Logo

“ኢህአዴጎች” ሆይ ሁለቱን ሙሰኞች አሰራችሁ ዘጠና ዘጠኙ ሙሰኞች የታሉ?

May 30, 2013

Mushe Semuሙሼ ሰሙ (የኢዴፓ ፕሬዚደንት)

(PDF) መንግስትና ኢህአዴግ አንድና ሁለት ባለስልጣናትን በመሰዋት ሙስናን በቁርጠኝነት እየታገሉ መሆኑን ለማስመስከር የሚሞክሩበት ዘመን ጀምበሩ እንዳዘቀዘቀ ግልጽ ሆኗል፡፡ ዛሬ ላይ ሕጻን አዋቂ ሳይል “እቺን ዓይነቷን ጨዋታ” ከዚህ ቀደም ተጫውተናታልና ጨዋታና ዜማ ለውጡ፤ ከዚህ ቀደም አንድ ጊዜ ተወናብደናል ሁለተኛ አትደግሙንም እያለ ነው፡፡ የሁላችንም ጥያቄ አንድ አይነት ነው፡፡ እስካሁን አንድ ሁለቱ ሙሰኞች ታስረዋል ቀሪዎቹ ዘጠና ዘጠኙ የታሉ ነው? ከበርካታ መልስ የሚሹ ጥያቂዎች ጋር ተግባራዊ መልስ እንሻለን፡፡

ለበርካታ ዓመታት በሕዝብ ዘንድና በግል የሕትመት ውጤቶች ላይ በሰፊው ይናኝ የነበረው ጥያቄ ኢህአዴግ እንደ ድርጅት በሙስና ነትቧል፤ አልፎ ተርፎም መንግስትንም እያነተበ ነው የሚል ነበር፡፡ ምንም ያህል ለመሸሸግ ቢሞከር ከሕዝብ ዓይንና ጆሮ የሚሰወር ነገር እንደሌለ ግልጽ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የጥያቄያችን መነሻ ሌላ ሚስጥር የለውም፤ በቅርብ ርቀት የምናውቃቸውንና  ከተጎራበቱን አንዳንድ የመንግስት ሹመኞቻችንና ባለስልጣናት የአኗኗር ሁኔታ በመነሳት ነው፡፡ ዓይን አይቶ ልብ ይፈርዳል እንዲሉ ከወረዳና ከቀበሌ ሹመኞቻችን ጀምሮ እስከ ትልልቁ ባለስልጣን ድረስ አኗኗራችን ለየቅል ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ምን ያህል እውነት እንደሆነ ለማረጋገጥ አዳጋች ቢሆንም ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ባለስልጣናት (የደሞዛቸው ልክ ምንም ይሁን ምን) እራሳቸውን ጨምሮ ቤተሰቦቻቸው፤ አልፎ ተርፎም ዘመዶቻቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ስላካበቱት ሃብት፣ ስለሚያሽከረከሩት መኪና፣ ስለሚገነቡት ሕንጻ መስማት የእለት ተእለት ቀለባችን ሆኗል፡፡ ይህ ጉዳይ “ማስረጃ አይቅረብበት እንጂ በመረጃ ደረጃ” የአደባባይ ሚስጥር መሆኑን አሌ የሚል የለም፡፡ በእኔ እምነት ቀደም ብሎና ገና ከጠዋቱ ኢህአዴግም ሆነ መንግስት በሙስና ላይ ይባንኑ ዘንድ በቂ ጥቆማና ማስረጃ፤ ምንም ነገር ከማይሰወረውና ከማይሳነው ሕዝብ – በሕዝባዊ ሃሜት ደረጃ ደርሶቸዋል፡፡ውሎ አድሮ  ዛሬ ላይ ሙስናን መዋጋትን “ሀ” ብሎ መጀምር ለምን አስፈለገ የሚለው ጥያቄ የሁላችንም ነው፡፡ ኢህአዴግ ከአሉባልታውና ከቱማታው እንጸዳ ዘንድ አሁንም መልስ ሊሰጠን ይገባል፡፡

ይህ ሁሉ ቦታ ያጣ “በመረጃ እንጂ በማስረጃ” ያልተደገፈ የሕዝብ ሮሮ እንደተጠበቀ ሆኖ ዛሬ ላይ ከሳሽና ተከሳሽን መለየት ቢያዳግተንም መንግስትም ሆነ ከፍተኛ የኢህአዴግ ባለስልጣንት ማስረጃው እንደነበራቸው ግልጽ አድርገውልናል፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ይህንን አስመልክቶ የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናት በጽሁፍም ሆነ በቃል ከተናገሩት ለመረዳትና ከተለያዩ ሃገራት ተሞክሮ ለማወቅ እንደሚቻለው መንግስታዊ ከበርቴነት ለሙስና በሩን ወለል አድርጎ የከፈተ ስርዓት መሆኑ ምስክር የማያሻው ነው፡፡ ኢህአዴጎችም  እጃችንን ታስረን በሙስና ትንንቅ ላይ ነን ማለታቸውን መለስ ብሎ ማጤን ያስፈልጋል፡፡ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር ከአቶ መለስ ዜናዊ ጀምሮ በተዋረድ “የሁለት ምርጫዎች ወግ” የሚለውን መጽሐፍ እስከጻፉት አቶ በረከት ድረስ ሙስና የፖለቲካ ፍልስፍናቸው ውጤት እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገልጹ ለማንበብና ለማዳመጥ ታድለናል፡፡ በሙስና እጅ መታሰሩም ሆነ ሙስና የፍልስፍናቸው ውጤት መሆኑን ቢነግሩንም፤ የሙስናው መነሻና አጠቃላይ ውጤቱ ከነመገለጫው የፈቃደኝነት ጉዞ መገለጫ መሆኑን ግን አምነው የተቀበሉበት ጊዜ ፈጽሞ አልነበረም፡፡

ከላይ ያነሳሁት የሕዝቡ ሮሮ ሳያንስ ከጥቂት ዓመታት በፊት በሕገወጥ ነጋዴዎችና በሙሰኛ ባለስልጣናትና ቤተሰቦቻቸው አማካኝት በተለያየ መንገድ ከሃገር እንደኮበለለ የሚነገርለት የውጭ ምንዛሬያችን መጠን ከ8 ቢሊየን ዶላር በላይ  መሆኑንና በአሁኑ ጊዜ የውጭ ምንዛሬ ምጣኔውን ባናሰላው ከአንድ መቶ ስድሳ ቢሊየን ብር በላይ መሆኑ በዓለም አቀፍ  የገንዘብና የልማት ተቋማት ዘንድ በሰፊው ሲዘገብ እንደነበረ የሚታወስ ነው፡፡ ኢህአዴግና መንግስት አፍ እንጂ ጆሮ የላቸውም እንደሚባለው ሁሉ በተለመደው መልክ ይህንን ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኘ ጥናት ለመማሪያነት ከመጠቀም ይልቅ፤ ጥናቱን በስም ማጥፋት ከሰውና ተረባርበው ተድበስብሶ እንዲያልፍ አድርገዋል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊትም የሙስናን ችግርን አስመልከቶ በስፋት ጥናት የተደረገበትንና ከ400 ገጽ በላይ ትንታኔ የተሰጠበትን ሰነድ በራሳቸው ቃለ ነቢብ አስተርጉመው ኢትዮጵያ ከሙስና የጸዳች ሀገረ መሆኗ ተመሰከረልን ማለታቸው አይረሳም፡፡ ልክ እንደ ባድመ የፍርድ ቤት ድል መሆኑ ነው፡፡ ይህ ሁሉ እንደ አጫ በረዶ ከሙስና የጸዳሁ ነኝ የሚለው የኢህአዴግ ትረካ የሚዘንብልን የእነ አቶ ያረጋል አይሸሹም፣ የበርካታ ክልል ባለስልጣናትን የአዲስ አበባ ሹመኞች እንዲሁም የአሁኖቹ ቱባ ባለስልጣናት በሙስና ተጠርጥረው ጉዳያቸው በክትትል ላይ እያለ መሆኑ ነው፡፡

ሌላው ሙስናን በኢትዮጵያ ውስጥ ስር መስደዱን ጠቋሚ የነበረው ጉዳይ ደግሞ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመክበር የሚሻ ከመነገድና ተግቶ ከመስራት ይልቅ ኢህአዴግን ጠጋ ማለት ፈጣን ምላሽ ያስገኝለታል፡፡” የሚለው የከተማችን ብሂል ነው፡፡ ይህ አባባል የከተማው ወሬ ከሆነ ውሎ ማደሩን ኢህአዴግም ሆነ አባላቱ አሌ የሚሉት ጉዳይ አይደለም፡፡ በተግባር ላጤነውም እዚህም እዚያም ማንነታቸው በሕዝብ ዘንድ በግልጽ የሚታወቁ አንድንድ ግለሰቦች የኢህአዴግ አባል በሆኑ በጥቂት ዓመታት ውስጥ በመጀመርያ ቱባ ባለስልጣን ሆነው ሲያዙና ሲናዙ ማየት፤ ቀጥሎም ባለሁለትና ባለሶስት ፎቅ መኖርያ ቤት እንደዘበት ሲገነቡ መመልከት፤ ቀስ እያሉም በቤተሰቦቻቸው አማካኝነት ከዝቅተኛ የኑሮ ዘይቤ ወጥተውና የሙያ ዘርፍ ለውጠው ወደ ደቡብ ሱዳንና ዱባይ ለንግድ ሲያመሩ ወይም ፎቅ ገንብተው የማከራየት ስራ ላይ ሲሰማሩ ማስተዋል ይችላል፡፡

ከዚህ በላይ እጅግ አሳዛኝ የሆነው ጉዳይ ደግሞ እኛን አልፈው ቤተሰቦቻችንን ላይ ያሳደሩት ያለተገባ ዝንባሌ ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ ከበርካታ ቤተስብ የሚሰጠው ቤተሰባዊ ምክር ጨዋነትን፣ የሰው አለመመኘትን ጠንክሮ መማርን፣ በርትቶ ማጥናትን፣ ስራ አለመናቅን አይደለም፡፡ የሚሰጠው ምክር “እንደው ዝም ብለህ እዚህ ከምትጃጃልና ከምትበለጥ እንደነ እገሌ አንተም እንዲያልፍልህ ከፈለግክ እስቲ ወደ ቀበሌ ከሹመኞቻቸው አልፈው ተርፈው ወደ ማህበረሰባችን በመፍሰስ በአጠቃላይ ማንነታችን ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደሩ ይገኛሉ፡፡ በማህበረሰባችን ዘንድ ጠንካራ የነበረው የሕዝብና የሃገር ፍቅር ስሜት፣ እኔን ብቻ በሚል ዝንባሌ እንዲተካ መንስኤ እስከመሆን ደርሷል፣ ለስራ ከመትጋትና የእራስ በራስ ተነሳሽነት ይልቅ በአቋራጭ ለመክበር መቋመጥ ስር እያሰደደ ይገኛል፡፡ ጥቅመኝነት፣ ግለኝነት፣ ስግብግብነትን የመሳሰሉ አደገኛ ዝንባሌዎች እየተንሰራፉ ይገኛሉ፡፡ በአጠቃላይ “ሳይጠሩት አቤት፤ ሳይልኩት ወዴት ባይነትንና የቀን ሕልመኝነት ባሕል ለመሆን መሬት እየተቆናጠጡ ይገኛሉ፡፡

ከላይ በዝርዝር ለማሳየት እንደሞከርኩት የኢህአዴግ አስተዳደር የተዘፈቀበት የሙስና ዓይነት፣ ጥልቀትና ስፋት በአጠቃላይ በሃገሪቱ ላይ እያሳደረ ያለው አስፈሪ ተጽእኖ ከዚህም በላይ ሊወራለት የሚችል ጉዳይ እንደሆነ ከኔ በላይ ሕዝብ ሕያው ምስክር ነው፡፡ በጥቅሉና በግልጽ ለማስቀመጥ እንደሞከርኩትም ሙስናው ከፖለቲካ ፍልሰፍና ጀምሮ አቅም በማጣት ውሳኔ ለመስጠት እስከ መልፈስፈስ ባደረሰው ውጥንቅጥና ሴራ የተተበተበ ከመሆኑም በላይ ከስጋትም በላይ ስጋት እንደነበረ ከራሳቸው ከኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናት ንግግርና ጽሑፍ ከማደመጥ በላይ ሌላ ምስክር ማምጣት አያሻም ባይ ነኝ፡፡ በእርግጥም ሙስናውን ለመታገል በኢህአዴግ በኩል ቁርጠኝነቱ ካለ በአንድ መንግስታዊ ተቋም ላይ ብቻ አተኩሮ ከሃምሳ ሰው በላይ መታሰሩ የሚገልጥልን ነገር ቢኖር  በሌሎቹም የመንግስታዊ ተቋሙ ውስጥ በሙስና የተዘፈቁ  በርካታዎች ስለማይጠፉ ከየዘርፉ ጥቂት ደብለቅ  ቢያደርጉበት መልካም ይሆናል ባይ ነኝ፡፡ ያኔ ሊሆን ይችላል በሙስና ጉዳይ ልባችን የሚረጋው፡፡ ነገር ግን ዛሬ ላይ ደርሶ ከየብሔሩ አንድ ወይም ከአንድ መንግስታዊ ተቋም ከየእርከኑ ጥቂት ሰዎችን በማሰር ሙስናን በቁርጠኝነት እየተዋጋሁ ነው የሚለው ቱማታ ” ከሩጫውና ከሁካታው ቀዝቀዝ”፤ “ዳግም ጥረቱ እንዳይነቅዝ” እንድንል የሚያስገድደን ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን በሙስና ምክንያት አይከፍሉ ዋጋ እየከፈልን ነው፡፡ እለት ተእለት የሚመዘበረው ሃብትም የጥቂት  ነጋዴ ግለሰቦች ሃብት ብቻ ሳይሆን የኛዎቹ በተለይ -ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ የምንገፋውና “ይበሉት እንጂ ይገብሩት አያጡም” በሚል ብሂል ኪሳችንን አራግፈን ግብር የምንገብረው ዜጎች ደም፣ ላብና አጥንት ጭማቂ ነው፡፡ ከሙስና ጋር የተያያዘው መከራችን በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ ኪሳችን መራቆቱ ሳያንስ ስርዓቱ ለሙሰኞችና ለዘራፊዎች አመቻችቶ ሰጥቶናል፡፡ ሙስና ሕገ ውጥ የገንዘብ ዝውውርን በማስፋፋቱ ምክንያት የገንዘባችንን የመግዛት አቅም ተዛብቷል፡፡ ሙስና የወለደው ሃብት አግባብ ባልሆነ መንገድ ሳይለፋበትና ሳይደከምበት  የሚታፈስ በመሆኑ አወጣጡም በግዴለሽነትና በዝርክርክነት የተሞላ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሳይጣሩና ሳይደራደሩ የተጠየቁትን ከፍሎ መሸመትን በግብይት ስርዓቱ ውስጥ አስለምዶብናል፡፡ አቅም የሌለው ቢፈልግ ይገዛ ቢፈልግ አይግዛ የቸርቻሪው ዘይቤ ሆኗል፡፡ እድሜ በሙስና ለተገኝ ሃብት ዓይናቸውን ሳያሹ የሚከፍሉ ሙሰኞች  በገፍ ሞልተዋል፡፡ ሙስና በዜጎች መካከል ከፍተኛ የገቢና የአኗኗር ልዩነት እንዲስፋፋም ምክንያት ሆኗል፡፡ ሙስናው ያለድካም በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እንደዋዛ እንዲታፈስ መንስኤ በመሆኑ በከተማችን ውስጥ የአስረሽ ምችው፣ የዝሙት፣ የስካርና የመሳሰሉት አደገኛ የአኗኗር ዝንባሌዎች እንዲስፋፉ ምክንያት ሆኗል፡፡ የሚዘረፈው ገንዘብም ሕጋዊ ማድረግ እያዳገተ በመምጣቱም የቁጠባ አቅምችንን ቀይዶ ይዞታል፡፡ የቁጠባው ማነስን ተከትሎ መንግስት ገቢውን ለማሳደግ አስገዳጅ ቁጠባን በዜጎች ላይ በተጽእኖ እንዲጭንብን ምክንያት ሆኖል፡፡ ሌላም ሌላም ማለት ይቻላል፡፡

ዛሬም ኢህአዴግና መንግስት እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁላ አንድ ሁለት ቱባ ባለስልጣናት ማሰራቸውን ተመልክተናል፡፡ መልካም ጅማሮ ነው፡፡ ይህም ሆኖ የአሁኖቹ ተጠርጣሪዎች ከቀድሞዎቹ ታሳሪዎች ጋር ሲወዳደሩ በስልጣን ተዋረዳቸው እዚህ ግባ የሚባሉ አንዳይደሉ ኢህአዴጎች ልቦናቸው ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ሙሰኞቹም እነዚህ ብቻ እንዳይደሉም በቅጡ ይረዱታል፡፡ ቁርጠኝነት በስልጣን እርከን የሚለካ ከሆነ እንደ ጠቅላይ ሚኒስቴር ታምራት ላይኔ፣ አንደ አቶ ስዬ አብርሃና አንደ ቀድሞው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ያረጋል አይሸሹም ዓይነቱን ጨምሮ በርካታ ሹመኞች በሙስና ታስረዋል፡፡ ከዚህ በመነሳት ዛሬ በሙስና ተጠርጥረው እስር ቤት የገቡት ባለስልጣናትን ጉዳይ ስናጤን ከዚህ ቀደም ታስረው ከተዳኙትም ሆነ ጉዳያቸው በእንጥልጥል ከሚገኙት ባለስልጣናት ጋር በስልጣን ስፋትና ጥልቀትም ሆነ በተጠረጠሩበት የገንዘብ መጠንና ደረጃ ሲለኩ ለውድድር የሚያሳጫቸውና የተለየ የሚያደርጋቸው አንድም አዲስ ነገር ይዘው አልመጡም፡፡

ምናልባትም መጀመርያውኑ እነዚህን ሰዎች ማን ሾማቸውና ታላላቅና ተፈሪ ሰዎች ተባሉ የሚል ጥያቄ ማንሳት አለብን? እውንስ ኢህአዴግ ትልልቅ ሰዎቼን አስርያለሁ የሚል መከራከርያ ሊያነሳ የሚችልበት መሰረት አለው ወይ? የሚለው ሌላው መሰረታዊ ጥያቄ ነው፡፡ ኢህአዴግ ታላላቅ ባለስልጣናትን አስሪያለሁ ሲል ምን ማለቱ ይሆን ? ታላቅ ናቸው ሲባልስ ከየትኛው ሕዝባዊ መነሻና መሰረት ያገኙት ድጋፍ የተቀዳጁት ታላቅነት ነው የሚወሳው፡፡ ታላቅነታቸው የመነጨው ከሹመታቸው ከሆነ፤ ኢህአዴግ ሹመትን እንደ ሙሰኞቹ መገልገያ እንጂ እንደ ሕዝብ ማገልገያ እንደማይቆጥረው ማሳያ ከመሆን አያልፍም፡፡ አቶ መላኩም ሆነ አቶ ገብረዋህድ በስልጣን እርከን ላይ ከመፈናጠጣቸው በፊት ማን ያውቃቸው እንደነበረ ለመገመት አዳጋች ነው፡፡ እርግጠኛ ባልሆንም በየመኖርያ ሰፈራቸው ሲወጡና ሲገቡ ሕዝብ ከመሸበሩ ውጭ ስማቸውን የሚያስጠራ፤ ኢህአዴግ ከሰጣቸው የታላቅነት ክብር በስተቀር ሕዝባዊ ታላቅነትን የሚያጎናጽፋቸው ስራ ሰርተው እንደነበረ የሚገልጽ “መረጃም ሆነ ማስረጃ” አላገኘንም፡፡ ወጣም ወረደ ሂደቱ ሌላ አይደለም፤ ኢህአዴግ የጠረጠረና ያሰራቸውን ሰዎች የቀድሞ ማንነት በሕዝብ ፊት “ታላቅነት” ስም በማቆለጳጰስ ሙስናውን ለመዋጋት ጀመርኩ የሚለውን ቁርጠኛነት ለማወጅ ከመፍጨርጨር ውጭ ብዙ ርቀት የሚወስድ ስልት ሆኖ አላገኝሁትም፡፡ ውጤቱ እንደ ወትሮው ሁላ እንደ ድመቷ ተረት “ምን ቢታለብ ያው በገሌ” ብቻ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የተጠረጠሩትን ሙሰኞች አስመልክቶ ስንነጋገር ከግምት ውስጥ ማስገባት የሚገባን የኢህአዴግ ሹመኛነታቸው ከፈጠረላቸው ክብርና ሞገስ፤ አልፎ ተርፎ የሚዘመርለት ታላቅነት የላቸውም እንዲያውም ያንን ተከትሎ የተቀዳጁት ታላቅነት ሙስኝነት አበርክቶላቸዋል፡፡ ይህ በመሆኑም ኢህአዴግ አሁንም ከባለስልጣኖቹ ትልቅነት ይልቅ ለሕዝብ ትልቅነት ቅድሚያ መስጠትን አጀንዳው ማድረግ አለበት፡፡

ከላይ በስፋት እንዳነሳሁት ተጠርጣሪዎቹ  ሹመኞቹ በኢህአዴግ ስሌት ከሕዝብ በላይ ታላቅነት ያላቸውና ከሕገ-መንግስቱ በላይ ከፍተኛ ክብርና ሞገስ የተቀዳጁ አድርገው እራሳቸውን እንዲቆጥሩ ያደረጋቸው ሕገ-መንግስትን የሚጥስ መብት ስለተሠጣቸው ነበር፡፡ ለምን ቢባል ነጋዴው ማህበረሰብ ግብርን በወቅቱ ስለማይከፍልና ስለሚያጭበረብር፤ በሕገ-መንግስት ውስጥ የሰፈሩትን የሕግ አውጭውን፣ የሕግ አስፈጻሚውንና የሕግ ተርጓሚውን ሚና የሚያደበላልቅና የሚሸረሽር መመርያ አውጥቷል፡፡ ሹመኞቹም ስልጣኑንና “ታላቅነቱን” በተረዱበት መንገድ ተረድተው “የሚገባቸውን” አድርገዋል፡፡

ኢህአዴግ ከሰው መርጦ ለሹመት፤ … ብሎ ከሕዝብ በላይ ያነገሳቸውንና ያሞላቀቃቸውን ባለስልጣናቱን ተጠራጥሮ ስላሰረ፤ ሕዝብ ሆይ የሚያሰጉኝን ታላላቅ ባለስልጣኖቼን አስሪያለሁ ቢል የሚከተለው መልስ “አንቺው ታመጭው አንቺው..! ”  እንደሚሆን  መገመት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ መንገድ ሄዶ – ኢህአዴግ በራሱ ፈቃድ ትልልቅ ያደረጋቸውን ሰዎች በሙስና ጠርጥሮና አስሮ፤ ታላላቅ ባለስልጣኖቼንም ቢሆን አስራለሁ፤ “ማንንም አልምርም” ቢለን!  ፉከራው ሊዋጥልን አይችልም፡፡ ምክንያቱም ቢያንስ ፉከራው ከዚህ ቀደም ኢህአዴግ ታላላቅ  ባለስልጣኖቹን ለማሰር ይፈራ ነበር እንዴ የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያድርገናል እንጂ ሊያሳምነን አይችልም፡፡
ኢህአዴግ እስካሁን ያልደፈራቸው ስንት የሚያሰጉ ባለስልጣናት እንዳሉት በምን እናውቃለን? እውነታው ይህ ከሆነ ደግሞ በእኔ እምነት ዛሬም ሆነ ነገ ወይም ለዘለቄታው መንግስትና ኢህአዴግ ይህንን ምስቅልቅል እንድንሸከም ላለመፍረዳቸው ምንም ዓይነት ማረጋገጫ ሊሰጡን አይችሉም? በከተማው እንደሚናኘው ወሬ ከሆነ ደግሞ ጉዳዩ የፖለቲካ ወይም የዘረኝነት አለመሆኑን ዓይነት ማስረጃ ማቅረብ አይቻልም? የእነዚህ ቱባ ባለስልጣናት የፍርድ ሂደት እንደተለመደው ዘግይቶና ተልከስክሶ፤ በስተመጨረሻው ላይም ሚሊዮኖቻቸውን ታቅፈው ከጥቂት ዓመታት በኋላ በአመክሮና በይቅርታ ከእስር ተፈተው ኢንቨስተር ሆነው በድጋሚ በዘረፉት ሕዝብ ላይ ላለመሰየማቸው ከጊዜ ውጭ ምን ዓይነት መከላከያና ማረጋገጫ የለንም?

ተጠርጣሪዎቹና ገና በመረብ ውስጥ ያልወደቁት ብጤዎቻቸው የመንግስትን ተቋማትን እጅ ከወርች አስረው የፍትሕ ስርዓቱንና ተቋማቱን በሙስናና ባልተገባ ጥቅማ ጥቅም ተብትበው ሽባ እንዳደረጓቸው፤ እንደ ሕዝብ ሁላችንም እናውቃለን፡፡ መንግስትም ይህንኑ በአደባባይ መስክሮልናል፡፡ ይህ ሁሉ ምስቅልቅል እዚህ እስኪደርስ ድረስ ችላ በመባሉ ምክንያት በሙስና ተዘፍቀው በመገኘታቸው የሚጠየቁትን ባለስልጣናት ጉዳይን ጨምሮ ሙስናን በአጠቃላይ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ለመግታት በመፍትሄነት ለሕዝብ ሊቀርብ የሚገባው አማራጭ ጥቂት ግለሰቦችን ማሰርና ማገለል ብቻ ሊሆን እንደማይችል እውነታው መራራ ቢሆንም ኢህአዴግ ሊዋጥለት ይገባል ባይ ነኝ፡፡ መንግስትና ኢህአዴግ በዚህ መንገድ ቀጥለው የዘረፉንን ባለስልጣናት እያሰሩ በምትካቸው አዳዲስ ዘራፊዎችን በፖለቲካ ዝንባሌያቸው እያሰባሰበ አንጡራ ሃብታችንን ለአዳዲስ ጅቦች በማስተላለፍ የሙሰኞች መሳቂያና መሳለቂያ ሊያደርጉን አይገባም፡፡ ስለዚህም ግለሰቦችን አሳዶ ከማሰር በተጨማሪ ኢህአዴግም ሆነ መንግስት በመጀመርያ ደረጃ አጠቃላይ የሆነ የመዋቅርና የአሰራር ለውጥን ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው፡፡ ቀጥሎም ክትትል ያለበት ተጠያቂነትንና ግልጽነትን የሚያሰፍን አሰራርን መዘርጋት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በመጨረሻም ከፖለቲካ ጥቅመኝነትና ከአምቻ ጋብቻ አሰራር ተላቀው፤ ብቃትና ችሎታን፣ ለሕዝብና ለሃገር ታማኝነትን መሰረት ያደረገ የቅጥርና የሹመት መመዘኛ ተግባራዊ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡

የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የራሱ ፍርድ ቤት፣ የራሱ ፖሊስ፣ የራሱ ደህንነትና የራሱ እስር ቤት የነበረው የአምላክ ታናሽ ወንድም የሆነ ተቋም ነበር፡፡ ተቋሙ ዜጎችን ከሕገ መንግስቱ እውቅና ውጭ ይሰልላል፣ ያስረል፣ ይዳኛል፡፡ እንደዚህ አይነት ተቋም በዜጎች ላይ ያሻውን ያደርግ ዘንድ ሁሉ ነገር የተመቻቸለት ስለሆነ ዜጎች ከፍላጎቱ ውጭ ሊሆኑ አይችሉም፡፡  መንግስትና ኢህአዴግ ከዜጎችም ሆነ በዜጎች ይሁንታ ከጸደቀ ሕገ-መንግስት በላይ ሆኖ ሙስናን ለመፈልፈል አስተማማኝ አቅም የገነባ ተቋም መፍጠራቸው ሙስናን እንደ አደገኛ የሃገርና የዜጎች ደህንነት ጠንቅ አድርገው እንደማያዩት ገላጭ ነው፡፡  የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የታላላቅ ግብር ከፋዮችን ግብር በተለያየ መንገድ በድርድርና በመጠቃቀም መርህ እየቀነሰ፤ አነስተኛ ግብር ከፋዮችን ደግሞ ለአነስተኛ የባለስልጣኑ ሙሰኞች ሲያመቻች እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ቁጥር ስፍር የሌለው ነጋዴ  ለአራጣ አበዳሪ ሲሳይ ሆኖ የስንቱ ሕይወት በከንቱ እንደቀረና የስንቱ ቤት እንደፈረሰ ታሪክና ጊዜ ሁሌም የሚያወሳው ጉዳይ ነው፡፡ መንግስት የራሱን ታላላቅ ሙስኞች እረሱ ተዋጋ መንግስት በሾማቸው ሙሰኞች ሕይወታቸው በከንቱ ያለፈ፣ ለበሽታ የተዳረጉና የትም የቀሩ ዜጎችን ደምና እንባ ማን ያብስ?

Share