Logo

የዓረና አመራሮች በመደብደባቸው ምክንያት ሕዝባዊ ስብሰባ መሰረዛቸውን ገለጹ

January 29, 2014

ሪፖርተር – በትግራይ ክልል ሕጋዊ ዕውቅና አግኝቶ በተቃዋሚነት እየተንቀሳቀሰ ያለው ዓረና ትግራይ ፓርቲ፣ በአዲግራት ከተማ ሊያካሂደው ላሰበው ሕዝባዊ ስብሰባ አባላቱ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ ሳሉ በመንግሥት አደራጅነት በሠፈር ልጆች በመደብደባቸው ስብሰባውን ለመሰረዝ መገደዱን አስታወቀ፡፡

ዓረና ትግራይ በቅርቡ በመቐለ ከተማ ባካሄደው ሦስተኛ ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ያስተላለፋቸው ውሳኔዎችን ለሕዝብ ለማሳወቅ በክልሉ ተከታታይ ሕዝባዊ ስብሰባዎች ለማድረግ ዕቅዱ ነበር፡፡ በመሆኑም ቀደም ሲል በውቅሮ፣ በዓብይ ዓዲና በማይጨው ሕዝባዊ ስብሰባዎች አካሂዷል፡፡ ጥር 18 ቀን 2006 ዓ.ም. በዓዲግራት ሊያካሂድ ባቀደው ተመሳሳይ ስብሰባ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ አባላት ወጣት አብርሃ ደስታ፣ መሥራቹ አቶ አስገደ ገብረ ሥላሴ፣ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ወጣት ዓምዶም ገብረ ሥላሴና ሌሎች የፓርቲው አባላት ሕዝቡን ለመቀስቀስ ሲመጡ ድብደባ እንደደረሰባቸው ፓርቲው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ወጣት አብርሃ ደስታ ጉዳዩን አስመልክቶ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ ቀደም ሲል አዲግራት ከተማ አቅራቢያ በሚገኙት በእፀጋ ሐሙስና በፋፂ ከተሞች በመቀስቀስ ላይ ሳሉ ችግር ገጥሟቸው ነበር፡፡ ዓርብ አመሻሽ ላይ የፓርቲው አባላት በከተማው በመቀስቀስና ወረቀት በመበተን ላይ ሳሉ፣ ዕድሜያቸው ከ12 እስከ 16 የሚገመት ቁጥራቸው ወደ 50 የሚጠጉ ታዳጊዎች ተሰብስበው አባላቱ የሚበትኑትን ወረቀት እየቀደዱ፣ በአባላቱ ላይ የአካል ድብደባ እንዳደረሱባቸው አስረድቷል፡፡ በቅስቀሳ ላይ በነበሩት በዓረና ትግራይ ፓርቲ አባላት ላይ አፈር በመበተንና በመትፋት፣ እንዲሁም ድንጋይ በመወርወር ጉዳት እንዳደረሱባቸው ገልጿል፡፡ ይህ ሲፈጸም የአካባቢው አስተዳዳሪዎችና ካድሬዎች ጭምር እየተመለከቱ እንደነበሩ፣ ለታዳጊዎቹ መብታቸው መሆኑን በመንገር ሞራል መስጠታቸውን አብርሃ አስረድቷል፡፡ በፕላስቲክ የታሸገ አፈርና ድንጋይ የሚያቀብሉ ትልልቅ ሰዎች መኖራቸውንም አክሎ አስረድቷል፡፡

ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

Share