የሕወሃቱ ዳንኤል ብርሃኔ ነገር

የሕወሃቱ ዳንኤል ብርሃኔ ነገር!

በአሰፋ ቶላ

የትህነግ ማህበራዊ “አንቂዎች” (a misnomer for “ደናቁርት አደንቋሪዎች”) ትልቁ ችግራቸው፣ ህግና ስርዓትን እስከ ጠቀማቸው ድረስ ብቻ እንከተል ማለታቸው ነው። አይተ ዳንኤል ብርሃኔ ሰሞኑን የትግራይ ጊዝያዊ አስተዳደር ህግ የማውጣት ህጋዊ ስልጣን አለው ወይ ብሎ በመጠየቅ ትንሽ ሊደሰኩር ሞክሯል።

እስቲ የዳንኤል ብርሃኔን ሃሳብ እስከ ዛሬ ድረስ ከሚያራምደው አቋም አንጻር ትንሽ እንፈትሸው፣

፩. ድሬ በትውልድ፣ ወያኔነት በምርጫ

ወጣ ወጣና እንደ ሸምበቆ ተንከባለለ እንደ ሙቀጫ ሆነና፣ ዳንኤል ብርሃኔ ድሬን የመሰለ በአብሮነት የተሞላ ሰው ሰው የሚሸት ከተማ ተወልዶ አድጎ፤ አውዳሚውን የሕወሃት የጎሳ ፓለቲካ መርጦ፣ መቀሌ የሚርመጠመጥ በጎሳ ደዌ የተመረዘ ድኩማን ሆኖ ቀርቷል። ለ27 ዓመታት መቀሌን ለማስደግ ተብሎ፣ ተወልዶ ያደገባት ድሬ በእቅድ ወደ ኋላ እንድትቀር ሲደረግ፣ ህግና ስርዓት ይከበር ከማለት ይልቅ ወያኔን ግፋ በለው እያለ ሲያጫፍር የኖረ ግለሰብ ነበር።

፪. የዳንኤል ብርሃኔ በቅርቡ የጻፈው መጽሃፍ

እኩል ሆኖ መኖር ሞት የሆነበት ወያኔ የጦርነት ከበሮ ኢትዮጵያ ላይ ነጋ ጠባ በሚደልቅበት በዚያ ፈታኝ ወቅት ፣ ዳንኤል ብርሃኔ በየሚድያው እየቀረበ ጦርነቱን ቶሎ ጀምረን ቶሎ በመጨረስ ወደ “ቀድሞው ሰላማችን” እንመለስ፤ አይጦች ተሰብስበው ድመት ስትመጣ ከማለቃችን በፊት እንድንሰማ አንገቷ ላይ ቃጭል እናጠልጥል ብለው ተስማሙና፣ ድመቷ አንገት ላይ ግን ማን ቃጭሉን ያጥልቅ ሲባል ቤቱ በዝምታ ተዋጠ እያለ፣… በድህረ ገጹ የወያኔን ኃያልነት ሲሰብክ፣ ጦርነትን በግልጽ በአደባባይ ሲያበረታታ የነበረ ሰው፣ ዛሬ አይኑን በጨው አጥቦ ” War on Tigray” የሚል መጽሃፍ ደርሶ ብቅ ብሏል።

ጦር አውርድ እያለ ሲጸልይ ሲማፀን ከርሞ፣ የእሱና መሰሎቹ ጸሎታቸው ደርሶላቸው ይሄ ሁሉ መከራ የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ከደረሰ በኋላ፣ ንስሃ መግባትና ይቅርታ መጠየቅ ሲገባው ጭራሽ ልክ እንደ ተበደለ የጦርነት አስጸያፊነትን ቀድሞ ሲመክር እንደነበረ፣ መጽሃፍ ደርሶ ብቅ አለ።

፫. ትግራይ ትምረጥ የፌስ ቡክ ገጽ ሽፋኑ

በማናቸውም ሀገር ምርጫ መቼ፣ የትና እንዴት እንደሚካሄድ በህግ የሚወስነው ምርጫ ቦርድ መሆኑ ይታወቃል። በመላ ኢትዮጵያ ከኮቪድ ጋር በተያያዘ ምርጫ ቦርድ ምርጫ መራዘሙን ሲገልጽ፣ ጦርነቱ ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ትግራይ ትምረጥ የሚል ምስል በድረ ገጹ ላይ አስፍሮ ህገወጥነት ሲያበረታታ የነበረ ሰው ነው ዛሬ የጌታቸው ረዳ ጊዝያዊ መንግስት ህግ የማውጣት ስልጣን አለው ውይ ብሎ የህጋዎዊነት ጥያቄ የሚያነሳው።

መቼም ህወሃት ቤት ህሊና፣ ሃፍረት፣ ዞር ብሎ የሚያይ አንገት የለም።

፬.. የመለስ ዜናዊ የሽግግር መንግስት

ወያኔ ስልጣን እንደያዘ የሰኔ 24 ኮንፈረንስ ላይ፣ ነፍሳቸውን ይማረውና ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ፣ በህዝብ ያልተመረጠ የሽግግር መንግስት ስለሆነ፣ ስለ ኤርትራና የወደብ ባለቤትነት ጉዳይ የመወሰን ስልጣን የለውም ብለው ነበር።

የድሬው ዳንኤል ብርሃኔ በሎሌነት የሚያገለግለው የአድዋው መለስ ሕወሃት ግን፣ የሽግግር መንግሥት ሆኖ ሳለ ኤርትራ ትገንጠል ብሎ ለአፍሪካ አንድነትና ለተባበሩት መንግስታት ደብዳቤ ጻፈ፣ የሚጠላትን ኢትዮጵያን ወደብ አልባ አድርጎ ተበቀለ፣ ኢትዮጵያን በአፓርታይድ ክልል/ ባንቱስታን ሸነሸነ፣ የኢትዮጵያን መከላከያ፣ ደህንነትና ፓሊስ አፈረሰ፣ ወልቃይትን ከጎንደር ራያን ከወሎ በጠራራ ፀሀይ ዘረፈ።

ይሄ ሁሉ የተደረገው እንግዲህ የሽግግር መንግስት በሆነው በአድዋው መለስ ሕወሃት ነው። ይሄ ሁሉ ሲደረግ ዝምታን መርጦ ስርዓቱን በዋናነት ሲደግፍ የነበረ ዳንኤል ብርሃኔ፣ የጌታቸው ረዳ የሽግግር መንግስት ህግ የማውጣት ማንዴት አለው ወይ ብሎ መደስኮሩ ቀልድ ነው።

፭. የሰሞኑ የዳንኤል ብርሃኔ የሞኝ ዘፈን

ለእንደ ዳንኤል ብርሃኔ አይነት ነገን ደግመው ደጋግመው መገመት ለማይችሉ የአይምሮ ድኩማኖች፣ ነጮቹ “be careful what you are wishing for” ይላሉ።

ኢትዮጵያን ለጊዜው ለቀቅ አድርገው፣ እስቲ ዳንኤል ብርሃኔና መሰሎቹን ወደ መንደርተኝነታቸው እንመልሳቸውና፣ ከምር የወሰዱት በአድዋ ሕወኃቶች ምናብ ውስጥ ስለተፈጠረችውና “በኢምፓየሯ ኢትዮጵያ ፍርስራሽ” ላይ ሊገነቡት ስላሰቡት “አባይ ትግራይ” ትንሽ ልበል።

ወልቃይት ወደ ጎንደር፣ ራያ ወደ ወሎ ወደ ባለቤቱ ተመልሷል። የቀሩት ትግራይ ውስጥ የሚኖሩት የተለያዩ ጎሳዎች፣ በሕወሃት ቋንቋ በወያኔ አህዳዊ ስርዓት ተጨፍልቀን ለስብሃት ነጋ ቤተሰብ የአድዋ ገዢ መደብ አፈና እንዲያ መች በአቅጣጫ ( ደቡብ/ሰሜን/ምዕራብ፣ምስራቅና ማዕከላዊ) አንሰየምም ብለው፤የይሮብ፣ የእንደርታ፣ የሳሆ፣ የኩናማ፣ የአገው፣ የተንቤን፣ የአክሱም የአገው፣ የዋጀራት፣.. ድርጅት መስርተው ምርጫ ቦርድ ተመዝግበው እየተንቀሳቀሱ ነው።

ኩናማዎች ኩናማ ውስጥ ከእንግዲህ ወዲያ ልጄ በአፍ መፍቻ ቋንቋው በኩናምኛ እንጂ በትግርኛ መማር የለበትም በማለት ትግል ጀምረዋል። የምሩጽ ይፍጠርና የዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ የይሮብ ህዝብ በግዛታችን ውስጥ የፍርድ ሂደቱ በአድዋ አህዳውያን በተጫነብን ትግርኛ ሳይሆን በይሮብኛ መሆን አለበት እያሉ ነው። መቀሌ እንደርታዎች መቀሌን ጨምሮ የእንደርታ ህዝብ በአድዋ አህዳውያን ሳይሆን በራሷ በእንደርታ ልጆች ትተዳደር ብለው ትግል ከጀመሩ ሰንብተዋል።

በሕወኃት ታሪክ ውስጥ አውራጃዊነት ትልቁ የሕወኃት አንጃ አደጋ ነበር። አውራጃዊነትን የአድዋው አህዳዊው ቡድን በብረት ለመጨፍለቅ ቢሞክርም፣ ይሄው ጊዜው ጠብቆ መሬት ረግጧል።

ዳንኤል ብርሃኔ ግን ይሄን ቀድሞ የሚተነብይ ጭንቅላት አልፈጠረበትም። አድዋን ታቅፎ “ዓባይ ትግራይን” መመስረት የሚያዋጣው ከሆነ መንገዱን ጨርቅ ያድርግለት።

ጃዋር እንኳን ባቅሙ፣ ከእስር ከተፈታ በኋላ ልኩን አውቆ፣ በተለያዩ ሀገሮች እየዞረ ለደጋፊዎቹ ንግግር ሲያደርግ፣ “ኦሮሚያ” የምትኖረው ኢትዮጵያ እስካለች ድረስ ብቻ ነው እንጂ፣ “በኢትዮጵያ ፍርስራሽ” ላይ አይደለም ብሎ በድፍረት ተናግሮ፣ ትልቅ ተቃውሞ እስከ አሁን ድረስ እያስተናገደበት ነው።

ኢትዮጵያ ከሌለች፣ የሸዋ፣ የወለጋ፣ የሀረርጌ፣….ህጋዊ ባለቤት ስላላቸው፣ ‘ኦሮሚያ” እውን አትሆኑም እርሱት ማለቱ ነበር።

 

 

The views expressed in this article are those of the author and do not necessarily reflect the views or opinions of ethiofact.com. Ethiofact.com is not responsible for the content or accuracy of the information presented.