ዘላለም ሙላቱ እና ኦሮሙማ
የኦሮሙማን እቅድ እንዲያስፈጽም የተሾመው ዶ/ር ዘላለም ሙላቱ

አዲስ አበባ ላይ ኦሮምኛን በግዳጅ መጫን የኦሮሙማን ሞት ማፋጠን ነው

በአሰፋ ቶላ

በአብይና በአዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሆኖ የኦሮሙማን እቅድ እንዲያስፈጽም የተሾመው ዶ/ር ዘላለም ሙላቱ ይባላል። ዶ/ር ዘላለም በፓርላማ ንግግሩ “የመረጠኝና የምወክለው” የሚለውን የአዲስ አበባን ህዝብ “ከርሱን ሞልቶ ፈርሱን” ኦሮሞ ላይ የሚጥል ህዝብ ብሎ መስደቡ በሪኮርድ ተመዝግቦለታል። ጊዜውም ሲደርስ በእርግጠኝነት ይጠየቅበታል።

ዶ/ር ዘላለም ማንንም ሳያማክር ከህግ ውጪ የአዲስ አበባን የትምህርት ቢሮ አርማ ወደ አማርኛና ኦሮምኛ ለውጧል። ዶ/ር ዘላለም በአዲስ አበባ ት/ቤቶች ኢትዮጵያኖችን የሚያዋርድ የኦሮሙማን መዝሙር ታዳጊ ልጆችን ካለዘመርኩኝ ብሎ ለብዙ ተማሪዎችና አስተማሪዎች ሞት፣ መሰቃየትና መንገላታት ምክንያት ሆኗል። በእርግጥ ጌታዋን የተማመነች በግ እንደሚባለው፣ ዶ/ር ዘላለም የሚያስፈጽመው የአብይንና የአዳነች አቤቤን የተረኝነቱን የኦሮሙማ ፕሮጄክት እንደሆነ ይገባናል።

ኦሮሙማ አራማጆች ሊያውቁት የሚገባው፣ ወያኔ ደደቢት ተወልዶ፣ በዋናነት በወልቃይት ጉዳይ ተሽመድምዶ ነፍሱ ልትወጣ እየጣጣረ ይገኛል። ኦሮሙማ በወለጋ ሚስዮናውያን ተወልዶ ፣ በሸዋ አዲስ አበባ እንኩትኩቱ እንደሚወጣ የሚከተሉትን ናሙና ምክንያቶች እንያቸው።

፩. የሕወሃት የአዲስ አበባ ልምድ

የወያኔ መሪ መለስ ዜናዊ አዲስ አበባን እንደተቆጣጠረ 1 ዓመት ሳይሞላው፣ ካድሬዎቹን ሰብስቦ አዲስ አበባን በጎሳና በኃይማኖት መከፋፈል አልቻልንም። ከአሁን በኃላ የአዲስ አበባን ህዝብ በጥቅማ ጥቅም ብቻ ነው መያዝ የምንችለው ብሎ፣ ፓሊሲ ቀርጸው ወያኔ ከስልጣን እስኪወገድ ድረስ ሲተገብሩት ቆዩ።

የአዲስ አበባ ህዝብን ከኢትዮጵያዊነት አሳንሶ በጎሳና በኃይማኖት መከፋፈል ስሪቱ ስለማይፈቅድ፣ ኦሮሙማን የአዲስ አበባ ህዝብ ላይ በሃይል የመጫን ፕሮጄክትም በእርግጠኝነት ይከሽፋል። የአብይ አገዛዝ በሁለት ጉዳዮች በአጭር ጊዜ ውስጥ በህዝቡ ሙሉ ለሙሉ ተሸንፏል። የመጀመሪያው ከኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጋር በገባው ትንቅንቅ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የኦሮሙማን መዝሙር በአዲስ አበባ ት/ቤቶች ለማዘመር ሞክሮ፣ በየት/ቤቱ ተቃውሞው እንደ ሰደድ እሳት ተሰራጭቶ እጁ በእሳት ተለብልቦ 1 ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ወደ ኋላ አፈግፍጓል።

፪. የአዲስ አበባ ህዝብ የጎሳ ስብጥር

አዲስ አበባ የተለያዩ ብሄሮች የሚኖሩባት ከተማ ናት። ኢትዮጵያዊ ነን የሚሉ ህዝቦችን ቁጥር በእጅጉ አሳንሶ የሚዘግበውን የሕወሃትን የቅርቡን የአዲስ አበባን ስታትስቲክስ ብንወስድ እንኳን፤ አማራ (48%)፣ ኦሮሞ (19%) ጉራጌ ( 17% )፣ ትግሬ (6.2%) ነው። ሕወኃት ክፍፍል እንዲያመቸው የስልጤን ህዝብ ከጉራጌ ስለለየ ነው እንጂ፣ የጉራጌና የስልጤ ህዝብ ብዛት በአዲስ አበባ ሲደመር ከኦሮሞው ቁጥር ይበልጣል።

ታዲያ በምን ምክንያት ነው የአዲስ አበባ ህዝብ ካለምንም ምርጫ ኦሮምኛ በግድ እንዲማር በኦሮሙማ አራማጆች የተጫነበት? እውነተኛ ስታትስቲክስ ቢወሰድ የጉራጌውና የአማራው ቁጥር እላይ ከተጠቀሰው ቁጥር እንደሚበልጥ ጥርጥር የለም።

በአዲስ አበባ የሚኖረው የጉራጌውና የኦሮሞው ህዝብ ብዛት ተቀራራቢ ሆኖ ሳለ፣ ለምን ትምህርት በጉራጊኛ እንዲሰጥ አልተደረገም? ለምን ኦሮምኛ ከጉራጊኝ ይልቅ ተመረጠ? ተረኝነት?

የአዲስ አበባ ህዝብ ከአማርኛ ቀጥሎ፣ ተጨማሪ የአገር ውስጥ ቋንቋ መማር ካለበት የግድ ምርጫ ሊሰጠው ይገባል። ጉራጌው ልጆቹ ከኦሮምኛ ይልቅ በጉራጊኛ እንዲማሩለት ከፈለገ፣ በግድ በኦሮምኛ መማር የለባቸውም። ትግሬውም ልጆቹ ከኦሮምኛ ይልቅ በትግርኛ እንዲማሩለት ከፈለገ መብቱ ሊከበርለት ይገባል። ለሌሎቹም ብሄረሰቦች እንዲሁ።

የኦሮሙማ አራማጆች ይሄን የህዝብ የተፈጥሮ መብት ወደው ሳይሆን በህዝብ ትግል ተገደው የሚቀበሉበት ጊዜ ሩቅ አይደለም።

፫. ኦሮምኛን በኢትዮጵያ ወይስ በላቲን ፊደል?

አዲስ አበባ ውስጥ ኦሮምኛን እንደ ሁለተኛ አገር በቀል ቋንቋ ለመማር የሚፈልግ ህዝብ ደግሞ ተጨማሪ አማራጭ ሊቀርብለት ይገባል። ኦሮምኛን በኢትዮጵያ ፊደል ወይስ በላቲን መማር እንደሚፈልግ ሊጠየቅ ይገባል።

ኢትዮጵያ ቀኝ ያልተገዛች ብቸኛዋ ጥቁር አገር፣ የራሷ ፊደል፣ ውብ ባህል፣ ታሪክ፣ ኃይማኖት ያላት አገር ናት። በእርግጥ ማንም ህዝብ በአፍ መፍቻ ቋንቋው መማሩ ትክክል ነው። ነገር ግን ኦሮምኛን በኢትዮጵያ ፊደል ከመማር ይልቅ ለምን በቀኝ ገዢዎች በላቲን ፊደል መማር አስፈለገ?

ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ አይደለም ተብሎ እስካልተካደ ድረስ፣ ኦሮምኛን በላቲን ፊደል የሚማርበት አንዳችም ምክንያት የለም። በአዲስ አበባ የቋንቋ ክፍል ፕሮፌሰር ባየህ ይማሞ በውይይት የአዲስ አበባ ዩኑቨርስቲ የአስተማሪዎች ልሳን ላይ እንደገለጹት፣ በማናቸውም መስፈርት ኦሮምኛን በላቲን ፊደል ከመማሩ ይልቅ በኢትዮጵያ ፊደል መማሩ ይጠቅማል።

በደርግ ዘመን በሪሳ የሚባል በኢትዮጵያ ፊደል የሚጻፍ የኦሮምኛ ጋዜጣ ነበር። አጼ ኃይለስላሴ መጽሃፍ ቅዱስን በኢትዮጵያ ፊደል ወደ ኦሮምኛ አስተርጉመዋል።

በግልጽ ቋንቋ የላቲን ፊደል አጀማመሩ ወለጋ ውስጥ በጀርመን ሚስዮኖች የተጫነ የቀኝ ገዢዎች ፊደል ነው። እንዚህ የጀርመን ሚሲዮኖች ይሁኑ ወይም አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ በኋላ፣ በናዚ ወንጀል የሚፈለጉ በሚሲዮኖች ስም የተደበቁ ወንጀለኞች ይሁኑ አይታወቅም።

ፀረ ኢትዮጵያ፣ በጣም ጠባብና ዘረኛው የኦሮሙማ አራማጅ ኦነግ የቀኝ ገዥዎችን ላቲን ፊደል የወሰደው ከጀርመን ሚሲዮናውያን ነው። በተለይ የኦርቶዶክስና የሙስሊሙ ኦሮሞ ህዝብን ከኢትዮጵያ የታሪክ ባለቤትነት በማራቅ፣ አዲስ የጀርመን ሚሲዮናውያን ተረት ተረት ለመጫን እንዲያመቸው ነው።

የኩሩዎቹ ኢትዮጵያን በደማቸው ያጸኑ የራስ ጎበና ዳጬ፣ ጃጋማ ኬሎ፣ የአብዲሳ አጋ፣ የጄኔራል ካሳዬ ጨመዳ፣ አሊ በርኬ፣ …ልጆች በሸዋ፣ በሀረር፣ በባሌ፣ በአርሲ፣ በወለጋ ኦሮምኛን በቅኝ ገዢዎች ላቲን የሚማሩበት ምንም ምክንያት የለም።

ለአህያ ማር አይጥማትም እንደሚባለው፣ ከፈለጉ በራሳቸው ታሪክ የሚያፍሩ፣ ኢትዮጵያዊነታቸውን የሚጠሉ፣ በራስ መተማመን ያልፈጠረባቸው፣ የጀርመን ሚሲዮናውያን ግርፍ ኦሮሙማ አራማጆች በላቲን ፊደል መማር መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል።

ለመደምደም ያህል አፉን በኦሮምኛ የፈታ ልጅ፣ በኦሮምኛ የመማር መብቱ ሊከበርለት እንደሚገባ ሁሉ፣ በመላ ኦሮሞ ኦሮምኛን በራሱ በአባቶች የኢትዮጵያ ፊደል ወይም በኦነግ ሚስዮናውያን የተጫነውን በቀኝ ገዢዎች በላቲን ፊደል መማር እንደሚፈልግ ምርጫ ሊሰጠው ይገባል።

፬. የህዝብ ፍቃድ

ዶ/ር ዘላለም ሙላቱ ከላይ በጥቂቱ ገለጽ ያደረግነውን የኦሮሙማ ፓሊሲ የአዲስ አበባ ህዝብ ላይ ሲጭን የሚሰጠው ምክንያት ደግሞ፣ “በህዝብ የተመረጥኩኝ” ስለሆንኩኝ ይሄን የማድረግ ህጋዊ መብት አለኝ በማለት ነው።

በዘመነ ወያኔ ወልቃይት ላይ አማርኛ መናገር፣ አማርኛ ዘፈን ማጫወት፣ የፋሲል ከነማ ማልያ መልበስ፣ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ መያዝ፣…..ያስገድል ያስረሽን ነበር። አሁን ላይ ያ ሁሉ የወያኔ ቅዠት አፈር ድሜ ሲበላ አይተናል።

የአዲስ አበባ ህዝብ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ አድርጎ፣ በመረጣቸው ተወካዮቹ አማካኝነት፣ አዲስ አበባ ላይ በግዳጅ የተጫነውን የኦሮሙማን ፕሮጄክት አንድ በአንድ ይሽራል። በምትኩም የአዲስ አበባን ህዝብ የጎሳና የኃይማኖት ስብጥር፣ የህዝቡን ፍላጎትና ፍቃድ ላይ መሰረት ያደረገ፣ ዘመኑንና እዲስ አበባን የሚመጥን ህግ ያወጣል።

 

 

The views expressed in this article are those of the author and do not necessarily reflect the views or opinions of ethiofact.com. Ethiofact.com is not responsible for the content or accuracy of the information presented.