Logo

በሚያዚያ ወር የሚካሄደውን የአካባቢ ምርጫ አስመልክቶ ከኢዴፓ የተሰጠ መግልጫ

March 4, 2013

ይህ የዴሞክራሲ ትንሳኤ ድምጽ ከተሰጠበት ቀን ማግስት ጀምሮ በሁሉም ዘንድ መወያየትና መደማመጥ  ባለመቻሉ ሂደቱ ሊቀለበስ ችሏል፡፡ በድምጽ መስጠት፣ ቆጠራና ውጤት ገለጻ ሂደት በገዢው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የተፈጠረው ልዩነት ተቀራርቦ በመነጋገር ችግሮችን እየፈቱ ልዩነትን አጥብቦ ባልተፈቱ ችግሮች ዙርያ ሳይግባቡ ተግባባቶ በይደር ለመነጋገር ከመወሰን ይልቅ በእለቱ ውሳኔ ለማስወሰን እጅ ጥምዘዛ ውስጥ በመገባቱ ሃገርና ዜጎች በተለይ ደግሞ ጭል ጭል ሲል  የነበረውን ዴሞክራሲ አይከፍሉ ዋጋ አስከፍለውታል፡፡

በወቅቱ የተፈጠረውን ሕዝባዊ ተነሳሽነት ኢህአዴግ በስልጣን ላይ ለመቆየቱም ሆነ ከስልጣን ከወረደ በኃላ በሰላም ትግሉ ለመቀጥል ብቸኛው መተማመኛ መሆኑን መቀበል ባለመቻሉ ብልጭ ካደረገው አንጻራዊ ዴሞክራሲ ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ አፈግፍጓል፡፡ ተቃዋሚዎችም የተገኘውን ድል አጣጥመን በሕዝቡ ውስጥ የተፈጠረውን ተነሳሽነት በማጎልበት ለሌላ ድል ከመዘጋጀት ይልቅ ከመንግስትነት ውጭ ያለው አማራጭ ሁሉ ለመቀበል ባለማቻላችን ሁሉንም ለማጣት ተገደናል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ለማያበቃ መከፋፈል ተዳርገናል፡፡

ኢህአዴግ በመቀጠል በተደረጉት ተከታታይ ምርጫዎች ላይ ሕጋዊ የሆኑ መንገዶችን ብቻ በመጠቀም ምርጫዎችን ሊያሸንፍ የሚችልበት እድል ሰፊ ቢሆንም ከሕግም ሆነ ከዴሞክራሲያዊ መስፈርት አኳያ ያልተገቡ ድርጊቶችን በመፈጸም ምህዳር በማጥበብ፣ አማራጭ በማሳጣት፣ በማዋከብ፣ ከስራ በማፈናቀል፣ በማሰርና የሃገሪቱን አንጡራ ሃብት መደለያ በማድረግ ምርጫዎችን ሙሉ በሙሉ ከማሸነፍ ውጭ ዝቅተኛም ቢሆን የተቃዋሚን ተሳትፎ የማይፈቅድ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

የ2002 ዓ.ም ምርጫ የተካሄደው በዚህ ፍጹም ሚዛናዊነት በጎደለውና ውድድር አልባ በሆነ መንፈስ ውስጥ ነበር፡፡ በዚሁ ሃገራዊ ምርጫ ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን በቅድሚያ መገምግም የቻለው ኢዴፓ በምርጫው አንዳችም ቅድመ ሁኔታ ሳያስቀምጥ የተፈጠሩ እድሉችንና ክፍተቶችን አሳልፎ ላለመስጠት ካለው ጽኑ እምነት በመነጨ በምርጫው ከአራት መቶ ሃምሳ በላይ እጩዎችን ለተወካዩች ምክር ቤት በማቅረብ ተሳትፎል፡፡ ኢዴፓ ምርጫን የሚለካው ውጤት አስፈላጊ ቢሆንም በሚገኘው ውጤት ብቻ ሳይሆን በዜጎች ንቁ ተሳትፎና ከተሳትፎው በሚገኝው ተመክሮ ላይ ተመስርተው ችግሮቻቸውን በማረም የተሻለ አቅምና ብቃት ያላቸው ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን በመፍጠር ዴሞክራሲያዊ መደላድልን መፍጠር ስለሚቻል ጭምር ነው የሚል ጽኑ እምነት ስለነበረው ጭምር ነው፡፡

በምርጫ ሂደት የሚፈጠሩ ሕጸጾችን ለማረም የሚያግዝ የመወያየት እድል ጠባብም ቢሆንም ሙሉ ለሙሉ እስካልተዘጋ ድረስ ቅደመ ሁኔታ በማስቀመጥ ከምርጫ ሂደት እራስን ከማግለል ይልቅ በምርጫው ሂደት እያተሳተፉ የምርጫ ቦርድን ፍትሀዊነትንና ሚዛናዊነት የጎደለው አሰራረር፣ የመገናኛ ብዙሃን ጭፍን ክልከላ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎችን ገለልተኛነት እና ኢህአዴግ ያሰማራቸውን የምርጫ ሰራዊቶች መታገል ይቻላል የሚል እምነት አለን፡፡ ለአማራጭ አስተሳሳብ፣ ለመተራረምና ለሕጋዊነት ቅድሚያ የመስጠት በመርህ ላይ ከተመሰረተ አሰራራችን በመነሳትና አሁንም ለመርህና ለሕጋዊነት ካለን ጽኑ እምነት በመነጨ ተነሳሽነት ወደ ምርጫው ገብተን ነበር፡፡ ሆኖም ግን የምርጫ ሂደቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከመሻሻል ይልቅ ምርጫ ቦርድም ሆነ ኢህአዴግ ነጻ፣ ገለልተኛና ተአማኒነት ያለው ምርጫ ከማድረግ ይልቅ ወደኃላ በማፈግፈጋቸው የምርጫ ሂደቱ ሚዛናዊነት በመዛባቱና የውድድር መንፈሱን ፍጹም እያጣ በመምጣቱ ቆም ብለን ሂደቱን ለመገምገም ተገደናል፡፡

ለምርጫ ስርዓት፣ ለሕግና ለመርህ ተገዢ መሆን ማለት ግን ውጤቱ ቀድሞ በታወቀበት፣ የተቃዋሚዎች ሚና ትርጉም አልባ እንደሆነ በሚሰበክበት፣ ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበትን ጨምሮ ትርጉም የሌለው የሞራል ዋጋ በሚከፈልበት ምርጫ ለተሳትፎ ስንል ብቻ በሂደቱ እንቀጥላለን ማለት እንዳልሆነ ለማንም ሃይል ግልጽ ሊሆን ይገባዋል፡፡

ኢዴፓ በሚያዚያ ወር በሚካሄደው የአካባቢ ምርጫ በሚታወቁ የምርጫ ቦርድና የመንግስታዊ መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም በምርጫ አስጻሚዎች የተወቁ ችግሮች ውስጥ ሆኖም በሙሉ አቅሙ በምርጫው ለመሳተፍ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ በዚህ ዝግጅትም ለአዲስ አበባ ምክር ቤት የሚወዳደሩ እጨዎችን መልምሎ የአቅም ማዳበርያ ስልጠና በየሳምንቱ ሲሲጥ የቆየ ሲሆን በጋራ ፖለቲካ ፓርቲዎች መድረክ አማካኝነት የምርጨውን ሂደቱን ነጻነትን ገለልተኛነት ለመከታተል በሁሉም ክፍለ ከተማዎች በተቋቋሙት  ኮሚቴዎች አማካኝነት በተሟሉ አባላት ተሳትፏል፡፡ ከአዲስ አበባ ውጭ በሚካሄዱ የአካባቢ ምክር ቤቶች ምርጫም  በባህርዳር፣ በጎንድር፣ በወሎ፣ በላሊበላ፣ በትግራይ፣ በደብረማርቆስ፣ በወላይታ፣ በአለታወንዶ፣ በሃረር፣ በድሬደዋ፣ በአርባምንጭ፣ በአዳማ በአብዛኛዎቹ ወረዳዎችና  በምዕራብና ምስራቅ ጎጃም፣ በዳውሮ ዞን፣ በምዕራብ አርሲ ዞን፣ በአዳማና በቸሃ ወረዳና አካባቢዎቹ በከፊል እጩ የማወዳደር ዝግጅቱን አጠናቆ ነበር፡፡

ኢዴፓ ምክንያታዊም ሆነም ኢ-ምክንያታዊ የሆኑ ሕጸጾች ባሉበት ሁኔታም ቢሆን በምርጫ መሳተፍ ለድርድር የማይቀርብ አጀንዳው ሆኖ የቆየ ነው፡፡ ነገር ግን ከህዝብ፣ ከፓርቲው አባላትና ከደጋፊዎቹ የቀረቡለት የምርጫ ህጸጾች ምርጫውን ትርጉም አልባ የሚያደርጉት ከመሆናቸውም በላይ የውድድር መንፈስ ያልተላበሰና በአሰራር ሂደትም ይህ ቀረሽ የማይባል ቸልተኝነትና ምንቸገረኝነት የተስተዋለበት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

ለዚህም በመረጃነት የሚቀርቡት፡-

1)       በመራጩና በተመራጩ መካከል ድልድይ ሆነው አማራጭ የማቅረብ እድልን ትርጉም የሚሰጡት የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን የሚተካ ሚና እንደሌላቸው እየታወቀ ጉዳዩ ለውይይት ቀርቦ መፍትሔ እንዲያገኝ የተደረገው ጥረት በተለያየ ምክንያት ተደናቅፏል፡፡

2)     የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ሕግን ተከትሎ በምርጫ ቦርድ በተደነገገው ደንብ ቁጥር5/2001ና በሕገ-መንግስት መሰረት አዲስ አበባ የፌደራላዊ መንግስት አካል ሆኖ በሃገራዊ የምርጫ ሂደቱ ውስጥ ተካቶ በተደጋጋሚ የምርጫ ፋይናንስና ድጋፍ እንደተሰጠው ቢታወቅም ለዚህ ምርጫ ድጋፍ እንዳይኖር ተደርጓል፡፡

3)     መራጩ ሕዝብ በሕገ መንግስቱ ከተረጋገጠው በፍላጎቱ የመምረጥና የመመረጥ እንዲሁም በምርጫ የመሳተፍ መብቱን በመጣስ ተጽእኖና አስገዳጅ ሁኔታ በተቀላቀለበት መንገድ በር ለበር በተካሄደ ዘመቻ የምርጫ ካርድ ተሰራጭቷል፡፡ በሚስጥር የመምረጥ መብቱን በሚጋፋ መልኩ ማንነቱ የተጋለጠ ሆኖ እንዲሰማውና እንዲሸማቀቅ ተደርጓል፡፡

4)     በምርጫ ጣቢያዎች የተደረጉ ምዝገባዎችና የምርጫ ካርድ ማደል ስራዎች በምርጫ ህጉ መሰረት የነዋሪነት መታወቂያ ሳይጠየቅና ተመዝጋቢው ማንነቱ ሳይረጋገጥ የተከናወኑ በመሆኑ ኢህአዴግ ደጋግሞ የመምረጫ ካርድ  ለመውስድ የተጋለጠ ሆኗል ፡፡

5)     በምርጫ ጣቢያዎች የተመደቡ አስፈጻሚዎች የኢህአዴግ አባልና በተለይ እንደ ወረዳ ባሉ አነስተኛ መንግስታዊ መዋቅሮች ውስጥ በልማታዊ ሰራዊትነት የተደራጁ አባላት ከመሆናቸውም በላይ ገለልተኝነታቸውን የሚረጋግጡ ቅጾችን ያልሞሉ መሆኑን ለመታዘብ ችለናል፡፡

6)     የምርጫ ጣቢዎች እጅግ የተቀራረቡ ወይም እጅግ የተራራቁ በመሆናቸው ለክትትል፣ ለምዝገባም ሆነ ለመምረጥ የማይመቹ ሆነዋል፡፡

7)     ኢህአዴግ በበርካታ የምርጫ ጣቢያዎች ፈቃደኝነታቸው ሳይረጋገጥና አንዳንዶቹም ከአባልነት የለቀቁ መሆኑ እየታወቀ፤ እጩዎቹ በግንባር ምርጫ ጣቢያ ሳይቀርቡ በደብዳቤና በትዕዛዝ ስም ዝርዘር ብቻ እየተላከ እንዲመዘገቡ ተደርጓል፡፡

8)     ከኢህአዴግ አባልነት የለቀቁና በምርጫ መሳተፍ የማይፈልጉ ግለሰቦች እጩ ናችሁ የሚል ማዘዢያ እየደረሳቸው በግዳጅ እጩነት እንደተመዘገቡ ጥቆማ ደርሶናል፡፡

9)     በተደጋጋሚ ስጋታችንን እንደገለጽነው ኢህአዴግ በመንግስት ወጪና አወቃቀር ያደራጃቸው የልማት ሰራዊቶች ወደ ምርጫ ሰራዊትነት በመለወጥ በእጩዎች፣ በመራጩ ሕዝብና በደጋፊዎች ላይ ከፍተኛ ወከባ ማካሄዳቸውን ለመታዘብ ችለናል፡፡

10)   በተደጋጋሚ በምርጫ ሂደት ችግር ፈጥረዋል የተባሉ የምርጫ አስፈጻሚዎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ገለልተኛነታቸውን ባላረጋገጡላቸውና የሁሉንም ይሁንታ ባላገኙ አስፈጻሚዎች እንዲተኩ የቀረቡ በርካታ ጥያቄ በምርጫ ቦርድ በኩል እስካሁን መልስ አላገኙም፡፡

ከነዚህ መሰረታዊ የምርጫ ሂደት ችግር በተጨማሪ በርካታ ህጸጾችን መዘርዘር ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ አንድ እጩ ለምርጫ የሚያስፈልግው ድጋፍ ባለመዘጋጀቱ  በቂ ፖስተር፣ ፍላየርስ፣ የተሸከርካሪ ቅስቀሳ ሳያደርግና በመገናኛ ብዙሃን የፖለቲካና የኢኮኖሚያዊ ፍልስፍናውን ሳያቀርብ፣ በቂ ታዛቢ ለማሰማራት ሳይችል ምርጫው ሚዛናዊና ውድድር ያለበት ነው ለማለት አይቻልም፡፡ በምርጫው የሚኖረን ተሳትፎ ውድድርና ሚዛናዊነት የጎደለው ውጤቱም ቀድሞ የታወቀ ከመሆኑም በላይ ከምርጫ ውጤት በኃላ በአባላት ላይ በተለያየ መንገድ ሊከሰት የሚችለውን ተጽእኖ ለማስቆም የሚቻልበት አንዳችም መንገድ የለም፡፡ ለምርጫ ስርዓትና ለህግ የበላይነት ሲባል በምርጫ  ተሳትፎ በማድረግ በተጽእኖ ስር ሆኖ ውጤቱን መቀበል ለዴሞክራሲ ማበብም ሆነ ለሰላም ትርጉም አይኖረውም፡፡

በኢዴፓ እምነት ይህ የአካባቢ ምርጫና የ2002 ሃገራዊ ምርጫ አጠቃላይ ሂደትና ውጤት ለዴሞክራሲና ለኢህአዴግ የማንቂያ ደውል ጥሪ እንደሆነ ያምናል፡፡  ኢህአዴግ እንደሚለው በምርጫዎች ላይ የተቃዋሚዎች ተሳትፎ  ትርጉም የማይሰጠው መሆኑን ደጋግሞ ከመግለጹም በላይ ውጤቱ ቀድሞ ከውድድር በፊት እየገለጸና የተቃዋሚዎች ሚና ትርፍና ኪሳራ የሌለው አድርጎ መግምገሙን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን መከታተላችን፤ በቀጣይ በ2007 ዓ.ም የሚካሄደው ሃገራዊ ምርጫ አያስፈልግም ወደሚል ሌላ አሳሳቢ ግምገማ እንዳይደረስ በዚህ አጋጣሚ ስጋታችንን ለማስቀመጥ እንወዳለን፡፡

የምርጫ ትርጉሙ የተሳትፎ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ወገን ዘንድ ውጤት የሚጠበቅበትና ፉክክር የሚደረግበት እንዲሆን ኢህአዴግ የመንግስትነት ሚናውን እንዲጫወት  እናሳስባለን፡፡ መንግስታዊ የሆኑት የዴሞክራሲ ተቋማትም ተቃዋሚዎችን እንዲያዋክቡና እንዲያዳክሙ ምክንያት እያቀበሉ የተቋቋሙበትን ዓላማ እንዲዘነጉና በተጻራሪው እንዲቆሙ ከማበረታታትና ከማገዝ ይልቅ ተቋማቱ ከገቡበት ማጥ እንዲወጡ እንደመንግስት ተገቢውን የእርምት እርምጃ በመውስድ ቀጣዮ የ2007 ሃገራዊ ምርጫ ነጻ፣ ገለልተኛና አሳታፊ፣ በሕዝብ ዘንድ ተአማኒነት ያለው እንዲሆን በድጋሚ እናሳስባለን፡፡

በመጨረሻም ኢዴፓ ከምርጫ ሳይወጡ በምርጫ ስርዓት ውስጥ ሆኖ ነጻና ገለልተኛ ምርጫ እንዲሰፍን ሁለናተናዊ ትግል ማድረግ ይቻላል ብሎ ያምናል፡፡ በዚህም ምክንያት ኢዴፓ ከህጋዊ መስፈርት አኳያ በዚህ ምርጫ ውስጥ በመርህ ደረጃ የሚገኝ መሆኑ እንደ ተጠበቀ ሆኖ ኢህአዴግ ለተቃዋሚው ትርጉም የሌለውና ውጤቱ እየታወቀ ባለው ምርጫ ውስጥ ያለውን ቀጣይ ተሳትፎ በአንድ እጩ  ደረጃ ብቻ የገደበ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ሰላምና ሕብረ ብሔራዊነት ዓላማችን ነው !!

የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ

የካቲት 1 ቀን 2005 ዓ.ም.

 

Source EDP

Share

2 comments on “በሚያዚያ ወር የሚካሄደውን የአካባቢ ምርጫ አስመልክቶ ከኢዴፓ የተሰጠ መግልጫ

Comments are closed