Logo

እውነትም “ያለበት” ይገንበት እንዳይሆን ?

May 22, 2013

Mushe Semuከሙሼ ሰሙ(የኢዴፓ ፕሬዚዳንት)

“በዓለም ላይ ያሉ  ሃገሮች የራሳቸው መከላከያ ሰራዊት አላቸው፡፡ የኛ መከላከያ ሰራዊት ግን አልጄሪያ የሚባል የራሱ ሃገር አለው፡፡”   

አዲስ አድማስ ጋዜጣ በዜና ዘገባው ላይ የመከላከያ ሳምንትን አስመልክቶ የፖለቲካ ፓርቲዎች አቋማችንን እንድንገልጽ እድል ሰጥቶን ነበር፡፡ በዚህ እድል ሃሳባቸውን ከገለጹት ተጋባዦች መካከል አንዱ እኔ ነኝ፡፡ ዜና ዘጋቢው ለአምዱ ስፋት ይመጥናል ባሉት ልክ ሃሳቤን ቀንጨብ አድርገው በማቅረባቸው በርካታ ሃሳቦቼ በዓምዱ ላይ የመካተት እድል ሊገጥማቸው አልቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት በአንባቢያን ዘንድ በቂ ግንዛቤ አልተፈጠረም የሚል ስጋት ነበረኝ፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በአዲስ አድማስ ሳምንታዊ ጋዜጣ ላይ የመከላከያ ሳምንትን አስመለክቶ በሰጠሁት አስተያየት ላይ “ጭስ የለውም እንጂ እሳቱስ አሪፍ ነው” በሚልና “የሠራዊት ቀንና የተቃዋሚዎች መሠረተ- ቢስ እሳቤዎች” በሚሉ ሁለት ርዕሶች ስር የተለያዩ ጸሐፊዎች ዘለፋና ዛቻ አዘል ትችቶች በአዲስ ዘመንና በአይጋ ድረ ገጽ ላይ  አቅርበዋል፡፡ በአጠቃላይ ተቺዎቼ የመከላከያ ሳምንት ኢግዚቢሽንን ከጎበኝሁ በኃላ ለመታዘብ በቻልኳቸው ሕጸጾች ላይ የሰጠኋቸውን ገንቢ አስተያየቶች የሚያጣጥልና አንደውም ምን ሲደረግና ሲታሰብ በመከላከያ ላይ አስተያየት ተሰጠ በሚሉ በብስጭቶችና ቁጭቶች የታጠሩ ናቸው፡፡

ስልጣን በምርጫ  አማካኝነት ይገኝ በሕገ ወጥ መንገድ በሕዝብ ሃብት ላይ እያዘዙ “የሹም ዶሮ ነኝ እሽ አትበሉኝ ” ማለት የማያዛልቅ ጸሎት ለ— ከመሆን አይዘልም፡፡ ዜጎች በማንኛውም ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ መረጃ የማግኝት፣ ሃሳብ የመሰንዘር፣ የማዳመጥና ልዩነቶችን የመመርመር ዘለግ ሲልም የተሻለውን የመምረጥ መብት አላቸው፡፡ በተለይ ደግሞ በሕገ-መንግስታችን ላይ የሰፈሩት በርካታ ዓለም አቀፍ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ድንጋጌዎች ማንም ከሕዝብ ዓይንና ጆሮ ውጭ እንዲሆን እድል የሚሠጡ አይደሉም፡፡

የሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 12 “የመንግስት አሰራርና ተጠያቂነት” በሚለው ርዕስ ስር ከተራ ቁጥር 1 ጀምሮ አስከ ተራ ቁጥር 3 ድረስ የተደነገጉት ሕግጋቶች ማናቸውም በመንግስታዊ ተግባራት ላይ የተሰማራ ሃይል በግልጽነትና በተጠያቂነት እንደሚመራ ይደነግጋል፡፡ ሁሉም የመንግስት ሹመኞችም ኃላፊነት በጎደለው መንፈስ ለሚፈጽሙት ተግባር በሕግ ፊት ተጠያቂ እንደሚሆን በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ ከዚህ አኳያ ለምን አስተያየት ተሰጠብኝ የሚያዛልቅ ጉዞ አይሆንም፡፡

ወደ ዋናው ሃሳቤ ከመግባቴ በፊት ከነዚህ መሰረታዊ የሕገ-መንግስት ድንጋጌዎች በመነሳት፤ ከላይ ለጠቀስኳቸው ተቺዎቼ ሰለ ተጠያቂነትና “ስለውዳሴ ከንቱ” ጥቂት ነገር ማለት እፈልጋለሁ፡፡ ጥንታዊ ግሪኮች “ሂውብረስ” “Hubris” የሚሉት አንድ አቻ የማይገኝለት ስረው ቃል አላቸው፡፡ የእንግሊዘኛ ትርጉሙ  “Big headedness, Audacity, Arrogance ” ወይም  The Excessive Pride and Ambition that Usually Leads to the Downfall of a Hero in Classical Tragedy” ይለዋል፡፡ አዛማጅ የአማርኛ ትርጉሙ ደግሞ “አጅግ በጣም መሰረቱን ከሳተ ማንአለብኝነት በሚመነጭ መንፈስ ላይ ተኮፍሶ  “ከከንቱ ውዳሴ” በስተቀር የልዩነት ሃሳብን ለማስተናገድ አቅም በማጣት  ለውድቀት የሚዳርግ ትምክህት” ይሆናል፡፡

ሕገ-መንግስቱ የሚደነግገው ሕገ-መንገስትን ስለሚያስከብርና ስለሚያከብር መከላከያ ሰራዊት እንደመሆኑ መጠን መከላከያ በሕገ-መንግስቱ ላይ በሰፈረው መሰረት እንደማንኛውም የመንግስት አስፈጻሚ አካል በሕግ ፊት ቀርቦ እንደሚጠየቅንና   በሚቀርቡት ሃሳቦችም ላይ ተመርኩዘው ለሚነሱ ትችቶች፣ ጥያቄዎችንና ለልዩነቶችን በራቸው ክፍት መሆን እንዳለበትና ሕገ-መንግስታዊ ግዴታ መሆኑን መረዳት ያሻል፡፡ ተቺዎቼ ግን  ከ“ውዳሴ ከንቱ” ከ“ማቆለጳጰስ” በስተቀር አማራጭ ሃሳብንም ሆነ ገንቢ አስተያየትን ለማስተናገድ ልቦናቸውን የደፈኑ ስለመሆናቸው ከጽሑፋቸው ለመረዳት ፈላስፍ መሆን አያሻውም፡፡

ለግንዛቤ እንዲረዳን እስኪ ሕገ-መንግስቱ በመከላከያ ሰራዊት መርሆዎች ዙርያ ስለሚደነግጋቸው ጉዳዮች ጥቂት ልበል፡፡ ሕገ-መንግስቱ በአንቀጽ 87 ላይ ከተራ ቁጥር 1 ጀምሮ አስከ 5 ድረስ የመከላከያ ሰራዊት የሚመራባቸውን መርሆዎች በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ የመከላከያ ሰራዊት የሃገራችንን ሉአላዊነት ከማስከበር በተጨማሪ ሌሎች ማንኛውንም ዓይነት ሃላፊነቶችን ሊሰጠው የሚችለው ሕገ-መንግስቱ ውስጥ በሚደነገገው መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ( State of Emergency ) ተከትሎ ለሚፈጠሩ ግዳጆች ብቻ ነው፡፡ በሌሎች ማንኛውም ሃገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የመከላከያ አባላትና በዜግነታቸው መከላከያ በተቋምነቱ ከሚኖራቸው ሚና ውጭ፤ መንግስትን ወክለው በማናቸውም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በራሱ ተነሳሽነትም ሆነ በመንግስት ፍላጎትና ጥያቄ ጣልቃ መግባት የሚያስችላቸው አንዳችም ሕገ-መንግስታዊ ክፍተት አልተጸፈም፡፡ በሕገ-መንግስቱ ላይ በተደነገገው መሰረት መከላከያ ሰራዊት እንደተቋም በሰላም ጊዜ በግል ዘርፉ መሸፈን የቻሉ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ጣልቃ መግብት ይቅርና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ( State of Emergency ) አዋጅ ባለበት ጊዜም ቢሆን መከላከያን ከሚመለከቱ ጉዳዮች ውጭ በማንኛውም የሲቪል ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳትፎው እንዲኖረው የተከፈተ በር የለም፡፡

ወደ ኢግዚቢሽኑ እንምጣ መንግስታዊ መገናኛ ብዙሃን በስፋት እንዳተቱት የመከላከያ ኢንጂነሪንግ በኢግዚቢሽኑ ላይ ያቀረባቸው የሲቪል ቁሳቁሶችና ምርቶች እንኳን ለግል ኢኮኖሚ ዘርፉ የሚተርፍ እውቀት ሊኖረው ይቅርና የመከላከያ ሰራዊቱን አባላትንም ቢሆን ከሚታወቀው ውጭ በዘመናዊና በላቀ ቴክኖሎጂና ሳይንስዊ ግኝት ላይ የተመሰረቱ የጦር መሳርያዎችን ለማስታጠቅ አቅም የፈጠረ መሆኑን የሚያሳዩ አልነበሩም፡፡

ለዚህ ደግሞ በመጀመርያ ደረጃ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ዛሬ የታጠቃቸው የጦር መሳርያዎች በኢግዚቢሽኑ ላይ ከቀረቡት በእጅግ የላቁና ዘመናዊ ሊሆኑ እንደሚችሉ ለመገመት ይቻላል፡፡ ምናልባትም መከላከያ የታጠቃቸው የጦር መሳርያዎች የትውልድ(ፍብረካ) ዘመን (Generation) የቅርብ ጊዜ ከመሆናቸው የተነሳ አምራቾቹም ቢሆኑ የጦር መሳርያውቹን በግዢ ካልሆነ በስተቀር ለሚገጠጥሙ ድርጅቶች በሽያጭ የሚያቀርቧቸው ዓይነት እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡

በሌላ በኩል የመገጣጠም በሳይንሳዊ ፈጠራ ታግዞ ማምረት   በዕውቀት ዘርፍ አሰላለፋቸውም ሆነ በመሰረተ ሃሳብ ደረጃ የማይወራረሱ ለየቅል የሆኑ ስራዎች ናቸው፡፡ በኢግዚቢሽኑ ላይ የታዩት የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች፣ ተሸከርካሪዎችና የቤትና የቢሮ ቁሳቁሶች ከ-እስከ ሳይባል የሜካኒካልም ሆነ የኤሌክሪቲካል ክፍላቸው፣ ዲዛየናቸውና ተገጣጣሚ አካላቶቻቸው በሙሉ ከአምራቾቹ ሃገራት በውጭ ምንዛሪ ተገዝተው የመጡ መሆናቸው በወቅቱ የነበሩት አስጎብኝዎቻችንም ቢሆኑ የደበቁት ጉዳይ አልነበረም፡፡ ከዚህ ተነስተን የምንደርስበት ድምዳሜ ቢኖር በእለቱ ከቀረቡት ምርቶች ውስጥ አንዱም በመከላከያ የጥናትና ምርምር መምሪያ አማካኝነት ተፈጥረው በሳይንስና ፈጠራ ምርቶች ባለቤትነት እውቅና ሰጭ  በሆነ ተቋምት አማካኝነት በፈጠራ መብት ባለቤትነት የተመዘገቡ ምርቶች አልነበሩም፡፡

ማንም ሊገምተው በሚችለው ደረጃ ስለቴክኖሉጂ ስናወራ ስለጥናትና ምርምር ወይም ስለፈጠራ ሳይንስና ስለመፈብረክ እያወራን መሆኑን ግልጽ ነው፡፡ የፈጠራ ሳይንስና የቴክኖሎጂ ፍብረካ በየትኛውም መለኪያ ከትንሹ ብሎን ጀምሮ እስከትልቁ ሞተርና ተገጣጣሚ አካላት ድረስ በውጭ ምንዛሪ በማስመጣት መገጣጠምን አያካትትም፡፡ ይህንን ለመረዳትም ሆነ ለማስረዳት ምንም ዓይነት እውቀትን  መጎናጸፍ አያስፈልገውም፡፡ ሲቀጥልም ተሸከርካሪ፣ ሞባይልና ኮምፒዩተርን አሁን ደግሞ ቴሌቪዥን መገጣጠም በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ከዚህ ቀደም ያልነበረ እውቀትና አዲስ ግኝት ወይም ፈጠራ ተደርጎ መቅረቡ አስቂኝ ከመሆኑም በላይ ታሪክን እንደገና ለመጻፍ የሚደረግ ሽሚያ ከመሆን አይዘል፡፡ ለዘመናት የኖርንበት ተጨባጭ እውነታውም ይህንን አይፈቅድም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ተሸከርካሪ የመገጣጠም ታሪክ ከበርካታ አስርት ዓመታት በፊት በአምቼ “ሀ” ብሎ ይጀምራል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በመካከለኛ መጋዘንና በዘመናዊ ጋራዥ ውስጥ በመጀመርያ በሆላንድ ካርና በሊፋን ቀጥሎም በበላይ አብና በመስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ አማካኝነት መገጣጠም መቀጠሉ ዘመን የቆጠረ ታሪክ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ልቦና ሰጥቶት ላጤነው ተጠቃሾቹ የግል ዘርፍ (ከመስፍን ኢንዱስትሪያል በስተቀር) ድርጅቶች ተሸከርካሪ የ“መገጣጠም ታሪካቸው” ከመከላከያ ምሕንድስና በፊት ዓመታትን ያስቆጠሩ መሆናቸው አስጣ አገባ የሚያስከትል ነገር የለውም፡፡

“ተሽከርካሪ የመገጣጠም” ታሪካችን መነሻው ይህ ከሆነ ደግሞ በእውቀት ሽግግርም ሆነ በልምድ ልውውጥ ቀዳሚዎቹ ተሸከርካሪ ገጣጣሚዎች ከመከላከያ ምሕንድስና የሚማሩት ነገር ሊኖር እንደማይችል ዘመን የቆጠረ ተመክሯቸው ምስክር ነው፡፡ እንደውም የመማር ነገር ከተነሳ መማር ያለበት መከላከያ ምሕንድስና ለመሆኑን በርካታ ጠቋሚ ጉዳዮች ማንሳት ይቻላል፡፡ ቢያንስ ቀደምቶቹ የተሸከርካሪ መገጣጣሚያ ድርጅቶች በየመንገዱ በሚቆሙ ተሽከርካሪዎች ምክንያት አስካሁን ሲታሙ አልሰማንም፡፡

ሞባይል መገጣጠምን በሚመለከት በአሁኑ ጊዜ ከሦስት ያላነሱ ሞባይል የሚገጣጥሙ ድርጅቶች፣ ሞባይልን በብቃት እያመረቱ ለገበያ በማቅርብ ውጤታማ ስራ እየሰሩ እንደሆነ የከተማችን ወሬ ከሆነ ሰንብቷል፡፡ ኮምፒየተር መገጣጠምን በሚመለከትም ከዚህ ቀደም በርካታ ድርጅቶች እንደነበሩና አሁንም ኮምፒዩተር ለመገጣጠም በዝግጅት ላይ ያሉ በርካታ የግል ዘርፉ ባለሟሎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ቴሌቪዢንም ቢሆን ከቬስቴል ጀምሮ አስከ ሳምሳንግ ምርቶች መዝለቅ ይቻላል፡፡ እንግዲህ በግርድፉ፤ እውነታው ይህን ከመሰለ የመከላከያ ምሕንድስና እነማንን የአዲስ ቴክኖሎጂ ባለቤት ለማድረግ አቅዶ በግሉ ዘርፉ ሊሸፈኑ በሚችሉ ስራዎች ውስጥ ጣልቃ መግባት እንዳስፈለገው ማብራሪያ ሊሰጠን ይገባል፡፡

እዚህ ላይ ቆም ብለን በርካታ ጥያቄ ማንሳት ይኖርብናል፡፡ የግል ዘርፉ አቅም ሳያንሰውና ከተቋቋሙት ፋብሪካዎችም በላይ በርካታዎቹ ወደ ገበያ በስፋት በመግባት ላይ እንደሆኑ እየታወቀ የመከላከያ ኢንዱስትሪ በመንግስት አቅምና ከግብር ገቢ በሚሰበሰብ በጀት እየታገዘ በነዚህ ዘርፎች ውስጥ ጣልቃ መግባት ለምን አስፈለገው? ሁለተኛው እንደው አስፈላጊ ነው ቢባል እንኳን ኢትዮጵያ ቅድሚያ የምትሰጣቸው በርካታ ሕዝባዊና ሃገርዊ የልማት ጥያቄዎች እያሉ ተሸከርካሪዎችንና ሞባይሎችን መገጣጠም የመከላከያን ዓይንና ጆሮ ወይም ትኩረት እንዴት ሊስብ ቻለ? ወይስ የግል ዘርፉ ልማታዊነት ስለሚንስው በልማታዊ ስም መንግስታዊ ከበርቴነትን ለማስፈን? ሦስተኛው መከላከያ ገቢው የተመሰረተው ከትርፍ ከሚገኝ ፈሰስ መሆኑ ያታወቃል፡፡ እውነታው ይህ ከሆነ መከላከያ የተመሰረተበት እርሾ ከየት ፈሰስ ተደረገ? ከምሰረታው በኃላስ የመከላከያ ምሕንድስና ገቢና ወጭው በማን ቁጥጥርና ክትትል ስር ይገኛል? ለብክንት፣ ለሙስና፣ ለአምቻ ጋብቻና ለመጠቃቀሚያ አለመጋለጡንስ በሚመለከት ማን ማረጋገጫ ማቅረብ ይችላል? ወዘተርፈ …

Share