Fano

ዘጠኝ የፋኖ ድርጅቶች!

በአቦጊዳ

ፋኖ በአሁኑ ጊዜ ዘጠኝ ዋና ዋና ድርጅቶች በተለያዩ ይሃገሪቱ ክፍሎች ያሉት ንቅናቄ መሆኑ እየተነገረ ነው። ከአጭር ጊዜ ታሪኩ እና ከምስረታው እና ከተጋድሎው ውስብስብነት አኳያ ሲታይ ይህ እንደ ዓይነተኛ ስኬት ሊቆጠር ይችላል።

ይሁን እና ተጋድሎው በአንድ ወጥ ድርጅት ወይም ዕዝ እንዲመራ የሚወተውተው የህዝብ ድምጽ እየጎላ መጥቷል። ይህን ተከትሎ አንድ ዕዝ ለመፍጠር እጅግ ውስብስብ እና ፈታኝ የሆነ ውይይት እና ድርድር መካሄድ እንደሚኖርበት ይታመናል።

ሂደቱን የሚያወሳስበው የፋኖነት ዓይነተኛ ባህሪያት ናቸው። እነዚህም፡ ፋኖነት የእምቢተኝነት ውጤት መሆኑ፤ ማንኛውም ግፍ የታከተው እና መገፋት በቃኝ ያለ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በግሉ የሚወስነው ማንነት እንጂ በማንም ኃይል ወይም አካል የሚታደል ሹመት አለመሆኑ፤ በየአካባቢው የተነሱ ፋኖዎች ቀስ በቀስ እየተደራጁ እና እየተባበሩ መሪዎቻቸውን እየመረጡ እና እየሾሙ የሚያጎለብቱት እና የሚያሳድጉት ሃገር በቀል መዋቅር መሆኑ ናቸው። እነዚህ ባህሪያቱ በተፈለገው ፍጥነት አንድ ወጥ ድርጅት እና ዕዝ ጥላ ስር ለመሰባሰብ አዳጋች ያደርጉታል።

ስለ አንድነት ሲታሰብ ሌላ መጤን ያለበት እና እንደ ስጋት የሚታይ ሁኔታም አለ። ይህም “ምናልባት ይህ ንቅናቄ በአንድ ሰው ወይንም በአንድ ቡድን ስር ቢወድቅ በማዕከላዊነት ታስሮ አሁን በራሱ አነሳሽነትና በየአካባቢው ሁኔታ የሚያካሂዳቸውን ንቅናቄዎችና ማጥቃቶች በቢሮክራሲያዊ በማዕከላዊነት ቢታሰርስ?” የሚል ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ የፋኖ ንቅናቄ በከፍተኛ ደረጃ የተካሄደው እና ውጤት ያመጣው አምስት ዓመት ከፋሺስት ኢጣሊያ ጋር በተረገው ትንቅንቅ ነበር። ልክ እንደ አሁኑ፡ ያን ጊዜም ፋኖ በየአካባቢው በየራሳቸው የጎበዝ አለቆች እና መሪዎች ነው እየተመሩ ይታገሉ የነበሩት፡፡ “ያገሩን ሰርዶ ባገሩ በሬ” እንዲሉ ሁሉም የፋኖ አርበኞች ዓላማቸው ጠላትን ድል መምታትና ማባረር ቢሆንም እንደየአካባቢያቸው ሁኔታ ነበር የተደራጁት።

የያኔው የፋኖ አንድነት በዓላማ እንጂ በአንድ ዕዝ የመደራጀት ብቃት አዳብሮ ያለፈ ስለመሆኑ አልተዘገበም። ምናልባት ከመካከላቸው አንዳንድ ገዘፍ ያሉት ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር የተወሰነ ግንኙነት ኖሯቸው ሊሆን ይችላል። ይህ አጠቃላይ የፋኖ ንቅናቄ ምን ያህል ውስብስብ ችግር ሊገጥመው የሚችል መሆኑን ለማሳየት እንጂ፡ በኢጣሊያ ወረራ ጊዜ ያለው እና የአሁኑ ፋኖ በአንድ ሚዛን የማይመዘኑበት ምክኒያት ብዙ ነው። ስለዚህ የዚህ ዘመን ፋኖዎች በአንድ ዕዝ ስር ለመካተት ቢበቁ፡ ይህን ለማሳካት የመጀመሪያዎቹ ፋኖዎች ይሆናሉ ማለት ይቻላል።

ወደ አንድ ዕዝ መምጣት አማራጭ የሌለው ነገር መሆኑ አያነጋግርም።

ይህንን ዕዝ ለመመስረት ምን መደረግ ይገባዋል? አንኳር የሆኑትን የሂደቱን አካላት እንደሚከተለው መዘርዘር ይቻላል።

  • ግልጽ የሆነ ከፍ ያለ ግብ ላይ መስማማት ያስፈልጋል። ለምሳሌ ዘመቻ ወደ አዲስ አበባ ቢጀመር የግድ ትብብርና የተቀናጀ አመራር ይጠይቃል። አሁን ግን የጎንደር ጎንደርን፤ የወሎ የወሎን፤ የጎጃም የጎጃምን ወይንም የሸዋ የሽዋን ለመመከት ዐራቱም ክፍለ ሃገር አንድ አመራር አያስፈልገውም።
  • የሁሉም ፋኖ ድርጅት መሪዎች “ወደ አንድ ዕዝ መምጣት አስፈላጊ ነው” ብለው ማመን አለባቸው
  • እነዚህ መሪዎች ተከታዮቻቸውን በዚህ ጉዳይ የማሳመን ፖለቲካዊ ዐቅም ሊኖራቸው ይገባል
  • የፋኖ መሪዎች በሚመሰረተው አንድ ዕዝ ውስጥ የግድ የከፍተኛ አመራር ቦታ አገኛለሁ ብለው ማሰብ የለባቸውም። ይህን መቀበል እጅግ ዐቢይ እመርታ ነው።
  • መሪዎች በቅን ልቦና ውይይት እና ድርድር ለመጀመር ዝግጅት ማድረግ መጀመር
    • የግንኙነት መስመር መፍጠር
    • በጥቅል የምስረታው ዓላማዎች ላይ ስምምነት ላይ መድረስ
    • የመወያያ አጀንዳዎችን መቅረጽ እና ማካፈል
    • ሌሎች ያዘጋቿቸውን የመወያያ አጀንዳዎች ማንበብ እና መመርመር
    • የፓለቲካ ማኔፌስቶ ማርቀቅና ማጽደቅ ያስፈልጋል። በሰው ዙሪያ ሳይሆን በግብ ዙሪያ ነው አንድነት የሚፈጠረው።
    •  
  • ለዕዙ ምስረታ አዋቃሪ ጉባኤ ለማዋቀር መስማማት
  • ከእያንዳንዱ ቡድን ለዕዙ ምስረታ አዋቃሪ ጉባኤ ሁለት፣ ሦስት ወይም እንደየስምምነቱ ሰዎችን መመደብ
  • እያንዳንዱ ቡድን ስለ ዕዙ ምስረታ ያላቸውን ራዕይ የሚያሳይ ድርሳን ማዘጋጀት እና መላክ
    • ምን ዓይነት ድርጅታዊ መዋቅር? ለምሳሌ፡ በአንድ ሰው ወይስ በላዕላዊ ጉባኤ (committee) የሚመራ?
    • የግለሰብ ቋሚ መሪ ወይስ ተዘዋዋሪ ሊቀመንበር
    • የመሪዎች አመራረጥና አወራረድ እንዴት ይካሄዳል የሚለውን ማጽደቅ። ብዙ ሰዎች የሚፈሩት መሾም እንጂ ማውረድ ቀላል አለመሆኑን ነው
    • ምን ምን ነዑሳን አካላት ይኑሩት
    • ወታደራዊ አደረጃጀቱ እና አመራሩ እንዴት ይዋቀር?
    • ፖለቲካዊ አደረጃጀቱ እና አመራሩ እንዴት ይዋቀር?
    • በተለያዩ ጉባዔያት (committee) ውስጥ ያሉት ስዎች በምን መመዘኛ ይሰየሙ? ይህስ እንዴት ይተግበር?
    • የማዕከላዊ ዕዙ እና የእያንዳንዱ ቡድን የግንኙነት መስመር ምን ይምሰል?
    • በማዕከላዊው ዕዝ ውስጥ ተመርጠው የሚሰየሙ ሰዎች በኃላፊነታቸው ምን ያህል ጊዜ ይቆዩ?
    • ...
  • አዋቃሪ ጉባዔው በተወከለበት ጉዳይ ላይ እና በተሰጠው ስልጣን መጠን መምከር / መወያየት
    • ከሁሉም ቡድኖች የመጡትን ሃሳቦች እያነሱ መምከር እና መመዘን
    • የሚያስማሙ ጉዳዮችን (ነጥቦችን) ለይቶ ማውጣት እና መሰነድ
    • የበለጠ ውይይት የሚያስፈልጋቸውን ነጥቦች ሰንዶ ወደየቡድኖቹ ለውይይት ማድረስ
    • ተቃርኖ እና አለመስማማት ያለባቸውን ጉዳዮች ነቅሶ ማውጣት እና በእነዚህ ላይ ግልጽ ውይይት እና ክርክር እንዲደረግ ማመቻቸት
    • የሚደረጉ ውይይቶች እና ክርክሮች በብስለት እና በጨዋነት እንዲደረጉ እና ውጤት እንዲያመጡ ማመቻቸት
    • ውይይቶች እና ክርክሮች ከግለሰባዊ ፍላጎት እና ባህሪይ በተቻለ መጠን የጸዱ ሆነው ተጋድሎውን ዳር ለማድረስ የሚደረገውን ጉዞ እና ዓላማ ያስቀደሙ እንዲሆኑ መጣር
  • አዋቃሪ ጉባዔው ከእያንዳንዱ ቡድን ጋር በተፈጠረው የግንኙነት መስመር ከላይ የተመለከተውን ሂደት እስከመጨረሻው ማስኬድ እና ማዕከላዊ አደረጃጀት ለማዋቀር ስምምነት ላይ የተደረሰበት ሰነድ እስኪዘጋጅ በትጋት መስራት
  • ምንም እንኳ መቶ በመቶ ስምምነት ላይ ባይደረስ፡ ማዕከላዊ ድርጅት ለመመስረት የሚያበቃ ያህል መግባባት ላይ ከተደረሰ (consensus) ጉባዔው በተረሰበት መግባባት መሰረት ማዕከላዊ ድርጅቱን አስመስርቶ ራሱን ማክሰም

ምን እንቅፋቶች አሉ?

የፋኖ መሪዎች እና አባላት ሃሳብ አና አስተሳሰብ

አንዱ እና ዋናው እንቅፋት ሊሆን የሚችለው የተለያዩ የፋኖ ቡድኖች መሪዎች እና አባላት አስተሳሰብ ነው። ይህን ማለት በዱር በገደሉ ህይወታቸውን መስዋዕት እያደረጉ ያሉ ወገኖቻችንን ማራከስ እና ማጣጣል እንዳልሆነ በአንክሮ ሊጤን ይገባል። ይልቁንም ይህን ሃሳብ የምናቀርበው ለውድ ወገኖቻችን ባለን ወሰን የለሽ ክብር እና የተጋድሏቸውን ስኬት የሚያፋጥን መንገድ ለመጠቆም ነው።

በዚህ በተፋፋመ ተጋድሎ ውስጥ ብዙ የፋኖ መሪዎች እና አባላት ትኩረታቸው በጦር ሜዳ ውሎ እና በየዕለቱ በሚያጋጥሟቸው ሁነቶች ላይ ቢሆን አይገርምም። ምክኒያቱም እነዚህ ሁነቶች ግዙፎች ናቸው። ሙሉ ህዋሳትን ቀን ከሌሊት ወጥረው እና አስጨንቀው የሚይዙ ሁነቶች ናቸው። ይህ የጦር ሜዳ ውሎን እና በውሎም ለሚገኙ ድሎች የሚሰጠው ትኩረት የረዥሙን ጊዜ ጉዞ እና ዕቅድ በመጠኑም ቢሆን በቂ ትኩረት እንዳይሰጠው ምክኒያት ሊሆኑ ይችላሉ። ይህም ወደ አንድ አደረጃጀት የመምጣትን እስፈላጊነት በበቂ ትኩረት ለመከታተል አዳጋች አድርጎባቸው ሊሆን ይችላል። ወደ አንድ አደረጃጀት መምጣት ግን በአጠቃላይ እየተከፈለ ያለውን ውድ መስዋዕትነት ለመቀነስ እና ድሉን ለማፋጠን አማራጭ የሌለው መንገድ ነው።

የመሪዎች ባህሪይ

ሌላው የማይካድ እንቅፋት የአንዳንድ የፋኖ ቡድን መሪዎች ባህሪይ ነው ማለት ይቻላል። እነዚህ ሰዎች የመሪነት ስልጣን መያዝን ለድርድር ያለማቅረብ ውሳኔ ያሳለፉ ይመስላሉ። በሚመሩት ቡድን ተገቢው ተቀባይነት ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። በአመራር ብቃታቸውም የተመሰከረላቸው እና በበርካታ አባሎቻቸው እና ተከታዮቻቸው የተከበሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህ እጅግ የሚያረካ እና አኩሪ ስብዕና ነው። ይሁንና፡ እነዚህ ሰዎች የያዙትን ቡድን ብቻ ይዘው እየተዋጉ አዲስ አበባ እንደማይገቡ እነርሱም ይገነዘቡታል። አዲስ አበባ ላይ ስልጣኑ ካልተነቀነቀ ደግሞ የአቢይ አህመድ መንግስት ሊደራደርም ሆነ ሊሸነፍ አይችልም። ስለዚህ ራሳቸውን መጠየቅ ያለባቸው ጥያቄ አለ። እንዴት ነው ተጋድሎው ከዳር የሚደርሰው? እኔ በምመራው ቡድን ብቻ ወደ ድል መገስገስ እችላለሁ? እንዴት ነው ኃይሌን የማጎለብተው? ሌሎች የፋኖ ቡድኖን ወግቼ አስገብሬ በግድ የኔ ጭፍሮች ላደርግ እና ጦሬን ላሳድግ እችላለሁ? ከሌሎች ጋር ተባብሬስ? እንዴት ነው የምተባበረው፣ እስከምን ድረስ? ከሌሎች ጋር ተባብሬም የመሪነት ስልጣኔንም ሳልለቅ መቀጠል እችላለሁ? እንዴት አድርጌ ተደራድሬ ትብብር እና እንድነት ልፍጠር?

ዋናው ማሰላሰል እና በቅንነተ ለህሊናቸውም ለአምሃራ ህዝብም ለኢትዮጵያም ሲሉ መወሰን ያለባቸው ነገር ግን ግልጽ ነገር ነው። “እኔ በመሪነት ካልቀጠልኩ ተጋድሎው ይኮላሽ? ወይም የፈጀውን ያህል ጊዜ ይፍጅ፣ የሚያልቀውን ያህል ወገን ይለቅ እኔ መሪነቴ እስቲረጋገጥ አንድነት አይፈጠርም!” ብለው መወሰን ወይም ከዚህ በተቃራኒው “ለተጋድሎው ሥምረት አንድነት ለመፍጠሩ ሂደት ቅድሚያ ልስጥ፣ መሪ ለመሆን በተቻለኝ ሁሉ እሞክራለሁ፤ ባይሳካልኝም ግን የአንድነት ምስረታውን አላደናቅፍም” ብለው መወሰን!

በነገራችን ላይ ይህ እንግዳ ነገር አይደለም። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ላይ ለመሪነት የሚፋለሙ ሰዎች ከሌሎቻችን (ከተራ ሰዎች) በለየ ሁኔታ አለቅጥ ያገረገሩ ቢሆኑ፤ ከእነርሱ በላይ ሰው ያለ ባይመስላቸው፤ ወይም “በዚህች ዓለም ላይ የተለየ ተልዕኮ ያለኝ ሰው ነኝ፡ ስለዚህ አምኜ ለሌላ ሰው ቦታዬን አልለቅም” ብለው የሚያስቡ ቢሆን ለገርመን አይገባም። ቁም ነገሩ የጥንካሬያቸውን ያህል ብልሃት እና (ምናልባትም ሽፍጥ ቢጤ ፡)) ኖሯቸው አንዳቸው በአሸናፊነት መውጣታቸው ነው።

እነዚህ ሰዎች ማገናዘብ ያለባቸው ሌላው ጉዳይ ይህ ነው። አሁን ባለበት ሰቆቃ ውስጥ እየኖረ ያለው አምሃራም ሆነ ሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ፡ ይህ ተጋድሎ ተሳክቶ ከግፍ ቀንበር መገላገሉን እና የፋኖ ደም እና አጥንት የነፃነት ፍሬ ማፍራቱን እንጂ፡ የፋኖዎች የበላይ አዛዥ አበበ ወይም ከበደ መሆኑ መሆኑ እዚህ ግባ የሚለው ጉዳይ አይደለም። አሁን የመሪነት ስልጣን ከሚያማልላቸው ውስጥ ማናቸውም በድርድር እና በውይይትም ሆነ በፖለቲካዊ ሽፍጥ በአሸናፊነት ስልጣኑን ጨብጠው የህዝቡን ተጋድሎ ወደ ድል ከመሩት፡ ቁም ነገሩ ያ ነው! ስለዚህ በድፍረት ይወያዩ፣ ይደራደሩ፣ አማካይ አስታራቂ ሃሳብ ያመንጩ እና እንድነት ይፍጠሩ። የሚፈጠረው አንድነት ድርጅት ቢፈልጉ በግለሰብ ቢፈልጉ በፈረቃ፣ ቢፈልጉ በጉባዔ (committee) ይመራ። ግን አንድነት ይፈጠር!!

የግንኙነት መስመር መዘርጋት

ሌላው እንቅፋት በተለያዩ ቡድኖች መካከል የተማከለ እና በበቂነት ምስጢራዊ የሆነ የግንኙነት መስመር መዘርጋት ነው። ይህ ችግር ፋኖዎች የሚንቀሳቀሱበት ሰፊ የኢትዮጵያ ግዛት መሆኑ እና መልካዐምድራዊ አቀማመጡም ያባባሰው ሲሆን፣ የሃገሪቱ የመገናኛ አውታሮች በጠላት ቁጥጥር ስር መሆናቸው የበለጠ ውስብስብ ያደርገዋል። ይህም ሆኖ በተለያየ አካባቢ ያሉ ፋኖዎች እንደየአመቺነቱ መጠነኛ ግንኙነት እየፈጥሩ በከባድ ሁኔታም ቢሆን ትግላቸውን እያፋፋሙ ይገኛሉ።

የስደተኞች ፖለቲካ

የማይናቀው ሌላ ትልቅ እንቅፋት የስደተኞች ፖለቲካ ነው። “ዳያስፖራ” እየተባሉ የሚሞካሹት በመላው ዓለም የተበተኑት ኢትዮጵያን በሃገር ውስጥ የሚደረገውን ተጋድሎ ከሚደግፉት በላይ እያኮላሹት እና እያቀጨጩት ይገኛሉ። በእርግጥ ይህ በቅንነትት እና በከፍተኛ የሃገር ፍቅር ተነሳስተው፡ ጥረው ግረው ከሚያገኟት ላይ ሳይታክቱ ለተጋድሎው ዕርዳታ የሚያደርጉትን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ስደተኞች አይጨምርም። ዋናዎቹ ሳንካዎች ቁጥር ስፍር በሌላቸው የተለያዩ ጥቃቅን ድርጅቶች ውስጥ ተደራጅተው የሚነታረኩ እና የሚራኮቱ መሰሪዎች እና የሚከተሏቸው የዋሃን ናቸው። የነዚህ ስዎች ፀቦች፣ እና ንትርኮች ክራሳቸው አልፎ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገውን ትግል እያጨነገፈው ይገኛል።

ማጠቃለያ

የአንድነት ጥያቄ አስፈላጊ ነው። ይሁንና በሌላው በኩል ደግሞ ለአንድነት ብቻ ተብሎ የሚፈጠር አንድነት በደካማ አመራር ስር ከወደቀና ትግሉ በቢሮክራሲያዊ ማዕከላዊነት ከተጠረነፈ፡ ውጤት ማጣት ብቻ ሳይሆን ውድቀትም ሊጋብዝ ይችላል። የተማከለ አመራር በሌላ በኩል የሚያመጣው ስጋት ለሥርዓቱ ዋነኛ ኢላማ መሆኑ ነው። ከተመታም ትግሉን የማዳከም ዕድል ይኖረዋል። ስለዚህ የአንድነትን አስፈላጊነት ከዚህ ስጋት ጋር አብሮ መመልከት እጅግ አስፈላጊ ነው።

በዋናነት አንድነት አስፈላጊ ነው የሚለው ሁሉም የሚያምንበት ጉዳይ ነው። አሁን ያለው ሁኔታ ይሄንን አንድነት እኔ ካልመራሁት የሚለው እንቅፋት ነው። ስለዚህ ይሄንን ደግሞ ለማረቅ ጠንካራ እና ሁሉም የሚወስንበት ምክር ቤት መፍጠር ያስፈልጋል። ይህም ምክር ቤት መሪውን መምረጥ ብቻ ሳይሆን ማውረድም እንደሚችል በደንብ ጥርስ ያለው እንዲሆን አድርጎ ማዋቀር ነው። ከዚያ አልፎ፡ አመራሩ በግለሰቦች ተክለ ሰውነትና በአጫፈሪዎች እንዳይጠለፍ ሁሉም ፋኖዎች የተክለ ሰውነትን ግንባታ መቃወምና መሪ ማለት ንጉሥ ሳይሆን አገልጋይ መሆኑን የሚያሳይ ባህል መገንባት ያስፈልጋል። የተጋነነ የተክለ ሰውነት ግንባታ እንኳን ስልጣን የሚመኘውን ይቅርና ጤነኛውንም ሰው የሚያሳብድና አንድ ሰው ከመላው ህዝብ በላይ አስፈላጊ ነኝ ብሎ እራሱን እንዲያሳምን የሚያደርግ ነው።

ፋኖ እስከአሁን በደረሰበት የዕድገት ደረጃው የተለያዩ ትንንሽ ቡድኖችን ተለቅ ወዳሉ ቡድኖች በማደራጀት የትብብር እና የውህደት ሂደቶችን በብዛት የተለማመዱባቸው ክስተቶች ተስተውለዋል። ወደ አንድ ብሔራዊ ድርጅት ምስረታ መሄድ የነዚህ ሂደቶች ቀጣይ ደረጃ ነው። በእርግጥ በአንድ አካባቢ የሚገኙ ቡድኖችን ማስተባባእር እና በየ ፍለሃገሩ ያሉትን ወደ አንድ ማዕቀፍ ማምጣት ከፍተኛ ልዩነት አላቸው። በሰው አቅምም ሆነ በቁሳቁስ እየጎለበተ ላለው የፋኖ የሚቀጥለው አቀበት ይህ ነው።

ቁም ነገሩ ግን ይህ ሥራ በዋናነት ለፋኖ መሪዎች የሚተው መሆኑ ነው። ህዝቡም ይወተውታል፤ አንዳንድ ሰዎች፣ ቡድኖች እና ተቋማት ይበጃል ያሉትን በቃልም በጽሁፍም ለፋኖ መሪዎች ያቀርባሉ ወ... ወጣም ወረደ ግን፡ ጉዳዩ ተንጠልጥሎ የሚቀረው በፋኖ መሪዎች ጫንቃ ላይ ነው።

ወጤቱ የሚወሰነው በፋኖ መሪዎች ብስለት እና ብልሃተኝነት፤ በአጠቃላይ ለተጋድሎው ሥምረት የራሳቸውን ሚና አንጥሮ ለመለየት ባላቸው ብቃት ይሆናል። ከደም እና ከአጥንት (ከህይወት) መስዋዕትነት በመለስ፡ በድርድር እና በውይይት እውነትን (ሃቅን) የመጋፈጥ ድፍረት ሊኖራቸው ይገባል። መርታት እና ተቀባይነት ማግኘት ብቻ ሳይሆን መረታት እና የሌሎች ጓዶቻቸውን ሃሳብ የመቀበል ድፍረት ሊኖራቸው ይገባል።

የፋኖ ድርጅታዊ አንድነት መፍጠር እጅግ አንገብጋቢ ጉዳይ እንደሆነ እና ምን ያህል ውስብስብ ችግር መታለፍ እንዳለበት በስፋት ተነግሯል። በተለያዩ ሰዎች ተጽፎበታል። በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ቁጥር ስፍር የሌላቸው ውይይቶች ተደርገው የተለያዩ ሃሳቦች ተነስተው ተንሸራሽረዋል። ስለዚህ የሃሳብ እና የትንታኔ እጥረት ፈጽሞ የለም። ምን መደረግ እንዳለበት ፋኖም ህዝቡም ያውቃሉ። መደረግ ያለበትን ማድረግ ያለባቸው ብቸኛ ተዋንያን፣ የፋኖ መሪዎች ናቸው። እየተጠበቁ ነው።