Logo

“ሕገ መንግስትና ምርጫ ‘እያነቡ እስክስታ’ ”

Mushe Semu
December 17, 2012

 ከዚህ ቀደም እንደታየው ሚዛናዊ የሆነ ውድድር ማድረግ ባለመቻሉ ምክንያት ውጥረት ውስጥ የወደቀው የመድብለ ፓርቲ ምርጫ ስርዓታችን በሂደት ፍጹም እንዳይዳፈንና በአንጻራዊነትም ቢሆን ሚዛናዊነቱን ሳይስት ከቅርጫ ወደ ምርጫነት እንዲሸጋገር በማሰብ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ባደረግነው ድርድር መሰረት በ2001 ዓ.ም በተረቀቀውና በጸደቀው የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ደንብ አንቀጽ “አርባ ሰባት” ንዑስ አንቀጽ “አንድ” ላይ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የገንዘብም ሆነ የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያገኙ በሕግ ቢደነገግም በአሁኑ ምርጫ፣ ይህ ሕጋዊ መሰረት ያለው ድጋፍ እንደማይኖር  ምርጫ ቦርድ ገልጾል፡፡

ምርጫ “ሰላማዊ ነጻና ገለልተኛ” በሁሉም አካለት ዘንድ የታመነና ተቀባይነት ያለው እንዲሁን ከተፈለገ አንዱና ወሳኙ ነጥብ የውድድር ሜዳውን ጨምሮ የቁሳቁስና የገንዘብ አቅርቦቱ ያለአድልዎ ለሁሉንም በእኩልና በሚዛናዊነት መኖሩ ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ ይህን ሚዛንዊ ስሌት ተጠብቆ ምርጫው ተግባር ላይ መዋሉን የማረጋገጥ ኃላፊነት የተጣለው ደግሞ በምርጫ ቦርድና በሌሎች መሰል የዴሞክራሲ ተቋማት ላይ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጉዳይ በኃላፊነት እንዲመራ  በሕግ ስልጣን የተሰጠው ምርጫ ቦርድ የሃገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ በማጤን ፓርቲዎች ተመጣጣኝ የውድድር አቅም እስኪፈጥሩ ድረስ በገንዘብና በቁሳቁስ እንዲደገፉ፣ በቂ፣ አስተማማኝና ቀጣይነት ያለው፣ ሁሉንም አካታችና ሚዛናዊ የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን እንዲያገኙ መከታተልና በተግባር ላይ መዋሉን ማረጋገጥ አለበት፡፡ ጉድለትም ካለ ሚዛናዊነቱን ማስከበር ይጠበቅበታል፡፡

በዚህ ምርጫ እየታዘብን ያለነው እውነታ ግን ከዚህ በእጅጉ የራቀ ነው፡፡ ከላይ እንዳነሳሁት ምርጫው ከመጀመሩ በፊት ምርጫ ቦርድ እያወጣ ከሚገኝው መግለጫ ለመረዳት እንደሚቻለው ፓርቲዎች ንቁ ተሳትፎ አንዲኖራቸው ለማገዝ በተለምዶ ይደረግ የነበረው የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አይኖርም፡፡ በዚህም ምክንያት፤ በተለይ ደግሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እዚህ ግባ የማይባል አቅማቸውን ይዘው ተቀናቃኛቸው ከሆነውና እጅግ ከተደራጀው፣ ከ-እስከ በማይባል ደረጃ በሃገሪቱ ሃብት ላይ የማዘዝ መብት ከተጎናጸፈው ኢህአዴግ ጋር ለመወዳደር ወደ ምርጫ እንዲገቡ እየተገደዱ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ማንም ዜጋ እንደሚረዳው በዚህ ምርጫ ላይ ትርጉም ያለው ፉክክር ሊያደርጉ እንደማይችሉ ግልጽ፡፡

የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር  5/2001 አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት “ መንግስት በፌደራል ወይም በክልል ምክር ቤቶች ምርጫ ላይ ለሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ እንደሚሰጥ ” ይደነግጋል፡፡  ምርጫ ቦርድ በሕግ ላይ ከሰፈረው ድንጋጌ ውጭ ረጅም ርቀት በመሄድና ያለ በቂ ምክንያት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፉን መከልከል ለምን እንደስፈለገው ወይም ይህንን የአድልዎ መንገድ ለምን እንደመረጠ ለመረዳት ምርመራ የሚያሻው ጉዳይ አይደለም፡፡

ምርጫ ቦርድ ነጻና ገለልተኛነቱን ሊያረጋግጥባቸው ከሚገቡ እርምጃዎቹ መካከል አንዱና ዋነኛው በሕግ የተደነገጉ ምርጫና ፖለቲካ ፓርቲ ነክ ጉዳዩች እንዲከበሩ ዘብ ሲቆምና ለምን ብሎ መጠየቅ ሲጀምር መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ በሚወስደው ከመድሎ የጸዳና በሕግ ላይ የተመሰረተ ውሳኔው ምክንያት ሌሌች መንግስታዊ ተቋማት ያልተገባ ተጽእኖ የሚደርጉበት ከሆነ ከተጽኖዎቹ እራሱን ለመላቀቅ የሚችለው በመጀመርያ እራሱ እንደ ተቋም የሚገዛበትን ሕግንና ደንብ ሲያከብር ነው፡፡ ሕግን ለማስከበር በመጀመርያ ደረጃ ሕግን ማክበር  ይላልና፡፡  

በዚህ መልኩ ለሕግና ለስርዓት የመገዛት ዝንባሌ ወይም ተሞክሮ በምርጫ ቦርድ ታሪክ ውስጥ ከዚህ ቀደም ፍንጩ ያልታየ ቢሆንም ምርጫ ቦርድ ለፍትህና ለርትዕ ዘብ ለመቆም ከወሰነ ጊዜው ስለማይረፍድና ከታሪክ ተጠያቂነት ለመዳንም ምክንያት ስለሚሆን  ምርጫ ቦርድ ዛሬም ከፊቱ የተደቀነውን ይህንን እድል ተጠቅሞ ከፍትሕና ከርትዕ ተርታ በመቆም ሰልፉን ማሳመር ይኖርበታል፡፡    

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ምርጫ ቦርድ የምርጫውን ታአማኒነት ከወዲሁ በእጅጉ የሚሸረሽሩና ተስፋ የሚስቆርጡ (ተስፋ የሚቆርጥ ከተገኝ) አሳሳቢ እርምጃዎችን መውሰዱ ሕግን ተጻሮ እየቆመ መሆኑን ለማስረዳት በገሃዱ ዓለም ከዚህ የተሻለ መረጃ ሆኖ ሊቀርብ የሚችል አንዳችም ነገር የለም፡፡ ከዚህ በመነሳትም ላጤነው የምርጫው ውጤት በማንኛውም መስፈርት ከጅምሩ የተዛባ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡  

የ2002 ዓ.ም. ምርጫ እንዳስተማረን ከሆነ የምርጫ ውድድሩ በሕዝባዊና ሃገራዊ አጀንዳዎች ዙርያ በሚቀርቡ አማራጭ ፖሊሲዎች ዙርያ ከመወዳደር ይልቅ ልክ በአሜሪካ እንደሚደረጉት ምርጫዎች ሂደቱ ያተኮረው የምርጫ ዘመቻን በማሳመርና በማስዋብ ማለትም ፖስተርን፣ ፍላየርስንና ቲ-ሸርትን ለማሳመር እንደ ሰዓትና ብዕር የመሳሳሉ ቁሳቁሶችን በነጻ ለማደል ወይም ምሳ፣ ቁርስና እራት እንዲሁም ቡና ለመጋበዝ የሚያስችል በቂ መዋለ-ንዋይ ማፍሰስ መቻል ላይ  ነበር፡፡

በዚህም ምክንያት የ2002 ምርጫ በአንድ በኩል ገደብ በሌለው የገንዝብና የቁሳቁስ አቀርቦት ተደራጅቶ በሚንቀሳቀሰው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግና በሌላ በኩል እጅግ በተመናመነ አቅም እጅ ከወርች ተቀይደው በሚፍጨረጨሩ ተቃዋሚዎች መካከል የሚደረግ ሚዛናዊነት የጎደለው ምርጫ ሆኖ ማለፉ አንዱ አሳዛኝ ገጽታው ነበር፡፡ ችግሩ ይህ ብቻ አልነበረም፡፡ ሂደቱ በአጠቃላይ ለመመዘን ናላ በሚያዞር የቅስቀሳና የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ላይ ምርጫ ማጭበርበር፣ እጩ ማሳደድ፣ ማዋከብና  አፈና በአናቱ ላይ ጨመሩበትና አስሉት ውጤቱ ላይ መድረስ የሚቻለው ያኔ ብቻ ነው፡፡

በ97ቱ ምርጫ አርባ ስልሳ የነበረው የምርጫ ውጤት አቻምና በ2002 ዓ.ም ላይ ውጤቱ ወደ 99.6 ፐርሰንት ተመንድጎ በኢህአዴግ ቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ የቀረችውን 0.4 ፐርሰንት ኢህአዴግ ጠቅልሎ ሊወስደው እንደሚችል በርካታ አመላካች ጉዳዮች እየታዩ ነው፡፡ ይህ ውጤት እንግዲህ ለታሪክም ቢሆን ትንግርት  መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ምክንያቱም እንደ ሳዳም ሁሴን፣ መንግሰቱ ሃይለማርያማና፣ ሆስኒ ሙባረክ ያሉ በበላኤ ሰብነት በእጅጉ የተዘመረላቸው አምባገነኖችም  ቢሆኑ በታሪካቸው ዘጠና ዘጠኝም ሆነ መቶ ፐርሰንት አሸንፈው አያውቁም፡፡ ከዚህ አኳያ ለተመለከተው በሕገ መንግስቱ አማካኝነት የተረጋገጠው የመድብለ ፓርቲ ስርዓታችን ለአደጋ አልተጋለጠም በሚል የሚነዛው የገዢው ፓርቲ ፕሮፓጋንዳ ጉንጭ አልፋ ከመሆን እንዳልዘለለ የሚያረጋግጥ ነው!!

ከምርጫ ቦርድ መርሃ ግብር ለመረዳት እንደሚቻለው ከሆነ የምርጫ ቦርድ ስራ በሂደት እየቀጨጨ መጥቶ በተለይ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ዓይነተኛ ተግባሩ ምርጫን ማመቻቸት፣ ሂደቱንና ውጤቱን መታዘብ ብቻ ሆኗል፡፡ በምርጫዎች መካከል ፓርቲዎች የት እንደደረሱና ምን እያከናወኑ እንደሆነ መረጃ የለውም፡፡ ለጠቅላላ ጉባኤ ካልተጠራ በስተቀረ የሕልውናው መሰረት የሆኑ ፓርቲዎችን ከፖለቲካ ፍልስፍናቸውና ርዕዮተ ዓለማቸው ውጭ ባሉ በርካታ ጉዳዮች ላይ አቅም የመገንባትም ሆነ የማጠናከር ስራ ሲሰራ አይታይም፡፡ ያለፉትን ምርጫዎች ሂደትና ውጤት በመመርመር ተግዳሮቶቹን በመቅረፍና የተሻለ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን የሚያጎለብት ጥረት ሲያደርግ አይታም፡፡ አልፎ ተርፎም ከመድብለ ፓርቲ ስርዓታችን አጠቃላይ ሂደትና ፋይዳ ጋር ባለው የተሳሰረ ግንኙነት ምክንያት ዓይነተኛ ተጠቃሽና ባለቤት የሆነው ምርጫ ቦርድ ስርዓቱን በዴሞክራሲያዊ መንገድ እየተመራ መሆኑን ለማረጋገጥ ከሁሉም ፓርቲዎች ጋር ተባብሮ ካልሰራ ጉዳዩ ለማን እንደተተወ ማወቅ አይቻልም፡፡

ምርጫ ቦርድ ኃላፊነቱን ከመወጣት ጀምሮ በራስ ተነሳሽነት ላይ ተመስርቶ የሕዝባዊነትን መርህ በማስቀደም ከጥላቻ ፖለቲካ መጽዳትን፣ እውቅና መስጠትን፣ የመቻቻል ፖለቲካ ማስረጽንና ይህንን የመሳሰሉ ሌሎች ክትትል የሚያሻቸው  በርካታና ትልልቅ ሃገራዊ ፋይዳ ያላቸው ቁም ነገሮች እንዳሉ ለምርጫ ቦርድ መንገር ለቀባሪው የማርዳት ያህል ነው፡፡

ለዚህም በምሳሌነት የሚነሳው በገዢው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል በየወቅቱ የሚነሱት ውዝግቦችና ንትርኮች ሕዝቡን ዘወትር ግር ሲያጋቡት መታየቱ ነው፡፡ በዚሁ እሰጣ አገባ ንትርክ ምክንያት ሕዝቡ የጥላቻ ፖለቲካ ሰለብ እየሆነ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ይህንን መሰረታዊ ችግር ቆሞ ከመታዘብ ባለፈ በገለልተኝነትና በያገባኛል መንፈስ ውዝግቦቹ ተፈተው ፓርቲዎቹ ለማህበረሰቡ መልካም ምሳሌ እንዲሆኑ አልፎ ተርፎም ዴሞክራሲያዊ መድብለ ፓርቲ ስርዓቱን በማጠናከር በባላንጣነት ከመተያየት ይልቅ ተቀራርበው ለመስራት እንዲችሉ፤ በመነጋገርና በመቻቻል መፍትሔ እንዲያመነጩ የሚያስችል የማግብብት ሚና ሲጫወት ታይቶ አይታወቅም፡፡ ይልቁንም ገዢው ፓርቲ ከሁሉም ምድራዊ ችግሮችና ስህተቶች የጸዳ ተቃዋሚ ፖርቲዎች የሃገሪቱ ችግሮች ሁሉ ማከፋፈያ ምንጭ አድርጎ ከማየት ያለፈ ዝንባሌ ኖሮት አያውቅም፡፡

በአጠቃላይ የምርጫ ቦርድ የወቅቱ ሚና ምርጫው ሲቃረብ ተፍ ተፍ በማለት ምርጫውን አጉልቶ ለማሳያት ብቻ ወቅት እየጠብቁ ተቃዋሚዎች የትገባችሁና ድረሱልኝ ከማለቱ ውጭ የተቋቋመበትን ዓላማና የታቀደለትን ግብ ተመርኩዞ ፓርቲዎችን በቁሳቁስና በገንዘብ ከማጠናከር እዚህ ግባ የሚባል ድርጊት እየፈጸመ አይደለም፡፡

ምርጫ ቦርድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውጣ ውረዱን ተቋቁመው ለዴሞክራሲያዊ ስርዓቱና ለሂደቱ ታማኝ በመሆን ለውድድር መብቃታቸውን አድንቆ ችግሮቻቸውን በቅን መንፈስ በማዳመጥ መፍትሄ ከመሻት ይልቅ ጥያቄዎቻቸውን ማጣጣልና ፓርቲዎቹን በደካማነትና በሕገ ወጥነት መክሰስና መውቀስ የተለመደ ተግባሩ ነው፡፡

ከዚህ አኳያ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሆኑ ገዢው ፓርቲ የዚህ ስርዓት መገለጫዎች ናቸው፡፡ በተለይ በዚህች አገር ፖለቲካና ታሪክ ውስጥ ተምረውና አድገው እራሳቸውን ለፖለቲካ ትግል ያጩ ግለሰቦች ስብስብ የሆኑት ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ደካማ ከሆኑ ደካማነታቸው ከተቀናቃኛቸው ከኢህአዴግ አባላት በአስተሳስብ፣ በተሞክሮ አሊያም በትግል መንፈስ የሚያንሱ ስለሆኑ ወይም እንዲያው ሊታወቅ በማይችል አንዳች ሚስጥራዊ ምክንያት ደካማ ሆነው ስለተፈጠሩ ሊሆን አይችለም፡፡ ፓርቲዎቹ እንደማንኛውም ተቋም የማያካዱ አንዳንድ ውስጣዊ ችግሮቻቸው እንደተጠበቁ ሆነው፤ ደካማ የሚያደርገቸው ነገር ካለ ምክንያቱ ሌላ ሳይሆን የተሰናከለና (dysfunctional) ለችግሮቻቸው መፍትሄ መስጥት ያልቻለ ሚዛናዊነት የጎደለውና አድሎአዊ የዴሞክራሲ ስርዓት በመዘርጋቱ መሆኑን መረዳት ያሻል፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዴሞክራሲያዊ የሆነ የመደብለ ፓርቲ ስርዓትን ለመገንባት ገና አንገቱን ቀና በማድረግ ላይ በሚገኝ ማህበረሰብ ውስጥ በመፈጠራቸው ምክንያት መጠነ ሰፊ ውጣ ውረድ ወከባና እንግልትን ተቋቁመው ማለፍ እንደለባቸው ነባራዊ ሁኔታው የግድ ብሏቸዋል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአፈና ውስጥ ተወልደው በአፈና ውስጥ በማደጋቸው ምክንያት መብትና ግዴታቸውን ለማስከበር ይቅርና በህይወታቸው ላይ ለመወሰን ህልውናቸውን በተካዱ ዜጎች መሃል አድገው አንገታቸውን ቀና በማድረግ ቁጥር ለመሙላት ያህል እንኳን በተደራጀ መልኩ የመሰንበታቸው ዜና ለትንግርት ሊነገር የሚገባው እውነታ ነው፡፡
 ምርጫ ቦርድ ከማንም በፊትና በላይ በተጠሪነት የሚያስተዳድራቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች መዳከምና መጥፋት በሂደት የመድብለ ስርዓቱን መዳከምና መጥፍተና በማስከተል በመጨረሻም የራሱ የምርጫ ቦርድን ህልውናን አደጋ ላይ ሊጥለው እንደሚችል ይገነዘብው ዘንድ ምርጫ ቦርድ ጠንቋይ መቀለብ አያስፈልገውም፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሌሉበት ስለመድብለ ፓርቲ ስርዓትና ስለምርጫ ለመነጋገር ማሰብ አይሮፕላን በሌለበት ስለኤርፖርትና ስለአየር መንገድ እንደማውራት የሚቆጠር ነው፡፡

ስለ ዴሞክራሲያዊ መድብለ ፓርቲ ስርዓትና ስለምርጫ ሰላማዊነት፣ ነጻና ሚዛዊነት ለመነጋገር ከተፈለገ የተጀመረው በዚህ ጉዳይ ላይ ምርጫ ቦርድና ሌሎች መስል ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ተጨባጭ ሁኔታውን ቆም ብለው ሊመረምሩት ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ሕገ መንግስቱ፣ ምርጫና ምርጫ ቦርድ እያነቡ እስክስታ ከመሆን አያልፉም፡፡

Share

4 comments on ““ሕገ መንግስትና ምርጫ ‘እያነቡ እስክስታ’ ”

  1. የምርጫ ቦርድ ችግር አድርገን እንየው እንጂ ችግሩ ያለው የምርጫ ቦርድ ሀላፊዎችን በፈለገው ጊዜ እንደፈለገው ሊሽርና ሊሾም በሚችለው ኢህአዴግ ዘንድ ነው:: የምርጫ ቦርድ ሀይልና ተሰሚነት የሚኖረው የህግ የበላይነት በሰፈነባቸው አገሮች ብቻ ነው እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ የምርጫ ቦርድን መኮነን አይታየኝም::

    ለዚህ ምን መፍትሄ እንዳለ አይታየኝም ነገር ግን ቢያንስ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትና በሰላማዊ መንገድ የሚነቀሳቀሱት ዋና ዋና ተቃዋሚ ፓርቲዎች የድርጅት ህልውናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በጋራ ጉዳዮች ላይ አንድ ላይ ቢሰሩና ተመሳሳይ አቋም ቢውስዱ ጥሩ ነው እላለሁ:: ይሄም እንዲሳካ ተቃዋሚዎች በጋራ የሚወያዩበት ወይም ተገናኝተው የሚነጋገሩበት ሁኔታ ቢመቻች የተሻለ ይመስለኛል:: በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ጋዜጦችም ይሄ እንዲሳካ የራሳቸውን ጥረት ቢያደርጉ ለስኬቱ አስተዋጽኦ ያደርጋል::

  2. We have seen and heard about such kinds of illegal practices time and again. What is amusing is the opposition is likely to fall in the same old trap. As Einestein once said “stupidity is doing the same thing and expecting a different result ” . My take on this issue is BOYCOTT the election.

Comments are closed