
የትግራይ ህዝብና ሕወሃት
በአሰፋ ቶላ
ከዚህ አውዳሚው የሕወሃት አካሄድ ለመውጣት ፣ ቢያንስ የሚከተሉትን 3 ነገሮች በጥሞና መዳሰስ ያስፈልጋል።
፩. የትግራይ ህዝብና የሕወሃት ፍላጎት ከመሰረቱ እንደሚጣረስ መቀበል
የትግራይ ህዝብ ታሪክ ቢያንስ ከአክሱም ሲጀምር፣ ሕወሃት የትግራይን ህዝብ ታሪክ በድርጅቱ እድሜ ገድቦታል። እነ አጼ ዮሃንስ፣ ራስ አሉላና ራስ መንገሻ የተዋደቁለት ሰንደቅ ዓላማ አረጓንዴ ቢጫ ቀይ ሲሆን፣ ሕወኃት የትግራይ ህዝብ ላይ የጫነበት ባንዲራ ግን ከታሪኩ ጋር ምንም ትስስር የሌለውን ባለ ቀይ ኮከብ የኮሚኒስት ባንዲራ ነው። የትግራይ ህዝብ የጸና ኃይማኖተኛ ሲሆን፣ ሕወሃት ግን ሃይማኖት መጥፋት አለበት ከሚለው የኮሚኒስት አስተምሮ በመነሳት በትግራይ የሃይማኖት ተቋሞችን በፓለቲካ ካድሬ ሞልቶ፣ የህዝቡን ሃይማኖት አራክሷል። የትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የጸና ሲሆን፣ የሕወኃት መሪዎች ግን የኢትዮጵያ ጥላቻቸው ወደር አይገኝለትም።
የሕወሃት የፓለቲካ ፓርቲ ፕሮግራም፣ እንደ ወረደ ወደ ኢትዮድያ ህገ መንግስትነት ተለውጧል። ለዚህም ነው ህገ ሕወኃት/ህገ ጎስኝነት ብሎ መጥራት አግባብነት የሚኖረው። ሕወሃት ታንኩንና ባንኩን መቆጣጠሩ ሲያበቃ በተግባር እንደታየው፣ ይሄ ህገ ሕወኃት ደግሞ እንደ ትግራይ ህዝብ ላሉ በቁጥር አናሳ ለሆኑ ህዝቦች በጣም ይጎዳል። የርዕዮቱ ቴድሮስ ፀጋዬ አስርግጦ እንደተናገረው፣ ህገ ሕወሃት የትግራይ ህዝብን ለዘላለም አናሳ ሆኖ አስቀርቶ፣ ከኢትዮጵያ ከሚገባው ስልጣንና ጥቅም እንዲርቅ የፈረደበት ሰነድ ነው።
የትግራይ ህዝብና የሕወሃት ጥቅም እንደሚጣረሱ፣ አሁን ብዙ የትግራይ ሰዎች በድፍረት መናገር ጀምረዋል። አነ ቴድሮስ ርዕዮት፣ አሉላ ሰለሞን፣ ዳንኤል ብርሃኔ፣….መጥቀስ ይቻላል።
በግምት ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጋ የትግራይ ህዝብ እልቂት ስለዳረገ፣ ጦርነቱ እንዴት እንደተጀመረ፣ የሕወሃትን ሚና ምን እንደነበረ፣ የትግራይ ህዝብ መጠየቅ አለበት። የትግራይ ህዝብ እንደ ቅጠል ሰረግፍ ግድ ያልነበረው የሕወሃት አመራር፣ መቀሌ ሲከበብ ህይወታቸውን ለማትረፍ ሲሉ አድርጉ የተባሉትን ሁሉ አድርገው የፕሪቶሪያን ስምምነት ፈረሙ።
ከስምምነቱ በኋላ የስልጣን ጥያቄ እንጂ፣ የተፈናቃዮችና የትግራይ ህዝብ ያለበት አሳቃቂ ሁኔታ፣ የሕወኃት አጀንዳ ሆኖ እንደማያውቅ ጌታቸው ረዳ ከክፍፍሉ በኋላ አጋለጠ።
አሁንም ለማያባራ የስልጣን ጥማታቸው ሲሉ፣ የሕወሃት መሪዎች የትግራይን ህዝብ ወደ ዳግም ጦርነት ሊከቱ ሲፍጨረጨሩ፣ ህዝቡ መቃወም መጀመሩ የሚበረታታ ነው።
፪. የትግራይ ህዝብ ህገ ሕወኃት መጥፊያው፣ ኢትዮጵያዊነት መዳኛው መሆኑን መረዳት
ህገ ሕወኃት ኢትዮጵያኖችን አገር አልባ አድርጎ ሀገር ለጎሳዎች ስለሰጠ፣ ከተለያዩ ጎሳዎች ለተወለዱ ውህድ ኢትዮጵያኖችም ቦታ የላቸውም።
የቀድሞ የሕወሃት ቁጥር 1 ደጋፊ የሆራይዘን ሚዲያዋ ማርያማዊት፣ ግማሽ ትግሬና ግማሽ አማራ ስለሆንኩኝ፣ ከሕወሃት ክፍፍል በኋላ ትግሬዎቹ የአማራ ደም አላት ብለው አገለሉኝ። አማሮቹ ደግሞ የሕወሃት ደጋፊ ትግሬ ናት ብለው አይቀበሉኝም። ስለዚህ የሚያዋጣኝ ከአሁን በኋላ ኢትዮጵያዊ መሆን ነው ስትል ሰሞኑን ተደምጣለች። ህገ ሕወሃቱ እስካልተቀየረ ድረስ፣ ውህድ የትግራይ ልጆች እጣ ፋንታቸው ከማርያማዊት አይለይም።
ኢትዮጵያኖችን ሀገር አልባ አድርጎ መሬት ለጎሳ የሰጠው ህገ ሕወሃት እስካለ ድረስ፣ በተለይ አሁን ላይ መሬት ላይ ያለውን ፓለቲካ ላስተዋለ፣ ለምን ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለባድመ ደሙን እንደሚያፈስ እንዳለበት የትግራይ ህዝብ እራሱን መጠየቅ አለበት።
የትግራይ ህዝብ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እኩል ባለቤት ሆኖ ለመኖር፣ ለመነገድ፣ ለመስራት፣ ለመምረጥ፣ ለመመረጥ፣ ….ይሄ ህገ ሕወኃት እንቅፋት ሆኖበታል።
ለዚህም ነው እንደ ትግራይ ህዝብ በቁጥር አናሳ ለሆኑ የኢትዮጵያ ህብረተሰቦች፣ ህገ ሕወኃት መጥፊያቸው ሲሆን፣ ኢትዮጵያዊነት ግን መዳኛቸው የሚሆነው።
፫. ወልቃይትና ራያና የገንደርና የወሎ ክ/ሀገር መሬቶች መሆናቸውን ካለምንም ማመንታት መቀበል
ሕወኃት ብዙ ታሪካዊ ስህተቶች ሰርቷል። ኢትዮጵያን ወደብ አልባ አድርጓል፣ ኤርትራ ትገንጠል ብሎ ለተባበሩት መንግስታት ደብዳቤ ጽፏል፣ ኤርትራ የሰሜን ሱማሌ እጣ ሳይደርሳት እውቅና አግኝታ ኤርትራ እንድትገነጠል አድርጓል፣ ኢትዮጵያኖችን አገር አልባ ያደረገ፣ የትግራይ ህዝብን ሚናና ጥቅም አናሳ የሚያደርግ የፓለቲካ ፕሮግራም ህገ ህወሃት/ ህገ ጎሰኝነት ቀርጿል።
ወልቃይትና ራያን ከጎንደርና ከወሎ ወስዷል። የቀድሞው የሕወኃት መሪ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ እንደገለጸው፣ ወደ ሱዳን መውጪያ ለማግኘት ሲባል ወልቃይትን ሕወኃት ደርግ ስልጣን ላይ እያለ ወስዷል። በሕወሃት ተጽዕኖ እራሳቸውን እስኪጻረሩ ድረስ፣ ራስ መንገሻ ስዩም ወልቃይት ምንጊዜም የጎንደር ክፍለ ሀገር አካል እንደነበር መስክረዋል።
በእነ ቦብ ጌልዶፍ “We are the World” ነጠላ ዘፈን ሰሞን የወሎ ድርቅ ዋና ማሳያ የነበረችውን ኮረምን ከወሎ ወስዷል። ራያና ወልቃይት ወደ ትግራይ በሕወሃት እርኩስ ዕላማና ማንአለብኝነት የተወሰዱት፣ ከሕወሃት የሽግግር መንግስቱ ምስረታ በፊትና ህገ ሕወሃት ከመርቀቁ በፊት ነበር።
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በታሪክ እንደሚያቀው፣ ራያ የወሎ ወልቃይት ደግሞ የጎንደር ክ/ሀገር አካሎች ነበሩ። ይሄን ሃቅ መለወጥ አይቻልም። መካድም አያዋጣም።
የትግራይ ህዝብ ከአማራ ህዝብ ጋር ዘላቂ ሰላም ለምፍጠር፣ ለመታረቅ፣ የመጀመርያው ድፍረት የተሞላበት እርምጃ መሆን ያለበት፣ በሕወሃት እብሪትና ትዕቢት የተወሰዱትን ወልቃይትና ራያን ለባለቤቱ ጎንደርና ወሎ መሆኑን በመቀበል፣ የሕወሃትን ዋናውን ታሪካዊ ስህተት መቀልበስ አለባቸው።