Logo

ስለ ሊዝ አዋጁ በቴሌቭዥን የተደረገዉ ክርክርና ምላሽ ለመስጠት ያልተቻለው ጥያቄ

January 10, 2012

የውይይቱ ዋነኛ ጭብጥ ሆኖ በአወያይ ጋዘጠኛዉ የተነሳዉ የሊዝ አዋጁ የዜጎችን የንብረት ባለመብትነትን ያጠባል ወይስ ያሰፋል የሚለዉ ሲሆን ተቃዋሚዎቹ የተከራከሩት አዋጁ በህገ -መንግስቱ የተረጋገጠዉን የንብረት ባለመብትነት እንደሚያጠብ መሆኑን በማሳየት ሲሆን የመንግስት ባለሥልጣናቱ የተከራከሩት አዋጁ የንብረት ባለመብትነትን የሚያሰፋ ስለመሆኑ ነዉ፡፡ ባለሥልጣናቱ ለክርክራቸዉ መነሻ ያደረጉት በስፋት እየተካሄደ ነዉ ያሉት ልማት አብዛኛዉን ህዝብ ተጠቃሚ ያደረገ ልማት በማምጣት እንዴት የንብረት ባለመብትነትን እንዳረጋገጠ ነዉ፡፡

ሚኒስትር መኩሪያ ኃይሌ ከክርከሩ መግቢያ ጀምሮ መሬት የመንግስትና የህዝብ እንዲሆን በህገ- መነግስቱ መደንገጉ ምን ያህል አብዛኛዉን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ያስቻለ ልማትና አድገት እንዲመጣ ለማድረግ እንዳስቻለ ሰፋ አድርገዉ አብራርተዋል፡፡ እንደ ሚኒስትር መኩሪያ ገለጻ የሊዝ አዋጁ መንግስት ከከተማ ቦታዎች አስተዳደር ብዙ ገንዘብ ለመሰብሰብ ያስቻለዉ በመሆኑ በዚህ ገንዘብ አብዛኛውን ነዋሪ ተጠቃሚ ያደረገና የከተማውንም ልማት ማሳደግ ያስቻለ ስራ ተስርቷል፡፡ ክቡር አቶ መኩሪያ ለዚህ ማስረጃ አድርገዉ ከጠቃቀሱት ጉዳዮች መካከል የኮንዲሚኒየም ቤቶች ግንባታና የመሰረተ ልማት አቅርቦት እንዲሁም በአንስተኛና ጥቃቅን ልማቶችን ለማስፋፋት ያስቻለ መሆኑን ያብራሩት ይገኛል፡፡

አቶ መኩሪያ አዲሱ የሊዝ አዋጀ ይህኑን አጠናክሮ ለመቀጠል ያስችላል ነዉ ያሉት፡፡ እንዴት ቢባል ቀደም ሲል በነበረዉ የመሬት አስተዳደር ሂደት በመሬቱና ፈላጊዉ መካከል አገናኝ ሆነው ራሳቸዉን የዋጋዉ ወሳኝ በማድረግ አቅርቦቱን የተቆጣጠሩት ኃይሎችን አዲሱ አዋጅ ከጨዋታ ዉጪ ስለሚያደርጋቸዉ አቅርቦቱ ይፋጠናል ዋጋዉም ይቀንሳል፡፡ ሚኒስትር መኩሪያ ካነሷቸዉ ሀሳቦች መካከል መሬት የጋራ ሀብት በመሆኑ መጀመሪያ ያገኘ ብቸኛ ተጠቃሚ ሆኖ መቀጠል ስለሌበት መንግስት የመሬት ባለቤት በመሆን የተጠቃሚነትን መብት እያከፋፈለ አብዛኛዎችን ዜጎች ተጠቃሚ ማድረግ ያለበት መሆኑን ያብራራበትና አንድ ሰዉ መሬት በአንድ ጊዜ በእጁ ስላስገባ ብቻ ሳያለማበት በማቆየት ብዙ ሚሊዩኖችን የሚያተርፍበትን ለማስቀረት ሲባል መሬትን በእጁ አቆይቶ አትርፎ ከሚሸጥ ሰዉ መሬቱን የገዛበት ዋጋና ይህ ዋጋ በባንክ ቢቀመጥ ሊያስገኝ የሚችለዉ ወለድ ወይም በሌላ ስራ ላይ ቢዉል ሊያስገኝ የሚችለዉ ጥቅም ሲቀር ቀሪዉን መንግስት የሚወስድ መሆኑን ያብራሩት ትኩረትን የሚስብ ነዉ፡፡

ከንቲባ ኩማ እንደ አቶ መኩሪያ ሁሉ የልማቱን መስፋፋት በማብራራት የንብረት ተጠቃሚነት እንደተራጋጠ ያስረዱ ሲሆን ከዚህ ጸሐፊ እይታ አንጻር ሁለት መሰረታዊ ሀሳቦችን በእግረ መንገድ አንስተዋል፡፡ የመጀመሪያዉ የመሬት አስተዳደር ስርዓቱ ቀደም ሲል በነበረበት ድክመት የተነሳ የህዝብ ሀብት የሆነዉን መሬት አለአግባብ በመጠቀመም የከበሩ ጥቂት ሰዎች መኖራቸዉንና አዋጁ ለዚህ ዓይነት ኢ-ፍታሃዊነት መንገድ የሚዘጋ መሆኑን ሲሆን ሁለተኛዉ ልማት አመጣለሁ ያለ መንግስት ሁሉ ልማት አመጣለሁ ስላለ ብቻ ልማት እንደማያመጣ ይልቁንስ ልማት ሊያመጣ የሚችለዉ የህዝብ መንግስት እንደሆነ የተናገሩት ነው፡፡
የኢህአዴግ ባለሥልጣናት በክርክሩ ሂደት በርካታ ሀሳቦችን ያብራሩ ቢሆንም ሁሉም ከላይ የቀረበዉን ዋነኛ ሀሳብ ለማብራራት የቀረቡ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ ክርክራቸዉ በዋናነት መሬት የመንግስት ሆኖ በህገ- መንግስቱ ባይደነገግ ኖሮ አሁን በኢትዮጵያ የሚታየዉ ልማት ሊመጣ የማይችል የነበረ መሆኑን በሌላ አገላለጽም መሬት የመንግስት ሆኖ በህገ-መንግስቱ መደንገጉ ሰፋ ላለ ልማትና የህዝብ ተጠቃሚነትን እንዳረጋገጠ የሚያስረዳ ነዉ፡፡ ባለሥልጣናቱ ያቀረቧቸዉን ሀሳቦች በሚከተለዉ መልክ ሸንሽነን እንተቸዉ፡፡

1. የሊዝ አዋጁ የንብረት ባለቤትነትን የሚያሰፋ ነዉ ያሉትን በሚመለከት የኢህአዴግ ባለስልጣናት የውይይቱ ዋነኛ ጥያቄ የሆኖ የቀረበዉን የሊዝ አዋጁ የንብረት ባለቤትነትን ያጠባል ወይስ ያሰፋል የሚለዉን ጥያቄ የመለሱት ያሰፋል በሚል ሲሆን ይህንን ለማስረዳት ያብራሩት በዋናነት በአገሪቱ እየተስፋፋ ያለው ልማት ብዙሀኑን ተጠቃሚ በማድረግ ሀብት ለመፍጠርና የባለቤትነት መብት ለማረጋግጥ መነሻ ሊሆን መቻሉን ነዉ፡፡ ይህን ለማብራራት ሲሉም ከውይይቱ ሀሳብ ጋር ግንኙነት የሌላቸዉን በርካታ ማብራሪያዎችን አቀርበዋል፡፡ የሊዝ አዋጁ መሬቱንም ባይሆን በመሬቱ ላይ የመጠቀምን መብት ማስተላለፍን እንደማይከለክል ያነሱትንም አንስቼ ማለፍ እፈልጋለሁ፡፡ ይሁን እንጂ እንደሚገባኝ ከሆነ የልማት ተጠቃሚትና የንብረት ባለመብትነት ተነጣጥለዉ መታየት ያለባቸዉ ሁለት የተለያዩ ጉዳዮች ናቸዉ፡፡ አንድ ዜጋ የልማቱ ተጠቃሚ ሆኖም የንብረት ባለመብትነቱ ሊረጋገጥ የማይችልበት የንብረት ባለመብትነቱ ተረጋግጦም የልማት ተጠቃሚነቱ ሊጎድል የሚችሉባቸዉ በርካታ ሁኔታዎች መኖራቸዉን መረዳት ይቻላል፡፡

መንግስት የመሬት ባለቤት በመሆኑ ይህም ለልማት የሚሆን ብዙ ገንዘብ ለመስብሰብ ስላስቻለዉ በዚህ ምክንያትም ብዙ ልማት በመከናወኑ ዜጎችም በብዛት የዚህ ልማት ተጠቃሚ መሆናቸዉ ወ.ዘ.ተ ክርክሮች በኢትዮጵያ የንብረት ባለቤትነትና ሀብት ለማፍራት ያለዉ መብቶች የተጠበቁ ስለመሆናቸዉ ማሳያ ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ ከሊዝ አዋጁ ጋር ተያይዞ እየተነሳ ያለው ዋነኛ ጥያቄ አንድ ሰው የመሬቱ ተጠቃሚነት ባለመብት በመሆኑ ምክንያት በመሬቱ ላይ ባፈራዉ ንብረት ላይ ያለውን መብት አዋጁ ያሰፋል ወይስ ያጠባል የሚለው ነው፡፡ ህገ-መንግስቱ የዜጎች የንብረት ባለመብትነት የተጠበቀ መሆኑን
የሚደነግገዉ በሌላ ሁኔታ መሬት የመንግስት መሆኑን ደንግጎ እያለ ነዉ፡፡ መሬት የመንግስት እንዲሆን ለመደንገግ ያለዉ ምክንያት ምንም ይሁን ምን ይህ ድንጋጌ የግለሰብና ቤተሰብ ዋነኛ አሴት ሆነው ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገሩ ቋሚ ንብረቶች የቆሙበት መሬት የመንግስት በመሆኑ ምክንያት ብቻ በንብረቶቻቸዉ ላይ ያላቸዉ መብት የተቀነሰ መሆን ግልጽ ነዉ፡፡ የሊዝ አዋጁ መንግስት ቀድሞውንም ቢሆን በህገ-መንግስቱ መሰረት በመሬት ላይ ያለዉን ባለመብትነት መነሻ አድርጎ በመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ቁጥጥርን በማጥበቅ ለማስወገድ የተዘጋጀ መሆኑ በግልጽ የሚታይ ነዉ፡፡

የዚህ ዋነኛ ውጤት ሆኖ ሊወሰድ የሚገባዉ ቀደም ሲል በነበረው አሰራር ምንም እንኳን መሬት የመንግስት መሆኑ በህገ መንግስቱ ተደንግጎ ያለ ቢሆንም ዜጎች በመሬቱ ላይ የተጠቃሚነት መብትን በማነኛዉም መንገድ በማግኘት ሀብትና ንብረት እሰካፈሩና ይህም ሀብትና ንብረት በስማቸዉ በተመዘገበዉ መሬት ላይ እስከቆመ ድረስ መንግስት የመሬት ባለቤት መሆኑ ብዙም ትርጉም ያለዉ ሳይመስል የቆየበትን ሁኔታ የሚቀይር መሆኑ ነዉ፡፡ ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ አንድ ሰዉ በመሬት ላይ የተሰራውን ቤት በግዥም በስጦታና በዉርስም ቢያገኝ ቤቱን ለመሸጥ ይችል ስለነበር መሬት መሽጥና መግዛት ባይቻልም በቤቱ ስም ይሽጥና ይገዛ የነበረው መሬቱን ስለነበር መሬት አይሸጥም የሚለው ድንጋጌ ብዙም ትርጉም አልነበረዉም፡፡ የቤቱ ባለቤት መሆን የመሬቱም ባለቤት የመሆን ያህል ነበር፡፡ አዲሱ የሊዝ አዋጅ ይህንን ገልብጦ መንግስት የመሬቱ ባለቤት በመሆኑ ምክንያት የንብረቱ ባለቤት የመሰለበትን ሁኔታ ፈጥሯል፡፡

አዋጁ ይህንን ያደረገዉ ለሶስተኛ ወገን ማስተላለፍን (ቤትን መሸጥን) ሳይከለክል የሚተላለፍበትን መንገድ በማጥበብ ነዉ፡፡ ይህ በተለይም በነባር ይዞታዎች ላይ የተለየ ጫና እንዲኖር ተደርጎ ተደንግጓል፡፡ ነባር ይዞታ ባለቤት የሆነ ሰዉ ቤቱን
መሽጥ ቢፈልግ በስሙ የተመዘገበዉ መሬት ወደሊዝ አሰራር ስለሚቀየር ገዥዉ ቤቱን ከግለሰቡ ግዝቶ በሊዝ አዋጁ መስረት መሬቱን ከመንግስት መግዛት አለበት ማለት ነዉ፡፡ ነባር ይዞታ ወደ ሊዝ እንዲሸጋገር ስለሚደረግ የሊዝ አዋጁ ገደቦች ሰለባ ይሆናል፡፡ ከእነዚህ አንዱ የዕድሜ ገደቡ ነዉ፡፡ በሊዝ አዋጁ መሠረት በተገኘ መሬት ላይ ቢሆንም የሽያጩ ሂደት ንብረትን ለብቻ መሬትን ለብቻ የሚያደርግ ነዉ፡፡ በዚህ ሁኔታ መንግስት መሬት እንዳይሽጥ የፈጠረዉ ጫና በመሬት ላይ ያለዉ ንብረትም እንዳይሽጥና እንዳይተላለፍ የሚያደርገዉ በመሆኑ ማነኛዉም ሰዉ ቤቱን በፈለገበት ጊዜ በፈለገዉ የገበያዋጋ የሚሽጥበት ዕድል መ
ጋቱን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ አዋጁ ከዚህ በላይ መብትን እንደምን አድርጎ እስከየት ድረስ ይገድብ?

2. መሬትን የመሽጥ ጉዳይ

ሚኒስትር መኩሪያና ከንቲባ ኩማ መሬት የመንግስትና የህዝብ እንዲሆን በህገ- መንግስቱ መደንገጉ ምን ያህል አብዛኛዉን ህዝብ መሬትን እንዲጠቀም ለማድረግ ያስቻለ እንደሆነ ያብራሩትን መነሻ አድርገን አንዳንድ ጥያቄዎችን እናንሳ፡፡ የኢህአዴግ ነባር አስተሳሰብ መሬት የሚሸጥ የሚለወጥ ቢሆን ገንዘብ ያላቸዉ ጥቂት ሀብታምች ብቻ ገዝተዉ ስለሚያከማቹት አብዛኛዉ ሰዉ በእነሱ ተፅዕኖ ሥር ይወድቃል የሚል ነዉ፡፡ በርግጥ ይህ ብቸኛ መከራከሪያ አይደለም፡፡ ሚኒስተር መኩሪያ በህገ- መንግስቱ መንግስት የመሬት ባለቤት እንዲሆን መደንገጉ መንግስት መሬትን በማከራየት ብዙ ገንዘብ ለመስብሰብና በዚህም ገንዘብ ብዙ ልማት ለመስራት እንዲሁም የብዙሀን ሀብት የሆነውን መሬት መጀመሪያ የመጡት ብቻ ተጠቅመዉ ከኋላ የመጡት ሳይጠቀሙ እንዳይቀሩ ለማደረግ አስችሏል ያሉትንም እንጨምር፡፡

በመጀመሪያ መሬት የመንግስት የመሆንና ያለመሆን በመሬት አጠቃቀም ዙሪያ ዜጎች ሁሉ እኩል ድርሻ እንዲኖራቸዉ ለማድረግ አያስችልም፡፡ ባለፉት ዓመታትም መሬት የመንግስት ሆኖም ገንዘብ ያላቸዉ ጥቂት ሰዎች ሰፊ መሬት መያዛቸዉ አልቀረም፡፡ ወደፊትም የመሬት ዕኮኖሚያዊ ጉልበትና የገበያ ፍላጎት እያደገ እስከቀጠለ ድረስ ገንዘብ ያላቸው መሬትን በቋሚ ሀብትነት መያዛቸዉ አይቀርም፡፡ የሊዝ አዋጁም ቢሆን ይህን ማድረግን የማይቋቋመው መሬት በጨረታ እንዲቀርብ የሚደነግግ በመሆኑ ነዉ፡፡ በጨረታ እየተወዳደሩ ሊያሸንፉ የሚችሉት ገንዘብ ያላቸዉ መሆናቸዉ አይቀርም፡፡

የመሬት እኮኖሚያዊ ፍላጎትና ጉልበት እያደገ እስከቀጠለ ድረስ ገንዘብ ያላቸዉ መሬትን ገዝተዉ ሰፋ አድርገዉ ቢይዙ እንኳን ዝም ብለዉ ያከማቻሉ ማለት አይቻልም፡፡ ማከማቸትን የሚያስከትለዉ የመሬት ገበያዉን መንግስት አሰሮ ሲይዘዉና ይህም መሬት እየተወደደ እንዲሄድ ሲያደርግ ነዉ፡፡ የመሬት ገበያው ለተፋጠነ መተላለፍ ክፍት ከሆነ የመተላለፍ ፍጥነቱ (turn over) ይጨምራል፡፡ ይህ ማነኛውም አምራች ዜጋ ጥሮና ግሮ በሚያገኘዉ ገንዘብ የመሬት ባለቤት እንዲሆን ዕድል ይፈጥራል፡፡ መሬት በአንድ ሰዉ ባለቤትነት ሥር ታስሮ ለረጅም ጊዜ የሚቀመጠዉ ከአንዱ ወደሌላዉ የመተላለፍ ሂደት ጠባብ ወይም ዝግ ሲሆን ነዉ፡፡ ቀድመው የተወለዱ ሰዎች የመሬት ባለቤት የሚሆኑት በገንዘባቸዉ ገዝተዉ ከሆነ ይህ ዕድል ኋላ ለሚመጡትም እስካለ ድረስ እነሱም መሬትን በገንዘባቸዉ ገዝተዉ ባቤት ሊሆኑ ዕኩል መብት ይኖራቸዋል ማለት ነዉ፡፡ ሂደቱ አንድ ሰዉ መሬትን ሊያገኝ የሚችለዉ በጥረቱና በላቡ ብቻ ስለሚሆን አለአግባብ መጠቀምና በሙስና ማግኘትን እንዲሁም ተለዋዋጭ በሚሆነው የመሬት ገበያ ሂደት ወስጥ መሬትን ይዞ መቆየትን አለአስፈላጊ ያደርገዋል፡፡ ይህ መሬትን ቀድሞ የያዘ ብቻ ሲጠቀም እንዴት ዝም እንበል ለሚለዉ ለሚኒስትር መኩሪያ ስጋት መፍትሄ ይሆናል፡፡ አለበለዚያ መንግስት ራሱን የመሬት ባለቤት በማድረግ እተከታተሉ ለሚመጡ ትዉዶች ሲያከፋፍል ሊኖር አይችልም፡፡ መሬትም በመንግስት ይዞታ ሥር ተቋጥሮ ስለቀጠለ ብቻ ለትዉልዶች ሁሉ የሚበቃ ሆኖ እየሰፋ ሊቀጥል አይችልም፡፡ መሬት ሙሉ በሙሉ በመንግስት ባይያዝ ከሁሉም በላይ መንግስት ራሱን የመሬት ተጠቃሚነት መብት አዳይና ደልዳይ በማድረግ ለደጋፊዎቹ እያዳላ በዜጎች መካከል የሚፈጥረዉ አድልዎና የአስፈጻሚዎቹ በሙስና መበልፀግ ይቀርልናል፡፡

በሌላ በኩል መሬት በህግ የሚሸጥ የሚለወጥ ቢሆን ከአንዱ ወደ ሌላዉ የሚተላለፍበት ሁኔታ የተፋጠነ እስከሆነ ድረስ መንግስትም የመሬት ግብር በመሰብሰብ ገቢ የሚያገኝ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የመተላለፉን ሂደት በማሳለጥ ብዙ ገንዘብ ሊያገኝ ይችላል፡፡ አንድ መሬት በአጭር ጊዜ ወስጥ ብዙ ጊዜ ሊተላለፍ ስለሚችል የመተላለፉሂደትም ለመንግስት ብዙ ተደራረቢ ገቢ እንዲያገባ ምክንያት ይሆናል ማለት ነዉ፡፡

በአሁኑ ወቅት መንግስት ራሱን የመሬት ባለቤት ማድረጉ በኢትዮጵያ የዕድገት እንቅፋት ከሆኑ ችግሮች መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህን በቀላል ምሳሌ ላስረዳ፡፡ ኢህአዴግ ሚሊየነር አደረኳቸዉ ከሚላቸዉ ገበሬዎች አንዳንዶቹ በቴሌብዥን እየቀረቡ ይህን በሚያህል መሬት ላይ ይህን ያህል አምርቼ ይህን ያህል ገንዘብ አገኝቼበት በከተማ ይህን ያህል ቤት ሰራሁበት እያሉ ሲናገሩ ብዙ ጊዜ ስምተናል፡፡ ይህ እውነት ከሆነ እነኝህ ሰዎች ባገኙት ገንዘብ በከተማ ቤት ከመስራት ይልቅ በገጠር እርሻቸዉን ቢያስፋፉበት የበለጠ ትርጉም ያለዉ ኢንቨስትመንት ይሆን ነበር፡፡ እነኝህ ገበሬዎች ከኖሩበትና ከለመዱት የእርሻ ስራ ይልቅ
ከተማ ጡሩ ኢንቨስተሮች ሊሆኑ አይችሉም፡፡

3. የልማት አምጪነት ጉዳይ
ከንቲባ ኩማ ልማት አመጣለሁ ያለ መንግስት ሁሉ ልማት አመጣለሁ ስላለ ብቻ ልማት እንደማያመጣ ይልቁንም ልማት ሊያመጣ የሚችለዉ የህዝብ መንግስት የሆነ እንደሆነ የተናገሩት ትክክል ነው፡፡ አገራዊ ልማት በአገራዊ አቅምና ችሎታ ሳይሆን የአንድ ፓርቲ አመራር መልካም ፍቃድና ችሮታ ሆኖ ከእሱ ብቃትና ችሎታ ብቻ እንደሚመነጭ ከተያዘ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ አንጻር ሲታይ ይህ የበለጠ ትክክል ነዉ፡፡ ነገር ግን ይህ ጊዜ ያለፈበት የአምባገነን ፓርቲዎች የህገ-ወጥ ስልጣን ተቀባይነት ( legitimacy) መመሥረቻ ውትወታ ነዉ፡፡ የልማት ፍላጎት ብሄራዊ ዓላማና ምኞት በሆነበትና ይህም በዴሞክራሲያዊ አግባብ ተቋማዊ ሊሆን በቻለበት ፖለቲካ ውስጥ ይህ አስተሳሰብ ስህተት ብቻ ሳይሆን ኋላቀር አስተሳሰብ ነዉ፡፡ በዚህ ዓይነት ፖለቲካ ውስጥ የህዝባዊ መንግስትነት ትርጓሜ በህዝብ ድምፅ ከመመረጥ ሌላ መገለጫ የለውም፡፡ አንድ ፓርቲም በህዝብ ድምጽ መመረጥ የሚችለውም በሚያራምደው የልማት አጀንዳ መሆኑ የግድ ነው ፡፡ ቃል የገባውን ልማት ሊያመጣ ካልቻለም በህዝብ ውሳኔ ይወርዳል፡፡ አይመረጥምና፡፡ ህዝቡ ከሱ የተሻለ የልማት አጀንዳ ያለውን ፓርቲ ይመርጣል፡፡

የኢህአዴግ ዋነኛ ፍላጎት በማነኛውም መንገድ ስልጣን ላይ መቆየት ስለሆነ ይህ ተቀባይነት ካለው ምክንያት የሚመነጭ መሆኑን ሊያስረዳን ከሚሞከሪባቸዉ ኢ- ተፈጥሮአዊ ክርክሮች መካከል አንደኛዉ የኢትዩጵያ ዕድገት ሊረጋገጥ የሚችለዉ በእኔ አመራር ብቻ ነዉ የሚለው ነዉ፡፡ ኢህአዴግና የህንድ ኮንግረስ ፓርቲ መወዳደር የማይገባቸዉ ቢሆኑም ይህ በአንድ ነገር የህንድ ኮንግረስ ፓርቲን ያስታውሰኛል፡፡ የህንድ ኮንግረስ ፓርቲ የህንድ አንድነትና ዕድገት ሊቀጥል የሚችለዉ እኔ ስልጣን ላይ መቆየት ስችል ብቻ ነው፡፡ ያለበለዚያ ተቃዋሚዎች አገሪቱን ያፈርሷታል ልማትም ሰላምም አይኖርም እያለ የህንድን ህዝብ በማሞኘት
ለብዙ ዓመታት ጸረ- ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በስልጣን ላይ መቆየት ችሎ ነበር፡፡ ተቃዋሚዎች ስልጣን ይዘው የአገሪቱን አንድነት ማስቀጠል ብቻ ሳይሆን ከሱ የተሻለ ልማት መምጣቱ ሲታይ ህዝቡ የኮንግረስ ፓርቲን የዚያ ጥፋቱ ዋጋ ከፋይ አደርገው፡፡
አሁን ያለንበት ዓለም እንደቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ያሉ የለየላቸው ፈላጭ ቆራጮች ብቻ ሳይሆኑ እንደ ህንድ ኮንግረስ ፓርቲ ዓይነት አንድ እግራቸዉን በዴሞክራሲ ሌላኛዉን እግራቸዉን በአምባገነንት ያደረጉ ፓርቲዎችም በብቸኛ ልማት አምጭነት ለብዙ ዓመታት ሥልጣን ላይ መቆየት የማይችሉበት ነው፡፡ የዓለም ህዝብ የአንድ ፓርቲ አገዛዝና መሪ የረጅም ዘመናት ገናናነት ይብቃ ታሪክ ይሁን እያለ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብም ዘላቂ ልማትና አገራዊ ተሀድሶ የአንድ ፓርቲ ፍልስፍናና አመራር ችሎታና ችሮታ ሆኖ ሳይሆን አግባብነት ያላቸዉን ፖለቲካ ሓይሎች የጋራ ትብብርን በሚያጎናጸፍ ዴሞከራሲና መድብለ -ፓርቲ ወድድር ፓለቲካ አማካኝነት ብቻ ሊመጣ እንደሚችል ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ኢህአዴግ እንዲህ ዓይነቱ ፖለቲካዊ ዕድገት እንዳይመጣ ለምን እንደሚታገልም ጭምር፡፡

4. ስለኮንዴሚኒዬም ቤቶች ግንባታ
የዛሬ ሰባት ዓመታት ገደማ የኮንዴሚኒየም ቤቶች ግንባታ በወቅቱ ለሚሊየነሮችና ባለብዙ መቶ ሺህ ብር ባለቤቶች ይቀርቡ ከነበሩ የሪልስቴት ቤቶች አንጻር አንስተኛ ገቢ ላላቸዉ መንግስት እንዲያቀርብ ነበር የተጀመረዉ፡፡ ሀሳቡ ጣፋጭ የነበረ ቢሆንም አፈጻጸሙ ችግር ያለበት በመሆኑ ግቡን አልመታም፡፡ ሚኒስትር መኩሪያ ሲናገሩ እንደሰማሁት በመላ አገሪቱ እስካሁን የተሰሩት የኮንዴሚኒዬም ቤቶች ቁጥር ከመቶ ሰባ ሺህ አይበልጥም፡፡ ይህ ከሆነ ሰማኒያሚሊዮን ህዝብ ባለበት አገር በምንም መንገድ የኮንዴሚኒየም ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት የብዙሀን ተጠቃሚነት አብነት ሊሆኑ አይችልም፡፡ ምክንያቱም ከሰባት ዓመታት ሙከራና ስለስኬቱም ያልተቋረጠ ጉራ በኋላ፡፡ የተጠቃሚዎቹ ቁጥር ከህዝባችን ቁጥር ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አልሆነም፡፡
ችግሩ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የተሰሩት የኮንዴሚኒዬም ቤቶች ቁጥር ትንሸ ቢሆንም ወጪዉ ከፍተኛ ነዉ፡፡ ይህን በመንግስት ከፍተኛ ድጎማ የሚገነባውን መኖሪያ ቤት ተጠቃሚ የመሆን ዕድል የሚገኘዉ በሁለት መንገድ ነዉ፡፡ አንደኛዉ የኢህአዴግ አባልና ደጋፊ በመሆን ሲሆን ሁለተኛዉ እንደሎቶሪ በዕጣ ነዉ፡፡ ሁለቱም ፍትሐዊ መንገዶች አይደሉም፡፡

ማጠቃለያ
ይህን ውይይት በማዘጋጀቱ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ድርጅት መመስገን የለበትም፡፡ ምክንያቱም ኢቴቪ የህገ መንገስቱንና የተቋቋመበትን አዋጅ ድንጋጌ ተከትሎ የሚሰራ ተቋም ቢሆን ኖሮ እንዲህ ዓይነት ውይይቶችን ማዘጋጀት መደበኛ ስራዉ መሆን ይኖርበት ነበር፡፡ ይህ ድርጅት ይህን ውይይት ያዘጋጀዉ በህገ- መንግስቱ በተደነገገዉ መሰረትና ለተፎካካሪ ሀሳቦች ዕድል በመስጠት እንዲያገለግል በማቋቋሚያ አዋጁ በተቀመጠዉ መሰረት ግዴታዉን ሊወጣ ሳይሆን የሊዝ አዋጁ አጨቃጫቂነት ለኢህአዴግ አሳሳቢ ሆኖ በመገኘቱ ታዞ መሆኑን መገመት ይቻላል፡፡

ይህም ቢሆን የተከበሩ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት የውይይቱ ዋነኛ ጥያቄን ከራሳቸዉ መነሻ አንጻር ለመመለስ የሄዱበት ሁኔታ የሊዝ አዋጁ ግልጽ እንዲሆን የሚያደርግ አይመስልም፡፡ የሊዝ አዋጁ የንብረት ባለመብትነትን መብት ያጠባል ወይስ ያሰፋል የሚለዉን ጥያቄ ለመመለስ ያሰፋል ያሉበት መነሻ ብዙ እንዲናገሩ አደረጋቸው እንጂ ብዙ ሊያሳምኑ አላስቻላቸዉም፡፡ ምክንያቱም የሊዝ አዋጁ የዜጉችን የንብረት ባለመብትነትን ከማጥበብ በላይ የሚነጥቅ መሆኑ ግልጽ ስለሆነ ማንም ቢሆን ያሰፋል ብሎ ተከራክሮ ማንንም ሊያሳምን አይችልምና፡፡ ይህ አዋጅ በህገ- መንግስቱ የተደነገገዉን የዜጎችን የንብረት ባለመብትነትን መብት በግልጽ ይነጥቃል፡፡

Share

5 comments on “ስለ ሊዝ አዋጁ በቴሌቭዥን የተደረገዉ ክርክርና ምላሽ ለመስጠት ያልተቻለው ጥያቄ

  1. According to this writer, the government also is one of the losers because of the new lease policy.

  2. Do You know Ethiopian history? Why Emperor Haile Selassie overthrown by the 1974 popular revolution? The main reason is that he could not solved land problem! Why coloen Mengistu Haile Mariyam regime came to an end in 1991? Due the fact that he could not gave ultimate solution to land question! History told us above fact.
    Why EPDRF formulate new land tax system?
    Why EPDRF ignore to learn previous goverments problem?
    Why EPDRF immersed themselves above accumlate previous problem?

Comments are closed