TPLF

የትግራይ ህዝብና ሕወኃት ምን አገናኛቸው?

በአሰፋ ቶላ

የሚከተሉትን አንኳር ነጥቦች እንደማሳያ በመውሰድ፣ የትግራይ ህዝብና ሕወኃት አንድ ናቸው የሚለውን የሕወኃት ፌዝ እንፈትሻለን።

፩. የትግራይ ህዝብ ኃይማኖትና ሕወኃት

አብዛኛው የትግራይ ህዝብ ለኃይማኖቱ ቅናኢ ኦርቶዶክስ ክርስትያን ቢሆንም፤ የሌሎች ኃይማኖት ተከታዮችም አሉት። ባጭሩ የትግራይ ህዝብ ዋናው መገለጫው ጥብቅ ኃይማኖተኛ መሆኑ ነው።

ሕወሃት በአንጻሩ ከፍጥረቱ ጀምሮ “ኃይማኖት የአይምሮ አደንዛዥ እጽ” ነው የሚለውን የማርክሲስት መሪ ቃል ተቀብሎ፣ ኃይማኖት መጥፋት አለበት ብሎ የሚያምን፣ የአልቤንያን ሶሻሊዝምን ርዕዮት የሚከተል አብዮታዊ ፓርቲ ነው።

ሕወኃት ባለፈው 50 ዓመትት በትግራይ ውስጥ የሃይማኖት አባቶችን ከህግ ውጪ ገድሎ፣ አሰቃይቶ፣ ሰውሮ ፣አሳዶ፣….በምትካቸው የሕወኃት ካድሬዎችን ወደ ስልጣን አምጥቷል። የሰው ልጅ በሙሉ በአርአያ ስላሴ ምስል የተፈጠረ መሆኑን ዘንግቶ፣ ከትግራይ ህዝብ ውጪ የተዋለደ የትግራይ ሰው “የረከሰ፣ የቆሸሸ፣…” ልጆች አፍርቷል ብሎ በግልጽ የሚሰብክ አባ ሰረቀ ብርሃንን ልብ ይሏል።

፪. የትግራይ ህዝብ ሰንደቅ ዓላማና የሕወኃት ባንዲራ

የትግራይ ህዝብ በሰርጉም በሃዘኑም ባለ 3 ቀለም አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ይዞ የሚያከብር ህዝብ ነው። አጼ ዮሃንስ በመተማ የተቀሉት፣ ራስ አሉላ በኤርትራ ሰዓጢና ጉንዲት የተዋደቁለት ለዚህ ሰንደቅ ዓላማ ነበር። በአድዋ፣ በካራማራ፣ በማይጨው፣….የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያኖች ጋር አብሮ የተሰዋው ለዚሁ ሰንደቅ ዓላማ ነበር።

የሕወሃት ድርጅትና የትግራይ ባንዲራ ግን የተቀዳው ሃይማኖትን ከሚጠየፉ ከነአካቴው ለማጥፋት ከሚሰሩ ከቬትናም፣ ከአልቤንያና ከቻይና ኮሚኒስት ፓርቲዎች ነው።

ልክ እንደ ቻይና ሁላ፣ የሕወሃት ፓርቲና በትግራይ ላይ የጫነው ባንዲራ ቀይና ቢጫ ቀለሞች ይዘዋል። ልክ እንድ ሕወሃት ባንዲራ ሁሉ፣ የቻይና ባንዲራ ቀለሞቹ ትርጉም ቀዩ አብዮትን፣ ትልቁ ቢጫ ኮኮብ ደግሞ ኮሚኒስት ፓርቲውን ይገልጻል። “The red color of the flag symbolizes revolution;….The larger star represents the CPC ( communist party)…..”

፫. የትግራይን ታሪክ በሕወሃት ጫማ ልክ መገደብ

ከወንጀሎች ሁሉ ወንጀል ደግሞ፣ ሕወኃት የትግራይ ህዝብን የሺ ዓመታት ታሪክ አውርዶ አውርዶ፣ በድርጅቱ የ50 ዓመት እድሜ መገደቡ ነው። የእነ ሳባጋዲስ፣ የራስ አሉላ፣ የአጼ ዮሄንስ፣ የራስ መንገሻ፣ የኢዲዩ፣….ታሪክ ሙሉ በሙሉ ተፍቆ፣ በሕወኃት አስተምሮት የትግራይ ህዝብ ታሪክ የሚጀምረውም የሚያበቃውም በሕወኃት እድሜ ልክ ነው።

ከሕወኃት ውጪ የትግራይ ህዝብ መገለጫ እንዳይኖረው ሕወኃት ደክሟል። የርዕዮቱ ቴድሮስ ፀጋዬ በአንድ ፕሮግራሙ በትክክል እንደገለጸው፣ የተገላቢጦሽ ሳይሆን “ለሕወሃት ህልውና የትግራይ ህዝብ መኖር የግድ ያስፈልጋል” ብሎ ሕወኃት ያምናል።

፬. ትግራይ ውስጥ አሁን ያለው ሃቅ

ትግራይ አሁን ላይ ከሞላ ጎደል እንደበፊቱ በሕወሓት ጥብቅ ቁጥጥር ስር ስላልሆነች፣ የትግራይ ህዝብ ፍላጎቱና ማንነቱ ከሕወኃት በላይ መሆኑን በተለያየ መንገድ እየተገለጸ ነው። የተለያዩ በአውራጃ ሳይቀር የተደራጁ የፓለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማህበረሰቦች፣ ፣….የትግራይ ህዝብ አማራጭ ድምጽ እየሆኑ ብቅ ብቅ እያሉ ነው።

አንድ ህዝብ በአንድ ድርጅት ሙሉ ለሙሉ እንደማይወከል ግልጽ ነው። ሕወሃት እራሱም ቢሆን “የትግራይ ህዝብ ማለት ሕወሃት፣ ሕወኃት ማለት የትግራይ ህዝብ ነው” የሚለውን ተረት ተረቱን አሁን ደፍሮ አይናገረውም። አባባሉ ጊዜው ያለፈበት የተበላ እቁብ ሆኗል።

መደምደሚያ:

ላለፈው 50 ዓመት ሕወኃት ያለመታከት የትግራይ ህዝብ ማለት ሕወሃት፣ ሕወሃት ማለት የትግራይ ህዝብ ነው ብሎ ካለምንም ሃፍረት ሲሰብክ ነበር።

አሁን ላይ ግን በተግባር መሬት ላይ እንደሚታየው፣ በጦርነቱ የተፈናቀሉ፣ አካለ ስንኩል የሆኑ ተዋጊዎች፣ …. የሕወሃት ችግር አይደሉም። ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ ማለቂያ የለሹ የሕወሃት ስብሰባና ግምገማ አጀንዳ የሚያጠነጥነው አንድና አንድ ጉዳይ ላይ ነው። በጌታቸው ረዳና በዶ/ር ደብረ ጽዮን ቡድኖች መካነው።የሚካሄደው ሕወሃትን የመቆጣጠር ትንቅንቅ።

የትግራይ ህዝብ ላይ በሕወሃት የተጫነው ባንዲራ ከታሪኩ ጋር ምንም ትስስር ከሌለው ከቻይና ከቬትናምና አልቤንያ ኮሚኒስት ፓርቲዎች የተቀዳ ነው። የትግራይ ህዝብ ለኃይማኖቱ ቀናኢ ሲሆን ፣ ሕወኃት ደግሞ ኃይማኖት ጠል ድርጅት ነው። የትግራይ ታሪክ የሺህ ዓመታት ሲሆን፣ የሕወሃት እድሜ ደግሞ ገና የአንድ ጎልማሳ እድሜ 50 ዓመት ነው።

የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያን በደሙ ያጸና ሲሆን፣ ሕወኃት ደግሞ ከፍጥረቱ ለኢትዮጵያ ወደር የለሽ ጥላቻ ባላቸው መሪዎች የተሞላ ነው።

በትግራይ የተለያዩ ድምጾች መስማት በመጀመራቸው፣ የትግራይ ህዝብና ሕወኃት ለየቅል መሆናቸውን ማሳያ ነው።

0 0 votes
Article Rating
Subscribe
Notify of
guest

0 Comments
Oldest
Newest Most Voted
Inline Feedbacks
View all comments

0
Would love your thoughts, please comment.x
()
x