የቄስ ሞገሴ፤ የዶክተር ብርሀኑ እና የአታተርክ ጉዳይ

የቄስ ሞገሴ፤ የዶ/ር ብርሀኑ እና የአታተርክ ጉዳይ ክፍል 2

ያሬድ ኃይለመስቀል

ባለፈው የዶክተር ብርሀኑን ከሌኒኒስትነት ወደ ሶሻል ዲሞክራትነት ከዛ ደግሞ አሁን ወደ አታተርክ አይነት ወታደራዊ አንባገነንነት ያደረጉትን ሽግግር አይተናል። ዶ/ር ብርሀኑ “.. …ሰዋችን ሰው የሚያደርጋቸው የነጻነት ፍላሮጎቸው በመሆኑ ሆድን እስከምትሞላ ድረስ ነጻነት አያስፈልግም የሚለው አባባል ሰው ሆዱን እስከሚሞላ ሰውነቱን አጥቶ እንደ እንስሣ ይቆጠር የማለት ያህል ነው” ብለው የጻፉት ቀለም ሳይደርቅ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት እንደ ጄኔራል አታተርክ ያሉ አንባገነናዊ ሰው ነው አሉ።

የሳቸውን ሀሳብ መቀያየርና እምነት አልባ ንግግሮች ከፍቅር እስከ መቃብር ቄስ ሞገሴ ጋር አወዳድሬ በክፍል አንድ ጽፌ ነበር።

አሁን ደግሞ እሳቸው ያደነቁት ጄኔራል አታተርክ ለመሆኑ ማናቸው የሚለውን ትንሽ አነባብቤ የሚከተለውን አቀርባለሁ።

ኢትዮጵያ ውስጥ በንባብና በመረጃ ላይ የተመሰረተ አስተያየት መስጠት የታገደ እስከሚመስል ድረስ የእልፍኝ ምሁራኖች አለቆቻቸውን እየተከተሉ በእውነት ፈጥራ ተሰማርተዋል። ለዚህ ችግር መንሳኤው በአንድ በኩል የኢትዮጵያ ትምህርት ስርአት ምሁራንን መፍጠር ባለ መቻሉ ሲሆን፣ ሁለተኛ ደግሞ እንደ ቄስ ሞገሴ የእልፍኝ ምሁራን መሆን ቀላል መተዳደሪያ እየሆነ መምጣቱ ነው። ስለዚህ ምሁራኖቹም አለቆቻቸውን የሚሉትን የሰሙትን እንጂ ብዙ አንብበው መፍትሄ ሲሰጡ አይታዩም። ጆርግ ኦርዌል የመንግስት የፕሮፓጋንዳ ሰራ “… is designed to make lies sound truthful and murder respectable, and to give an appearance of solidity to pure wind” ይላል። ትርጉሙም የእልፍኝ ምሀራን ስራቸው “ውሸትን እውነት፤ ነፍስ ገዳይነትን የሚያስከብር፤ ነፋሱን ጠጣር ብረት” ብለው ለማሳመን የሚደክሙ ይላቸዋል። ሌላው ማሀበራዊ ሀያሲያን ኢትዮጵያ መፍጠር አልቻልንም። አንድ ባለስልጣን ሁለት ሲደመር ሁለት አምስት ነው ሲል። ትልቅ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የሚያስተምር የሂሳብ ጠበብት ሚዲያ ደውሎ ቢጠይቀው አራት ነው ለማለት ይፈራል። ሌላው አለም አንድ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰው የተሳሳተ ነገር ሲናገር ወድያው ጋዜጣውም፤ ሚዲያውም፤ የምርምር ጸሀፊዎችም በሞያቸውና በንባባቸው ዙሪያ የተገለጸውን ስክተት ያርማሉ። ያስተካክላሉ።

እንግሊዝ ወይንም ኬንያ ሳይቀር አንድ ጠቅላይ ሚኒስቴር አንድ የተሳሳተ ነገር ቢናገር በምሳ ሰአት ትንታኔ ላይ በጉዳዮ አዋቂ የሆነ ምሁር ተጋብዞ ስህተቱን ያስተካክላል። ማታ ደግሞ ቀልድ በመስራት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጅልነት ይሳለቁበታል። አሜሪካም እነ ትራቨር ኖሀ እነ ቢል መሀር ያሉ የማታ ቀልደኞች ስህተቱን ያስቁበታል። ሰውም ያዝናኑበታል።

እኛ ሀገር ደግሞ ሀሳቡ ከባለስልጣኑ ከመጣ ስህተቱን ማረም ቀርቶ እንደ ቄስ ሞገሴ የእልፍኝ ምሁራኑ ሲያሽቃብጡ ይገኛሉ። ስለዚህ ትላንት ስታሊን፤ ማኦ፤ ሌኒን ትላልቅ በጎ መሪዎች ናቸው ብለው ጫካ የገቡት እነ ዶ/ር በርሀኑ ዛሬ ደግሞ አታተርክን ይዘውልን ብቅ ሲሉ አረ ተዉ የሚል የለም።

አታተርክ ማናቸው?

አታተርክ የኦቶማን ተርክ ሲያቀብጠው ጀርመን አገር አብሮ በአንደኛው አለም ጦርነት ገባና ከተሸናፊው ወገን ሆነ። እኛም ሀገር ልጅ እያሱ ወዳጅነታቸውን ከጀርመንና ከተርኪ ጋር ለማቆራኘትና የዛ ቡድን አባል ለመሆን መሞከራቸው እንደ በጎ ነገር ተቆጥሮ ሲተረክ ሰምተናል። በእርግጥ ኢትዮጵያ ከተሸናፊው ወገን ጋር አብራ ተሰልፋ ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያ እጣ ፈንታም ከኦቶማን ተርክ አይለም ነበር። ሱማሌና ኤርትራ ላይ የሰፈረው የጣልያን ጦር፤ ጅቡቲ ላይ የነበረው የፈረንሳይ ጦር፤ እና በሱዳን በኬንያና በሱማሌ ላይ ሰፍሮ የነበረው የብሪትሽ ቅኝ ገዢ እንደ ኦቶማን ይቀራመተን ነበር።

ጦርነት ሲጀመር ሳይሆን ሲጠናቀቅ ነው አሸናፊው የሚታወቀው። ኦቶማን ከተሸናፊው ወገን ሆነች። በዚህ ስህተት ምክንያት ኦቶማን ሁሉንም ግዛትዋን በፈረንሳይ፤ እና በእንግሊዝ ተቀማች። ከዛ ትንሽ ቱርክ በምትባል ምድር አርፋ እንድትቀመጥ ተደረገ። እንዲሁም ከአሁን ወድያ የምዕራቡ አለም አገልጋይ እንጂ ተቀናቃኝ እንዳትሆን ሁሉ ነገር ተሰራ። ጀነራል አታተርክ በግሪክ ጋር ባለ ግጭት ውጤት ስላመጡ ገናና ሆነው የሀገር መሪ ሆኑ። ይሁንና አታተርክ የሚሞገስና ለኢትዮጵያ መሪዎች የሚሆን ተምሳሌትነት ምንም የለም?

የኦቶማንና የተርኪ ግዛቶች በንጽጽር

ኦቶማንን ኢሮፕን፤ ሜዴትራኒያንን፤ መካከለኛውን ምስራቅን፤ ሰሜን አፍሪካንና ምስራቅ አፍሪካን ሲገዛ የኖረ ትልቅ ሀይል ነበው። ከ12ኛው ክፍለዘመን እስከ 20ኛው ማለትም እስከ አንደኛው የአለም ጦርነት ዋነኛው ተፎካካሪ ሀይል ነበር። እኛንም አንዴ በላይ አንዴ በታች ሲወረን ነው የኖረው።

እስቲ ግማሽ አለምን የገዙት የኦቶማን ኢምፓየር ሱልጣኔትና ጀነራል አታተርክን እናወዳድር። እኔ በአጋጣሚ ቱተኪ ሄጄ እነዚህ ትልቁዋን ኢሮፕን ስታንቀጠቅጥና ብዙ ሚሊዮን ኢሮፕያውያንን ባርያ አድርገው ሲገዙና ሲሸጡ የነበሩ የኦቶማን ሱልጣኔትን መቃብር ጎብኝቻለሁ። እግረ መንገዴንም ትንሽ አንብቤያለሁ።

የኦቶማን ኢንፓየር የሚባለው ይገዛው የነበረው ሀገራት። 1. የትውልድ ሀገራቸውን ተርኪ፤ 2. ግሪክ፤ 3. ቦዝንያ እና ሄርዘጎቪና፣ 4. አልባያ፣ 5, ኮሶቮ፤ 6. ማሲዶንያ፣ 7. ሰርቢያ፣ 8. ሮማንያ፣ 9. ሀንጋሪ፣ 10. ግብጽ፣ 11. ሶርያ፣ 11. ኢራቅ፣ 12. ጆርዳን፣ 13. ፓለስቲያን፣ 14. ሳይፕረስ፣ 15. ሊቢያ፣ 16. ቱኒሲያ፣ 17. አልጀርያ፤ 18. ሱዳን፣ 19. የመን፣ 20. ሳውዲ፣ 21. የኢራን የተወሰነ ክፍል፣ 22. አርመያ፤ 23 አዘርባጃን 24 የሱማሌንን ዋነኛ የወደብ ከተሞች እንደ ሞቃድሾ፣ የኛን ምጽዋ እና መካከለኛ ምስራቅ የሚባለውን አካባቢ በሙሉ። ኦቶማኖች እንደ ሱልጣን መሀሚድ 2ኛ (Mehmed the Conquero) እና Suleiman the Magnificent (Suleiman I) የመሳሰሉ ትላልቅ ሀገር አሸንፈው ኦቶማንን የአለም የገዙ ሞሪዎች ነበሯቸው።

የኦቶማንና የተርኪ ግዛት ሲወዳደር

አታተርክ በፈረሰች የኦቶማን ኢንፓየር ውሽት 15% መሬት ተሰጥቶት በእንግሊዝና ፈረንሳይ የተመሰረተ ሀገር ነው። ፈረንጆቹ የፈለጉትን ነገር ሁሉ በማድረጉ በምዕራብ ፕሮፓጋንዳ አሰራጮች እንደ ትልቅ አርቆ አሳቢ መሪ ተደርጎ ቀርቧል።
ፈረንጆቹ አታተርክን አጋነው የጻፉላቸው ምክንያቶች፣

1ኛ፣ የቱርክን/የኦቶማን ለሺ አመታት የጻፉበትን የተርኮችን ፊደል በአዋጅ አግደው በፈረንጆቹ በላቲን ፊደል ስለጻፉ

2ኛ፤ የተርኪ ዜጎች የእስላም ኮፍያ በግድ እንዲያወልቁ ስላወጁ

3ኛ፤ የተርኪዎችን ባህላዊ ልብስ በምዕራባዊያን ልብስ እንዲለውጡ በማስገድዳቸው፣

4ኛ፤ የተርኪን ሰንበት ቀን ከአርብ ወደ እሁድ፤ ቀን መቁጠሪያቸውን ከእስልምና ወደ ኢሮፕ በአዋጅ ስለቀየሩ፣

5ኛ፤ የተርኪን ስም በፈርንጆቹ የቤተሰብ ስም እንዲጠራ በማወጃቸው (surname)፤ እሳቸው አታተርክ ተባሉ። ማለትም የተርኪ አባት። ይሁንና ይሄንን ስም ማንም ለልጁ መስጠት አንዳይችል አደረጉ። ልጆቻቸውም በአታተርክ የቤተሰብ ስም አንዳይጠሩ አደረጉ።

6ኛ፤ ቁራን በአረብኛ እንዳይነበብ በማድረግ በተርኪ ቋንቋ ብቻ እንዲነበብ አወጁ።

7ኛ፤ ትልቁ የዶክተር ብርሀኑ ስህተትና ከኦፒዲኦ የሚያጋጫቸው አታተርክ ከተርኪ ቋንቋ በቀር የማንም ብሄረሰብ ቋንቋ በአደባባይ እንዳይነገር ማውጃቸው ነው። የኛ ሀገር የብሄር ፓለቲከኞች “አሀድያን” ብለው የሚከሱትን እሳቤ ነው።

አታተርክ በ1922 ስልጣን ሲይዙ ቱርኮች እምነታቸው እስልምናም ቢሆን እንደ ኢሮፓውያን ከለበሱ፤ ከጻፉ፤ ቀን ከቆጠሩ ኢሮፕያውያን ይሆናሉ ብለው አስበው ነው። የሚገርመው ግን ኢሮፕ ህብረት ውስጥ ተርኪ ለመግባት በ1987 አመልክታ እስከ 2018 ደረስ ለ32 ዓመት ደክማ የኢሮፕያ ህብረት እናንተ ኢሮፕያውያን አይደላችሁም፤ ይህ የክርስቲያን ስብስብ ነው ብሎ በር በ2018 በሩ ተዘጋባት። ትላንት ከኮሚኒዝም ወጥተው ኢሮፕን ለመቀላቀል የጠየቁት እነ ችኮዝላቫኪያ፤ ፓላንድ ቡልጋርያ ወዲያው ነው ወደ ኢሮፕ መሀበር የተቀበሉዋቸው። እውነታው ፈጦ ሲመጣ፤ አንድ ሰው ልብሱን ስለቀየረ ፈረንጅ እንደማይሆነው ሁሉ ተርኪ ተመልሳ በ1922 የጣለችውን ማንነት ፍለጋ ላይ ነች። እስልምና ይሰበካል፤ ከዛም አልፎ ኦቶማን ተርክ ይገዛቸው የነበሩ ቅኝ ግዛቶችን እያሰባሰበች መሪ እየሆነች ነው። ከሱማሊያ እስከ ሊቢያ፤ ከካታር እስከ እየሩሳሌም እጇን እያስገባች ነው።

ዶ/ር ብርሀኑና አታተርክ

አታተርክ ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲም እድገትም የሚያበረክተው አንደም ነገር የለም። ብዙ ወጣት እንኳን የተርኪን የኢትዮጵያውያን ታሪክ ለማንበብ እድል ስለማይኖራቸው በዶ/ር ብርሀኑ መፈክር ሊሳሳቱ ይችላሉ።

ተርኪ ኦቶማን በምትባለው ዘመን ብዙ ትላልቅ ንጉሶች ነበሯት። ለምሳሌ መሀሚድ ድልነሺው የሚባለው ሱልጣን (ንጉስ) በ21 አመቱ ሲነግስ ነው በኢሮፕ ለመጀመሪያ ትልቅ መድፍ የሰራው። በ14ኛው ክፍል ዘመን ትልቅ መድፍ አስርቶ ነው ኮንስታንቲኖፓሎስን ድል የመታው። ይህንን የመድፍ ንድፈ ሀሳብ የሰራው የሀንጋሪ ኢንጂነር ቢሆንም የጀርመን የሀንጋሪ እና ሌሎች ሀገሮች ንጉሶች ይሄንን ፈጠራ ስላላመኑትና ስላልተቀበሉት ወደ ተግባር አልገቡም። ይሁንና ሀሳቡን ኦቶማን ሲሄድ ወጣቱ ንጉስ ሀሳቡን ገዛው። በዛን ግዜ ወጣት የነበረው ሱላጣኔው ገና ንግስናውን በወረሰበት ግዜ ነበርና ብዙ ዩሮፕያውያን ያላመኑበትን የመድፍ መገንባት ፕሮጄክት ተቀብሎ ብር ሰጥቶ አሰራው። በዛን ግዜ የነበረው መድፍ የብረት አሎሎ የሚያስፈነጥር ሲሆን ቁመቱም እስከ 18 ሜትር ይደርስ ነበር። ይሄንን ይዞ ጠንካራ በግንብ የታጠረውንና እና በኢሮፕያውያን ወታደሮች ሲጠበቅ የነበረው የኮንስታንቲኖፓሊስ ግንብ በመድፍ ደብድቦ ማፍረስ ቻለ። አሁን ኢስታንቡል የሚባለው ከተማ ድሮ ኮንስታንቲፕሎስ የሚባለው የምስራቅ ኦርቶዶክ የክርሥትና ማዕከል የነበረው ነው። ዛሬ መስጊድ የሆነው ድሮ ዋነኛ የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ማአከል የነበረው ነው።

ለምን ኢሮፕያውያን ሱልጣኔቶቹን አጣጥለው አታተርክን አደነቁ?

ምሁር ነኝ የሚል ለምን ኢሮፕያውያንን ለምን የኦቶማን ሱልጣኔቶችን አናንቀው አታተርክን ማጋነነው ፈለጉ ብሎ መጠየቅ ይገባው ነበር። ዶ/ር ብርሀኑ እንዳላነበቡ የሚያሳብቅ ይህ ነው። ኦቶማን ኢሮፕን ረግጦ ብቻ ሳይሆን ባርያ አድርጎ የገዛ የዕስልምና ሀገር ነበር። ኢሮፕያውያንን እንቅልፍ የነሳ ኦቶማን ነበር። ዛሬ ባርያ (Slave) ማለት ከጥቁር ቀለም ጋር የተያያዘ ሆንዋል፤ ይሁንና ስሌቭ የሚለው ከስላቭ (slav) ከሚለው የምስራቅ ኢሮፕ የዘር መጠሪያ ነበር። ይህ የኦቶማን ሀይል ከ 1453 እስከ 1700 ከሁለት ሚሊዮን ተኩል (2.5) በላይ የሚገመት ነጭ ባርያ አድርጎ የሸጠና ኢሮፕያውያን አጥብቀው የሚጠሉት ኢንፓየር ነበር። ዋናው የባርያ ንግድ ገበያው ደግሞ ኢስታንቡል (ተርኪ)፤ ካይሮ (ግብጽ) እና ባግዳድ (ኢራቅ) ነበር

የነጭ ባርያ ገበያ

ግብጽን ሲገዛ የነበረው የመሀመድ አሊ ወይንም የመሀመድ አሊ ፓሻ በባርነት የተያዘና በ ተዋጊ የሆነ የአልባያ ዝርያ ያለው ነጭ ነው። መጨረሻ ኦቶማን ሲዳከም ገንጥሎ ሊገዛ ሞከረ በኋላ ደግሞ ኦቶማንን ፈርቶ በኦቶማን ስር የግብጽ ንጉስ ሆኖ ወደዚህ እየመጣ ከአሉላና አጼ ዮሀንስ ጦር ጋር ሲዋጋና ሲሸነፍ የኖረውል።

ዶ/ር ብርሀኑ በመጽሐፋቸው እንደገለጹት ንባብ የጀመሩት በሌኒን ጽሁፎች እንጂ ከዛ አልፈው የኢትዮጵያንም ታሪክ ሆነ የሌላውን አለም ታሪክ ያነበቡ አይመስሉም።

ዶ/ር ብርሀኑ በወጣትነታቸው ኢትዮጵያውያን እንደ ቻይና ቢጫ ተቀብተው ኮሚኒስት ቢሆኑ ያልፍላቸዋል ብለው ትግል የገቡ ሰው ናቸው። እሳቸው የማንበብ ፍቅር ቢኖራቸው ኖሮ በምስራቅ ጀርመንና በምዕራብ ጀርመን መሀከል ያለውን የኑሮ ደረጃ ልዮነት ያዩ ነበር። ወይንም በሰሜን ኮርያና በደቡብ ኮርያ መሀከል ያለውን ልዮነት ያዩ ነበር። አሁን በሰሜን ኮርያና ደቡብ ኮርያ መሀከል የሀብትና የኑሮ ደረጃ ልዮነት ብቻ ሳይሆን ቁመታቸው ራሱ የ10 ሳንቲም ልዮነት አምጥቷል። አማካይየደቡብ ኮርያ ቁመት 174 ሲሆን የሰሜን ኮርያ ደግሞ 164 ነው የወንዶቹ። ይህ እንግዲህ የነ ዶ/ር ብርሀኑ ምኞት እኛን ሰሜን ኮርያ ማድረግ ነበር።

መቼም ኢኮኖሚክስ ተምረዋልና የሰሜን ኮርያ አጠቃላይ ገቢ 28 ቢሊዮን ዶላር ነው። የደቡብ ኮርያ ደግሞ 1.71 ትሪሊየን ዶላር ሲሆን የነፍ ወከፍ ገቢያቸው የሰሜን ኮርያ 1,217 ዶላር ሲሆን የደቡብ ኮርያ ደግሞ 33,121 ዶላር ነው። እግዚአብሄር አወጣን እንጂ እነ ዶ/ር ብርሀኑ ስልጣን ይዘው ቢሆን ኖሮ ከሰሜን ኮርያም ያነሰ ኢኮኖሚ ነበር የሚኖረን።

አሁን ደግሞ አሜሪካ ኖረው፣ ስዊዲንን፣ ኖርዌይን፣ ካናዳን እና በአጠቃላይ ኢሮፕን አይተው፤ በሶሻል ዲሞክራሲ ተጠምቂያለሁ ካሉ ቦሀላ አታተርክን ሲመኙ በጣም ልንፈራቸው ይገባል። ተርኪ ራሷ የአታተርክን ስም እንጂ ህልሙን ጥላ ሀይማኖትዋን ማክበርና የድሮ ሱልጣኔቶች ሲያደርጉ እንደነበር የከርሞ ቅኝ ግዛቶቿን እያባበለች እያስፈረመች የጦር ሰፈር እያሰፋች ነው፣ አሁን ሱማሌ ላይ ተመልሳ መጥታለች፣ ግማሽ ሊቢያን ይዛ ለስልጣን እየትፎካከረች ነው፣ በፓለስታይን፣ በዮርዳኖስል በሲሪያ፣ በካታር ጎዳይ ገብታ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆናለች። ትላንት ደግሞ ሲሪያን ያጥለቀለቀው የአማጺ ቡድን የቱርክ እጀ አለበት ይባላል።

ፊልድ ማርሻል ሙስጠፋ ከማል አታተርክና ዲሞክራሲ

መጽሀፍ ማንበብ ለሚፈልግ ዛሬ ሁሉም ነገር በኢትተርኔት ይገኛል። አታተርክ የሚታወቁት አንደኛ የፓለቲካ ፓርቲዎችን በማገድ ነው (Progressive Republican Party የሚባለውን ተቃዋሚ አገዱ። ሁለተኛ፡ አስቸኳይ ግዜ አዋጅ አውጀው የፍትህ ስርአቱን አቆሙ፤ ሶስተኛ ሚዲያውን ተቆጣጥረው ከሳቸው ሀሳብና ፍላጎት ውጪ ሌላ ሀሳብ እንዳይተላለፍ አገዱ።

ታድያ ዶ/ር ብርሀኑ ዲሞክራሲ ለህዝብ አየር ነው ብለው የጻፉት መጽሀፍ በእርግጥ የሳቸው ነው ወይስ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ይሆን? መጽሀፉ እስር ቤት ተጻፈ ተብሎ ነው የታተመው። ይሁንና ውጪ ያሉ ሰዎች አርመው አስተካክለውታል ሲባል ነበርና በእርግጥ በመጽሀፉ ውስጥ ያሉ ሀሳቦች የሳቸው ይሆኑ?

ከሁሉም በላይ ኦፒዲኦን ሊያስቆጣ የሚችለው የአታተርክ አንድ ቋንቋ ሀገር መፍጠራቸው ነው። አታተርክ የኩርድስታን ተገንጣዮችን በከባዱ ወግተው ጨፍጭፈዋል። ይሁንና የኩርድስታን ንቅናቄ ዛሬም በትጥቅ ከተርኪ ጋር እየተዋጋ ተርኪም እስከ ኢራቅ፤ ሲሪያ ድረስ እየገባች በጀት እየደበደበች ትገኛለች። ለማንኛውም ስለ ፊልድ ማርሻል አታተርክና ስለ ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ ንባብ አልባ ንግግር ለማወቅ የሚፈልግ የሚከተለውን ጽሁፍ ያንብብ። የቻለም ደግሞ የአታተርክና የዶ/ር ብርሀኑ ስርአት ከመምጣቱ በፊት ወደ ጋራው ይሽሽ።

 

 

The views expressed in this article are those of the author and do not necessarily reflect the views or opinions of ethiofact.com. Ethiofact.com is not responsible for the content or accuracy of the information presented.