Logo

ታዋቂው ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ ዐረፉ

March 2, 2012

ልጆቻቸውም ማሞ ውድነህ ድነው ያልታተሙላቸው ፅሁፎቻቸውም ለህትመት እንዲበቁ ይመኙ ነበር ። ግን አልሆነም ከቀናት በፊት ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ህክምናቸውን በሚከታተሉበት ስፍራ ድረስ ሄዶ ያናገራቸው ማሞ ውድነህ አሁን አርፈዋል።

የዛሬ 77 ዓመት በዋግ አውራጃ የተወለዱት ማሞ ውድነህ በጉልምስና እድሜያቸው በደራሲነት፣ ጋዜጠኝነትና ተርጓሚነት ሰርተዋል። በአዲስ ዘመንና በፖሊስና እርምጃው ላይም ፅፈዋል። በ1954 ላይ የመጀመሪያቸውን መፅሃፍ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በሚል ርእስ ለህትመት አበቁ።

ከዚያም ቀጠሉ። ሁለቱ የዓለም ጦርነቶች፣ የስድስቱ ቀን ጦርነት፣ ሾተላዩ ሰላይ፣ በረመዳን ዋዜማ፣ ሞት የመጨራሽ ነውን ከፃፏቸው መፅሃፍቶች 53 መፅሃፍት ዝርዝር መካከል ናቸው። ስምንት ትያትሮችም ለመድረክ በቅተውላቸዋል።

ዛሬ ማለዳ ላይ ከረዥም የህክምና ክትትል በኋላ ኢትዮጵያችን እኝህን ደራሲ፣ ጋዜጠኛና ተርጓሚ አጥታለች። በሰባሰባት ዓመታቸው ማሞ ውድነህ አርፈዋል።

የሶስት ሴቶችና የሶስት ወንዶች ልጆች አባት የሆኑት ማሞ ቀድመው ለህትመት ያበቋቸውም ሆነ ህትመትን እየተጠባበቁ ያሉት መፅሀፍቶቻቸው ሁሉም በነበር እንዳይቀር አድርገዋል። ስለራሳቸው የህይወት ጉዞ የተረኩበት መፅሀፍት ሶስተኛ ክፍልን ጨምሮ ለአንባቢያን መድረስን የሚፈልጉ በርከት ያሉ መፅሀፍትንም ትተውልን አልፈዋል።

የታላቁ ደራሲ፣ ጋዜጠኛና ተርጓሚ ማሞ ውድነህ የቀብር ስነ ስርአት ነገ ከቀኑ በ9 ሰአት ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ቤተ ክርስቲያን ይፈጸማል።

source Fana Broadcasting

Share