Logo

አማራጮች ያልቀረቡበት የዘንድሮ ምርጫ!

May 5, 2013

Mushe Semuከሙሼ ሰሙ

ምርጫዎች ቀን ቆጥረው ይመጣሉ፤ ውጤቱን እንዲለውጡ ግን አንፈልግም”

ሶሻሊስቶች ለህዝብ ጥቅም በሚል ሰበብ በሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚሹት በዲሞክራሲያዊ መንገድ አይደለም፡፡ በዚህም ሳቢያ ፍትሃዊ ምርጫ ማድረግ አይዋጥላቸውም፡፡ ተፈጥሯዊ ባህርያቸውም አይደለም፡፡ የእነሱ ዝነኛ ብሂል “የትም ፍጪው [ስልጣኑን] አምጭው” የሚል ነው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ በአገራችን በሚካሄዱ ምርጫዎች፣ ምርጫ ቦርድና አስፈጻሚዎቹ ለምርጫ ሕጎችና አሰራሮች አልፎ ተርፎም ለመርሆዎች ተገዢ አለመሆናቸውና ለጉዳዩ ትኩረት መንፈጋቸው ሳያንስ፣ ገዢው ፓርቲ በገሃድ “ተቃዋሚዎች መጡም አልመጡም ግድ የለንም” እስከማለት መድረሱ ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት ፈታኝ ጥያቄ ነው፡፡ የምርጫ ቦርድና የአስፈጻሚዎቹ ትኩረት፣ አማራጭ ሃሳቦች አብብው ሕዝብ በአማራጭ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖረው ማገዝ ሳይሆን እንደ ዓመታዊ በዓል ቀን ቆጥሮ ምርጫውን በማንኛውም ኪሳራ(At any cost) ውስጥ ማስፈፀም እየሆነ የመጣ ይመስላል ፡፡

ይህ አካሄድ የሚጠቁመን ነገር ቢኖር ከጊዜ ወደ ጊዜ ስር እየሰደደ የመጣው ሃቀኛ ዴሞክራሲ ሳይሆን የመንግስታዊ ከበርቴና የልማታዊ መንግስታት አስተሳሰብ መሰረት የሆነው የተምሳሌታዊ ዴሞክራሲ መሆኑን ነው፡፡ መጀመርያ ተቃዋሚዎችን ከነአቤቱታቸው በማስወገድ፣ ቀጥሎ በምርጫው አካሄድና ወግ አልባነት የተቆጣውን መራጭ ሕዝብ፣ ከቁጣው ለማብረድና እምነቱን በተጽእኖ ለማስለወጥ፣ ቤት ለቤት በሚያደርጉት መጠነ ሰፊ ፕሮፓጋንዳና ወከባ ማስጨነቃቸው፣ የፈለጉት የሕዝቡን “የይስሙላ ተሳትፎ” እንጂ ውጤት የማስለወጥ ሕጋዊ መብቱን እንዳልሆነ አይተናል፡፡ ልማታዊ መንግስታት፣ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የመሸነፍና የለውጥ ጥያቄ እንዲነሳባቸው አይፈቅዱም፡፡ ለዚህ ሲባልም የምርጫ ውድድር ቀንን ጠብቆ ምርጫ አለ ከማለትና ሕዝብ አማራጭ በሌለበት እንዲሳተፍ ከማዋከብ ውጭ ሌላ አማራጭ ሃሳብ እንዲጎለበትና እንዲያብብ እድል አይሰጡም፡፡

በእኛም አገር የገጠመን ይሄ ዓይነት ችግር ነው፡፡ የውይይትና ክርክር መድረኮች አሳታፊ፣ ሚዛናዊና ክፍት ሆነው ከውይይቱና ክርክሩ በሚገኙ ግብአቶች ላይ ተመርኩዞ፣ ሕዝብ ይሁንታውን እንዲሰጥ የሚያደርጉ ዴሞክራሲያዊ አሰራሮች ፈተና ገጥሟቸዋል፡፡ አሁን አሁን ደግሞ ምርጫ ቦርድና አስፈጻሚዎቹ ለመገናኛ ብዙሃን በሚሰጧቸው ዘገባዎች ላይ ማዳመጥ የጀመርነው ነገር ቢኖር፣ አማራጮች ይበቁናል ወይም ከዚህ በላይ አያስፈልጉም ፤ የሚሉ ሆነዋል፡፡ ይህ እንግዲህ በዘመናዊ አባባል ፤ ምርጫዎች ቀን ቆጥረው ይመጣሉ፤ ውጤቶቹን እንዲለውጡ ግን አንፈልግም፡፡ መራጭም ሆነ ተመራጭ ይህንኑ በቅድሚያ አምኖ ትርጉም በሌለው ምርጫ ከፈለገ ይሳተፍ፤ ካልፈለገ ይቅርበት የማለት ያህል ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ለልማቱ የተመረጡ፣ የተሰጡ ወይም የተቀቡ ሰዎች ስላሉ፤ የሕዝብ ሚና መሳተፍ እንጂ ምርጫን መለወጥ እንዳልሆነ የሚያሳይ ድርጊት ነው፡፡

ወደ ኋላ የምመለስበት ጉዳይ ቢሆንም የዚህ አይነቶቹ ዝንባሌዎች በስፋት ለመስፈናቸው በቂ ምሳሌዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ ጊዜው እጅግ ከረፈደና ለዝግጅት በማይመች ሁኔታ በወር ለአስር ደቂቃ ብቻ የተሰጠው የአየር ሰዓትን ሚዛናዊ ለማስመሰል የተቀነቀኑት ቀመሮችና ስሌቶች፤ ምን ያህል በ“ተጨፈኑ ላሞኛችሁ” የተሞሉና ብትፈልግ ተቀበል ወይም ተወው (Take it or leave it) በሚል ማን አለብኝነት የታጠሩ እንደነበረ መገመት ይቻላል፡፡ አማራጭ ሃሳቦች ቀርበው ተሳትፎው በራሱ ጊዜ እንዲደምቅ ከመስራት ይልቅ፤ በድራማ ላይ ማተኮር የተለመደ በመሆኑ ምርጫው በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነትና ተአማኒነት የነበረው ለማስመሰል፤ መራጮች ተገደውም ቢሆን መውጣት አለባቸው እስከማለት በመደረሱም “እስኪ የመረጥክበትን ጣት አሳየን” በማለት የተፈጸሙት ማዋከቦችና ማስጨነቆች ሌሎቹ መገለጫዎች ናቸው፡፡ የምርጫው እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ በምርጫ ቦርድ ኃላፊነት የሚከናወን መሆኑ ቀርቶ፤ በቀበሌና በመሰረታዊ ድርጅቶች አማካኝነት ለእለት ጉርሳቸውም ሆነ ለኢኮኖሚያዊ ፍጆታቸው ሲባል በአንድ ለአምስት በተደራጁና በቀበሌ አስፈጻሚዎች እጅ መውደቁን ለመታዘብ ችለናል፡፡

ይህ ድርጊት የምርጫ ቦርድን ሕገ-መንግስታዊ ስራና ሚናውን የጨፈለቀ ከመሆኑም በላይ፣ ገና ከጠዋቱ በሕዝብ ዘንድ የምርጫውን ተአማኒነትና ተቀባይነት ፈጽሞ ያደበዘዘ ነበር፡፡ ምርጫው ከተጀመረበት እለት ጀምሮ “ሕዝብ በምርጫው ላይ በንቃት እንዲሳተፍ የማድረግ መብትና ግዴታ አለብን” በሚል ግልጽነት የጎደለው ሰበብ፤ በመደራጀትና በመሰባሰብ በዜጎች ላይ ልክ ያጣ ማዋከብና ማስገደድ ተፈጽሟል፡፡ የነዋሪነት መታወቂያ ካርድ ሳይጠየቅ የመራጮች ምዝገባ ተካሂዷል፡፡ የማህበራዊ አገልግሎት ተጠቃሚነትን ማስገደጃ በማድረግ፣ የነዋሪነት ስም ዝርዝር ተይዞ ቤት ለቤት በተደረገ ዘመቻ፤ የመምረጫ ካርድ መውሰድ ያልፈለጉ ዜጎች የምርጫ ካርድ በግድ እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡ እጩ ምዝገባን በሚመለከት የተፈጠረውን የእጩ ክፍተት ለመሙላት፤ በተለያየ መንገድ በተቀነባበረ ስልት በፓርቲዎች እውቅና የሌላቸው ግለሰቦች በፓርቲዎች ስም እንዲመዘገቡ ተደርጓል፡፡ በምሳሌነት የሚነሳው በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብሔራዊ ክልል ውስጥ በኢዴፓ እውቅና ያልተሰጣቸው፤ ነገር ግን የኢዴፓ እጩ ነን የሚሉ ግለሰቦች ያለ ፓርቲው የድጋፍ ደብዳቤና የአባልነት መታወቂያ እጩ ሆነው እንዲቀርቡ ተደርጓል፡፡

የምርጫው እለትም ምርጫው በሕዝብ ዘንድ ተቀባነት ያለውና የዜጎችን ይሁንታና ታማኝነት ያገኘ ለማስመሰል፣ ገና ጎሕ ከመቅደዱ ጀምሮ በአንድ ለአምስት የተደራጁ ሃይሎችን ወደ ምርጫ ጣቢያ እንዲተሙ በማድረግና ለዚሁ በተዘጋጁ የመገኛኛ ብዙሃን ተዋናዮች አማካኝነት ቪዲዮ በመቅረጽ፤ ምርጫውን ደማቅ ለማስመሰል ተሞክሯል፡፡ ቀኑ እየረፈደ ሲመጣና ዜጎች በምርጫው ለመሳተፍ ፍላጎት ማጣታቸውንና ወደ ምርጫ ጣቢያ እንዳልወጡ ሲታወቅ፣ በሞባይል ስልክ ጥሪ በማድረግ፣ መንገድ ላይ በመጠበቅና ቤት ለቤት በመዝመት፣ ሕዝብ ወደ ምርጫ ጣቢያ እንዲሄድ ተጽእኖ የታከለበት ከፍተኛ ውትወታ ተካሂዷል፡፡ በሳምንቱ እሁድም የነበረው የመራጩ ተሳትፎ ቁጥሩ በእጅጉ እንደሚመናመን ስለተገመተ ሕገ-መንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው አንመርጥም ያሉትን ዜጎች፣ “የማትመርጡ ከሆነ የመምረጫ ካርዳችሁን መልሱ” በማለት ባላመኑበት ምርጫ ያለመሳተፍ ሕገ-መንግስታዊ መብታቸው ሲጣስ ተስተውሏል፡፡

ከላይ እንዳየነው መነሻው ኢ-ሞራላዊ በሆነ ተጽእኖ በአፈና፣ በወከባና በማስጨነቅ ለጊዜውም ቢሆን ሕዝብ ወደ ምርጫ ጣቢያ እንዲሄድ ማድረግ ችለዋል፡፡ ነገር ግን ሂደቱ ለውጤትና ለቆጠራ የሚበቃ የመምረጫ ወረቀት ከኮሮጆ ውስጥ ለማግኘት አልረዳቸውም፡፡ መጨረሻም ላይም ቆጠራው የተደረገው መራጮችን በማወዳደር አሸናፊውን ለመወሰን መሆኑ ቀርቶ፤ በምርጫ ኮሮጆ ውስጥ የሞላውን በብሶት፣ በቁጣና በምሬት የታጨቀ ሃተታ ሲያነቡ ለመዋል ተገደዋል፡፡ የምርጫውን ጉዳይ ከማሳረጌ በፊት በምርጫው ሰሞን የገጠሙኝን ጉዳዮች አንስቼ ጸሑፌን ላሳርግ፡፡ የምርጫውን ሂደት ለመታዘብ ተዘጋጅቼ ስለነበረ፣ የምርጫው ዕለት በአንድ በኩል የሸገር ኤፍ ኤምን የቀጥታ የምርጫ ዘገባ እያዳመጥኩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በርካታ የምርጫ ጣቢያዎችን እየተዘዋወርኩ ለመከታተል ችያለሁ፡፡ መንግስታዊ መገናኛ ብዙሃን በተደጋጋሚ ከሚያዘንቡት የዘጠና ዘጠኝ ፐርሰንት የሕዝብ ተሳትፎ በስተቀር ምልዕተ ሕዝቡም ሆነ እኔ በግሌ፣ የሸገር ኤፍ ኤም ዘጋቢዎችም በተናጠል መታዘብ የቻልነው እውነታ ቢኖር፣ ምርጫው ቀኑን ቆጥሮ ከመከናወኑ ውጭ፣ ሂደቱ በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ በመድብለ ፓርቲ አሳታፊነቱም ሆነ በመራጭ ሕዝብ ቁጥር ብዛት እጅግ ዝቅተኛ ሆኖ አልፏል፡፡

ሌላው በዚህ ምርጫ ላይ የታየውና ለምስክርነት የሚቀርበው ጉዳይ፣ በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ ምርጫ ጣቢያ የወጣው ሕዝብ፤ የምርጫ ካርዱን በተለያየ መንገድ የተቃውሞ መግለጫው ሲያደርግ መዋሉ ነው፡፡ በምርጫው ቀን ሕዝቡን በነቂስ ለምርጫ እንዲያስወጡ ግዳጅ የተሰጣቸው የአንድ ለአምስት ሰራዊቶች፤ ሕጋዊም ሆነ ኢ-ሕጋዊ በሆነ መንገድ በማስጨነቅና በማዋከብ በርካታ መራጭ ወደ ጣቢያ ማስወጣት ችለዋል፡፡ ይህ አካሄዳቸው ባዶ ኮሮጆ ከማግኘት አድኗቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ተገዶ የወጣው መራጭ ግን ለፈለጉት አላማ መሳርያ ሊሆን አልቻለም፡፡ በእምቢታው እንዳይፀና የደረሰበት ተጽእኖና እንግልት ቢያግደውም፣ ያለፍላጎቱ ወደ ምርጫ ጣቢያ መሄዱን እንደማይቀበል ጨዋነት በተሞላበት መንገድ ተቃውሞውን ገልጿል፡፡ መራጩ ሕዝብ ተገዶ በተገኘባቸው የምርጫ ጣቢዎች ላይ ነጻ ጋዜጦችን ያገኘ ይመስል በምርጫ ሰነዶች ላይ የብሶት ስሜቱን በመፃፍ ለቆጠራ የማያገለግሉ አድርጓቸዋል፡፡ ሌላው ትዝብቴ በማታው ኢቴቪ ዜና እወጃ ላይ ያዳመጥኩት ጉዳይ ነበር፡፡ በምሽቱ የሁለት ሰዓት ዜና እወጃ ላይ የተለያዩ ክልሎችን የምርጫ እንቅስቃሴ ዘገባ ካደመጥን በኋላ የአማራ ክልል ዘገባ ተከተለ፡፡ ዘጋቢው በአማራው ክልል ውስጥ የምርጫው እንቅስቃሴ አስደሳች እንደነበረ ከገለፀ በኋላ፣ በጠቅላላ በአማራ ክልል ለምርጫ ከተመዘገበው ዘጠኝ ሚሊዮን ሕዝብ መካከል ስድስት ሚሊዮኑ እንደመረጠ ገለፀ፡፡ ጆሮዬን ማመን አቃተኝ፡፡ ማመን ያዳገተኝ ቁጥሩ አልነበረም፡፡

ምርጫው የተጠናቀቀው ከረፋዱ አስራ ሁለት ሰዓት ላይ ሆኖ እያለ፣ ዘጋቢው ዜናውን ያቀረበው ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ላይ መሆኑ ነበር፡፡ ለመገመት እንደሚቻለው በመሃል ያለፈው ጊዜ ሁለት ሰዓት ብቻ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ የስድስት ሚሊዮን መራጭ መረጃ አቀናብሮ መዘገብ መቻሉ እውነትም ምርጫ ቦርድ ዘምኗል የሚያስብል ነበር፡፡ እንግዲህ የአማራውን ክልል የቆዳ ስፋት፣ የምርጫ ጣቢያ ስብጥርና ብዛት ገምቱት፡፡ ከዚህ ሰፊ ቦታ የሚሰባሰበው የመራጭ መረጃ በስልክ ተጠናክሮ ቀረበ ቢባል እንኳ መረጃው ዜና ለመሆን እንደቦታው ርቀትና እንደ መረጃው ስፋት ቢያንስ አንድ ቀን አሊያም ሳምንታት ሊፈጅ እንደሚችል ለመገመት አያዳግትም፡፡ ዘጋቢው ግን ለዚህ ጉዳይ ደንታ አልነበረውም፡፡ ምርጫ ቦርድ በተለያየ ጊዜ የሰጣቸውን መግለጫዎችና ማብራሪያዎችን ለተከታተለው እንዲህም ማለትና ማድረግ ይቻላል እንዴ የሚያሰኙ ናቸው፡፡ በአንድ በኩል ለምርጫው ሃያ አንድ ፓርቲዎች እንደተመዘገቡ እየተለፈፈ፤ በሌላ በኩል ከሁለትና ከሶስት ያልበለጡ ፓርቲዎች ያቀረቧቸውን እጩዎች ስም መለጠፍና ማስተዋወቅ የመረጃ እጥረት ወይስ ምርጫን ለማድመቅ የተሰራ ፕሮፓጋንዳ የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ምርጫን በነጻና ገለልተኛ መንፈስ፣ በሕጋዊ አሰራር ላይ ተመስርቶ ሁሉም ፓርቲዎች እንዲሳተፉበት ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያለበት ምርጫ ቦርድ፤ የተዛባ መረጃ መስጠቱ አሳሳቢ ሂደት ነበር፡፡ ምርጫ ቦርድ አልፎ ተርፎ የተወዳዳሪ ፓርቲዎችን ቁጥር አዛብቶ በማቅረብ፣ ቀሪዎቹን ማጣጣል ለምን እንዳስፈለገው ፈፅሞ አይገባም፡፡

ምን አልባት የተቋቋመበትን ዓላማ መርሳት ሊሆን ይችላል፡፡ በለሆሳስ ሲባል የከረመው “ኢህአዴግ እስካለ ድረስ ሌላው ሃይል ቀረም መጣ የሚያመጣው ነገር የለም” የሚል ድምዳሜ ላይ ላለመደረሱስ ምን ማረጋገጫ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ጉዳዩ አሳሳቢና መልስ የሚሻ ጥያቄ ነው፡፡ በመራጭች ምዝገባ ወቅትና በእጩ ማስመዝገብ ሂደት ላይ በተግባር የታዩ በተለይም ምርጫውን ጥርጣሬ ላይ የጣሉ ጉዳዮችን መፍታት የምርጫ ቦርድ ስራ ነው፡፡ በተለይም የምርጫን ውጤት ሊያዛቡ እንደሚችሉ የተገመቱ ግዴለሽነቶችን በመመርመር ለመታረም ከመዘጋጀት ይልቅ ጥያቄ ያነሱትን ፓርቲዎች ሐሰተኛ ማድረግ ለምን አስፈለገ? ምንም ይሁን ምን ለውድድር የቀረቡ ፓርቲዎች እስካሉ ድረስ ለቀሪዎቹ ጥያቄ ቦታ አልሰጥም ማለት የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን በማዳከም ተጠያቂ ማድረጉ አይቀሬ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ከተቋቋመበት መሰረታዊ ዓላማ መካከል ዋነኛው የፓርቲዎችን ተሳትፎ በማጎልበት ሕዝቡ አማራጭ ሃሳቦችን እንዲያገኝ ማገዝ ነው፡፡ በመቀጠልም ነጻና ገለልተኛ ምርጫ በማካሄድ፡፡ ሕዝብ የሚደግፈውን ፓርቲ እንዲመርጥ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው፡፡ የሕዝብ የስልጣን ባለቤትነትም የሚረጋገጠው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ በምርጫ ቦርድ ዘገባ መሰረት፣ ከተመዘገቡት 23 ፓርቲዎች በላይ 30 ፓርቲዎች ጥያቄ አለን እያሉ፤ ጥያቄያቸውን በማጣጣልና ሕዝብን አማራጭ በማሳጣት፣ ምርጫን ማካሄድ የትም የማያደርስ የዝግ መንገድ ጉዞ መሆኑ የምርጫ ቦርድ ቃል አቀባዮች ሊያጡት ባልተገባ ነበር ፡፡ አሁን አሁን የምርጫ ቦርድ ቃል አቀባዮች “ትልቅና ትንሽ የሚባል ፓርቲ የለም፡፡ ለኛ ሁሉም ፓርቲዎች እኩል ናቸው” ሲሉ ማዳመጥ የተለመደ ነው፡፡

ለፕሮፓጋንናዳ ፍጆታ ካልሆነ በስተቀር ፓርቲዎች ከምን አኳያ እኩል ሆኑ የሚል ጥያቄ ቢነሳ፣ የምርጫ ቦርድ ቃል አቀባዮች መልስ እንደሌላቸው ግልጽ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢህአዴግ ለምርጫ ከሚደለደለው የመገናኛ ብዙሃን የአየር ሰዓት ውስጥ ሰባ በመቶውን፣ በመንግስት ከሚመደበው የገንዘብ ድጎማ መካከል የአንበሳውን ድርሻ ሲወስድ ትልቅና ትንሽ ከሚል መስፈርት ውጭ ምንም ዓይነት የክፍፍል ቀመር እንዳልነበር “የአዋጁን በጆሮ” ነው፡፡ ይህም ሆኖ በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ውስጥ አልፈው ለምርጫ የተዘጋጁ ፓርቲዎች ቁጥሩ ከሚወዳደሩት በላይ መሆኑ እየታወቀ፣ “ለመወዳደር የፈለጉ ፓርቲዎች እስካሉ ድረስ ችግር የለብኝም” በሚል ስሌት ምርጫን ያህል ነገር ማካሄዱ፤ ምርጫው “ኢህአዴግ እስካለ ድረስ ሌላ ምን ያስፈልጋል” ወደሚል ድምዳሜ ሊገፋ እንደሚችል ጠቋሚ ነው፡፡ ልማታዊ መንግስት መጀመርያውንም ቢሆን ፓርቲዎችን አዳክሞ “ተወዳዳሪ ስለጠፋ ምን ማድረግ ይቻላል፤ ምርጫው ባለው ተሳታፊ መቀጠል አለበት” ማለቱ የተለመደ ስልቱ ነው፡፡ በዚህ ኢ-ዴሞክራሲያዊ ስሌት ከቀጠልን የመድብለ ፓርቲና ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን ከአውራ ፓርቲ ወደ አንድ ፓርቲ ስርዓት እየተሸጋገረ ላለመሆኑ ከምርጫ ቦርድ ውጭ ማን ማረጋገጫ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ምርጫ ቦርድ ይህ እንዳይሆን የተቋቋመ ዴሞክራሲዊ ተቋም መሆኑን መዘንጋቱ ግን ከሁለም በላይ አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡

ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ይህ ካልተከሰተላቸው ሂደቱ መልስ የሚጠይቀው ለፓርቲዎች ሕልውና ሳይሆን ቅድሚያ ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት ሲሆን ቀጥሎ ተቋማቱ ለተቋቋሙበት ሕገ-መንግስት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ እንደ ማጠቃለያ በዚህ ምርጫ ሂደት የተጐሳቆለውና የታመመው ሌላ ሳይሆን በማቆጥቆጥ ላይ የነበረው የመድብለ ፓርቲ ስርዓታችንና የሕዝብ የስልጣን ባለቤትነት ነው፡፡ በእኔ እምነት በምርጫ የመወዳደርና ያለመወዳደር እሰጥ አገባ የፈጠረው ተግዳሮት በማንም አሸናፊነት አልተጠናቀቀም፡፡ ሊጠናቀቅም አይችልም፡፡ ተቃዋሚዎች በአቅማችንና በልካችን ወንበር አሸንፈን የመድበለ ፓርቲ ስርዓቱን ለማጠናከርም ሆነ አማራጭ ሆኖ ለመቅረብ የነበረንን እድል የነፈገ ምርጫ ነበር፡፡

ኢህአዴግ የተሰዋለትና የተዋደቀለት የመድብለ ፓርቲ ስርዓት፤ አማራጭ ሃሳቦችን በቅጡ ማስተናገድ አልቻለም፡፡ የዴሞክራሲ ተቋማትም ይህንን አጣብቂኝ ለመፍታት የሚያስችል ሃቀኛነት፣ ብቃት፣ ተነሳሽነትና ተቆርቋሪነት ማሳየት አልቻሉም፡፡ በመጨረሻም ሂደቱ የተጠናቀቀው ሕዝብ በምርጫ ስርዓትና በመድብለ ፓርቲ ፖለቲካችን ላይ ስጋት እንዳደረበት ነወ፡፡ ሕዝብ አማራጭ በሌለበትና ውድድር በደበዘዘበት የምርጫ ሂደት ውስጥ ሆኖ የስልጣን ባለቤትነቱን በተግባር ማየትም ሆነ ማሳየት አልቻለም፡፡ ማብቂያ ከሌለው አጣብቂኝ እንወጣ ዘንድ ቆም ብለን እንድናስብ ጊዜው የግድ ይላል፡፡

ምንጭ አዲስ አድማስ

Share