Logo

“ከባዶ ጭንቅላት ባዶ እግር ይሻላል”

February 26, 2014

ከፍቅሩ አየለ በላይ

ይህ ጽሑፍ ዛሬ በታተመው 9ኛ ዓመት፣ ቁጥር 442፣ ሰንደቅ ጋዜጣ ላይ ታትሟል፡፡ ጋዜጣውን የማያገኙ፣ በተለይም በውጭ ሀገር ያሉ ዜጎች ሁሉ ቢያነቡት ‘ይጠቅማል’ በሚል መንፈስ በዚህ ድረ-ገጽ በኩል እንዲታተም ተልኳል)

ሰንደቅ ጋዜጣ ባለፈው ሳምንት እትሟ ትኩረት ከሰጠቻቸው ጉዳዮች አንዱ የአማራ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ አለምነው መኮንን “ተናግረውታል” የተባለውን ንግግርና ያስከተለውን ውዝግብ በተመለከተ ነው፡፡ በጋዜጣው ላይ ከቀረበው ማብራሪያ በተጨማሪ አቶ አለምነው ራሳቸው በአማራ ክልል ቴሌቪዥን የሰጡትንም ማብራሪያ ካዳመጥኩ በኋላ ይህቺን ማስታወሻ ከተብኩ፡፡

የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውም በዚሁ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በቴሌቪዥን እንዳየሁት አቶ ገዱ የአቶ አለምነውን በጎ ተግባራት በመጥቀስ ከማሞካሸትና በደፈናው ሕዝብን አለመሳደባቸውን ከመናገር ውጪ አቶ አለምነው ተናገሩት የተባለውን ቃል ጠቅሰው “ይህንን አላለም” የሚል ምስክርነት አልሰጡም፡፡ እሳቸው የሚሉት “አቶ አለምነው የክልሉ ሕዝብ ሕይወት እንዲለወጥ ሌት ተቀን የሚሰራ ነው” ነው፡፡ በመሰረቱ ለሀገር ልማትና ለሕዝብ ተጠቃሚነት ሌት ተቀን የሚሰራ ሰው አፍ እላፊ ንግግር አይናገርም፣ ስህተት አይሰራም ብሎ መደምደም አስቸጋሪ ነው፡፡

በሀገራችን፤ በተለይ ባለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የወጡ የፖለቲካ ልሒቃን በማንነታቸው ዙሪያ ተደራጅተው በመታገላቸው የመጡበትን ማህበረሰብ መብትና ጥቅም አስጠብቀዋል፡፡ በማንነቱ እንዲኮራ አድርገዋል፡፡ በቋንቋው እንዲናገር፣ እንዲማር፣ እንዲዳኝ አድርገዋል፡፡ ሌሎችንም መብትና ጥቅሞች አስገኝተውለታል፡፡ በአማራው ሕዝብ ስም የተደራጀው ብአዴን ግን ለአማራው ሕዝብ ምን ጥቅም አስገኘለት? የትኛውን መብት አጎናጸፈው? የነዚህ ጥያቄዎች መልስ ጥልቅ ምርምርን የሚጠይቅ መስሎ ነው የሚታየኝ፡፡

አበው ‘ጽድቁ ቀርቶብኝ በወጉ በኮነነኝ’ እንዲሉ በኔ እይታ ብአዴን ለአማራው ሕዝብ ካስገኘው ጥቅም ይልቅ ያደረሰው በደል ያመዝናል፡፡ አንዳንድ የሀገራችን የፖለቲካ ልሂቃን “ከዚህ ወርቅ ሕዝብ በመፈጠሬ ደስተኛ ነኝ” በማለት ራሳቸው ኮርተው የወጡበትን ማሕበረሰብ የሚያኮራ ንግግር ሲያደርጉ፤ የብአዴን አንዳንድ መሪዎች ግን ከአቶ ታምራት ላይኔ ጀምሮ የገዛ ወገናቸውን ሰድበው ለሰዳቢ የሚሰጡበት ሁኔታ ብዙ ጊዜ ታይቷል፡፡

የምኒልክን የግዛት ማስፋት እንቅስቃሴ ፊት አውራሪ ሆኖ የመራውና ያስፈጸመው ነፍጥ አንጋቹ የምኒልክ የጦር ሰራዊት ከአማራውም፣ ከኦሮሞውም፣ ከጉራጌውም፣ ከትግሬውም፣ ከሌላውም አካባቢ ማህበረሰብ የተውጣጣ ሆኖ ሳለ፤ “ነፍጠኛነት” የአማራው ሕዝብ መለያ ምልክቱ እንዲሆን ብአዴን ግንባር ቀደም ሚና አልተጫወተም ብሎ ለመናገር በበኩሌ ድፍረት የለኝም፡፡ የአማራው ብሔር ለዘመናት ከኖረበት የተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች፣ ያፈራትን ንብረት በትኖ እንዲፈናቀል ሲደረግ የአማራው ወኪል ነኝ የሚለው ብአዴን አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ ሆኖ ከማለፍ ውጪ አለኝታነቱን አላሳየም፡፡

ብአዴን እንዲህ ያሉ የተሳሳቱ ሁኔታዎች እንዲታረሙና የአማራው ብሔር እንደ ሌሎች የሀገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች መብትና ጥቅሙ እንዲጠበቁለት ከማድረግ ይልቅ የአንዳንድ መሪዎቹ ግንባር ቀደም ተሳዳቢነት ላለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት አማራውን ሲያቆስለው ኖሯል፡፡ ስድቡና ዘለፋው እስከ አሁንም ሊቆም አልቻለም፡፡

የአዲሱ ትውልድ አመራር አካል እንደሆኑ የሚነገርላቸው አቶ አለምነው ከሃያ ዓመታት በላይ የተሄደበትን የተሳሳተ መንገድ ማስተካከል ሲገባቸው ሰሞኑን እንደተናፈሰው “የአማራው ሕዝብ ሰንፋጭ የሆነ ትምክህተኛነት የተጠናወተው በመሆኑ በቤንሻንጉልና በሌሎችም ቦታዎች ለመሰደዱ ምክንያት ሆኖታል፡፡… በባዶ እግሩ እየሄደ የሚናገረው ንግግር ግን መርዝ ነው… አማራው የትምክህት ለሃጩን ማራገፍ አለበት፡፡ ይሄ ለሃጭ ሳይራገፍ በጋራ መኖር አይቻልም” ብለውት አረፉ!

አቶ አለምነው ይህንን አባባል ብለውታል አላሉትም የሚለውን በተመለከተ በግል ያለኝን እይታ ወደኋላ እመለስበታለሁ፡፡ ከዚያ በፊት አንድ ነገር ላስቀድም፡፡ አቶ አለምነው ተናገሩት የተባለውን ተገቢ ያልሆነ፣ ነውረኛ ንግግር ለማስተባበል በአማራ ክልል ቴሌቪዥን ቀርበው የተናገሩት ሃሳብ የባሰ ግምት ላይ የሚጥላቸው ሆኖ ነው የታየኝ፡፡ እንዲህ ነበር ያሉት “ተቃዋሚዎች ኮምፒዩተር ተጠቅመው፣ በተለያየ ሁኔታ የተናገርኩትን ቆርጠውና ቀጥለው፣ ያላልኩትን እንዳልኩ አድርገው አቀረቡት” ይላሉ፡፡

በበኩሌ፤ ከዚህ የአቶ አለምነው አባባል ሁለት ነገሮችን ተገንዝቤአለሁ፡፡ አንደኛ፡- አቶ አለምነው ስለኮምፒዩተር ምንም ዓይነት ግንዛቤ የሌላቸው መሆኑን፣ ሁለተኛ፡- በርግጥም አቶ አለምነው ያንን ሃሳብ መናገራቸውን ፍንጭ የሚሰጥ መሆኑን ተገንዝቤአለሁ፡፡ ሁለቱንም ሃሳቦች እንደሚከተለው ፈታ አድርጌ ላብራራ፡፡

ስለ ኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ በቂ ግንዘቤና እውቀት ያላቸው ሰዎች እንደሚሉት (እኔም ላለፉት 20 ዓመታት የኮምፒዩተር ተጠቃሚ በመሆኔ ባለኝ ግንዛቤ) ኮምፒዩተር ላዩ ላይ በተጫነው ፕሮግራም (Application Software) አማካይነት የሰው ልጅ የሚሰጠውን ትእዛዝ ይፈጽማል እንጂ የሰውን ድምፅ አይፈጥርም፡፡ ያልተነገረን ንግግር አስመስሎ አያፈልቅም፡፡ “ተቃዋሚዎች በተለያየ ሁኔታ የተናገርኩትን ቆርጠው ቀጠሉ” የሚለውን በተመለከተ ለተቃዋሚዎች በነበረኝ ቀረቤታ ተቃዋሚዎች አቶ አለምነው በተናገሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህንን ለማድረግ አቅም የሌላቸው መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ደግሞስ ተቃዋሚዎች ያን ያህል ችሎታና ብቃት ቢኖራቸው፤ እዚህ ግባ የሚባል ታዋቂነት በሌላቸው አቶ አለምነው ላይ ከማድረግ ለምን በሌሎች አመራር አባላት ላይ አላደረጉትም?

እናም፤ አቶ አለምነው ከብት ባልዋለበት ኩበት እንደማይለቀም ሁሉ ፍፁም ያልተናገሩት ቃል በኮምፒዩተር ሊቀነባበር አይችልምና ነገሩን ለማስተባበል የሄዱበት መንገድ የበለጠ ትዝብት ላይ የሚጥልዎት ከመሆኑም በላይ በትክክልም ቃሉ ከእርስዎ አንደበት የወጣ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡

በርግጥ አቶ አለምነውም “በተለያዩ ሁኔታዎች የተናገርኳቸው ቃላት ተለቅመው ተቀናበሩ” ነው እንጂ ያሉት “ቃሎቹ ከአንደበቴ አልወጡም” አላሉም፡፡ በኔ እምነት ግን በየትኛውም ሁኔታ ቢሆን እነዚያ የተለቀሙ ቃላት አንድን ክልል ከሚመራ ሰው አንደበት መውጣት የሚገባቸው ቃላት አልነበሩም፡፡ ምንም ይሁን ምን ሕዝብን እንደ ሕዝብ መስደብ፣ ማንጓጠጥ፣ ማላገጥ፣… ነውር ነው፡፡

ከሁሉም በላይ እኔን የከፋኝ ደግሞ ትምክህትን በባዶ እግሩ ከሚሄደው አርሶ አደር ጋር ማያያዛቸው ነው፡፡ የእርሳቸውን ቃል ልጠቀምና የሚራገፈው የትምክህት “ለሃጭ” ያለው እንደ እርሳቸው ከረቫት ያበተ የአማራ ልሒቃን (ከልሒቃኑም የፖለቲካ ልሒቃኑ) አካባቢ ይመስለኛል፡፡ ባለ ባዶ እግሩማ እንደ እርሳቸው ያሉ “ዝሆኖች” የሚራገጡበት ሣር ነው!!!

አማራው፤ በምኒልክ ዘመን ወደ ምስራቅ፣ ደቡብ እና ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢ ነፍጥ አንግቶ የሔደው የዘመኑ የፖለቲካ ልሒቃን (ምኒልክና በዙሪያቸው የተኮለኮሉት የሸዋ መኳንንት) ለፖለቲካ ዓላማቸው ሲሉ ወንድሞቹንና እህቶቹን እንዲወጋ ስላስገደዱት፣ ያንን ባያርደርግ ባርነት የማይቀርለት መሆኑን በመገንዘብ እንደነበር አስባለሁ፡፡ በዚህ ወቅት ወደ ጉራ ፈርዳ ወረዳ የሚወርደውም ሆነ ወደ ቤንሻንጉል የሚያቀናው ደግሞ አሁን ስልጣን የያዙት የአማራ ልሒቃን (እነ አቶ አለምነው) ሕይወቱን ሊለውጡለት ስላልቻሉ ቁራሽ በልቶ፣ ቆሎ ቆርጥሞ ማደር ስላቃተው ጓዙን ጠቅልሎ “በቀተ” እንጂ ባለ ባዶ እግሩ ያገሬ ሰው እትብቱ የተቀበረበትን ቀዬ ትቶ መሰደድን ወዶና ፈቅዶ ያደረገው እንዳልሆነም እገነዘባለሁ፡፡

አቶ አለምነውስ ሰው ናቸውና ለስጋቸው በማድላት በአንደበታቸው የተናገሩትን ሽምጥጥ አድርገው ክደው አስተባበሉ እንበል፡፡ እኔን የገረመኝ ድርጅታቸው ብአዴን ነው፡፡ ያንን ሃሳብ ሰው አምኖ ይቀበለዋል ብሎ በቴሌቪዥን ደግሞ ደጋግሞ እንዲሰራጭ ማድረጉ የሚያስተዛዝብ ነው፡፡ ደግሞስ የብአዴን መሪዎች አቶ አለምነው በስልጠናው ላይ የተናገሩትን ቃል በቃል ሳያውቁት ቀርተው ነው እንዲያ ያለው የክህደት ቃለ ምልልስ በቴሌቪዥን እንዲተላለፍ የፈቀዱት?

ቆርጦ መቀጠልን በተመለከተ ማንም የኮምፒዩተር እውቀት ያለው ሰው ሊያደርገው ይችላል፡፡ ድምፅን መፍጠር ግን አይችልም፡፡ ከአቶ አለምነው አንደበት ያልወጣን ቃል ግን በፍፁም በፍፁም መፍጠር አይችልም፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን ቆርጦ የመቀጠል ስራ ተቃዋሚዎች ናቸው ያደረጉት የሚለውን በበኩሌ ለመቀበል ይቸግረኛል፡፡ ለመሆኑ አቶ አለምነው ይህንን ያሉት ተቃዋሚዎች ለመሆናቸው ምን ማረጋገጫ ይዘው ነው? ወይስ ተቃዋሚዎች “ጠላቶች” ስለሆኑ ይህንን ከማድግ አይመለሱም ብለው በማሰብ? በኢሳት ለቀረበ ዜና ሁሉ ምንጩ ተቃዋሚዎች ናቸው ብሎ መደምደምም ትክክል አደለም፡፡

አቶ አለምነው፤ እኔ ግን ከተቃዋሚዎች ይልቅ ሌላ ጥርጣሬ አለኝ፡፡ እንደሚታወቀው በዚያ ስብሰባ ላይ የነበሩት ነባርና ጀማሪ የብአዴን አባላት ናቸው ተብሏል፡፡ ይህ እውነት ከሆነ በዚያ ስብሰባ ላይ አንድም የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ወይም ደጋፊ የለም ማለት ነው፡፡ ስለሆነም፤ ያንን የአቶ አለምነውን ንግግር የቀዱት የብአዴን አባላት ናቸው ማለት ነው፡፡ ብአዴን ውስጥም ይሁን ሌላ ፓርቲ ውስጥ የውስጥ ሽኩቻና የስልጣን ሽሚያ መኖሩ ደግሞ ጥርጥር የለውም፡፡ እና ይህንን የተንኮል ስራ የሰሩት የብአዴን አባላት ላለመሆናቸው ምን ማረጋገጫ ይኖራል?

ተቃዋሚዎች በአቶ አለምነው ላይ ሴራ እንዳልሸረቡ ለማሳየት አሁንም ሌላ ሃሳብ ልጨምር፡፡ አቶ አለምነው በሰጡት የቴሌቪዥን ማብራሪያ ላይ ስልጠናውን ለአራት ቀናት መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዘው በኮምፒዩተር የተቀናበሩት ቃላት በአራቱ ቀናት ካደረጉት ንግግር ተወስዶ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ታዲያ ተቃዋሚዎች አራት ቀናት ሙሉ በብአዴን ስብሰባ ላይ ቁጭ ብለው የአቶ አለምነውን ንግግር ሲቀዱ ነበር ማለት ነው? ተቃዋሚዎች ጠንቋይ የሚቀልቡ ካልሆነ በስተቀር አቶ አለምነው እንደዚያ ዓይነት ተገቢ ያልሆነ ንግግር እንደሚናገሩ በምን አውቀው ለመቅዳት ይጠባበቃሉ? ለመሆኑ የአራት ቀን ንግግር የሚቀዳ መሳሪያስ ይኖራቸዋል?

ጥሩ! መቀዳቱም ተቀዳ እንበል፡፡ ከአራት ቀን ንግግር ላይ መጥፎ የሚባሉ ቃላትን መርጦ ለማቀናበር እኮ በቂ ጊዜና መሳሪያ ያስፈልጋል፡፡ በእኔ እምነት በቢሮአቸው የረባ ኮምፒዩተርና ባለሙያ የሌላቸው ተቃዋሚዎች (አንዳንዶቹ እንዲያውም በባህር ዳር ቢሮ ያላቸው አይመስለኝም) ይህንን ያደርጋሉ ብዬ ለመቀበል ይቸግረኛል፡፡ በዚያ ላይ እንኳን አቶ አለምነውን የአዲሱን የክልሉን ፕሬዝዳንት የአቶ ገዱን ስም በቅጡ የማያውቁ ተቃዋሚዎች ይህንን ያደርጋሉ ማለት ድመትን በቆሎ መጠርጠር ሆኖ ነው የታየኝ!

ታዲያ ይህንን ሴራ ማን አቀናበረው? በበኩሌ ተቃዋሚዎች በአቶ አለምነው ላይ ሴራ ጎንጉነዋል የሚለውን አምኖ ከመቀበል ይልቅ በአቶ አለምነው ላይ ሴራ ያቀናበሩት ራሳቸው የብአዴን አባላት ናቸው ብሎ መቀበል ለእውነት የቀረበ ሆኖ ይታየኛል፡፡ አመነውም አላመነው እውነቱ ወደዚህ አቅጣጫ ነው የሚያመለክተው፡፡ ይሄ ደግሞ በብአዴን ውስጥ አለ እየተባለ “በጭምጭምታ” የሚወራውን የስልጣን ሽኩቻና ቡድናዊ ስሜት የሚያመላክት ይመስለኛል፡፡

ይህንን ጥርጣሬ ለማጠናከር አንዳንድ ጥያቄዎችን ልጨምር፡፡ እውነት ብአዴን አመራር ውስጥ ሸዋ፣ ወሎ፣ ጎንደር፣ ጎጃም፣ አገው፣… የሚል ጠባብ (ጎጠኛ) አስተሳሰብ የለም? ቡድናዊ አመለካከት የለም? “የወንዜ ልጅ” የሚል መንደርተኛ መሰባሰብ የለም? የብአዴን ሊቀ መንበር አቶ ደመቀ መኮንን ሀሰን፣ የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ አለምነው መኮንን፣… ከአንድ አካባቢ የመጡ መሆናቸው የፈጠረው ነገር የለም?… እንዲህ ያለው ሁኔታ በአጋጣሚም ይሁን ሆን ተብሎ፤ ሁኔታው ያናደዳቸውና ያበሳጫቸው ሰዎች ብአዴን ውስጥ ሊኖሩ እንደሚችሉ መጠርጠር የፖለቲካ ጠቢብነትን የሚጠይቅ አይመስኝም፡፡

እናም አቶ አለምነውም ሆኑ ብአዴን ጣታቸውን ተቃዋሚዎች ላይ ከመቀሰራቸው በፊት ዙሪያ ገባቸውን ቢቃኙ መልካም ነው እላለሁ፡፡ ካንጀት ካለቀሱ እንባ አይገድም እንዲሉ፣ ብአዴን እውነቱ እንዲወጣ ፍላጎት ካለው ይህ ንግግር ማን፣ ከየት፣ በየትኛው ኮምፒዩተር ወይም ሞባይል ጭምር እንደላከው ማረጋገጥ የሚያዳግተው አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ማንኛውም የመረጃ ልውውጥ የሚያልፈው በቴሌ ሰርቨር በኩል ስለሆነ ይህንን ማወቅ አስቸጋሪ አይሆንም፡፡

በአጠቃላይ፤ ፖለቲከኞች በአደባባይ የሚያደርጉት ንግግር ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ አቶ መለስ ነፍሳቸውን ይማረውና በአንድ ወቅት “ባንዲራ ጨርቅ ነው” በማለታቸው እድሜ ልካቸውን ሲወቀሱ ኖሩ፡፡ በርግጥ ባንዲራ ብረትም እንጨትም አደለም፡፡ እናም፤ ጨርቅ መሆኑን ማንም አይክደውም፡፡ በ1923 ዓ.ም በወጣው የአፄ ኃ/ስላሴ ሕገ መንግስትም ላይ ጨርቅ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ግን አቶ መለስ የሀገር መሪ ስለነበሩ እንደዚያ ዓይነት ንግግር (ነገሩ እውነትም ቢሆን) ከፖለቲካ አኳያ ስህተት (politically incorrect) ተደርጎ ነው የተወሰደው፡፡ አንድን ጉዳይ ፖለቲከኛ ሲናገረውና ተራው ዜጋ ሲናገረው ልዩነት አለውና!!!

አቶ አለምነው ያቀረቡት ሃሳብ እንደ ሃሳብ ትክክል ቢሆን እንኳ፣ ከፖለቲካ አኳያ ስህተት (politically incorrect) ነው፡፡ ሰውየው ብልህና ብልጥ ፖለቲከኛ ቢሆኑ ኖሮ ይህንኑ ሃሳብ በጥሩ ቋንቋ፣ ሳይሳደቡ ማቅረብ ይችሉ ነበር፡፡ ታዲያ ምን ያደርጋል የተቀመጡበት ወንበር ሰውየውን ዝሆን አድርጎ አሳበጣቸውና ፊት ለፊታቸው ተቀምጠው የሚያደምጧቸውን ሰዎች ትንኝ ሆነው እንዲታዩዋቸው አደረጋቸው፡፡ እናም በንቀት የተሞላ ንግግራቸውን ባልተሞረዱ ልቅ ቃላት አጅበው ያለ ይሉኝታ በተኑት፡፡ ውጤቱ “ከባዶ ጭንቅላት ባዶ እግር ይሻላል” የሚል ውግዘትን አስከተለ፡፡ ምናልባትም በረጅሙ ያቀዱትን የፖለቲካ ጉዞ በአጭሩ ያስቀረው ይሆናል፡፡

ከፍቅሩ አየለ በላይ
Email: fikruayelebelay@yahoo.com

Share

One comment on ““ከባዶ ጭንቅላት ባዶ እግር ይሻላል”

  1. ሰውዬው ብልጥ ያለመሆን ጉዳይ ሳይሆን አስበውበትና የልባቸውን አውጥተው የተናገሩት ሊሆን ይችላል።

Comments are closed