
ለፋኖ አዋጪው መንገድ ውህደት ወይስ ቅንጅት?
በአንበርብር ሀይሉ
ወደ ኋላ መለስ ብለን የፓለቲካ ተሞክሯችንን ብንቃኝ፣ ህዝቡ በተደጋጋሚ “ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ” በማለት የተለያዩ ፓለቲካ ፓርቲዎች ላይ ጫና ቢያሳድርም፣ ከቅንጅት በስተቀር ከኢድኃቅ እስከ አማራጭ ኃይሎችና አሁን ድረስ ይሄ ነው የሚባል ለብዙ ጊዜ የቆየ ተጨባጭ ለውጥ ያመጣ ትብብር ሲያደርጉ አልታየም።
በአንጻራዊነት በአጭር ጊዜ ውስጥ በአነስተኛ ዋጋ ክፍያ ወደ ድል ለመቅረብ፣ የብዙ የፋኖ ደጋፊዎች ፍላጎት ፋኖ አንድ እንዲሆን ነው። ይሄ የተቀደሰ ሃሳብ ነው። አንድነት ስንል ግን ምን ማለታችን ነው?
አንድነት በተመረጡ አጀንዳዎች ዙርያ መተባበር ወይም መቀናጀት ከሆነ፣ በእርግጥም አንድነት በአስቸኳይ እንዲፈጠር ሁሉም የራሱን በጎ ተጽዕኖ ማሳደር አለበት።
ነገር ግን አንድ ሁኑ ሲባል አሁኑኑ በመዋሃድ የሚዋሃዱት ድርጅቶች ይክሰሙ ማለት ከሆነ፣ ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን ሰከን ረጋ ብለን ማሰብ አለብን። ይሄ ማለት ግን ትብብሩ ወይም ቅንጅቱ በሂደት የተፈጥሮ እድገቱን እየጠበቀ ድርጅቶቹ ወደ ውህደት እንዲሄዱ መሰራት የለበትም ማለት አይደለም። ጊዜውን ጠብቆ፣ ካለ ምንም አሉታዊ ጫና በጥንቃቄ የተመሰረተ ውህደት፣ የሚደርስበትን ወጀብ ተቋቁሞ አንድነቱን ጠብቆ ወደ ድል የማምራቱ እድል በጣም ሰፊ ነው።
፩. የቅንጅት ተሞክሮ
የ97 ምርጫ እስኪጠናቀቅ ድረስ ፣የቅንጅት ትልቁ ውበቱና ስኬቱ ተቀራራቢ ፓለቲካ ፕሮግራም ያላቸው አራት ህብረ ብሄር ፓርቲዎች እንደ ስሙ መቀናጀታቸው ነው። ለቅንጅት መቀናጀት ደግሞ ብዙ ገፊ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ ዋናው ምክንያት እርስ በርሳቸው በአንድ የምርጫ ጣቢያ ድምጽ እንዳይወሳሰዱና ለገዢው ፓርቲ የተመቻቸ ሁኔታ እንዳይፈጥሩ ነበር።
የቅንጅት የምርጫ ስኬት ህዝቡን ያስደመመ፣ መሪዎቹን ያስፈነጠዘ፣ ህወሃትን ክፉኛ ያስደነገጠ ክስተት ነበር።
ካለምንም ጥናት በችኮላና በቀስተደመና መሰሪ ፊታውራሪነት፣ ሊያመጣ የሚችለው አሉታዊ ተጽንኦ በሰፊው ውይይት ሳይደረግበት፣ ቅንጅት የ4ት ፓርቲዎች ቅንጅት መሆኑ ቀረና አንድ ውህድ ፓርቲ ተደረገ። ይሄ ውህደት ጊዜ ተወስዶበት ተመክሮበት ተዘክሮበት በቅንነት ስላልተመሰረተ፣ ብዙም ሳይቆይ በ4ቱ ፓርቲዎች የእርስ በእርስ የውስጥ ሽኩቻ ተጠምዶ ቅንጅት እንዳይነሳ ሆኖ ተንኮታኮተ። ባጭሩ የቅንጅት ስኬቱ መቀናጀቱ ሲሆን፣ ውድቀቱ ደግሞ በዋናነት ቅንጅትነቱን በችኮላና በሴራ አንድ ውህድ ፓርቲ መሆኑ ነበር።
፪. የኢትዮጵያ ፓለቲካ ተመክሮ (ኢድኃቅ፣ ህብረት፣ አማራጭ ኃይሎች፣…..)
ህዝቡ የአንድነትን ሁለገብ ጠቀሜታን በመገንዘብ፣ የተለያዩ ድርጅቶችን ለረጅም ዓመታት “ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ” በማለት በተለያየ ወቅት ግፊት በማሳደር የተለያዩ ጊዝያዊ ህብረቶች ቢፈጠሩም፣ አብረው ተባብረው በመስራት ይሄ ነው የሚባል እመርታ ሊያሳዩ ግን አልቻሉም። የዚህ ውድቀት ዋናው ምክንያት ደግሞ ምንም አንድ ላይ ሊያስተባብራቸው የሚችል መሰረታዊ ጉዳይ ሳይኖር፣ አንዳንዶቹ እንዲያውም በመርህ ደረጃ ከተቃዋሚ ኃይሎች ይልቅ ለገዢው ፓርቲ የሚቀርቡ ሆነው ሳለ፣ አንድ ላይ ተሰባስባችሁ ህብረት ፍጠሩ ተብሎ የተደረገባቸው አላስፈላጊ ግፊት ነበር።
፫. ፋኖ “አንድ” ይሁን ስንል ምን ማለታችን ነው?
ፋኖ እንደ ተቀሩት ኮሚኒስት ፓርቲዎች ከላይ ወደታች ሳይሆን፣ ከታች ወደ ላይ የተዋቀረ ፍጹም ኢትዮጵያዊ መሰረት ያለው ድርጅት ነው። ፋኖ እንደሌሎች ፓርቲ አባሎች ተሰብኮ የተሰበሰበ ሳይሆን፣ መሬት ላይ ባሉ ገፊ ምክንያቶች በሬውን ሸጦ ህልውናውን ለማስቀጠል በራሱ አነሳሽነት በየአካባቢው የተሰባሰበ ኃይል ነው። ፋኖ ለምን፣ ከማን ጋር ምን ለማሳካት መስዋዕትነት እንደሚከፍል ጠንቅቆ ያውቃል።
ይሄ በየቀዬው የተደራጀ የፋኖ ኃይል፣ የተፈጥሮ እድገቱን ጠብቆ መሬት ላይ በነበሩ ገፊ ምክንያቶች፣ ወደ ዞን ከዚያም ወደ አውራጃ በጎጃምና በወለጋ ደግሞ ደግሞ ወደ ጠቅላይ ግዛነት አድጓል። በጎንደር፣ በወሎና በሸዋ ጠቅላይ ግዛቶች ደግሞ ሁለት ቢበዛ ሶስት የፋኖ አደረጃጀቶች አሉ። የደቡብ ፋኖ መቋቀሙን ሰምተናል። በሁሉም የኢትዮጵያ ግዛት ፋኖ መቋቋሙ አይቀሬ ነው። ይበልጥ የመቀናጀቱ ሥራ ተጠናቅሮ መቀጠል እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እዚህ ደረጃ በዚህ በአጭር ጊዜ መደረሱ በራሱ አመርቂ ውጤት ነው።
የፕ/ሮ ጌታቸው ኃይሌ “አንዳፍታ ላውጋችሁ” የሚለው መጽሃፍ ላይ፣ በ5 ዓመቱ የጣልያን ወረራ ጊዜ፣ የሸዋ አርበኞች መጀመሪያ ሁሉም በመንደራቸው መደራጀታቸውንና፣ የተፈጥሮ እድገታቸውን ጠብቀው መሬት ላይ በነበሩ ገፊ ምክንያቶች እየተቀናበሩ በራስ አበበ አረጋይ መሪነት የሸዋ ፋኖ እንደተመሰረተ ጽፈዋል።
የፋኖ ከታች ወደላይ አወቃቀር ብዙ ጥቅሞች አሉት። እታች ያለው አባል በድርጅቱ አካሄድ ላይ ሁነኛ ድምጽ ይኖረዋል። አመራሮች አባላቱ ያላመኑበትን ሃሳብ በግድ ሊጭኑባቸው አይችሉም። ይሄ ልክ እንደ ስዊዘርላንድ ዲሞክራሲ የራስን ጉዳይ በራስ የመወሰን ጥሩ መገለጫ ነው። አደረጃጀቱ እላይ ያሉት አመራሮች እንዳይባልጉ ያደርጋል። እንደ ቅንጅት ትግል የፋኖ ትግል በግለሰቦች እንዳይጠለፍ ይከላከላል። የክፍለ ሀገሮቹ ታሪካዊ ማንነትም ይጠበቃል።
ነገር ግን የኢትዮጵያ ፓለቲካ የሚከካው፣ የሚቦካውና የሚጋገረው ሸዋ አዲስ አበባ ውስጥ ስለሆነ፣ የኦሮሙማን ስርዓት ከስልጣን ለማስወገድ የፋኖ ኃይሎች አስቸኳይ ቅንጅት የግድ የሚያስፈልግበት ደረጃ ላይ ተደርሷል።
የተለያዩ የፋኖ አደረጃጀቶች ቁጭ ብለው ተወያይተው የጋራ የሚሊቴሪ ስትራተጂ ነድፈው ወደ አዲስ አበባ የሚገሰግሱበትን መንገድ መፈለግ አለባቸው። የህዝቡንና የተዋጊውን ሞራል እንደገና ይበልጥ ከፍ ለማድረግ፣ እንደ ወረርሽኝ የተስፋፋውን እገታን ለመግታት፣ በጋራ በአንድ አቋም ከ3ኛ አካል ጋር ለመደራደር፣ የጋራ የሚሊተሪ ስትራተጂ ለመንደፍ፣ አንድ ወጥ ምልጃ፣ የህዝብ ግኑኝነት ስራና ትሬይኒንግ ለመስጠት፣ በጋራ የማንቃት የማደራጀት ገንዘብ የማሰባሰብ ስራ ለመስራት፣ …..በአስቸኳይ መቀናጀት የግድ ይላል።
ስለዚህ ፋኖ መቀናጀት ወይስ መዋሃድ ያለበት? ፋኖ የተፈጥሮ እድገቱን ጠብቆ በጥንቃቄ እራሱን ከትግል ጠላፊዎች ጠብቄ ወደፊት የግድ መዋሃድ ይኖርበታል።
ውህደት እስኪመጣ ድረስ ግን የተላያዩ የፋኖ ኃይሎች በቅንጅት መስራት የግድ ይኖርባቸዋል። በመላ ኢትዮጵያ ያሉት ሁሉም የፋኖ አደረጃጀቶች በተለያየ ምክንያት አንድ ላይ መቀናጀት ካልቻሉ ግን፣ አብዛኛዎቹ እስከተቀናጁ ድረስ፣ ስራ እየሰሩ በሂደት ያልተቀናጁት ቅንጅቱን የሚቀላቀሉበት መንገድ መፈለግ አዋጭ መንገድ ነው።
የፋኖ ኃይሎች ቅንጅት እንዲሳካ ቢያንስ የሚከተሉት መሰረታዊ ጽጥንቃቄዎች መደረግ አለባቸው።
፩. ከ5ቱም ጠቅላይ ግዛቶች ( ወለጋን ጨምሮ) እኩል ተዋጽኦ ያለው የጋራ አመራር መፍጠር።
፪ ከተመረጡት የጋራ አመራር ሰብሳቢውና ፀሃፊው በየ6 ወር በተራ ከ5ቱ ጠቅላይ ግዛቶች የሚቀያየሩበት አሰራር መዘርጋት፣
፫. የአመራሩ የስልጣን ዘመን በማይራዘም የ2 ዓመት የጊዜ ገደብ መገደብ።
“አብዛኛዎቹ እስከተቀናጁ ድረስ፣ ስራ እየሰሩ በሂደት ያልተቀናጁት ቅንጅቱን የሚቀላቀሉበት መንገድ መፈለግ አዋጭ መንገድ ነው።”
“ከተመረጡት የጋራ አመራር ሰብሳቢውና ፀሃፊው በየ6 ወር በተራ ከ5ቱ ጠቅላይ ግዛቶች የሚቀያየሩበት አሰራር መዘርጋት፣”
በጣም መደገፍ ያለበት ሃሳብ ነው።
አንድነት ማለት ውህደት ማለት ነው። የፋኖ ስብስቦች የጠራ ፖለቲካዊ አላማ ሳይኖራቸው አንድ ሁኑ ማለት ደግሞ፣ በኔ እምነት፣ ወደፊት ሊያራምዳቸው የሚችል ነገር አይደለም።
በተጨማሪም፣ የፋኖ ትግል ቀንና አጋጣሚ እየጠበቀ ባለ አምባገነን የመጠለፍ አደጋ ሊገጥመው ይችላል።
ስለዚህ ጸሀፊው እንደጠቀሱት ቅንጅት መፍጠር ትክክለኛው መፍትሄ ነው።