Logo

ግልፅ ደብዳቤ ለክቡር ዶ/ር ቴድሮስ ኣድሃኖም

February 5, 2014

Dr. Tedros Adhanom
Dr. Tedros Adhanom

ግልፅ ደብዳቤ ለክቡር ዶ/ር ቴድሮስ ኣድሃኖም
የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር

በቅድሚያ ክቡርነትዎ በጤና ሚንስትርነትዎ ጊዜ በሠሩት መልካም ስራ ምክንያት የብዙሃን ኢትዮዽያውያን እናቶችና ህፃናት ህይወት ማትረፍ በማስቻልዎ ለሌሎች ሃገራትም ኣርኣያ የሚሆን መከላከል ላይ ያተኮረ የጤና ስርዓት በመዘርጋትዎ ላመሰግንዎ እወዳለሁ። ወደ ውጭ ጉዳይ ሚንሰትርነት ከተዛወሩም በሁዋላ በብዙ ኣገራዊ ጉዳዮች ከልብ በመቆርቆር ደፋ ቀና ሲሉ በማየቴ፤ እንዲሁም በኣነጋገርዎም ሆነ በተግባርዎ ከብዙ የኢህኣዴግ ባለስልጣናት በተለየ ኢትዮዽያዊ ጨዋነት የሚታይብዎ በመሆንዎና ከፖለቲካዊ ጥቅም ይልቅ የኣገርና የህዝብ ፍቅርን የሚያስቀድሙ ሆነው ስለታዩኝ ከዚህ በታች የማነሳቸውን ሁለት ጉዳዮች በቅን ልቦናዎ እንዲመለከቱልኝ እማፀንዎታለሁ።

1.      የመጀመሪያው ከሳውዲ ኣረቢያ በግዳጅ እንዲመለሱ የተደረጉ ኢትዮዽያውያንን በተመለከተ ነው።

የሳውዲ ኣረቢያ መንግስትና ኣንዳንድ ሰብኣዊነት የጎደላቸው የሳዑዲ ዜጎች በወገኖቻችን ላይ ያደረሱት ኢሰብኣዊ ተግባር ምን ያህል እንዳሳዘነዎ በተለያዩ የሚዲያ ተቁዋማት በተላለፈው አንድ ንግግርዎ ላይ ታዝቤያለሁ። ከዚያም በሁዋላ በድርጊቱ የተጎዱ ወገኖቻችንን ወዳገራቸው ለማስመለስ ቀን ተሌት መድከምዎን ኣይተናል። ሆኖም ግን እኚህ ወገኖቻችን የደረሰባቸው በደል እንዲካስ ምንም ኣይነት ህጋዊ ጥረት መስሪያ ቤትዎ አለማድረጉ ብዙ ኢትዮዽያውያንን ያሳዘነ ነው። ጉዳዩ በቅርቡ በተካሄደው የኣፍሪካ መሪዎች ጉባኤ አለመነሳቱ መስሪያቤትዎ ለኢትዮዽያውያን ያለውን ክብር ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ነው።  ኣንድ ኣገር ሕጋዊም ሆነ ኢሕጋዊ በሆነ መንገድ የመጡበትን ስደተኞች የማስወጣት ሙሉ መብት ቢኖረውም ስደተኞቹን እንደሰብኣዊ ፍጡር ማስተናድ ይኖርበታል። ህጋዊም ሆነ ሕጋዊ ያልሆነ ስደተኛ ሰብአዊ ክብሩ ሊዋረድ ኣይገባውም፣ ያፈራውን ሃብትና ንብረት ሊነጠቅ ኣይገባውም። ሃላፊነት የሚሰማው መንግስት የዜጎቹን ውርደት በይሁንታ ሊቀበል ኣይገባውም፤ የዜጎቹንም መብት ለማስከበር ህጋዊም ዲፕሎማሲያዊም ጥረት ሊያደርግ ይገባዋል። ስለሆነም መስሪያ ቤትዎ  በተባበሩት መንግሰታት ምክርቤትና በሌሎች ኣህጉራዊና አለምኣቀፍ ተቁዋማት በኩል የሳውዲ መንግስት ተገቢውን ካሳ ይከፍል ዘንድ እንዲሁም ላደረሰው በደል በይፋ ይቅርታ ይጠይቅ ዘንድ ተፅእኖ ማድረግ ይገባዋል። ከህጋዊ መንገድ በተጨማሪ መንግስትና ህዝብ በጋራ በተለያዩ መድረኮች ተፅእኖ ማድረግ ይገባቸዋል። ክቡርነትዎ ይህን ጉዳይ በቀና ልብዎ እንዲመለከቱ እጠይቅዎታለሁ።

2.     ሁለተኛው በኢትዮዽያና በኤርትራ መንግስታት መካከል ያለውን ግንኙነት በተመለከተ ነው።

ሰሞኑን የቀድሞ የዩናየትድ ስቴትስ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ተከታታይ ፅሁፎች አውጥተዋል። ከነኚህም ኣምባሳደር ኸረማን ኮህን፣ ኣምባሳደር ዴቪድ ሺን፣ ኣምባሳደር ፕሪንሰተን ሊይማን የሚጠቀሱ ናቸው። የነኚህ ተከታታይ ፅሁፎች ይዘትና መልእክት ዩናየትድ ስቴትስ ኢትዮዽያን ፣ ኤርትራንና የኣፍሪካ ቀንድን በተመለከተ የፖሊሲ ለውጥ እንድታደርግ የሚገፉፋ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ያመላክታል። የአሜሪካውያኑ ዲፕሎማቶች መልእክቶች ጥቅል መልእክት የኤርትራን ህዝብ ከችግር ለማውጣት የኢትዮዽያም ሆነ የኤርትራ መንግስታት የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ እንዲቀበሉና እዲፈፅሙ  ማሳሰብ ነው።፡ ለድንበር ኮሚሽኑ መቁዋቁዋም መሰረት የሆነው ደግሞ ባለ አምስት ነጥቡ የአልጀርስ ስምምነት መሆኑን ክቡርነትዎ ጠንቅቀው ያውቃሉ። የአልጀርስ ስምምነት ከመነሻው በአብዛኛው ኢትዮዽያውያን ተቀባይነት ያላገኘ ከመሆኑ በተጨማሪ ስምምነቱ ተፈርሞ ቀለሙ ሳይደርቅ ኣብዛኞቹ የስምምነቱ ነጥቦች በኤርትራ በኩል መጣሳቸው የሚታወቅ ነው። በዚህ መሠረት ክቡርነትዎ በዚህ ጉዳይ የሚከተሉትን ሁለት ጉዳዮች እንዲመለከቱ በትህትና እጠይቃለሁ።

1.      የአልጀርስ ስምምነት የኢትዮዽያን ጥቅም የማያስጠብቅ በመሆኑ እንዲሁም በሁለቱም ወገኖች በመጣሱ ውድቅ ተደርጎ የሁለቱንም ወገኖች መሰረታዊ ጥቅም የማይጎዳና ዘላቂ ሰላምና እድገት ሊያመጣ የሚችል ሁሉን አቀፍ አዲስ ስምምነት እንዲፈጠር መጣር

2.     የኢትዮዽያን የባህር በር የማግኘት ጥያቄ ከኤርትራ ጋር የሚደረጉ ማናቸውም ድርድሮች ዋነኛ ጥያቄ እንዲሆን ማድረግ

ክቡር ዶ/ር ቴድሮስ ኣድሃኖም፤ የኤርትራንም ሆነ የኢትዮዽያን ህዝብ በውስጣቸው የኖሩ በመሆንዎ ከእርስዎ በተሻለ የሚያውቃቸው ኣይኖርም። ለሁለቱም ህዝቦች መልካም እንዲገጥማቸው እንደሚመኙም ጥርጥር የለውም። የኢትዮዽያን ሉኣላዊ የባህር በር መብት ያላስጠበቀ ማንኛውም ስምምነት ደግሞ ዘለቂ ሰላምም ሆነ መልካም ጉርብትና ያመጣል ብሎ ማሰብ የዋህነት ይሆናል።

ኢትዮዽያዊ ታናሽ ወንድምዎ

መርስኤ ኪዳን

ከሜኔሶታ ሀገረ አሜሪካ

mersea.kidan@gmail.com

(PDF version)

Share

5 comments on “ግልፅ ደብዳቤ ለክቡር ዶ/ር ቴድሮስ ኣድሃኖም

  1. የኢትዮጵያን ጥቅም በማስጠበቅ በኩል መቼም የአሁኑ ኢህአዴግ ከበፊቱ ኢህአዴግ እንደሚሻል ብዙ አመላካች ነገሮች አሉ። ከዚህ በመነሳት የኢትዮጵያንና የኤርትራን ጉዳይም በሚመለከት ኢህአዴግ ከእንግዲህ ወዲያ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዳ ነገር ይፈጽማል የሚል እምነት የለኝም። ቀደም ብሎ የተሰሩ ስህተቶችን ማረም ግን በጣም ከባድ እንደሚሆን መገመት አይከብድም።

  2. I am not sure if normalisation with Eritrea is possible because most of the Diaspora Eritreans I get are so negative about Ethiopia which convince me to believe that these people wish bad things to happen to Ethiopia.

  3. In 2001 five opposition parties namely All Amhara People’s Organization, Council of Alternative Forces for Peace and Democracy in Ethiopia, Ethiopian Democratic Union Party and Ethiopian Democratic Party sent a letter to Secretary General of the U.N rejecting the Algiers agreement.

    Ethiopian Democratic Party went further by holding big demonstration in Addis Ababa and also collecting and sending to the U.N. hundred thousands of petitions. The government responded by labeling the parties as as anti-peace.

    Why Ethiopian Government had that stance at the time is still a puzzle to me.

Comments are closed