የአብይ ማደናገሪያ፣ ” በህዝብ የተመረጥኩኝ” መንግስት
የተለያዩ የጦሩ አመራሮች ወደ ሚድያ ብቅ ባሉ ቁጥር፣ የአብይን ነጭ ውሸት እንደ ወረደ ነጋ ጠባ እንደበቀቀን ከመድገም ተቆጥበው፣ ሃቁን መፈተሽ መጀመር አለባቸው።
አብይና የሚመራው የኦሮሙማው መንግስት ዋናው መገለጫው ቅጥፈት፣ ማስመሰል፣ ሴራና ማደናገር ነው። “በህዝብ የተመረጥኩኝ” መንግስት ስለሆንኩኝ፣ “የጊዜ ገደቤን የመጨረስ” ህጋዊ መብት አለኝ የሚለው አንዱ የአብይ መንግስት ህዝቡን ማደናገሪያው መንገድ ነው።
የኢትዮጵያ ጦር አካዳሚ እነ ኮሎኔል ጎሹን የመሳሰሉ ስመጥር መኮንኖች እንዳላፈራ ፣ ዛሬ ላይ ብርሃኑ ጁላና የጦር ወንጀል ተባባሪዎቹ መፈንጫ ሆኗል። እነዚህ በአካዳሚው ያልገፉ፣ መሰረታዊ የዲሞክራሲ ግንዛቤ የሌላቸው፣ ለውትድርና ሳይንስ ባዕድ የሆኑ፣ በጎሳ ኮታ የተሾሙ፣ እራሳቸውን መግለጽ የማይችሉ፣ በቅጡ ማሰብ የተሳናቸው፤ አብይ እራሱን ስልጣን ላይ ለማቆየት የሰበካቸውን ነጭ ውሸት እንደ በቀቀን ከመድገም ተቆጥበው፣ እራሳቸውን ባስቸኳይ መፈተሽ መጀመር አለባቸው።
ሲጀምር ኮሮጆ ገልብጦ አጭበርብሮ ወደ ስልጣን የመጣ መንግስት ሳይቀር፣ የህዝብ ይሁኝታ አግኝቼ ነው ስልጣን የያዝኩት ብሎ እንደሚደሰኩር መታወቅ አለበት። የሀገራችንን ጉድ ሕወኃትን እንደምሳሌ ብንወስድ፣ 100% አሸንፌያለሁ ብሎ ራሱን ሲያጃጅል፣ ብዙም ሳይቆይ በህዝባዊ ቁጣ እንደተወገደ ማጤን ተገቢ ነው።
ምርጫ ቦርድ እንጂ ወታደሩ አንድ መንግስት በነጻና ገለልተኛ ምርጫ ወደ ስልጣን ይምጣ አይምጣ የመመስከር ችሎታውም፣ ልምዱም የለውም። ህጉም አይፈቅድለትም።
የወታደሩ ህጋዊ ሚና የሀገር ዳር ድንበር መጠበቅና ማስከበር ስለሆነ፣ በማያገባው ገብቶ መፈትፈቱን አቁሞ፣ በሱዳን ላለፈው 5 ዓመት በወረራ የተያዘውን የጎንደር ጠቅላይ ግዛት አል ፋሻጋ ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት የማስመለስ ህጋዊ ግዴታ አለበት። ይሄን የዳር ድንበር መደፈር የአብይ ሴራ ተባባሪ ሆኖ አይቶ እንዳላየ ማለፍ፣ ጊዜው ሲደርስ በጦር ፍርድ ቤት በሀገር ክህደት ወንጀል የጦሩ አመራሮች ይጠየቁበታል።
ሲቀጥል በነጻና ገለልተኛ የተመረጠ መንግስት እንኳን ቢሆን፣ የተመረጠበት የጊዜ ዘመን እስኪያልቅ ድረስ በስልጣን የግድ ይቆያል ማለት አይደለም። እንድ በምርጫ ወደ ስልጣን የመጣ ፓርላመንታሪ ዲሞክራሲን የሚከተል መንግስት፣ የስልጣን ዘመኑን ሳይጨርስ እራሱን ከስልጣን ሊያገል ይችላል። የብሪታንያ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩን በአውሮፓ ህብረት የመቆየት ህዝበ ውሳኔ ሽንፈት በኋላ ያደረጉት ይሄን ነው። ስልጣን ከለቀቁ በኋላ ዴቪድ ካሜሩን በቅድሞዋ ጠቅላይ ሚንስቴር ትሬሳ ሜይ ተተክተው ነበር።
በህዝብ የተመረጠ መንግስት በአብላጫው የፓርላማ ተመራጮች እምነት ካጣ ወይም የመተማመኛ ድምጽ ካጣ፣ አዲስ መንግስት ወይ በስምምነት ወይም በአዲስ ምርጫ ይመሰረታል።
ለምሳሌ ልክ እንደ ኢትዮጵያ ፓርላመንታሪ ዲሞክራሲን በምትከተለው ብሪታንያ፣ በአብላጫ ድምጽ ለ5 ዓመት የተመረጡት የቀድሞው የኮንሰርቫቲቭ ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን፣ በተመረጡ 1 ዓመት ውስጥ የምርጫ ዘመናቸውን በቅጡ ሳይጀምሩት መንግስታቸው ከስልጣን እንዲለቅ ተገዷል።
ከላይ ብሪታንያን በምሳሌ አንስተን እንዳየነው፣ በፓርላመንታሪያን ዲሞክራሲ ህዝብና የፓርላማ ተመራጮች እስከፈለጉ ድረስ፣ በነጻና በገለልተኛ መንገድ የተመረጠ መንግስትን ሳይቀር የጊዜ ገደቡ ሳያልቅ በህጋዊ መንገድ መቀየር ይቻላል።
የኢትዮጵያ ህዝብና የፓርላማ ተመራጮችም ከፈለጉ፣ የአብይን መንግስት በህጋዊ መንገድ መቀየር ይችላሉ ። እንደሚስተዋለው በህጋዊ መንገድ አልሄድም ብሎ የአብይ መንግስት ካስቸገረ፣ ልክ በ100% ምርጫ አሸንፌ የመጣሁ መንግስት ነው ብሎ ሲመጻደቅ እንደነበረው የሕወሃት መንግስት በሁለንተናዊ ህዝባዊ ትግል የአብይ አገዛዝ የግድ ይወገዳል። ይሄን ጦሩ ሊያስቆመው እንደማይችል መታወቅ አለበት።
ነገ ከጦር ፍርድ ቤት ከመቆም ለመትረፍ፣ ቢያንስ ቢያንስ ይሄ መሰረታዊ የዲሞክራሲ ግንዛቤ የጦሩ አመራሮች ኖሯቸው እራሳቸውን ከመጪው የህግ ተጠያቂነት ሊጠብቁ ይገባል። አብይ የቁርጥ ቀን ሲመጣ ከቻለ እንደ ኮሎኔል መንግስቱ የጦር መሪዎቹን ጥሎ እንደሚፈረጥጥ ሊስቱት አይገባም።
ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ እንደሚባለው፣ የጦሩ አመራሮች ” በህዝብ የተመረጠ” መንግስት እያገለገልን ነው የሚለውን የአብይን ቧልት አቁመው፣ የአብይ የግል አገልጋይ ሰራዊት ሆነው ህዝቡን መጨፍጨፋቸውን በቃ ብለው፣ የአብይ አገዛዝን ለማስወገድ የህዝቡን ትግል መቀላቀል አለባቸው።