረጋገጥ ችያለዉ፡፡ ከአቶ በረከት ጋር በብዙ ጉዳዩች የሰፋ አስተሳሰብ ልዩነት ያለኝ ብሆንም ስለምቀናባቸዉ አንዳንድ ነገሮቻቸዉ ለጓደኞቼ አዉረቼ አዉቃለሁ፡፡ ሁል ጊዜ ይገርመኝ የነበረ አንድ ነገር አቶ በረከት የተወያየንባቸዉንና የተከራከርንንባቸዉን ጉዳዮችን የሚመለከቱበትንና የሚተነተኑበትን መንገድ በጥሞና ባስተዋልኩ ቁጥር በተመሳሳይ መንገድ ካወኳቸዉና ከተረዳኋቸዉ ከሌሎች ሰዎች እጅግ በበዛ መልኩ በወስጣቸዉ ኢህአዴግ ይታየኝ የነበረ መሆኑ ነዉ፡፡ አቶ በረከት ከኢህአዴግ አስተሳሰቦች በስተጀርባ ብቸኛ ሰዉ አለመሆናቸዉ ግልጽ ቢሆንም ከሁለት ከማይበልጡ ሰዎች አንዱ ስለመሆናቸዉ ብዙ ጊዜ የሰማሁትን አረጋግጭያለሁ፡፡ከዚህም በመነሳትአቶ በረከት መጽሀፍ ሊያሳትሙ መሆናቸዉ ዜና እንደተሰማ ስለኢህአዴግ ነባር አስተሳሰቦች መነሻና በተግባራዊ ሂደት እየተገለባበጡ እዚህ ስለደረሱበት ያለፉት ሃያ ዓመታት የሥልጣን ላይ ቆይታ ኢህአዴግ ስለወሰዳቸዉ አጨቃጫቂ ብቻ ሳይሆኑ አስጨናቂ ስለነበሩ ዉሳኔዎችና ወጤቶች እንዲሁም አቶ በረከት ከየት ተነስተዉ እንዴት የዚህ ሂደት አካል እንደሆኑና እዚህም ስላደረሳቸዉ እምነትና ተስፋ ሰፋ ያለ ትንትና ሚያስነበቡን ስለመሆናቸዉ ተስፋ አድርጌ ነበር፡፡ ነገር ግን በመጽሀፋቸዉ ያስነበቡን ነገር ከዚህ በጣም ያነሰ ነዉ፡፡ አቶ በረከት የጻፉት መጽሐፍ ስለሁለት ምርጫዎች ብቻ በመሆኑ ምክንያት፡፡

የአቶ በረከት ስምኦን ዓይነት ባለታሪክ የጻፈዉን መጽሐፍ የሚያነብ ሰዉ በመጽሀፉ ወስጥ የባለታሪኩን ማንነት የግል እምነቱንና ስሜቱን የባለታሪክነቱን ድርሻ አብዝቶ መፈለጉ የማይቀር ነዉ፡፡ አቶ በረከት የመጽሐፋቸዉን አተራረክ ያዋቀሩት እንዲህ ዓይነት ፈላጊ በቀላሉ እንዳያገኛቸዉ ቢያገኛቸዉም በደንብ እንዳያያቸዉ አድርገዉ ነዉ፡፡ በመጻፋቸዉ ሌሎች ሰዎችን ስለታዘቡበት የግላቸዉን ትዝብት ግምት ስሜት ድምዳሜ የሚያቀርቡ ቢሆኑም ይህኑን ሊያሳዩ የመረጡበት መንገድ ይህ አብዝቶ ከራሳቸዉ የግል አስተሳሰብና ድምዳሜ በላይ የኢህአዴግን ቡድናዊ አስተሳሰብን ወካይ እንዲሆን አድርገዉ ነዉ፡፡ ይህ ከሳቸዉ አንጻር ተመራጭ አቀራረብ መሆኑ ቢገባኝም መጽሐፉ አቶ በረከት ይህን ቡድናዊ አስተሳሰብ እንዲጋሩ ያስቻላቸዉን ሀሳብ እንዴት አንዳገኙና በወስጣቸዉ እንዴት አድርጎ በምን ምክንያት ወደዚህ እንዳደረሳቸዉ የሚነግሩን ነገር ቢኖር ጥሩ ነበር፡፡

በጎንደር ተወልደዉ በጉንደር አድገዉ ኢህአፓን ተቀላቅለዉ ከኢህአፓ ተገንጥለዉ ወደ ኢህዴን ምስረታ ባቡር እንደተሳፈሩና ከዚያም ከብአዴን መሪዎች አንዱ ወደመሆን እንደተሸጋገሩ እናዉቃለን፡፡ እሳቸዉም ይህን አረጋግጠዉልናል፡፡ ይሁን እንጂ አንድ ጎንደር የተወለደና ያደገ ሰዉ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋነኛዉ ችግር የዴሞክራሲ እጦት ሳይሆን የብሄር ጭቆና ነዉ ወደሚል ድምዳሜ የደረሰዉ ከራሱ የህይወት ልምድ ይሁን ወይስ ከሌሎች ትምህርት እንደሆነ ማወቅ ለምንሻ መጽሀፉ ምላሽ የለዉም፡፡ የአቶ በረከት አስተሳሰብ በምን ምክንያት ከኢህአፓ ህብረብሄራዊነት ወደ ብአዴን ዘዉግነት እየተንሸራተተ እንደደረሰ የእሳ
ዉን ትንተና በመጻፋቸዉ ወስጥ ብናገኘዉ ጥሩ ነበር፡፡ እርግጥ ነዉ ስለእነኝህና የመሳሰሉት ጉዳዮች አቶ በረከት ማንሳት ያልፈለጉት ገና መጻሀፋቸዉ ምን ዓይነት መሆን እንዳለበት ሲወስኑ ነዉ፡፡

 
2. ተደራሲዉ ማነዉ?

የአቶ በረከትን መጽሀፍ ካነበብኩ በኋላ አንድ ለራሴ ያነሳሁት ጥያቄ ለመሆኑ የዚህ መጽሀፍ ተደራሲ ማነዉ አንዲሆን ታሲቦ ነዉ የሚል ነዉ፡፡መጽሀፉ በታወቁና በተረጋገጡ የኢህአዴግ አቋሞች መነሻነት ከላይ ለገለጽኩት የኢህአዴግ ቡድናዊ አስተሳሰብና ስሜት በሚመች አቀራረብ(አልፎ አልፎ ሪፖርት በሚመሰል ሁኔታ) በሁቱ ምርጫዎች መካከል ኢህአዴግ የነበረበትን ሁኔታ ምን አስበዉ ምንስጠብቀዉ ምንስ እንዳገኙ ጭምር እጅግ ወገናዊ በሆነ መንገድ ይተርካል፡፡አቶበረከት ራሳቸዉ ያልካዷቸዉን የኢህአዴግ ወድቀቶቸንም ጭመር አንባቢ በከፍተኛ ረህራሄ ስሜት እንዲመለከት በሚጫን የአተራረክ ዉበት የምናዉቀዉን ኢህአዴ
ግን እያብረቀረቀ ሌሎችን ሁሉ ያጠቁራል፡፡ ይህ መጽሀፉ ቀድመዉንም በኢህአዴግ ክበብ ወስጥ በተለይም አስተያየታቸዉን ከሰጡ ሰዎች ፍላጎት አንጻር መሳጭ እንዲሆንና ከዚያ በተለየ መንገድ የሚያስብና የሚመለከት ሊኖር መቻሉን እንኳን ከግምት ወስጥ ያላስገባ አድርጎታል፡፡
የአቶ በረከት መጽሀፋ ከሥነጹሁፋዊ ዉበቱና ከአተራረክ ማራኪነቱ በቀር በመቅደማቸዉ ካነሱት የዘመናዊ ኢትዩጵያ ታሪክ በትክክል እንዲጻፍ ከማድረግ አስተዋጾዉ አንጻር ካየነዉ ፋይዳ ያለዉ መሆኑን ለመረዳት ተቸግሪያለሁ፡፡የኢትዩጵያ ታሪክን እጅግ አጨቃጫቂ ካደረጉት ምክንያቶች አንደኛዉ በየዘመኑ ስልጣን ላይ የነበሩ ሰዎች እዉነታዎች የእነሱን ዓላማን በሚያገለግልና ፍላጎታቸዉን በሚያረካ መልክ ብቻ እንዲጻፍ ማድረጋቸዉ ነዉ፡፡ በኢህአዴግ ዘመን (ከመንግስት ዝንባለ ሳይሆን የመጸፍ ነጸነት በመጀመሩ) መሻሻሎች ያሉ ቢሆኑም የአቶ በረከት መጽሀፍ ያንን ዝንባለ ተከትሎ የተጻፈ ነዉ፡፡ መጽሀፉ ግልጽ የሆኑ
የኢህአዴግ አስተሳሰቦችን መነሻ በመድረግ ድርግቶችን አስተሳሰቦችን ስለሰዎችም ለራሱ ለኢህአዴግ በኢህአዴግ ስሜትና ምኞት መንገድ እያጣፈጠ ያቀርባል፡፡ይህ ከዋነኛ ወረዎቹ በአንዱ ስም የቀረበ ቢሆንም ኢህአዴግን ?እንዲህ ድርስት መቼ ቸግሮት ያዉቃል?

ያም ሆነ ይህ ሀሳባቸዉን እንንገዛላቸዉ ለገበያ አቅርበዉልናልና ይህን በአግባቡ ማሳየት ተገቢ ነዉ፡፡ ይህ አጭር ጹሁፍ መጽሐፉ ዉስጥ የተነሱ ሀሳቦችን በቀጥታ በመጥቀስና ባነሷቸዉ ሀሳቦች መነሻነት አሰተያቶችን በማቅረብ ይህኑን ለማሳየት ይሞክራል፡፡

3.ከምክንያትና እዉነት ሳይሆን ከፍቅር የመነጨ

የአቶ በረከት መጽሀፍ ከምንም ነገር በላይ እሳቸዉ ለኢህአዴግ ያላቸዉን ጥልቅ ፍቅር ያሳያል፡፡ ፍቅርን ምንድነዉ ነዉ የሚሉት? እንዲህ ዓይነት ፍቅር ስሜታዊ እንጂ ምክንያታዊ ወገናዊ እንጂ ሚዛናዊ እንደማያደርግ አቶ በረከት በመጻፋቸዉ ያነሷቸዉን በርካታ ጉዳዮችን ሊያሳዩን የፈለጉበት መንገድ በቂ ማረጋገጫ ነዉ፡፡ የሌሎች ወገኖች ሀሳብ ሁሉ ከክፋት የመነጨ ህዝብንና አገርን ካለመዉደድ የመጣ የደካማነት ማረጋገጫ ኢህአደግ ያሰበዉ ሁሉ ለአገር ከማሰብና የኢትዮጵያን ገበሬ ከመዉደድ የመነጨ አድርገዉ አቅርበዋል፡፡ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ወዲህ በኢትዩጵያ ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ የተካሄዱ ምርጫዎች ሁሉ እንደ አቶ በረከት አገላለጽ “የኢትዩጵያ ህዝቦች በተግባራዊ ምርጫ ወሳኝ የስልጣን ምንጭና ባለቤቶች መሆናቸዉን….”(ገጽ51) ያረጋገጡ ናቸዉ፡፡ ሌላዉ ቀርቶ ኢህአዴግ የሽግግር ዘመኑን ማን ከሱ ጋር መጀመር እንዳለበት ራሱ ወስኖ እራሱ መርጦ አንዳንዶችን ጠርቶ ሌሎችን ከልክሎና አግልሎ ከሱ ጋር በሂደቱ ባቡር ከተሳፈሩት መካከልም እንደሱ ሀሳብና ፍላጎት አልሆን ያሉትን በተለያዩ መንገዶች እያዋከበ በሂደቱ እንዳይዘልቁ አድርጎ በመጨረሻም ብቻዉ መጨረሱን ያለፈና የተረሳ አድርገዉ እንደገና በአዲስ መልክ በማቅረብ በሁሉም ስምምነትና መግባባት የተጠናቀቀ መሆኑን ይነግሩናል፡፡ በሽግግሩ ዘመን የም/ቤቱ አባል የሆኑ ድርጅቶች ይመሩ የነበሩ ሰዎች ከአዲስ አበባ ወጥተዉ ወደተወለዱበት አካባቢ ሲደርሱ የአካባቢ የኢህአዴግ ካድሬዎች የተቀነባበረ ጥቃት እየፈጸሙ ከህዝብ ጋር እንዳይገናኙ ሰዉን እንዳያደራጁ አደርገዉ አዋክበዉና አሳደዉ ወደ አዲስ አበባ ይመልሱ እንደነበር በወቅቱ ተደጋግሞ የተዘገበ ነገር ነበር፡፡ አንዳንዶቹ በምሬት ለምክር ቤቱ ሲያስረዱ የተደረጉ ወይይቶችን አስከሁንም አሰታዉሳለሁ፡፡

ከ1997 ቱ ምርጫ ጋር በተያያዘ ኢህአዴግ ያደረጋቸዉን ግልጽና የታወቁ ህፀፆችን ሁሉ ከተገቢ ምክንያት የመነጩ አድርገዉ የሌሎች ፍላጎትና አቋም የመነጨዉ አመጽን ከመፈለግ ብቻ እንደሆነ አቅርበዋል፡፡እነኝህን በዝርዝር መሟገት ሌላ ትልቅ መጽሐፍ መጻፍን ይጠይቃል፡፡ ጥቂት ነጥቦችን ብቻ ላንሳ፡፡ የመጀመሪያዉ ገና ከ1997ቱ ምርጫ ጅምር ጀምሮ ተቃዋሚዎች የሰላማዊ ምርጫ ፍላጎት ሳይሆን የአመጽ ፍላጎትና ስትራተጂ አንደነበራቸዉ ለማሳየት የቅንጅት መሪዎች ከምርጫዉ በፊት ኢህአዴግ ያቀረበዉን የእንደራደር ጥያቄን ከመንግስት ጋር ካልሆነ ከኢህአዴግ ጋር አንደራደርም ብለዉ ያልተቀበሉ መሆናቸዉን ማስረጃ አደርገዉ ያቀረቡት ነዉ፡፡ (ገጽ 58) ከመንግስት ጋር ካልሆነ ከኢህአዴግ ጋር አንደራደርም ማለት ለመደራደር ፍቃደኛ ያለመሆን ማረጋገጫ ሆኖ መቅረብ ካለበት ለምንድነዉ እንደኢህአዴግ ካልሆነ እንደመንግስት አንደራደርም ማለት ለመደራደር ፍቃደኛ ያለመሆን ማረጋጫ ሆኖ የማይቀርበዉ? ኢህአዴግ እንደ ኢህአዴግ ሆኖ መደራደር ለእሱ በሚሰጠዉ ጥቅም ምክንያት እንደኢህአዴግ ካልሆነ አልደራደርም ብሎ ድርድር ያፈርስና ተቃዋሚዎችም ከራሳቸዉ ጥቅም አኳያ ከመንግስት ጋር ካልሆነ ከኢህአዴግ ጋር አንደራደርም ማለታቸዉን የጥፋት ማስረጃ ለማድረግ ይሞክራል፡፡ በመሰረቱ በምርጫዎች ሂደት ኢህአዴግ አንድ ተወዳዳሪ ሆኖ ሳለ መን
ግስታዊ ስልጣኑን በመጠቀም አንድ ጊዜ አንደመንግስት ሌላ ጊዜ እንደፓርቲ እየቀረበ ሲያደናገር ቆይቷል፡፡ እንደፓርቲ ካልሆነ እንደመንግስት አልደራደርም የሚለዉ የኢህአዴግ አቋም ከተቃዋሚዎች ጋር የሚደረግ ድርድርን ለማሳነስ የሚጠቀምበት ስልት ነዉ፡፡ በወቅቱ ቅንጅት ያልወደደዉ ይህንን እንደነበር አስታዉሳለሁ፡፡ ለነገሩ ኢህአዴግ እንደኢህአዴግም ሆነ እንደመንግስት ተደራድሮ ቢሆን ተደራዳሪዉ ያዉ ኢህአዴግ ከመሆን የተለየ እንደማይሆን ሁሉ የሚወክወለዉም ከአቶ በረከት ሌላ እንደማይሆን የታወቀ ነበር፡፡

በኢትዩጵያ ተቃዋሚዎች መካከል የትግሉን ስልት ብቻ ሳይሆን ግቡንም ጭምር በተመለከቱ ያሉ በርካታ ልዩነቶችን አቶ በረከት ያዉቃሉ፡፡ ይሁን እንጂ ለኢህአዴግ በሚመቸዉ መንገድ ተቃዋሚዎችን በመሉ በአንድ ላይ በመቋጠር ፖለቲካዊ ትግላቸዉና ፍላጎታቸዉ ምን ያህል አለአስፈላጊ እንደሆነ በማሳየት የኢትዩጵያ ፖለቲካ ክርከርን (National political discourse) ሳይሆን ኢህአዴግን ማሳየት ፈለጉ፡፡

አቶ በረከት “ኢዴፓ-መድህን ከምርጫ 97 በኋላ በፓርላም ግቢ ወስጥ የምርጫ ህጉን ለማሻሻል ከኢህአዴግ ጋር ሁለት ወራት የፈጀ ድርድር አካሂዷል፤ በዚህ ወቅት ከፓርቲዉ ጋር ሳይሆን ከመንግስት ነዉ መደራደር የምንፈልገዉ የሚል አንዲትም ቃል አልተነፈሰም፤ ከፓርቲዉ ጋር አለመደራደር የመርህ አቋም ቢሆን ኖሮ ከ97 ምርጫ በኋላ ለዛዉም በተመሳሳይ የምርጫ ህግ ላይ ለመደራደር ፍላጎት ባልኖራቸዉ ነበር፡፡” (ገጽ 59)ብለዉ ጽፈዋል፡፡ ከምርጫ 97 በኋላ ኢዴፓ በፓርላማ ወስጥ ያለ ኃይል ሆኗል፡፡ፓርላማዉ የመንግስት አካል አይደለም ካልተባለ በቀር ኢዴፓ ይህን ዓይነት ቅድመ ሁኔታ ቢያቀርብ ትክክል እንደማይሆን ይረዳል፡፡ ሁለተኛ ማነኛዉንም ዓይነት ህግን በፓርላማ አማካኝነት ለማሻሻል በፓርላማ ወስጥ ለሚገኝ ኃይል ተገቢ የሚሆነዉ በፓርላማዉ ማዕከልነት በፓርላማዉ ዉስጥ በሚገኙ ቡድኖች መካከል የሚደረግ ድርድር ነዉ፡፡ የፓርላማ አስፈላጊነትም ህግ ለማዉጣት ብቻ ሳይሆን የዚህ ዓይነት ድርድር ማዕከል ሆኖ የሚያገለግ መሆኑ ጭምር ነዉ፡፡ ለመሆኑ አቶ በረከት ይህን ተራ እዉነታ እንዲስቱ ያደረጋቸዉ ነገር ምንድነዉ?

ሁለተኛዉ ጉዳይ በ97ቱ ምርጫ ዕለት የልደቱን “ክፋትና ድፍረት” እና ኢንጅነር ኃይሉ ሻዉል የድምጽ የመስጠቱ ሂደት ገና ሳይጠናቀቅ ሰጡት ባሉት የፕሬስ መግለጫ ድርጅታቸዉ አዲስ አበባን ማሸነፉን ያም ሆኖ ምርጫዉ የተጭበረበረ እንደሆነ መግለጻቸዉ የተሳሳተ ስለመሆኑ ያቀረቡት ማብራሪያ ነዉ፡፡ (ገጽ 93-95) እዚህ ላይ ሁለት ነገሮችን አነሳለሁ፡፡ የመጀመሪያዉ በአዲስ አበባ ማሸነፋችንም ሆነ ምርጫዉ መጭበርበሩ የተረጋገጡ እዉነታዎች ናቸዉ፡፡ በመረጃ ደረጃ ኢንጅነር ኃይሉ አልተሳሳቱም፡፡ በአዲስ አበባና በሌሎች ቦታዎች ያሸነፍነዉ ምርጫዉ ስላልተጭበረበረ አይደለም፡፡ የድምጽ ቆጠራንና የዕለቱን ሥራ በተመለከተ ቅንጅት ባሸነፈባቸዉ ቦታዎች ሁሉ ቅንጅት ያሽነፈዉ በራሱ ድርጅታዊ ብርታትና ብቃት ሳይሆን የኢህአዴግን የተለመደ የምርጫ ማጭበርበር ማዕበልን ህዝቡ ስለተጋፈጠዉ ነዉ፡፡ ስለዚያ ምርጫ የተለየዉ ነገር ያን ሥነ ልቦና በህዝቡ ዉስጥ ለመፍጠር መቻላችን ነዉ፡፡ አቶ በረከት ኢህአዴግን ምን ያህል እንደሚያፍቅር ደግመዉ ደጋግመዉ ያንቆለጳጰሱት ገበሬ በወቅቱ እሳቸዉ ራሳቸዉ ባብራሩት ምክንያት ጭምር ኢህአድግን ያለመምረጥ ዉሳኔ በማድረጉ ኢህአዴግ ተበሳጭቶ ድምጹን ከመንጠቅ ባሻገር በጅምላ እንደተገረፈዉና እንደተቀጠቀጠዉ ምስራቅ ጎጃምን ምሳሌ አደርገን ማየት እንችላለን፡፡

ሶስተኛዉ ጉዳይ የኢንጂነር ሃይሉ መግለጫ ስህተት ቢሆን እንኳን ይህ ድፍረት እንደሆነ የምርጫ ህጉንና አሰራሩን መነሻ አደርገዉ ያብራሩት ገና ቆጠራዉ ሳያልቅ አሸናፊነቱን በይፋ ላወጀዉ ለኢህአዴግም የሚሠራ መሆን አለበት፡፤እኔ በተመረጥኩበት የድምጽ ቆጠራዉ የተጠናቀቀዉ ግንቦት ስምንት ከቀኑ ወደአምስት ሰዓት አካባቢ ነዉ፡፡ በብዙ የምርጫ ክልሎች ቆጠራዉ ከዚህ የበለጠ ጊዜ ወስዷል፡፡ ኢህአዴግ አሸናፊነቱን ያወጀዉ ግንቦት ሰባት ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ ነዉ፡፡ ይህ ቆጠራዉ ከመጠናቀቁ በፊት መሆኑን አቶ በረከት ራሳቸዉ ሲያረጋግጡ እንዲህ ይላሉ “አስቀድሞ በእጃችን የገባዉ የከተሞችና ለከተሞች ቀረብ ባሉ የገጠር ቀበሌዎች የተካሄደዉ የቆጠራ ዉጤት ነበር፡፡ ራቅ ያሉት ቀበሌዎች እንዲህ እንደዛሬዉ የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች ስላልነበሩ የቆጠራ ዉጤታቸዉ የሚደርስን ዘግይቶ ነበር፡፡ ከክልል ከተሞች ይገኝ የነበረዉ ዉጤት ከአዲስ አበባ የተሻለና ድልና ሽንፈት የሚፈራረቅበት ነበር፡፡”( ገጽ 97) ይህ በአቶ በረከት መጽሀፍ ወስጥ ካነበብኳቸዉ ጥቂት እወነተኛ ትረካዎች አንዱ ነዉ፡፡ በዕለቱ በዚህ መሀል ኢህአዴግ ምርጫዉን አሸንፊያለዉ ብሎ ለማወጅ በሚያስችል ሁኔታ ወስጥ አልነበረም፡፡ ይሁንና አደረገዉ፡፡ የድምጽ ቆጠራዉ ሳይጠናቀቅ አሸናፊነትን ማወጅ ለኢንጅነር ኃይሉ ሻዉል ሲሆን ሀጥያት ይሆንና ለኢህአዴግ ሲሆን ፅድቅ ይሆናል ማለት ነዉን?

ከምርጫ 97 ዝግጀትና አፈጻጸም ጋር በተያያዘ አቶ በረከት ሊያሳዩን የፈለጉትን ያህል ኢህአዴግ ሀቀኛና ቅን ቢሆን ኖሮ ታሪክ የተለየ ይሆን ነበር፡፡ በመሠረቱ ኢህአዴግ እንዲህ ዐይነት ሀቀኝነትንና ቅንነትን ካለተፈጥሮዉ ከየትም ሊያመጣዉ አይችልም፡፤ ይህን ማሳያ ሊሆኑ ከሚችሉ ብዙ መቶ ማሰረጃዎች መካከል ከምርጫ 97 ጋር በተያያዘ አንድ ነገር ብቻ ላንሳ፡፡ ምርጫ 97 ከተጠናቀቀ በኋላ የስራ ጊዜዉን ያጠናቀቀዉ ፓርላማ ከቀሩት ጥቂት የሰብሰባ ጊዜዎች በአንደኛዉ ስለመጪዉ ፓርላማ አሰራር ህግ አወጣ፡፡ ያ ፓርላማ ህግ የማዉጣት ስልጣን እንዳለዉ አያጠያይቅም፡፡ ጥያቄዉ ተቃዋሚዎች ባልተለመደ ሁኔታ የገቡበት አዲስ ፓርላማም ስለራሱ አሰራር ህግ የማዉጣት የሚችል መሆኑ እየታወቀ ኢህአዴግ ለምን ይህን ማድረግን መረጠ የሚለዉ ነዉ፡፡ ኢህአዴግ ይህን ያደረገዉና አንዳንድ በአዲስ አበባ አስተዳደር ሥር ያሉ መ/ቤቶችን ወደፌደራል የወሰደዉ በወቅቱ ሙሉ በሙሉ ኢህአዴግን ያልመረጠዉ የአዲስ አበባ ህዝብ እንዲበሳጭ በኢህአዴግ ላይ እንዲነሳሳ በዚህም ምክንያት ግጭጥ እንዲፈጠር አልነበረም?
ለምንድነዉ በብዙ ጭቅጭቅ አንዳንዶች በመቃወማቸዉ ምክንያት ዋጋ እንዲከፍሉ ተደርጎ ጭምር ወደ አዳማ እንዲሄድ የተደረገዉ የኦሮሚያ ም/ቤት ወደአዲስ አበባ እንዲመለስ የተደረገዉ? የከተማዋን አስተዳዳደርነት ይረከባል ተብሎ በሚጠበቀዉ ቅንጅትና በኦሮሞ ህዝብ መካከል የግጭት መሠረተ ለማበጀት አልነበረም?

4. አቶ በረከት ስለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ተቃዋሚዎችና ቀለም አብዮት—-ከትናንትናዉ ጥፋት የሚበልጥ የነገዉ ስጋት

አቶ በረከት በመጻፋቸዉ ስለቅድመ ምርጫ 97 በተረኩበት ክፍል የኢህአዴግ መንግስት በኢትዩጵያ “የብሄርና ዕኩልነትና ዴሞክራሲ ጥያቄዎችን በመመለስ የአርሶአደሩ ከእዝ ኢኮኖሚ ተላቆ የምርት ነጻ ተጠቃሚነት መብትን እንዲጎናጸፍ በማስቻሉ ከፍተኛ የአርሶ አደር ፍቅርና ድጋፍ ያተረፈ መንግስት…(ገጽ27) “ መሆኑን በከፍተኛ መተማመን ይገልጻሉ፡፡ የመጽሀፉ አብዛኛዎቹ ክፍሎች የዚህ ማብራሪያዎች ናቸዉ፡፡ አቶ በረከት እንደሚሉት ከሆነ በኢትዮጵያ የብሄር እኩልነትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ተመልሰዋል፡፡ የአርሶ አደሩም ጥቅሙ የተረጋገጠለት በመሆኑ ኢህአዴግን የሚቃወምበት ምክንያት የለዉም፡፡ በመጻፋቸዉ ከምርጫ 97 በፊት በነበረዉ ጊዜ ወስጥ በዝቅጠት ዝንባለ መስፋፋት ምክንያት በፖሊሲ አፈጻጸም ጉድለቶች የተነሳ የኢኮኖሚ እድገት መዋዠቅ የነበረ በከተሞች በአመራር ልምድ ማነስ የተነሳ የ”አርማጌዶን ምልክቶች” መታየት የጀመሩበት ወቅት ቢሆንም ምርጫዉ የደረሰዉ ኢህአዴግ እነኝህን ለማረም በሚጣደፊበት ዉጤቶችም መገኘት በጀመሩበት መሆኑን በተዋሱት የቻርለስ ዲከንስ አገላለጽ “…….ፍንትዉ ካለ ብርሃን ጎን ድቅድቅ ጨለማ…..”ይታይ የነበረበት ነበር፡፤ በምርጫ 97 ሂደት ኢህአዴግን የገጠመዉ ፈተና መሰረታዊ የሆነ የስርዓት ግንባታ ወድቀት ተግዳሮት ሳይሆን ከዚያ ያነሰ ችግር ነበር፡፡ በሁለት ምርጫዎች “ወግ” ትረካ ረጅም ጉዟቸዉ አቶ በረከት ሁሉንም ነገር ሊያሳዩን የሚሞክሩት ከላይ ከተጠቀሱ ሁለት ድምዳሜዎች መነሻነት ነዉ፡፡

ለእሳቸዉ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጥያቄ ምላሽ ያገኘ በመሆኑ ተቃዋሚዉን የሚያታግል ተገቢ ምክንያት የለዉም፡፡ በቅንጅት ስር ተሰልፈዉ የነበሩ ድርጅቶች አባላት ከቀድሞዎቹ የኢተዮጵያ ገዥዎች የሚመዘዙና አዲስ የስልጣን ተስፈኞች የብሄሮች ዕኩልነትን የማይቀበሉ ፌደራላዊ ስርዓት ከተመሰረተ በኋላ ይህንን እዉነታ መቀበል የተሳነቸዉ አሃዳዊ ሰርዓትን መመለስ የሚፈልጉ ወይም የድሮዋን ኢትዮጵያ ትሻለን ነበር በሚል ቅኝት (ገጽ59) ኢህአዴግን የሚቃዉሙ ወይም ከኢህአዴግ ጋር የሚታገሉ ናቸዉ፡፡ የህብረት መስራቾችም እንዲሁ የትላንቷ ኢትዮጵያ ለህዝቦች የተመቸች አይደለችም በሚል መነሻ አንድም አብሮ ለመኖር የሚቻልበት ዕድል የለም እያሉ መነጣጠልን የሚሰብኩ የብሄራቸዉ ገዥ መሆን የሚፈልጉ ወዘተ ናቸዉ፡፡ (ገጽ 60) በግሌ የኢትዩጵያ ተቃዋሚ ሃይሎች የወደፊቷ ኢትዩጵያ ተስፋና የዴሞክራሲያዊ ለዉጥ ኃይሎች ናቸዉ ወይ የሚለዉ ብዙ ጊዜ ያጠፋሁበት ጥያቄ ነዉ፡፡ ሆኖም በምርጫ 97 ኢህአዴግን ለተቃወመዉ ሃይል አቶ በረከት የሰጡት ሥዕል ማንም ቢሆን ይህን ስርዓት ለመቃወም የሚያስችለዉ ተቀባይነት ያለዉ(legitimate) ምክንያት የሌለዉ የሚመስል ድምዳሜን ለማስረገጥ የቀረበ በመሆኑ የእኔ አመለካከት ከዚህ መነሻ ፈጽሞ የተለየ ነዉ፡፡

ባለፋት የኢህአዴግ የስልጣን ዓመታት የብሄር መብት ተረጋግጧል ቢባልም የብሄር መብትም ሆነ የዜጎች መብቶች በአግባቡ ሊከበሩ አልቻሉም፡፡ ለብሄረሰቦች ራሳቸዉን በራሳቸዉ የማስተዳደር መብት አልተሰጠም፡፡ የመደራጀት መብት ህጋዊ ሆኖ የተደነገገ ቢሆንም ካለመደነገግ ጋር ያለዉ ልዩነት ትንሽ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ሀሳብን በነጻ መግለጽ ነጻነት ህገ መንግስታዊ ቢሆንም ዋጋ ማስከፈሉን እንደቀጠለ ነዉ፡፡ በአገሪቱ የዴሞክራሲን ተግባራዊነት የሚያረጋግጡ ነጻ ተቋሞችን ለመፍጠር ኢህአዴግ እምቢተኛ ሆኖ ይገኛል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የተጀመረ ቢሆንም የህዝብን የስልጣን ምንጭነትን በእዉነተኛነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ነጻና ሚዛናዊ ምርጫ ገና አልተጀረም፡፡ የመልካም አስተዳደር አለመኖር በአገሪቱ የመንግስት አስተዳደር ዋነኛ ችግር ነዉ፡፡ ኢህአዴግ ስለስርዓቱ ዴሞክራሲያዊነት በየቀኑ ሊያስረዳን ቢሞክርም ስርዓቱ የህዝብ ተቋማዊ ተሳትፎ ያልተረጋገጠበትና በህግ በላይነት ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ ዜጎችን በጥቅም ከፋፍሎ ማቧደንና አግላይነትን ማስፈን እንደ አገዛዝ ስልት ሆኖ ስራ ላይ ዉሎ ይገኛል፡፤ ጊዜ ያለፈበትን የአንድ ፓርቲ አገዛዝ ለማጠናከር ሲባል የዘመናዊ ዴሞክራሲ ዋነኛ መገለጫ የሆነዉ የመድብለ ፓርቲ እድገት ሆን ተብሎ እንዲገታ እየተደረገ ነዉ፡፡ ይህ እንደኔ ዓይነት ሰዎች ኢህአዴግን ከስልጣ ተስፈኝነት በዘለለ ምክንያት እንድንቃወመዉ ያስገድድናል፡፡

አቶ በረከት ስለኢትዮጵያ ገበሬ መሻሻል ያላቸዉን ምኞትና ከኢህአዴግ ጋር ያለዉን ቁርኝት ከተቃዋሚዉ ወገን ጋር ያለዉን ርቀት ደጋግመዉ የገለጹበት አኳኋን እኝህ ጎበዝ ሰዉ የአህአዴግን የስርዓት ግንባታ ስኬትን ከጥቂት ሚሊዩኖች ኩንታል የምርት ዕድገት ባሻገር ማየት ተስኗቸዋል ማለት ነዉ ወይ በዬ አስባለሁ፡፡ በደርግ ጊዜ የኢትዮጵያ ገበሬ በጭቆና ወሰጥ የነበረ መሆኑ አይከራክርም፡፡ ይህም ሆኖ ደርግ በገበሬዉ ላይ ኮታ ጥሎ ምርቱን ለመንግስት እንዲሽጥ ያስገድድ ነበር አንጂ ዝምብሎ ሲነጥቅ አልነበረም፡፡ ኢህአደግ ገበሬዉን ደርግ ሲያደርግ እንደነበረዉ ምርቱን በግዳጅ እንዲሸጥ ባያስገድድም ለገበሬዉ ከደር
ግ የተሻለ ፖለቲካዊ ነጻነትን አላጎናጸፈም፡፡ ኢህአዴግ ምርት እንዲያድግ የገበሬዉ ኑሮ እንዲሻሻል የሚፈልግና የሚሠራ መሆኑ ባያጠራጥርም ከዚህ በላይ ግን ገበሬዉን የአገዛዝ መሣሪያ አድርጎ ለመጠቀም ገና ከጧቱ አልሞ ተነስቷል፡፡ ገበሬዉ ለኢህአዴግ በተለመደዉ የዘመናዊ ፖለቲካ በህብረተሰብ ወስጥ የተለያዩ ፍላጎቶችን ወካይ ከሆኑ ልህቃን ጋር የሚደረግ ድርድርንና ከዚህም የሚመነጨዉ ፖለቲካዊ መመቻቸት የሚፈጥረዉን የስልጣን ጨዋታ ተጋሪነትን ሸሽቶ የሚደበቅበት ጫካ ነዉ፡፡ አቶ በረከት የማስታወቂያ ሚኒስትር በነበሩ ጊዜ መ/ቤቱ በ1995 ዓ.ም ያሳተመዉ አንድ የፖሊሲ ሰነድ እንዲህ ይላል፡፡ “አንድ ድርጅት
አርሶ አደሩን መብትና ጥቅም ማስጠበቅን በዋነኛ ዓላማነት ይዞ ከተነሳና በአርሶ አደሩም ተቀባይነት ካገኘ በፖሊቲካ ሂደቱ ላይ ወሳኝ ተፅዕኖ ማሳረፍ የሚችል ይሆናል፡፡ ከዚህ ወጭ ያለዉ ፓርቲዎች ቦታ እጅግ ጠባባና የፖሊቲካ ሥልጣን ለመያዝ በቂ እድል የማይከፍት ይሆናል፡፡” ኢህአደግ በኢትዮጵያ ገበሬ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት የሚፈልገዉ ሌሎች ፓርቲዎች ወደስልጠና መምጫ መንገድ ከማጥበብ ለላቀ ዓላማ ቢሆን ኖሮ ለኢትዩጵያ ገበሬ ከቻይና ገበሬ የተሻለ ዕድል የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሥርዓት ከቻይና ፖለቲካ ስርዓት የተሻለ ይሆን ዘንድ ይመኝ ነበር፡፡

አቶ በረከት በመጽሀፋቸዉ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዘንድ የታየዉን መነቃቃት በተሀድሶ ምክንያት የተገኘ የኢህአዴግ ነባር የፖሊሲ አፈጻጸም ዉጤት አድርገዉ አቅርበዋል፡፡ ኢህአዴግ በተደጋጋሚ ተሀድሶ የሚለዉ ነገር በድርጅቱ ወስጥ ሲደረግ ለነበረዉ የበላይነት ሽኩቻ መቋጫ የፈጠረ ካልሆነ በቀር በፖሊሲና አፈጻጸም አኳያ ከተለመደዉ የተለየ ለዉጥ ያመጣ መሆኑ ግልጽ አይደለም፡፡ የአፈጻጸም ደካማነት የአገሪቱ ዋነኛ ችግር መሆኑን ኢህአዴግ ራሱ በየቀኑ ሲነግረን የቆየዉ ጉዳይ ነዉ፡፡

ለኢትዩጵያ ገበሬ ከፍተኛ የምርት ዕድገትን ያስገኘዉና ወደዘመናዊ ግብይት ያስገባዉ የኢህአዴግ የእርሻ መር ኢኮኖሚ ፖሊሲ ለአስራ አራት ዓመታት ተሞክሮ ወጤት አልባነቱ ከተረጋገጠ በኋላ ኢህአዴግ ከዚህ ፖሊሲ በማፈግፈግ በከተሞች አካባቢ የመሰረተ ልማት ግንባታንና የገንዘብ አቅርቦትን በማሻሻል ከተማ ተኮር ኢንቨስትመንት በብዙ እጥፍ እንዲጨመር በማድረግ የተከተለዉ አዲስ አቅጣጫ ነዉ፡፡ ይህ በከተማ የአግልግሎት ዘርፉንና ኢንዱስትሪን በከፍተኛ ፍጥነት በማሳደግ የከተማ ነዋሪዉን የፍጆታ ችሎታን በማሳደጉ ለገበሬዉ ምርት ከፍተኛ የገበያ እድል ተፈጠረ፡፡ ኢህአዴግ ፈጣን ልማት አስመዘገብኩ የሚልባቸዉ የባለፉት ዓመታት አድገት ምንጩ እድገትን ሊያመጣ ካልስቻለዉ የራሱ ፖሊሲ እየሸሸ ቀስበቀስ በተቃዋሚዉ አካባቢ ይባል የነበረዉንና በተለይም በምርጫ 97 በቅንጅት በኩል ወደቀረበዉ አማራጭ እየተጠጋ መምጣቱ ነዉ:: ይህ የኢህአዴግ ከራሱ ነባር የፖሊሲ አስተሳሰብ የመንሽራተት ሂደት ላለፉት የፈጣን ዕድገት ክንዋኔዎች መሰረት ጥሏል፡፡ ለገበሬዉ ምርት ከተማዉ ጣፋጭ ገበያ እንዲሆንም አድርጎታል፡፡

ኢህአዴግ በገበሬዉ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘትን አልሞ መነሳቱ በራሱ ስሕተት አይሆንም፡፡ ጥያቄዉ ይህን አቶ በረከት በሚሉት መንገድ በፍታሃዊ መንገድ ለማግኘትና እዉነተኛ ፍቅርን ማትረፍ ችሏል ወይ የሚለዉ ነዉ፡፡ ባለፉት ዓመታት ለኢህአደግ በገበሬዉ ዘንድ በፍትሀዊ መንገድ ተቀባይነት ማግኘት ቀላል ሆኖ ባለመገኘቱ ገበሬዉን በተለያዩ ስልቶች በመጠቀም ጠፍሮ የመያዝ ስልት ሲከተል ቆይቷል፡፡ ወደ ገጠሩ ሌሎች ፓርቲዎች እንዳይደርሱበት ለማድረግ ብዙ ስራዎችንም ሲሰራ ቆይቷል፡፤ በኢህአዴግ አባልነታቸዉ ገበሬዉን እንዲመሩ የሚደረጉ የገበሬ አደረጃጀት አመራሮች በደርግ ጊዜ እንደነበሩት የኢሠፓ ካድሬዎች መንግስታዊ ሥልጣንን ተገን በማድረግ የህገ በላይነትና ተጠያቂነት በለሌበት መንገድ ገበሬዉን የሚያዋክቡ ናቸዉ፡፡ በሁሉም ክልሎች የገበሬ አካባቢ ሸንጎ በመቶች የሚቆጠሩ አባላት ያሉት ሲሆን በአካባቢ ምርጫ እያንዳንዱ ፓርቲ በዚያ ልክ ዕጩ ማቅረብ አለበት፡፡ ሁለትና ሶስት ፓርቲዎች በሸንጎ መጠን ዕጩ ለማቅረብ ቢሞክሩ የአጠቃላይ የዕጩዎች ቁጥር ከመራጮች ወይም የአካባቢዉ ነዋሪዎች በቁጥር የበለጠ ይሆናል፡፡ ኢህአዴግ የመንግስት ስልጣኑን በመጠቀም በአካባቢዉ ዕጩ ሊሆኑ የሚችሉትን ሁሉ ቢያቀርብ ሌላዉ ፓርቲ ዕጩ አጥቶ በምርጫዉ ሳይሳተፍ ይተዋል፡፡ በዚህ መልክ የአካባቢ ምርጫ ኢህአዴግ ብቻ የሚመረጥበት እንዲሆን ተዘይዷል፡፡ የኢህአዴግ አባላት ብቻ የሆኑ የገበሬ ሸንጎ አባላትና ከመካከላቸዉ የተመረጡ አመራሮች ወደየአካባቢያቸዉ ኢህአዴግን የሚቃወም ጸጉረ ልዉጥ ድርሽ እንዳይል ማድረግ ዋነኛ ሥራቸዉ ነዉ፡፡ በአካባቢ የሚገኝ አንድ ገበሬ ልጅ የሆነ ወጣት ወይም ወጣቶች የሆነ ተቃዋሚ ድርጅቶች ደጋፊዎች ናቸዉ ከተባለ የቀበሌ አመራር የሆነ ነገር ፍጥሮ ይወነጅላቸዋል፡፡ የቀበሌ ታጣቂና የወረዳ ፖሊስ ሥራዉ እነሱን ማሳደድ ይሆናል፡፡በተፈበረከዉ ወንጀል ፍ/ቤት በትዕዛዝ እንዲፈርድባቸዉ ይደረጋል፡፡ ከዚያ በዚህ ምክንያት የተበሣጨ ፍትህ እንደሌለ የተናገረ ለአቤቱታ የተመላለሰ ሁሉ ተቃዋሚ ነዉ፡፡ ተቃዋሚ በሚል ፍረጃ መዓት አንዲመጣበት ይደረጋል፡፡ የመስኖ ዉሃ ይከለከላል፡፡ የማዳበሪያ ዕዳም ካለበትም የማጨናነቂያ መንገድ ይሆናል፡፡ ከ97ቱ ምርጫ በኋላ ይህ ስልት ከማስፈራራትና ማዋከብ በተጨማሪ ኢህአዴግን ጠንክረዉ የሚቃወሙትንና በግልጽ ወደመጋፈጥ የተሸጋገሩትን በመለመንና በማስለመን ማለስለስ ተጨምሮበታል፡፡ በገጠር የኢህአዴግ ተልዕኮ ፈጻሚ ተንቀሳቃሾች ለድርጅቱ ባላቸዉ ታማኝነትና በተሰጣቸዉ ገደብ የለሽ ስልጣን በመጠቀም የሚያሳዩት አምባገነንትና ይህም የህዝብን ሀብትና ንብረት እንደፈለጉ እንዲመዘብሩ የተከፈተላቸዉ መንገድ ገበሬዉን ጠፍረዉ እንዲይዙ ብቻ ሳይሆን የገጠሪቱን ኢትዩጵያ
ፖለቲካዊ ህይወት እጅግ ጨፍጋጋ እንዲሆን አደርጎት ይገኛል፡፡

አቶ በረከት በመጻፋቸዉ እላይ ከገለጽኩት የትግል ምክንያት በተጨማሪ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተዉ የብዙ ሰዎችን ስም እየጠቃቀሱ ካቀረቡት የተቃዋሚ መሪዎች የባህርይ መገለጫዎች ጋር ብዙ ጥል የለኝም፡፡ ከእሳቸዉ በላይ ለማወቅ እኔም በቂ እድል ነበረኝ፡፡ ነገር ግን እየተማርንና እየለመድን እናድጋለን ለምንል ሰዎች ፖለቲካ ቢስማርክ እንዳለዉ ሁልጊዜም ቢሆን ትክክለኛ ሳይንስ አይደለም፡፡ከዚያ በላይ መታሰብ በሚገባቸዉ ነጥቦች ዙሪያ ሁለት ማሳሰቢያዎችን ማቅረብ ግድ ይለኛል፤፤የመጀመሪያዉ አቶ በረከት በከፍተኛ የንቀትና ጥላቻ ስሜት ለማንኳሰስ የአማርኛ ቋንቋ ትንሽ እስከሚሆንባቸዉ ድረስ የተቸገሩት የተቃ
ዋሚ ፓርቲዎች ድክመት የተቃዋሚዎች ድክመት ብቻ ከመሆን በላቀ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ችግር መሆኑን ልብ ማለት የሚያስፈልግ መሆኑ ነዉ፡፡ የታንዛኒያዉ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ቤንጃመን ሙካፓ ከሞላጎደል በኛ አገር በ1997 ከተካሄደዉ ምርጫ ትንሽ ቀደም ብሎ(2004) በተካሄደዉ የአገሪቱ ሁለተኛ መድብለ ፓርቲ ምርጫ ተቃዋሚዎች አንስተኛ ዉጤት በማምጣታቸው ይህ በአገሪቱ ዴሞክራሲ ላይ ሊያስከትል የሚችለዉን አደጋ በማሳሰብ በፓርላማዉ ፊት የተናገሩትን የኢህአዴግ መሪዎች እጅግ ሊያጠኑት የሚገባ በመሆኑ ሳልተረጉመዉ ላቅርበዉ
Mr. Speaker, there are two issues that cause me some measure of distress. The first relates to the weakness of the opposition political parties. If we do not have serious political competition between comparable teams, we will degenerate into political frivolity. As president of the country, I realize that a strong opposition is……….good for our people and our country.
ባለፉት ዓመታት የተቃዋሚዎችን ድክመት ኢህአዴግ እንደፈተና ሳይሆን እንደእድል ለመጠቀም ሲመክር ቆይቷል፡፡ ምክንያቱም የአህአዴግ ዓላማ በምኞት ደረጃ ተቃዋሚዎች ወስጥ አንዳንዶቻችን ካለን ምኞት እጅግ ባነሰ ሰርዓት ከመገንባት ይልቅ ስልጣን መገንባት ነዉና፡፡

ሁለተኛዉ ይህ ድክመት የተቃዋሚዉ ጎራ የሚታገልለትን ዓላማ የሚያሳንሰዉ መሆኑ ነዉ፡፡ ኢህአዴግ በኢትዩጵያ የዴሞክራሲ ጥያቄን ለመመለስ ያልቻለ መሆኑ ግልጽ ነዉ፡፡ በኢትዩጵያ ተጀመረ የተባለዉ የዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ከህዝብ መብትና ነጻነት በላይ ሌላ የጭቆና አገዛዝን በማጠናከር ሂደት ላይ እየተጓዘ ይገኛል፡፡ ተቃዋሚዎች በኢትዩጵያ የለዉጥን ተስፋንና የዴሞክራሲ ጥያቄን ለመወከል ያላቸዉ ችሎታና ብቃት ከፍ ያለም ሆነ ዝቅ ያለ በኢትዮጵያ የሀቀኛ ለውጥና የዴሞከራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጥያቄ ከኢህአዴግም ሆነ ከተቃዋሚዎች የላቀ የአገር ህልዉና ጥያቄ ነዉ፡፡ ተቃዋሚዎች ደካማ ስለሆኑ አንሶ የሚታይ አይሆንም፡፡ ኢህአዴግም ብዙ ድክመቶች ያሉበት ድርጅት መሆኑ የታወቀ ነዉ፡፡ ያም ሆነ ይህ አቶ በረከት ኢህአዴግ እየገነባ የሚገኘዉ ስርዓት የአገሪቱን ዴሞክራሲ ጥያቄን ያልመለሰ ይልቁንስ አዳዲስ ቅራኔዎች በፍጥነት አየመነጩበት የሚገኝና የተቃዋሚዉ ጎራ ትግልና ፍላጎትም ተቀባይነት ካለዉ ዓላማ የማይነጭ መሆኑን ያብራሩበት ሁኔታ ኢህአዴግና መሪዎቹ አሁንም የሰርዓቱን ጉድለቶችን በአግባቡ እየተረዱ ካለመሆናቸዉ በላይ ለአገራችን ከምንመኘዉ የለዉጥና የሰርአት ግንባታ ሂደት መድረሻ እጅግ ርቁዉ ከወደኋላ የቆሙ መሆናቸዉን ያሳያል፡፡

ሌሎችንም ተጨማሪ ጥያቄዎቸን እናንሳ፡፡ ለምንድነዉ ተቃዋሚዎች ኢህአዴግ በሚፈልገዉ መጠን ህገ መንግስቱን የማይቀበሉት? ለምንድነዉ ሁልጊዜ በተቃዋሚዎች አካባቢ የሚታዩ የአመፅና የግጭት ዝንባሌዎች ለአህአዴግ አሳሳቢ እየሆኑ የሚመጡት? ለምንድነዉ የቀለም አብዩት ጉዳይ በኢትዮጵያ ወስጥ ኢህአዴግ በሚያቀርበዉ ክስ መጠን የሚቀርበዉ? በእዉነት አንዳንድ የተቃዋሚ መሪዎች ነዉጥ የሚፈልጉ የአገር ሰላምና መረጋጋት የማይሹ በመሆናቸዉ ነዉ? የውጭ መንግስታት ኢትዮጵያን በቅኝ አገዛዝ ለመያዝ ስለሚፈልጉና ይህ ለተቃዋሚዎች የማይሰማቸዉ ስለሆነ ወይንም አገሪቱን ለውጭ ሃይሎች አሳልፎ የመስጠት ፍላ
ት ስለተጠናወታቸዉ ነዉን? የአቶ በረከት መጽሀፍ ሊያስረዳን የሚሞክረዉ በዚህ መንገድ ነዉ:: ኢህአዴግም የሚያስበዉ በዚህ መንገድ ነዉ:: ይህ ግን ከባድ ስህተት ነዉ፡፡ ምክንያቱም ለእነዚህ ውጤቶች መነሻዉ በኢህአዴግ ዘንድ ጭምር መሆናቸዉን ለመረዳት የግድ በዲፕሎምና ድግሪ መመረቅ አያስፈልግም፡፡

ተደጋግሞ እንደሚባለዉ ፖለቲካ በህብረተሰብ ወስጥ የቡድን ፍላጎት መገለጫ ነዉ፡፡ በአምባገነን ስርዓት መንግስት ከብዙ ፍላጎቶችና አነሱንም ከሚወክሉ ሃይሎች የአንደኛዉ ብቻ መሳሪያ መሆኑ ተፈጥሮአዊ ነዉ፡፡ በአምባገነን ስርአት ስልጣንን የሚይዘዉ ሃይል እሱ የህብረተሰብ ፍላጎት ብቸኛ ወካይ አንደሆነ የአገር ጥቅምና ፍላጎት በሱ ብርታትና ጉብዝና ብቻ እንደሚቆም ለማሳየት ከመሞከር አልፎ ሌሎች ፍላጎቶችን የሚወክሉትን በአገር ጥቅምና ፍላጎት ከሱ አተረጓገም የሚለዩትን ሁሉ ለማጥፋት ይሞክራል፡፡ ይህም በመሆኑ ምክንያት ሀሳብን በነጻ ከመግለጽና የመደራጀት ነጻነቶች ጋር የእጅግ የተጣላ ይሆናል፡፡ ዴሞክ
ራሲያዊ ሰርአትን ተመራጭ ከሚያደርጉ ነገሮች አንደኛዉ ለተለያዩ ፍላጎቶችና እነሱንም ለሚወክሉ ኃይሎች እዉቅና የሚሰጥና የፖለቲካ ብዙሃንነትን (political pluralism) ተቋማዊ የሚያደርግ መሆኑና በብዙ ሓይሎች መካከል ሰላማዊ ዉድድርን ወደ ስልጣን መምጫ መንገድ የሚያደርግ መሆኑ ነዉ፡፡

የ1990ዎቹን የዓለም አቀፍ የዴሞክራሲ ማዕበልን ተከትሎ የዴሞክራሲያዊነትን ጭምብል አጥልቀዉ ወደስልጣን ከመጡ ሃይሎች አንደንዶቹ ምንም እንኳን አምባገነን መሪዎችን ታግለዉና አሸንፈዉ ስለሚመሰርቱት ስርዓት ዴሞክራሲያዊነትና ህዝብን ስለሚያጎናጽፏቸ መብቶች ይህ ቀረሽ በማይባል ደረጃ ብዙ ቃል የገቡ ቢሆኑም ውለን አድረን ያየነዉ ስልጣን እየጣማቸዉ ሲመጣ ተመልስዉ አምባገነንት ባህርይን እተላበሱ መምጣታቸዉን ነዉ፡፡ በእነኝህ ሃይሎች የተመሰረተዉ ስርዓት በቅርጽ ቀደም ሲል ከነበሩት አምባገነን አገዛዞች የተለየ ቢሆንም በይዘት አምባገነንነትን የሚወከል ነዉ፡፡ በእነኝህ አገዛዞች ስር ሁሉም መብቶች ህጋ
ዊ ሆነዋል፡፡ ግን በአፈጻጸም ዉጤታቸዉ ህጋዊ ካለመሆን ጋር እኩል ነዉ፡፡ ገዥ የሆኑ ፓርቲዎች የመንግስትን ስልጣን በመጠቀም ከመንግስት ቁጥጥር ዉጪ ያለዉን የህብረተሰብ ማቀፍ ሁሉ ጨምድደዉ በመያዝ ራሳቸዉን የበላይ በማድረግ ብቻ ሳያበቁ ሌሎችን ቦታ በማሳጣት ብቸኛ ገዥዎች ሆነዉ የመዝለቅ ስልትን ይከተላሉ፡፡ የዴሞክራሲን ተግባራዊነት ማረጋገጫ የሆኑ ተቋማትን አይገነቡም ወይም ቢገነቡም በራሳቸዉ ፍላጎት መጠን በማንሻፈፍ እነሱን ብቻ እንዲያገለግሉ ያደርጋሉ፡፡ በዴሞክራሲ አግባብ መንግስትና ፓርቲ መካከል ሊኖር የሚገባዉ ልዩነትም ሆነ የስልጣን ከፍፍል ስለማይኖር ከእነኝህ ገዥ ፓርቲዎች ጋር በም
ጫ የሚደረግ ዉድድር ከራሱ ከመንግስት ጋር የሚደረግ ይሆናል፡፡ እነሱ በመንግስት ጉልበትና አቅም ሲሰሩ ሌሎች እንደድርጅት ለመንቀሳቀስም አቅም ስለሚያንሳቸዉ እንደግለሰብ የሚወዳደሩ እየሆኑ ምርጫዉ ሁልጊዜ እነሱ ብቻ የሚያሸንፉበት ይሆናል፡፡ በአንዳንድ አገሮች በዚህ ዓይነት ሂደት ዴሞክራሲ ተራ የውሸት ጨዋታ ሆኖ መቅረት ብቻ ሳይሆን እንደእሬት የሚመር ውጤት እያስከተለ በማስቸገሩ እነኝህን በተጭበረበረ ምርጫ ራሳቸዉን አሸናፊ እያደረጉ በማሳወጅ ለዓመታት የሚዘልቁትን ከስልጣን የሚያወርድ ህዝባዊ ንቅናቄ መፍጠር የግድ ሆኗል፡፡ የቀለም አብዮት የዚህ ንቅናቄ ስያሜ ነዉ፡፡ በተለያዩ አገሮች የተደረጉ የቀለም አብዮት ንቅናቄዎች ከአምባገነን አገዛዞች ጋር የተደረጉ ትግሎች በመሆናቸዉ ሰፊ ዓለም አቀፍ ድጋፍ አግኝተዋል፡፡ ሁልጊዜም ራሳቸዉን የሰዉ ልጆች የነጻነት እሴቶችና የዴሞክራሲ አሸናፊነት ጠበቃ የሚያደርጉ የምዕራብ መንግስታትና የዴሞከ
ሲ ተሟጋች የሆኑ ብዙ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች የቀለም አብዩትን እንደፍታሀዊ የህዝብ ነጻነት ትግል በመቁጠር ይደግፋሉ:: ያበረታታሉም፡፡ በእነኝህ አገሮች ያሉ ተቃሚዎችም ለዴሞክራሲ በሚያደርጉት ትግል የእነኝህ ወገኖችን ድጋፍ ለማግኘት ይሞክራሉ፡፡ በአንጻሩ የቀለም አብዩት የሚያነጣጥርባቸው መንግስታት የቀለም አብዮትን ያወግዛሉ፡፡ ተቃዋሚዎች ከምዕራብ መንግስታት ጋር የሚያደርጉትንም በከፍተኛ ስጋት በማየት በውጭ ሓይሎች ላይ መተማመና አገርንም አሳልፎ እንደመስጠት እየቆጠሩ ይኮንናሉ፡፡ ይህን የሚያደርጉት እነሱም ከተቃዋሚዎች የበለጠ ለአገር አሳቢና ተቆርቋሪ ሆነዉ ሳይሆን የስልጣን ፍቅር ስ
ለሚያስጨንቃቸዉ ነዉ፡፡

የተለያዩ የፖለቲካ ተመራማሪዎች ኢህአዴግ ደርግን አሸንፎ ስልጣን ከያዘ በኋላ በኢትዮጵያ የመተሰረተዉ አገዛዝ በቅርጹ ዴሞክራሲያዊ ሆኖ በይዘቱ ዴሞክራሲያዊ አለመሆኑን ጽፈዋል፡፡ ይህን በቀለም አብዩት የሚያምኑና ስለቀለም አብዮት የሚሰብኩም ሆነ በቀለም አብዮት የማያምኑ እንደኛ ዓይነት ተቃዋሚዋች የሚሉት ነዉ፡፡ ከጅምሩ ጀምሮ ኢህአዴግ ተቃዋሚዎችን ገንቢ አጀንዳ የሌላቸዉ አድርጎ በመመልከት ሥርአቱ በእነሱ ስምምነትና ትብብር ጭምር የቆመ አንዲሆን ለማድረግ በሐቀኝነት አልሰራም፡፡ አገሪቱን በራሱ ሀሳብ መንገድ አንደገና ለመቅርጽ ባደረበት ፍላጎት የተነሳ የራሱን ብቸኛ ወሳኝነት ለማረጋገጥ በመፈለ
ግ በኢትዩጵያ የመድብ ፓርቲ እንዲያድግ አልፈለገም፡፡ ነጻና ገለልተኛ የሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲያድጉም አልፈለገም፡፡ እካሁንም የተካሄዱ ምርጫዎች ምንም እንኳን የዴሞራሲያዊነት ባሕርይ ያላቸዉ ቢሆኑም ነጻና ሚዛናዊ ባለመሆናቸው የህዝብ ስልጣን ባለቤትነትን ያረጋገጡ አይደሉም፡፡

ይህ እዉነታ በኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሃይሎችና በገዥዉ ኢህአዴግ መካከል ያለዉ ግኑኝነት ከውድድር ይልቅ የትግል ባህርይ እንዲኖር አድርጎት ቆይቷል፡፡ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ይህ ሁኔታ ቀስ በቀስ እየተለወጠ ኢህአዴግ ወደ መደበኛ የዴሞክራሲ ተግባራዊነት አቅጣጫ እንዲመጣ መጣር ሲገባቸዉ በተራ ምክንያት ከድርድር ማፈግፈጋቸዉና ከተሳትፎ መሸሻቸዉ አግባብ ስለአለመሆኑ ባለኝ እምነት አንዳንድ የአቶ በረከት ትችቶችን እጋራለሁ፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ የግንኙነት ሂደት የተቃዋሚዎች ባህርይ ግጭትን ከመፈለግ ሳይሆን ከስርዓቱ ባህርይ ይመነጭ የነበረ መሆኑ ግልጽ ነዉ፡፡ ኢህአደግም ግጭትን እንደስልት ለመጠቀም በመፈለግ ተንኳሽነትን ሲያሳይ እንደነበር ግልጽ ነዉ፡፡ ይህ ሁሉ የማያከራክር ሆኖ ሳለ አቶ በረከት ተቃዋሚዎችን የአመጽ ፈላጊዎች ብቻ ኢህአዴግ ግጭት እንዳይፈጠር የሰላም ዘንባባን አንጥፎ ይማፀን የነበረ አድርገዉ አቅርበዋል፡፡ ይህ ኢህአዴግና መሪዎቹ አሁንም የትናንትና ችግሮች መንስኤዎችን ነገ ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር ለማረም በሚያስችል አቅጣጫ እየተመለከቱ እንዳልሆነ ያሳያል፡፡
ይህ ትልቅ የስጋት ምንጭ ነዉ፡፡ ካለፈዉ ከትናንትናዉ ሣይሆን ከመጪዉ ዕድላችን በስተጀርባ ያለስጋት! ኢህአዴግ በኢትዩጵያ የተጀመረዉ የደሞክራሲያዊ ሰርዓት ግንባታ እየዳበረ እንዲሄድ እስካለደረገ ድረስ የዴሞክራሲ ተቋማት ነጻና ገለልተኛ ሆነዉ እንዲያድጉ እስካላደረገ ድረስ በነጻና ሚዛናዊ ምርጫ የህዝብ የስልጣን ምንጭት እንዲረጋገጥ አስካላደረገ ድረስ በህገ መንግስቱ የተደነገጉ መብቶች በአግባቡ እስካልተከበሩ ድረስ በአትዮጵያ የፖለቲካ ግጭት አዝማሚያና የቀለም አብዩት ፍላጎት እየጨመረ እንጂ እያነሰ አይሄድም፡፡ከአቶ በረከት የሁለት ምርጫዎች ትረካ እሳቸዉ በግላቸዉም ሆነ ድርጅታቸዉ ይህኑን የተረዳ መሆኑ አይታይም፡፡ ታሪኩም እንደ ምርጫዎቹ አፈጻጸም ሆኖ ቀርቧል፡፡

Share

8 comments on “የአቶ በረከት ስምኦን መጽሐፍ

 1. A very interesting piece. The writer has articulated salient shortcomings of Ato Bereket’s government very well. He says: ”ባለፋት የኢህአዴግ የስልጣን ዓመታት የብሄር መብት ተረጋግጧል ቢባልም የብሄር መብትም ሆነ የዜጎች መብቶች በአግባቡ ሊከበሩ አልቻሉም፡፡ ለብሄረሰቦች ራሳቸዉን በራሳቸዉ የማስተዳደር መብት አልተሰጠም፡፡ የመደራጀት መብት ህጋዊ ሆኖ የተደነገገ ቢሆንም ካለመደነገግ ጋር ያለዉ ልዩነት ትንሽ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ሀሳብን በነጻ መግለጽ ነጻነት ህገ መንግስታዊ ቢሆንም ዋጋ ማስከፈሉን እንደቀጠለ ነዉ፡፡ በአገሪቱ የዴሞክራሲን ተግባራዊነት የሚያረጋግጡ ነጻ ተቋሞችን ለመፍጠር ኢህአዴግ እምቢተኛ ሆኖ ይገኛል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የተጀመረ ቢሆንም የህዝብን የስልጣን ምንጭነትን በእዉነተኛነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ነጻና ሚዛናዊ ምርጫ ገና አልተጀረም፡፡ የመልካም አስተዳደር አለመኖር በአገሪቱ የመንግስት አስተዳደር ዋነኛ ችግር ነዉ፡፡ ኢህአዴግ ስለስርዓቱ ዴሞክራሲያዊነት በየቀኑ ሊያስረዳን ቢሞክርም ስርዓቱ የህዝብ ተቋማዊ ተሳትፎ ያልተረጋገጠበትና በህግ በላይነት ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ ዜጎችን በጥቅም ከፋፍሎ ማቧደንና አግላይነትን ማስፈን እንደ አገዛዝ ስልት ሆኖ ስራ ላይ ዉሎ ይገኛል፡፤ ጊዜ ያለፈበትን የአንድ ፓርቲ አገዛዝ ለማጠናከር ሲባል የዘመናዊ ዴሞክራሲ ዋነኛ መገለጫ የሆነዉ የመድብለ ፓርቲ እድገት ሆን ተብሎ እንዲገታ እየተደረገ ነዉ፡፡ ይህ እንደኔ ዓይነት ሰዎች ኢህአዴግን ከስልጣ ተስፈኝነት በዘለለ ምክንያት እንድንቃወመዉ ያስገድድናል፡፡” and mre. Thanks Ato Mesfin.

 2. What are you saying Mesfine? Shame on you! አንተ ተደራጅተህ ኢዴፓን እየመራህ አደለም እንዴ? እና የመደራጀት መብት ባይኖር አንተ የኢዴፓ ዋና ፀሐፊ ትሆን ነበር? አንተ ይህንን ጽሁፍ መጻፍህስ ሃሳብ የመግለጽ መብት ስላለ አይደለም? መቼም ጋሞ ጎፋ ላይ የትግራይ ወይም የሰሜን ሸዋ ነፍጠኛ የተሾመ አይመስለኝም፡፡ እኔና ኢዴፓ ስልጣን ካልያዝን ከሆነ የምትለው፣ የመጀመሪያው ጥያቄዬ በየትኛው አቅማችሁ? የሚል ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢዴፓ አገር ቀርቶ አንድ ወረዳ ለማስተዳደር አቅም አላት? ከሁለተኛ ደረጃ የዘለለ እውቀት የሌላቸው እነ ነፃነት ደመላሽ፣ እነ ሙሼ ሰሙ ናቸው አገር የሚመሩት? ባታላግጥ ምናለ አያ መስፍን?!!!!!

 3. Gonder የተወለደና ያደገ ሰዉ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋነኛዉ ችግር የዴሞክራሲ እጦት ሳይሆን የብሄር ጭቆና ነዉ ወደሚል ድምዳሜ የደረሰዉ ከራሱ የህይወት ልምድ ይሁን ወይስ ከሌሎች ትምህርት እንደሆነ ማወቅ ለምንሻ መጽሀፉ ምላሽ የለዉም፡፡ የአቶ በረከት አስተሳሰብ በምን ምክንያት ከኢህአፓ ህብረብሄራዊነት ወደ ብአዴን ዘዉግነት እየተንሸራተተ እንደደረሰ የእሳ
  ዉን ትንተና በመጻፋቸዉ ወስጥ ብናገኘዉ ጥሩ ነበር፡፡

 4. አንተ ተደራጅተህ ኢዴፓን እየመራህ አደለም እንዴ? እና የመደራጀት መብት ባይኖር አንተ የኢዴፓ ዋና ፀሐፊ ትሆን ነበር? አንተ ይህንን ጽሁፍ መጻፍህስ ሃሳብ የመግለጽ መብት ስላለ አይደለም? መቼም ጋሞ ጎፋ ላይ የትግራይ ወይም የሰሜን ሸዋ ነፍጠኛ የተሾመ አይመስለኝም፡፡ እኔና ኢዴፓ ስልጣን ካልያዝን ከሆነ የምትለው
  our today’s enemy is not poverty but peoples like zeleke !!
  we should pry for GOD to destroy peoples like him from us.
  our brothers and sisters peoples like him are our(rulers of Gamos) current leaders. sham(yalemetadel)!!!!!!!!!!!!!!!

 5. gamo ethiopians,

  ምነው ወንድሜ “we should pry for GOD to destroy peoples like him from us.” ይባላል? ከኢዴፓ መሪዎችና አፍቃሪዎች የማይጠበቅ ነው፡፡ ይሄ ነው የናንተ ዴሞክራሲ? ሃሳቤን ገልጽኩ እንጂ ጠመንጃ አልመዘዝኩ?! ከናንተ ጎን እንድጠፋ ጦም ጠሎት ከሚያበዙ እኔ ራሴ እጠፋልዎታለሁ፣ የኔ መጥፋት ግን ሀቁን የሚደብቀው አይመስለኝም፡፡ ለማንኛውም እኔ እርስዎን ስላላደለሁ መልካሙን ሁሉ እመኝልዎታለሁ፡፡

 6. የኔ መጥፋት ግን ሀቁን የሚደብቀው አይመስለኝም፡፡ denkem hqe!!
  ሃሳቤን ገልጽኩ እንጂ ጠመንጃ አልመዘዝኩ?
  ከናንተ ጎን እንድጠፋ ጦም ጠሎት ከሚያበዙ እኔ ራሴ እጠፋልዎታለሁ፣ benathe ante ena mesel guadegnoche ersachewn byatefu. Gamo kebere malet aydeel ende?
  arbaminch yalen ye gamo ligoch melkam zena yehonal.ሃሳቤን ገልጽኩ እንጂ ጠመንጃ አልመዘዝኩ? ye gamo lijocen yemyasafir hasbe selehone new simeten meqotater yaqatign.Gamo gofa is suffering from good governance kemechem geze belye be enante yetenesa.

 7. This write has done excellent job. The way he explains and articulates is very attractive.I thank him

Comments are closed