Logo

ዜጎችን አሳንሶ ራሱን ያገዘፈው “ልማታዊ መንግስት” (ከሙሼ ሰሙ)

February 22, 2013

በሌላ በኩል ደግሞ የሊብራል ዴሞክራሲ ፍልስፍና፤በዜጎች እኩልነትና ነጻነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ሊብራል ዴሞክራሲ ዜጎች በፖለቲካውና በኢኮኖሚው ለሚኖራቸው አይተኬ ሚና ልዩ ጥበቃ ያደርጋል፡፡ በዚህም ምክንያት ዜጎች በኢኮኖሚው ውስጥ በሚኖራቸው ተሳትፎ ልክ የሃገርን ኢኮኖሚያዊ አቅም ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ በማጎልበት የስራ እድል ፈጠራን በማስፋፋት፣ለሃገር ልማትና እድገት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ በመንግስትም ሆነ በተቋማቱ እንዳይተካ ፍጹም የሆነ ከለላ ይሰጣል፡፡ በፖለቲካው ዘርፍም ቢሆን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፤ የፍትሕ የበላይነት እንዲረጋገጥ፤ዜጎች ለሚጫወቱት ሚና ከለላ እንዲሰጡና ጥበቃ እንዲያደርጉ፣ እንዲሁም በመንግስታዊ ተቋማትና አስፈጻሚዎቹ እንዳይጠለፉ ዘብ ይቆማል፡፡ ዜጎች የሃገር ሉአላዊነትን ከማስከበር ጀምሮ የሃገር ኩራትና ክብር በመሆን ለገጽታ ግንባታ የሚኖራቸው ትሩፋት በመንግስትና በተቋማቱ ወይም በሹመኞችና አስፈጻሚዎቹ ሊተካ የማይችል ሚና እንደሆነም ጠንቅቆ ይገነዘባል፣ ለተፈጻሚነቱም ይታገላል፡፡

መንግስት እጅግ ገዝፎ ከሕዝብና ከሃገር ሉዓላዊነት በላይ ሲሆን የዜጎች ሚና በዛው ልክ እየቀጨጨና እየኮሰመነ በመሄድ፤የሃገር ባለቤትነታቸው ጉዳይ ወደ አጋፋሪነትና አስተናጋጅነት ይወርዳል፡፡ ራእይና ትልምን ለማሳካት የሚያስፈልገው የመንግስትና የሕዝብ አንድነትና ምሉዕነት በሕግ፣ በስርዓትና በደንብ “እኔ አንተን ስለሆነኩ ሁሉን ነገር አውቅልሃለሁ” በሚል ይተካል፡፡ ቀጥሎም የፖሊሲ አቅጣጫህን፣ ራዕይህን፣ የፖለቲካ ፍልስፍናህንና ሃይማኖትህን በአዋጅና በመመርያ ካልጋትኩህ ይመጣል፡፡ ዘመኑ የአማራጭና የምርጫ በመሆኑ እንደዚህ አይነቱ “የልጋትህ ፖለቲካ” ለማንም ዜጋ ሊዋጥ የሚችል አይሆንም፡፡ መጽሐፉ “ያልተጠመቀ አይድንም” እንዲል፤ ያልተጋተ ስለ መብቱና ጥቅሙ ዘብ ስለሚቆምና አልፎ ተርፎም በኒዎ ሊብራሎቹ ፊት በማሳጣት ብድር፣ እርዳታና ስጦታ ስለሚያጓድል ወቅቱን የጠበቀ ምርጫ ማካሄድ የግድ ነው፡፡ ምርጫ ካለ ደግሞ አማራጭ የግድ ነው፡፡ ምርጫን ያለአማራጭ ማስተናገድ የሚቻለው ነጻና ገለልተኛ ምርጫን በማዛባት የህልውና ማስቀጠያ በማድረግ ብቻ ነው፡፡

“የልማታዊ መንግስታት” የግዙፍ መንግስት ፍላጎትና መንስኤ ከግለኝነትም ይመንጭ ከቡድናዊነት፤አብዛኛዎቹ ግራ ዘመም “ልማታዊ መንግስታት” በስልጣን ላይ ለመቆየት በምክንያትነት የሚያቀርቧቸው መከራከርያዎች አዲስ አይደሉም በሃይማኖት፣ በብሄር፣ በፖለቲካ ወይም በኢኮኖሚያዊ ምክንያት በቁጥር አናሳ የሚሏቸውን የሕብረተሰብ አካላት ጥያቄ ሚዛናኑን በሳተ መንገድ በማጋነንና መራራ ቀለም በመቀባት ከተበዳዮቹ በላይ ለበደሉ ዘብ በመቆም፣ ጀግኖች የተሰውለትን የሰማዕታት ጥሪ አናስደፍርም የሚል የጥገኝነት አቋም በማራመድ፣ “ከኔ በላይ በሃገሬ ጉዳይ ተጠሪ ላሳር” የሚል ጭፍንነት በመፈከር፣“ለእኔ ካልተመቸኝ ለማንም አይመቸው” በሚል ግለሰባዊነት ወይም የጥቂት ቡድናዊነት ስሜት የጋራ ሃገራዊ ጉዳይን መያዢያ በማድረግና “ትጥቁና ስንቁ የኔ ስለሆነ” የሚነቀንቀኝ የለም በሚሉ የግብዝነት አባዜዎች እድሜያቸውን ያራዝማሉ፡፡

ግዙፍ መንግስት መመስረት የሚቻለው ወሳኝ በሆነ መልኩ የዜጎችን የባለቤትነትና ሁለንተናዊ አይተኬነት በማዳከም መንግስትን ማዕከል አድርጎ፣ሁሉም ነገር በገዢው ፓርቲና በአመራሮቹ ዛቢያ እንዲሽከረክር በማድረግ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በሃገራዊና በሕዝብ ሃብት ላይ የመወሰን ጉልበትን በተማከለ መንግስታዊ ስልጣን አማካኝነት በማያወላዳ መልኩ የመቆጣጠር እድልን ይሰጣል፡፡ ይህንን ለመተግበር እንደ መሬት ካሉ የተፈጥሮ ሃብቶች ጀምሮ በዜጎች ቁጥጥር ስር የሚገኙ የግል ሃብቶችን እንዲሁም የጋራና የማህበራዊ እሴት መገለጫና ውጤት የሆኑትን እንደ እድር ያሉ ማህበራት ጭምር በሕገ-መንግስታዊ ሽፋን የመንግስት ተጠሪ ማድረግ ያስፈልግል፡፡

˝ልማታዊ መንግስት በስልጣን ላይ ለረጅም ጊዜ ለመቆየት የሚችለው፣ በልማት ስም በተፈጥሮ ሃብትና በግለሰቦች ሃብት ላይ የማዘዝ አቅምን በማጎልበትና በመንግስት እጅ በማከማቸት ላይ ሲመሰረት ነው፡፡˝ እንዲህ ያለው የግለሰቦችን ሃብት ለሕዝብና ለሃገር ልማት በሚል ሰበብ የመቆጣጠር ስልት በበርካታ ልማታዊ ነን በሚሉ የአፍሪካ ሃገሮች ግንባር ቀደም ፍልስፍና እየሆነ መጥቷል፡፡

ልማታዊ መንግስታት በዚህ ስልት በመጠቀም መንግስትና ሃገርን ለዘለቄታው እንዳይፋቱ አድርገው በማቆላለፍ፤የማይታደስና የማይለዋወጥ ጥገኝነት እንዲፈጠር አድርገዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የ“ልማታዊ መንግስታቱ” ስርዓት ከዴሞክራሲያዊ አስተዳደርነት ይልቅ ስልጡን የአገዛዝ ስልት ሆኗል፡፡ መንግስታዊ ተቋማቱን የሚመሩት ግለሰቦች ደግሞ ራሳቸውን የልማቱ አይተኬ ሃይልና ልዩ አንቀሳቃሽ ሞተር አድርገው በመቁጠራቸው፤በአኗኗራቸው ከቀሪው ተራ ዜጋ ፍጹም የተራራቁትን የ17ኛና 18ኛው ክፍለ ዘመን ኑቮ አሪስቶክራቶችን ሚና ተክተዋል፡፡ የቢሮአቸው ዘመናዊነት፣የሚጓጓዙበት ተሽከርካሪ ውድነትና ግዙፍነት፣የሚዝናኑበት ሁኔታ፣እንዲሁም የሚለብሱትና የሚጫሙት ሁሉ የተጠቀሰውን ሚናቸውን በቅጡ የሚያሳይ ሆኗል፡፡ ይህ ሁሉ እንግዲህ ለልማቱ ሲባል የሚፈጸም ነው፡፡ ያለነሱ ልማቱ፤ ያለልማቱ እነሱ አይኖሩምና፡፡

ይህንን ፍጹማዊነት የተላበሰና መንግስታዊ የበላይነት የሰፈነበት ስርዓት ቀጣይነት ማረጋገጥ ይቻል ዘንድ የመንግስትን ሚናና አይተኬነቱን የሚያጎሉ ስራዎችን መስራት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ የሚመቸውም በሁሉም ዘርፍ የተከፋፋለ ሕዝብ ነው፡፡ የተከፋፈለ ልብ ያለው ሕዝብ ለመፍጠር ደግሞ ልዩነቶችንና ተቃርኖዎችን መፈብረክና ማጋነን እንዲሁም ማራገብ የግድ ይላል፡፡ በነጋዴው፣ በምሁሩ፣ በአርሶ አደሩ፣ በሸቃዩ፣ በአምራቹ፣ በአስመጭው ወዘተ መካከል ውጥረትን በማንገስና እርስ በእርሱ በጥርጣሬ እንዲተያይ በማድረግ ዜጎችን ለአገልጋይነት ማመቻቸት የተፈለገውን ዓላማ ለማሳካት አንዱ ስልት ነው፡፡ የአቅርቦትና የእጥረት ችግር በተፈጠረ ቁጥር የእጥረቱን መንስኤ ተከታትሎ ከማከም ይልቅ ጣትን ነጋዴው ላይ በመቀሰር ዜጎች ነጋዴውን በጥርጣሬ እንዲያዩት በመገናኛ ብዙሃን ማውገዝ የተለመደ ነው፡፡ የትራንስፖርት ችግር፣ የመብራት፣ የኢንተርኔትና የስልክ መቆራረጥ በተከሰቱ ቁጥር በሌሎች ወገኖች ላይ ማላከክ በእጅጉ የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡ መሰረታዊ ችግሩ ያለው በመንግስታዊ ተቋማት ዘንድ ቢሆንም ልማታዊ መንግስት ስሙ በክፉ እንዲነሳ አይፈለግም፡፡ ስለዚህም ከየትም ተብሎ ማሳበቢያዎች ይፈለግለታል፡፡ ስግብግብ ነጋዴ፣የአጠቃቀም ችግር ያለበት ተጠቃሚ፣ ኪራይ ሰብሳቢ፣ ትምክህተኛ ምሁር፣ አክራሪ ወዘተርፈ ሰበቦች ይፈጠሩና ልማታዊ መንግስቱ ከወቀሳና ከትችት ያመልጣል ማለት ነው፡፡

ድሃና ኋላ ቀር ሃገር ውስጥ ለልማቱም ለአስፈጻሚውም ለተስፈኛውም የሚሆን በቂ ሃብት ስለሌለ ግዙፍ መንግስት ለመፍጠር ዜጎች ጉርድ መሆን አለባቸው፡፡ እናም እያንዳንዱ ባለሃብት፣ኢንቨስተር ወይም ቋሚ ገቢ ያለው ዜጋ ለስራ እድል ፈጠራ፣ ለፓርቲ ማጠናከርያ፣ ለምርጫ፣ ለስታድየምና ለሆስፒታል ግንባታ እየተባለ ማብቂያ የሌለው መዋጮና “የእናት ሃገር ጥሪ” ይገብራል፡፡ ድሃ ይበላው እንጂ ይገብረው አጥቶ አያውቅም እንዲሉ፡፡ ይህን አልፈፅምም ብሎ ሁሉ በእጁ ሁሉ በደጁ ከሆነ ልማታዊ መንግስት ጋር የሚጋፈጥ በአፍራሽነት ወይም በጸረ ልማታዊነት…. የመፈረጅና በጥርጣሬ የመታየት ዕዳ ይጣልበታል፡፡ የልማቱም ሆነ ያልተጠቀሙና ያላደጉ ክልሎች እንቅፋት ከሚል ታርጋ ለማምለጥ የተጠየቁትን መገበር ለባለሃብትም ሆነ ለዜጎች (ለጊዜውም ቢሆን) እንደ ብልህነት የሚቆጠር ይሆናል፡፡

ሊብራል ዴሞክራቶች የግለሰብ ሃብትን የምንገነዘበው ከአብዮታዊ ዴሞክራቶችና ከዘመናችን “ልማታዊ መንግስታት” ፈፅሞ በተለየ መንገድ ነው፡፡ ስለ ሃብት ፈጠራና ስለዜጎች እኩልነት ስናስብ፣ ሃብት የማከፋፈልን መንገድ እንደአማራጭ አንመለከትም፡፡ ይልቁንም በመጀመርያ ለባለሃብቱ ሃብት እውቅናና ጥበቃ በመስጠት እምነትና መነቃቃትን መፍጠር፣ ከዚያም በተመቻቸ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ አማካኝነት ሃገራዊና የግል ሃብቱን በማሳደግ የስራ እድልን እንዲያስፋፋና አስተማማኝ የመንግስት የገቢ ምንጭ እንዲሆን ማገዝ ነው፡፡
በኛ እምነት የትም ሃገር ላይ ለሚኖሩ ዜጎችም ሆነ ባለሃብቶች፣ሃብት የማፍራት ስራ ከባድና ፈታኝ ተግባር ነው፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራቶችና የዘመናችን “ልማታዊ መንግስታት” እንደሚያስቡት ሃብት ማፍራት ቀላል ስራ ቢሆን ኖሮ፣ መበልፀግን የሚጠላ የሰው ዘር ስለሌለ የዓለም ሕዝቦች ሁሉ ከዳር እስከዳር በበለፀጉ ነበር፡፡ ነገር ግን የተፈጥሮና የኢኮኖሚክስ ጉዳይ በመሆኑ እያንዳንዳችን እንደ መክሊታችንና ተፈጥሮ እንደቸረችን አቅም መኖር የግድ ይለናል፡፡ ልማታዊ መንግስታት ይሄን እውነታ በመካድ ሃብት ያላቸው ሃብታቸውን እንዲያሳድጉ፣የሌላቸው ደግሞ ሃብት እንዲያፈሩ፣የሚያሰሩና የተመቻቹ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ ለእድገት መሰረት የሆነውን የግለሰብ ሃብት ማከፋፈል የመረጡት መንገድ ሆኗል፡፡ ይህ ደግሞ በሂደት ተያይዞ ገደል መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ልማታዊ መንግስታትን ዘመናዊ ሶሻሊስት የሚያደርጋቸውም ይኸው ሃብት የማከፋፈል ዝንባሌያቸው ነው፡፡ ሶሻሊዝም ሁሉንም ወርሶ ድሃ በማድረግ፣የወረሰውን ሃብት አጣጥሞ ከጨረሰ በኋላ ድህነትን ለሁሉም በማከፋፈል የተሳካለት ሥርዓት እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ “ልማታዊ መንግስታት”ም ሃብትን ከመፍጠርና ከመውረስ ይልቅ ማከፋፋልን መርጠዋል፡፡ ያለውን ሃብት አከፋፍለው ከጨረሱ በኋላስ? ጉዳቸውን ወደፊት እናይላቸው ይሆናል፡፡

እጅግ ከፍተኛ በሆነ ድህነትና ኋላ ቀርነት ውስጥ በሚዳክሩ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሃገሮች ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ሃብት ማፍራት የሚችሉት ከባድ ውጣ ውረድን ተቋቁመው፣ አስቸጋሪ ሂደቶችንና ፈተናዎችን አልፈው እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ በበርካታ የበለጸጉ ሃገሮች ከመንግስት፣ ከተቋማቱና ከአስፈጻሚዎቹ ይልቅ ግለሰብ ዜጎች ከባድና አስቸጋሪ የሆነውን ውጣ ውረድ ተቋቁመው የሚፈጥሩት ሃብት፣ለሃገር እርሾ እየሆነ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ሲለውጥና ሲታደግ፣ መንግስት በበኩሉ የግብር ከፋዩን መሰረት በማጠናከር የመንገድ፣የስልክና የውሃ አቅርቦትን የሚያጎለብቱ የመሰረተ ልማት አውታሮችን በመዘርጋት ትርጉም ያለው ኢኮኖሚያዊ ልማትና እድገት እውን በማድረግ ዓይነተኛ ሚና ሲጫወት ማየት የተለመደ ነው፡፡

እንደ አለመታደል ሆኖ ይህ እውነታ በኛ ሃገር ውስጥ ለዘመናት ተግባራዊ ሲሆን ለማየት አልቻልንም፡፡ ኢትዮጵያውያን እጅግ ደብቶ ከያዘን ኢኮኖሚያዊ ድቀት እንዲሁም አንገታችንን ካስደፋን ድህነትና ኋላቀርነት ቀና በማለት በንግዱ፣ በግብርናውና በአገልግሎቱ ዘርፍ የተትረፈረፈ ምርት ማስመዝገብ በጀመርናባቸው በ1960ዎቹ ማብቂያ ላይ በድንገት የደረሰው ደርግ፣አግባብነት የነበረውን የመሬት ላራሹን ጥያቄ ከባለቤቶቹ ነጥቆ፣ በአናቱ ላይ ሁሉንም ዜጋ እኩል አደርጋለሁ ከሚል ኢ-ተፈጥሮአዊ አስተሳሰብ ጋር አዳቀለ፡፡ ቀጥሎም መኪና የነዳና የወፈረን ሁሉ ፊውዳልና ካፒታሊስት የሚል ታፔላ የሚለጥፉ ሃሳበ ድኩማንን በአብዮት ጠባቂነት በማሰማራት፣ለሃገሪቱ ኢኮኖሚ እርሾ ሊሆኑ ይችሉ የነበሩ ዜጎችን ሃብት በመውረስ እንዲሁም ያንገራገሩትን በማሰርና በመግደል የግል ዘርፉ እስካሁን ቀጭጮ እንዲቀር ምክንያት ሆኗል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም ለግል ዘርፉ አስፈላጊ የሆኑ የካፒታል፣ የሰው ሃይልና የምርት መሳርያዎችን ጨምሮ ኢንተርፕረንርሺፕ፣ ፈጠራ፣ ክህሎት፣ የስራ ተነሳሽነትና ምርታማነት ይኸው እስከዛሬም ድረስ እንደጠፉ ቀርተዋል፡፡ በእርግጥ የደርግ መንግስት በጊዜው የነደፈውን ሃገሪቱን የኋላቀሮችና የድሆች አገር የማድረግ እቅድ ካሰበውም በላይ አሳክቷል፡፡

እንደደርግ ባሉ ለቡድን መብት ቆመናል በሚሉ ስርዓቶች፣ ግለሰቦች ለብዙሃን ጥቅም ሲባል መሰደድ፣ሃብታቸውን መነጠቅ፣ በግፍ መገደል፤ ፈለጉም አልፈለጉም፤ ወደዱም ጠሉም በርዕዮተዓለም መታቀፍ ግዴታቸው ነው፡፡ በደርግ ስርዓት ከዚህ ያፈነገጡ ሁሉ እንደ ዘመናዊው ልማታዊ መንግስት እጣ ፈንታቸው መገለልና መገፋት ብቻ ሳይሆን መራራውን ሞት መጎንጨትም ጭምር ነበር፡፡

አብዮታዊ ዴሞክራሲ ከደርግ ተግባርም ሆነ አስተሳሰብ እጅግ የራቀ ቢሆንም ሶሻሊስት ዘመም ለመሆኑ በማረጋገጫነት ሊነሱ የሚችሉ በርካታ የትጥቅ ትግሉ ቅሪቶች በውስጡ እንዳዘለ ግን ራሳቸው አብዮታዊ ዴሞክራቶቹም ቢሆኑ አሌ አይሉትም፡፡ በመሬት ይዞታ ላይ ያላቸው አቋም፣ የግለሰቦችን ሃብት በተጽእኖቸው ስር በማድረግና በመቆጣጠር ለብዙሃኑ እናከፋፈል ማለታቸው፤ በተለይ ደግሞ የግል ዘርፉን ለመንግስት ቦታ እንዲለቅ በማድረግ ግዙፍ መንግስት ለመመስረት ያላቸው እቅድና የግል ክፍለ ኢኮኖሚውን አቅም በማሟጠጥ ማዳከማቸው ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በፖለቲካው መስመርም ተቃዋሚ ኖረም አልኖረም ፋይዳ የለውም፤እኛ ካለን ይበቃል እስከማለት መድረሳቸውና በምርጫ 99.6 ፐርሰንት እንደነሱ ስሌት “ማሸነፋቸው˝፤ በተለይ ለተመረጠ አንድ መደብ “ለአርሶ አደሩ ዘብ ቆመናል” ማለታቸው በጥቂቱም ቢሆን የሶሻሊስት ዘመም ዝንባሌያቸው መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በበርካታ ልማታዊ ነን በሚሉና ሶሻሊስት ዘመም በሆኑ ግዙፍ መንግስታት ዘንድ የዜጎች ሉአላዊነት ምልዑ በሚመስል መልኩ በሕገ-መንግስታቸው ውስጥ የመካተት እድል ቢያገኝም ወደ ተግባር ሲገባ ግን የግለሰቦች ኢኮኖሚያዊም ሆነ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው በሁለተኛ ደረጃ ሲቀመጡ ማየት ወይም የብዙ ነገሮች ተቀጥላ ሆነው ሲመነዘሩ መከታተል የተለመደ ነው፡፡

ለማንኛውም የግልም ሆነ ለቡድን መብት ጥያቄ ግዴለሽ የነበረውና ቅጥ አምባሩ የጠፋው የደርግ ሶሻሊዝም፤በከፍተኛ መስዋእትነት በኢህአዴግ መራሹ ትግል ከተሸነፈ በኋላ ሶሻሊስት ዘመም ወደ ሆነው “አገር በቀል” የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር ተሸጋግረናል፡፡ በተለይ ከኢኮኖሚ መብቶች አኳያ ከላይ በሰፊው የገለፅኩት እንደተጠበቀ ሆኖ፤አብዮታዊ ዴሞክራሲ በሌላው የግዙፍ መንግስትነት ገጽታው የቡድን መብትን አማክሎ የተመሰረተ ፍልስፍና መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህም ሆኖ በተለይ ቆሜላቸዋለሁ ከሚላቸው የብዙሃን ብሄር ብሄረሰቦች ኢኮኖሚያዊና የፖለቲካ ስልጣን ባለቤትነት ጥያቄ በሂደት እያፈገፈገ፤ አሁን አሁን በመደብ ደረጃ ታማኝነቱን አረጋግጦልኛል ወይም ለግዙፍ መንግስትነቴ በቁጥር ደረጃ ተመችቶኛል ለሚለው ለአርሶ አደሩ መደብ ቅድሚያ ሰጥቶ ዘብ እየቆመ ያለ ድርጅት እንደሆነ በፖለቲካ ፕሮግራሙና በተግባር ከሚፈጽመው ድርጊት መረዳት ይቻላል፡፡

በኢህአዴግ ስድስተኛው ኮንግረስ ላይ አብዮታዊ ዴሞክራቶች አሻሽለው ባቀረቡት የፓርቲያቸው የፖለቲካ ፕሮግራም፤ ገጽ 6 መግቢያ በሚለው ርዕስ ስር ተራ ቁጥር 14 ላይ በጥቅል የቀረበው ሃሳብ ሰለሶስት መደቦች ይተነትናል፡፡

“Our Front is fundamentally an organization of the peasantry which is the main force behind revolutionary democracy. In consequence, to rally the peasantry around our objectives is the first and foremost task of our struggle. The broad masses in urban areas, workers, intellectuals, low- income earners of our society are also our allies and supporters. We shall, therefore, try hard to mobilize the urban populace to march forward with us. Private entrepreneurs engaged in real development also play a special (vital) role in our development endeavor. We shall struggle so that they do not succumb to parasitic mentality and instead become our partners in the development endeavors.”

ከፓርቲው ፕሮግራም ተቀድተው እንዲደምቁ የተደረጉት ሃሳቦች እንደሚያስተጋቡት፤ ለአብዮታዊ ዴሞክራቶች አንደኛ ተጠሪ መደብና የፓርቲው የግንባር ስጋ (Vanguard) ተደርጎ የተወሰደው እንደተለመደው ብሔር ብሔረሰቦች ሳይሆኑ አርሶ አደሩ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የጋራ ሃገራችን ብትሆንም አርሶ አደሩ አቅም በፈቀደ ሁሉ ከየትኛውም ዜጋ በላይ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ዜጋ እንደሆነ ፕሮግራሙ ይገልጻል፡፡ (ግን አርሶ አደሩስ ቢሆን እውነት ተጠቃሚ ሆኗል?) በመቀጠል የተጠቀሰው ደግሞ በጥርጣሬ የሚታየው ሰፊው የከተማ ነዋሪ ሲሆን (ምሁሩ፣ ሰራተኛው፣ ዝቅተኛ ገቢ ያለው የከተማ ነዋሪ የመሳሰሉት…) ይህንን መደብ የሃገሩና የራሱ ጉዳይ ባለቤት ሳይሆን የአርሶ አደሩ አጋርና ተቀጥላ በማድረግ በሌላውና ጥገኛው ወይም በኢህአዴግ አባባል ኪራይ ሰብሳቢ በሚባለውና በግልጽ ማን እንደሆነ በማይታወቀው መደብ ላይ በማነሳሳት ከአርሶ አደሩ መደብ ጋር አብሮ ይተም ዘንድ የሚቻለውን ጥረት እንደሚያደርግ ፓርቲው ይገልጻል፡፡ በሶስተኛ ደረጃ የቀረበው መደብ የግል ዘርፉ ኢንተርፕረነር ሲሆን ይህ መደብ ለልማቱ አስፈላጊ ሚና እንዲሚኖረው ድርጅቱ ያምናል፡፡ ይህም ሆኖ መዝጊያው ላይ እንደተቀመጠው ግን በጥገኝነት (parasitic) ስለሚጠረጠር ከዚህ ዝንባሌው እንዲላቀቅና የልማቱ አጋር እንዲሆን ማንኛውንም ጥረት እንደሚያደርግ ይገልፃል፡፡

በአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ውስጥ የግለሰብ መብት የቡድን መብት ተቀጥላ ሆኖ መሰለፉ ሳያንሰው የግዙፍ መንግስት መገለጫ የሆነው “ለሕዝብ ጥቅም መቆም” የሚለው የተለመደ ማደናገርያ ታክሎበት፤ዜጎችን ከማይሸረሸር የግለሰብ መብት ይልቅ በቡድናዊ ስሜት ከፋፍሎ ለስልጣኑ ማራዘሚያነት በሚያመቻች መልኩ በተቃርኖ ውስጥ አጉሯቸው እናገኘዋለን፡፡ በዚህም ግለሰቦች በግል ጥረታቸው ያፈሩት ሃብትና በተፈጥሮ ያገኙት ሰብእና፤ ዴሞክራሲዊ ነጻነትና መብታቸቸው እንዲከበር እንዳይጠይቁ ሆነው በድጋሚ ተከፋፍለዋል፡፡ ዛሬ ዜጎች የራሳቸው ሕይወት የሌላቸው ይመስል ጥያቄዎቻቸው ከልማቱና በቁጥር ከሚልቁት ጥቅም አኳያ ድፍን የሆነ አቅጣጫ ተቀምጦላቸው መተንተናቸው ነገና ከነገ ወዲያ በደቦ እየተመዘኑና ከቁጥር ውጭ የሚገልፃቸው ነገር እየጠፋ፤ ስለራስና ስለቤተሰብ የሚያስብ ሁሉ ላለመገለሉ አንዳችም ማረጋገጫ አይኖርም፡፡

በተለይ ደግሞ ኪራይ ሰብሳቢና ልማታዊ የሚሉት ቅርጫቶች ሁሉንም ለማሸማቀቅ እንዲመቹ ተደርገው ስለተቀረጹ “ለልማቱና ለሕዝብ ጥቅም” እስካልተመቸ ድረስ በአማራጭነት ሃሳብን ለማስረዳት እድል ሳይኖር፤ ማናችንንም ጠራርገው ሊወስዱ የሚችሉ ጎርፍ ናቸው፡፡

ግለሰቦች የቡድኖች ተቀጥላ እንጂ በራሳችሁ ሙሉ አይደላችሁም የሚለው ትንታኔ፤ ግለሰቦች ለኢኮኖሚያዊ መብታቸውም ሆነ ለአስተሳሰብ ነጻነታቸው ዘብ መቆም እንዳይችሉ ማነቆ ነው፡፡

እስከዛሬ የብሔር ብሔረሰቦች የመብት ጥያቄ የግለሰብ የመብት ጥያቄ አካልና መገለጫ ከመሆን ይልቅ የብሄር ብሄረሰብን የቡድን መብት ጥያቄ እንደሚጻረር ተደርጎ ሲቀርብ ኖሮ፤ ዛሬ የብሄር ብሄረሰብ ጉዳይ ተራውን በቁጥር ለሚልቀው ለአርሶ አደር መልቀቁ የቀደመው ሂደቱ እጅግ የሰለጠነ ማደናገርያ እንደነበር በቅጡ ያሳያል፡፡

የብሄር ብሔረሰቦችም ጥያቄ ውሎ አድሮ በመጨረሻ የአርሶ አደሩ መደብ ተቀጥላ መሆኑ እንደማይቀር ከላይ የቀረቡት ምሳሌዎች በግልጽ ያሳያሉ፡፡ የመብት ጉዳይ በቁጥርና በስሌት ውስጥ ሲወድቅ፤ ቁጥርና ስሌቶች ሁሌም ለሚበልጠው ዘብ መቆማቸው የተለመደ በመሆኑ ብሄር ብሄረሰቦችም ከዚህ የቁጥር ስሌት ውጭ መብታቸውን የሚያረጋግጡበትን የግለሰብ መብት መከበር አጥብቀው ካልያዙ ሂደቱ ወዴት ሊገፋቸው እንደሚችል ለመተንበይ አዳጋች ነው፡፡ በዚህ መልኩ ከቀጠሉም በብዝህነታቸው ያገኙት መብት ምንጩ ቁጥር እንደመሆኑ መጠን፤ በሂደት የተለያየ ስሌትን በመጠቀም ከነሱ በቁጥር ለሚበልጠው መደብ ተቀጥላ ሊሆኑ እንደሚችሉ ሊረዱት ይገባል፡፡

ብሄር ብሄረሰቦች ቁንጽል ከሆነው የቡድን ተቀጥላነት ውጭ የላቀ መገለጫ የሌላቸው ይመስል የቡድን መብት በሚል ጥቅል የመብት ጥላ ስር ለግዙፍ መንግስት ከለላነት እንዲሰለፉ መደረጉ በግለሰብና በቡድን መብት መካከል ፍትጊያና ሽኩቻ በመፍጠር ግልጽ የሆነ የመስመር ልዩነት እንዳይኖር መሰናክል ከመፍጠሩም በላይ ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት መብትን ለተረኛው ባለቁጥር ማስረከብን አይቀሬ ያደርገዋል፡፡

ከዚህ ድንግርግር ለመላቀቅ ብቸኛው መፍትኼ ግዙፍ መንግስት እራሱን ተአምራዊ ሃይል ለማስመሰል ጉርዶችን መፍጠሩን ማቆም አለበት፡፡

ሌላው በግዙፍነቱ የሚቆጣጠራቸውና እንደመሳርያ የሚጠቀምባቸው መሰረታዊ የሆኑ ኢኮኖሚያዊ የልማት አውታሮች እንደአስፈላጊነቱ በጋራ ሃብትነት በሼር ወይም በተናጥል በግልም እያለሙ ውድድር፣ጥራትና አቅርቦት የሚስፋፋበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት፡፡ ይህ ደግሞ ሊረጋገጥ የሚችለው የመንግስት ሚና ገዝፎ ከዜጎች በላይ በተንሰራፋበትና አልፎ ተርፎም ሃገራዊ ሃብትን በማከፋፈል ጥቂቶችን ነገር ግን ሃገራዊም ሆነ ግለሰባዊ ሃብት በመፍጠር ሂደት ሚና ያልነበራቸውን ሚሊዬነር በማድረግ፤የስርዓቱ ልዩ ተጠቃሚና ልዩ ጠባቂ በሚያደርገው በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፍልስፍና ውስጥ ሳይሆን የግለሰብ መብት በግልም ሆነ በተደራጀ መልኩ ሲቀርብ ከምንም በላይ በሚከበርበት በሊብራል ዴሞክራሲ ፍልስፍና ውስጥ ብቻ ነው፡፡

ሊብራል ዴሞክራሲ ኃብትን ከብዙሃኑ ላይ ተቀራምቶ በማሰባሰብ የተለየ መደብን ሚሊዬነር የማድረግ መንገድን አይከተልም፡፡ ሊብራል ዴሞክራሲ የዜጎችን ሃብት በመቀራመት ጥቂት ታማኝ ሚሊዬነሮችን ከመፍጠር ይልቅ፤ ሁሉም ዜጎች ሃገራቸው ባፈራችው ሃብት ላይ እኩል የመስራት፣ የመጠቀምና የመበልጸግ እድልን የሚያመቻች አቅጣጫን የሚቀይስ አስተሳሰብ ነው፡፡

የሊብራል ዴሞክራሲ ትሩፋቶች በሚፈጠረው እድገትና ልማት አማካኝነትም አብዛኛዎቹ ዜጎች እራሳቸውን እንዲችሉ ያደርጋል፡፡ ዜጎች ኢኮኖሚያዊ ልዩ ጥቅምን በጥገኝነት በመሻት መብትና ግዴታቸው የማይቀየድበት፤ሁሉም ዜጎች ተመጣጣኝ የገቢ አቅም ፈጥረው በፖለቲካዊም ሆነ በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የመወሰን ክህሎታቸውን ያለተጽእኖ የሚያዳብሩበት፣ መብትና ግዴታቸውን የሚያውቁበት፣ ጥቅማቸውን አሳልፈው የማይሰጡበትና የማይወናበዱበት መደላድል መፍጠር

Share