አቶ ልደቱ ከአዲስ አድማስ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ

ቀጣዩ ምርጫ አንድ አመት ብቻ ነው የቀረው… ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ አንድነት ቢኖር ጥሩ ነበር፡፡ ችግሩ ግን በተቃዋሚ ጐራ ውስጥ የመቻቻል አዝማሚያ የለም፡፡ አንዳንዱ ታቃዋሚ ከሱ የተለየ አመለካከት የምታራምድ ከሆነ አሉባልታ ያስወራል፤ ጥላቻ ያራምዳል፡፡ ይሄ የሚያሳየው ከእኔ አመለካከትና መስመር ውጭ ማራመድ አይቻልም የሚል ስሜታዊ የፅንፍ አስተሳሰብ መያዙን ነው፡፡ በእንደዚህ አይነት አስተሳሰብ ደግሞ፣ መቻቻልን መፍጠር አይቻልም፡፡ በዚህ ረገድ በ2007 ዓ.ም ምርጫም ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጣል ብዬ አላስብም፡፡
ኢዴፓን በሚመለከት ፓርቲያችን ብቻውን ተዓምር ይፈጥራል የሚል እምነት የለኝም – የፓርላማና የክልል ምርጫ ላይ፡፡ ከፍተኛ ውጤት ሊያመጣ ይችላል ብዬ የማምነው የ‹‹ሶስተኛ አማራጭ››ነት ሚናውን በማጉላት ነው፡፡ ምክንያታዊ ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ምትክ የሌለው ምርጫ መሆኑን፤ እንዲሁም ገዢው ፓርቲና አብዛኛው የተቃዋሚ ጐራ እስካሁን የተጓዝንበት መንገድ እንደማይበጀን በማሳየት ረገድ ኢዴፓ ትልቅ ውጤት ያመጣል ብዬ አምናለሁ፡፡ በአግባቡ ከተጠቀምንበት፣ ሃሳባችንን ህብረተሰቡ ጋ ካደረስን፣ አጀንዳችንን በግልጽ ማስረዳት ከቻልን፣ የማይናቅ ውጤት እናመጣለን ብዬ አስባለሁ፡፡ የተወሰኑ መቀመጫዎችን ማሸነፍም እንችላለን፡፡
Far-sighted politician.